አዲሱ ዓመት ከባተ አንድ ወር አስቆጥሯል። ብራ ሆኖ የከረመው መስከረም ለብዙዎች መልካም ሆኖላቸው አልፏል። በርካቶች ዓመቱን የተቀበሉት በተለየ ስሜትና ብሩህ በሆነ ተስፋ ነው። ተማሪዎች በአዲስ መንፈስ ትምህርት ቤት መዋል ጀምረዋል። አንዳንዶች ደግሞ በዓመቱ ጅማሬ ውጥናቸውን ለማሳካት ዕቅድ መንደፍ ይዘዋል። የወቅቱ አየር ንፋስና ፀሐይ የደባለቀ ነው። ብዙዎች ወቅቱን ወደው ተቀብለውታል።
አሁን ደማቁ የመስከረም ወር ተጠናቋል። ተረኛው የጥቅምት ወር ጊዜውን ሲረከብ ተከትሎ የመጣው ቅዝቃዜና ውርጭ ለበርካቶች የተመቸ አይመስልም። ክረምቱን በዝናብና ጭቃ ያሳለፈ ሁሉ የመስከረምን ፈገግታ በወጉ ሳይጠግብ ውርጫሙ ጥቅምት ደርሶበታል። በቅዝቃዜው ጭብጥ ኩርምት ማለት የጀምሩ አንዳንዶች የወቅቱን ጠባይ ለማስታመም በወፋፍራም ልብሶች መጀቦን ይዘዋል። ‹‹በጥቅምት አንድ አጥንት›› የተባለለት እግረ ቀዝቃዛው ወርም ማንነቱን አልዘነጋም። በእርጥብ ትንፋሹ ከመላ ሰውነት ዘልቆ ማንዘፍዘፍ ማንቀጥቀጡን ቀጥሏል።
ብርዱን ማሸነፍ ያሰቡ ጥቂቶች ራሳቸውን ለማሞቅ አልኮል ቢጤ መቀማመስን ለምደዋል። ከመጠጥ ቤት ጓዳ የመሸጉ አንዳንዶችም ወቅቱን አሳበው ከሚቀዳላቸው መጠጥ አንድ ሁለት ማለትን ቀጥለዋል። ሰሞኑን ደግሞ እንዲህ የሚያደርጉ ደንበኞች ተበራክተዋል። ክረምቱን አልፈው ከበጋው ሲገኙ ዳግም በቅዝቃዜ ላለመረታት የፈጠሩት መቆያ መሆኑ ነው።
የአገር ልጆች
በአንድ አካባቢ ተወልደው ያደጉት ባልንጀሮች በአገር ልጅነት ስሜት መሰባሰብ ልማዳቸው ነው። በተገናኙ ጊዜ የአካባቢያቸውን ኑሮና የተለመደ ሕይወት እያነሱ ያወጋሉ። ርቀው ለመጡበት አላማ ሰርተው በማግኘት ወላጆቻቸውን ስለመደገፍ ደጋግመው ያወራሉ።
አራቱ ባልንጀሮች ከአንድ ቀዬ ተወልደው አላደጉም። የሁሉም መገኛና ዕድገትም በቀረበ አካባቢ አይደለም። በውሏቸው አጋጣሚ በተነሳ ጨዋታ ግን ሁሉም የአንድ አገር ልጆች መሆናቸውን ካወቁ ቆይተዋል። ይህ እውቂያቸው ደግሞ ከሌሎች የበለጠ አቀራርቦ ከአንድ እያዋለ ምስጢር ያጋራቸው ጀምሯል። ጓደኛሞቹ አንዳንዴ ጊዜያቸውን በመዝናናት ሲያሳልፉ አብሮነታቸውን ማሳየት ይሻሉ። ሁሌም ለጨዋታም ይሁን ለሚፈጠር ግጭት አንድ መሆናቸውን ማሳየታቸው አይቀርም።
አራቱ ጓደኛሞች ያቀራረባቸውን የአገር ልጅነት ብዙዎች ያውቁታል። እንደወንድም ሲተባበሩ ያዩ በርካቶች ሁሌም ያደንቋቸዋል። ባልተገባ መንገድ ሲቀናጁ የሚያውቁ አንዳንዶች ደግሞ ድርጊታቸውን እያወሱ ያነውሩታል።
ባልንጀሮቹ በተለያየ ጊዜ አዲስ አበባ ከመጡ ወዲህ ኑሯቸውን በከተማ ሕይወት ወስነው ዓመታትን አስቆጥረዋል። ሁሉም ለእንጀራ ፍለጋ ከቀያቸው እንደወጡ ያውቃሉ። ዓመታትን የቆጠሩበት የቀንሥራ ገቢም ተመሳሳይ ሕይወትን ያጋራቸዋል። በእረፍት ቀናቸው በተገናኙ ጊዜ ጨዋታቸው ሁሉ አንድ ዓይነት ነው። ስለዕለት ውሏቸው ስለሚከፈላቸውና ስለወደፊት ዕቅዳቸው ያወጋሉ።
አንዳንዴ ሰብስብ ብለው መዝናናትን ሲሹ በቀጠሮ ይገናኛሉ። በግብዣና ጨዋታ ብዛት ሰዓቱን ገፍተውም ሌሊቱን አጋምሰው ይገባሉ። በቆይታቸው ከሌሎች ጋር ችግር ቢያጋጥም እንደሁልጊዜው እኩል ከማበር አይመለሱም። ጠብም ይሁን ጭቅጭቅ በአንድ ክንድ ተባብረው ይመክቱታል።
ባልንጀሮቹ ከአንዳንዶች ጋር ጠብ በገጠሙ ጊዜ ጭካኔያቸው ይበዛል። በስፍራው ያገኙትን ወንበርም ይሁን ጠርሙስ እንደ መሣሪያ መጠቀም ልምዳቸው ነው። ምህረት የለሽ ድርጊታቸውን የሚያውቁ በርካቶችም እነሱ ካሉበት ስፍራ መቆየትን አይሹም።
የላምበረት አካባቢን ለመኖሪያ የመረጡት ወጣቶች ለቤት ኪራይና ለሌሎች ወጪዎች የሚጠበቅባቸው ገንዘብ ቀላል አይደለም። አንዳንዴ አውደዓመትን አስታከው ወደቤተሰብ የሚልኩት ገንዘብም መጓደል እንደማይኖርበት ያውቃሉ። ለዚህ ስኬት በርትተው መስራት አለባቸውና ጉልበታቸውን ለሥራ አይቆጥቡም።
ያገር ልጆቹ ከቤት ጣጣና ከግል ጉዳይ የተረፈውን ለመዝናኛቸው ማድረግን ለምደዋል። አንዳንዴ ውለውና አምሽተው በሚሄዱበት መጠጥ ቤት በርከት ያለ ገንዘብ ያጠፋሉ። በዚህ መሀል ሞቅታ ቢፈጠርና ስካር ቢኖር ደግሞ ማንንም መመከት እንደሚችሉ ለራሳቸው ይነግሩታል።
አስታራቂው
ብሩክ ገቢሳ የላምበረት አካባቢ ነዋሪ ነው። ሰላማዊና ጠብ የማይሻ ወጣት ስለመሆኑ ብዘዎች ይመሰክራሉ። አንዳንዴ ብቅ እያለ በሚዝናናበት ቦታ ጥቂት ጓደኞቹ ያጅቡታል። በነዚህ ስፍራዎች ሲገኝ ደግሞ የሁልጊዜም ምርጫው ሳቅና ጨዋታን ማስቀደም ነው። ለእሱ ጠብ ይሉት ግርግር ተመችቶት አያውቅም። ድንገት የሚፈጠር አለመግባባትና ድበድብ ካለ ደግሞ እንደዋዛ አይቶ ማለፍ አይሆንለትም። ብዙ ጊዜ በጠብ መሀል ዘሎ ይገባል። የተያያዙትን አላቆ የተናነቁትን አለያይቶ ነገሩን በሰላም ይፈታል። ዘወትር ለበጎነት የሚፈጥነው ወጣት ችግሮችን ለመፍታት ጊዜ ወስዶ አያውቅም። በሽምግልናና በእርቅ መሀል ተገኝቶ የተቀያየመን ያስማማል። የተኳረፈን እጅ ለእጅ አጨባብጦም ፍቅርና ሰላምን ይመልሳል ።
ብሩክ የጥቅምት ብርድ ባየለበት አንድ ምሽት ከቅርብ ጓደኛው ጋር ቀጠሮ ይዟል። ሁለቱ የሚገናኙበት ስፍራ ምግብ ቤት እንደመሆኑ እንግዶች ይበዙበታል። በዚህ ስፍራ ራት በልተው የሚለያዩ፣ ምሽቱን መጠጥ ይዘው የሚዝናኑ ፣ በጨዋታ ጥቂት ቆይተው የሚሄዱ አይታጡም።
ወጣቱ ከምግብ ቤቱ ሲደርስ ሰዓቱ ገፍቷል። ራመድ እያለ ወደ ሳሎኑ ዘለቀ። ወዲያው ውስጥ ያለው ሙቀት ፈጥኖ ተቀበለው። ይህኔ አብሮት የቆየው ቅዝቃዜ ሲለቀው ተሰማው። ምግብ ቤቱን ዳር እስከዳር እየቃኘ ፍለጋውን ቀጠለ። የሚፈልገው ሰው አልታየውም። ባሻገር እያስተዋለ ከአንድ ጥግ አረፍ አለና የሚታዘዘው አስተናጋጅ እንዲያየው ወደባንኮኒው አንጋጠጠ።
ብሩክ ከአንድ ጠረጴዛ ከበው የተቀመጡ ጓደኛሞች መኖራቸውን አስተውሏል። ሁሉም በሞቅታ እየተዝናኑ ነው። ከነዚህ መሀል አብዛኞቹ እርስበርስ እየተደማመጡ አይደለም። ሁሉንም በትዝብት እያስተዋለ ወደ መግቢያው በር አተኮረ።
አራቱ ባልንጀሮች እንደተለመደው በአንድ ጠረጴዛ ከበው ያውካካሉ። ፊትለፊታቸው የተደረደሩ ባዶ የቢራ ጠርሙሶች ለሞቅታቸው ምስክሮች ሆነዋል። ደጋግመው የሚያዙትን መጠጥ በፍጥነት እያጋቡ ይጫወታሉ። ምሽቱ እየገፋ ቢሆንም አንዳቸውም ለመውጣት የቸኮሉ አይመስሉም።
ጥቂት ቆይቶ አንድ ሰው ከውጭ ወደውስጥ ሲገባ ታየ። የብሩክ ጓደኛ መኮንን ነበር። በባልንጀራው መድረስ ፊቱ የፈካው ወጣት ያለበትን ቦታ በእጁ እያመለከተ እሱ ወዳለበት ወንበር እንዲመጣ ጋበዘው። መኮንን የብሩክን አቅጣጫ ተከትሎ አጠገቡ ደረሰና ከጎኑ ተቀመጠ።
የሚፈልጉትን አዘው መገባበዝ እንደጀመሩ አንድ ሰው ከጓደኞቹ መሀል ተነስቶ እነሱ ያሉበትን ሦስተኛ ወንበር ተጋራ። ብሩክ ከመኮንን ጋር እንደሚተዋወቁ ገባው። የሰውዬው ግንባር በአንዳች ምክንያት መኮሳተሩ ያስታውቃል። ጎናቸው እስኪደርሰ በገጽታው ላይ ፈገግታ አይታይም። መኮንንን እንዳገኘ ማውራት የፈለገው ጉዳይ ነበር። ሰላምታውን ገሸሽ ብሎ ቀጥታ በጉዳዩ ላይ መነጋገር ጀመሩ። ጨዋታቸው ሰላማዊ አልነበረም። የቆየ ጉዳይ እየመዘዙ፣ ያለፈውን ከአሁን እያወሱ ያለቅጥ ተጨቃጨቁ ተወዛገቡ።
ብሩክ የሁለቱን ሁኔታ እንዳየ ከመሀል ለመግባት ፈለገ። ሀሳቡ ካሉቡት መንፈስ ተመልሰው እንዲስማሙ ማድረግ ነበር። ሁለቱም ሊሰሙት አልፈቀዱም። በሀይለቃል እየጮሁ፤ በንዴት እየተወራጩ፣ ጭቅጭቃቸውን ቀጠሉ።
ከነሱ አለፍ ብሎ ካለው ጠረጰዛ ላይ የተቀመጡት ሦስት ሰዎች የሁለቱን ጭቅጭቅ በአትኩሮት ያስተውላሉ። ከመኮንን ጋር የሚጨቃጨቀው ወጣት የእነሱ የቅርብ ጓደኛና የአገር ልጅ ደነቀው ነው። የደነቀው ጓደኞች ባልንጀራቸው ችግር ላይ መሆኑን እንዳዩ በዓይናቸው ተናበቡ። እንደለመዱት ከመሀል ገብተው ጉዳዩን መስመር ማስያዝ እንዳለባቸው ወስነውም ከነበሩበት ተነሱ።
ሦስቱ ባልንጀሮች እነብሩክ አጠገብ እንደደረሱ ሁኔታውም ቀረብ ብለው አስተዋሉ። ብሩክ ሁለቱን ለማስማማት የበኩሉን ማድረግ ይዟል። በየመሀሉ የደነቀውን ትከሻ እየነካም ጉዳዩን ቀለል እንዲያደርገው መወትወት ጀምሯል። ደነቀው የብሩክ ደጋግሞ ማግባባት አልተመቸውም። በየመሀሉ እየገባ ነገሩን እንዲተው ትከሻውን መንካቱም ያበሳጨው ይዟል።
አሁንም ጭቅጭቁ ጠንክሯል። ብሩክም የደነቀውን ትከሻ እየነካ ተው ማለቱን ቀጥሏል። ደነቀው ይበልጥ እየነደደው ነው። ሦስቱ ባልንጀሮች ከዳር ሆነው ማየታቸውን አልተዉም። ድንገት ከመኮንን ወደ ደነቀው የተሰነዘረ ቡጢ የጠቡን ከባድ ምዕራፍ ሊያስጀምር ግድ አለ። ይህኔ በተጠንቀቅ የቆሙት ሦስቱ ጓደኛሞች ለባልንጀራቸው ለማገዝ ከጠቡ አውድማ ተቀላቀሉ።
ቡጢውና እርግጫው ቀጠለ። አራት ሆነው ሁለቱን ከበቡ። መኮንን ሁኔታውን እንዳየ ራሱን ለማዳን ተዘጋጀ። ጉዳዩ ወደእሱ እንደሚዞር ያልገባው ብሩክ አሁንም ተስፋ ሳይቆርጥ ግልግሉን ቀጠለ። እንደታሰበው አልሆነም። በሁኔታው ሲበሽቅ የቆየው ደነቀው እጁን ከጓደኛው ላይ አሳልፎ ጸጉሩን ጨምድዶ ያዘው። ይህን ያዩ ሌሎች ባልንጀሮችም እሱን ተከትለው በብሩክ ላይ ተረባረቡ።
ደነቀው ከመሀል ወጣና አንድ የቢራ ጠርሙስ አነሳ። አነጣጥሮም ወደ ብሩክ አቅጣጫ ላከው። ጠርሙሱ ዒላማውን አልሳተም። የብሩክን ጭንቅላት ለሁለት ገምሶና በደም ተለውሶ ከመሬት ወድቆ ተሰበረ። ደነቀው ዞር ብሎ አንድ የብረት ወንበር አነሳ። እሱን ከመወርወሩ አንድ ወንበር አዘጋጅቶ የያዘው ሌላ ጓደኛው አስተካክሎ ወረወረው። አሁንም ከብሩክ አካል ላይ ያረፈው ወንበር ያሰበውን ፈጽሞ ከመሬት ላይ አረፈ።
ደነቀው የያዘውን ወንበር ሳይለቅ ዳግመኛ ወደ ብሩክ ወረወረ። ይህኔ ሌላው ተጠጋና በወንበሩ የብሩክን እጆችና ትከሻ ደጋግሞ እየቀጠቀጠ አዳከመው። ሦስተኛው ሰው ወደብሩክ ሲንደረደር የቢራ ጠርሙስ ይዞ ነበር። በጠርሙሱ ያሻውን አድርጎ ሲመለስ አራተኛው ከውጭ ያገኘውን ወፍራም አጣና እንደጨበጠ ወደብሩክ ተጠጋና ጭንቅላቱን፣ እጅና ጀርባውን እያፈራረቀ ቀጠቀጠው።
በደም ተለውሶ ከመሬት የተዘረረው ብሩክ የአራቱን ባልንጀሮች ጡጫ መቋቋም አልተቻለውም። ከሁሉም ትከሻ በጭካኔ የወረደበትን የግፍ ጥቃት ተቀብሎ በሽንፈት እጁን ሰጠ። በድብደባው ድል የነሱት ጓደኛሞች ‹‹በበቃን›› ስሜት ከሆቴሉ ለመውጣት ተሰናዱ። በድንገት ደርሶ የሆቴሉን ግቢ የከበበው ፖሊስ ግን ከስፍራው ሳይርቁ ሁሉንም በቁጥጥር ስር አውሎ ወደሕግ አደረሳቸው።
የፖሊስ ምርመራ
ጥቅምት 25 ቀን 2011 ዓ.ም ከምሽቱ አምስት ሰዓት ሲል ጥቆማ የደረሰው ፖሊስ ወደ ሆቴሉ ገሰገሰ። ተጠርጣሪዎችን ወደ ሕግ ከማቅረቡ በፊት ጭካኔ በተመላበት ጥቃት በደም ተለውሶ ከመሬት የተዘረረውን ወጣት ትንፋሽ አዳመጠ። ብሩክ አይኖቹ ተከድነው መላ ሰውነቱ ቀዝቅዟል። በሕይወት አለመኖሩን የተረዳው ፖሊስ ተጨማሪ ምርመራዎችን ለማድረግ ቡድኖችን አዋቅሮ አስከሬኑን አነሳ።
አራቱ ተከሳሾች በድንገቴው ጠብ መሀል ተገኝተው በወጣቱ ላይ የፈጸሙትን ድርጊት አልካዱም። በመርማሪው ዋናሳጂን ሰመረ ገብረኪዳን የሚቀርብላቸውን ጥያቄዎች በመመለስ የዕምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጡ። ይህ መረጃ ትክክል ስለመሆኑ ያረጋገጡበት የተጠርጣሪዎች ፊርማና ቃል በፖሊስ መዝገብ ቁጥር 564/ 11 ላይ ሰፍሮ ክስ ይመሰረትበት ዘንድ በአስረጂነት ለዓቃቤሕግ ተላለፈ።
ውሳኔ
መጋቢት 3 ቀን 2012 ዓ.ም በችሎቱ የተሰየመው የልደታው ከፍተኛ ፍርድቤት በከባድ የሰው መግደል ወንጀል ተከሰው የቀረቡትን አራት ጓደኛሞች ክስ ሲመረምር ቆይቶ ለመጨረሻው ወሳኔ በቀጠሮ ተገኝቷል። ፍርድቤቱ ተከሳሾቹ ነውረኝነትና ጭካኔ በተመላበት ድርጊት በአንድ ወጣት ላይ የፈፀሙት ግድያ ጥፋተኛ እንዳሰኛቸው አረጋግጧል። በዕለቱ ባሳለፈው ውሳኔም ሁሉም ወንጀለኞች እጃቸው ከተያዘበት ጊዜ ጀምሮ በሚታሰብ የ18 ዓመት ጽኑ አስራት ይቀጡልኝ ሲል በይኗል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 8/2012
መልካምስራ አፈወርቅ