የዘንድሮው የአድዋ ድል በዓል ሲከበር ወጣቶች በወኔ ተነሳስተው አሸብርቀው ደምቀው አክብረውት ነበር።እንደውም የአራዳው ምኒልክ አደባባይ በሰዉ ተሞልቶ ሳየው የበዓሉ መቶኛ ዓመት እስኪመስለኝ ደንቆኝ ነበር።ያ ቀን ግብፅ አባይን አስመልክቶ የዓለም ባንክንና አሜሪካንና ተታካ ልታሳካ ያሰበችው እና ኢትዮጵያ እስከ 20 ዓመት ወንዙን መሙላት አለባት የሚለው ሃሳብ ሰውን ለቁጣ እንዳነሳሳውና ውጡ ሳይባል ወጥቶ ለሀገሩ ያለውን ፍቅርና ለመንግሥት ያለውን ክብር አሳይቶ የዋለበት አድዋንም አስታኮ ያከበረበት ቀን ነበር፡፡
የሀገራችን ረጅም ዘመን የጦርነት ታሪክ ነው። በነገሥታቱ ዘመን የአካባቢ ገዢዎች ገብሩ ሲባሉ አልገብርም ካሉ ግጭት ይነሳል። በነበረው ግብርና ሥራ እያረሰ እየገበረ ግጭት ሲመጣ ደግሞ ተነሳና ተዋጋ ይባላል፤ ሳይወድ በግድ ይዘምታል ይዋጋል።በሰላም ቀን ግብርናውን እየሠራ በግጭት ቀን ደግሞ ወደ ውትድርናው ይሄዳል።በወቅቱ አርሶ አደርም አርብቶ አደርም የሆኑት ገበሬዎቻችን በክፉ ጊዜ ደግሞ ወታደሮቻችን ነበሩ።ሀገራችን በማንም ፉከራ አትደናበርም ወታደሮቻችን ሁሌም ዝግጁዎች ናቸው።የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ነፍስ ሄር አቶ መለስ ዜናዊ መለስ ዜናዊ ግድቡ ሲጀመር ግብፅ ጦር ብታዘምትስ ተብለው ሲጠየቁ እኛ የምናዘምተው የእግር ኳስ ብሄራዊ ቡድን አይደለም አሉ ሲባልም ሰምቻለሁ፡፡
ለዘማቾቹ ደመወዝ የሚባል ነገር አልነበረም፤ ዘማቹ ከሄደበት አካባቢ ስንቅ ካለቀ አምጡ ይላል።አልያም ዘርፎ ይበላል።በግብርናም በውትድርናም የሚያገለግሉ ሰዎች እንጂ ዘላቂ ወታደር አልነበረም።ከላይ እንደጠቀስነው የአካባቢ ገዢዎች ተገዢነታቸውን የሚያረጋግጡት ለበላዮቻቸው በመገበር ነበር።እንደ ዘመናችን የሚሠራ መንገድ ድልድይ፣ የህክምና ቦታና ትምህርት ቤት የለም።ግፋ ቢል ደግሰው ለአካባቢው ሰዎች እና ለባለሟሎቻቸው ያበላሉ ያጠጣሉ።በወቅቱ አባባል “ግብር አበሉ” ተብሎ ይነገርላቸዋል፡፡
ይህ ሁሉ የሚሆነው በገባሪና አስገባሪ ሽኩቻ ነው። የውጪ ጠላት ሲመጣ ግን ሁሉም ልዩነቱን ወደ ጎን ትቶ ፣መሣሪያውን አንግቶ፣ ወራሪውን ለማባረር በአንድነት ከትቶ ይረባረባል።በዚህም ከሀገር በላይ ማንም እንደሌለ ለእኛ የእናት ሀገር ፍቅርና ውሉ ለጠፋብንና በድንግርግር ለምንሄድ ያሳየናል፡፡
የአባይ ግድብ የታሰበው በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመን ነው፤ በ1950ዎቹ መጨረሻ።ንጉሡ በወቅቱ በታዋቂ የውጭ ባለሙያዎች ጥናት አስጠንተው ጨርሰው ለግድብ ግንባታ ቢዘጋጁም አልተሳካም።የዓለም ባንክ ለግንባታው ብድር ለመስጠት አሻፈረኝ አለ፤ ለዚህ ደግሞ የግብፅ ዲፕሎማቶች ጫና ነበረበት።ንጉሡም ፕላኑ ይቀመጥና አንድ ቀን የኢትዮጵያ ሕዝብ (ን)ብረትና ዕውቀት ሲያገኝ ይገነባዋል አሉ ይባላል።
ዘውዳዊው መንግሥት ተገርሥሶ ወታደራዊው ደርግ ቢተካ በመሃል ሀገር የነበረው የነ ኢህአፓ ሽኩቻ በሰሜንና በምዕራብ የነበረው የነፃ አውጪ ግንባሮች ንቅናቄ ፋታ ሊሰጠው አልቻለም።በዚሁ ላይ የሶማሊያ መንግሥት ውጊያም ነበረበት።ደርግ በምዕራብና በሰሜን ሲያደርገው የነበረው ውጊያ ቀጥሎ በኢህአዴግ ተጋዳላይ ደርግ ሥልጣኑን ትቶ ጦሩን በትኖ ተደመሰሰ።ኢህአዴግ ደግሞ ጊዜ ሲያገኝ ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ብድርና ርዳታ ለግድቡ ግንባታ እንደማይሰጡ አስተውሎ ህዝቡን አስተባብሮ የአባይን ግድብ አስጀመረ።ለጅማሬው አድናቆታችን እየገለፅንና እየተሳተፍን ቀጠልን፡፡
ይሁንና ግብፅ አሁንም የ1929 እና 1959 ኢፍትሃዊ ስምምነቶች እየጠቀሰች አይገነባም እያለች በሰመመን ሆና መባነኗን ቀጥላለች።ግብፅ መጀመሪያ የወንዙ ባለቤት እኔ ስለሆንኩ ወንዙ መገደብ ቀርቶ አንዲት ጠብታ አይነካም ስትል ነበረ።መገደብ ከተጀመረ በኋላ ደግሞ ግድቡ በ20 ዓመታት መሞላት አለበት ማለት ጀመረች።አይገነባም ከሚለው ግትር አቋም በተወሰነ ዓመት ግድቡ ይሞላ የሚለውን አፈገፈገች ፤ ሃሳብ ባንቀበለውም ለኔ ይሄ በራሱ ራሱን የቻለ ድል ነው።
የአባይ ግድብ ግንባታ ሲጠናቀቅ ለኢትዮጵያውያን እንደ አክሱም ሀውልት የምናደንቀው፣ እንደ ጎንደር አብያተ መንግሥት የምንጎበኘው፣ እንደ ሐረር ጀጎል ቅርሳችንና መኖሪያችን የሚሆን ነው ማለት እንችላለን።ከዚህም ባለፈ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ሕይወታቸው ይቀየራል።ግድቡ ከሱዳን ድንበር እስከ 50 ኪሎ ሜትር የሚርቅ በመሆኑ ሱዳን እና ሌሎች ጎረቤት ሀገራት ተጠቃሚ ይሆናሉ።ብዙ ፋብሪካዎች ሊመሠረቱ የሚችሉበት ምቹ አጋጣሚም ይፈጥራል፤ ግድቡ ለእኛ ራትና መብራት በመሆን የሚያገለግል የህልውናና የብልፅግና ምንጫችንም ነው።በእንቦጭ ወረራ እየታመመና እየታከመ ላለው ጣና ሀይቅ አቻ ሀይቅ ፈጠርንለት ማለት ነው።“አባይ ማደሪያ የለው ግንድ ይዞ ይዞራል” ያልነውን አባይ ማደሪያ አለው ፋና ይዞ ይዞራል በሚልም መቀየሪያችንም ይሆናል።
የግድቡን ሥራ ለማደናቀፍ ግብፅ ብዙ ዕኩይ ዓላማ ያላቸውን ዜጎች እየፈለፈለች እና በነፃነት ተዋጊነት ስም እያደራጀች ብዙ ሀብትና ንብረትዋን አራገፈች።ይሁንና ያራገፈችው ገንዘብ ግድቡን ከመገደብ ሊገታው አልቻለም።ግድቡን ሊገታው ቢችል ኖሮ የነፃ አውጪ ግንባሮች ሽኩቻ ሊያቆመው ይችል ነበር።የግብፅ ድካም ግን “ዘጠኝ ገዝቶ ዘጠኝ እንደመሸጥ ትርፉ ዘጥ ዘጥ” ሆነ፡፡
ዓይኗን በጨው የታጠበችው ግብፅ በህዳሴ ግድብ ግንባታ 11ኛው ሰዓት ላይ ከስ መሰል ነገር በተባበሩት መንግሥታት ድምፅን በድምፅ የመሻር ላላቸው አምስቱ ሀገሮች አቀረበች፤ የኢትዮጵያ መንግሥትም ግብፅ ላቀረበችው ኢፍትሃዊ ጥያቄ የግድቡን አስፈላጊነት፣ ጥቅም እና ለኢትዮጵያውያን የህልውናና የብልፅግና ጉዳይ መሆኑን የሚገልፅ ምላሽ ሰጠ፡፡
ሀገራችን ያለችው በክረምት ውሃውን እንሞላለን ነው።ገብጋባ ሆነን እኛ ብቻ ይድላን የምንል ብንሆን ኖሮ በአንድ ዓመት ሙሉ ግድቡን መሙላት እንችል ነበር።ክረምት እንዲሞላ የተፈለገው ወንዞች ከወሰናቸው አልፈው ስለሚፈሱ እና በታችኛው ተፋሰስ ሀገሮች ጉዳት ስለሚያደርሱ ነው፡፡
ባለፈው የካቲት ወር አሜሪካና የዓለም ባንክ ኢትዮጵያን ሱዳንና ግብፅ አደራድራለሁ ብለው ስብሰባ ጠሩ።አደራዳሪ መስላ የቀረበችው አሜሪካ ጭንብሏን አውልቃ ተደራዳሪና ውሳኔ ሰጪ አካል ሆና ብቅ አለች።ባስ ብላም በድርድሩ ሥፍራ የግብፅ ቃል አቀባይ ሆና ተገኘች።በአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስቴር አማካይነት ኢትዮጵያ ላይ ተፅዕኖ ለመፍጠር መግለጫ አወጣች። ኢትዮጵያ ረቂቅ ስምምነቱን እንድትፈርም፣ ስምነነቱ ከመፈረሙ በፊት ምንም ዓይነት የግድብ ሙሊት ሙከራና እንቅስቃሴ እንዳታደርግ ፣ ስምምነቱን ከመፈረሟ እና ግድቡን መሙላቷ ከመጀመሯ በፊት በዓለም አቀፍ ደረጃዎች መሠረት ሁሉንም አስፈላጊ የደህንነት መስፈርቶች የመተግበር አስፈላጊነትና ዕውቅና እንድትሰጥ የሚል እንደነበር ሰነዶች ያስረዳሉ።
ግብፅ በህዳሴ ግድብ ላይ በድርድር ሰበብ በአሜሪካና በዓለም ባንክ በኩል ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር ብትሞክርም ሀገራችን አልተቀበለችውም።ግብጾች የህዳሴው ግድብ መገንባት ምንም ዓይነት ጉዳት እንደማያደርስባቸው ያውቁታል በዓባይ ወንዝ ላይ ተሰሚና እና ተፅዕኖ ፈጣሪ ሆነን እንቀጥል በሚል ዕሳቤ ነው፡፡
ይሁና ቅኝ ተገዝታና በሉዓላዊነቷ ተደራድራ የማታውቀው ኢትዮጵያ ይህንን ውሳኔ አልተቀበለችውም። ይልቁኑ የግድቡን ግንባታ ማንንም በማይጎዳ መልኩ መገንባቷን እንደምትቀጥል አስታውቃለች። ስለሆነም ዜጎች ሁሉ ከመንግሥት ጎን ሊሆኑ ይገባል ፤ ባለንበት የኮረና ወረርሺኝ ምክንያት አደባባይ ወጥቶ ሃሳብን መግለፅ ባይቻልም በአውሮፓና በአሜሪካ ያሉ ምሁራን ዜጎች ለመንግሥት ያላቸውን አጋርነት የአሜሪካንን አድሏዊነት በመንቀፍ ጭምር ሊያሳዩ ይገባል።የአባይ ግድብ የህልውናና የብልፅግና መሠረታችን ነውና!
አዲስ ዘመን ግንቦት 13/2012
ይቤ ከደጃች.ውቤ