መጋጋልና ማጋጋል ወይስ መስከንና ማስከን
በሰው ልጅ የአኗኗር ባህል ውስጥ ነገር እንደያዥው መሆኑ የታመነ ነው። ሰው በህይወት አጋጣሚ በሥራው በትዳሩ፣ በተሰጥኦው፣ በሙያው፣ ከሰዎች ጋር መገናኘቱ እውነት ነው። ሁሉም ነገር ፣ ቢኖርህ ያለሰው ምንም ነው። ስለዚህ ሰው ያስፈልግሃል።
ታዲያ ከሰው ጋር ያለህ ግንኙነት ሁልጊዜ በሁሉም ነገር ስምሙ ሆኖ አይዘልቅም። ግጭት አለመግባባት ወይም አለመስማማትም በሉት ሊፈጠር የመቻሉ ሁነት ተፈጥሯዊ ነው። “አይ…ሰው መሆን ትል ነበረ፤” አያቴ፣ ከሰው አልጥም ያለ ነገር ሲገጥማት።
እናም የሚገጥመንን ነገር አጋግለን መጋጋል ይሻላል… ወይስ አብርደን መብረድ? ምርጫው በእጃችን ነው። አንዳንዶቻችን የነገር አያያዛችን ብጤት አስቂኝም አሳዛኝ ነው። ይህንን ያልኩት አለምክንያት አይደለም ። አሁን በቅርቡ አንድ በኤሌክትሮኒክስ ሚዲያው ገናና የሆነ ስም ያለው “ትልቅ” ሰው “ጭቃ ሲያቦካ ተያዘ” ተብሎ፣ ሐገሩ በአብዛኛው ከስራ ይገለል ብቻ ሳይሆን ዓይኑም ይውጣ ለማለት እየቃጣው ነው።
እውነቱን እንነጋገር ከተባለ የሰውየው ጥፋት አደገኛ የሚሆነው እያደረገ ያለውን ነገር ህጋዊ በሆነ፣ በሚሰማ ወይም በሚታይ የመገናኛ ብዙሃን እርቃኑን ወጥቶ በሚታመን መንገድ፣ የህይወት እቅሜና አቋሜ ይህ ነው፤ ተከተሉኝ ብሎ አምኖበት ሲናገር ወይም ሲያደርገው ቢታይ ነበረ። ይሁንናም፣ ጉዳዩን ለአደባባይ ያወጡት አካላት ፣ ግላዊ ድንበሩን ጥሰው ሰብእናውን አራክሰው በሥራውና በኑሮው አካሄድ ላይ ደንቃራ የሚፈጥር ነገር እስኪመጣ ድረስ ለትዝብት አጋልጠውታል። ደግሜ ልጠይቅና፣ ከዚህ ሰው የባሱ ጥፋቶችን የፈጸሙና እየፈጸሙ ያሉ ሰዎች፣ በቤታችን፣ በጎረቤታችን፣ በመስሪያ ቤታችን የሉምን ? አሉ፤ ግን ለእነርሱ ዓይናችን ይታወራል፤ ወይም እነዚያ ሰዎች “እኛ ነን” ማለት ነው።
ከዚህ ሰው ጋር፣ ጠባቸው የሚጀምረው ደግሞ ከልጁ አስተዳደግና ከድሮ ስሙ ጀምረው ነው። ድሮ ስሙ እኮ አስናቀ ነበር የሚባለው፤ አሁን “ሣሙኤል ነኝ”፤ ያለው በቅርቡ ነው፤ ብለው ነው ዝርጠጣው የሚጀመረው። በነገራችን ላይ “አስናቀ” ትርጉሙ ወደርየለሽ፣ ምቹ፣ ለዓይን ማራኪ፣ ከሰው በውበትና በአደራረግ የሚበልጥ፣ ለስላሳ ሌላን የሚያስንቅ፣ የሚልቅ ማለት ሲሆን ሰውየው ይህንን ስም ትቶ “ሳሙኤል ነኝ” ያለው ዕብራዊ ሴት ጓደኛ ከያዘ በኋላ ነው፤ ነው የሚሉት። እናስ ? ዕብራዊ ስም መምረጥም መጠራትም ማነስም መብቱ ነው። ይህም አንደኛ አሁን ተሰራ ከሚባለው ስህተት ጋር የሚያስተሳስረው አንዳችም ገመድ የለም፤ ሁለተኛ ይህ የግል ምርጫው ነው።
ሌላው እና ዋናው ነገር ደግሞ የተፈጸመውን ስህተት መመርመር ሳያስፈልገን ያለበትን የህይወት ከፍታ ካለመገንዘብ የመነጨ፣ የየዋህነት ውጤት መሆኑን ለመቀበል የስንቶቻችን ልብ ተዘጋጅቷል? ከዚያ ይልቅ እርኩስነቱን (በነገራችን ላይ የሰው ርኩስም ትንሽም የለም) ለማውጣትና ለማዋረድ ለምን ፈጠንን? ብለን ብንጠይቅ ስህተትን እንጂ፣ ጉድለትን እንጂ ሙላትን ማየት ጉዳያችን ስላልሆነ ነዋ፤ መልሱ። ሲዋረድ አይተን፤ ጸጉሩን ተቆርጦ የወህኒ ልብስ ለብሶ ተቆራምዶ ለማየት ከሚቃትተው እና አንሶና ኮስሶ በማየት አንጀታችንን ቅቤ ለማጠጣት ከቆረጠው ማንነታችን የሚነሳ ነው።
ብዙ ሰዎች የተፈጠረውን ነገር አይተው “ይገርማል እንዴት እርሱ ይህንን ይናገራል፣ እንዴት እርሷ ይህን ታደርጋለች “ ለማለት ይጣደፋሉ እንጂ፤ ራሳቸው የቆሙበትን ቦታ አያጤኑትም። አንዳንድ ሰው ከነበረበት ሁኔታ ተነስቶ ብዙ የማይታይበትንና የማይታወቅበትን ነገር ሊናገር ይችላል። ይህንን ታላላቆች የምንላቸው ሰዎች በንግግራቸው ሌሎችን ሰብረው ወይም ተተርጉሞባቸው አይተናል፤ ሰምተናል። ሌላው አስገራሚው ነገር አስተያየት ለመስጠት ማንም ሳይጋበዝ ለመናገር የብዙዎች መጣደፍ ነው። እዚህ ላይ አስተያየት አለኝ ብሎ ሰውን ለማዳን፣ ለማነጽና ለመገንባት ከመምጣት ይልቅ ሁሉም መፈንከቻ ድንጋዩን በአፉ ጎርሶና በብእሩ ጨብጦ “ለመግደል” ነው፤ የሚጣደፈው።
“በድንጋይ ተወግራ ትሙት” ሲባል፣ “-ትሙት” ለማለት እንጂ “ለምን እንዴት በምን አግባብ?” ብሎ ለመጠየቅ አይዘጋጁም። የሚዘጋጅም ልብ የለንም።
ከአጋጋዮቹ አንዱን አግኝታችሁ፣ እንዲህ ማድረጉ ለምን አስገረመህ? ብላችሁ ብትጠይቁት፣ በዚህ በዚህ ምክንያት ነው፤ ከማለት ይልቅ “እንዴት አባቱ ጭቃ ያቦካል፤ ወጥ ይረግጣል?” ብሎ ነው፤ በቁጣ የሚመልስላችሁ። ራሱን በአጥፊው ቦታ አስቀምጦ ለማየት ምንም አይፈልግም። እዚህ ላይ በተወቃሹ እድሜ ላለ ሰው እንደ ልጅ “ጭቃ ማቡካት”፣ እንደ ቀበጥ “ወጥ መርገጥ” ልክ ላይሆን ይችላል። ነገር ግን የሚከተሉትን ጥያቄዎች ማንሳት ወደምንፈልገው ትክክለኛ ግብ ያደርሰናልና መጠየቅ ተገቢ ነው።
በቅድሚያ ድርጊቱ የተከናወነበት አውድ ምን ይመስላል? እርሱ ተገኘበት በተባለውና ፊልሙ በተቀረጸበት ወቅት ካሜራ ማኑ ምን እየሰራ ነበረ ? ብሎ የሚጠይቅ ማን ነው። ለዚህም እንደክስና ጥፋት ማካተቻ፣ የቀረጸው ሰው መቼም ይህንን ለመቅረጽ ከገዳም የወጣ መነኩሴ፤ ዝማሬ አቋርጦ የወጣ የኳየር አባል ወይም ቅዳሴ ትቶ የወጣ ሊቀ መዘምራን አይሆንም። እዛው መሳቢያውና መጋፊያው ሰፈር ያለ አብሮ ሰራተኛ -ግብረ- አበር ነው፤ የሚሆነው።
አንዲት ከባሏ ጋር ከነበረች ወይም ካለች ሴት ጋር፣ አብረዋት የተኙት ሁሉ፣ እርሷ በአደባባይ ለክስ በቀረበች ቀን በድንጋይ ተወግራ ትሙት ሲባል፣ ነውራቸው የሚሸፈነው እርሷ ስትሞት ነውና ፣ ሊወግሯት ሾል ሾል ያሉና ቶሎ ከህይወት ወደሞት የሚያፈጥኑ ድንጋዮችን ይዘው ነው፤ ከተፍ ያሉት። “ከከሳሾቿ መካከል አንድም ሃጢያት የሌለበት ድንጋዩን አንስቶ ይውገራት”፣ ብሎ ዳኛው ሲናገር ግን ማንም ከነድንጋዩ ሊቆም አልቻለም። ልጂት ሆይ፣ ከሳሾችሽ የት አሉ?
ይህ ሰው፣ የተፈጠረችው ከእኛው ማህበረሰብ ነውና፤ አብሮ ሰሪዎቿ መጥተው እኔም ከእርሷ ጋር ወንጀሉን ፈጽሚያለሁ፤ ከእርሷ ጋር መስመር ጥሻለሁ፤ ከእርሷ ጋር ጭቃ አቡክቻለሁ፤ ለማለት ድፍረቱ ሊኖራቸው ይገባል። አንዳንዶች ስም ያለውን ሰው፤ በማሳነስና በመዝለፍ ክብር ያገኙ ሲመስላቸው እንዲህ ያደርጋሉ። አንዳንዶች ደግሞ ፍርፋሪ ለመለቃቀም የደግ ጊዜውን የአብሮነት ውሎና መታሰቢያ፣ የድምጽና የምስል “ቅጂ” ለክፉ ቀን መጠቀሚያ በማድረግ የኪሳቸውን ረሐብ ለመሙላት ይጠቀሙበታል። እንግዲህ ይህች ልጅ የደረሰባት ሰቆቃ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ሰፊው አድማጭ ደግሞ ከእውነታው ይልቅ ስሜት ዳኛው ነውና፤ “ትወገር” ሲባል “አብሮ ለመውገር” “ትሙት” ሲባል በተለያየ ምክንያት እንድትሞት የእጅ ማውጣት ሥነሥርዓት ላይ ሊካፈል ይችላል።
አሁን ይህ ምስል በማህበራዊ ሚዲያ የተለቀቀበትን ምክንያት ስታስቡት አውጭው፣ በኮሮና ሳቢያ ርቀታችሁን ጠብቁ የሚለውን አዋጅ የሚጻረር፣ እጅ ለእጅ አትጨባበጡ የሚለውን መመሪያ የሚጥስ፣ እጃችሁን በቻላችሁት መጠን ታጠቡ የሚለውን ደንብ በመተላለፍ፤ ማጨሻ ተቀባብላለች፤ ጢስ ተጋርታለች፣ ወዘተ…. ለማሰኘት የሚያመች ወቅት ላይ ሳሉ የማይደረግ አድርጋለች ለማሰኘት የወጣ ነው። በእርግጥ ምስሉ የተወሰደው በቅርቡ ነው ወይስ የኖረ ነው ? ብለን ለመጠየቅ ብዙዎቻችን አያስጨንቀንም። ከዚህ ይልቅ በየ “ሚሚ”ው ላይ፣ ቧልት በመልቀቅ ውግዘት ለማባባስ መትጋት ውስጥ ነው፤ የምንገባው። “እንደ ዛፍ ሲወድቁ ደግሞ ምሳር መብዛቱ” ያለ ነው ።
ይህንን ስህተት ተሰራበት የተባለ፣ የማጋለጫ “የማላገጫ” (ማለት ይቀላል) ቪዲዮ ወይም ምስል ለመልቀቅ ያሰቡበት እውነተኛ ምክንያት ትውልድን ለማዳንና ሌላው ከዚህ እንዲጠበቅ በማሰብ ነው ብንል እንኳን፣ የቀረበበት መንገድ ራስን ንፁህ ሌላውን ትንሽ ለማድረግ የተሰራ መሆኑ አያጠያይቅም። የውጤቱ መንስኤ ነገር ምንም ይሁን ምን- አሁን ይህ ሰው ከአቃላዮቹም በሉ ከአውራጆቹ ሰዎች ራሱን የሚሸሽግበት አቅምና የሚገዳደርበት ትከሻ የለውምና፤ ክፉ እጃቸው ላይ ወድቋል ወይም ጥለውታል። ዝና፣ ገንዘብ፣ ክብር፣ ተሰሚነትና ሥፍራ ተደራርበው፣ በዚህ በለጋ እድሜ ባለ ሰው ትከሻ ላይ ወደቁና እንደወጣበት ፈጣን ከፍታ፣ ገፍተው ከማማው ሊጥሉት ከጀሉ። አልቻለውምና ወደጠርዝ ገፉት። አሁንም ግን መልሶ ለመነሳት ጊዜ አለው፤ ተመልሶ ለመቆም ይችላል።
ከላይ እንዳልኩት በተጋጋለው እሣት የሆነ ወሬ ላይ ቤንዚን አከል ሌሎች ወሬዎችን በመጨማመር ማጋጋል እርሱን ጨርሶ ባያጠፋ ድርጅቱን ጥላሸት ሊቀባው ስለሚችል ተገቢውን ቦታ ሊነፍጉት ቢችሉ አይገርምም። ለዚህም አንደኛው ዘዴ ጨርሶውኑ የተሰራው ሥራ እርሱን፣ ስሙንና አመለካከቱን የማይወክል፣ በሚጠሉት ሰዎች የተቀናበረ የጥላቻ ዘመቻ አካል መሆኑን ማስረጃ አስደግፎ በማስረዳት መቋቋም ካልሆነም አዋጪው ዘዴ፣ ስህተትን በማመንና ከልብ ይቅርታ በመጠየቅ፣ ዳግመኛ በመሰል ማህበረሰብን በሚያስቀይም ተግባራት ላይ ላለመሳተፍ ወስኖ ለጥቂት ጊዜ ከህዝብ እይታ ራስን ገለል አድርጎ ቆይቶ መመለስ ነው።
እዚህ ላይ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ማንንም በጥፋቱ ለመውቀስና ወንጃዩን ለመኮነን፣ እንዲሁም የጠፋ ስምን ለማደስ የሚደረግ የጥብቅና ጥረት ሳይሆን፣ ሁልጊዜ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ስናልፍ ችግሩን አሸንፈን የምንወጣበትን መንገድ በመጠቆም ለተሻለ ማንነት መስራት የተገባ መሆኑንና ቡጢና ምክር ለሰጪው ቀላል ቢመስልም በገንቢ መልክ ማቅረቡ መልካም መሆኑን ለማሳየት ነው።
በዚህ መንገድ ውስጥ ሲያልፉ ላይመለሱ ያሸለቡ የታላላቅ ሰዎችን ታሪክ እዚህ ላይ ማውሳት የተገባ ነው፤ የሚሆነው። ሥም አጥፊው ባጠፋው ስም የሚጠቀመው የረባ ነገር ሳይኖር፣ ባለስሙን ቅስሙን በመስበር በኮናኝነት ራሱን መሰየሙ ሲገርም በሌላ ወገን ሥሙ የጠፋበት ሰው “አፈር ልሶ” የሚነሳበት ወቅት እንዳለ አውቆ በመጽናናት ፋንታ ራሱን ለአደጋ የሚያጋልጥበት አጋጣሚ መፈጠሩን ስታውቁ ልባችሁን መሪር ሐዘን ጠቅ ያደርገዋል።
የዌልስ ልዕልት በመባል የምትታወቀው እና በብዙ የበጎ አድራጎት ሥራዋ ሽፋን የተሰጣት፣ የልኡላኑ ዊሊያም እና ሐሪ እናት፣ ልእልት ዳያና ፕሪስተን፣ ከባሏ ከልኡል ቻርልስ ጋር የነበረው አለመግባባት ወደፍቺ ካመራ በኋላ፣ በነበራት ህይወት ላይ የአሳዳጅ ጋዜጠኞች፣ ክትትል ህይወቷን ምንኛ እንዳጎሳቆለውና በመጨረሻም ለሞት እንዳደረሳት እናውቃለን። ፈረንጆቹ፣ Paparazzi የሚሏቸው ጉድለት ብቻ፣ አፈንፋኝ “ጋዜጠኞች” መግቢያና መውጫዋን በመከታተል በፎቶ የተደገፈ ዘገባ እየሰሩ ስላስጨነቋት ነበረ፤ ከልኡሉ ጋብቻ ፍቺ በኋላ በይፋ ግንኙነት ካልጀመረችው ከግብጻዊው ባለሃብት ልጅ ከዶዲ ፋይድ ጋር በመሆን የሪትዝ ሆቴል ሥራአስኪያጅና ሾፌራቸው ከነበረው ሰው ጋር ሲጓዙ በገጠማቸው የመኪና አደጋ የሞተችው።
ይህች ሴት በንጉሳዊ ቤተሰብ ማንነቷ ወቅት በበርካታ የእንግሊዝ የቀድሞ ቅኝ ግዛት ወይም፣”የጋራ ንብረት ሀገሮች” ጉባኤ ላይ ንግስቲቱን በመወከል የምትገኝና የምትደመጥ፣ በድርቅና በሌሎች የተፈጥሮ አደጋዎች የተጎዱ ህጻናትንና ወጣቶችን በሚደግፉ የበጎ አድራጎት ሥራዎች ላይ በመሳተፍ የተመሰገነችና በስተመጨረሻም የጦር ቀጠና በነበሩ የዓለም ክፍሎች ፈንጂ በማምከን ሥራዎች ላይ ከተሰማሩ ድርጅቶች ጋር በጋራ ባከናወነቻቸው ተግባራት የተከበረ ሥም ያገኘች ነበረች።
ይሁንናም፣ ወደግል ህይወቷ ስንመጣ ለብሪታኒያ የዘውድ መንግስት ሁለተኛ ወራሽ (የልጅ ልጅ) የሆኑትን ልኡል ዊሊያምንና ልኡል ሐሪን ብትወልድምና በንጉሳውያኑ ብትመሰገንም በግሏ ደስተኛ አልነበረችም። ደስታ ያጣችባቸውን ምክንያቶች ፊት ለፊት ባታወጣውም ከደስታ ያራቃትን የልእልትነት ክብር፣ እንደባርነት በመቁጠር ለራሷ በነጻነት የህዝብን ኑሮ መርጣ ነበረ። ንጉሳውያኑ ግን፣ እንዲህ እንደዋዛ ውልቅ ብለሽ ወጥተሽ፣ “ነፃ” ኑሮ አንፈቅድልሽም ያሏት ይመስላል። እናም በእያንዳንዱ እንቅስቃሴዋ እግር በእግር እየተከታተሉ ተመለሽ፣ “አለዚያ ወዮልሽ” እንዳሏት ይነገራል። በዚህም አስጨናቂ ድርጊት፣ ምንም እንኳን፣ ከምክር ያለፈ ነገር አልተናገርናትም ብለው አበክረው ቢያስተባብሉም ንግስት ኤልሣቤጥ ክፉኛ ተብጠልጥለውበታል።
ይህችን ነገር ብትቋቋም ኖሮ ካለችበት ከፍ ያለ፣ ከንግስት እኩል የሆነ ስፍራ ሊጠብቃት ቢችልም፣ ያለፍቅርና ሰላም ልኖርበት የምችለው ከፍታ ይቅርብኝና በነጻነት እንደልቤ ደስ ብሎኝ ልኑር ብላ ብትመርጥም ከውስጣዊ ውጥረትና ከውጫዊው ጫና ጋር የተፈጠረው ወከባ፣ በ36 ዓመት፣ ለጋ ዘመኗ እንድትቀጠፍ ምክንያት ሆኗል። በብሪታኒያ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ ከ32 ሚሊዮን በላይ ተመልካች በቀጥታ በሐገር ውስጥ፣ በቴሌቪዥን የቀብሯን ሥነ-ሥርዓት መከታተሉ ግርምትን የፈጠረና በኣለም ዙሪያ ሌሎች ሚሊዮኖችም ተከታትለውታል ተብሎ ይታመናል። ልብ በሉ፤ ሞቷን እንጂ ሰላማዊና ነጻ ህይወቷን አይደለም።
አሁንም የእኛውን ሰው፣ “ጭቃ አቦካ ወይም ወጥ ረገጠ” ተብሎ በፈጠረው ይሁን ሊፈጥረው ነበረ፤ በተባለው “ጥፋት” ግን የግል ምርጫው ሲሞትና ሲለቀስለት ለማየት የከጀለ መንፈስ የለቅሶ ድግስ ያሰበ ይመስላል።
ይህንን ሐሳብ ወደሐገራዊ ርእሳችን ብናመጣው እኛን የጎዳና ሐገራችንን የማይጠቅም ሐሳብ አንሸራሸረ፤ ሰላማችንን አንሸዋረረ፤ አልተስማማንም የምንለውን ተቃዋሚ ሰው፣ ስናንቋሽሽ ዘር ማንዘሩ ድረስ የምንሄደው ነገር አለብን። ይህን አላቲ ሰው የወሎ ምድር እንዴት አበቀለችው፤ ብሎ መንዘርዘር ከሰውየው ሐሳብ ይልቅ ሰውየውን ማጥቃት አይሆንምን? የደቡብ መሬት ያንን ክፉ ሰው እንዴት አመነጨችው ብሎ መሳለቅስ ለምን ይጠቅማል? ሁልጊዜ የሚነሱ ሐሳቦችን በተጣራና በተመሰጠረ ለሰው ሊገባ በሚችል መንገድ ሞግቶ ማቅረብ እንጂ ሀሳብ በቀረበ ቁጥር “አባቱ ሸክላ ሰሪ የነበረ፣ እናቱ ሽሮ ቸርቻሪ የነበረች፤ በስካሩ ሰፈር የሚበጠብጥ አጎት ያለው ድኩም ሰው ነው፤” ብሎ ዘር ማንዘሩን ማጣጣል ምን ይረባናል? እኛው በታናሽነት ወድቀን እንቀር ይሆናል እንጂ።
ምድራችን በአባት እዳ ልጅና የልጅ ልጅ መከራው ያለጥፋቱ የሚቆጠርባት ሐገር ሆና ፣ ጥላቻችንን በሰፊ የፀብ ብረት ምጣድ ላይ በማመስ ማጋጋል እና ራስንም ማጋል ይገባናል፤ ወይስ በሰከነ መንፈስ በርደን በጨዋ መልክ ችግሮቻችንን ማብረድና መፍታት ይመረጣል።
ህግንም ሆነ ሥርዓትን ህዝብ እንዲተዳደርበት ለህዝቡ በሚበጅ መስመር ለመስራትና ለማሰራት ተሰራ እንጂ የማይለወጥ የማይገሰስ አምላካዊ አዋጅ አይደለም ። (የፋርስና ሜዶንን ህግ እንኳን ዘመን ሽሮታል) ሐገር ለማዳን፣ ለህዝብ ሰላምና ጤና ሲባል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንደሚወጣ ሁሉ፣ ለዚሁ ህዝብ መረጋጋት ሲባል ህዝብን በጊዜያዊ ህግ ማስተዳደርም ሌላኛው አማራጭ ነው። እኔ ያላቦካሁት ቂጣ አይጋገርም፤ እኔ ያልጠነሰስኩት ጠጅ አይጠጣም፤ ብሎ ድርቅ ማለት ነገር ከማጋጋል ውጭ ለህዝቡ ሰላም የሚፈይደው ነገር የለም።
ሁሉም ወገን እንዲረዳው የሚያስፈልገው ነገር የምትመሩንን የእኛን የህዝቦቻችሁን ደስታ ለማምጣት የምትተጉ ከሆነ በሰከነ መንፈስ ቁጭ ብላችሁ ተነጋገሩ። በእናንተ ፀብ ክፉኛ ተጋግላችሁ በጥባጭ እያሰማራችሁ ሰላማችንን ለማደፍረስና ደስታችንን ለመንጠቅ ከከጀላችሁ ፍጻሜያችሁ መልካም አይሆንም። ሰክናችሁ የሰከነ ሐሳብ ስጡን፤ ደፍርሳችሁ እያደፈረሳችሁ እኛን ድፍርስ ለማጠጣት አትሯሯጡ። መርጠን እንጫናችሁ እንጂ፤ መርጣችሁ አትጫኑብን፤ ሃላፊነትን ተቀበሉ እንጂ፤ ለስልጣን አታስፈራሩን።
አንዳንዶቻችሁን ሳስብ ሳቄ ይመጣል፤ ነግራችሁት መክራችሁት፤ አልሰማ ብሎ፣ ቀደም ሲል መንገዳችሁን ላይ ቆሞ ጠጠር ወርውሮባችሁ፤ መለስ ብላችሁ ስትሰነዝሩበት ከሥራችሁ ከወደቀ በኋላ መሬት ላይ እየተንደባለለ፤ “ከተነሳሁ ወዮልህ” እያለ እንደሚያስፈራራ አቅመቢስ የሰፈር ልጅ ትመስላላችሁ። እባካችሁ፣ እኛ ከሌለንበት ዝናብ አይወርድም፣ እኛ ከሌለንበት ስንዴው አይበቅልም፤ እኛ ካልገባንበት ማሩ እሺ ብሎ አይቆረጥም አትበሉን። ዝናቡም ከሰማይ ይወርዳል፤ ስንዴውም ከመሬት ይወጣል፤ ማሩም ከጫካው ቀፎ ይቆረጣል። እኛ ሰማይ ነን፤ እኛ ምድርን ነን፤ እኛ ጫካውን ነን፤ ወንዙን ነን አትበሉን። ስከኑና ነገር አስክኑ!!
አዲስ ዘመን ግንቦት15/2012
አገልጋይ ዮናታን አክሊሉ