ባለፈው ዓመት በኢትዮጵያ ምድር በአረንጓድ አሻራ የችግኘ መርሐ ግብር አማካኝነት ከ300 ሚሊዮን በላይ ችግኝ በአንድ ቀን በመትከል በዓለም አቀፍ ደረጃ ተይዞ የነበረውን ሪከርድ በመስበር የታላቅ ታሪክ ባለቤት መሆን ችለናል። ከዚያም በላይ በከፍተኛ ሁኔታ የተራቆተውን የሀገሪቱን የደን ሽፋን ትርጉም ባለው መልኩ ማሳደግ የሚያስችል፤ ለመጪው ትውልድ የሚሻገር የአርበኝነት ተግባር አከናውነናል።
በመርሀ ግብሩ በአጠቃላይ ከአራት ሚሊዮን በላይ ችግኞችን መትከል አስችሎናል፡፡ ይህ አሀዝ በራሱ እንደ አንድ ትልቅ ሀገራዊ ጉዳይ የሚያነጋግር ቢሆንም ከዚህ የበለጠው ግን ከተተከሉት ችግኞች 84 በመቶው የመጽደቃቸው ትልቅ ዜና ነው። እውነታው የከፍተኛ ውጤታማነት ማሳያ ከመሆኑ ባለፈ ከልብ ሆነው የሠሩት ሥራ የቱን ያህል ፍሬያማ እንደሚሆን ተጨባጭ ማሳያ ጭምር ነው።
የአረንጓዴ ልማት ጉዳይ ዓለም አቀፍ አጀንዳ በመሆን ትልቅ የመነጋገሪያ ርዕሰ ጉዳይ እየሆነ ባለበት፤ በተለይም የዓለም የሙቀት መጠን በየወቅቱ እጨመረ ለዓለም ስጋት በሆነበት በዚህ ወቅት የዚህ ትልቅ ውጤት ባለቤት መሆናችን በቀደሙት አኩሪ ታሪኮቻችን ላይ ሌላ አኩሪ ታሪክ የመደመር አካል ነው።
ለችግኘ ተከላ የነበረን መነሳሳት ፤ያስመዘገብነው ታሪካዊ ውጤት ምን ያህል የዓለም ስጋት የሆነውን ችግር በእጃችን ባለ መፍትሔ አሸንፈን ለመውጣት ያለንን ፅኑ ፍላጎት ከማሳየት ባለፈ አደጋውን ቀድሞ ለመከላክ ያለንን ቁረጠኝነት ያመላከተ ነው።
በርግጥ በቀደሙትም ዓመታት ችግኝ የመትከሉ ጉዳይ ለኛ አዲስ ባይሆንም ትልቁ ቁም ነገር ግን ከመትከልና በተተከሉ ችግኞች ቁጥር ከመመጻደቅ ወጥተን ተንከባክቦ ወደ ማሳደግና ከማሳደግ ወደሚገኝ ተጠቃሚነት የሚያሸጋግር ታሪክ ውስጥ መግባት መቻላችን ነው ።
ችግኝ ማሳደግ ቀላል ኃላፊነት አይደለም፤ ልጅ ወልዶ ከማሳደግ የማይተናነስ ድካም፣ ቁርጠኝነትና ተስፈኝነት የሚጠይቅ ነው። ከዚህ አንጻር በባለፈው ዓመት የችግኝ ተከላ መረሐ ግብር ያስመዘገብነው ውጤት የቱን ያህል ትልቅ እንደሆነ ለመገመት የሚከብድ አይደለም፤ በጣም ትልቅ ውጤታማነት ነው።
ይህን ውጤታማነትና ውጤታማነቱ የሚፈጥረውን የላቀ ስሜት ይዘን በመጪው የክረምት ወቅት 5 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል በዝግጅት ላይ እንገኛለን። የዚህ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ካለፈው ዓመት የሚለየው ሁለት ዋና ዋና ጉዳዮች አሉት። አንደኛዉ በዚህ ዓመት የሚተከሉ ችግኞች በአብዛኛው አትክልትና ፍራፍሬዎችን በስፋት ማካተቱ ሲሆን፤ በዚህም የተሻለ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ታሳቢ ያደረገ መሆኑ ነው።
ሌለኛውና ትልቁ ጉዳይ ደግሞ የችግኝ ተከላውን የምናካሂደው በሀገሪቱ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት በሆነበትና ወረርሽኙን ለመከላከል መጠነ ሰፊ ርብርብ በምናደርግበት ወሳኝ ወቅት ላይ መሆኑ ነው። በከፍተኛ ጥንቃቄና በነፍስ አድን ዘመቻ ውስጥ ሆነን የምንተገብረው መሆኑ ነው።
ከዚህ የተነሳም ለዘመቻው የምናደርገው ዝግጅት ከችግኝ ማፍላት፤ ወጥቶ ከመትከል ባለፈ ለራሳችንና ለወገኖቻችን ህይወት ዋጋ ሰጥተን በከፍተኛ ጥንቃቄ የምንተገብረው፣ ለመጪው ትውልድ በችግር ወቅት የሚፈጠር የዓለማ ጽናትና ቁርጠኝነት ምን ሊመስል እንደሚችል የምናስተምርበት ታሪካዊ ምዕራፍ ነው።
በባለፈው ዓመት ከመትከል ባለፈ ማጽደቅ ወደሚያስችል የኃላፊነት ምዕራፍ የተሸጋገርነውን ያህል፤ በቀጣይ ደግሞ ሕይወትን በማትረፍ ትግል ውስጥ ሆነን የምናካሂደው የችግኝ ተከላ እንደ ህዝብ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ገጽ ለመጻፍ የሚያስችለን ታሪካዊ አጋጣሚ ነው።
በዚህ የአዲስ ታሪክ ምዕራፍ መግቢያ ላይ ሆነን ልናሰላስለው የሚገባን ትልቁ ጉዳይ ትናንት ከልብ ሆነን በታላቅ የኃላፊነት መንፈስ የሥራ ነው ሥራ ሀገራችንን በዓለም አቀፍ መድረክ ከፍ ብላ እንድትታይ ያደረጋትን መሆኑን ነው፡፡ ይህም እንደ ሀገር በዜጎች ላይ ታላቅ ብሄራዊ ክብር ጨምሯል፡፡
በቀጣይ የምንደርገው የችግኝ ተከላ ከሁሉም በላይ ለህይወታችን ክብር የምንሰጥበት ፣ ከዚህም በመነሳት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የተቀመጡ የጥንቃቄ መርሆችን በአግባቡ ተግባራዊ በማድረግ አስቸጋሪውን ወቅት ከአስቸጋሪነቱ ባለፈ ለአዲስ ታሪክ ጅማሮ እራሳችንን የምናዘጋጅበት ነው።
አዲስ ዘመን ግንቦት15/2012