ባለዘርፈ ብዙው የኢንቨስትመንት ኩባንያ
ሥራውን የጀመረው ከዛሬ ሃያ ዓመታት በፊት በአገር ውስጥ ቡና ንግድ ነው።በዚሁ የቡና ንግድ ባካበተው ልምድ በ1998 ዓ.ም ቡናን ወደ ውጭ አገር በቋሚነት የሚልክ ኩባንያ ሆኖ ተመስርቷል።ቡናን ተከትሎ ቅመማ ቅመሞችን፣ የጥራጥሬ እህሎችን፣ የቅባት እህሎችን፣ ስጋና የቀንድ ከብቶችን ወደውጭ አገር መላክና ማሽነሪዎችን ከውጭ ሀገር ማስመጣት ጀምሯል።
በአሁኑ ወቅት ደግሞ በከፋና በጅማ ዞን ሁለት የቡና እርሻዎች ያሉት ሲሆን፤ በእነዚሁ የእርሻ መሬቶች ላይ መዋዕለ ነዋዩን በማፍሰስ በኢትዮጵያ የቡና ኢንዱስትሪ ስማቸው ገኖ ከሚነሱና የቡናን ቢዝነስ እያጧጧፉ ከሚገኙ ኩባንያዎች መካከል አንዱ ለመሆን በቅቷል።የቀንድ ከብት ወደ ውጭ ሀገራት የሚልኩና ከባድ ማሽነሪዎችን ወደ ሀገር ውስጥ የሚያስገቡ ሁለት እህት ካምፓኒዎችን በማቋቋምም የኢንቨስትመንት አድማሱን አስፍቷል- አልፎዝ ኢንቨስትመንት ግሩፕ።
ሼኽ አሊ ሁሴን የአልፎዝ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ባለቤትና ፕሬዚዳንት ናቸው።ተወልደው ያደጉት ጅማ ሊሙ ነው።የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እዛው ጅማ ተከታትለዋል።የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ከጅማ ቡናን በማስመጣትና በመሸጥ የንግዱን ዓለም ተቀላቀለዋል።ከዚሁ በተጓዳኝም ከሳኡዲ አረቢያ የመኪና እቃ መለዋወጫ በማስመጣት ማከፋፈል ጀመሩ።ቡናን እየነገዱና የመኪና መለዋወጫ እቃዎችን እያከፋፈሉ በተልእኮ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ከፓኪስታን ኢንስቲትዩት ኦፍ ማኔጅመንት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል።
ሼኽ አሊ በዚሁ የቡና እና የመለዋወጫ እቃዎች ንግድ ወደ ሳውዲ አረቢያ የመሄድ አጋጣሚ ይፈጠርላቸዋል። ከሳዑዲ አረብያ ወደ አገራቸው ሲመለሱ በአውሮፕላን ውስጥ ካጠገባቸው ተቀምጦ የነበረ አንድ የሳኡዲ ባለሃብት ተዋወቅው ማውራት ይጀምራሉ። የባለሃብቱ ፍላጎት ስጋን እያቀነባበሩ ወደ ውጭ አገር መላክ ነበር።ቢሆንም እርሳቸው ይህንን የንግድ ዘርፍ ባያውቁትም ሥራውን ሊሰሩት እንደሚችሉ በመተማመንና በድፍረት በጋራ ለመስራት ይወስናሉ።
ሥራውን በጀመሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ነግደው በጋራ ማትረፍ ቻሉ።ከሳኡዲው ባለሃብት ጋር ሁለት ዓመታትን በሸሪክነት ከሰሩ በኋላ እርሱ ሥራው ሌላ በመሆኑና አብሮ ለመስራት ባለመፈለጉ የተጀመረውን ሥራ ለብቻቸው በመሆን አስቀጠሉ።ይህም አጋጣሚ በንግድ ሥራቸው ከፍተኛ ለውጥ ያመጡበትና አልፎዝ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዛሬ ላይ ለደረሰበት የእድገት ደረጃ መነሻ ሆነ።
ከሁለት አሥርት ዓመታት በፊት 200 ሺህ ብር በሚሆን መነሻ ካፒታል የመሰረቱት አልፎዝ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በአገር ውስጥ በመቀጠልም ከሀገር ውጭ በቡና ንግድ ሥራውን ጀምሯል።ከወጪ ንግድ ገበያ ያገኘውን ልምድ በመጠቀምም ኢንቨስትመንቱን አስፍቶ ቅመማ ቅመሞችን፣ የጥራጥሬ እህሎችን፣ የቅባት እህሎችን፣ ስጋና የቀንድ ከብቶችን ወደውጭ አገር ወደመላክ ተሸጋግሯል።
በአሁኑ ወቅትም ከባድ ማሽነሪዎችን፤ ተሽከርካ ሪዎችንና የኮንስትራክሽን ማሽኖችን ከውጭ አገር በማስመጣት ለሀገር ውስጥ ገበያ እያቀረበ ይገኛል። በቅርቡም ገርጂ አካባቢ በ3 ሺ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ሁሉን አቀፍ ትልቅ የገበያ ሞል በመገንባት ለአገልግሎት ክፍት አድርጓል።በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ ሚካኤል አካባቢም የእንግዳ ማረፊያ አፓርትመንቶችን በመገንባት የሪልእስቴት ኢንቨስትመንት ዘርፉን ተቀላቅሏል።
ኩባንያው ቡናን እንደየሚልክባቸው አገራት ፍላጎት በራሱ በማዘጋጀትና ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ድርጅት በመግዛት የሚልክ ሲሆን፤ ለእዚህም በዓመት እስከ 30 ሺህ ቶን ቡና ማጠብና ማቀነባበር የሚያስችሉትን ሁለት ኢንዱስትሪዎች በአዲስ አበባና በድሬዳዋ አቋቁሟል።በተመሳሳይም ኩባንያው እንደደምበኞች ፍላጎት ስጋና የቁም ከብቶችን ወደ ውጭ አገራት የሚልክ ሲሆን ምርቶቹንም በአብዛኛው ወደ መካከለኛው ምስራቅ አገራት ይልካል።
የኩባንያው ምርቶች በእስያና በአውሮፓ አገራት ተፈላጊነት ቢኖራቸውም አገራቱ በሚጠይቁት የማስገቢያ ደረጃ ምክንያት ምርቶቹን መላክ አልቻለም።‹‹በተለይ በቻይና ምርቱ በብዛት የሚፈለግ በመሆኑ መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠትና ድርድር በማድረግ ምርቱ የሚላክበትን መንገድ ማመቻቸት ይኖርበታል›› ይላሉ፤ ሼክ አሊ።
የሪል እስቴት ኢንቨስትመንትን በሚመለከት ኩባንያው ገና ወደ ገበያው እየገባና እየተለማመደ ሲሆን፤ በቅርቡ ገረጂ አካባቢ በገነባው የገበያ ሞል አጠገብ ረጅም የመኖሪያ አፓርታማ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመገንባት እቅድ ይዟል።እያደገ የመጣውን የመኖሪያ ቤት ፍላጎትን ከግምት በማስገባት በቦሌ ሚካኤል አካባቢ በተመሳሳይ የመኖሪያ አፓርትመንት እየገነባ ይገኛል።‹‹ለሀገር የኢኮኖሚ ግንባታ ሊውል የሚችል ትልቅ የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት ዋነኛ ዓላማዬ ነው›› የሚለው፤ ኩባንያው በአሁኑ ወቅት ከሁለት ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ እድል ፈጥሯል።የካፒታል መጠኑም ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ይገመታል።
ሼኽ አሊ እንደሚሉት፤ ኩባንያው በርካታ ባለሃብቶች በአገራቸው ላይ የሥራ መቀዛቀዝ ቢኖርም ምርጫቸው እያደረጉ ያሉት ኢትዮጵያን በመሆኑ የአገሪቱ ኢንቨስትመንት በጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል።ይሁንና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንቱን ይበልጥ በማሳደግ ለዜጎች የበለጠ የሥራ እድል ለመፍጠር መንግሥት ጠንክሮ ሊሰራ ይገባል።በዚህ ወቅት የተከሰተው የኮሮና ወረርሽኝ በአጭር ጊዜ መፍትሄ የሚያገኝ ከሆነም ተቋርጦ የነበረው የአገሪቱ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ይበልጥ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይችላል።
‹‹በሌላም አገር ይሁን በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ውስጥ ጥቃቅን ችግሮች ምንጊዜም ያሉ ቢሆንም መነጋገር የሚገባው በትላልቅ ጉዳዮች ላይ ነው›› የሚሉት ሼኽ አሊ፤ በተለይ የመሬት አቅርቦት ላይ ከመንግሥት በኩል የሚታዩ ክፍተቶች በመኖራቸው ሊታረሙ እንደሚገባ ይገልፃሉ።ከኢንቨስትመንት ፍቃድ አሰጣጥ ጀምሮ ያሉ ሂደቶች በአሁኑ ወቅት እየተስተካከሉ በመምጣታቸው በኢንቨስትመንቱ በኩል መሻሻሎች እንዳሉም ይጠቁማሉ።ሆኖም ወደታች ሲወረድ አሁንም ችግሮች በመኖራቸው ሊስተካከሉ እንደሚገባ ያመለክታሉ።
በቅረቡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የኮሮና ወረርሽኝ በኩባንያው የቡና ንግድ ላይ በቀጥታ የፈጠረው ተፅእኖ እንደሌለና እንደውም ቀድሞ እንደሚሸጠው አሁንም ቡናን እየሸጠ እንደሚገኝ ሼኽ አሊ ይናገራሉ።አብዛኛው ሰው በቤቱ ሆኖ ቡናን በፊት ከሚጠጣው በበለጠ አዘውትሮ የሚጠጣ በመሆኑ የቡና ፍላጎት ከፍ እያለ እንደመጣም ይገልፃሉ።በመሆኑም ‹‹ከዚሁ ንግድ የሚገኘው የውጭ ምንዛሪም እየተሻሻለ እንጂ እየቀነሰ አልመጣም›› ይላሉ።በተመሳሳይ የቁም ከብትና የስጋ ንግዱም ልክ እንደቡናው ባይሆንም መርከቦች ሥራቸውን በማቆማቸውና በመዳረሻ አገራት አካባቢ ያለው የሎጀስቲክ ሁኔታ አስቸጋሪ በመሆኑ ልክ እንደ በፊቱ በፍጥነት መላክ እንዳልተቻለም ያስረዳሉ።
አልፎዝ በተለያዩ ዘርፎች ከሚያከናውናቸው የኢንቨስትመንት ሥራዎቹ ጎን ለጎን ታዲያ ባለፉት ሃያ ዓመታት ውስጥ ልዩ ልዩ ማህበራዊ ኃላፊነቶችን ሲወጣ ቆይቷል።ሀገራዊ ጥሪዎች ሲቀርቡም በግምባር ቀደምትነት ተሰልፏል።በገጠር ድልድዮችን በመስራት፣ የንፁህ መጠጥ ውሃ በማቅረብ፣ መንገዶችን በመገንባትና በሌሎች የልማት ሠራዎች ላይ በመሳተፍ የበኩሉን አስተዋፅኦ አበርክቷል።ለአባይ ግድብ ግንባታም አስር ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል።
በተጨማሪም ኩባንያው በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙ በኑሮ ደረጃቸው ዝቀተኛ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች በልዩ ልዩ መልኩ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።በቅርቡም በባሌ ድሬ ሼኽ ሁሴን አካባቢ ለሚገኙ ተረጂዎች ድጋፍ አድርጓል።የኮሮና ቫይረስ በአገሪቱ መከሰቱን ተከትሎም አንድ ሺህ የህክምና አልባሳትን በመግዛት ለኦሮሚያ ክልል አስረክቧል።
በቀጣይም አልፎዝ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በኢንዱስትሪው ዘርፍ በመግባት ለመስራት እቅድ የያዘ ሲሆን፤ በተለይ ከውጭ ባለሃብቶች ጋር በመሆን በኤሌክትሪክ የሚሰሩ መኪናዎችን ገጣጥሞ ለገበያ ለማቅረብ አቅዷል።ይህን እቅድ ለማስፈፀም ሂደት ላይ የነበረ ቢሆንም በተከሰተው የኮሮና ወረርሸኝ ምክንያት ለጊዜው ሥራውን አቋርጧል።ይሁን እንጂ የኮሮና ቫይረስ በቀጣይ መፍትሄ የሚያገኝ ከሆነ ይህን እቅዱን ይፈፅማል።
የኩባንያው ባለቤትና ፕሬዚዳንት ሼኽ አሊ ሁሴን፤ ‹‹በዘርፈ ብዙ የኢንቨስትመንት ሥራዎች ውስጥ በመሳተፍና ገንዘብ በመስራት ለስኬት በቅቻለው›› ይላሉ።ይሁን እንጂ በስኬት ሂደት ውስጥ ሁሉ ‹‹ተመስገን›› ማለት እንደሚገባም ይናገራሉ።በሌላ በኩል ደግሞ ‹‹በቃኝ ብሎ መቆም ሳይሆን ገና ብዙ መስራት ይቀረኛል›› ብሎ ወደፊት መቀጠል እንደሚገባ በማስታወስ፤ እስካሁን በንግድ እንቅስቃሴያቸው ያካበቱት ልምድ በቀጣይ ለሚገቡባቸው ሌሎች የኢንቨስትመንት ሥራዎች ጥርጊያ መንገዱን እንዳመቻቸላቸውም ያስረዳሉ።
‹‹ለዚህ ስኬት ያበቃኝ ትልቁ ምስጢር በንግድ አለም ውስጥ ደፋርና ወሳኝ መሆኔ ነው›› የሚሉት ሼኽ አሊ፤ በተለይ በእያንዳንዱ የንግድ እንቅስቃሴ የተሻለ ውሳኔዎችን ማሳለፍ መቻላቸው ወደቀጣዩ የስኬት ምእራፍ ለማለፍ ትልቁን ሚና እንደተጫወተላቸው ያስረዳሉ።ለዚህም ያለገደብ ሥራን ማዘጋጀት፣ ጠንክሮ መስራትና ቆራጥ መሆን እንደሚገባ ይጠቁማሉ።ሥራን ለነገ ማሳደር እንደማይገባና ከተቻለ ዛሬን ሰርቶ ነገን ለሌላ ሥራ ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ያሳስባሉ።
ሙሉ ጊዜያቸውን በሥራ እንደሚያሳልፉ የሚናገሩት ሼኽ አሊ፤ በንግድ ከአውሮፓውንና ከአረቦች ጋር እንደሚሰሩ ይጠቅሳሉ።ታታሪነትና ታማኝነት ደግሞ ከሁሉ በላይ የስኬት ቁልፉ መንገድ መሆኑንም ይጠቁማሉ።ለታማኝነት ትልቅ ዋጋ ከመስጠታቸው የተነሳም ለአንድ ታማኝና ታታሪ ሰራተኛቸው ቤት ገዝተው እስከመሸለም እንደደረሱ ይገልፃሉ።ሁሌም ቢሆን ህጋዊ መንገዶችን ተከትለው በመስራታቸው ለተጨማሪ ስኬት መብቃታቸውንም ያስረዳሉ።
በተመሳሳይ ሌሎች ሰዎችም በልዩ ልዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ላይ በመሳተፍ ለስኬት መብቃት ከፈለጉ አብረው የሚሰሯቸውን ሠራተኞች ጓደኛ አድርገውና ከእነርሱ ጋር አብረው በመስራታቸው ስኬት እንደመጣ አውቀው መስራትና ፍቅርና የተሻለ ግንኙነት መፍጠር እንዳለባቸው ይመክራሉ።ታትረው፣ ጠንክረውና ታማኝ ሆነው የሚሰሩ ሠራተኞችንም ሁሌም ማበረታታትና መሸለም እንደሚገባም ይጠቁማሉ።
ራስን ካለአስፈላጊ ሱሶችና ሌሎችም ጎጂ ነገሮች በማራቅ በሥራ ላይ ብቻ ማተኮር እንደሚገባቸውና ይህን ማድረግ የሚችሉ ከሆነም ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ይገልፃሉ።ውጤቱ ዛሬ ባይመጣም እንኳን ነገ ሊመጣ እንደሚችል በማሰብ ሥራን በትጋት መስራት እንደሚገባም ያመለክታሉ።በንግድ ዓለም ውስጥ ዛሬ ትርፍ ካለ ነገ ደግሞ ኪሳራ ሊያጋጥም እንደሚችል ከግምት ውስጥ በማስገባት መስራት እንደሚያስፈልጋም ይናገራሉ።‹‹አእምሮን ሁሌም ለሥራ ዝግጁ ማድረግ ከተቻለ ውጤት ማምጣት ይችላልም›› ይላሉ።
እንደ ሼኽ አሊ ያሉ ታላላቅ አልሚዎች ዛሬ ላይ ለስኬት ሊበቁ የቻሉት የወጣትነት ጊዜያቸውን በሥራ በማሳለፋቸው፣ ገንዘባቸውንና ጊዜያቸውን በአግባቡ በመጠቀማቸውና ድፍረት የታከለበትና የተሰላ ውሳኔዎችን በሥራቸው በማሳለፋቸው ነው።ታዲያ እነዚህ አልሚዎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አገራቸውንና ዜጎቻቸውን እየጠቀሙ የሚገኙ በመሆናቸው በልዩ ልዩ የኢንቨስትመንት መስኮች መሰማራት የሚፈልጉ ሌሎች ዜጎችም የእነርሱን አርአያ ሊከተሉ ይገባል።
መንግሥትም ህጋዊ መንገድን ተከትለው ለሀገርና ለዜጎች ጠንካራ ሥራን ሰርተው ለማለፍ የሚታትሩ አልሚዎችን ሊደግፍና ሊያበረታታ ይገባል።እኛም ሼኽ አሊ ሁሴን እያከናወኗቸው ባሉ ልዩ ልዩ የኢንቨስትመንት ሥራዎች ለአገር ኢኮኖሚ እያበረከቱ ያሉትን አስተዋፅኦ እያደነቅን በቀጣይም ሥራዎቻቸውን በማጠናከርና በሌሎች የኢንቨስትመንት ሥራዎች ላይ በመሳተፍ አገርንና ህዝብን እንደሚጠቅሙ ያለንን ተስፋ እየገለፅን ቀጣይ የሥራ ዘመናቸው ስኬታማ እንዲሆን ተመኘን።ሰላም!
አዲስ ዘመን ግንቦት 11/2012
አስናቀ ፀጋዬ