ባለፈው ሳምንት በጋራ በነበረን የትዝብት ማዕድ አንዳንድ ነጥቦችን እየመዘዝን ለመሄስ ሞክረናል። ከፀሐይ በታች የማይተች ወገን እንደሌለ የቤታችን ቋሚ መርህ አስረግጦ ይነግረናል። በተለይ የወግ አጥባቂው ማህበረሰባችን የማንነት መሰረት በሆነው ዘልማዳዊ ባህል ዙሪያ ኅብረተሰቡን ወደ ግብረገብነት መስመር የሚመልሱ ትችቶችና ሚዛናዊ ሂሶች እጅግ ጠቃሚ መሆናቸው አሻሚ አይደለም። ስለሆነም የጀመርነውን የማህበረሰባዊ ስነሂስ ዘመቻችንን አጠናክረን እንቀጥላለን። አብራችሁን ሁኑ።
መዘናጋት ውድ ነው
የኮሮናን ስርጭት ለመግታት ማህበረሰባዊ ልቀትና አኗኗራችንን መሰረት ያደረገ ግንዛቤ መፍጠር ከሁሉም የላቀ አዋጭ መሳሪያ ነው። በተፈጥሮው ከዚህ በፊት የተለያዩ ወረርሺኝና ቸነፈር የፈጠሩለትን አጋጣሚ በመጠቀም ህዝባችን በቂ ልምድ ያለው ከመሆኑም በላይ የሚሰጡትን ምክሮች በጨዋነት በመቀበል መተግበር የሚችል ማህበረሰብ በመሆኑ የግንዛቤ ተግባሩ ውጤታማ እንደሚሆን ይታመናል።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስርጭት አድማስ፥ ይህ ፅሑፍ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ፥ ቫይረሱ በዓለም ዙሪያ ባሉ 200 እና በላይ አገራትን አካልሏል። በዚህም ምክንያት፥ እስከአሁን ከአምስት ሚሊዮን በላይ ሰዎች በቫይረሱ ተጠቂዎች ሆነዋል። ከዚህ ውስጥ፤ ከ320,000 በላይ የሚሆኑት ደግሞ በበሽታው ህይወታቸውን አጥተዋል።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በሽታ በሰው ልጆች ጤና ላይ ከሚያደርሰው ጉዳት በተጨማሪ፥ የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴዎችን አስተጓጉሏል፣ ለዘመናት የተገነቡ ማህበራዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊ፣ … መልካም መስተጋብሮችን አፈራርሷል፤ የምርት፣ ግብይት፣ ኢኮኖሚክ እንቅስቃሴ በማዳከም አገራትን ለከፋ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ በመዳረግ ላይ ይገኛል።
ይህ በሽታ ትልቁ የዓለም ፈተና ነው። ከማንኛውም ጦርነት የከፋ። ምን አለ ታዲያ ሰዉ ሚባለውን ሰምቶ አዎ ብሎ ቢንቀሳቀስ? ከአሁን በኋላ በሽታው ከውጭ አይመጣም ቫይረሱ ዜግነቱን አግኝቶ ከኛ ጋር ተዋህዷል። ከዚህ አኳያ ሁለት ሁሌ የማንዘነጋቸው ነገሮች አሉ። እነርሱም አንደኛው የበሽታው የመዛመት ኃይሉ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የመራባት ፍጥነቱ ናቸው።
የመዛመት ኃይሉ ሲባል ምንም እንኳን ነገሩ ሂሳብ ቢሆንም እዚህ ላይ ግን ትኩረት ይፈልጋል። አንድ ሰው በቫይረሱ ሲጠቃ በአማካይ ለስንቱ ነው ሚያስተላልፈው ነው። አንድ ሰው ለአንድ የሚያስተላልፍ ከሆነ ትንሽ ቢመስልም ግን በሁለተኛ ደረጃ የጠቀስኩት የመራባት ፍጥነቱ ትልቅ ሚና ይጫወታል።
በኛ የኑሮ ሁኔታ አንደ ሰው ለአንድ ብቻ ነው ሚያስተላልፈው ብለን መጠበቅ የለብንም። ግን አንድ ሰው ለሁለት በአማካይ ቢያስተላልፉ እነዛ ሁለት ሰዎች ደግሞ መልሰው ለሌላ ሁለት ሰው ቢያስተላልፉ መጀመሪያ ያስተላለፈው ሰው ለሁለት ሳይሆን በአንዴ ለስድስት ስዎች በሽታውን የሚያሰራጭ ይሆናል ማለት ነው። ለዚህም ነው የምንሰማቸው ቁጥሮች ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ከፍ ከፍ እያለ የሚሄዱት። በዚህ የተነሳ የመዛመት ኃይሉን እና የመራባት ፍጥነቱን መቀነስ አስፈላጊ ነው። ይህ እንዲሆን ደግሞ ብዙ መራራቅን ከበፊት ከነበረው በላይ ይጠይቃል። አተርፋለሁ ብሎ ዋጋ የጨመረው ነጋዴ የሆነ ሰዓት ላይ የታመመው ሲበዛ እሱም ያተረፋትን ሳይበላ ትን ትለዋለች። እናም ኃላፊነት ሊሰማን ይገባል።
ሌላው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ወደሥራ ከማስገባት ጋር ተያይዞ ብዙ የሚቀረን ነገር እንዳለ በትዝብት መነፅራችን ማስተዋል ችለናል። እንግዲህ የኮሮና ድንቁርና ጫፍ ደርሷል ማለት የምንችልበት ሁኔታ ላይ ነው ያለነው። ጎበዝ እስኪ አሁን የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ወይም ማስክ አድርግ አታድርግ በሚል ከፀጥታ ኃይል ጋር ግብግብ መፍጠር ምን የሚሉት ድንቁርና ነው? በዚህስ ምክንያት የሰው ህይወት መጥፋት ነበረበትን? የመቀሌውን ጉዳይ ማስታወስ ይቻላል። በዚሁ ሳምንት እዚሁ አዲስአበባ ከሁለት ሺህ ስምንት መቶ በላይ ነዋሪዎች ርቀታችሁን ጠብቁ፣ ህዝብ በተሰበሰበበት እና በትራንስፖርት አውታር ላይ የፊት መሸፈኛ ጭምብል አጥልቁ በሚል ሰዶ ማሳደድ ውስጥ ተገብቶ የከተማው ፖሊስ ቢቸግረው ያንን ሁሉ ሰው በቁጥጥር ስር እንዳዋለ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው።
ማክሱን በኪሱ ይዞ ሰው መሀል ዘው የሚል ርቀት ጠብቅ ስትል ባክህ ኮሮና የለም የሚል ዜጋ በየአካባቢው ተበራክቷል። የኛ ነገር መች እንዲህ እንደዋዛ ያሰኘኝም ይኸው ግራ መጋባት ነው።
ሕግ ማስከበርና የሰውን ሕይወት ማጥፋት ይለያያል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለዜጎች ደህንነት ነው። ዓላማውን ሲስት ማስተካከል የመንግሥት ኃላፊነት ነው። ሕይወት ለማዳን የወጣ አዋጅ ሕይወትን እንዲያጠፋ በቸልተኝነት ሊታይ አይገባውም።
የሆነው ሆኖ በተለይ የንግዱን ምህዳር መንግሥት በቅርበት ሊከታተለው ይገባል የሚለው ይሰመርበት። ምክንያቱም አንዱ የበሽታው ማስፋፊያ መስኮት እሱ ሆኖ ይታያልና። አንድ የማይካድ ሀቅ የሚገዛ ካለ የሚሸጥ አለ። ገዢ እጁን የሰበሰበ ቀን ግን ሻጭ ኮተቱን በትኖ ይበተናል። ይህ የማይሆነው የሚሸጠው ነገር ለመኖር የግድ አስፈላጊ ሲሆን ነው። ያኔ ሻጭ ቢበተንም ገዢው ፈልጎ እና የተጠየቀውን ከፍሎ ነፍሱን ያተርፋል። አስተውለን ከሆነ ኮሮና ለዚህ በቂ ትምህርት ሰጥቶናል። ሁላችንም ያቀድነውን ትተን ህይወታችንን ለማቆየት ዱቄት እና ዘይት ስናሳድድ ነው የሰነበትነው።
ዛሬስ? አሁን እያየን እንዳለነው የበሽታው ጉዳይ ገበያውን ቀዝቀዝ እያደረገው ነው። የዚህ ምክንያት በሽታው እየጠፋ ስለሆነ ቢሆን እሰየው ነበረ። ስለመጥፋቱ ያለን ማስረጃ ግን ከቀቢጸ ተስፋ የዘለለ አይደለም። እያየነው ያለው ደግሞ የማስክ እና የሳኒታይዘር ገበያ እየቀዘቀዘ የዱቄት እና የዘይት አሳሳቢነት እየቀነሰ ሲሆን ትቶን ሳይሆን ትተነው እፎይ ያልንበት የግጭት እና እልቂት ንግድ የመሞቅ አዝማሚያ እያሳየ ነው።
ታዲያ “ውሻ ወደ ትፋቱ እንደሚመለስ” እንዲል መጽሐፍ እኛም ወደ ተውነው ውጥንቅጥ አየተመለስን መሆኑ እንደጠዋት ጀምበር እየጠራ መምጣቱን አለማስተዋል የከፋ ድንቁርና ነው። አይ የሚል ወገን ካለ ጤናማ ሰው ስለመሆኑ ወደ አቅራቢያው የጤና ተቋም ሄዶ ይመርመር። ኮሮናም እንዲሁ አይደል ሳይታወቅ የሚያሰምጠው?
መማር የፈለገ ሰው በርቀት ይማራል። ያልፈለገ ተማሪ ደግሞ ከክፍል ጠፍቶ ይሄዳል። የኛ ነገር እንደ ሁለተኛው ተማሪ ነው። በዚህ ሰሞን ካሳለፍነው ሁኔታ ካልተማርን ደግሞ መጨረሻችን ግልጽ ነው። የምንኖረው ደሃ እና ለዓለም አስፈላጊ ያልሆነች ሀገር ላይ ነው። የምንገዛውን ሃሳብ ካልመረጥን የሚገጥመን ምን እንደሆነ ግልጽ ነው።
ቸር ሰንብቱ።
ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች እንኳን ለ1441ኛው ዓመተ ሂጅራ የኢድ አልፈጥር በዓል በሰላም አደረሳችሁ። በዓሉ የሰላም የደስታና የጤንነት ይሆንላችሁ ዘንድ እመኛለሁ።
አዲስ ዘመን ግንቦት 14/2012
ሐሚልተን አብዱላዚዝ