ረቡዕ ግንቦት 5 ቀን 2012 ዓ.ም የአዲስ አበባ ፖሊስ ሥራ በዝቶበት ውሏል። የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ (ማስክ) አላደረጉም ያላቸውን ነዋሪዎችን ወደማረፊያ ሲያግዝ ታይቷል። ማምሻውን በሰጠው መግለጫ እንዳሳወቀውም በዕለቱ ብቻ 1 ሺ 305 ሰዎችን በቁጥጥር ሥር አውሏል። እርምጃው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መሠረት ያደረገ ነውም ተብሏል። በአዋጁ መሠረት የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛዎች በተለይም ሕዝብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ማድረግን አስገዳጅ ከሆነ ሰንብቷል። ሕዝቡ ግን ይኸን በሚገባ የተረዳ ስለመሆኑ አጠራጣሪ ነው።
ፖሊስ በአዲስ አበባ ነዋሪዎች ላይ የወሰደው እርምጃ እንደተሰማ “ማስተማር መቅደም ነበረበት” ከሚሉ አስተያየቶች ጀምሮ “ጎሽ ይበላቸው” እስከሚል አስተያየት ተደምጧል። በሌላ በኩል ሰዎችን በጅምላ አሥሮ አንድ ቦታ ማስቀመጥ የኮሮና ቫይረስን ከመከላከል አኳያ አሉታዊ ገጽታው የጎላ ነው በሚል የፖሊስን ግዴየለሽነት አጥብቀው የሞገቱ ወገኖች ነበሩ። መንግሥታዊው የሰብዓዊ መብት ኮምሽንም ቅሬታ ካቀረቡ ተቋማት መካከል ግንባር ቀደሙ ነበር። ኮምሽኑ የመንግሥት ገመናን የመደበቅ የቆየ ልማዱን ሽሮ፤ የመንግሥትን ጉድለት ነቅሶ ወደማሳየት መሸጋገሩ እሰየው የሚያሰኝ ነው። እናም ኮምሽኑ በመግለጫው በፖሊስ የተወሰደውን እርምጃ ጉድለቱን በመጥቀስ ነቅፏል። ፖሊስ የአፍና የአፍንጫ መከለያ አላደረጉም በማለት በጎዳና ላይ ሰዎችን እያሠረ ያለው ከሕግ ውጭና በዘፈቀደ በመሆኑ በአስቸኳይ ሊቆም ይገባልም ሲልም ማስጠንቀቂያ አዘል ማሳሰቢያ መስጠቱንም ሰምተናል።
እኔ ግን እላለሁ፤ ከዚህ ይልቅ በአጠቃላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተገቢው መንገድ እየተተገበረ አለመሆኑ በእጅጉ ያሳስበኛል። መጪው ጊዜም ያስፈራኛል። በመጋቢት ወር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሲወጣ መሠረታዊ ዓላማው የወረርሽኙ ሥርጭት እያስከተለ ያለውንና ሊያስከትል የሚችለውን ሰብዓዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳቶች ለመቀነስ እና ለመከላከል ነው። በተጨባጭ እየሆነ ያለው ግን የአዋጁን መንፈስ የተፃረረ መሆኑ ያሳስባል።
አዋጁን ተከትሎ ከወጡ ድንጋጌዎች አንዳንዶቹን አንቀጾች ስናይ ስለምን እያወራሁ እንደሆነ ይበልጥ ግልጽ ሊሆን ይችላል። አዋጁን ተከትሎ ከወጣው ደንብ ካስቀመጠው ክልከላዎቹ መካከል ጥቂት የማይባሉት እስካሁን አለመተግበራቸው ፀሐይ የሞቀው ሐቅ ነው። የአዋጁ ክልከላዎች ሰፋ ያሉ የማህበረሰቡን የዕለት ተዕለት መስተጋብሮች የሚነካ፣ አንዳንዱንም የሚያቅብ ከመሆኑ ጋር ተያይዞም በቀላሉ ለመተግበር ይቻላል ተብሎም አፍን ሞልቶ መናገር አያስደፍርም። ቻሌንጁ ውስብስብ ነውና!
ከክልከላዎቹ ጥቂቶቹ፡-
- ማንኛውም ሃይማኖታዊ መንግስሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የግል ድርጅቶች ይሁን ፖለቲካዊ ስብሰባዎች፣ እድር፣ ደቦ፣ እቁብና ሌሎችም ከአራት ሰው በላይ ስብሰባዎች ክልክል ስለመሆናቸው፣ አራት ሰዎችም ቢሆኑ ሁለት የአዋቂ ሰው እርምጃ የጠበቀ መሆን እንዳለበት፣
- የባንክ አገልግሎት በሚሰጥባቸው አካባቢዎች፣ በገበያዎች፣ በትራንስፖርት መሳፈሪያ ቦታዎች፣ በትራንስፖርት ውስጥ፣ በሱቆች፣ በመድሃኒት መሸጫ አካባቢዎች፣ ህዝባዊ አገልግሎት በሚሰጥባቸው ቦታዎችና ሌሎች ህዝብ በሚበዛባቸው መሰል አካባቢዎች የሚገኝ ማንኛውም ሰው አፍና አፍንጫው ላይ መሸፈኛ የማድረግ ግዴታ እንዳለበት፣
- የቤት ተከራዮች በራሳቸው ፍላጎት ካልወጡ በስተቀር ማስወጣትና ኪራይም መጨመር ስለመከልከሉ፣
- በሠራተኛና አሠሪ አዋጅ የሚተዳደሩ የግል አሠሪ ድርጅቶች ሠራተኞችን መቀነስና የሥራ ቅጥር ውል ማቋረጥም ስለመከልከሉ፣
- ስፖርታዊ ጨዋታዎች፣ የህፃናትም ይሁን የሌሎች መጫወቻ ስፍራዎች እንዲሁም የእጅ መጨባበጥ ሠላምታ የተከለከለ ስለመሆኑ፣
- ማናቸውም አገልግሎት የሚሰጡ የመንግሥትም ሆነ የግል ተቋማት አገልግሎት ለማግኘት ወደ ተቋማቱ የሚሄዱ ተገልጋዮች ሁለት የአዋቂ እርምጃ ተራርቀው የሚቆሙበትን ቦታ ምልክት የማድረግ ኃላፊነት እንዳለበት፤
- በትራንስፖርት ዘርፍም አገር አቋራጭ፣ የከተማ ውስጥ የታክሲ አገልግሎት የሚስጡ እንዲሁም የፐብሊክ ስርቨስ የሚስጡ ካለው ወንበር ከ50 በመቶ በላይ ተሳፋሪ መጫን የተከለከለ ስለመሆኑ ተደንግጓል።
አፈፃፀሙ
አፈፃፀሙ ከቦታ ቦታ መለያየቱ የሚጠበቅና የተለመደ ነው። በአመዛኙ ቡራቡሬ አይነት መልክ ያለው ነው። በአንዳንድ የከተማው አካባቢዎች ትግበራው ጥሩ ሲሆን በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ ጨርሰውኑ አዋጁ ስለመውጣቱ፣ አገሪቱም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሥር ስለመሆኗ የተሰማ እንደማይመስል ታዝቤያለሁ።
መጠጥ ቤቶች፣ ምግብ ቤቶች አሁንም ሙሉ ናቸው። ሙሉ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን ርቀት መጠበቅና አንድ ጠረጴዛ ከሦስት ሰው በላይ አለመቀመጥን የሚተገብሩ አይደሉም።
በሕዝብ ትራንስፖርት ላይ ተሽከርካሪዎች ከመጫን አቅማቸው በግማሽ እንዲነሱ የሰፈረው ድንጋጌ በታክሲዎች ላይ በአመዛኙ የተተገበረ ሲሆን እንደአንበሳ የከተማ አውቶብስ ያለ የሕዝብ ትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች ላይ መተግበር አለመቻሉን መታዘብ ችያለሁ። አንበሳ አውቶቡስ በወንበር ልክ እየጫነ መሆኑን ለመመልከት የቻልኩ ሲሆን ይኸም የትራንስፖርት እጥረቱን ለመመለስ የተወሰነ ቢመስልም የአዋጁን ድንጋጌ የጣሰ ድርጊት ነው።
አብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ (ማስክ) መቼ፣ በምን ሰዓትና ቦታ ይደረጋል የሚለው እኩል አረዳድ የለውም። በዚህ ረገድ የወጣ ወጥ መመሪያ ስለመኖሩም በግሌ አላውቅም። እንዲህም ሆኖ ህብረተሰቡ በመደበኛነት ማስክ አድርጎ የመንቀሳቀስ ልማድ ገና አላዳበረም። ጥቂት የማይባል ሰው ማስክ በኪሱ ይዞም የማይጠቀምበት ሁኔታ የሚታይ በመሆኑ በዚህ ረገድ ለውጥ ለማምጣት ከመንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት ብዙ ሥራ ይጠበቃል።
በሌላ በኩል ከግንቦት 4 እስከ 6 ቀን 2012 ዓ.ም የተካሄደው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ ያወጣው መግለጫ ምናልባትም በቤተክርስቲያኗ እና በመንግሥት መካከል አዲስ ውጥረት ሊፈጥር የሚችል ነው። ለዚህ ትልቁ ምክንያት ደግሞ ቅዱስ ሲኖዶስ የተዘጉ የቤተ ክርስቲያን በሮች ክፍት ሆነው መንፈሳዊ አገልግሎቱ በጥንቃቄ ተግባራት እየተመራ እንዲፈፀም በማዘዙ ነው።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከአራት ሰው በላይ ለሃይማኖት፣ ለፖለቲካ፣ ለማህበራዊ ጉዳዮች መሰብሰብን የከለከለበት አዋጅ ሳይሻር እንዲሁም የተለያዩ ቤተ እምነቶች አዋጁን አክብረው ደጃቸውን ዘግተው በተቀመጡበት ሁኔታ ይኸ ውሳኔ እንደምን ሊፈፀም ይችላል የሚለው እንደተጠበቀ ሆኖ ግን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈፃፀም ወቅት እዚህም እዚያም በፀጥታ አካላት ዘንድ የታዩ የአሠራር ግድፈቶች በራሱ ቤተክርስቲያኗ እና አማኞቿን ሆድ አስብሶ ለውሳኔው እንደገፋ ይታመናል።
ይህን አባባል በማስረጃ ለማስደገፍ ያህል የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ በቤተክርስቲያንና በሀገር ደረጃ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስና ለመከላከል ይቻል ዘንድ፣ በጠቅላይ ጽ/ቤት ደረጃ በቋሚ ሲኖዶስ የተቋቋመው የተስፋ ልዑክ ግብረ ኃይል ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ሰሞኑን ያቀረበውን ሪፖርት በጥቂቱ እጠቅሳለሁ።
“….መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ካወጀበት እና ተግባራዊ ማድረግ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ማንም እገዛ ሳይጠይቃቸው የፖሊስ ኃይሎች በቤተ ክርስቲያን በር ላይ በመቆም የቤተ ክርስቲያኒቱ ሃይማኖታዊ ሥርዓተ አምልኮ በሚፃረር መልኩ ጥንቃቄ አድርገው የሚያገለግሉ የዘወትር ልዑካን ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብተው በተወሰነው ቁጥር መጠን አገልግሎት እንዳያከናውኑ፣ ምእመናንም በአፀደ ቤተ ክርስቲያን ተገኘው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከምትሠጠው ምሥጢረ ቁርባን እንዳይሳተፉ፣ የክርስትና (ጥምቀተ ክርስትና)፣ ሌሎች ምሥጢራት፣ ሥርዓተ ፍትሐት እንዳያገኙ ከፍተኛ የሆነ የኃይል እርምጃዎች እየወሰዱ፣ እየተሳደቡ፣ እየደበደቡ ምእመናኑን እያስቸገሩ ይገኛሉ። ይህንንም የሚያደርጉት በራሳቸው ተነሳሽነት እና ቤተ ክርስቲያናችንን ዝቅ ያደረጉ በመሰላቸው የሌላ እምነት ተከታዮች ነው። …” በማለት የተፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ረገጣዎችን ወደመዘርዝር ይገባል። የዚህ ጽሑፍ ትኩረት ይህን ጉዳይ ማሳየት ባለመሆኑ ዝርዝሩን ከማቅረብ ተቆጥቤአለሁ።
ምናልባት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈፃፀም መርማሪ ቦርድ በቤተክርስቲንዋ ተፈጽሞብኛል የምትላቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በማጣራት ተገቢውን የእርምት እርምጃ ሊወስድ እንደሚችል የዚህ ፀሐፊ ግምት ሲሆን የቅዱስ ሲኖዶስ የቤተክርስቲያን በሮች ይከፈቱ በሚል ያሳለፈው ውሳኔ ግን መንግሥት በምን መልክ ሊቀበለው እንደሚችል፣ ከአዋጁ ድንጋጌም ጋር በምን መልኩ ተጣጥሞ ሊተገበር እንደሚችል የሚታወቅ ነገር የለም።
እንደመቋጫ
ይኸን መጣጥፍ እያዘጋጀሁ በነበርኩት ያለፈው ሐሙስ ግንቦት 6 ቀን 20012 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ ድረስ አጠቃላይ የዓለም አቀፉ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር 4 ነጥብ 5 ሚሊየን ደርሶ ነበር። የሟች ቁጥር ወደ 300 ሺ ተጠግቷል። 1 ነጥበ 7 ሚሊየን ሕዝብ አገግሟል። ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ወደ 1 ነጥብ 4 ሚሊየን ሰዎች ተይዘውባት፣ 85 ሺ 197 ሰዎች በሞት ገብራ በመጀመሪያው ረድፍ ላይ ስትገኝ፣ ስፔን እና ሩስያ እንደሚከተሉ የወርልዶ ሜትር ሪፖርት ያሳያል።
ከአፍሪካ ትልቅ የተጠቂ ቁጥር ያላት ደቡብ አፍሪካ ከዓለም በ39ነኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠች ሲሆን እስከ ዕለተ ሐሙስ ድረስ 12 ሺ 74 ሰዎች ተይዘው 219 ሰዎች በሞት ተነጥቃለች። ኮንጎ ብራዛቪል የሚገኘው ዓለም የጤና ድርጅት የአፍሪካ ጽ/ቤት በወጣው መረጃ መሠረት በአህጉሪቷ ኮሮና ቫይረስ ታማሚ ቁጥር ከ70 ሺ በላይ ሲደርስ የሞቱት ቁጥር 2 ሺ 475 እንዲሁም ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 25 ሺ 270 ሆኗል። ደቡብ አፍሪካዊቷ ሌሴቶ የመጀመሪያ የኮሮና ቫይረስ ሕመምተኛ ማግኘትዋም ተሰምቷል።
ከአፍሪካ የሰሜኑ ክፍል በጥቅሉ 24 ሺ 300 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን ምዕራብ አፍሪካ 21 ሺ 500፣ የደቡብ አፍሪካ አገራት 13 ሺ፣ የምሥራቅ አፍሪካ አገራት 7 ሺ 100 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው አናዶሉ የዜና ወኪል ዘግቧል።
በኢትዮጵያ እስከ ዓርብ ዕለት ድረስ ብቻ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 287 መድረሱ ታውቋል።
ከዚህ በተጨማሪም የዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ኮቪድ 19 ከዓለማችን መቼ እንደሚወገድ ጨርሶ እንደማይታወቅ፣ እንዲውም እንደኤች አይቪ/ኤድስ ወረርሽኝ ለረዥም ጊዜ አብሮን ሊዘልቅ እንደሚችል በመግለጽ ብቸኛ መዳኛው መንገድ ጥንቃቄ ብቻ ነው ብሏል።
አሁን አስጊው ነገር በኢትዮጵያ ከቀን ወደቀን እየጨመረ ከመጣው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር እና በህብረተሰብ ውስጥ ካለው ሠርጭት አንፃር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ድንጋጌዎች ከልብ አክብሮ በማስከበር ረገድ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ የቱን ያህል ጠንካና በተዋረድ የሚናበብ ነው የሚለውን ማወቁ ላይ ነው።
ሕብረተሰቡ በማወቅም ባለማወቅም አዋጁን የሚጥስበት ሁኔታ ሰፊ መሆኑን መረዳት ተገቢ ይሆናል። ሰዎችን የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ አላደረክም በሚል አንድ ቦታ ሰብስቦ ከማሰር ወይንም ለቅጣት ከመቸኮል ይልቅ አድካሚ ቢሆንም ማስተማሩ ላይ በተደጋጋሚ ርብርብ ማድረጉ የተሻለ ውጤት እንዳለው መገንዘብ ያስፈልጋል።
በእውነት ለመናገር፤ የኦርቶዶከስ ተዋህዶ ልጅ እንደመሆኔ ቤተክርስቲያን መሄድ፣በጣም እንደናፈቀኝ መደበቅ አይቻለኝም። ይኸም ሆኖ ቤተክርስቲያን ከመንግሥት ቀጥሎ ልጆችዋ የመጠበቅ ግዴታ ስላለባት ይህን አስቸጋሪ የፈተና ጊዜ ለማለፍ አባቶች ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው። ከጾምና ጸሎት በተጨማሪ ልጆችን በመምከርና በመገሰጽ የፈተናውን ጊዜ ለማለፍ መትጋት ከአባቶች እና ከምእመናን ይጠበቃል።
መንግሥትም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈፃፀም መርማሪ ቦርድ ሥራው በተገቢው መንገድ እንዲወጣ በማገዝ እና በተለይ የእምነት ተቋማት በፀጥታ ኃይሎች ያልተገባ ችግር እንዳያጋጥማቸው፣ አጋጥሞ ሲገኝም ደግሞ አቤቱታ እንኳን እስኪቀርብ ሳይጠበቅ ተገቢውን የእርምት እርምጃ መውሰድ ይገባዋል። ከምንም በላይ ደግሞ በእምነት ተቋማት አካባቢ የሌላ እምነት ተከታይ የሆኑ የፀጥታ አካላትን ማሰማራት ያለውን አሉታዊ እና አዎንታዊ ፋይዳ ማመዛዘንና በትክክል መመርመርም በኋላ ሊፈጠር የሚችል ችግርን ከወዲሁ ለመቅረፍ ይረዳልና የሚመለከታቸው አካላት ቢያስቡበት?!
አዲስ ዘመን ግንቦት 8/2012
ፍሬው አበበ