ከዛሬ 73 ዓመት በፊት ነው በሸዋ ክፍለሃገር ጅባትና ሜጫ አውራጃ ነው የተወለዱት። ለትምህርት እንደደረሱ ቤተሰቦቻቸው ወደ አዲስ አበባ በመምጣታቸው የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በደጃዝማች በየነ መርዕድ ትምህርት ቤት ተማሩ። በዳግማዊ ምኒሊክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገብተውም እስከ 11ኛ ክፍል ተማሩ። 12ኛ ክፍል ሲደርሱ ግን እሳቸውና ሌሎች ከመላው አገሪቱ የሚገኙ ከፍተኛ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች ተመርጠው በሉዕል በዕደ ማርያም መሰናዶ ትምህርት ቤት ገቡ። የመሰናዶ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ በቀጥታ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብተው በታሪክ ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያዙ።
ከመመረቃቸው አንድ ዓመት በፊት ግን ከትምህርቱ ጎን ለጎን ብሔራዊ አገልግሎት በሚል አጋሮ ከተማ በሚገኝ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ለአስር ወራት አስተማሩ። ከምርቃት በኋላ ደግሞ በነቀምቴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለአንድ ዓመት ተኩል አስተማሩ። የጊምቢ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር ሆነውም እስከ 1968ዓ.ም አገልግለዋል። ይሁንና በዚያው ዓመት ላይ በተግባረዕድ ስር በነበረውና ወደ ኮተቤ በተዛወረው መምህራን ኮሌጅ የስራ ማስታወቂያ ይወጣና ተወዳድረው በማለፋቸው ኑራቸውንም ሆነ ስራቸውን በአዲስ አበባ አደረጉ።
እኚሁ የዛሬው የዘመን እንግዳችን በ1970 ዓ.ም በመምህራን ጉባኤ ተመርጠው የኮሌጁ ምክትል የአካዳሚና የአስተዳደር ዲን ሆነው ለሰባት ዓመታት ለማገልገልም ችለዋል። በተባበሩት መንግስታት የልማት ድርጅት አማካኝነት የተመቻቸውን የውጭ የትምህርት እድል ውድድር አሸንፈው በአሜሪካው አሪዞና ዩኒቨርሲቲ በትምህርት አስተዳደርና አመራር ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ያዙ። አዲስ አበባ ከተመለሱ በኋላ ኮተቤ መምሀራን ኮሌጅ ከፍተኛ ትምህርት ኮምሽን ስር በነበረው የስኮላርሽፕና የውጭ ጉኑኝነት መምሪያ ሃላፊ ሆነው ተሾሙ። አራት ዓመት ካገለገሉ በኋላ ግን በወቅቱ የትምህርት ኮምሽን ከነበሩት ከወይዘሮ ገነት ዘውዴ ጋር ባለመስማማታቸው በገዛ ፍቃዳቸው ስራቸውን ለመልቀቅ ተገደዱ። ለቀውት የመጡት የሃላፊነት ቦታ ሳያሳሳቸው ተመልሰው በኮተቤ መምህራን ኮሌጅ ውስጥ መምህር ሆነው መስራታቸውን ቀጠሉ፡
በማስተማር ላይ ሳሉ ግን በአጋጣሚ በጀርመን የተማሪዎች አታሼ መሆን ለሚችሉ መምህራን ማስታወቂያ ይወጣና ተወዳድረው ያሸንፋሉ። በዚያ መሰረትም በጀርመንና በሌሎች ጎረቤት አገራት በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎችን ሁኔታ በመከታተል መብቶቻቸው እንዲጠበቁ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል ። ይሁንና አሁንም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ ካሉ ሃላፊዎች ጋር በተማሪዎችና በሌሎችም ፖለቲካዊ ጉዳዮች መስማማት ባለመቻላቸው ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ ተደረጉ። በወቅቱ ታዲያ ጥገኝነት ጠይቀው እዛው ጀርመን የሚቆዩበት እድል ቢኖርም ሳይማር ያስተማረኝ ህዝብና አገር ትቼ እኔ በምቾት አልኖርም ብለው ወደ አገራቸው ተመለሱ። ከዚያ ወዲህም አገሪቱን የሚያስተታድረው መንግስት አካሄድ አልመች ቢላቸውና የሚሰራውን ግፍ እያዩ ማለፍ አእምሯቸው ሊቀበለው ባለመቻሉ በይፋ የፖለቲካውን መስመር ተቀላቀሉ። ኢዴፓና ቅንጅት ፓርቲዎች ውስጥ ለረጅም ዓመታት በሃላፊነት ሰሩ።
ከ1997 ዓ.ም ምርጫ ጋር ተያይዞም ለሁለት ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ የመታሰር እጣ ወድቆባቸውም ነበር። ከእስር ከተፈቱ በኋላም ከትግል ጓዶቻቸው ጋር በመሆን አንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲን አቋቁሙ። ፓርቲው በእነትግስቱ አወሉ እጅ ተላልፎ እስከሚሰጥበት ጊዜ ድርስ ሥርዓቱን መቃወማቸውን ቀጠሉ። ከፓርቲው መፍረስ በኋላ ግን ፖለቲካውን እግፍ አድርገው ተዉ። በቅርቡ ደግሞ ኢዜማ ሲመሰረት ደግሞ በአገሪቱ በተፈጠረው ምቹ የፖለቲካ ምህዳር ምክንያት የተዉቱን ፖለቲካውን ለመቀላቀል ወደዱ። በአሁኑ ወቅትም በፓርቲው አባል ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ። ከዛሬው የዘመን እንግዳችን ከአቶ አስራት ጣሴ ጋር በህይወታቸው ዙሪያና በተለየዩ አገራዊ ፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገናል። እንደሚከተለው ይቀርባል።
አዲስ ዘመን፡- በትምህርት ኮምሽን ውስጥ በሚሰሩበት ጊዜ ከወይዘሮ ገነት ዘውዴ ጋር ያጋጫችሁ ምክንያት ምን ነበር ?
አቶ አስራት፡- ከዚያ በፊት ግን የዘመን እንግዳ አድርጋችሁ ስላቀረባችሁኝ ማመስገን እወዳለሁ። ወደጠየቅሽኝ ጥያቄ ስመልስ ፣ ቀደም ብሎም ቢሆን ከወይዘሮ ገነት ጋር የምትዋወቅ ቢሆንም የግል ፀብ ግን አልነበረንም። ግጭቱ የመነጨው በደርግ ጊዜ የተለያየ ደረጃ የነበራቸው የኢትዮጵያ ወታደሮች ወደ ሶሻሊስት አገራት ሄደው ይማሩ ነበር። ኢህአዴግ ከገባ በኋላ ግን ለወይዘሮ ገነት ዘውዴ ከመከላከያ ሚኒስቴር በተለይ ራሺያ ያሉ ተማሪዎች ከዚህ በኋላ የኢትዮጵያ መንግስት የማያውቃቸው ስለሆነ የትምህርት እድላቸው እንዲቋረጥ የሚል ደብዳቤ ይደርሳትና እኔ እንዳስፈፅም ትልክልኛለች። እኔ ግን በሃሳቡ ስላልተስማማሁ ቀጠሮ ይዤ ቢሮዋ ሄድኩኝ። እነዚህ ተማሪዎች ከፊሎቹ በዚያው ዓመት የሚጨርሱ ናቸው። ቀሪዎች ጥቂት ጊዜ ይቀራቸው ነበር። ይህ በሆነበት ሁኔታ ተማሪዎቹ ትምህርታቸውን እንዲያቋርጡ ማድረግ ተገቢ አይደለም ስል ተቃወምኩ። ደግሞም በወቅቱ የኢትዮጵያ መንግስት የሥርዓት ለውጥ አደረገ እንጂ የዜግነት ለውጥ አላደረገም። እነዚህ ሰዎች ኢትዮጵያውያን ናቸው። በውትድርና አገልግለው የሄዱ ስለሆነም ይሄ የትምህርት እድል መሰረዝ የለበትም ብዬ ተከራከርኩ።
የሚገርምሽ የሚሰጧቸው ጥቅማጥቅሞች ሁሉ እንዲቋረጥ ተደርጎ ነበር። ይህ አልበቃ ብሎ ትምህርት እድል ማቆም ትክክል አይደለም ብዬ ወይዘሮ ገነትን ሞገትኩ። ልንግበባ ግን አልቻልም። በመሆኑም ራስሽ አድርጊው እንጂ እኔ አላደርገውም ብዬ በገዛ ፍቃዴ ስራዬን ለቀቅኩኝ። እናም በቀጥታ ወደ መምህራን ኮሌጅ ተመልሰኩና ከሃላፊነት ወደ ማስተማር ስራ ገባሁ።
ኮተቤ እያስተማርኩኝ እያለሁ መቀመጫው በጀርመን አገር ሆኖ የሩሜኒያ ፣ የቡልጋሪያ፣ የቼክ ስሎቫኪያ፣ ሃንጋሪ ያሉ የኢትዮጵያ ተማሪዎች አታሼ ስራ በካውንስል ማዕረግ መወዳደር ለሚፈልጉ ማስታወቂያ ይወጣል። ማስታወቂያው ሳየው ሁለት ልብ ውስጥ ሆንኩ ። ምክንያቱም ከወይዘሮ ገነት ጋር በመጣላቴ እንድወዳደር አትፈቅድልኝም የሚል ስጋት ስለነበረኝ ነው። ግን ለማንኛውም ልወዳደር ብዬ ተወዳደርኩ። እንደፈራሁትም «ይህ ኢሰፓ መወዳደር አይችልም» ብላ ተከላከለች። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን አንድም ጊዜ የኢሰፓ አባል ሆኜ አላውቅም ነበር። በወቅቱ ታዲያ አብረዋት የሚሰሩ ሃላፊዎች በተለይም በእኔ ቦታ የተመደበው ሰው እውነታውን ያውቁ ኖሮ «አስራት ኢሰፓ አልነበረም፤ እንዳውም የታሰረው በኢህአፓነት ነው» ብለው አስረዷት።
አዲስ ዘመን፡- በደርግ ጊዜ ታስረው ነበር ማለት ነው?
አቶ አስራት፡- አዎ፤ ግን ለአጭር ጊዜ ነው የታሰርኩት ፣ ወዲያው ተፈታሁ። ይሁንና አብረውኝ ከታሰርን ስድስት መምህራን መካከል አንዱ ተገድሎ እዛው ቀርቶ ነበር። እናም እነዚያ ሰዎች ወይዘሮ ገነትን አሳመኗትና እንድወዳደር ፈቀደችልኝ። በዚያ መሰረት ተወዳድሬ በማሸነፌ በጀርመን የኢትዮጵያ ተማሪዎች አታሼ ሆኜ እንድሄድ ተደረገ። ይህ የሆነው እንግዲህ በ1986 ዓ.ም መጀመሪያ አካባቢ ነው። የትምህርት አታሼ ሆኜ በማገልገል ላይ ሳለሁ በዚያን ወቅት የነበረው አምባሳደር ብርሃኑ ወልደተንሳይ ከዚህ ቀደም አውቀው ስለነበር እዛው ኤምባሲ ውስጥ እንድኖር ፈቀደልኝ። እየሰራን እያለ ግን ችግር ተፈጠረና ከውጭ ጉዳይ ሃላፊዎች ጋር መግባባት አቃተን።
አዲስ ዘመን፡- ምንድን ነበር ችግሩ?
አቶ አስራት፡- ቀደም ብዬ በጠቀስኩልሽ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ብዙ ችግር ይደርስባቸው ነበር። የችግሩ ምንጭ ደግሞ የአገሬው መንግስት የሚሰጣቸው ገንዘብ የማይበቃቸው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ለፓስፖርት ማሳደሻም ሆነ ለሌሎች አገልግሎቶች የሚውል ገንዘብ ማግኘት አለመቻላቸው ነው። እኔም በየሃገሩ ተዛዙሬ ስጎበኝ ችግሩ አሳማኝ ሆኖ አገኘሁት። በተለይም በቡልጋሪያ የነበረው ችግር በጣም የከፋና ልጆቹ መታወቂያቸውን ባለማሳደሳቸው ክሊኒክ እንኳን መሄድ አይችሉም ነበር። የነበረውን ሁኔታ ለአምባሳደሩ በፅሁፍ አቀረብኩለትለትና እኔ ባቀረብኩት ማስታወሻ መሰረት ፈቀደ። ተማሪዎቹ መታወቂያቸው ከኤምባሲው ወጪ ተደርጎ ታደሰላቸው። የሚያስፈልጋቸው ሁሉ ተሟልቶላቸው ከችግራቸው ወጡ። በዚያን ወቅት ወጪ የተደረገው ገንዘቡ መወራረድ ስለነበረበት ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይላካል። የተደረገው ድርጊት ልክ አይደለም በሚል ለተማሪዎች የተከፈለው ገንዘብ ከአስራት ደመወዝ ይቀነስና ለመንግስት ገቢ ይደረግ የሚል ደብዳቤ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለኤምባሲው ይላካል። የሚገርምሽ ይህ ደብዳቤ አሁንም አለ። በወቅቱ የነበረው አምባሳደር ግን «እኔን አስፈቅዶ የተደረገ በመሆኑ መቆረጥ ካለበት ከአስራት ላይ ሳይሆን ከእኔ ደመወዝ ነው» በማለት ከአቶ ስዩም መስፍን ጋር ተጨቃጨቀ። በዚህ ምክንያት ሳይቆረጥብኝ ቀረ።
ይህ ጉዳይ በዚህ እንዳለ ሌላ ችግር ደግሞ ተፈጠረ። ይኸውም ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያምና የግርማ ወልደጊዮርጊስ ልጅ ወይዘሮ ገነት ግርማ ለኢትዮጵያውያን ንግግር ለማድረግ በወቅቱ የኤምባሲያችን መቀመጫ በነበረችው ቦን ከተማ ይመጣሉና እነሱ ንግግር በሚያደርጉበት መድረክ ለመሳተፍ ከኤምባሲው ሁለት ሰዎች ተመረጥን። እነዚህ ሰዎች የሚያደርጉትን ንግግር አዳምጣችሁ አስተባብሉ የሚል ትዕዛዝ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይደርሰናል። በወቅቱ ታዲያ እነዚህ ሰዎች የታወቁና የተማሩ ሆነው ሳለ እንዴት ብዬ ነው በትዕዛዝ ንግግራቸውን የማስተባብለው? ምንአልባት የተሳሳቱት ካለ ማስታወሻ ይዤ ማስተባበል እችላለሁ እንጂ አላደርገውም አልኩኝ። አብሮኝ የተመደበው ሰው ልንባረር እንችላለን የሚል ግምት ስለነረው በዚያ መድረክ ላይ ሲገኝ እኔ ግን አልሄድም ብዬ ቀረሁ። በነገራችን ላይ ቀደም ሲል አምባሳደሩ የአባልነት ጥያቄ አቅርቦልኝ ነበር። አባል ከሆንኩኝ የአፍሪካ አገራት ውስጥ አምባሳደር እንደሚያደርጉኝ ነግሮኝም ነበር። እኔ ግን የኢህዴግ አባል የምሆነው ከውስጤ ሲመነጭ ነው እንጂ በሹመት ወይም ደግሞ በማላለል አልሆንም አልኩት። እናም እነዚህ ሁኔታዎች ተጠራቀሙ። በተመደብኩበት ስራ ላይ ግን በታማኝነት በተለይ ተማሪዎችን በምጎበኝበት ጊዜ ያጋጠማቸውን ሁሉ ችግር እንዲፈቱ ሰርቻለሁ። እናም ይህን አመለካከቴን ሲረዱ «እሱ በጭራሽ የአብዮታዊ ዴሞክራሲን መንገድ አያራምድም፤ የእኛን መስመር ተቃዋሚ ነው» የሚል መረጃ ሪፖርት ተደረገብኝ።
በመሰረቱ እኔ የማደርገው የማምንበት እንጂ የምከተለው ተቃዋሚ ስለሆንኩ አልነበረም። ስለዚህ እዛ መቀጠል እንደሌለብኝ ተወስኖ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአስተዳደር ሃላፊ ኤምባሲው ድረስ መጣና ብዙ ውይይት አደረግን። «አንተ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አታራምድም» ሲለኝ፤ ትክክል ነው፤ እኔ አባል አይደለሁም፤ የምከተለውም መስመር የለም አልኩት። ወደ ጀርመን የመጣሁት በሙያዬ ነው፤ እኔ የትምህርት ሰው ነኝ። በመሆኑም ከእኔ ይህንን መጠበቅ ልክ አይደለም አልኩት። እንግዲያውስ የፖለቲካ ስራ የማትሰራልን ከሆነ ለትምህርት ስራ ብቻ ይህንን ደመወዝ አንከፍልም እዚህ አናስቀምጥም አለና ተመልሶ ሄደ። በወቅቱ እንደሚያባርረሩኝ አውቄ ነበር፤ አምባሳደሩም በግልፅ ነግሮኝ ነበር። እኔ ግን ወደ አገሬ መመለስ ችግር አይሆንብኝም ብዬ አልኩት። እንደተባለውም ተከታትሎ ደብዳቤው መጣ።
በወቅቱ ጥገኝነት ጠይቄ እዛው መኖር የምችልበት ምቹ እድል ቢኖርም፤ ይህ ሥርዓት እስከሚወድቅ ድረስ ከአገሬ ወጥቼ መኖር ስለማልፈልግ ለመመለስ ወሰንኩ። በሌላ በኩል ግን ልጆቼ እዚህ ይማሩበት ከነበሩበት ደህና ትምህርት ቤት አስወጥቼ ጀርመንኛ ካስተማርኩ በኋላ እንደገና መመለሱ ከበደኝ። በመሆኑም ከአምባሳደሩ ጋር ተነጋግረን ልጆቼ ነፃ የትምህርት እድል አገኙልኝ። እኔና ባለቤቴ ትንሹን ልጃችን ይዘን ወደ አገራችን ተመለስን። ከመመለሴ በፊት ግን አንዳንድ ቤተሰቦቼን ያስጨንቋቸው ስለነበር ከመጣሁ ልታሰር እንድምችል ይነግሩኝ ነበር። እኔ ግን ከአገሬ ህዝብ ተለይቶ ከመኖር ቢያስሩኝ ይሻላል ብዬ ተመለስኩ። ግን ምንም የደረሰብኝ ነገር አልነበረም።
አዲስ ዘመን፡- ከዚያ ወዲህ የመንግስት ስራን ለቀቁ ማለት ነው?
አቶ አስራት፡- አይደለም፤ ከጀርመን እንደመጣሁ በቀጥታ የሄድኩት ወደ ኮተቤ መምህራን ኮሌጅ ነው። ባመለከትኩት መሰረት የማስተማር ስራዬን ቀጠልኩ። ባለቤቴ ትሰራበት በነበረው መስሪያ ቤት ግን በቦታዋ ሌላ ሰው ተክተው ስለነበር ስራዋን መቀጠል አልቻለችም። በኋላም ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሄጄ ሚኒስትር ዴኤታውን አነጋገርኩትና ባለቤቴ ወደ ስራዋ እንድትመለስ አደረገልኝ።
አዲስ ዘመን፡- በይፋ ወደ ተቃውሞ ጎራ የገቡበት አጋጣሚ ምን ነበር ?
አቶ አስራት፡- እንደነገርኩሽ በአገለገልኩባቸው ተቋማት በተለይ በኤምባሲው ሲሰራ የነበረውን ድርጊት እመለከት ስለነበር ሁኔታው ሁሉ አንገሸግሾኝ ነበር። እርግጥ ቀደም ብሎ ህገመንግስቱ ሲፀድቅም በኤምባሲ ውስጥ በነበረው ውይይት ላይ በተለይ አንቀፅ 39ኝ ተቃውሜ ነበር። ይህች ጉዳይ እንደ ጥቁር ነጥብ ተይዛብኝ ነበር። ለነገሩ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለሁ ጀምሮ የነቃ የፖለቲካ ተሳትፎ ነበረኝ። ዩኒቨርሲቲ በነበርኩበት ጊዜ እነ ጥላሁን ግዛውና ዶክተር ነጋሶ ጋር የክፍል ጓደኞቼ ነበሩና ከእነሱ ጋር እንወያይ ነበር። ያ መሰረት ስለነበረኝ ይህን ሥርዓት መታገል አለብኝ ብዬ ወሰንኩ። በዚያ መሰረትም ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢዴፓ ገባሁ። ኢዴፓ በገባሁበት ዓመት የስራ አስፈፃሚ ሆኜ ተመረጥኩኝ። በመቀጠልም የቅንጅት ምስረታ መጣ። ከተዋሃዱ አራት ፓርቲዎች አንዳንድ ሰው እንዲመረጥ ይደረግና ከኢዴፓ እኔ ተመረጥኩ። በዚያ መሰረት በ1997 ዓ.ም ምርጫ በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 16 ተወዳድሬ አሸነፍኩኝ። ይሁንና ልክ እንደሌሎቹ ሁሉ ፓርላማ አልገባሁም ነበር። ምክንያቱም አንቺም ሆነ አንባቢዎች ታውቁታላችሁ ብዬ ስለምገምት ወደ እዛ ዝርዝር ውስጥ መግባት አልፈልግም።
ከምርጫው በኋላ ሌሎች የቅንጅት ስራ አስፈፃሚ አባላት ሲታሰሩ እኔ ግን አልታሰርኩም ነበር። ይሁንና እነሱ ሲታሰሩ ሃላፊነቱን ተረክቦ የሚሰራ ሰው በማስፈጉ ሃላፊነት ተረክቤ ከተወሰኑ ሰዎች ጋር በህቡ የቅንጅት እንቅስቃሴ መምራት ጀመርኩ። በዚያ ጊዜ ያስሩኛል የሚል ስጋት ስለነበረኝ ከቤት ወጥቼ ተደብቄ ነበር የምኖረው። ብዙም ሳልቆይ ግን ኢፍቲን የምትባል ጋዜጣ ቅንጅትን በህቡ ከሚመሩት ሰዎች አንዱ መሆኔን ስሜን ጠቅሳ አወጣች። በሌላውም እትሟም ደግማ ስሜን አወጣች። በዚህ ምክንያት ደህንነቶች ይከታተሉኝ ጀመር። አንድ ቀን ከአንድ ሰው ጋር ቦሌ አካባቢ በሚገኝ የግል ሆስፒታል ውስጥ ለመነጋገር ቀጠሮ ይዘን ተገናኘን። ለካ ደህንነቶች ሲከታተሉን ነበርና መጥተው ማንነቴን አጣሩ። እኔ መሆኔን ሲያውቁ እዛው ሆስፒታሉ ጊቢ ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ ደበደቡኝ። ከዚያ ማዕከላዊና ቃሊቲ ለሁለት ዓመት በሚጠጋ ጊዜ ታሰርኩኝ። ከ22 ወራት የእስር ቆይታ በኋላ እነ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ከመፈታቸው አስቀድሞ ያለምንም ይቅርታ በነፃ እንድፈታ ተደረገ። ከዚያ በኋላ ወጥተን አንድነትን መሰረትን ብርቱካን ሚደቅሳ ሊቀመንበር ሆና ስትመረጥ እኔ ዋና ፃሃፊ ሆኜ ተመረጥኩኝ። አንድነት ውስጥ በ2007 ዓ.ም በነ ትዕግቱ አወሉ እስከ ተቀማንበት ድረስ እንቅስቃሴ ስናደግ ነበር። ከዚያ በኋላ ግን የፖለቲካ እንቅስቃሴን ሙሉ ለሙሉ አቁሜ ጥሩ የእረፍት ጊዜ ማሳለፍ ቻልኩ።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ታዲያ በምን ሁኔታ ውስጥ ነው ያሉት?
አቶ አስራት፡- በፖለቲካው ረገድ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የየትኛውም ድርጅት አባል አልነበርኩም። ነገር ግን የተለየዩ ፖለቲካ አስተያየቶችን በመገናኛ ብዙሃንም ሆነ በመፃሃፍ ላይ እሳተፍ ነበር። ኢዜማ ሲመሰረት ግን ፓርቲውን ተቀላቅያለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ፖለቲካውን እርግፍ አድርገው ከተውት በኋላ ዳግመኛ ለመሳተፍ ምን የተለየ ምክንያት አጋጠሞት ?
አቶ አስራት፡- እንዳልሽው ፖለቲካው ይበቃኛል ብዬ ነበር የተቀመጥኩት። ነገር ግን ከፓርቲው አመራሮች እንዳግዝ በቀረብልኝ ጥሪ መሰረት በዚህ ወሳኝ በሆነ ሰዓት የአቅሜን ለመርዳት ስል ፓርቲውን ተቀላቅያለሁ። ምክንያቱም ወቅቱ ፈተናው የበዛበት ጊዜ ነው። ማንም በእድሜ ትልቅ ነኝ፤ ጤናዬ ተናግቷል ብሎ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ወደ ጎን የሚባልበት ጊዜ አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- ወቅታዊው የፖለቲካ ሁኔታ የሚያሰራ ነው ብለው ያምናሉ?
አቶ አስራት፡- እኔማ በሃይለስላሴ ዘመን ቢሆን በተለይ በመሬት ስሪት ጥያቄ የረሃቡ ሁኔታን እንዲህም የፊውዳል ሥርዓቱ ራሱን ባለመቻሉ ያስከተለውን ችግር ጠንቅቄ አውቀዋለው። በደርግም ሥርዓት ባሃላፊነት የኖርኩበት ታስሬም የተፈታሁበት በመሆኑ ምን አይነት ግፍ ይሰራ እንደነበር አይቻለሁ። ባለፉት 27 ዓመታተ በህወሃት ኢህአዴግ የተመሰረተው የፖለቲካ ሥርዓት ሁሉም ህዝብ እንደሚያውቀው የተበላሸ ነበር። አብዮታዊ ዴሞክራሲ ማለት የአንድን ፓርቲ አምባገነንነት ለሁልጊዜ ለማቆየት ያለመ ሥርዓት መሆኑን አውቃለሁ። በተለይ ህውሓት መድብለ ፓርቲ ሥርዓት አለኝ የሚለው ለማተለያ እንጂ መሬት ላይ የወረደ እንዳልነበር ይታወቃል። ስለዚህ እነዚያን ሥርዓቶች ጠንቅቄ ስለማውቅ እኔ የአሁኑ የለውጥ እንቅስቃሴ የምመዝነው ከአሜሪካ ወይም ከጀርመን ሥርዓት ጋር ሳይሆን ካሳለፍናቸው አስቸጋሪ የመንግስት ሥርዓቶች ጋር ነው።
ከዚህ አንፃር እንግዲህ ካለፈው ሁለት ዓመት ወዲህ የመጣው ለውጥ ተስፋ ሰጪ እንዳውም በተጨባጭ ኢትዮጵያዊነት ጎልቶ የተቀነቀነበት ዘመን ነው። የእነ አቶ ለማ መገርሳ «ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው» ንግግር የነ ዶክተር አብይ ኢትዮጵያ ታማለች መዳን አለባት ብለው በቁርጠኝነት የፈፀሟቸውን ተግባራት ከእነዚያ አስቃቂ ጊዜያት ጋር ላወዳድረው የምችለው አይደለም። ለእኔ የኢትዮጵያን እስር ቤት ከፍቶ ከሰቆቃ የእድሜ ልክ የተፈረደባቸው መፈታት፣ የአርበኞች ግንቦት 7 ና የሌሎች ፖለቲካ አባላት ወደ አገራችው መምጣት በቀላሉ የሚታይ ነገር አይደለም። ያለፉት ሁለት ዓመታት እነዚህ ሰዎች በአገራቸው ጉዳይ ላይ እንዲሳተፉ እድል የተሰጠበት ነው። እኛም ከተቃዋሚ ወደ ተፎካካሪ መባል የቻልነው በዚህ ዘመን ነው።
ደግሞስ «ኑ፤ እንምከር» ተብሎ መንግስት እንደ አንድ ህዝብ ለአገር የቆመበት ጊዜ የቱ ነው? መቼም በእነዚህ ሁለት ዓመታት የተፈፀሙትን መልካም ነገሮች በሙሉ መዘርዘር ለኢትዮጵያ ህዝብ ‘ለቀባሪው አረዱት!’ ነው የሚሆንብኝ። በመሆኑም ይህ ለውጥ እንዲደናቀፍ አልፈልግም። ይህ በጎ ጅማሮ ነው። በእኔ አስተሳሰብ ይህንን ሥርዓት ስህተቱ እየተነገረው፤ እንዲታረም እየተደረገና ከተለያዩ ፅንፈኞች ተጠብቆ እንዲቆይ መደረግ አለበት። ምክንያቱም የኢትዮጵያን ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል ብሩህ ተስፋ ያየሁበት ስለሆነ ነው። በ ነገራችን ላይ የአሁኑን ሥርዓት ለመጣል መታገል ማለት ሥርዓቱ ሲወድቅ ከመሬት የሚነሳ ነገር እንዳይኖር ማድረግ ማለት ነው። ስለዚህ ቢቻል ትከሻችንንም ጠጋ አድርገን የዚህን የለውጥ አራማጆችን ችግር መሸከም ይገባናል። ይህ ማለት ግን ብልፅግናን የፈለገውን ይስራ፤ ፀረ ዴሞክራሲያዊ ይሁን ማለት አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- አንዳንድ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ግን ምርጫን ማራዘም ማለት ዴሞክራሲያዊ ባልሆነ መንገድ አሁን ያለውን መንግስት እድሜ ማራዘም ነው ሲሉ ይሞግታሉ?
አቶ አስራት፡- በእኔ እይታ ብልፅግና በጭራሽ የአምባገነንት አዝማሚያ አለው ብዬ አላምንም። የአምባገነንነት መንገድ እኮ ይሄ አይደለም። የአምባገነኖች መንገድ የመገዳደል እንጂ የመነጋገር አይደለም። ማንኛው የተቃዋሚ መሪ ዛሬ ከጠቅላይ ሚኒስትሩም ከየትኛውም የመንግስት አካል ጋር ቁጭ ብለው መወያየት የሚችሉበት እድል ተፈጥሯል። ይልቁኑ እንዳውም ይህንን መንግስት ሰዉ እያማረረ ያለው ቁንጥጫ አይጠቀምም፤ ሃይል አይጠቀምም በሚል ነው። በተለይ ብዙ ህዝብ ሲፈናቀል፣ ሞት ሲደርስበት፣ ተከበቡኩኝ ባለ አንድ ግለሰብ ምክንያት 86 ሰዎች ሲያልቁ ፣ በዚሁ ሁሉ ማሃል እርምጃ አልተወሰደም በሚል ነው ቅሬታ ሲቀርብ የነበረው። እኔ ይህ ሥርዓት ሲከሰስ የማውቀው በዚያ ነው። እኔም አንዳንድ ጊዜ ሆድ ይብሰኝና እርምጃ መወሰድ አለበት እላለሁ። ነገር ግን አሁን ካለው መልካም ነገር ጋር የሚነፃፀር አይደለም። በእኔ እምነት ያለውን መልካም ነገር ማየት የማይችሉ የታወሩ ብቻ ናቸው። በክፋት የታጀለ ሰው ነው።
ዛሬ ኮቪድ 19 በዓለም ላይ ወደ አምስት ሚሊዮን ህዝብ ይዟል፤ 400 ሺ የሚደርሱ ሰዎችን ገድሏል። ይህ በሽታ እያለ ምርጫ ለማካሄድ ይቅርና ህዝቡ በሰላም ወጥቶ መግባትና ስራ መስራት ባልቻለበት፤ ትምህርት ቤቶች በተዘጉበት ሁኔታ፣ ፋብሪካዎች በሙሉ አቅማቸው በማይሰሩበት ሰዓት እንዴት አድርጎ ነው ምርጫ ማካሄድ የሚቻለው? ምርጫ ከሰው ህይወት የሚበልጥ ነገር ነው እንዴ? በእርግጥ የሚያሾፉና የሚቀልዱ ሰዎች እንዳሉ አውቃለሁ። ኢትዮጵያ ውስጥ አልተስፋፋም በማለት በህዝብና በአገር ችግር ላይ የሚሳለቁም መኖራቸውን እረዳለሁ። ምንአልባት እኮ ምርጫ የምናካሂድበት ወቅት ኮቪድ 19 ከፍ ብሎ የሚነሳበት ሊሆን ይችላል። ከዚህ ጋር ተያይዞ አንድ ጥሩ ምሳሌ ላንሳልሽ፤ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ በሩሲያ የኮቪድ ተጠቂዎች ጥቂት ነበሩ። ዛሬ በአጭር ጊዜ አሜሪካ ላይ ልትደርስ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ተሰልፋለች። እናም ምርጫ መካሄድ አለበት ለሚሉ ግለሰቦች በህዝብ ጤንነትና ህይወት ላይ መቀለድ አይቻልም የሚል መልዕክት ማስተላለፍ እወዳለሁ።
አዲስ ዘመን፡- በህግ ባለሙያዎች የቀረበው የህገመንግስት ትርጓሜን ጉዳይ ህገመንግስቱን መጣስ ነው የሚሉም አሉ፤ በዚህ ላይ ምን አስተያየት አሎት?
አቶ አስራት፡- ይህንን የሚሉት ሰዎች ራሳቸው ህገ መንግስቱን ሲጥሱ እኮ በተደጋጋሚ ተመልክተናል። ለምሳሌ በኢትዮጵያ ህገመንግስት አንቀፅ 103 ላይ በየአስር ዓመቱ የህዝብ ቆጠራ መካሄድ እንዳለበት ይደነግጋል። እንደ አጋጣሚ ሆኖ የህዝብ ቆጠራውና የ 1997ቱ ምርጫ አንድ ላይ በመዋሉ ህውሃት /ኢህአዴጎች ሁለቱንም አንድ ላይ ማካሄድ አይቻልም በማለት የህዝብ
ቆጠራውን ዘለውታል። ያን ሲያደርጉ እኮ የህግ መንግስት ትርጉም አልጠየቁበትም። ለነገሩ አምባገነን ስለሆኑ ማን ይጠይቀናል፤ ማን ይናገረናል? በሚል እንደሆነ ይታወቃል።
ዛሬ ደግሞ በኮቪድ በሽታ ዓለም እንዲህ በመላው ዓለም ከ50 በላይ አገሮች የተለያዩ ምርጫዎች ያሸጋገሩበት ወቅት ነው። እነዚህ ሰዎች ናቸው ታዲያ «ህገመንግስት ተሸረሸረ» ብለው የሚጮሁት!።
ሌላ አንድ ምሳሌ ላንሳልሽ አቶ ቃሲም ፊጤ የሚባል የኦሮምያ ክልል ተወካይ የፓርላማ አባል የነበረ አንድ ወቅት በአቶ መለስ ዜናዊ ትዕዛዝ ያለመከስስ መብቱ እንዲነሳ ተጠይቆ ነበር። ፓርላማው በሆነ አጋጣሚ ሳይሰበሰብ ይቅርና ያለመከስስ መብታቸው ሳይነሳ ይቀራል። በማግስቱ ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፓርላማው ተሰብስቦ እንዲነሳ አስደረጉ። ይህንን ነው እንግዲህ ህገመንግስት ማክበር የሚሉት! ሌላም አንድ ምሳሌ ልጨምርልሽ አቶ አባ ዱላ ገመዳ ፕሬዚዳንት ሆነው ተመርጠው ሲመጡ አቶ መለስ ግን ሂዱና ተመልሳችሁ ሌላ ምረጡ ብሎ ነው አቶ አለማየሁ አቶምሳ እንዲሾሙ የተደረጉት። እንዲህ አይነት አምባገነን በኖረበት አገር ህገመንግስት ነበር፤ ህገመንግስት መከበር አለበት ብለው ሲጮሁ በምን አንደበታቸው እንደሚናገሩ ይገርመኛል። እንዴት ይሉኝታ እንደጠፋባቸውና ህሊናቸውን እንደሳቱ ማስተዋልም ይቻላል።
ስለዚህ ጠቅለል ባለ መልኩ ይህ ሥርዓት የሚያስፈልገው ሂስ የተሰጠው እንዲታረም ማድረግ ነው። ይህንን በሽታ መካለከል እንዲቻልና ህዝቡ ወደ ተረጋጋና ወደ ቀድሞው ህይወቱ ተመልሶ ምርጫ በተረጋጋና አስተማማኝ በሆነ መንገድ መካሄድ አለበት። አሁን ስለምርጫ የሚያወሩ ሰዎች አንድ የማይገነዘቡት ነገር አለ። ምርጫ ውጤት ብቻ አይደለም፤ ሂደትም ነው። አምስት ዓመት እኮ ቁጥር ነው። ደግሞም ህገመንግስቱ አምስት ዓመት ያለው ገደብ መጣል ስላለበት እንጂ የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ ሆኖ አይደለም። ስለዚህ ሂደቱ ኢትዮጵያ የምትፈልገውን ለአንዴና ለመጀመሪያ ጊዜ ፍትሃዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ታዓማኒነት ያለው ምርጫ እንዲመጣ ነው ሁላችንም መስራት ያለብን። ከቁጥር ጋር እዬዬ ማለት የለብንም። ይህ ማለት አምስት ዓመት ዝም ብሎ በአቦ ሰጥ ይዘለል ማለት አይደለም፤ ግን ከበቂ በላይ የሆነ ምክንያት አጋጥሞናል፤ ኮቪድ የሚባል ቀሳፊ በሽታ የመጣብን በመሆኑ ምርጫ መራዘሙ ተገቢ ነው ባይ ነኝ። የተጠየቀው የህግ ትርጉምም ተገቢ ነው የሚል አስተያየት ነው ያለኝ። በእኔ እምነት ከአንድ እስከ ሁለት ዓመት የምክር ቤቱን እድሜ አራዝሞ ቅድም ያልኩትን ፍትሃዊ ዓለምአቀፋዊ ቅቡልነት ያለው ምርጫ ቢካሄድ ነው የሚመረጠው።
አዲስ ዘመን፡-የሽግግር መንግስት ማካሄድ አለበት ከሚሉ ሰዎች መካከል በቅርበት አብሮዎት ሲሰራ የነበረ አንድ ፖለቲከኛ አለ፤ ይህንን ግለሰብ በቅርበት የሚያውቁት እንደመሆኑ የሚያነሳው ጥያቄ ከምን የመነጨ ነው ይላሉ?
አቶ አስራት፡- በነገራችን ላይ የሰዎችን ስም መጥራት የአገሬን ጉዳይ ያኮሰስኩ ያህል ይመስለኛል። የኢትዮጵያን የፖለቲካ ችግር አሳንሳለሁ ብዬም እሰጋለሁ። ግን ብዙ ታሪክ አላቸው። ይህ ታሪክ በቅንጅት ውህደት ወቅትም የታየ ነው። ከዚያም በፊት ተመሳሳይ ሁኔታ ነበር። እንደምታውቁት ቅንጅት እንዲፈርስ ሙከራ ተደርጎበት ነበር። በወቅቱ እንደነበረ ሰውና አንዱ ተደራዳሪ ስለነበርኩ የኢዴፓን ጥቅም እንዳስከብር ነበር አቅጣጫ የተሰጠኝ። በውቅቱ ኢዴፓ የተለየ ጥቅም የሚባል ነገር የለውም እኔ የማስጠብቀውም የማስቀድመውም የአገር ጥቅም ነው ብዬ ተከራክሪያለሁ። ነገር ግን ተቀባይነት አላገኘሁም። በኋላም ግጭት ተፈጠረ። ይኸውም ኢዴፓና መኢአድ ቀድመው የተመሰረቱ በመሆናቸው በቅንጅት ውስጥ ትርፍ ውክልና ማግኘት አለባቸው የሚል ነበር። ይህንንም አሳብ እኔ ተቃወምኩኝ። በዚህ ምክንያት ከተደራዳሪነት እንድነሳ ወይም ሌላ ሰው አብሮኝ እንዲደራደር ሃሳብ ቀረበ። እኔ ግን ማንም ደባል አይደረግልኝም ብዬ አንሱኝ አልኩ። ነገር ግን በድምፅ ብልጫ በተደራዳሪነት ልቀጥል ቻልኩ። ብቻ ብዙ አሻጥሮች ሲሰሩ ነበር። ስለዚህ በአሁኑ ጊዜ የሽግግር መንግስት እንዲመሰረት መጠየቅ ማለት የጥፋት አጀንዳ የመነጨ ነው የሚመስለኝ። ነባሩ መንግስት እንኳ ምርጫ ማካሄድ ባልቻለበት ጊዜ፤ መንግስት ጠንካራ ሆኖ መውጣት ባልቻለበት ሁኔታ፥ የአባይ ወንዝ መከራ ባንዣበበት ጊዜ ልፍስፍስና የሚበተን መንግስት መፈለግ ማለት ይህ አካል በአገርና በህዝብ ላይ ያለውን የበደልና የጥላቻ ደረጃ የሚያሳይ ነው። ደግሞም ማንንም መወከል የማይችል ስራ መሆኑን ነው የሚያሳየው። በምንም አይነት ሃላፊነት ስሜት አገራዊ ፍቅር ካለው ሰው የሚጠበቅ አይደለም።
ይህ የሽግግር መንግስት ሃሳብ «ከራሴ በላይ ንፋስ» ብለው ከሚያስቡ ሰዎች የሚጠበቅ ነው። ዛሬ የኢትዮጵያ ህዝብ መፈክር ከራስ በላይ አገር ነው መሆን ነው ያለበት። ምርጫ እኮ እንዲህ የሚሮጥበት ጉዳይ አይደለም። ደግሞስ በየትኛው ዝግጅታቸው ነው ምርጫ ምርጫ የሚሉት? እናውቃቸዋለን እኮ ድርጀቶቻቸውን። «ትልቅ ነን» የሚሉት ፓርቲዎች እንኳን የዝግጅት አቅማቸው ትንሽ ነው። እናም ሁኔታዎችን በበጎ አይቶ ለህዝብና ከአገር ማሰብ እንጂ እየተነሱ «ከዚህ ጊዜ በኋላ መንግስት እውቅና የለውም፤ ስልጣን ላይ ያሉ ሰዎች እንደኛ ግለሰቦች ናቸው» የሚል ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች የእውቀት ጥልቀታቸው መጠን ሚዛን የማይደፋ መሆኑን የሚያሳይ ነው። በነገራችን ላይ በህገመንግስቱ ውስጥ እኮ የህገ መንግስት ማሻሻያ አንቀፅ አለ። የህግ ትርጉም መጠየቅ የሚቻልበት አንቀፅ አለ። የሽግግር መንግስት የሚጠይቅ አንቀፅ ግን የለም። እነሱ ሲሰሩት ህገ መንግስት ቢጣስም ግድ የለም፤ ሌላው ግን ህገ መንግሰቱን ተከትሎም ቢሰራ ህገወጥ ነው። ይህ ሃላፊነት የጎደለው በከፍተኛ ደረጃ የሚያስጠይቅ ተግባር ነው።
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት ህወሓት መራሹ የትግራይ ክልል መንግስት ሁኔታ ወደየት ያመራል ብለው ያምናሉ?
አቶ አስራት፡- እኔ ህውሓት በአሁኑ ወቅት ጣር ውስጥ የገባ ይመስለኛል። በሁለት መንገድ የተሳለ ሰይፍ መሃል የቆመ ነው የሚመስለኝ። የሚያመጡት ሃሳብ ሁሉ መልሶ የሚበላቸው እንጂ እድል የሚሰጣቸው አይደለም። ከጥፋታቸው ተምረው አይመለሱም። ከዚህ በኋላም ይመለሳሉ ብዬ አላምንም። በተአምር ግን መልካምነት ቢመጣ ለትግራይ ህዝብም የሚበጅ ስለሆነ ጥሩ ነው ባይ ነኝ። በነገራችን ላይ ህውሓትን አንድም ቀን ከትግራይ ህዝብ ጋር አይቼው አላውቅም። የትግራይ ህዝብ የሚከበር፤ የኢትዮጵያ ታሪክ መሰረት ነው። የአክሱም ታሪክ መሰረት ነው። ኢትዮጵያዊነትን ከማንኛው ህዝብ በላይ የሚመለከት ነው። ለኢትዮጵያዊነት ያላቸው ቀንአዊነት ከፍተኛ ነው። ስለዚህ ህወሃት አሁን ላይ ዝም ብሎ አንድ ተዓምር የሚጠብቅ ይመስለኛል። አሁን ያለበትም ሁኔታ ሆነ የጫካ ታሪኩ የሚያሳየው ድርጅቱ ራሱ መቅሰፍት የሚደርስበት መሆኑን ነው። ይህንን የምልሽ ግን ከትግራይ ህዝብ ለይቼ ነው።
ህገመንግሰቱ እኮ የክልልም ሆነ አገር አቀፍ ምርጫ ማካሄድ የሚችለው ምርጫ ቦርድ መሆኑን ይደነግጋል። ስለዚህ ለምርጫ ቢካሄድም ውጤቱ ተቀባይነት የለውም፤ የተመረጡ ሰዎች በማዕከላዊ መንግስት ቦታ አይኖራቸውም፤ ለእነዚያ ሰዎች የሚላክ በጀት አይኖርም። የሚከፈልም ደመወዝ አይኖርም። ምክንያቱም እውቅና የለምና ነው። ህውሓቶች ግን ይህንን ነገር ከግምት ውስጥ አግብተውታል ብዬ አላስብም። ይልቁንም የምርጫ መራዘም ከማንም በላይ እነሱን ነው የሚጠቅመው ባይ ነኝ። ምክንያቱም ምርጫው ሲራዘም የእነሱም የሥልጣን ጊዜ ይራዘማል ማለት ነው። ይህ አንድ መውጫ በር ነበር፤ ግን ይፈሩታል፤ በጎ መስሎ እንዳይጎዳቸው ይሰጋሉ። አሁን ላይ የትግራይ ህዝብ እየተነቃነቀ ነው፤ የወረዳ ጥያቄ በብዛት እየተነሳ ነው። ከአድዋ አመራር ሊሾምልን አይገባም እያሉ ነው። ወጣቶች በሰበብ እየተገደሉ ነው። እነዚህ ሰዎች የትግራይ ህዝብ ጎትቶ ያወጣናል የሚል አጣብቂኝ ውስጥ ያሉ ቡድኖች ናቸው። ምክንያቱም ህውሓት እንደፓርቲ አለ ለማለት ይቸግረኛል፤ አሁን ያለበት የጣር ጊዜ ከሞት የሚያድናቸው አይመስለኝም፤ ቀናትን ይቆጥራሉ እንጂ ፤ አሁን ላይ ከኢትዮጵያ ትርምስ አንድ ነገር ይወድቅልናል የሚለው ቀቢፀ ተስፋቸው እውን ይሆናል ብዬ አላምንም። ላይ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼና ዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
አቶ አስራት፡- እኔም ያለሁበት ድረስ መጥታችሁ እንግዳችሁ ስላደረጋችሁኝ ከልብ ላመሰግን እወዳለሁ።
አዲስ ዘመን ግንቦት15/2012
ማህሌት አብዱል