ከዩኒቨርሲቲ ተመርቄ ሦስት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የሦስት መስሪያ ቤቶችን ጓዳ አንጎዳጎድኩ። እነዚህ ተቋሞች አንድ ነገር እንደሚያመሳስላቸው ታዝቤያለሁ፡፡ ዜጎች በዩኒቨርሲቲ፤ በመስሪያ ቤቶችና መኖሪያ መንደሮች አካባቢዎች ሰብሰብ ብለው ስለ አንድ ጉዳይ በተለይ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ጠንካራ ሃሳቦችን በመሰንዘር እንደሚወያዩ ይታወቃል። በዚህም በሁለት ከፍ ሲልም በሦስት ጎራ ተከፍሎ መከራከርም የተለመደ ነው፡፡
በየሰፈሩም ቢሆን ሰብሰብ ተብሎ እስከ ምሽት ሦስት እና አራት ሰአት ድረስ ትኩረት ስለሚስቡ ጉዳዮች መወያየት በወጣቶችም ሆነ በተለያየ የእድሜ ክልል ላይ በሚገኙ ሰዎች አዲስ ነገር አይደለም። በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጊቢ ውስጥ ከዋናው ጉዳይ ውጪ ስለፍቅር የሚወራበት፣ ሴቶችና ወንዶች ሰብሰብ ብለው የሚያወጉበት፣ ፖለቲካ የሚፈጭበት እና የችከላ ቦታዎች በስፋት አሉ፡፡
በእርግጥ እነዚህን ለምሳሌነት አነሳሁኝ እንጂ ሌሎችም አይጠፉም፡፡ ሁሉም ደስ ወዳለው እየሄደ ሃሳብን በሃሳብ ይመለክታል፤ አንዱ ለሌላው ያዋጣል። ይህ ደግሞ በየእለቱ ከአዲስ ሰዎች ጋር ለመተዋወቅ እድልን ይፈጥራል፡፡ ከፍ ሲልም ሊያወዳጅ ይችላል፡፡ ጉዳዩ የሰው ልጆች ባህል መሆኑን ለማመላከት ከጥንት ጀምሮ እንደሚፈፀም በርካታ መረጃዎችን በማንሳት ማሳየት ይቻላል።
የዛሬ ምልከታዬ በዋናነት በአገራችን በተለይ ደግሞ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት መዝናኛ ክበብ ውስጥ ክርክር ስለሚደረግበት አንድ ቦታ ማውሳት ነው፡፡ በዚህ ስፍራ ደንበኞች የሚስተናግዱባቸው ቦታዎች የራሳቸው የሆነ መለያ ቁጥር ተሰጥቷቸዋል፡፡ አስተናጋጆችም አንድ፣ ሁለት እና ሦስት ወዘተ. የሚል የመለያ ቁጥር አላቸው፡፡ በዚህ መሰረት ደንበኞቻቸውን ያስተናግዳሉ፡፡
ቁጥር ከተሰጣቸው ቦታዎች መካከል አስተናጋጆች በቅፅል ስሙ ‹‹ሲጋራ ተራ›› ብለው ይጠሩታል፡፡ እኔ ግን ወሬ ማጨሻ ቢባል የተሻለ ይመስለኛል፡፡ መጠሪያውን ያገኘው በቦታው ላይ ከሚቀመጡ ሰዎች ባህሪ አንፃር ነው፡፡ በብዛት የሚያዘወትሩ ሰዎች ሲጋራቸውን ማግ እያደረጉ ወሬ የሚያጨሱ ናቸው፡፡ ነገር ግን ቡና እየጠጡ እና ቁርሳቸውን እየበሉ የሚሳተፉም ሆነ የሚታዘቡም በስፍራው ይታደማሉ፡፡
ከዚህ ቀደም የዚያ ሰፈር ደንበኛ ስላልነበርኩ፤ በርከት ያሉ ሰዎች ተሰብስበው ድምፃቸውን ከፍ እያደረጉ ሲያወሩ ብሰማም ትኩረት ሰጥቼው አላውቅም ነበር። አንድ ቀን ግን የቦታውን ሁኔታ ከሚያውቅ ጓደኛዬ ጋር ሄደን ቁጭ አልን፡፡ አረፍ ከማለቴ ብዙ ነገሮች ሲወሩ (እየተነሱ ሲጣሉ) ሰማሁኝ፡፡ በስፍራው ተገኝቶ የራስን ሃሳብ አለመሰንዘር ከባድ ነው፡፡ ድንገት እራስን ከአንዱ ሃሳብ ጋር አዛምዶ አመክንዮን ሲወ ረውሩ ያገኙታል።
በወሬ ማጨሻ ስፍራዋ ፖለቲከኞቻችን ስልጣናቸውን ለማስጠበቅ ሲሉ ‹‹ፖለቲካንና ኤሌክትሪክን በሩቅ ነው›› እያሉ የሚያስፈራሩባት አባባል ቦታ ካለማግኘቷም በላይ ቃሏ ትዝ የምትለው ተከራካሪ የለም፡፡ እየተመረጠ እሳት እሳቱ ይወራል፡፡ በእርግጥ ‹‹ጋዜጠኞች›› በመሆናቸው ለሻይ አረፍ ሲሉ ይህን መሰል ሃሳብ መሰንዘሩ የሚጠበቅ ነው፡፡
ብዙ ዝምተኛ የሚመስሉ የስራ ባልደረቦቼ በሲጋራ ተራ ወሬ ለማጨስ ማርሽ ቀያሪዎች ናቸው፡፡ ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ በጥቅሉ ማህበራዊ ጉዳዮች ይወራሉ፡፡ በስፋት ይተነተናሉ፡፡ አንድ ወሬ ይወለዳሉ፤ በፍጥነት ያድጋሉ፤ ይሞታሉ፡፡ በጥቅሉ ለማውራት ‹‹እኛ እና እነሱ ›› ብሎ መፍራት የለም፡፡ በሀያሏ አሜሪካ በቅርብ እስከተዋለደችው ደቡብ ሱዳን ድረስ የማይንኳኳ በርና የማይነሳ ሀሳብ አይገኝም፡፡ የሚጎነተለው ተተንኩሶ፤ የሚብጠለጠለው ይጎሻሸማል። የሚወደሰውም እንደዛው፡፡
ስለ አገራችንም ፖለቲካ አንዱ ብድግ ብሎ አሁን ያሉ ችግሮች ሁሉ በቅርብ እንደሚፈቱና ከወቅታዊ ችግር በዘለለ ዘላቂ ችግር እንዳልሆነ ሲናገር ፤ በሌላ ጎራ የተሰለፈው ቡድን ደግሞ የኢትዮጵያ እድሜ ከአንድ ቀን የጸሀይ ውሎ እንደማይበልጥ በማስረጃ ‹‹እውነት ነው እንዴት?›› እስክትል ድረስ አስረድቶ ሊያሳምንህ ይሞክራል፡፡ በወሬ ማጨሻ ቦታ የአገራችን ፖለቲከኞች ምን እንደሚባሉ ቢሰሙ ብዬ ልከትበው አሰብኩና ከዚህም በላይ ሃሳብ በሃሳብ እንደሚደባደብ ሲገባኝ አለፍኩት።
ከላይ ካነሳሁላችሁ መነሻ አመክንዮ በተጨማሪ እንዲህ አይነት ክርክር እና ውይይት የማውቀው በመፅሐፍ ላይ የ1960ዎች ትውልድ እየተባሉ የሚጠሩ ተማሪዎችን ነው፡፡ ካፒታሊዝምን ጠልተው ሶሻሊዝምን አምልከው የእነ ሌሊን መፅሐፍትን እንደሕይወት መርህ ቆጥረው የሚከራከሩት ማለት ነው፡፡
በዚህ ስፍራ ከታደምኩ ወዲህ እንዲያውም የአገራችን ፖለቲከኞች ከስሜታዊነት ነፃ ሆነው ክርክር ማድረግ ከፈለጉ ወደ ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጎራ ቢሉ ከወቀሳ ይተርፋሉ የሚል እምነት አሳድሮብኛል። ጥሩ ልምድም እንደሚያገኙም አልጠራጠርም፡፡ ያው አለ አይደል ልምድ ልውውጥ ጥሩ ነው መቼም። በመደማመጥ ላይ የተመሰረተ ውይይት ከመልመድም፤ የአንድን ሰው እውነት ከማጣጣልና ከመንቀፍ ይልቅ፤ ሃሳብን በሃሳብ የመመከት ጥሩ ል ምድ መቅሰም ነው፡፡
እናማ ሃሳቤን ከማጠቃለሌ በፊት በመጨረሻ ይሄን ሃሳብ ጣል ለማድረግ ወደድኩ። ችግሮችን በክርክር የመፍታት ልምዱ ደካማ ለሆነ ማህበረሰብ ‹‹የወሬ ማጨሻ›› ተብላ እንደተሰየመችው ስፍራ በተመሳሳይ በተለያዩ ቦታዎች እንዲህ ያሉ የበረከቱ ጉሊቶች መኖር አለባቸው የሚል ሃሳብ አለኝ፡፡ በተለይ ደግሞ በመስሪያ ቤት፣ በትምህርት ቤት እና በመዝናኛ ቦታዎች ቢዘወተሩ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች ይኖራቸዋል፡፡ በተለይ ሃሳብን በነፃነት ለመተንፈስ።
አንዳንድ ወዳጆች በአጋጣሚ አልያም አስበውበት ወደ አራት ኪሎ ብቅ ካሉ ‹‹ወሬ ማጨሻ›› ጎራ በማለት፤ በአምስት ብር ቡና እየተጎነጩ ዋጋ የማይወጣለትን ሃሳብ እንደሚያዋጡ በሚስጥር ሹክ ማለት እወዳለሁ። ሰላም!
አዲስ ዘመን ግንቦት 16/2012
ሞገስ ፀጋዬ
የጋዜጠኛው ቅኝት
ከእርሶ ለእርስዎ
- በግብፅ አቋም እየተገረምኩ ነው፤ እሷን ለማናደድ ምን ላድርግ ?
ሳሚ ሳሚ (ከጉርድ ሾላ )
መልስ – 8100 ላይ ደጋግመህ “A” ብለህ ላክ - ቁመቴ አጭርና ደቃቃ ነኝ፡፡ የወደድኳት ልጅ ደግሞ ረጅም ግዙፍ ወንድ እንደምትወድ ሰምቻለሁ ምን ላድርግ?
ቶማስ ነኝ ከሳር ቤት
መልስ -በአመለካከትህ ገዝፈህ ተገኝ - ከእጮኛዬ ጋር ሁሌ እንጨቃጨቃለን፤ ሰሞኑን ደግሞ እርሷ እንጋባ እኔ ደግሞ እንቆይ በማለት እየተጋጨን ነውና ምን አስተያየት አለህ፡፡
ሰመረ አብርሃ (ከመቀሌ)
መልስ- ከመጋባታችሁ በፊት ተግባቡ - አሜሪካ በአባይ ጉዳይ ከግብፅ ጎን መሆንዋ አብሽቆኛል፤ አንተ ይህንን ስትሰማ ምን ተሰማህ?
ገብሬ (ከወሊሶ )
መልስ- ነገ ወደ ኢትዮጵያ እንደምትመጣ - ክረምቱን እንዴት ልታሳልፍ አስበሀል?
በላይነህ ከአዳማ
መልስ- በችግኝ ተከላ - ልጅ እፈልጋለሁ ግን ማግባት አልፈልግም ምን ይሻለኛል?
ሰላም (ከቦሌ)
መልስ – ሳይዘሩ ማጨድማ ደስ አይልም - የሰሞኑ መዘናጋት ምን የሚያስከትል ይመስልሀል?
ካሳሁን (ከውቅሮ)
መልስ – እልቂት
. አሁን ኢትዮጵያን ቀጥ አድርገው ያቆሟት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ናቸው ይባላል፤ እውነት ነው አይደል?
ሰላማዊት (ከ ፒያሳ)
መልስ- በነገር ደግፈው ?
. ፈጣሪ ከኮሮና ይጠብቀኛል ብለው የማይጠነቀቁ ሰዎችን ምከርልኝ
የኔነህ (ከአዳማ )
መልስ- “ ግመላችሁን አስራችሁ በኔ ተመኩ” ያለውን ገልብጠው ሰምተው ይሆናላ
አዲስ ዘመን ግንቦት 16/2012
ተገኝ ብሩ