በአገራችን ፖለቲካ ውስጥ አንዱ ባጠፋው ሌላው ሲወቀስ፤ ደግ የሠራው ቀርቶ መጥፎ የሠራው ሲሞገስ ማየት ብዙም አዲስ ላይሆን ይችላል፡፡ በእርግጥ የአገራችን ፖለቲካ መጥፎ ደዌ ከተጠና ወተው ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡
ነገር በረጅሙ አሻግሮ ካለማየት በመነጩ አልባሌ አስተሳሰቦችና በግለሰባዊ ጥቅም የተሳሰሩ ግለሰቦች ፖለቲካው ነቀዝ እንዲነቅዝበት ዕድሎች ተመቻች ተዋል፡፡ ይህም በመሆኑ አገሪቱ ከመቼውም በላይ በርካታ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፈተናዎች እንዲፈራረቁባት መጥፎ አጋጣሚዎችና ሁኔታዎች ተመቻችተዋል፡፡ በአገራችን ሊሆኑ እና ሊታሰቡ የማይችሉ መጥፎ ክስተቶች በተደጋጋሚ እየተፈጠሩና የዕለት ተዕለት ኑሯችን የሆኑ እስኪመስለን ድረስ ለመላመድ ተገደናል፡፡ የአንድነት፣ የሠላም እና የፍቅር አንደበቶች ተዘግተው የጥላቻ ንግግር የሚዘሩ፤ የጥፋት አሜካላ የሚተክሉ የሰፈር እንደራሴዎች ተበራክተዋል፡፡ ቀድሞ የነበረውን ፍቅር አፈርድሜ እያበሉ የሚገኙ ፖለቲካን የማይገነዘቡ ግን ፖለቲከኛ ነን ባዮች በየመንደሩ እንደ አሸን ተፈልፍለዋል፡፡ ይህም በሂደት የራሱን የሆነ መጥፎ አሻራ እያስቀመጠ ለዛሬ አድርሶናል፡፡
በፖለቲከኞች መካከል ያለውን ጊዜያዊ ቅሬታ ‹‹አልፋና ኦሜጋ›› ሆኖ አብሮ ለኖረ ህዝብ ከአንድነቱ ይልቅ ስለ ልዩነቱ እያሰበ እንዲኖር አጀንዳ እየተሰጠ ነው፡፡ የታሪክ ቅርሻቶችን ብቻ እየመረጡ መቧቀስ ተበራክቷል፡፡ አገር ነበረች፤ ዛሬም አለች፡፡ ነገ ስለመኖሯ ዋስትና የሚሆነው ግን ዛሬን ማሳመር ስንችል ብቻ ነው፡፡ ጥንካሬ እና ድክመትን ለመለካት አሊያም ለማወቅ የግድ የሰው በር ማንኳኳት አይጠበቅብንም፡፡ ጥሬ ታሪካችን በራሱ በእነዚህ ሁለት አንኳር ሁነቶች የተሞላ ነው፡፡
ጥንካሬን መማር ከፈለግን በእምዬ ሚኒሊክ መሪነት በዓድዋ ተጋድሎ ነጮችን ያንበረከክንበት፣ በአጼ ቴዎድሮስ ጥልቅ ፍላጎት ገና በዚያ ዘመን በጋፋት ላይ መድፍ የገነባንበትን ጊዜ ማስታወሱ በቂ ነው፡፡ በአጼ ዮሐንስ ዘመን ለአገር ክብርና ሞገስ ሲሉ መስዋዕት የሆኑባት፣ በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመን የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ለመመስረት የተጣጣር ንበት፤ የጠላትን ወረራ በመመከት ዳግም ድል የተቀዳጀንበት ዘመን ነበር፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ዘመንም በዓለም ላይ ከቀዳሚዎቹ አንዱ ሆነውን የህዳሴ ግድብ የጀመርንብት፤ በአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የስልጣን ዘመን ደግሞ ያለ አንዳች ደም መፍሰስ ስልጣን ርክክብ ማድረጋችን የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው፡፡ ዛሬ ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ዘመን ፍቅር፤ ሠላም እና አንድነት ከመቼውም በበለጠ የተማር ንብት፤ ብሎም ለዘመናት እንደጠላት ስንፈር ጃቸው ከነበሩት አገራት ጋር ሠላም ያወረድንበት እና የዲፕሎማሲ ከፍታችንን ያስመሰከ ርንበት ሲሆን፤ እነዚህ ከጀግንነቶቻችን በጥቂቱ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ እነዚህ እኛን የሚያበረቱ፤ ክብራችንን ከፍ ከፍ የሚያደርጉ ስለመሆናቸው አያጠራጥርም፡፡
በዚህኛው ጎራ ደግሞ ፀያፍ ታሪክ አለን፡፡ መገዳደል እና መወነጃጀል የታሪካችን ጉልህ ገጽታ ነው፡፡ ርሃብ፣ ድህነትና ቸነፈር ለዘመናት ተወዳጅተን አብረነው የኖርን፤ አሁንም አብረን ያለን መታወቂ ያችን ነው፡፡ በንጉሣዊ፣ አሃዳዊ፣ አምባገነናዊ ሥርዓቶች መፈራረቅ ወገባችንን ያጎበጥን ነን፡፡ ‹‹ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል›› በሚል አጉል ብሂል ተይዘን በሙስና እና በተጨማለቀ አሠራርና ሥርዓት ውስጥ ከትመን የኖርን አሁንም ከዚሁ ጋር ያለን ህዝቦች ነን፡፡ ዓለም አንድ መንደር ለመሆን በምትኳትንበት ዘመን እኛ ደግሞ በመግፋትና በመገፋፋት፤ አሳድጅና ተሳዳጅ ሆነን ጎልተን የወጣንበት ዘመን ላይ ነው፡፡ ግን ለምን?
መደማመጥና አስተዋይነት ቢኖር ኖሮ ዛሬ ወደብ አልባ አገር ባልሆንን ነበር፡፡ አርቆ አስተዋይነት ቢኖር ኖሮ ከዓለም የስልጣኔ ማማ ላይ ተፈጥፍጠን በድህነት አረንቋ ውስጥ ባልገባን ነበር፡፡ ዛሬም መደማመጥ ተስኖናል፤ በግልጽ መነጋጋር ከብዶናል፡፡ እኛው ፈራጅ፤ እኛው ፈቃጅ ሆነናል፡፡ ህግ ሰዎችን እንዲመራ ሳይሆን፤ ሰዎች ህግን እንዲመሩ ፈቅደናል፡፡ ሌባን ማባረር ስንችል፤ በጉያችን አቅፈን ተንከባክበናል፡፡ አስታራቂ ገፍተን፤ የሚያጣላ አንግሠናል፡፡
አንዳንድ ፖለቲከኞች ዛሬ የሚናገሩት፤ ነገ ላይ ምን ፍሬ እንደሚያፈራ ስለመገመታቸው እጠራ ጠራለሁ፡፡ አንዳንድ የመገናኛ ብዙሃን አውታሮች ዛሬ የሚያስተላለፉት መልዕክት ነገ በዶክመንት መልክ ለዋቢ ስለመቀመጡ መጠርጠራቸውንም እንጃ! አንዳንድ ታሪክ አዋቂ ነን ባዮች ልዩነትን አጉልተው በመነጋገር ብዙ ተከታይ እንዳላቸው ከመቁጠር ሌላ ነገ በታሪክ ስለመወቀሳቸው ማጤና ቸውን እጠራጠራለሁ፡፡ የተናገሩት ሁሉ ትክክል የሚመስላቸው፤ የመድረክ አጋፋሪዎች ነገ ‹‹ማይኩ›› በሌላ ሰው እጅ ስለመግባቱ የተገነዘቡት አይመ ስለኝም፡፡
አሁን በገባንበት የፖለቲካ የቃላት ጦርነት ለተወሰነ ጊዜ ለህዝቡ አጀንዳ ሰጥተነው ልንቆይ እንችላለን፡፡ ነገር ግን ህዝብ የሚበላው ያጣ ቀን በፖለቲካ አሻጥርና በዚያው አጀንዳ አይደለልም፡፡ ይልቅስ መቶ ገጽ ፖለቲካ አሻጥር ላይ አዘቅዝቆ ከመዋል፤ አንድ ገፅ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያለው ሥራ ላይ መጠመድ ይበጃል፡፡ የኢኮኖሚ ጥያቄ ያልተመለሰለት ማህበረሰብም ሆነ ህዝብ ሁሌም ጠያቂ ነው፡፡ ጥያቄው ማቆሚያ የለውም፡፡ የጥያቄዎችም ሆነ መልሶች ሁሉ መሰረቱ ኢኮኖሚ ነው፡፡ አሜሪካ ውስጥ በዓለም ላይ ያለ ሰው ዘር ሁሉ አለ፡፡ ግን አንድም ቀን ዘር ለይቶ አይቧ ቀስም፡፡ 55 ግዛቶች አሉ፤ ግን አንድም ቀን በአስተዳደራዊ ወሰን አይጋጩም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ መሰረታዊ የሆኑ የፍትሐዊ የሀብት ተጠቃሚነት እና ኢኮኖ ሚያዊ ጉዳዮች ፈር ይዘዋል፡፡
ጠቅለል ሳደርገው፤ እኛ ትናንት የተዘራን ዛሬ ያፈራን ተክሎች ነን፡፡ ነገ የምናጭደውና የምንሰ በስበው ፍሬ ደግሞ ዛሬ የምንዘራው ዘር ነው፡፡ በጥሩ መሬት ላይ እና በጥሩ ገበሬ የተዘራ ዘር ምርቱ አገር ያጠግባል፤ በጠፍ መሬት የተዘራ ዘር ደግሞ እንዲሁ ከንቱ ሆኖ ይቀራል፡፡ የምንሠ ራው፤ የምንናገረው ዛሬ የምንዘራውን ነገ የምናጭ ደውን መሆኑን አንዘንጋ፡፡ በጥቂት ቡድኖች እና አክቲቪስት ነን ባዮች የተዘራ ዘር ከምርቱ ገለባው የላቀ መሆኑ እምነቴ ነው፡፡ የህዝብ ፅኑ የጋራ መሠረቶችን እያናጋን፤ ህዝባዊ ቅቡልነት ለማግኘት መሞከር ያስተዛዝባል፡፡ ህዝብ ከህዝብ፤ አንዱን ብሄር ከሌላ ብሄር እያጋጩ፤ እያጋደሉ፤ እያፈናቀሉ መኖር የመጥፎ ታሪክን ለትውልድ ለማስተላለፍ ካልሆነ በስተቀር አንዳች ትርፍ አይኖረውም፡፡
አርሶ አደሩ የአገሪቱ ኑሮ መሰረት ሆኖ ሳለ፤ ጠዋትና ማታ ኑሮው እንዲናጋ ማድረግ አላዋቂነት ነው፡፡ ግብርና የአገሪቱ ጀርባ አጥንት ሆኖ ሳለ፤ የአርሶ አደሩን ጀርባ የሚጎብጡ ግጭቶችን መቀስቀስ ከተራ ፖለቲከኛ እና ከወረደ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ውጪ ከየት ሊመነጭ ይችላል? ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ ውስጣዊ ፍልሰቱ ወይንም ስደት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች ከቀያቸው ተፈናቅለው ከማየት በዘለለ ምን ሚያሳዝን ነገር አለ? አገሪቱን የሚመግብ አርሶ አደር፤ ተመፅዋች እንዲሆንና በካምፕ ውስጥ ቀለብ እንዲሰፈርለት ህይወቱን ከማናጋት ሌላ ምን አፀያፊ ተግባር ይኖራል?
አገሪቱ የጦር ቀጣና እንድትሆን ካልተፈለገ እንደምን ተብሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ የጦር መሳሪያዎች ጠዋትና ማታ እንዲዘዋወሩ ተፈለገ? በእርግጥ ይህ ከጤናማ አዕምሮ እንደማይመነጭ በግልጽ ቢታወቅም፤ ነገሮች ፈርጃቸውን እስከሚይዙ ድረስ መንገራገጮች መፈጠራቸው አይቀርም፡፡ ለመሆኑ ድህነት አናቱ ላይ ሆኖ የዕለት ጉርስ ለተቸገረ አርሶ አደር ቀለቡ ቦንብ እና ክላሽ ወይስ ስንዴ? ከፊደል ገበታ ጋር ላልተዋወቁ ሕፃናት ለመፍጀት ወይስ ለምቾታቸው መጨነቅ? ጊዜ ይወስድ ይሆናል እንጂ ይህ ሁሉ አንድ ቀን ተረት መሆኑ የግድ ነው፡፡
የታሪክ ምዕራፎች ሁሌም መከተብ አይተውም፡፡ ታሪክ ባለውለታዋን ታነግሣለች፤ ውለታቢ ሶችንም ቀን ቆጥራ ትኮንናለች፡፡ ሁላችንም የታሪክ አካል ነን፡፡ መጥፎ የታሪክ ምዕራፎችን ዘግተን፤ ልክ እንደ ማለዳ ጀንበር ደምቀን በአዲስ የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ ካልተገኘን ሕይወት ትርጉም አልባ ትሆናለች፡፡ መጥፎ ታሪኮች ዶሴያቸው ተዘግቶ፤ አዳዲስ የጀብድ እና የአንድነት አስተሳሰቦች ሥፍራ እንዲኖራቸው ካልተደረገ ከታሪክ አዙሪት መውጣት አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ለዚህም ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ አፍሪካ አገራት ሕያው ምስክር ናቸው፡፡
ሐሳቤ ሲጠቃለል፤ በማናቸውም ዓለም ውስጥ የለውጥ ማዕበል በመጣ ጊዜ፤ ሰዓቱ ደርሶ ለውጡ የሚውጣቸው አሊያም ከላይ እያንገዋለለ ለእውነት ፍርድ የሚያቀርባቸው እንዳሉ በመገንዘብ አሁናዊ ክስተቶችን በጥበብ ማለፍና ፈተናዎችን ወደ መልካም አጋጣሚ መቀየር ይገባል፡፡ የሆነው ሆኖ ግን መንግሥት ከላይ እስከ ታች ህዝባዊ መሰረት ያላቸው ተግባራት ላይ መጠመድ አለበት፡፡ ህዝብ የሚጠቅመውንና የሚጎዳውን አካል አንጥሮ እስኪገነዘበው በተገኙ አጋጣሚዎች ሁሉ እውነታ ውን ማሳየት ይገባል፡፡ ጨለማው እጅግ ጨግጎ ቢገዝፍም ጀንበር እንደጠለቀች እንደማትቀር ሁሉ፤ እብሪተኞችና አጥፊዎች በጊዜው የሚገ ባቸውን ቦታ ማግኘታቸው አይቀርም፡፡ በለውጥ ሂደት ውስጥ ሁሌም ዛሬ ከትናንት ይሻላል፤ ነገ ደግሞ ከዛሬ ይሻላል፡፡ በመሆኑም ወርቅ በእሳት ተፈትኖ እንደሚያብረቀርቅ ሁሉ፤ አገሪቱ የጀመረችው ለውጥ አሁን በሚታዩ አስቸጋሪ ውጣ ውረዶች ውስጥ አልፎ ነገ የብሩህ ተስፋ ባለቤት እንድምትሆን እምነቴ እንደ በርካታ ባለራዕዮችና ሁሉ ከተራራ በእጅጉ የገዘፈ ነው፡፡
ክፍለዮሐንስ አንበርብር