በአንድ ወቅት በአንድ መንደር ውስጥ የሚኖር አንድ ፈረስ ነበር። ከዕለታት በአንዱ ቀን ፈረሱ በጣም ብዙ ምግብ ይመገብና ከርሱ (ሆዱ) ከመጠን በላይ ስለሞላ ለመንቀሳቀስ ይቸገር እና አንድ ሜዳ ላይ ዝርግትግት ብሎ ይተኛል። ፈረሱ ዝርግትግት ብሎ መተኛቱን ያዩ አሞራዎች ፈረሱ የሞተ መስሏቸዉ ወደ ፈረሱ ተጠግተው ፈረሱን ለመብላት ሲሞክሩ ፈረሱ ከአንገቱ ቀና ብሎ አሞራዎችን ምን እያደረጋችሁ ነው ብሎ ይጠይቃቸዋል። በዚህ ጊዜ አሞራዎቹ በጣም ተደናግጠው ምን ቢሉ ጥሩ ነው፤ ታመሀል ስለተባለ ልንጠይቅህ ነው የመጣነው ብለው መለሱ። ፈረሱም ሊበሉት እንደመጡ በመረዳቱ እ.ህ.ህ.ህ ብሎ ጭንቅላቱን ነቀነቀ ይባላል።
ከዚህ ጊዜ በኋላ የፈረስ ጩኸት እ.ህ.ህ.ህ ሆኖ ቀረ ይባላል። በዚህ ወቅት ይህን ተረት ያስታወስኩት በኢትዮጵያ ያሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም የኢትዮጵያ ሕዝብ በችግር ውስጥ ባለበት ወቅት ፀጥ ብለው ኖረው ልክ እንደ አሞራዎች ሁሉ ለመብላት ሲሆን ከዚያም ከዚህም ተሰባስባችሁ ስለምርጫ ይህን ያክል ስትፋለሙ ሲታይ የኢትዮጵያም ሕዝብ እ.ህ.ህ. ማለቱ ትውስ ብሎኝ ነው።
«ኮሶ ሲጠጡ ስቅጥጥ ወተት ሲጠጡ ሽምጥጥ» ይህ አባባል በእውነት በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ያሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን በትክክልና ሳያዛንፍ የሚወክል ይመስለኛል። ምክንያቱም በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ያሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ለሥልጣን ሲሉ በቅድመ ኮሮና በነበሩ ጊዜያት የማይደረግ እያደረጉ፤ የማይባል እያሉ፤ ራሳቸውን እንደ አበባ ማለትም ተቀሳሚ፤ እንወክለዋለን የሚሉትን ሕዝብ እንደ ንብ ማለትም ቀሳሚ አድርጋችሁ በመሳል በየሚዲያው እኛ ከሌለን ይህ ሕዝብ አደጋ ላይ ነው ስትሉ እንዳልነበር፤ ምነው ኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ ችግር ሲያጋጥማት መደረግ ያለበትን ማድረግ ለምን ተሳናችሁ? ኢትዮጵያን አለንሽ የምትሏት ወተት በምትታለብበት ወቅት ብቻ ነው እንዴ? ምነው ሀገራችሁ ችግር በገጠማት ጊዜ የሀገራችሁን ችግር ለመካፈል እና የሀገራችሁን ችግር ለመጋፈጥ ፈራችሁ? ኢትዮጵያ በተቸገረች ወቅት ማለትም በኮሮና ወረርሽኝ እየተፈተነች ባለችበት ጊዜ ብዙ ኢትዮጵያውያን የኮሮና ስጋት አንዣቦባቸውም የዕለት ጉርሳቸውን ለማግኘት ለቫይረሱ ተጋላጭ ሆነው እየሰሩ እያያችሁ በገንዘብ እንኳን መደገፍ ቢያቅታችሁ ምነው የመፍትሄ ሀሳብ እንኳን ማቅረብ ተሳናችሁ?
በአጠቃላይ ሀገራችን በቫይረሱ ምክንያት ፈርጀ ብዙ ፈተና ሲያጋጥማት የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ ቢያቅታችሁ እንኳን እንዴት በሀሳብ እንኳን ከመንግሥት ጎን መቆም ተሳናችሁ? የኮሮና ቫይረስንም ለመከላከል የፖለቲካ አመለካከትን ይጠይቃል እንዴ? ኢትዮጵያዊ መሆን በቂ አይደለም እንዴ? ስለ ምርጫ ሲነሳ ግን ምነው የሕዝብ ልጅ ለመሆን ጣራችሁ? እውነት ለመናገር ብዙ ኢትዮጵያውያን ማዘን ብቻ አይደለም አፍረንባችኋል። ምክንያቱም ሕዝቡ በኮሮና ሲፈተን እና ስጋት ውስጥ ሲወድቅ ድምፃችሁን አጥፍታችሁና እንደ ክረምት እባብ ተኝታችሁ መኖራችሁን እንኳን እስከምንጠራጠር ጠፍታችሁ ሰሞኑን ስለምርጫ ሲወራ ግን ጩኸታችሁ ደምቆ ለአድዋ ዘመቻ ከተጎሰመው ነጋሪት በላይ በሀገሪቱ ሲያስተጋባ አየን። ሕዝቡም ሥልጣን መጠማታችሁን አይቶ እ.ህ.ህ.ህ አለ ፈረስ ብሎ ማሽሟጠጡ አልቀረም። ግን እናንተ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሕዝብ ከሌለ ምርጫም ሥልጣንም ምንም ዋጋ እንደሌለው ለማሰብ እንደምን ተሳናችሁ? እውነት ለመናገር ይህ ድርጊታችሁ ትልቅ የፖለቲካ ንቅዘት እንዳጋጠማችሁ ማሳያ ይመስለኛል።
ከጅብ ቆዳ የተሰራ ከበሮ እንብላው እንብላው ይላል እንዲሉ በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ያላችሁ አንዳንድ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ምነው የኢትዮጵያን እና የሕዝቦቿን ደህንነት ሳይጨንቃችሁ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ማለትም የኢትዮጵያ ሕዝብ በመላው ዓለም የሚሆነውን አያየ ሲያስብ በጭንቀት የወንዝ ውስጥ ቄጤማ ሆኖ ሳለ ምን የሚሉት ነው በምርጫ ይህን ያክል መነታረክ፤ ምን የሚሉት ነው እንዲህ ለሥልጣን መቋመጥ? ይህ ድርጊታችሁ የራሳችሁን ጥቅም ለማሳደድ እንደቋመጣችሁ በደንብ ያሳብቅባችኋል። እውነት በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያን ሕዝብ ያስጨነቀው ምርጫ ነውን?
ህወሀት ሃያ ሰባት ዓመት ሲገዛ አምስት ሀገራዊ ምርጫ ሲያደርግ አንድም ጊዜ ምርጫውን ያለሳንካ ማስሄድ ያልቻለ ፓርቲ ከሃያ ሰባት ዓመት በኋላ በስርቆት እና በተለያዩ ብልሹ አሠራሩ ከፌዴራል መንግሥቱ በመባረሩ ወደ መቀሌ ሸሽቶ መደበቁ የሚታወቅ ነው። ነገር ግን «የለመደ ልማድ ያሰርቃል ከማዕድ» እንዲሉ መስረቅ፤ ማጭበርበር፤ ሕዝብን ማሸበር ልማድ ያደረገው ህወሀት አሁንም ከእኔ ውጪ ሌላ ፓርቲ ሊወክልህ አይችልም የሚለውን ምስኪኑን ፣ ሥራ ወዳዱን፣ ለሀገር ዘብ ቋሚውን የአብራኩ ክፋይ የሆነውን የትግራይ ሕዝብም ልክ ሃያ ሰባት ዓመት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ሲፈፅም የኖረውን መስረቅ፤ ማጭበርበር፤ የማሸበር ሥራውን ሊደግመው የሌት ተቀን ተግባሩ አድርጎ ተያይዞታል። «ያደቆነ ሰይጣን ሳያቀስስ አይለቅም» አይደል የሚባለው። «የላይ ለምጡን የውስጥ እብጠቱን ባለቤቱ ያውቃል» እንዲሉ የትግራይ ሕዝብ ችግሩን ራሱ ያውቀዋል። ችግሩን በራሱ ይፈታ ዘንድ አማራጮችን ለትግራይ ሕዝብ ተዉለት። ህወሀቶች እናንተማ ለትግራይ ሕዝብ ችግርህን ከእኛ በላይ የሚያውቀልህ ላሳር እያላችሁ ይኸው አርባ ዓመት አለፋችሁ። ነገር ግን ምንም ጠብ ያለ ነገር ለትግራይ ሕዝብ የሰራችሁለት ነገር የለም። ስለዚህ በትግራይ ሕዝብ ላይ የምትፈፅሙት መስረቅ፤ ማጭበርበር፤ ሕዝብን ማሸበር እና ከሌሎች እህት ክልሎች ጋር የማቃቃር ሩጫ ብትገቱት ይሻላል ባይ ነኝ። ካልሆነ ግን ውጤቱ ለማየትም ለመስማትም ቀፋፊ መሆኑ የማይቀር ይመስለኛል።
በመጨረሻም በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ላላችሁ ተፎካካሪ ፓርቲዎች አንድ ነገር በማለት ጽሑፌን ልቋጭ። እውነት ፓርላማ ላይ ያለውን የሰዓት ቆጣሪ ከ10፡25 ላይ ማንቀሳቀስ ትፈልጋላችሁ? ማለትም ከዚህ በፊት የነበረውን ዓይነት ህፀፅ የበዛበት ምርጫ እንዳይኖር የምትፈልጉ ከሆነ መጀመሪያ ሀገራችን ከተጋረጠባት ችግር ትውጣና ትረጋጋ ማለትም ከወረርሽኙ ስጋት ነፃ ትሁን። ከዚያ በኋላ ምርጫውን ማከናወን ይቻላል ባይ ነኝ።
አዲስ ዘመን ግንቦት 10/2012
በአሸብር ሀይሉ