አንድ ስራ ከጀመሩ ማዋል ማሳደር የሚባል ነገር አይወዱም። በዚህ ጸባያቸው ምክንያት ደግሞ ሰነፍ ሰራተኛ ካጋጠማቸው ቁጡ ባህሪ እንዳላቸው ይናገራሉ። ይሁንና ሃሳባቸውን ተረድተው እና በአግባቡ ተግባብተው አብረዋቸው ከሚሰሩ ሰዎች ጋር ግን ሰላማዊ ግንኙነት እንዳላቸው አልሸሸጉም። የዛሬው ባለታሪካችን ከብዙ ውጣ ውረዶችን በኋላ ለበርካቶች የተረፈ ፋብሪካ መገንባት የቻሉ ኢትዮጵያዊ ናቸው።
ባለታሪኩ አቶ ከበደ በርታ ይባላሉ። በአዲስ አበባ ከተማ ልዩ ስሙ ተክለኃይማኖት ተብሎ በሚጠራው ሰፈር ነው 1962 ዓ.ም የተወለዱት። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል ድረስ የተከታተሉት ደጃዝማች ዘርአይደረስ ተብሎ በሚጠራው ትምህርት ቤት ነው። ከዚያም ሰባተኛ እና ስምንተኛ ክፍልን ደግሞ ተስፋ ኮከብ መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁት በቀድሞው አጠራሩ ልዑል መኮንን ትምህርት ቤት በአሁኑ ስሙ ደግሞ አዲስ ከተማ ሁለተኛ ደረጃ በተሰኘው ትምህርት ቤት ነው፡፡
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ከአጠናቀቁ ቦኋላ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማታው የትምህርት መርሃ ግብር የሲቪል ምህንድስና ትምህርት ጀምረዋል። ትምህርታቸውንም ከ1982 ዓ.ም እስከ 1984 ዓ.ም ድረስ ከተከታተሉ በኋላ ባጋጠማቸው የገንዘብ እጥረቱ ለማቋረጥ ተገደዋል ፡፡
ተወልደው ያደጉበት ተክለኃይማኖት ሰፈር ከፍተኛ የሆነ የመኪና መለዋወጫ ንግድ እንቅስቃሴ የሚካሄድበት እንደመሆኑ መጠን፣ እርሳቸውም ትምህርታቸውን ካቋረጡ በኋላ ቀስ በቀስ እንደ አካባቢው ነዋሪ ወደዚሁ የንግድ ሥራ ተደባልቀዋል። አልፎ አልፎ የሚያጋጥሟቸውን መለዋወጫ እቃዎች ለባለሱቆች እና ለተለያዩ ገዥዎች በመሸጥ የእለት ጉርሳቸውን መደጎሙን ተያያዙት።
ተባራሪ ስራዎችን መከወኑ ብቻ እንደማያዋጣቸው ሲገነዘቡ ግን ከቅርብ ጓደኛቸው ጋር በመሆን አንድ የንግድ ሱቅ መክፈት እንዳለባቸው ይወስናሉ። ከጓደኛቸው ጋር በሀሳቡ ላይ ተማክረው በጋራ ባዋጡት 500 ብር መዋጮ በ1986 ዓ.ም ተክለሃማኖት አካባቢ አነስተኛ የንግድ ሱቅ ተከራይተው የመኪና መለዋወጫ ንግድ ሥራን ጀመሩ፡፡
ሱቋ በጣም ጠባብ እና ጥቂት እቃዎች ብቻ የያዘች ብትሆንም አቶ ከበደ በነበራቸው የንግድ ስራ ፍላጎት የተነሳ ከጓዳኛቸው ጋር በመሆን ስራውን እያደራጁ እና ቀስ በቀስ እያስፋፉ ትርፋማ ወደመሆን ተሸጋገሩ። የመኪና መለዋወጫ ንግድ ሥራ ዘርፍ ጥሩ ካፒታል የሚጠይቅ ቢሆንም በትንሹ የጀመሯት ስራ በሁለት አመታት ውስጥ አድጋ መጠነኛ ጥሪት እንዲቋጥሩ አደረጋቸው።
አቶ ከበደ እና ጓደኛቸው በጋራ የንግድ ሥራው እስከ 1988 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ ከሰሩ በኋላ «የየራሳችንን ሱቅ መክፈት አለብን» በሚል ስምምነት አደረጉ። አቶ ከበደም ገንዘባቸውን አልባሌ ቦታ የማያውሉ ያገኟትን ትርፍ ወደተሻለ ስራ ለማዋል የሚጥሩ ሰው በመሆናቸው ስራቸውን ለብቻቸው ለመስራት የደረሱበት ውሳኔ የተሻለ ደረጃ ለመድረስ ትልቅ አቅም የፈጠረ ነበር ። የመጀመሪያውን የግል ንግድ ሲጀምሩም ምርጫቸው ያደረጉት የመለዋወጫ እቃዎች አስመጭነት ንግድ ሥራ በመሆኑ በዘርፉ ፈቃድ አውጥተው መንቀሳቀስ ጀመሩ።
የአስመጪነቱ ስራ አዋጭ ሆነላቸው። የገንዘብ አቅማቸው እየተደራጀ ሲሄድ ደግሞ ያቋረጥኩትን ትምህርት ለመከታተል ጥረት ማድረግ ጀመሩ። ለትምህርት ልዩ ፍላጎት ያላቸው አቶ ከበደ ዜጋ ቢዝነስ ኮሌጅ በተሰኘው የትምህርት ተቋም በማታው የትምህርት ክፍለ ጊዜ የንግድ አስተዳደር (business Administration) ትምህርትን መከታተል ጀመሩ።
ይሁንና በወቅቱ የአስመጭነቱ ንግድ ስራ ተደጋጋሚና ጉዞና የውጭ ሀገራት ቆይታ የሚጠይቅ በመሆኑ ከትምህርታቸው ጋር ፈጽሞ ሊጣጣም አልቻለም። በመሆኑም በተፈጠረባቸው የስራ ጫና ምክንያት በ1992ዓ.ም ዳግም የጀመሩት ትምህርት አቋረጡ። ከዚህ በኋላ ያተኮሩት ግን የተለያዩ አጫጭር ስልጠናዎችን ወደመከታተሉ ነው።
ከዚህ ጊዜ በኃላ ግን ሙሉ ጊዜያቸውን ለንግዱ ሥራ ማዋል በመቻላቸው በአስመጭነቱ ሥራ ጥሩ ውጤት ማምጣቱን ተያያዙት። በመለዋወጫ እቃዎች አስመጭነቱም በአጭር ዓመታት ጥሩ ታዋቂነት እንዲሁም ጠቀም ያለ ገቢን ማግኘት ቻሉ።
ው ጤ ታ ማ የ ሆ ኑ በ ት ን የ አ ስ መ ጪ ነ ት ስራ እየከወኑ ደግሞ በጎን በ ኢ ን ዱ ስ ት ሪ ው ዘርፍ ለመሰማራት እ ን ዲ ረ ዳ ቸ ው ጥናት ማድረግ ጀመሩ። ጥናት በ ሚ ያ ደ ር ጉ በ ት ወቅት ግን በ ኢ ት ዮ ጵ ያ የሚገኙ በርካታ አ ም ራ ች ኢ ን ዱ ስ ት ሪ ዎ ች ከፍተኛ የማሸጊያ ምርት እጥረት እ ን ዳ ለ ባ ቸ ው ይገነዘባሉ።
በ ተ ለ ይ ጥራትና ደረጃውን በጠበቀ የማሸጊያ እጥረት ምክንያት የውጭ ንግዳቸው ተ ቀ ባ ይ ነ ት የሚያጡ በርካታ የምግብ እና መጠጥ አምራች ኢንዱስትሪዎች መኖራቸውን ተረዱ። በዚህም ምክንያት አብዛኛዎቹ አምራቾች በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ማሸጊያዎችን ከውጭ እያስመጡ እንደሚሰሩ ዝርዝር ሁኔታውን በማጥናታቸው ወደዚሁ የማሸጊያ ምርቶች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ለመቀላቀል ያላቸው ፍላጎት ከፍተኛ ሆነ።
በዚህ መሠረት 1998 ዓ.ም የኢንቨስትመንት ፈቃድ በመውጣት እና ከፍተኛ የፋናንስ ወጪ በመመደብ የካርቶንና የፕላስቲክ ማሸጊያዎች ማምረቻ ፋብሪካ ለማቋቋም ተነሱ። በአዲስ አበባ ከተማ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ልዩ ስሙ ለቡ የኢንዱስትሪ መንደር በሚል በሚታወቀው ቦታ 2000 ካሬ ሜትር በሊዝ ቦታ በመግዛት ፋብሪካውን የማቋቋም ሥራ ጀመሩ። ለፋብሪካው የሚያስፈልጉትን ዘመናዊ ማሽኖችን እና የውጭ አገር ባለሙያዎችን ከውጭ ሀገራት በማስመጣት ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኙ የተለያዩ ፋብሪካዎች የማሸጊያ ምርቶችን ማቅረብ ጀመሩ።
የማሸጊያ ኢንዱስትሪ ዘርፉ በኢትዮጵያ ያላደገ እና በቂ የሰለጠነ የሰው ኃይል የሌለው በመሆኑ አቶ ከበደ በተደጋጋሚ የተቸገሩበት ጉዳይ መሆኑን ይናገራሉ። ለዚህ እንደመፍትሄነት የወሰዱት እርምጃ ደግሞ ገበያው ላይ ከሚያገኟቸው ባለሙያዎች ባለፈ አሰልጥኖ ማሰራት የሚለውን አካሄድ ነው። በዚህ አካሄድ ከውጭ የሚመጡ ባለሙያዎች ሰራተኞቻቸውን በማሰልጠን ባጭር ጊዜ ውስጥ የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ የፕላስቲክና የካርቶን ማሸጊያ ምርቶችን የማቅረቡን ስራ ማስቀጠል ችለዋል።
ስራውን እንደጀመሩ ግን የካርቶን ማምረቻው እና የፕላስቲክ ማሸጊያዎች ማምረቻ ቦታ አንድ ላይ ነበርና የእሳት አደጋ ይፈጠራል የሚል ስጋት በከፍተኛ ሁኔታ ያስጨንቃቸው እንደነበር ያስታውሳሉ።
ከስራ ሂደቱ አንጻር በፋብሪካው ያለው ቦታ አነስተኛ በመሆኑ የተለያዩ ተቀጣጣይ ኬሚካሎችን አንድ ላይ ማስቀመጡ አደጋ ሊፈጥር የሚችል በመሆኑ በቦታ እጥረት ምክንያት የካርቶን ምርቱን ወዲያውኑ ማቆማቸውን ይናገራሉ። በመሆኑም ትኩረታቸው በፕላስቲክ ማሸጊያዎች ላይ ብቻ በማድረግ የተለያዩ ኬሚካሎችን እያስመጡ ማምረቱን ተ ያያዙት።
በጥቂት ጊዜያት ውስጥ ክላሲክ ፓኬጂንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በሚል ስም በተመሰረተው ፋብሪካ ስር በተለይ ለጨርቃጨርቅ፣ የምግብ እና መጠጥ አምራቾች እንዲሁም ለተለያዩ አምራቾች የሚሆኑ ማሸጊያዎች በመቅረባቸው አምራቾቹ ከውጭ ሀገራት ይልቅ የአቶ ከበደን ፋብሪካ ማሸጊያዎች ምርጫቸው አድርገዋል።
የታሸገ የውሃ ምርት ላይ የሚለጠፉ አርማ እና ስም የያዙ ፕላስቲክ ማሸጊያዎች፣ የባልትና ውጤት ማሸጊያዎች እና የተለያዩ የፕላስቲክ ውጤቶችም ህትመትን ባካተተ መልኩ ተዘጋጅተው ለአምራች ድርጅቶች እያቀረቡ ይገኛል። በዚህም ቀደም ሲል ከውጭ የሚገቡትን ማሸጊያዎች በአገር ውስጥ በመተካት የአገርን የውጭ ምንዛሪን ችግርን በመቅረፍ ደረጃ አቶ ከበደ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ በመወጣታቸው የመንፈስ እርካታ እንደሚሰማቸው ይናገራሉ።
ከደንበኞቻቸው የሚቀርበው የምርቱን ፍላጎት እየጨመረ ቢመጣም ግን የፋብሪካውን አቅም ለማስፋፋት ባለው የቦታ ጥበቅ ምክንያት በሙሉ አቅም እየተንቀሳቀሱ አለመሆኑን አቶ ከበደ ይናገራሉ። ከዚህ ባለፈ የውጭ ምንዛሬው እጥረት እና የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት ችግር ስራቸው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል። በዚህ ምክንያት የፋብሪካቸው አቅም እስከ አምስት ሺ ቶን ምርት ቢሆንም በአሁኑ ወቅት የሚያመርቱት ግን 1ሺ 500 ቶን የፕላስቲክ ማሸጊያ ምርት ነው።
ይሁንና አቶ ከበደ ለኬሚካል ግብዓቶች በአንድ ቦታ ቢታጨቁም ሆነ የተለያየ የመስሪያ ቦታ ችግር ቢገጥማቸውም በችግሩ እራሳቸውን አጥረው ከማስቀመጥ የተጣበበ ቦታም ቢሆን ተጨማሪ የማምረቻ ማሽኖችን በፋብሪካቸው አስተክለዋል። በዚህም አቅማቸውን አደራጅተው በአመት 5ሺ ቶን ምርት ለማቅረብ ዝግጅት ላይ ናቸው።
ድርጅታቸው ክላሲክ ፓኬጂንግ ባዘጋጀው ሰፊ የማስፋፊያ ፕሮጀክት ውጤታማ ወደመሆን እየተሸጋገረ ነው። በዚህም በዓለም ባንክ እና ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ጋር በተደረሰ ስምምነት መሠረት ለማኒፋክቸሪንግ ዘርፍ የፋይናንስ ድጋፍ ለማድረግ ከተመረጡ ጥቂት የአገር ውስጥ ድርጅቶች መካከል አንዱ ሆኗል፡፡ በድርጅቱ ለቀረጸው የማስፋፊያ ፕሮጀክት የሚውል የፋይናንስ ድጋፍ በማግኘቱ ምክንያት ዘመናዊ የማሽነሪ ግዢ በመፈጸም ወደ አገር እንዲገቡ አድርጓል። ማሽኖቹም በህትመት የታገዘ ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን አዳዲስ የፕላስቲክ ማሸጊያዎችን የማምረት አቅም አለው።
በማስፋፊያ ፕሮጀክቱ የምርቱ ተጠቃሚ ለማድረግ የታሰቡት ደንበኞች በኤክስፖርት ንግድ ሥራ የተሰማሩ አግሮ ኢንዱስትሪ ፣ቡና እና በጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ምርት ላይ የተሰማሩ ናቸው። በአገር ውስጥ ገበያ ለሚመረቱና በከፍተኛ ማሸጊያ እጥረት ለሚቸገሩ እንደ ፓስታና መኮሮኒ ፣የስጋና ወተት ተዋጽኦ ምርቶች ለተሰማሩ ደንበኞች ለማቅረብ ዝግጅት አድርገዋል።
አሁን ላይ የአቶ ከበደ ማሸጊያ ማምረቻ ፋብሪካ ለ150 ሰዎች የስራ እድል መፈጠር የቻለ ሲሆን፣ ከህንድ የመጡ ባለሙያዎችንም ቀጥረው ለሰራተኞች የተለያዩ የስራ ላይ የቴክኖሎጂ ሽግግር የሙያ ስልጠናዎችን እየሰጡ ይገኛል። ፋብሪካው በሽፍት 24 ሰዓታት የሚሰራ ነው።
«ከጫማ ምርት እስከ ምግብ ማቀነባበሪያ ያሉ ፋብሪካዎችም ሆኑ የተለያዩ ማምረቻዎች በአሁኑ ወቅት ጥራቱን የጠበቀ የማሸጊያ ምርት የሚያስፈልጋቸው ጊዜ ላይ ነን» የሚሉት አቶ ከበደ፤ በዚህ ረገድ በኢትዮጵያ በቂ ስራ ተከናውኗል ተብሎ እንደማይታሰብ ይናገራሉ። በመሆኑም በቀጣይ ከመንግስት ጋር በመነጋገር የቦታ እና የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ሲመቻችላቸው በርካታ ሰራተኞችን መቅጠር የሚያስችል ግዙፍ የማሸጊያ ኢንዱስትሪ ለመክፈት ውጥን አላቸው። ውጥናቸው ከተሳካም እስከ 50ሺ ሰው መቅጠር የሚያስችል የስራ ፈጠራ እጃቸው ላይ እንዳለም ይገልጻሉ።
ባለትዳርና የአራት ልጆች አባት ለሆኑት አቶ ከበደ ስራ ማለት ከስምፍና የተላቀቀ እና ሰዎችን በለውጥ ጎዳና የሚያራምድ መሆን አለበት። በዚህ ረገድ ወጣቶች ከልግመኝነት ተላቀው በእራሳቸው መንገድ የስራ ፈጠራው ላይ ቢሰማሩ ለአገርም ለወገንም የሚበጅ ውጤት ማምጣት ይችላሉ ሲሉም ይመክራሉ ።
አዲስ ዘመን ግንቦት 8/2012
ጌትነት ተስፋማርያም