ዘንድሮ ኮቪድ 19 (የኮሮና ወረርሽኝ) ደሀ እና ሐብታም ሳይለይ በመቅሰፍቱ መቷል። በቴክኖሎጂ፣ በሐብት፣ በሕክምና ሳይንስ ምጥቀት፣ በመሠረተልማት ዕድገት… አብዝተው የሚኩራሩትን አገራት ሳይቀር ክፉኛ ደቁሷል። ዓለም በከፍተኛ ግራ መጋባት ውስጥ ሆኖ ከ90 በላይ የክትባት ሙከራዎችን በአቦሸማኔ ፍጥነት ወደማፈላለግ ተሰማርቷል። አማኙም ፈጣሪውን ምህረቱን እንዲልክ መማጸኑን ቀጥሏል። ይኸም ሆኖ ኮቪድ 19 መግደሉን፣ በሕመም ማሰቃየቱን፣ ማሸበሩን፣ ማደኸየቱን… የሚገታው ኃይል እስካሁን አልተገኘም። ከዚህ አስከፊ መቅሰፍት ለመገላገል በምንጸልይበት፣ በምንተጋበት በዚህ ወቅት ዓለማችን ሌላ ከባድ ፈተና ተደቅኖባታል። ቀጣዩ የሰው ልጆች የኑሮና የጤና ቀውስ ምንጭ የአየር ጠባይ ለውጥ የሚያስከትለው መቅሰፍት እንደሚሆን ሳይንቲስቶች ስምምነታቸውን ካሳረፉ ውለው አድረዋል፡
አምና አራት ቢሊዮን ዛፎችን ለመትከል በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ተነሳሽነት ሲወሰድ ወጣቶች በቲውተር የከፈቱት ዘመቻ ነበር። “የአራዳ ልጅ ዛፍ ይተክላል!” ይላል። ግሩም አባባል፣ ድንቅ መልዕክት ነበር።
አዎ!…የዓለማችን ሙቀት ጨምሯል። የዝናብ ወቅቶች ተዛብተዋል። ወንዞች ጎድለዋል፣ በአንዳንድ ቦታም ደርቀዋል። የሙቀቱ መጠን በዚህ ያህል ዲግሪ ጨምሯል፣ ቀንሷል የማለት ስሌት ውስጥ ሳንገባ ጭማሪው የምናየው፣ የሚሰማን መሆኑ በራሱ የሚነግረን ነገር አለ። ከችግሩ ጋር ተያይዞ ድርቅና ቸነፈር ተደጋጋሚነቱ ጨምሯል። የተፈጥሮ አደጋዎች (ጎርፍ፣ አውሎ ነፋስ፣ ቃጠሎ፣ የመሬት መንቀጥቀጥ፣ የበረዶ ግግሮች መቅለጥ…) የሰዎችን ኑሮ ወደሲኦልነት እየተቀየረ እያየን፣ እያስተዋልን ነው። የተፈጥሮ ሚዛን መዛባት የሰዎች ሕይወት በድንገተኛ አደጋ እንዲሞላ የራሱን አስተዋጽኦ አድርጓል። በአጭሩ ሕይወት ከፍቷል። ተመራማሪዎቹ እንደሚሉት በቅርቡ መቋቋም የማንችለው ሙቀት ምድራችን ይፈትናታል፤ የምድር የውሃ አካላትም
—ከፍታቸው ይጨምራል። ምንም እንኳን የካርቦንዳይኦክሳይድ ልቀት መጠንን ለመቆጣጠር ሃገራት ስምምነት ላይ ቢደርሱም፤ የምድር ሙቀት ከእለት ወደ እለት እየጨመረ መጥቷል። የምድር ሙቀት በየዓመቱ 2 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ የሚጨምር ከሆነ፤ የሁላችንም ሥጋት የሆነው ከፍተኛ ሙቀትና ተያያዥ ችግሮች ዓለምን ከኮሮናም በባሰ ማመሳቸው አይቀሬ ይሆናል።
አንድ ዓለማቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ የተመራማሪዎች ቡድን ያደረገው ጥናት ምድራችን የምትተማመንባቸው የተፈጥሮ ሃብቶቿ በቅርብ አስርት አመታት ውስጥ ለኑሮ አስቸጋሪ ወደሆነ መልክአ ምድርነት ይቀየራሉ ይላል።
ተፈጥሮአዊ አደጋዎች የበዙት እንዲሁ በገጠመኝ ሳይሆን የአካባቢ ጥበቃ መላላትና በአካባቢ ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት ወይንም ጥፋት መስፋፋት ጋር በቀጥታ የተገናኘ ነው። ጥቂት ክስተቶችን ዳሰስ እናድርግ።
ክሮሽያ፤ እንደማንኛውም የዓለም ሕብረተሰብ የኮቪድ ወረርሽኝን ጋር ግብግብ በገጠመችበት በዚህ ወቅት በተፈጥሮ አደጋ መመታቷ መሰማቱ ለሰሚው ሁሉ አሳዛኝ ክስተት ነበር። በዚህ ላይ፤ ዓለም በሩን ዘግቶ የኮሮና ወረርሽኝን እያስታመመ ያለበት ወቅት መሆኑ ደግሞ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖባታል። ከአንድ ወር በፊት በክሮሽያ መዲና ዛግሬብ በአገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር 6 ሰዓት አካባቢ የደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ በርካታ ሕንጻዎችን ሲደረማምስ፤ ፍርስራሹ ብዙ ቁጥር ያላቸው ተሽከርካሪዎችን በቆሙበት ከጥቅም ውጭ አድርጓል።
የመሬት መንቀጥቀጡ በሬክተር ስኬል 5 ነጥብ 3 የተመዘገበ ሲሆን እንዲህ ዓይነቱ አደጋ ለአገሪቱ በ140 ዓመት ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ነው ተብሏል።
በክስተቱም ከ16 በላይ ሰዎችም ጉዳት ደረሰባቸው። በአደጋው የተደናገጡ የዛግሬብ ነዋሪዎችም ቀደም ሲል በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ቤታቸው ውስጥ እንዲቀመጡ ቢነገራቸውም ይኸኛው ድንገተኛ አደጋ ግን አደባባይ እንዲወጡ አስገድዷቸዋል።
አንድ ላይ በድንገት መሰባሰባቸው ለቫይረሱ መዛመት እድል ይፈጥራል በማለት ሥጋት የገባቸው የአገሪቱ ባለስልጣናት ሰዎች በፍጥነት ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ ሲማጸኑ እንደነበር የቢቢሲ ዘገባ ያሳያል።
በተመሳሳይ የተፈጥሮ አደጋ የዛሬ ሶስት ዓመት በማዕከላዊ አሜሪካ “ኔት” ተብሎ የተሰየመው አውሎ ነፋስ በኮስታሪካ፣ በኒካራጓዋ እና በሆንዱራስ ቢያንስ 22 ሰዎችን ገድሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶችን አውድሟል። በማዕከላዊ አሜሪካ የሚገኙ ሃገራት 20 ሰዎች የገቡበት ሳይታወቅ ቀርቷል።
ከፍተኛ ዝናብ የቀላቀለው አውሎ ነፋስ የመሬት መንሸራተት እና ጎርፍ በመፍጠሩ መንገዶች ተዘግተዋል፤ ድልድዮች ተንደዋል፤ እንዲሁም በሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶች ፈራርሰዋል።
በወቅቱ ከአደጋው ጋር ተያይዞ በኮስታሪካ 400ሺ የሚሆኑ ሰዎች የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ሲቋረጥባቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ይገኛሉ።
በኮስታሪካ ቢያንስ 6፣ በኒካራጓዋ ደግሞ 11 ሰዎች ህይታቸውን አጥተዋል። በሆንዱራስ 3 ሰዎች መሞታቸው ሲረጋገጥ በርካቶች የገቡበት አልታወቀም ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
በሌላ በኩል ጃፓን የዛሬ ዘጠኝ ዓመት ገደማ ዓለም ፈጽሞ የማይረሳውን ዘግናኝ የተፈጥሮ አደጋ አስተናግዳለች። በጃፓን ሰሜናዊ ምሥራቅ የባህር ጠረፍ በተከሰተ የመሬት መንቀጥቀጥና የማዕበል አደጋ ከ18 ሺ በላይ ሰዎች መሞታቸውና የደረሱበት አለመታወቁ ይታወሳል።
በርዕደ መሬት መለኪያ ዘጠኝ የተመዘገበው የመሬት መንቀጥቀጥ ከፍተኛ ማዕበል እንዲነሳ በማድረግ በሀገሪቱ የመሰረተ ልማት ላይ ከፍተኛ ጉዳትም አስከትሏል።
አደጋው በፉኩሽማ የኑክሊየር ማብለያ ጣቢያ ላይ ያስከተለው ጉዳት በአካባቢው እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከፍተኛ የጨረር ሥጋት ፈጥሮ መቆየቱም የሚታወስ ነው።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የአረንጓዴ ሌጋሲ
ተፈጥሮን ጠብቆ ለመቆየት ዛፎችን መትከልና መንከባከብ የምርጫ ጉዳይ አይደለም፤ የውዴታ ግዴታ ሆኗል። በዘርፉ የተመራመሩ ባለሙያዎች የተፈጥሮ ሀብቶቻቸዉን በተገቢው መንገድ የማይዙ እና ጥቅም ላይ የማያዉሉ ማሕበረሰቦች ላልታሰበ ሥርዐተ-ምህዳራዊ አጥፍቶ የመጥፋት አደጋ ይጋለጣሉ ይላሉ።
የደኖች መመናመን፣ የዕጽዋት አይነት እና ብዛት መቀነስ፣ የደን ለበስ መሬቶች መራቆት፣ ሚዛን ያልጠበቀ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም፣ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ዕድገትና የመሳሰሉት ለተጠቀሰዉ አደጋ ምክንያት መሆናቸዉ ይነገራል። እናም ትልቁ መፍትሔ የተፈጥሮ ሐብትን መንከባከብ ነው። በዚህ ረገድ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ አምና የተጀመረው ኢንሼቲቭ ከአራት ቢሊዮን ተነስቶ ዘንድሮ አምስት ቢሊዮን ችግኞችን ወደመትከል ዕቅድ ተሸጋግሯል።
ሰሞኑን በዜና አውታሮች እንደተሰማው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት የዚህን ዓመት የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ቅድመ ዝግጅት በተመለከተ ውይይት ተካሂዷል።
በውይይቱ ላይ የችግኝ ተከላ ቅድመ ዝግጅት በተመለከተ የግብርና ሚኒስቴር ማብራሪያ ያቀረበ ሲሆን የብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚቴው አባላት፣ የቴክኒክ ኮሚቴ አባላት፣ የክልል ፕሬዚዳንቶች፣ ሕዝቡን የማነሳሳት ሥራን የሚከውኑ ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችን ጨምሮ ዐበይት ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
ባለፈው ዓመት የችግኝ ተከላ ወቅት የዜጎች መነሳሳት፣ ንቁ የመንግሥት አመራር ተሳትፎ፣ የተቋማት ትብብር እና የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ እንደነበረ ነው የተገለፀው። እነዚህን መልካም ተሞክሮዎች ማስፋት እንደሚያስፈልግም በውይይቱ ተነስቷል።
የዚህ ዓመት ግብ 5 ቢሊዮን ችግኞችን መትከል ሲሆን፥ ለዚህ የሚሆን ብዛት ያለው ችግኘ እንዲፈላ ቅድመ ዝግጅት ሲካሄድ ቆይቷል ነው የተባለው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም ጅማሮዎችን ማስቀጠል ጠቃሚ መሆኑን በመግለፅ አረንጓዴ አሻራ በመጭዎቹ ጥቂት ዓመታት በመላው ኢትዮጵያ 20 ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል እንደሚቀጥል መናገራቸውን ከጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
«ችግኝ መትከልን እንደዘመቻ ሥራ ሳይሆን የኑሮ ዘይቤ ማድረግ ይገባል» ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
“የኑሮ ዘይቤ” ሲባል እንዴት?
የአፍሪካ መዲና የሆነችውን አዲስ አበባ እንመልከት። በርካታ ኢንቨስትመንቶች አሉ። ካዛንቺስ አካባቢ ችምችም ብለው የበቀሉ ዓለም አቀፍ ሆቴሎች አንድ ትልቅ ነገር እንደሚጎድላቸው እነሱም በቅጡ የተረዱት አይመስሉም። ሆቴሎቹ በጠባብ ቦታዎች የሰፈሩ እንደመሆኑ መጠን ተጨማሪ ቦታ ቢያገኙ ባለሃብቶቹ ወደአዕምሮአቸው በቶሎ የሚመጣው የመኪና መቆሚያ ፓርኪንግ ወይንም እንደዋና ገንዳ፣ የስብሰባ አዳራሽ የመሳሰሉ የሆቴል ማስፋፊያ ሥራዎች መገንባት ነው። በእርግጥም እነ ኢሊሊ ሆቴል ባገኙት ተጨማሪ ቦታ ዘመናዊ ፓርኪንግ ሲገነቡ፣ ኢንተርኮንትኔታል ደግሞ ተጨማሪ ሆቴል ማስፋፊያ ማከናወኑን መታዘብ ይቻላል። ይኸም ሆኖ የሆቴል ኢንቨስትመንቶች ባለቻቸው አነስተኛ ቦታ ችግኞችና እጽዋቶችን በመትከልና የአካባቢውን ልምላሜ በመጠበቅ ረገድ ሙከራዎች ማድረጋቸው የሚካድ ባይሆንም አጥጋቢ ናቸው ብሎ ለመናገር ግን አይቻልም። በሌሎች የኢንቨስትመንት ዘርፎችም ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ከዚህ እምብዛም የሚርቅ አይደለም። ሌላው ቀርቶ በአካባቢ ጥበቃ ሥራ ላይ የተሰማሩ ወገኖችን በመደገፍና በማበረታታት ረገድ ባለሃብቶቹ ያከናወኑት ተግባር ለወሬ የሚበቃ አይደለም። ይኸ እንግዲህ የዛፍ ተከላ ወይንም የአካባቢ ጥበቃ ጉዳይ ከቀዳሚ አጀንዳዎች አንዱ እንዲሆን ከምንም ነገር ቀድሞ በሰዎች አእምሮ ላይ ብዙ መሥራትን የሚጠይቅ መሆኑን ተጨባጭ ሁኔታው አስረጂ ነው።
በሌላ በኩል የአረንጓዴ ልማትን አስፈላጊነት አስመልክቶ በመንግሥታዊ አካላት ዘንድም ያለው አረዳድ አንድ ወጥ አይደለም። እንዲያውም ከታይታና ከመገናኛ ብዙሃን ፍጆታ ያላለፈ ተግባር ውስጥ የተዘፈቁ ተቋማት ቁጥር የትየለሌ ነው። አዲስ አበባን እንመልከት…ባዶና ቆሻሻ መጣያ ቦታዎችን አልምተው፣ አረንጓዴ አልብሰው ለሚጠቀሙ ወጣቶች ቦታ ከልሎ ከመስጠት ይልቅ ባለበት እንደቆሸሸ እንዲቆይ የሚመርጥ አመራር በርካታ ነው። በአረንጓዴ የተከለሉ ቦታዎችን “ዛፍና እጽዋት ምን ያደርጋል?” በሚል ደካማ አስተሳሰብ ከፕላን ውጪ ላልተገባ ዓላማ እንዲውል በቀጥታም በተዘዋዋሪም የሚተባበሩ አመራሮች በብዛት መኖራቸው የአደባባይ ምስጢር ነው።
እናም የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የአረንጓዴ አብዮት ሕልም እንዲሳካ ከላይ እስከታች ያለው አመራር ቢያንስ ከአንድ መጽሐፍ ማንበብ መቻል አለበት። በርዕሰ ጉዳዩ ላይ ያለው አረዳድ እኩል እንኳን ባይሆን ቢያንስ የተመጣጠነ እንዲሆን የሚመለከታቸው አካላቶች ቀጣይና ተከታታይ የሥልጠና እና የልምድ ልውውጥ መድረኮች ለማዘጋጀት ከወዲሁ ሊያስቡበት፣ ሊሰሩ ይገባል። ችግኝ መትከል ወደ ኑሮ ዘይቤ ወይንም የእለት ተዕለት ልማድ ደረጃ እንዲያድግ እነዚህ መንገዶች ማለፍ፣ ራሳችንን አብጠርጥረን ለማየት እጅግ ወሳኝ ነው።
ከችግኝ ተከላ በፊት
አምና ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ. ም ኢትዮጵያ አንድ ቀን የወሰደ የችግኝ ተከላ ዘመቻ አከናውናለች። የታቀደው በመላው አገሪቱ 200 ሚሊዮን ችግኞች ለመትከል ነበር። የኋላ ኋላ ግን መንግሥት ከታቀደው በላይ በ12 ሰዓት ውስጥ 353 ሚሊየን 633 ሺ 660 ችግኝ መተከሉን ይፋ ማድረጉን የምናስታወሰው ነው። አምና በክረምቱ ወራት በድምሩ ከአራት ቢሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸው በመንግሥት ይፋ ሆኗል። የተተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ ረገድ አርአያ ለመሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩና ሌሎች ባለሥልጣናት ውሀ የማጠጣትና የመኮትኮት የተለዩ ፕሮግራሞች በተደጋጋሚ ቢያካሄዱም ከታች ያለው አመራር ጨምሮ አብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ይህን በሚጠበቅ መልክ አላስኬደውም። ምናልባት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ውትወታ በበቂ ሁኔታ ሚዛን አልደፋ ይሆን? ወይንም የችግኝ ተከላው እንደቅንጦት ነገር ታይቶ እንደሆነ ለጊዜው ለዚህ ጹሑፍ አቅራቢ ግልጽ የሆነ ነገር የለም።
ደግነቱ አምና ከተተከሉት ችግኞች ወደ 85 በመቶው መጽደቃቸው ዘግይቶም ቢሆን መሰማቱ መልካም ዜና ነው። ሥራውን በዘመቻ መልክ እንደማድረጋችን፣ በተከላና እንክብካቤ ወቅት እንዳለብን በርካታ ክፍተት ሲታይ ከተተከለው ግማሽ ያህሉ እንኳን ቢጸድቅ ትልቅ ድል ነው ብዬ አስባለኹ።
ወዳጄ ግሩም ተበጀ፤ ስለችግኝ ተከላ ጉዳይ ሰሞኑን ያካፈለን ሀሳብ የጠቅላይ ሚኒስትሩን የረዥም ጊዜ ሕልም ጠቋሚ ይመስለኛል። በጥቂቱ አነሳዋለኹ። “የዛሬ 30 ዓመት ዐቢይ አሕመድ ከሚመሰገንባቸው ነገሮች ዋንኛው ይህ አሁን ከቁብም የማንቆጥረው የችግኝ ተከላ ነገር ነው። ያኔ የዓለም ሕዝብ ብዛት 9 ነጥብ 6 ቢሊዮን ይደርሳል፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛት ደግሞ ወደ 180 ሚሊዮን ይጠጋል። የዓለም ሙቀት መጨመር፣ የአካባቢ መራቆት እና የመሳሰሉት የምር የሕልውና ጥያቄ ሆነው የሚጋረጡት ያኔ ነው። ያኔ የዓለም ሕዝብ ሁሉ (ትንቢት አስመሰልኩት እንዴት – ኖ … ይሄ እውነታ ነው … የሚታዩት ነገሮች ይሄን ነዋ የሚያሳዩት) ችግኝ ለመትከል ወደኋላ አይልም። ግን ምን ዋጋ አለው … በ2050 እ.ኤ.አ ዛፍ ለማግኘት ችግኙ መተከል ያለበት ዛሬ ነው። ይህ መሪም እኛ ቀልድ ያደረግነውን ነገር የምር አድርጎት ዛሬም 5 ቢሊዮን ችግኝ ሊያስተክለን ነው።
አሁንም የችግኝ ተከላው ነገር ያልገባን በ10 ሚሊዮኖች እንቆጠራለን። ስለዚህም ችግኙ እየተተከለ ያለው ጭንቅላታችን ውስጥ ነው። ቀስ ብሎ ነው የሚገባን።
አዎ!..ላልገባን፤ አውቀን ላልለገምን ቀስ ብሎ ነው የሚገባን። ግን ምንም ቢሆን እውነታውን አንርሳ!.. ችግኞች ልክ እንደጨቅላ ሕጻናት ናቸው። በጤና ለማደግ ተገቢውን እንክብካቤ ይፈልጋሉ። ችግኞችን ከማፍላት ጀምሮ እስከማጓጓዝና መትከል እንዲሁም የሚተከልባቸው ቦታዎች አየርና አፈር ተስማሚነት መመርመርና ጉድጓዶች ማዘጋጀት ድረስ ያሉ ሰፊ ሒደቶች የባለሙዎችን እገዛ ይሻሉ። ዝም ብሎ በዘመቻ ግር ብሎ በመሄድ ችግኞችን በመትከል ስም ቀብሮ መምጣት የሐብትና የጊዜ ብክነትን ከማስከተል ያለፈ ፋይዳ የለውም።
ዋናው ነገር ተቋማት የጠቅላይ ሚኒስትሩን የአረንጓዴ ልማት ፍላጎት፣ ፍላጎታቸው ማድረግና ይኼንን ለማሳካት ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ መንቀሳቀስ እንደሚገባቸው ለአፍታም ቢሆን ሊዘነጉ አይገባም። ቢያንስ ችግኝ ከመትከል በፊት እንዴት እንደሚተከል የጥቂት ደቂቃ የባለሙያ ምክርና ሀሳብ መስማት እንደልጆች የምናያቸውን ችግኞች ዕድገት ይረዳል። እናም ደግሞ አንድ እጅ አያጨበጭብም እንዲሉ በአረንጓዴ ልማት ለትውልዶች የሚተርፍ ቅርስን ለማቆየት ሁሉም በቅድሚያ ዓላማውን በአግባቡ ይረዳ!… በአብሮነት መንፈስም ይተጋገዝ!..ይንቀሳቀስ!!…
አዲስ ዘመን ግንቦት15/2012
ፍሬው አበበ