አየህ የሰከኑ ለታ የታመመ ሃሳብ ከስሩ ይጠልላል። ዝቃጭ ሆኖ እንደሚቀር ልክ እንደ ጠላው አተላ። እንደ ጠጁ አንቡላ!…። መቅበዝበዝ ክፉ ነው ወንድሜ። የጠለለን ያደፈርሳል። ያኔ ደግሞ አእምሮ ይታወካል፤ የጠራው ሃሳብ ይናወጣል። ግርዱ ከፍሬው ተሳክሮ የጎደለ ፍትህ ይወለዳል።
የሰከኑ ለታ…ታዲያ! የትናንት በደል ይዘቅጣል። የያኔው ጥላቻ ይሽራል። ከባዶ ወሬ ይልቅ ህዝብ በእውነት ይሰክራል። ከወንድምህ የነጠለህ ሰይጣን ድል ሆኖ በአደባባይ ይዋረዳል። አሁን የያዝከው እውነት እናትን ከልጇ የሚነጥል የክፋት መንፈስ ነው። ለምን ተሸነፍኩ የሚል እንጂ ቅሌትን በፀፀት የመሻር ምንም ፍላጎት የሌለው።
አሁን ላይ ያጋጠመን እውነት የኛን ታሪክ ይመስላል ወንድሜ። በተዛባ ትርክት ብዙሃኑን የህሊና እውር አድርጎ ለራስ ቁራሽ ደስታ የሚፈልግ ሞልቷል። ሰከን ብለህ ስታስተውል አይደለም ከወንድምህ ከራስህ የሚያጣላህ የናት ጡት ነካሽ ዙሪያህን ከቦታል።
እመነኝ ወንድም ዓለም አይንህና ጆሮህ ነን ያሉህ የመገናኛ ብዙሃን ልክ እንደ አርቴፊሻሉ እሳት የሚሰብኩህ ፕሮፓጋንዳ ‹‹superficial truth›› ከእውቀት እና ጥበብ ጋርዶሃል። የዘራፊ አመል እንዲህ ነው ወንድሜ። ተፅዕኖ የሚፈጥሩ እና የገንዘብ አቅም ያላቸው ግለሰቦች ማህበረሰቡን ወደ ለምለሙ ሜዳ ሳይሆን ጥልቅ ወደ ሆነው ገደል እንደሚመሩት እወቅ።
ምን መሰለህ ወንድሜ ፍሬውን ከገለባው ለመለየት፤ መንሽ እንደሚያስፈልገን ሁሉ እውነቱን ‹‹ከተዛባው እውነት›› ለመነጠል ጥበብ ‹‹wisdom›› ሊኖርህ ይገባል። በሰንሰለቱ ተጠፍረው እንደተያዙ የዋሻው እስረኞች አንተም ሆንክ ሁሉም ህዝቤ ጠፍሮ ከያዘው ‹‹አለማወቅ›› በጥሶ ለመውጣት ሃሞት ያስፈልጋል። እውቀትን መከተል እውነትን ማሳደድ ይኖርብሀል። ነፃ የሚያወጣውን ጥበብ እንደመሻት ማለት ነው።
ማመን ያለብን ወንድሜ በመርዝ በተለወሰ ቃላቶች እያረሰረሱን እነርሱ ወደሚፈልጉት አቅጣጫ የሚወስዱንን ጥቂቶችን ሳይሆን ፤ መርምሮ የሚያውቀውን መዝኖ የሚረዳውን ህሊናችንን ነው። ለዚህ ደግሞ እውቀትን መከተል ይኖርብናል። ነፃ አውጪዎችህ ነን ቢሉህም፤ እውቀት እንጂ ጥቂቶች ነፃ እንደማያወጡህ ተረዳ። እንዲህ ብዬ ልደምድም ወንድሜ…
መልካም ፍሬዎች በአንድ ጊዜ አይበቅሉም። የክፋት ፍሬዎችም እንዲሁ፡፡ ስኬታማ ሰዎች አይን ባወጣ ሌብነት ካልሆነ በቀር በአንድ ሌሊት ሀብት አያከማቹም፡፡ እውቅናም ሆነ እውቀት በአንድ ምሽት አይገኙም፡፡ የእኔና የአብዛኛዎቻችን ችግር ይህ ነው። ስኬትም ሆነ ውድቀት በአንድ ቀን ጥረት የሚመጡ ይመስለናል፡፡ መች ይሄ ብቻ ፤ ዛሬ የስኬት ፍሬ ዘርተን ነገ በቅሎ ማየት እንሻለን። የተፈጥሮን ኡደት መጠበቅ አቅቶን የዘራነውን እየነቀልን በትግስት ማጣት ወጥመድ እንወድቃለን፡፡ ጎጠኞች የዘሩት የክፋት መንገድ በአንድ ምሽት እንደ አረም ተነቅሎ፤ ካልተጣለ ብለን በድብርት ማቅ ውስጥ እንወድቃለን። እምነት እናጣለን፡፡ ለዘመናት የበቀለው መልካም የአንድነት ፍሬ በዓመታት የአረም ዳዋ የሚለብስና የሚነቀል ይመስለናል፡፡ ማስተዋል አቅቶን ለአያቶቻችን ጆሮ ነፍገን፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 16/2012
ዳግም ከበደ