የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ድሞክሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት የኢኮኖሚ ልማትን በተመለከተ አንድ መሰረታዊ አላማ አስቀምጧል።ይህም ህዝቡ በየደረጃው ተጠቃሚ የሚሆንበት፣ አገሪቱን ከተመጽዋችነት የሚያላቅቅ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገት በማረጋገጥ በአገሪቱ የዳበረ የነጻ ገበያ ኢኮኖሚ ስርዓት እንዲኖር ማድረግ ነው።
ይህ መሰረታዊ አላማ አራት ገጽታዎች ያሉት ነው። በመጀመሪያ ደረጃ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ማረጋገጥን በመሰረታዊ አላማነትና መነሻነት የያዘ ነው። የዚህን ኢኮኖሚ አላማ ሁለተኛው ገጽታ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ከማረጋገጥ ባሻገር ህዝቡ በላቀ ደረጃ ተጠቃሚ የሚሆንበት ሁኔታ እውን ለማድረግ ማስቻል ነው። ሶስተኛው የኢኮኖሚ ዓላማ አገሪቱ ከተመጽዋችነት ማላቀቅ እና በዓለም አቀፍ ኢኮኖሚያዊ ትስስሰር ውስጥ ደረጃዋ በቀጣይነት እየተሻሻለ እንዲሄድ ማድረግ እንደሆነ እሙን ነው።በአራተኛ ደረጃ ደግሞ ከላይ የተጠቀሰው ባህሪ ያለው ፈጣን እድገት በአገሪቱ የዳበረ ገበያ ኢኮኖሚ በመገንባት እውን እንዲሆን ማድረግ ነው።
ይህ መሰረታዊ የኢኮኖሚያዊ ልማት አላማ ተግባራዊ ለማድረግ የተሟላ የገጠር ልማት ራዕይና ይህንኑ የማስፈጸም አንቅስቃሴ መኖር ይኖርበታል። በገጠር በአሁኑ ሰዓት የሚካሄደው እና መካሄድም የሚገባው ነው። ይሁንና በገጠር ከግብርና ስራ ውጪ ሌላ የልማት እንቅስቃሴ አይኖርም ማለት አይደለም። ራሱን የግብርና እንቅስቃሴውን ለማሳካት ሰፊ መሰረተ ልማት እና የማህበራዊ ልማት እንቅስቃሴ መካሄድ አለበት።በግብርና ልማት ላይ ተመስርቶ ሰፊ የንግድ እና የኢንዱስትሪ ልማት አንቅስቃሴም ሊካሄድ ይችላል፤ ይገባልም። በመሆኑም የገጠር ልማት ስራ ማዕከሉን ግብርና ስራ ላይ ብቻ ያልታጠረ የልማት እንቅስቃሴ መሆን ይገባዋል።
ማዕከሉ ግብርና ያደረገ የገጠር ልማት እንቅስቃሴ፣ የተነደፈው የኢኮኖሚ ልማት መሰረታዊ አላማ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል አንድ የስራ መስክ ነው።መሰረታዊ የኢኮኖሚ ልማት ዓላማን ተግባራዊ ለማድረግ በሌሎች የስራ መስኮች ከፍተኛ ርብርብ የሚጠይቅ መሆኑ ግልጽ ነው።ግብርና መር የኢንዱስትሪው ልማት ስትራቴጂ እየተባለ የሚገለጸው የገጠርና ግብርናን ማዕከል የልማት እንቅስቃሴን መሪ መሆን ለማሳየት መሆኑ የሚታወቅ ነው።
ግብርና ለአለም ኢኮኖሚ እድገት ዋነኛና ወሳኝ የሆነ ዘርፍ ነው። ያለ ግብርና የሰው ልጅ ህልውና ቀጣይነት አይኖረውም። በዚህም ምክንያት የአለም ሃገራት ያላቸውን አቅም ሁሉ አሟጠው የግብርናውን ሴክተር ለማዘመንና ምርትን በሚፈለገው መጠን ለማቅረብ ከላይ እታች እያሉ ይገኛሉ። ከዚህም አልፎ ጥቂት የማይባሉ ሃገራት ከራሳቸው ፍጆታ ተርፎ ምርታቸውን ለሌሎች በማቅረብ የኢኮኖሚ አቅማቸውን በውጭ ንግድ ሲገነቡ ይስተዋላል። ኢትዮጵያም ከነዚህ ሃገራት ባልተናነሰ መልኩ ለግብርና አስፈላጊ የሆኑ የተፈጥሮ ሀብቶች የታደለች ቢሆንም የምርት አቅሟ ግን ለአገር ውስጥ ፍጆታም የሚበቃ አልሆነም።
የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር በድረ ገጹ ባወጣው ሪፖርት በኢትዮጵያ ውስጥ የከርሰ ምድር ውሃን ሳይጨምር ወደ 123 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር የሚጠጋ የውሃ ሀብትና ከ36 ሚሊየን ሄክታር በላይ ሊለማ የሚችል መሬት እንዳለ ጥናቶች ያመላክታሉ። እነዚህ የተፈጥሮ ሀብቶች ሃገሪቱ የምትፈልገውን ሰብል በተለያዩ አካባቢዎች ለማምረት እንድትችል እድል ይፈጥራሉ። ነገር ግን መረጃዎች እንደሚያመላክቱት በሰብል የለማው የአገሪቱ መሬት 16 ሚሊየን ሄክታር ገደማ ያህል ብቻ ነው። ከዚህ ውስጥም በመስኖ ልማት የለማው መሬት 1.1 ሚሊየን ሄክታር ያህሉ ነው።
በዘመናዊ መንገድ ቢለማ ኢትዮጵያም እንደሌሎቹ የዓለም አገራት ህዝቦቿን ከመመገብ አልፋ አንዱ የገቢ ምንጯ ይሆን ነበር።ነገር ግን ምንም ዘመናዊ የግብርና መሳሪያም እውቀትም በሌለበት በተፈጥሮ እውቀቱ ነጭ ወዙን ጠብ አድርጎ የአቅሙን ያክል ሲከውን የነበረው ደግሞ አርሶ አደሩ ነበር።
አገሪቱ ያላት የተፈጥሮ ሀብትም ሆነ ማዕድናት ያለ ዘርፉ ተዋናይ ከንቱ ነው፤አርሶ አደሩ ዋላ ቀር በሆነ የአተራረስ ዘዴ እስከ አሁን የቻለውን የሚችለውን ሲያደርግ ቆይቷል።ታዲያ ይህ ክንደ ብርቱ አርሶ አደር ለአደጋ የሚዳርጉ ከፊቱ የተጋረጡ እየተከሰቱም ያሉ አያሌ ችግሮች አሉ። ከእነዚህም መካከል የተፈጥሮ አደጋ ማለትም ወረርሽኝ፣የዝናብ እጥረት፣አንበጣ፣ ጎርፍ… ጥቂቶቹ ናቸው።በዚህም ወቅት እነዚህ ችግሮች አንዳንዶቹ ሲከሰቱ አንዳንዶቹ ደግሞ ቀን እየጠበቁ ነው።ስለሆነም እነዚህን ተግዳሮቶች ተቋቁሞ አርሶ አደሩ ህይወቱን እንዲመራ ድጋፍ ያስፈልገዋል።የተለያዩ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በቀጣይ ወራት በአገሪቱ የተለያዩ ቦታዎች የጎርፍ አደጋ ሊከሰት እንደሚችል ተጠቅሷል።ይህንን አደጋ ለመከላከል እና ከተከሰተም በአግባቡ ለመቆጣጠር የጉዳቱንም መጠን ለመቀነስ ምን እየተሰራ እንደሆነ የሚመለከተውን ተቋም አነጋግረናል።
ዝግጅት
አደጋ እና ስጋት በመጠቆም በመከላከል እና ሲከሰትም በመደገፍ የሚታወቅ ተቋም ነው በብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን፤ የኮምሽኙ የመጀመሪያ ስራው እንደ ጎርፍ ያሉ የተፈጥሮ ስጋት ያለባቸውን አካባቢዎች በመለየት ለህብረተሰቡ መረጃ ማድረስ ነው ያሉት አቶ ደበበ ዘውዴ በብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ናቸው።እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ በተለያዩ የጎርፍ ግብረ ሐይል በማቋቋም የቅድመ መከላከል ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።ከዚህም በአሻገር ህብረተሰቡም በግሉ ጥንቃቄ እንዲያደርግ መንገር ያስፈልጋል፤ ይህንንም ለማድረግ በስልክ መድረስ የተቻለውን በስልክ፤ ይህ ሊደርሰው ለማይችለው የህብረተሰብ ክፍል ደግሞ በደብዳቤ፣ ባህላዊ ሁኔታዎችን በመጠቀም ግንዘቤ እንደሚሰጥ ገልጸዋል።
በጎርፍ ወቅት የመሬት መንሸራተት፣ የመሬት መሰንጠቅ በላይ በስምጥ ሸለቆዎች አካባቢ እንደሚታይ የሚገልጹት አቶ ደበበ እነዚህን ለመከላከል የመጀመሪያ ጉዳይ ህብረተሰቡን በመረጃ ብቁ ማድረግ ነው ይህም ህብረተሰቡ በቂ መረጃ ከያዘ የተባለው ቦታ አደጋ ቢያስተናግድ እንኳ የሚደርሰውን ከፍተኛ ጉዳት ማቆም ባይቻልም ጉዳቱን ግን መቀነስ እንደሚቻል አስገንዝበዋል። ሌላኛው የጎርፍ መከላከያ ሊሆኑ የሚችሉ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ገልጸዋል።አደጋው ከተከሰተም በኋላ አደጋው የበለጠ ጉዳት እንዳያደርስ በአደጋው ቦታ ላይ ተግኝቶ ስራ እንደሚሰራም አስታውቀዋል።
የጎርፍ መከላከያ መዋቆሮችን ማጠናከር ያስፈልጋል ያሉት ዳይሬክተሩ መዋቅሮቹም በአደረጃጀት የሚመጡ እንደሆኑ ጠቅሰው ይህም ውሃዎችን የመገደብ የእርከን እና የተፋሰስ ስራዎች ለመስራት ያግዛል ብለዋል።
የደረሱ አደጋዎች
በኢትዮጵያ የአደጋ ክስተቶች የመጀመሪያ ደረጃ ድርቅ ሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ጎርፍ ነው፤ ጎርፍ ከፍተኛ አደጋ እና ጉዳት እንደሚያስከትል ይታወቃል ያሉት አቶ ደበበ ዘውዴ በብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ናቸው። የረጅም ጊዜ መረጃዎች አንደሚያመለክቱት በበልግና በመኸር ወቅት ጎርፍ ይከሰታል፤ ይህ ጎርፍ ብዙ ጊዜ የሚከሰተው ከመደበኛ በላይ ዝናብ ሲጥል ነው፤ ይህ ደግሞ ምንም ጥርጥር በሌለው መልኩ የአለም አቀፉ ንብረት ለውጥ እየተዛባ በሄደ ቁጥር ኢትዮጵያም ላይ ወቅቱ ተከትሎ ከመደበኛ በላይ የሚጥለው ዝናብ ጎርፍ ያስከትላል ብለዋል።
በጎርፉ መከሰት ምክንያት ደግሞ የመሬት መንሸራተት፣ የመሬት መሰንጠቅ እንዲሁም የመሬት መናድ ሁሉ ይከሰታል፤ አንደ ዳይሬክተሩ ገጻ በአብዛኛው የጎርፍ አደጋ የሚከሰተው በሚያዝያ ወር ነው፤ እንደሚታወቀው በተለይ በድሬዳዋ፣ በደቡብ ክልል በመሳሰሉ ቦታዎች ከፍተኛ ዝናብ ጥሎ ጎርፍ በመከሰቱ ከፍተኛ ጉዳት ማስከተሉን ጠቅሰዋል።
ሚያዝያ 16 ድሬዳዋ ላይ የተከሰተው ጎርፍ ለ4 ሰዎች ህይወት መጥፋት ምክንያት ሆኗል። 53 ቤቶችም ሙሉ ለሙሉ ውድመዋል። 212 ቤቶች ላይ ደግሞ በከፊል ጉዳት ደርሷል። 17 ቀበሌዎች ላይ የሚኖሩ 397 አባወራዎች 1985 ቤተሰብ ለምግብ ዕጥረት ተጋልጠዋል።እንዲህ ያለው አደጋ በድሬዳዋ ብቻ ሳይሆን በደቡብ ክልልም እንደተስተናገደ የሚናገሩት አቶ ደበበ ደቡብ ለግብርና የበልግ ዝናብን 60 ከመቶ የሚጠቀም ነው።እንዲዚህም ሆኖ በክልሉ አንዳንድ ቦታዎች በደረሰ አደጋ በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት አስከትሏል።
በሶማሊያ ክልልም እንዲሁ አስራ አምስቱን ቀበሌዎች ላይ የጎርፍ አደጋ ደርሷል። በዚህም ምክንያት 34 ሺ 577 ሰዎች ጉዳት ደርሶቧቸዋል።በተጨማሪም በአርሶ አደሩ ማሳ ላይም ጉዳት አደርሷል።ይህም ከ3 ሺ በላይ በሆነ ሄክታር ላይ የተዘሩ የሽንኩርት፣ በቆሎ፣ ሰሊጥ ሙሉ በሙሉ አውድሟቸዋል።ከ200 የሚበልጡ የውሃ ማጠጫ ሞተሮችም በጎርፍ ተወስደዋል።1 ሺህ 200 በላይ የሆኑ የቀንድ እና የጋማ ከብቶች ላይ እንዲሁ ጉዳት ደርሷል።
እንደዚህ ያሉ መረጃዎችን በብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የሚያገኘው አንደኛው ከብሔራዊ ሜትሪዎሎጂ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከውሃ ኤሌክትሪክ ሚኒስትር መስሪያ ቤት እና ከተፋሰሶች ባለስልጣን እንደሆነ ጠቅሰዋል።
ከብሔራዊ ሜትሪዎሎጂ በተገኘው መረጃ መሰረትም በግንቦት ወር ከበልግ ተጠቃሚ ከሆኑ ክልሎች በተጨማሪ በደቡብ ምዕራብ፣ በምዕራብ፣ በሰሜን ደቡብ ምስራቅ ባሉ ተፋሰሶች ላይ ዝናብ እየተስፋፋ ነው በሚል የትንበያ መረጃዎች ስለሚጠቁሙ አብዛኛው ኦሞ ግቤ፣ ስምጥ ሸለቆ፣ የላይኛው አዋሽ፣ የላይኛው እና መካከለኛው አባይ፣ ተከዜ እንዲሁም የዋቢ ሸበሌ ከፍተኛ እርጥበት እንደሚያገኙ ይጠበቃል።በተለይ በአንዳንድ ተፋሰሶች ላይ ከባድ እርጥበት እንደሚኖር ስለተጠቆመ በአሆንታዊ ጎኑ የወራጅ ውሃ ስለሚጨምር የግድቦች ውሃ ለማቆም እና እንዲህ ያሉ ስራዎችን ለመስራት አስተዋጽኦ ይኖረዋል።
ስጋት
እንደ አቶ ደበበ ዘውዴ በብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ገለጻ በመጪው ሁለት እና ሶስት ወራቶች የጎርፍ ስጋት ይኖርባቸዋል ተብሎ የተተነበየባቸው የተለያዩ ዞኖች እና ክልሎች አሉ፤ ከእነዚህም መካከል ጋምቤላ፣ ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ሶማሌ፣ አፋር ትግራይ፣ ደቡብ ብሔርብሔረሰቦች እና ህዝቦች፣ ድሬዳዋ፣ ሐረሪ፣ አዲስ አበባን ጨምሮ የጎርፍ ስጋት ያለባቸው ናቸው።
ድጋፎች
ኮሚሽኑ አንዱ እና ዋነኛውም ስራው ይህ ነው፤ አንደኛው አደጋው እንዳይከሰት ማድረግ ሲሆን ሌላኛው ከተከሰተ ደግሞ ተጎጂዎችን የተለያዩ አቅርቦቶችን ይቀርባሉ።እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ በመንግስት በኩል ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁነት እንዳለ ጠቁመዋል።
ይህ የተፈጥሮ ችግር ቢከሰት ምግብን ጨምሮ የተለያዩ ቁሳቁሶች ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁነቱ እንዳለ የጠቆሞት አቶ ደበበ እንደማሳያም ድሬዳዋ በደረሰው አደጋ ድጋፍ ተደርጓል ብለዋል።እንደዳይሬክተሩ ገለጻ ችግሩ እንደደረሰ ክልሉ ለፌዴራል መንግስት እንዳሳወቀ ኮሚሽኑ ወዲያው የድጋፍ ምላሽ የሚሰጥበት ሂደት እንዳለ ገልጸዋል።
እንደ አቶ ደበበ ገለጻ የህብረተሰቡን ማህበራዊ እሴት በመጠበቅ ማለት እንደ ዕድር የአገር ሽማግሎች እና ሌሎችን በመጠቀም ህብረተሰቡን ማስተማር ማስቀደም ያስፈልጋል ብለዋል።ለዚህም ይላሉ ከዚህ በፊት በየቦታው የተከሰቱ ግጭቶች እንኳ እንዲረጋጉ የሆኑት የህግ የበላይነትን በማስጠበቅ ብቻ ሳይሆን ባህላዊ መንገዶች በተከተለ መልኩ በተሰራው ስራ ነው፤ስለዚህም እነደ ጎርፍ ያሉ ተፈጥሯአዊ ችግሮችም ይህን መንገድ መከተል አዋጭ መሆኑን ገልጸዋል።
እንዲህ ያሉ የተፈጥሮ አደጋዎች ዓመቱን ሙሉ አርሶ አደሩ የለፋበትን የደከመበትን ገደል የከተቱት ክስተቶች ናቸው።ስለዚህም እንደ በጎርፍ ባሉ የተፈጥሮ አደጋዎች የአርሶ አደሩ ህይወት እንዳይጨልም ሁሉም ህበረተሰብ ክፍል በተለይ በዚህ ወቅት ሊረባረብ ይገባል ብለዋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 10/2012
አብርሃም ተወልደ