አሁን በቀደም እለት፣ በአንድ የንግድ መደብር ውስጥ ሶስት ሜትር በሁለት ሜትር የሚያክል፣ ትልቅ አልጋ ተንጣልሎ አየሁና ዋጋውን ስጠይቅ 32 ሺ ብር ነው፤ አሉኝ። እኔ የምለው… በዚህ አልጋ ስተኛ አባብሎ እንቅልፍ ይወስደኛል ወይስ እንቅልፉም አብሮት ይሸጣል? የኔ ጥያቄ ነበረ። አሻሻጯ ልጅ ግን አልሳቀችም ይህ ለእሷ ሥራ ለእኔ መከራ ነበረ።
ዋነኛው ርእሰ ነገሬ፣ ስለውድ አልጋዎች ትልቅነትና ስለሚሸምቷቸው ሰዎች ምጣኔ ለማውራት ሳይሆን፣ ስለሚተኙና ስለሚያሸልባቸው ሰዎች ልዩነት ልናገር አስቤ ነው።
ማንም ሰው፣ በህይወቱ ሊተኛባቸው የሚያስፈልጉ ሰዓቶች፣ እረፍትና ስራ ሊያከናውንባቸው የሚገቡ ሰዓታት ሊኖሩ እንደሚገባ አምናለሁ። ጥሩ እንቅልፍ የጥሩ ጤንነትም አጋር መሆኑን እቀበላለሁ። እንዲያውም የእንቅልፍ ውጤትና ተዛምዶውን የሚያጠኑ ሰዎች የሚቆራረጥ እንቅልፍ ያላቸውና መደበኛ የእንቅልፍ ጊዜ የሌላቸው፣ ወይም በቀን ከስድስት ሰዓት በታች የሚተኙ ሰዎች ከእድሜያቸው አንድ አስረኛውን ያህል ሊያሳጥሩ ወይም በዚሁ ጦስ ሊሞቱ ይችላሉ ተብሎ ይታመናል።
ስለዚህ በቀን ስምንት ሰዓት ያህል ለመተኛት መታደል መደበኛ እንቅልፍ ለመተኛት ብቻ ሳይሆን ረዥም እድሜ ለመኖርና ውጤታማ ሥራ ለማከናወን እንደሚያስችልም እሙን ነው።
ሌሎቹ፣ በሥራቸው ውጤታማ ያልሆኑ ሰዎች በሁለት ይከፈላሉ። አንደኛዎቹ ሰዎች ወይም ወገኖች፣ እንቅልፋቸው የሚቆራረጥባቸውና በቂ እንቅልፍ ለመውሰድ መድሃኒት ተቀላቢ የሆኑ ወይም በአልኮል ራሳቸውን አባብለው የሚያስተኙ ዓይነቶች ናቸው። ሁለተኛዎቹ ወገኖች የሚተኙት ለመተኛት የሆኑ ግለሰቦች ናቸው።
በአንዳንድ ወገኖች ዘንድ ስራቸውን ሲሰሩ ጠንቃቃ እና ወጥረው የሚሰሩ ሁሉን ነገር እኔ ልስራው ብለው የሚያስቡና ሥራቸው ላይ ቀልድ ያማያውቁ ታታሪዎች ሲሆኑ እንቅልፍ አልባ ሌሊቶች ያላቸው ዓይነት ናቸው።
ከጎረቤታችን ያሉ ዳቦ መጋገሪያ ቤት ያላቸው ሰው አሉ። ብዙዎቻችሁ እንደምታውቁት ዳቦ ጋጋሪዎች ቀን ያቦኩትን ሊጥ አስማምተውና አሰማምረው ለሌሊት በማዘጋጀት ንጋት አካባቢ ምርታቸውን ለተመጋቢ በገፍ የሚቀርቡ ናቸው ። ዳቧቸው አለቅጥ በአካባቢው ሰው ተፈላጊና ሽያጩም ጥሩ በመሆኑ፣ ይህ የሥራ አዙሪት ለረዥም ጊዜ ሳያቋርጥ የቀጠለ ነው። ሰውየው ዳቦው በስማቸው የሚጠራ በመሆኑም “ከሊፋ ዳቦ” ጥራቱንም ብዛቱንም ጠብቆ እንዲሄድ አጥብቀው ይታትራሉ። (ለጥንቃቄ ያህል ስማቸው ተቀይሯል)
“አይ… ጋሽ ከሊፋ !” ልዩው ነገር ግን፣ ይህ ሌት ተቀን የማያቆመው ወፍጮ ግን አንድ ነገር በእርግጥ ነጥቋቸዋል። እንቅልፍና ቤተሰባቸውን ሳይነግራቸው ወስዶባቸዋል። በሥራው መካከል ጎብኝተዋቸው የሚመለሱትን ባለቤታቸውንና ልጆቻቸውን ከቶውም እንደልብ አያገኟቸውም፤ በተለይ ሁለት ተጨማሪ ቅርንጫፍ ከተማው ውስጥ ከከፈቱ በኋላ ያደረሳቸው ቦታ ባዘጋጁት ፍራሽ ላይ እረፍት አይሉት ማንጎላጀት፣ አረፍ ይሉና ወይም ትንሽ አሸልበው ስለሚነሱ ቤታቸውን በውል ሳይተዉት፣ እንደዘበት ትተውታል።
አልፎ አልፎ ልጆቻቸው መጥተው ጎብኝተዋቸው ከመሄድ ውጭ እርሳቸው ሥራቸውን ሚስትና ልጅ ስላደረጉ፣ በማህበራዊና ቤተሰባዊ ግንኙነታቸው ላይ ያሏቸውን ክሮች በተገቢው ሁኔታ አልያዟቸውም። እና በዚህ መሐል አንድ ቀን ክፉኛ ታምመው ሲወድቁ እና ሆስፒታልም መግባት ኋላም ቤት መዋል፣ ግድ ሲሆንባቸው ልጆቻቸውን “አንቺ ደግሞ ማነሽ?” ብለው መጠየቅ በመጀመራቸው ቤተሰቡ ክፉኛ ተላቀሰ።
ትልቁ ልጃቸው አሁን፣ ህመምህ ወደስራህ የማይመልስህ መሆኑን ሐኪም ነግሮናል፤ አንደኛ የመተንፈሻ አካልህ ችግር ላይ ወድቋል፤ ሁለተኛ እረፍት አልባው አካልህ ክፉኛ እየደከመ ነው፤ በዚህ ላይ አደገኛ የደም ብዛት እንዳለብህ ተነግሮናል። ስለዚህ አንተን ተክቼ ሥራውን እኔ እሰራለሁ፤ አታስብ ይላቸዋል።
መቼም አንዳንድ ሰው ላግዝህም ቢሉት፣ ስልጣንና ችሎታውን ነጥቀው ለቦታው አትመጥን ያሉት ስለሚመስለው፣ ነዘር ያደርገዋልና ይቆጣል። “ሸክሙን ላግዝሽ ቢሏት ሲባጎ ደበቀች “እንደተባለው መሆኑ ነው።
እናም ጋሽ ከሊፋ፣ መልሰው፣ አንደኛ፣ ስራውን አትችለውም። ሁለተኛ እኔ አሁን ቶሎ ስለምነሳ፣ አንተ እኔን መተካት አይገባህም፤ ብለው በራሳቸው ከአልጋው ለመነሳት ሲሞክሩ አቅም ማጣታቸውን በማወቃቸው እንባቸው በጉንጫቸው ላይ ፈሰሰ።
ምንድነው የሆንኩት?….. ብለውም ሲጠይቁ ከሰመመን የነቁት ከሁለት ቀናት በኋላ መሆኑንና ይህም የተከተለው እንቅልፍ አልባ በሆነው የረዥም ጊዜ ሥራህ ሳቢያና ህመምህን መከታተል ራስህንም በጊዜው ማስመርመር ባለመቻልህ ነው፤ ተብሎ በሐኪም እንደ ተነገራቸው ልጆቻቸው ሹክ አላቸው።
አባባ፣ አሁን አንድ ወር ያህል፤ እዚሁ መድሃኒት እየወሰድክ ታገግማለህ፤ አካላትህ ከተፍታታ በኋላም ወደ ፊዚዮቴራፒስቶች ጋር እንወስድሃለን። በፊትም ስመክርህ እኮ፤ “ሥራ ሰውን የገደለው የት ሐገር ነው” ትለኝ ነበረ። እንደፈራሁትም አጥብቀህ የወደድከው ሥራ ይኸው ለዚህ አብቅቶሃልና ማረፍህ አስፈላጊ ነው፤ ሲል፣ ትልቁ ልጃቸው ነገራቸው።
እዚህ ላይ መገንዘብ ያለብን ዋነኛው ነገር፤ ለአቶ ከሊፋ አካላቸውን የሥራቸውን ያህል ይቅርና በግማሹ ቢንከባከቡት ኖሮ ለዚህ አስፈሪ ደረጃ አይደርሱም ነበረ። ዱቄቱ፣ ዘይቱ ነዳጁ፣ ክሬሙን፣ ማሽኑን፣ መጋገሪያውን እድሳቱን፣ የዳቦውን ኪሎና አቀራረቡን፣ የሂሳብ አወጣጥና አገባቡን፣ የባንክ ግንኙነቱንና ሽያጩን ሁሉ የሚቆጣጠሩት ራሳቸው ስለነበሩ እረፍት አልነበራቸውም። ልጆቻቸው፣ ድንገት ተከስተው ሲያናግሯቸው እንኳን፣ “ምን ፈለግክ” ከሚሉ የገንዘብ ጥያቄዎች ያልዘለለ፣ ጥያቄ አቅርበው፣ ከመሸኘት ወዲያ ብዙ አያነጋግሯቸውም ነበረ። ትልቁ ልጅ በኢኮኖሚክስ ተመርቆ እናትየው ለምረቃ ስትጠራቸው ማታ መጣለሁ፤ ብለው ነው፣ በዚያው ወደሌላ መደብር ሄደው ያደሩት።
እንደነዚህ ያሉ ጊዜያቸውን በአግባቡ የማይጠቀሙ፣ ያለእድሜቸው ሞትን የሚጠሩ ሰዎች ናቸው። መኝታ ነውር የሚመስላቸው ወይም በየስፍራው ትናንሽና የተቆራረጡ እንቅልፎች በመተኛት ተገቢውን እረፍት ለሰውነታቸው የነፈጉ እረፍት አልባ ሰዎች በእንቅልፍ እጦት የሚሞቱ ወይም የሚሰናከሉ ናቸው።
ከዚሁ ጋር፣ አንዳንድ የድርጅትና የሀገር መሪዎች በዚሁ ሁሉን እኔ በሚል ጠባያቸው፣ በእጅጉ ይታማሉ። በጣም ረዣዥም ሌሊቶቹንና ማለዳዎችን ለራሳቸው እንቅልፍ ከልክለው በፓርቲ ሥልጣንና በሐገር ጉዳይ ተወጥረው፣ እረፍት-አልባ ህይወት ይመራሉ። አንዳንዴም፣ በዚህ ጠባያቸው የተነሳ ሚዛናዊ ብይን መስጠትና ነገሮችን እንዳመጣጣቸው በሰከነ መንገድ ከመመለስ ይልቅ ጨካኝ፣ አስከፊና ሁሉን አውጋዥ በሆነ መልክ ሲናገሩና በምሬት ሲናገሩ የኃይል እርምጃ ሲወስዱም ከመታየታቸውም ሌላ ሶኬቱ ድንገት እንደተነቀለበት የኤሌክትሪክ ባቡር መስኮቱንም በሩንም ዘግተው፣ ጸጥ ይላሉ።
ስለዚህ ከሥራ በኋላ ጤናማ የሆነ ማንቀላፋት ለመልካም ጤንነት መልካም ነው። ክፉው፣ በሥራው ላይ መተኛት ነው እንጂ።
እንቅልፍ አልባዎቹ ሰዎች ራሳቸውን አንገላትተው ሌላውንም የሚያንገላቱና ሠው ሁሉ እንደ እነርሱ እንቅልፍ አልባ ሌሊትና ወከባ ያለው ህይወት እንዲኖረው ስለሚወዱ አለመተኛታቸው አንሶ ሌላውን የማያስተኙ አይነት ናቸው። በእቅድና በስልት ሊሰራ ከሚችል አሰራር ይልቅ ሁሉም አሁንና አሁን መደረግ እንዳለበት የሚያስቡና እናም ደጋግመው ሲስቡት የሚበጠሰው ገመድ የማያሳስባቸው እረፍት የለሽ ሰዎች ናቸው። እነዚህ ከላይኛዎቹ እንቅልፍ አልባዎቹ ሰዎች የሚደመሩና ሰው-ሰራሽ ወይም ተፈጥሯዊ አደጋ ብቻ የሚያስቆማቸው አይነት ፍጥረታት ናቸው።
አየር መንገድ ላይ ቢቀጠሩ ወይም ኩባንያውን ቢኖራቸው፣ አብራሪም፥ አስተናጋጅም ኩሽናም ውስጥ፣ ሥራ አስኪያጅም መሆን የሚቃጣቸው “ሁሉን እኔ ባይ” ሰዎች በድርጅት የአሰራር ከፍታና ዝቅታ መሪና ተመሪነት ተዋረድ የማያምኑና በሁሉም ስፍራ አሻራቸውን ማሳረፍ የሚፈልጉ የሁሉም ነገር ምንጭ ራሳቸው ብቻ እንደሆኑ የሚያስብ ሰብዕና ያላቸው ናቸው። ማንንም ሰው በስራው ውስጥ አያምኑም፤ በአሰራር ሂደቱ የማንንም ሰው እጅ አይቀበሉም፤ አንዳንዴም “የትም ፍጭው ዱቄቱን አምጭው” ባይ አንድ ወዳጄ እንዳለኝ፣ “ከማንም ሂጂና ገንዘቡን አምጭና”፤ እንደማለት ያሉ ሰዎች ናቸው፤ ይላቸዋል።
እነዚህ እረፍት-አልባ እረፍት-ነሺ መሪዎች ናቸው። እግዚአብሔር ይሁናቸው እንጂ ነገር ከእጃቸው ያመለጠ እለት ልቃቂቱ ተተርትሮ ማቆሚያው የት እንደሆነ አይታወቅም። ገንዘባቸው ያለበትን አያሳውቁም፤ ወይም አያውቁም፤ ንብረታቸው ያለበትን አድራሻ፣ ሰነዶቻቸው የሚቀመጡበትን ቦታ ስለማያስተውሉ ለጥቃት ንብረታቸውም ሀብታቸውም የተጋለጠ ነው። ሰውየው ሲጎዳ እዳ አለበት ባይ ሰው፣ እንደአሸን ከየትም ስፍራ ሊመጣ ይችላል። የእረፍት- አልባ እረፍት ነሺ ሰዎች ፍጻሜ ይኸው ነው።
እዚህ ላይ በመንግስቱ ለማ የተተረጎመው “ዳንዴው ጨቡዴ“ የተሰኘውን ባለ አንድ ገቢር ኮሜዲ አስታወስኩኝ። በዚህ ድራማ ላይ ዋናው ገጸ ባህሪ፣ ጨቡዴ ባሎቻቸው ሲባዝኑ የሞቱ ሀብታም ሴቶችን አሳዳጅ ገጸ ባህሪ ተደርጎ ነው የተሳለው። እነዚህ ባካኝ ባለመሬትና የንግድ ሥራ ባለጸጎች ብዙ ጊዜ ከሚስቶቻቸው መረጃ ስለሚደብቁ፣ ይህንን ጠባያቸው ተገን አድርጎ አስሶ የሚገባ ነው።
በዚህ ድራማ ላይ ጨቡዴ ባሏ በሞተ በሰባተኛው ቀን መጥቶ አለቅሶና አጽናንቶ ይወጣና በወሩ በመመለስ፣ “ባለፈው ሃዘንሽን ልካፈል መጥቼ ሳላወራሽ የሄድኩት አስቤልሽ ነው፤ ካለ በኋላ …..የሆኑ ሰነዶችን ካወጣ በኋላ፣ ……“ለነገሩ የምትኖሪበት ቤትም ቢሸጥ ብድሩን አይመልስም ግን…ባልሽ የዚህ ሁሉ ብር እዳ አለበትና እንድትከፍይኝ አስቤ ነው፤ የመጣሁት። በዚህም መሰረት እስከዛሬ ሳምንት ብሩን አዘጋጅተሽ ጠብቂኝ” ብሎ አፈፍ ብሎ ተነስቶ ይሄድና ባለው ቀን ተመልሶ ይመጣል።
ችኩልና ስክነት የሚጎድላቸው፣ ባሎች ለአዋካቢ ቀጣፊዎች ሚስታቸውን አጋልጠውና ሥራቸውን ሜዳ ላይ በትነው ነገር በወግ በወጉ ሳያደርጉ ይጠናቀቃሉ። እነዚህ ሰዎች እንቅልፍ ያጡ ብቻ ሳይሆኑ በቤተሰባቸው ጉዳይ ላይም ተኝተው የሚሞቱ አይነቶች ናቸው። መኝተኞች ብዬ የማስባቸው እነዚህ ዓይነቶቹ ሰዎች አያንቀላፉም ግን በብዙ ቸል ሊባሉ በማይገባቸው ነገሮች ላይ ግን ዓይናቸው ታውሮና ተኝተውበት በቁጥር የማይተመን ጥፋት አጥፍተው ይሄዳሉ።
ከእነዚሁ ጋር ሥራቸው ላይ ተኝተው ወሬያቸው ላይ ግን ነቅተው ሳይሰሩና ሳያሰሩ በሥራቸው ላይ ተኝተው የማያልፉ ሥራ እርማቸው የሆኑ እንቅልፋሞች ደግሞ በየቢሮው በየንግዱ መስክ በየኢንዱስትሪው ውስጥ ተቀምጠው የሚሄደውን አላግባብ የማያስኬዱ ዘገምተኞች ሆነው በየስፍራው ይገኛሉ።
በተገቢው ሁኔታ ማንቀላፋት ጤናማነት ሲሆን፣ ያላግባብ መተኛት ደግሞ ቤት አፍራሽ፣ ስራ አሳናሽና ሐገር አደፍራሽ ነው።
በተገቢው ሁኔታ ያንቀላፋች ነፍስ ቀጥሎ ምን መስራት እንደሚገባት አውቃ በእቅዷ መሰረት ወደ ሥራዋ ስታዘግም ስህተቷን ስትነቅስና በሥራዋ ተደስታ ለሌሎች የሀሴት ምክንያት ስትሆን እንቅልፍ አልባ ተዋካቢዎች ደግሞ ለራሳቸው እንቅልፍ አጥተው ሌላውን አሳጥተው ሊሰራ የሚገባውን ሥራ በአግባቡ እንዳይሰራና ጥሩ ድምድማት እንዳይኖረው እንቅፋት በመሆን በሥራው ላይ እንቅልፋም፣ የማይደሰት፣ ለሌላው የማይተርፍ ሰው ይሾሙበታል።
ስለዚህ በሥራችን ላይ የሚያስተኛ እንቅልፍ አልባነትን ትተን በተገቢው ሁኔታ በማረፍ ለተሻለ ቀን ውጤታማነት በንቃት እንመላለስ። በቅጡ አንቀላፍተን ውጤታማ እንሁን እንጂ፣ በየስፍራው በሚያጋጥመን የቆቅ እንቅልፍ እየተደበትን ውጤት አልባ ሰዎች አንሁን።
አዲስ ዘመን ግንቦት 8/2012
አገልጋይ ዮናታን አክሊሉ