ዛሬ በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ሙያ ታሪክ በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሰው፤የአስደናቂ ሰብዕና ባለቤት ከነበረው … ከጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ ፀሐፌ ተውኔት፣ ሠዓሊ፣ የታሪክ ፀሐፊ … ጳውሎስ ኞኞ አስገራሚ የሕይወት ጉዞ መካከል ጥቂቱን እንመለከታለን::
ጳውሎስ የተወለደው ኅዳር 11 ቀን 1926 ዓ.ም በቀድሞው የሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት፣ ቁልቢ አካባቢ ነው:: እናቱ ወይዘሮ ትበልጫለሽ አንዳርጌ ያወጡለት የመጀመሪያ ስሙ አማረ ነበር:: ቤተ ክርስቲያን አዘውታሪና መጽሐፍ ቅዱስ አንባቢ የነበሩት እናቱ፣ ከሰሙትና ካነበቡት የቅዱሳን ታሪክና ገድል ‹‹ጳውሎስ›› የተሰኘው ስም ስለሳባቸው አማረን ‹‹ጳውሎስ›› ሲሉ ሌላ ስም ሰጡት:: አባቱ ኞኞ የተባሉ ግሪካዊ መርከበኛ እንደሆኑና ልጅ እንዳላቸው ከማወቃቸው በዘለለ እንደአባት ማሳደግ፣ ተመላልሰው መጠየቅና እናቱንም መርዳት እንዳልቻሉ ታሪኩ ያስረዳል::
ዕድሜው 10 ዓመት ሲሞላው ወደ ትምህርት ቤት ገባ:: ይሁን እንጂ በእናቱ አቅም ማነስ ምክንያት ትምህርቱን ከአራተኛ ክፍል በላይ መቀጠል ሳይችል ቀረ:: ወይዘሮ ትበልጫለሽ ጳውሎስ ለአፍታም ቢሆን ከአጠገባቸው እንዲርቅ ስለማይፈልጉ በሄዱበት ቦታ ሁሉ ይዘውት ይንቀሳቀሱ ነበር:: የቅርብ ዘመዶቹ ትምህርቱን እንዲማር ወደ አዲስ አበባ መጥቶ ጥሩ ትምህርት ቤት እንዲገባ አድርገው የነበረ ቢሆንም እናቱ መልሰው ወደ ድሬዳዋ ወሰዱት::
ጳውሎስ ያቋረጠውን ትምህርቱን ለመቀጠል መላ ቢፈልግም ሳይሳካት ቀረ:: እናቱን ለመርዳትና ኑሮን ለማሸነፍ ልዩ ልዩ ሥራዎችን መሥራት ጀመረ:: እንቁላል፣ ጭራ፣ ሥዕል፣ ጋዜጣ … ይሸጥ ነበር:: ትምህርቱን ቢያቋርጥም ከማንበብና ከመፃፍ ግን አልተገለለም ነበር:: መንገድ ላይ ወድቆ ከሚያገኘው ጽሑፍ ጀምሮ መጽሐፍትን እየተዋሰ እስከማንበብ የደረሰ የንባብ ፍቅር ነበረው:: በዚህም ትምህርት ቤት ከሚያገኘው እውቀት ባላነሰ ሁኔታ ራሱን አስተማረ::
ስለዚህ ጉዳይ በአንድ ወቅት ሲናገር ‹‹ … ድሀ ነበርኩ:: በትምህርቴ በአስደናቂ ፍጥነት አራኛ ክፍል ደርሼ የምማርበት በማጣቴ አቋረጥኩ:: ከዚያም ወደ ሥራ ሄድኩ:: ትምህርቱ እንዲያውም ትንሽ ሲገባኝ መቀጠል አቃተኝ:: ክፍል ስለሚቆጠር ነው እንጂ ከተማሪ ቤት ከወጣሁ በኋላም ከትምህርቱ አልራቅሁም:: ራሴን በራሴ ማስተማሩን ቀጥዬበት ነበር:: መንገድ ላይ የወዳደቁ ጋዜጦችን አንስቼ ለማንበብና ለመረዳት እሞክራለሁ:: ፈረንጅና አረብ ቤት ስላክ እቃው ከተጋባ በኋላ ወረቀቱን አነባለሁ:: ያልገባኝን ነገር መንገደኛውን ሁሉ እጠይቃለሁ:: ከተማሪ ቤት ውጪ እንዲህ እየተፍጨረጨርኩ ነው ያወቅሁት:: የውጭ ቋንቋ በምናገርበት ጊዜ አላፍርም:: ነገሩ ሳይገባኝ ከቀረ ዝም ብዬ አላዳምጥም:: ግር የሚለኝ ከሆነ ‹ያ ያልከው ነገር አልገባኝም› እላለሁ:: ሁሌም እጠይቃለሁ …›› ብሏል::
በ17 ዓመቱ በእርሻ ሚኒስቴር የእንስሳት ሕክምና ክፍል የከብት መርፌ ወጊ ሆኖ ተቀጠረ:: በዚህ ሙያ ሐረርጌ ውስጥ ለሦስት ዓመታት ያህል ከሠራ በኋላ ወደ ደደር ሚሲዮን ሕክምና ማዕከል ተዛውሮ በመርፌ ወጊነት አገለገለ:: በዚያም ሳለ ከማንበብና ራሱን ከማሳደግ አልቦዘነም ነበር:: በ1946 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል ተቀጥሮ መሥራት ጀመረ:: የጋዜጣ ተሳትፎውን የጀመረውም በዚህ ወቅት ነበር::
ጳውሎስ ወደ ጋዜጠኝነት ሙያ ስለገባበት አጋጣሚ ተጠይቆ ሲመልስ ‹‹ … ጋዜጠኝነትን አላውቀውም፤ አልመኘውም ነበር:: በፊት ጋዜጣ፣ ሥዕል፣ ጭራ … እሸጥ ነበር:: ጋዜጣ ማንበብ ግን በጣም እወድ ነበር:: በ1948 ዓ.ም በምሠራበት መስሪያ ቤት ከደመወዛችን አበደሩንና ‹ልብስ ልበሱ› አሉን፤ለበስን:: በስድስት ወር ክፈሉ ሲሉን ከበደን:: ከዚያም ‹ሳንፈልግ አበድረውን ገንዘባችንን በሉን፤በቃሪያ ነው የምንዘልቀው› አልኩኝና ጽፌ ለማስታወቂያ ሚኒስቴር ላክሁኝ:: አሥመራ ውስጥ በሚታተም ጋዜጣ ላይ ወጥቶ አገኘሁት:: ደስ አለኝ:: ለካ እንደእኔም ዓይነት ሰው ቢጽፍ ይቀበላሉ ብዬ ተበረታታሁ:: በወቅቱ ከአንዲት ልጅ ፍቅር ያዘኝ፤ በጣም ፍቅር ያዘኝና ግጥም ጻፍኩ:: ስሟን ቁልቁል እንዲነበብ አደረግኩና እንዲህ ያሳበደችኝ እከሊት ነች፤ በእርሷ ፍቅር ተይዣለሁ ብዬ ጻፍኩ፤እሱም ወጣ:: በቃ ከዚህ በኋላ ሞራል መጣ …›› ብሎ ነበር::
በ1947 እና በ1948 ዓ.ም መደበኛ ሥራውን እያከናወነ በአዲስ አበባ እና በአሥመራ እየታተሙ በሚወጡ ጋዜጦች ላይም አልፎ አልፎ ጽሑፎችን በማቅረቡ የታዋቂነቱ ጅማሬ ሆነ:: በንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ 25ኛ የንግሥና ክብረ በዓል ሕትመቷን የጀመረችው ‹‹የኢትዮጵያ ድምፅ›› ጋዜጣ ስትቋቋም ጳውሎስ ምክር አዘል ቁም ነገሮችን እየፃፈ መሳተፍ ጀመረ:: በጋዜጣዋ ላይ መደበኛ ሥራ የጀመረው ጽሑፍ አራሚ ሆኖ ነው::
ውሎ አድሮ በሰፊው የማንበብ ባህሉ ያዳበረውን እውቀቱን ወደ ጋዜጣ ሲያወጣው ‹‹ጳውሎስ ማን ነው›› ተብሎ መጠየቅ ተጀመረ:: በተለያዩ ርዕሶችና በማራኪ አፃፃፍ በተከታታይ በጋዜጣዋ ላይ ያሳተማቸው ጽሑፎቹ አንባቢዎችን ማስደመም ተያያዙት::
ጳውሎስ ደፋር ጋዜጠኛ ነበር:: የወቅቱን የፖለቲካ ሁኔታ እየተጋፋ በድፍረት የሚጽፋቸው ጽሑፎቹ በየጊዜው ከሹማምንቱ ጋር ያጋጩት ነበር:: በሚደርሱበት ተፅዕኖዎችም ስለተሰላቸ ለማስታወቂያ ሚኒስትሩ ለደጃዝማች ግርማቸው ተክለሐዋርያት የምሬት ደብዳቤ ጽፎ ነበር:: ሚኒስትሩም ለጳውሎስ ጥያቄ ፈጣን ምላሽ ስለሰጡት ተረጋግቶ ሥራውን ቀጠለ:: የጋዜጣዋ የአማርኛው ክፍል ረዳት አዘጋጅ ሆኖ እንዲሠራም ተወሰነ:: ዜና፣ ሐተታና ርዕሰ አንቀጽ ይጽፋል፤ የሌሎችን ጽሑፎች ያርማል፤ የጋዜጣዋን ዲዛይን ይሠራል፤ ይተረጉማል:: በተፈጥሮ የታደለው የማስተባበር፣ የመቀስቀስና የማቀናጀት ችሎታው ጋዜጣዋ እጅግ በርካታ አንባቢ እንድታገኝና እርሱም ዝነኛ እንዲሆን አስችሏል::
ጳውሎስ እጅግ በርካታ አነጋጋሪ የሆኑ ጽሑፎችን አበርክቷል:: የካቲት 25 ቀን 1951 ዓ.ም በ ‹‹የኢትዮጵያ ድምፅ›› ጋዜጣ ላይ የወጣውና ‹‹ይድረስ ለእግዚአብሔር›› የሚለው ጽሑፉ አንዱ ነው:: ይህን መሰል የሽሙጥ ጽሑፎችን፣ ቀልዶችንና አጫጭር የምልልስ ወጎችን ከማቅረቡ ባሻገር ዜናዎችንና በጥናት ላይ የተመሰረቱ ሰፋፊ ሐተታዎችን ይጽፍ እንደነበር የቀድሞ ጋዜጦች ምስክሮች ይሆናሉ:: ጳውሎስ ከሌሎች ጋዜጠኞች ጋር በሃሳብ ይሟገት ነበር:: ለአብነት ያህል በመንግሥት ግብር አከፋፈል ላይ ከደራሲ ማሞ ውድነህ ጋር በጋዜጣዋ ላይ በብርቱ ተከራክረዋል::
በ1955 ዓ.ም የጋዜጣዋ ምክትል አዘጋጅ ሲሆን ጋዜጣዋ በርካታ ማሻሻያዎችን እንድታደርግ ጥሯል:: በጥቅምት 18 ቀን 1956 ዓ.ም ‹‹ዳቦ እንጂ ጥይት አንሻም›› በሚል ርዕስ ያሳተመው ጽሑፉ የአፍሪካን ብጥብጥና ሁከት ለሚሹ የምዕራብ አገራት ጥሩ መልዕክት የያዘ ሐተታ በማስፈሩ በነቃፊዎቹ ሹማምንት ጭምር ተወዶለት ነበር:: ጳውሎስ ጋዜጣዋ ተነባቢነቷ እንዲጨምር ያከናወናቸው ተግባራት ፍሬ አፈሩ:: የጋዜጣዋ ዕለታዊ ሕትመት ከ30ሺ በላይ ደረሰ:: ንጉሰ ነገሥቱም በጋዜጣዋና በ‹‹መነን›› መጽሔት መሻሻል በመደሰታቸው ‹‹ጅምራችሁ አስደስቶናል:: የኢትዮጵያ ሕዝብ ማንኛውንም ነገር ሲጀምር በኃይል ይነሳና በቶሎ ይበርዳል፤እናንተ ግን እንደዚያ እንዳትሆኑ:: ጅምራችሁን የበለጠ ለማድረግ ሞክሩ:: ወደ ኋላ እንዳትሉ በርቱ›› በማለት ለጳውሎስና ባልደረቦቹ ሽልማት ሰጡ:: ጳውሎስ ሌላ ተጨማሪ ሽልማት (የጽሕፈት መኪና) ተሸለመ::
ይሁን እንጂ ጳውሎስ የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ‹‹የኢትዮጵያ ድምፅ›› ጋዜጣ የተሻለ ተነባቢ እንድትሆን ማድረጉ ሌሎች ጋዜጦች (‹‹አዲስ ዘመን›› እና ‹‹የዛሬዪቱ ኢትዮጵያ››) በገበያ ፉክክር ውስጥ ፈታኝ ሁኔታ ገጠማቸው:: ይህ ሁኔታም ሹማምንቱን አስቆጥቶ ጳውሎስ የደንብ ልብስ አልብሶ ጋዜጣዋን እያዞሩ ይሸጡ የነበሩ ሰዎችን ለእስራት ዳረጋቸው:: ጳውሎስም ‹‹ሚኒስትሮቻችን ጋዜጣ ሻጮቻችንን እየያዙ ማሰር ጀመሩ›› ብሎ ዜና ጽፎ ስለነበር ዜናው እንዳይሰራጭ ተብሎ የጋዜጣዋ ሕትመት ታገደ:: በዚህ ምክንያትም በጋዜጣዋ አዘጋጆችና በሹማምንቱ መካከል ከፍ ያለ አለመግባባት ተፈጥሮ ነበር:: ይኸው አለመግባባትም ጋዜጣዋ በማስታወቂያ ሚኒስቴር ቁጥጥር ስር እንድትሆን አደረገ::
ጳውሎስ የ1956ቱን የኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት ሂደት በመዘገቡ የ10 አለቃነት ማዕረግን አግኝቷል:: ከሹማምንቱ ጋር የፈጠረው አለመግባባትና ‹‹የኢትዮ-ሶማሊያ ጦርነት ሂደትን ሲዘግብ በጦርነቱ የደረሰውን ጉዳት በፎቶ አስደግፎ በጋዜጣዋ ላይ ማተሙ ሰብዓዊነት የጎደለው ተግባር ፈፅሟል›› መባሉ ከ‹‹የኢትዮጵያ ድምፅ›› ጋዜጣ ጋር እንዲለያይ ምክንያት ሆኗል::
ቀጣይ ማረፊያው ‹‹አዣንስ ዲሬክሲዮን›› እና ‹‹የኢትዮጵያ የወሬ ምንጭ›› በሚባሉት የቀድሞ ስሞቹ ይታወቅ የነበረው የአሁኑ ‹‹የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት›› ሆነ:: የአዲስ አበባ ወሬዎች ማዘጋጃ ክፍል ኃላፊ ሆኖ ተመደበ:: በዚህ መስሪያ ቤትም መጠነኛ እፎይታን ማግኘት ቻለ:: ስሙ እንደቀድሞው በጋዜጣ ላይ ስለማይታይ ‹‹ጳውሎስ የት ሄደ?›› ብሎ የሚጠይቀው ሰው ብዙ ነበር:: እርሱም ሃሳቡን እንደልቡ መግለፅ ስላልቻለ ምቾት አልተሰማውም ነበር:: አንድ ዓመት እንኳ ሳይቆይ ወደ ‹‹አዲስ ዘመን›› ጋዜጣ ተዛወረ::
ጳውሎስ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ሥራውን የጀመረው የጋዜጣው ምክትል አዘጋጅ በመሆን ነበር:: ስለበርካታ ማኅበራዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች የመፃፍ ዕድልን እንደገና አገኘ:: ጳውሎስ በእጅጉ ከሚታወቅባቸው የጋዜጣ ሥራዎቹ መካከል በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ‹‹አንድ ጥያቄ አለኝ›› በሚል አምድ የሚያቀርበው ጽሑፉ አንዱ ነበር:: በዚህ አምድ ላይ ከአንባቢያን ለሚደርሱት ዘርፈ ብዙ የሆኑ በርካታ ጥያቄዎች በጥልቅ ንባብና በቀልድ እያዋዛ የሚሰጣቸው መልሶች ጋዜጣውን ተነባቢ፤ ጳውሎስንም ዝነኛና ተወዳጅ እንዲሆን አድርገውታል::
ጳውሎስ የፕሬስ ነፃነት እንዲከበር በተባ ብዕሩ ሞግቷል:: ይህ ተጋድሎውም ለማስፈራሪያ፣ ለዛቻና ለእንግልት ዳርጎታል:: እርሱ ግን ለዛቻውም ሆነ ለማስፈራሪያው ያልተበገረ ጠንካራ ባለሙያ ነበር::
ጳውሎስ ጋዜጠኛ ብቻ አልነበረም:: ደራሲና የታሪክ ጸሐፊም ጭምር ነበር:: በርካታ መፅሐፍትንና ትያትሮችንም ለአንባቢያን አበርክቷል:: ከመጽሐፍቱ መካከል ‹‹የሴቶች አምባ››፣ ‹‹አጤ ምኒልክ››፣ ‹‹አጤ ቴዎድሮስ››፣ ‹‹አስደናቂ ታሪኮች››፣ ‹‹የኢትዮጵያና የጣሊያን ጦርነት››፣ ‹‹አጤ ምኒልክ ከውጭ ሀገራት የተፃፃፏቸው ደብዳቤዎች››፣‹‹አራዳው ታደሰ››፣ ‹‹የኔዎቹ ገረዶች››፣ የጌታቸው ሚስቶች››፣ ‹‹ቅይጥ››፣ ‹‹ምስቅልቅል››፣ ‹‹እንቆቅልሽ››፣ ‹‹ድብልቅልቅ››፣ ‹‹እውቀት››፣ … ዋናዎቹ ናቸው::
ለሕትመት ከበቁት ሥራዎቹ በተጨማሪ፣ ያልታተሙት ሥራዎቹም በርካታ ናቸው:: ከእነዚህም መካከል ‹‹የአጤ ዮሐንስ ታሪክ››፣ ‹‹የአዲስ አበባ ታሪክ››፣ ‹‹የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ››፣ ‹‹ሰዎቹ››፣ ‹‹የልጅ ኢያሱ ታሪክ›› እና ‹‹አዜብ›› የሚሉት ይጠቀሳሉ::
ጳውሎስ ብዙ የሙያ ዓይነቶችን ከባለሙያዎቹ ባላነሰ መልኩ ያውቅና ይከውን እንደነበር የሚያውቁት ሁሉ ይመሰክሩለታል:: ከአማርኛ በተጨማሪ ሌሎች ቋንቋዎችንም ይናገር ነበር:: በመፅሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሰውና ከአስራ ሁለቱ ሐዋርያት መካከል አንዱ የሆነው የሐዋርያው ጳውሎስ መልዕክቶች በውስጡ ሰርፀው እንደቀሩ በተደጋጋሚ ተናግሯል:: በተለይም ‹‹ሁሉን እወቅ፤ የሚሆንህን ያዝ›› ለሚለው የሐዋርያው ጳውሎስ መልዕክት የተለየ ትኩረትና ፍቅር እንደነበረው ገልጿል:: ጳውሎስ ኞኞ ከትዳር አጋሩ ወይዘሮ አዳነች ታደሰ ያፈራውን ልጁን ስሙን ‹‹ሐዋርያው›› ብሎ በመሰየም ለሐዋርያው ጳውሎስ ያለውን ፍቅርና አድናቆት ገልጿል::
ግልፅነት፣ ድፍረት፣ ለወገን ደራሽነትና ጨዋነትም የጳውሎስ መገለጫዎች እንደነበሩ ብዙዎች ምስክር ናቸው:: በድርቅና በረሀብ ለተጎዱ እንዲሁም ጠያቂና ዘመድ ለሌላቸው ሰዎች ደራሽ መሆኑን አስመስክሯል:: ጳውሎስ የትዳር አጋሩንና ትዳሩን አክባሪ፣ ለታሪክና ለባህል ተቆርቋሪ፣ ለማኅበራዊ ሕይወት መጠንከር ልዩ ትኩረት የሚሰጥ ሰው ነበር:: የዳግማዊ አፄ ምኒልክ እና የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ አድናቂ እንደነበርም በተደጋጋሚ ተናግሯል::
‹‹እኔ መቼም አደንቀዋለሁ:: ከጉብዝናው የተነሳ አንበሳን የሚያህል አራዊት ቤቱ ውስጥ ያሳድግ የነበረ ሰው ነው … በአነጋገሩ፣ በአፃፃፉ ሁሉ ድንቅ ሰው ነው:: ሥራዎቹ ደስ ይላሉ፤ጽሑፎችን አነብለት ነበር … ወገን በተቸገረ ጊዜ ብዙ የደከመና የተሳካለትም ሰው ነው … ቀልድ አዋቂና ተግባቢም ነው … ጎበዝ እንደነበር ሊነገርለት ይገባል …›› የቀድሞው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ፡-
‹‹ … አቶ ጳውሎስን ያወቅሁት በየካቲት ወር 1952 ዓ.ም ነው:: በፊደል አራሚነት ተቀጥሮ ይሠራ ነበር … ረዳት ጋዜጠኛ አደረግሁት … ጳውስ ‹ሥራ› ተብሎ የተሰጠውን በጥንቃቄ አዳምጦ በጥንቃቄ የሚሠራ ሰው ነው:: ሙያው የሚጠይቀውን ሁሉ አሟልቶ ጥርት ያለ ሥራ ያቀርባል … በጽሑፎቹ ውስጥ ነገሮችን በጥልቀት መርምሮና በርብሮ ያሳያል … በሚያምንበት ካልሆነ በስተቀር በትዕዛዝ ሃሳቡን ማስለወጥ አይቻልም … ለሀገራችን ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያበረከተ ባለውለታ ነው … ጳውሎስ በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ታሪክ ውስጥ ሚናው ትልቅ ነው …›› ጋዜጠኛ፣ የታሪክ ጸሐፊና ዲፕሎማት አምባሳደር ዘውዴ ረታ፡-
ጳውሎስ በልዩ ልዩ ሙያዎቹ ለሠራቸው ተግባራት ከንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ እጅ የተቀበላቸውን ጨምሮ በርካታ ሽልማቶችን አግኝቷል:: ልጁ ሐዋርያው ጳውሎስ ሽልማቶቹንና አንዳንድ እቃዎቹን በ2005 ዓ.ም ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ማዕከል በስጦታ አስረክቧል::
በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ሙያ ታሪክ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ ፀሐፌ ተውኔት፣ ሠዓሊ፣ የታሪክ ፀሐፊ … ጳውሎስ ኞኞ፣ ባጋጠመው የእግር ሕመም ምክንያት በአገር ውስጥና በውጭ አገራት ሕክምናውን ቢከታተልም መዳን ባለመቻሉ ግንቦት 29 ቀን 1984 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል:: ስርዓተ ቀብሩም በርካታ አድናቂዎቹና ወዳጆቹ በተገኙበት በቀራንዮ መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ተፈፅሟል:: ለእውነት ሟች የነበረው ጳውሎስ፣ በመጨረሻዎቹ የእስትንፋሱ ቀናት እንኳ ‹‹እኔ እንደማልድን አውቀዋለሁ፤ ግን ብሞትም እውነት እየተናገርኩ ነውና ከሞትኩ ነፍሴ አትጨነቅም›› ብሎ ነበር::
አዲስ ዘመን ግንቦት 12/2012
አንተነህ ቸሬ