የተወለዱት አዲስ አበባ በተለምዶ እሪ በከንቱ በሚባለው አካባቢ ነው። ይሁንና የቤተሰቡ ቤት ወንዝ ዳር በመሆኑ ጎርፍ ይከሰትና ይፈርሳል። መንግሥትም በልማት ድርጅቶች የአካባቢዎቹን ነዋሪዎች አንስቶ መገናኛ 24 ቀበሌ በሚባለው አካባቢ ቤት ሰጥቶ ያሰፍራቸዋል። በመሆኑም የዛሬው የዘመን እንግዳችን ገና የሁለት ዓመት ጨቅላ እያሉ እዚያው መገናኛ አካባቢ ለማደግ ተገደዱ። በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኙት ዘርፈሸዋል (ምሥራቅ በር) እና የካቶሊክ ሚሽን ትምህርት ቤቶች ተማሩ። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በምሥራቅ አጠቃላይ ተከታትለዋል። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብተውም የመጀመሪያና የሁለተኛ ዲግሪያቸውን በታሪክ ሰርተዋል።
አወሊያ፥ ኑርሰላምና ዲላ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት ከሰሩባቸው ተቋማት መካከል ይጠቀሳሉ። የታሪክ ምሁሩ እኚሁ ሰው ታዲያ ነፃ የትምህርት ዕድል አግኝተው ቱርክ የመሄድ ዕድሉን አግኝተውም ነበር። በቆይታቸውም ከትምህርታቸው ጎን ለጎን በቱርክ መንግሥት በሚደገፍ ትልቅ ሚዲያ መስራት ጀመሩ። ይሁንና የሚዲያ ሥራው ሰፊ ሰዓት የሚጠይቅ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሁለቱንም እኩል ማስኬድ ባለመቻላቸው የዶክትሬት ዲግሪ ትምህርታቸውን ለማቋረጥ ተገደዱ። ለሰባት ዓመታት ባገለገሉበት በዚሁ የሚዲያ ተቋም ውስጥ ግን በተለይም በምሥራቅ አፍሪካና በኢትዮጵያ ፖለቲካና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰሯቸው ዶክመንተሪዎች እንዲሁም በሚሰጧቸው ትንታኔዎች ከፍተኛ ተቀባይነት አግኝተዋል። ይህንን የተመለከተ አንድ የካናዳ ድርጅትም በእ.ኤ.አ 2018ዓ.ም የምሥራቅ አፍሪካ ተፅእኖ ፈጣሪ በሚል እውቅና ችሯቸዋል።
ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት የሆኑት እኚሁ የታሪክ ሰው በኢትዮጵያ የመጣውን ፖለቲካ ለውጥ ተከትለው ካለፈው ሁለት ዓ መት ወዲህ ወደ አገራቸው ተመልሰዋል። በአሁኑ ወቅትም በአካባቢያዊ ትስስር ላይ በሚሰራ ሴንተር ፎር ናሽናል ኤንድ ሪጅናል ኢንተግሬሽን ስተዲስ በተባለ ተቋም ውስጥ በሥራ አስኪያጅነት እያገለገሉ ይገኛሉ። ከታሪክ ምሁሩና የሚዲያ ባለሙያ ከአቶ ኢብራሂም ሙሉሸዋ ጋር በታሪክና በተለያዩ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ያደረግነው እንደሚከተለው ቀርቧል።
አዲስ ዘመን፡- ለትምህርት በሄዱባት ቱርክ ትምህርትዎን ትተው ወደ ሚዲያው ዓ ለም የገቡበትን አጋጣሚ ያስታውሱንና ውይይታችን እንጀምር?
አቶ ኢብራሂም፡- እንዳልሽው እኔ ወደ ቱርክ መጀመሪያ የሄድኩት ነፃ የትምህርት አግኝቼ የነበረ ቢሆንም በፖለቲካና በታሪክ ላይ በምሰጣቸው አስተያየቶች የተማረከው አንድ መምህሬ ይህንን ልጅ ልጠቀምበት ይገባል ብሎ አርታኢና የፖለቲካ ተንታኝ ሆኜ ሚዲያውን እንድቀላቀል አደረገኝ። በነገራችን ላይ ሚዲያው ትልቅ የቱርክ መንግሥት የፕሮፖጋንዳ ማዕከል ነው። እዚያ በቆየሁባቸው ጊዜያት በእነሱ ሚዲያ የእነሱን ፖለቲካም እተነትን ነበር። የሚዲያ ሥ ራው ብዙ ጊዜ የሚፈልግና ቀኑን ሙሉ መዋል የሚፈልግ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አብሬ ማስኬድ ባለመቻሌ ፊቴን ሙሉ ለሙሉ ወደ ሚዲያ ሥራው አዞርኩ።
በዚያ ሚዲያ በምሰራበት ጊዜ በተለይም በኢትዮጵያና በምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች ላይ ትንታኔ እሰጥ ነበር። ከሰራኋቸው ሥ ራዎች ውስጥ ኢትዮጵያ ብዝሃነቷን ጠብቃ አንድነቷን ለማስቀጠል ምን መስራት እንደሚገባት፤ ዘመኑን የዋጀ የፖለቲካ ሂደት እንዴት ሊፈጠር ይችላል?፤ በተለያየ መንገድ ተበድለናል ተገፍተናል ያሉ የማህበረሰብ ክፍሎች እንዴት አድርገው ለዚህች አገር ችግር በሰለጠነ መንገድ አስተዋፅኦ ያድርጉ? በሚሉ ርዕሶች የሰራኋቸው ይጠቀሳሉ።
በነገራችን ላይ የቱርክ ቆይታዬ ብዙ እውቀትና ልምድ ያገኘሁበት ነው። በተለይም የሙስሊም ሀገሮች የፖለቲካ ጉዳይ ላይ የነበረኝን ግንዛቤ አሳድጎልኛል። ቱርክ በመልካምድራዊ አቀማመጧ በእሲያና በአውሮፓ መካከል ያለች አገር እንደመሆኗ የሕዝቧ ባህልም ሆነ ፖለቲካዋ ከምዕራቡና ከምሥራቁ ዓ ለም የተቀዳ ነው። ይህም በተለይም የአገሪቱ ፖለቲከኞች ሁለት ፅንፍ እንዲይዙ ያደረገ መሆኑ ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ የሚያስተሳስረው መሆኑን በቱርክ ቆይታዬ ተረድቻለሁ። ግን ልክ እንደእኛ አገር የብሔር ሳይሆን የመልካምድር መገፋፋት ያለበት አገር ነው።
ሌላው እንደቱርክ ለእኛ አገር በፖለቲካ ምሳሌ የሚሆን አገር ያለ አይመስለኝም። ቱርኮች እንደኛ አገር በታሪክ ላይ የማይሰማሙባቸው ጉዳዮች አሉ። አገሪቱ ወዴት ትሂድ? የሚለው ጉዳይም አያግባባቸውም። በዘመናዊ ታሪኳ ብቻ ስድስት መፈንቅለመንግሥት አስተናግዳለች። ከ20 ዓመት ወዲህ ግን ዴሞክራሲን በራሳቸው መንገድ ለማስፈን ሙከራ አድርገዋል። አንዳንዶቹ የአውሮፓ አገራት ቱርክ ሙሉ ዴሞክራሲ የላትም ይላሉ። ግን ቱርክ ግን በራሷ ዴሞክራሲያዊ አገር መሆኗን ነው የምታምነው። እኔም ብሆን በራሷ አካሄድ ዴሞክራሲያዊ እንደሆነች አምናለሁ። ምክንያቱም አንድ አገር ዴሞክራሲያዊነው የሚያስብላትን ምርጫ ማካሄድ፥ ሚዲያዎች በነፃነት እንዲሰሩና ሁሉም የፖለቲካ ኃ ይል በነፃነት የመናገር መብቱ በቱርክ ጠብቆ እንደሚኖር ለመታዘብ ችያለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያውያንንና ቱርኮችን በታሪክ ላይ ያላቸው ምልከታ መመሳል የሚያሳይ አብነት ሊጠቅሱልኝ ይችላሉ?
አቶ ኢብራሂም፡- እንዳልኩሽ ቱርኮች በታሪካቸው ልክ እንደእኛ ሁሉ እርስበርስ አለመስማማታቸው ከእኛ ጋር ይበልጥ ያቀራርባቸዋል። ለምሳሌ እኛ በአፄ ምኒልክ ጉዳይ ላይ አንግባባም። አፄ ምኒልክ የታሪክ አንድ አካል ቢሆኑም እሳቸውን በሚመለከት ጫፍና ጫፍ የረገጡ አመለካከቶች አሉን። ለአንዳንዶች አፄ ምኒልክ እናት ናቸው። አፄ ምኒልክ ባይኖሩ ኖር እኛ አንኖርም ብለው የሚያስቡም አሉ። በሁለተኛው ጫፍ ደግሞ አፄ ምኒልክን እንደወንጀለኛ፤ ምንም ነገር እንዳልሰሩ፤ እንደጨቋኝ አድርገው የሚቆጥሩ ነበሩ። ልክ እንደእኛ ሁሉ ቱርኮችም አዲሲቷን ቱርክ የመሰረተው አታቱርክ ላይ ተመሳሳይ ሁለት ፅንፎች የያዙ አመለካከቶች አላቸው። ለአንዳንዶች በተለይ እስላማዊ አስተሳሰብ ላላቸው ሰዎች አታቱርክ ጠላት ነው። አታቱርክ የቱርክ መስራች ሳይሆን ቱርክ በኦቶማቾ ዘመን የነበራት ክብርና ገናናነት ያፈረሰና ለነጮች አሳልፎ የሰጠ ነው። ለሌሎች ደግሞ አታቱርክ ባይኖር ኖሮ ቱርክ የምትባል አገር አትኖርም ብለው እስከማምለክ የሚደርሱ አሉ። ቱርኮች አዲሱ መንግሥት እስከሚመጣ ድረስ ለ80 ዓመታት የአታቱርክ ደጋፊዎች ስልጣን ላይ የነበሩባት አገር ነች። በዚያን ወቅት አታቱርክን መንካት እንደወንጀል ነበር የሚያስቆጥረው።
ከ20 ዓመታት ወዲህ ግን እነኤርዶዋን የሚመሩት ፀረ አታቱርክ ኃይል መጣ። ይህ ኃይል የአታቱርክ ደጋፊዎች በተለይ በእምነት ላይ ያደርጉት የነበረውን ተፅእኖ በይፋ ይቃወም ነበር። ይሁንና ሥ ልጣን ሲይዙ ግን ግራ ገባቸው። ምክንያቱም አታቱርክ የሰራው መጥፎ ነገሮች እንዳሉ ሁሉ በርካታ መልካም ነገሮች መኖራቸውና ይህንንም የሚደግፉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጥቂት አለመሆናቸው ነው። እነሱ የሚከተሉት አመለካከት ከነባራዊው ሁኔታ ጋር የሚጣላ ሆነባቸው።
ይሁንና ይህን ችግራቸውን ቱርኮች የፈቱበት መንገድ ለኢትዮጵያ ጥሩ ምሳሌ የሚሆን ነው። እነ ኤርዱዋን በመጀመሪያ ያደረጉት አታቱርክ ሰው ነው እንደሰው መልካምም መጥፎ ነገር ሊሰራ እንደሚችል ማመናቸው ነው። አታቱርክ ቱርክን እንደአገር የመሰረተ እሱ ሆኖ ሳለ ከታሪክ መዝገብ ላይ መሰረዝ እንደማይችሉ ተቀበሉ። በተጨማሪም አታቱርክን እንደአንድ መሪ ማጥፋት ታሪካቸውን ማጥፋት እንደሆነም ተረዱ። ስለሆነም አታቱርክ ላይ ያላቸው ጥላቻ ከመግለፅ ተቆጠቡ። ጎን ለጎንም በሃይማኖት ላይ ይደረግ የነበረውን ተፅእኖ በተግባር አስወገዱ።
በመሆኑ አታ ቱርክን በማምለክና በመጥላት ያለውን ፅንፍ የወጣ አመለካከት ማስቀረት ቻሉ። እናም ይህ የቱርክ ተሞክሮ ለእኛም አገር የሚሰራ ይመስለኛል። ለአብነት ከጠቀስኩልሽ ከአፄ ምኒልክ ብንነሳ እኚህ ንጉስ ሰው ናቸው እንደሰው የሰሩትን መጥፎ ነገር ማውገዝ ብቻ ሳይሆን መልካም ሥራቸውንም ተቀብለን መሄዱ ጠቃሚ ነው የሚመስለኝ።
አዲስ ዘመን፡- አንዳንዶቹ በታሪክ አላግባባ ያሉ ጉዳዮች መፈጠር የጀመሩት ካለፉት 27 ዓመታት ወዲህ እንደሆነ ሆን ተብለው ታሪክ እንዲዛባ በመደረጉ እንደሆነ ይሞግታሉ፤ በዚህ ሃሳብ ይሰማማሉ?
አቶ ኢብራሂም፡- እኔ በዚህ ሃሳብ አልስማማም፤ በመጀመሪያ ደረጃ ይህች አገር ስትመሰረት በግጭት ነው የተመሰረተችው። ይህ ደግሞ የተለመደና የትም አገር የሚከሰት ነው። አንዳንድ ሰዎች ህወሓት ስለተሸነፈ ሁሉንም ነገር ህወሓት ላይ መጫን ይፈልጋሉ። በነገራችን ላይ ህወሓትም የተመሰረተው እኮ የትግራይ ሕዝብ ተጨቁኗል ከሚል ነው። ኤርትራም ልትገነጠል የቻለችው ተጨቁኛለሁ ከሚል ነው። ስለዚህ ትልቁ ጥያቄ ሊሆን የሚገባው ይህ እውነት አልነበረም ወይ? የሚለው ነው።
ኢትዮጵያ ውስጥ አገረ መንግሥቱ ሲመሰረት በአሸናፊና በተሸናፊ መካከል በተደረገ ጦርነት ነው የተመሰረተው። አፄ ምኒልክ ሁሉንም አካባቢዎች በጦር አስገብረው መሪዎቻቸውን አሸንፈው ነው አገር የመሰረቱት። እኔ በዚህ ጉዳይ ላይ ልክ ነው፤ ልክ አይደለም፤ በሚለው ላይ ብዙ መናገር አልፈልግም። ግን የሚያስከትለው ተፅእኖ እንዳለ አምናለሁ። ሁሌም ቢሆን አሸናፊ ካለ ተሸናፊ አለ። ለምሳሌ ሐረርን ይመሩ የነበሩት አሚር አብዱላሂ ተሸነፉ። ስለዚህ ይህች አገር አንዱ አንዱን ጨፍልቆ ነው የተመሰረተው። ይህ አንዱ እውነታ ነው። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ላይ አንድ ባህል አንድ ሃይማኖት አንድ ቋንቋ ሌሎች ላይ ተጭኗል። ይህ እውነታ ነው። ግን ይህ እውነት ሳያግባባን ኖሯል።
አዲስ ዘመን፡- ግን ይህ ችግር መፈጠር የጀመረው ከአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ብቻ ነው?
አቶ ኢብራሂም፡- አይደለም! እኔ እንዲያውም ችግሮች ሁሉ የተፈጠሩት በአፄ ምኒልክ ብቻ አድርገው የሚያነሱ ሰዎችን እቃወማለሁ። እኔ እንዲያውም በታሪክ በጣም ተጠያቂ አድርጌ መውሰድ ካለብኝ በአንደኛ ደረጃ የማስቀምጠው አፄ ኃ ይለስላሴን ነው። ምክንያቱም በታሪክ እንደምንረዳው አፄ ምኒልክ የጦርነት ዘመን ላይ ነው የመጡት፤ የነበራቸውም ዘመን በጣም አጭር ነው። በጣም ገነው የወጡትም በእ.አ.ኤ ከ1996ዓ.ም ታመው አልጋ ላይ እስከሚቆዩበት እስከ 1906 ዓ.ም ነው። በእነዚህ ጊዜያት ብቻ ነው ትልቅ ስልጣን የነበራቸው። አፄ ምኒልክ በየቦታው ሲያስገብሩ ሲዋጉ የነበሩ ሰው ነበሩ። ያንን ግን ለመለወጥ አልጋ ላይ ሆነው እንኳ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን አቋቁመዋል። አፄ ምኒልክ ሰሩ እንኳ ቢባል ያንን የመለወጥ ዕድሉ የነበራቸው በኋላ የመጡና የተረጋጉ መንግሥታት ናቸው። በዚህ ረገድ ይህንን ለማድረግ ትልቅ ጥረት ያደረጉት ልጅ እያሱ ናቸው። ልጅ እያሱ የተወገዱት እስላም ሆነሃል በሚል ነው፤ ግን አልሆኑም ነበር። ዋናው ነገር የፊውዳል ሥርዓቱ ኅብረተሰቡ ላይ የጫነው የባህል፥ የቋንቋ የሃይማኖት ተፅእኖ ሌሎቹንም ይዞ ኢትዮጵያ ሁልጊዜ ችግር ውስጥ እንድትገባ አድርጓል። ለነገሩ ሃይማኖትንም ሆነ ባህልን ተጭኖ ስኬታማ ብንሆን ኖሮ ችግር የለውም ነበር። ብዙ አገሮች ተሳክቶላቸው አይተናል። ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ፕሮጀክቱ ራሱ አልተሳካም። ይህ ካልተቻለ በተቻለ መጠን ሁሉንም ለማግባባት የሚደረግ ሥ ርዓት ለመፍጠር ዕድል መመቻቸት ነበረበት።
አዲስ ዘመን፡- ታዲያ የትኛው መንግሥት ነው ሁሉንም ሊያግባባ የሚችል ሥርዓት የፈጠረው?
አቶ ኢብራሂም፡- እውነት ለመናገር በሕግ ደረጃ የኢህአዴግ ሥ ርዓት ነው የሚሻለው። ይህ ሲባል ግን በንድፈሃሳብ እንጂ በተግባር ማለቴ አይደለም። ለምሳሌ የኢትዮጵያ ሕ ገመንግሥት በጣም ዴሞክራሲያዊ ነው። ማንም ይመሰክራል። የብሔርና የሃይማኖት እኩልነትን ለመጀመሪያ ጊዜ በሕግ ደረጃ ያረቀቀው ኢህአዴግ ነው። ግን ይህ ሕ ገመንግሥት ደግሞ በጣም ሴራ የበዛበትና ዴሞክራቲክ ካልሆነ አካል የመነጨ ነው። በተግባር ማዕከላዊ ያልሆነ ለክልሎች ስልጣን የሚሰጥ ነው። በስምምነት የፌዴራል መንግሥቱን የሚመሩ መሆናቸውን በሕግ ደረጃ ቢደነገግም በተግባር ግን ይህንን አናየውም። በተጨማሪም በተግባር በጣም ማዕከላዊ የሆነ በአንድ ሰው የሚመራ በየክልሉ መንግሥት የሚያምናቸው ሰዎች ተመርጠው የሚሰሩበት ነው።
በነገራችን ላይ ሁሉንም ዝም ብሎ መጨፍለቅ ተገቢ አይደለም። ደርግም ሆነ ኃይለስላሴ የሰሩት መልካም ሥራ አለ። ነገር ግን አንዱም ጥረታቸው ስኬታማ አላደረገንም። እንደእኛ ብዙ ያልተሳኩ ፕሮጀክቶች ያሉባት አገር የለም። አንዱ ችግራችን የሚመስለኝ ብዝሃነታችን ራሱ ዋናው ችግራችን መሆኑን አልተቀበልነውም። ብዝሃነት ሁልጊዜ አሽሞንሙነነው የምናቀርበው። ይህም ታዲያ ብዙ ጊዜ ችግር ሲፈጥርብን ቆይቷል። በመሆኑም ብዝሃነታችን ፀጋ ብቻ ሳይሆን ተግዳሮታችንም መሆኑን አምነን መቀበል አለብን።
በሌላ በኩል ደግሞ ሁልጊዜ መፍትሄ የሚመጣው በመንግሥት ብቻ መሆኑ ሌላው የሚያግባባን ነገር እንዳይፈጠር ምክንያት ነው ብዬ አምናለሁ። ሁልጊዜም የመንግሥት መፍትሄ ዴሞክራሲያዊ ባልሆነ መንገድ ነው የሚመጣው። በዚህ ረገድ ሁሉም መንግሥቶቻችን ይህ ችግር አለባቸው። «እኔ ብቻ ነው የማውቅላችሁ» ይላሉ። እርግጥ ደርግ ትልቅ ጥያቄ የነበረውን መሬት ላራሹ ጉዳይ ፈቷል። ኢህአዴግ የቋንቋ፥ የባህል የሃይማኖትን እኩልነት ጥያቄ ፈቷል። ግን እነዚህን ሁሉ ሲያደርጉ በዴሞክራሲያዊ መንገድ እውነተኛ ተሳትፎ ያለፈበት፤ ሁሉንም አቅርቦ በድርድር የሚደረጉ አልነበሩም። በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ የተለየ የፖለቲካ ችግር እንዳለብን ነው የምናወራው። ከማንኛውም አገር የተለየ የፖለቲካ ችግር የለብንም። ነገር ግን የፖለቲካ ኃይሎች ቁጭ ብለው የመነጋገርና የችግሩን መሠረት የማግኘትና ያንን ደግሞ የመፍታት ችግር ግን አለብን።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ላይ ያለው ትውልድ ታሪኩን አውቆ አገሩን እንዲወድ በማድረግ ረገድ የነበሩ ክፍቶች ምን ነበሩ?
አቶ ኢብራሂም፡- ትውልዱ አገሩንና ታሪኩን እንዲያውቅና እንዲወድ ተደርጓል ብዬ አላምንም። ታሪክን ከፖለቲካ ነጥሎ ማውራት ይከብዳል። ታሪካችን በራሱ አያጣላም ብዬ አምናለሁ። ታሪክን አሁን ላለው ሁኔታ እንዲጠቅመን አድርገን ስለማንቀርፀው ነው ችግራችን። ታሪካችንን የሁላችንም አላደረግነውም። ምክንያቱም የእኔ አባት በአፄ ም ኒልክ ተሸነፉ። የአንቺ አባት አሸነፉ። የአንቺአባት ታሪክ ይወራል። የእኔ አባት ታሪክ አይወራም። የእኔ አባት ከሃዲ ተደርጎ የአንቺ አባት አገር ገንቢ ይደረጋል። ይህንን ታሪክ ታዲያ እንዴት እንድወደው ይጠበቃል? ለምሳሌ ግራኝ አህመድ ወራሪ ነው ሲባል ነው የኖረው። እንደሙስሊም እኔ እንዴት እቀበለዋለው? ተመሳሳይ ሥ ራ የሰራው አፄ ገላውዲዎስ አገር ገንቢ ነው ተብለን ነው የተማርነው። አፄ ምኒልክ ተስፋፉ ኢማምአህመድ ግን ወረሩ ነው የሚባለው። እንግዲህ እንዴት አድርጌነው እኩል የሆነ ስሜት ለዚህ ታሪክ የሚኖረኝ? ይህንንም በጉልበት መጫን ይቻል ነበር፤ ችግር አልነበረውም። ግን በ1970ዎቹ ደግሞ የኤርትራ የትግራይ የኦሮሞ ታሪክን ይዘው መጡና ትውልዱ ውስጥ ሌላ ውዥንብር ተፈጠረ። የበፊቱ ታሪክ ችግሩ የአንድን አካባቢ፥ የአንድን ብሔርና የአንድ ሃይማኖት ታሪክ የኢትዮጵያ አድርጎ ማቅረብ ሲሆን የአሁኖቹ ታሪክ ጸሐፊዎች ደግሞ ኢትዮጵያ የምትባለውን አገር ወደጎን ጥሎ የራስን ብቻ ታሪክ ማውጣት ነው። በእነዚህ አስተሳሰቦች መካከል ትክክለኛ የሆነ ክርክርና ውይይት የምናዘጋጅበት ሥርዓት የለንም። ስለዚህ አንቺም ሆነ እኔ ስለራሳችን ነው የምናወራው። ስለእኛ የምናወራበት አጋጣሚ አንፈጥርም። ትውልዱ በተለይ በማህበራዊ ሚዲያ ዘመን የተለያየ መረጃ ትክክለኛው እውቀት እንዲኖረው ከማድረግ ይልቅ እንዲወዛገብ አድርጎታል።
አሁንም አንድ ዓይነት ታሪክ፥ አንድ ዓይነት ብሔርና ቋንቋ ብሎም ሃይማኖት እንዲኖር የሚፈልጉ አካላት አሉ። አገር ወዳድና አገር ወዳድ ያልሆኑ የሚል ስያሜ የተሰጣቸው አካላትም አሉ። በሌላ በኩል ደግሞ አብረን ልክ እንዳልኖርን፤ ኦሮሞና አማራ እንዳልተጋባ አድርገው የሚቆጥሩ ጥቂት አይደሉም። አንድ ወንድ አንዲት ሴትን መንገድ ላይ አይቶ የሚወዳት ዘሯን አይቶ እንደሆነ አድርገው የሚቆጥሩም አሉ። በእነዚህ መካከል ያለውን ችግር እንዴት እንፍታና ትውልዱን ታሪክ አልባ ከመሆን እንዴት እናድነው? እንዴት የጋራ እሴቶቻችን እናውጣ? የሚለው ነገር አሁንም አልተመለሰም። ለምሳሌ አሁን ይህ አገር የአፄ ምኒልክ ሐውልት አዲስ አበባ እንደተገነባ የኢማም አህመድ ሐ ውልት እንዲገነባ ይፈቅዳል? ለዚህስ ዝግጁ ነው? እንደዚህ ዓ ይነት ፈታኝ የሆኑ ነገር ግን አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች አሉ። አሁን ጅማ ላይ ሄደሽ የአፄ ም ኒልክን ሐ ውልት መገንባት የምትችዪበት ሁኔታ አለ? አዲስ አበባ ላይ ወይም ደግሞ የአሚር አብዱላሂን ሐውልት መገንባት ትቺያለሽ? ይህንን ካላደረግንና ይህን ዓይነቱ ድፍረት ከሌለ ይህ የፖለቲካ ድፍረት ከሌለ አሁንም መፍትሄ የለውም ባይ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ያሉት ችግር ታዲያ በምን መልኩ ነው መፈታት የሚችለው?
አቶ ኢብራሂም፡- የፖለቲካችንን ችግር መፍታት የምንችለው በዴሞክራሲ ውይይት እንደመሆኑ የታሪካችን እሰጣ ገባ የሚፈታውም በዚህ መልኩ ነው። እኔ እንዲያውም የተለያዩ ትርክቶች ራሳቸው የታሪክ አንድ አካል ናቸው። የታሪክ ባለሙያ ማለት ዳኛ ማለት ነው። ዳኛ ተከሳሹን ብቻ እንደማይሰማ ሁሉ የታሪክ ባለሙያም የሁሉንም ወገን ሃሳብና እይታ አይቶ ነው መፃፍ ያለበት። መፍትሄው ቀላል ነው ባይ ነኝ። ታሪክን ለታሪክ ባለሙያዎች መተው ይገባናል። ይህንን ለማድረግ ዝግጁ መሆን ይጠበቅብናል። እውነተኛው ታሪክ ለመፃፍ ከትክክለኛው ምንጭ መቅዳት ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- አንዳንድ የታሪክ ምሁራን መንግሥት 70በ30 በሚለው የትምህርት ፖሊሲው እንዳያድግ አንቆ ይዞታል ሲሉ ይተቹታል። ይህ ምንያህል እሙን ነው?
አቶ ኢብራሂም፡- በዚህ ላይ እኔ ብቻ ሳልሆን ሁሉም የታሪክ ባለሙያ የሚስማማ ይመስለኛል። በነገራችን ላይ አንድን ትውልድ ለመግደል ከፈለግሽ ታሪኩን እንዳያውቅ አድርገሽ መቅረፅ ነው የሚጠበቅብሽ። እሱ ብቻ አይደለም፤ ትላልቅ የሚባሉ የታሪክ ቦታዎቻችንን ሆን ብለው እንዲፈርሱ ባለፉት 27 ዓመታት ተደርገዋል ብዬ አምናለሁ። ለምሳሌ እኔ የተማርኩበት ዘርፈሽዋል ትምህርት ቤት(ምሥራቅ በር) አሁን ፈርሶ ክፍለከተማ ተገንብቶበታል። ይህ ለእኔ ታሪክን የማጥፋት አካል አድርጌ ነው የምቆጥረው። እንደዚህ ዓይነት ድርጊቶች ሆን ብሎ ከተሰሩ ሸፍጥ ነው። ግን ሳይታሰብ ከተሰራ መሃይምነት ነው። እንደዚህ ዓይነት አዲስ አበባ ውስጥ ብዙ ገጠመኞች አሉ። ለአብነት እንኳ በሼህኦጀሌ ቤተመንግሥት ላይ የተሰራው ሥራ ግፍ አንቺም የምታውቂው ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ ቱርክ ውስጥ ያስተዋልኩትን ለምሳሌ ልንገርሽ። ቱርክ ኢስታንቡል ከተማ ውስጥ 800 ዓመት ታሪክ ያለው ቤተክርስቲያን አለ፤ ቤተክርስቲያኑ በሚገኝበት አካባቢ ታዲያ አንድም ክርስቲያን የሌለ ቢሆንም ሙስሊሙ
ማህበረሰብ የእኔ ታሪክና ቅርስ ነው በማለት ስለጠበቀው ነው ይህንን ሁሉ ዓ መት መሻገር የቻለው። የአክሱምን ሐውልት ብትመለከቺ ታሪካችንን እንጂ ክርስትና አይደለም የምታዪው። እናም እኔ አንዳንዴ በቅርሶች ላይ የሚደረገው ግፍ ሆን ተብሎም ይመስለኛል። እንደዚህ ዓይነት ግፎች በልማት ሰበብ በበርካታ አካባቢዎች ተሰርተዋል። ይህም እኛ ዝም ብለን የበቀልን፣ ወፍ ዘራሽና ታሪክ አልባ እንደሆንን አድርጎ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ የሚዳዳ ነው። በሌላ በኩልም ፖለቲከኞች የታሪክን ጥቅም ካለማወቅ የሚነጭ ይመስለኛል። የታሪክ ባለሙያዎች በሕንፃ ግንባታና በልማት ሥራዎች ላይ ሚና እንዳይኖራቸው ማድረግ ፖለቲከኞች የፈለጉትና በህልም ያዩትን ሳይቀር ለመተግበር መሞከር ታሪካችንን የሚያጠፉበት አጋጣሚም በርካታ ሆኗል።
አዲስ ዘመን፡- በቱርክ ሚዲያ በሚሰሩበት ጊዜ በተለይ ስለታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ያለውን እውነታ የዓለም አገራት እንዲረዱ ምንያህል ሚናዎትን ተጫውተዋል?
አቶ ኢብራሂም፡- እኔ ምን ያህል ሚናዬን እንደተጫወትኩ አላውቅም። ለምሳሌ ስለኢትዮጵያ 34 ደቂቃ የሚሸፍን የህዳሴን ግድብንም ሆነ ታሪካችንን የሚያካትት ዶክመንተሪ ሰርቻለሁ። ከዚህ ባሻገርም አምስት የአፍሪካ አገሮች ላይ ዶክመንተሪና በርካታ ዜናዎችን ሰርቻለሁ። ዶክተር አብይ እስከሚመጡ ድረስ በኢትዮጵያ ለለውጥ ይደረጉ የነበሩ አመፆችን ጉዳይ በዜና ሰርቻለሁ። በቱርክ የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩትን ኢንተርቪው አድርጊያለሁ። በአፍሪካ ጉዳይ ላይ የሚዲያው አማካሪ ነበርኩ። ቱርኮቹ በኢትዮጵያም ሆነ በህዳሴ ግድብ ላይ መልካም የሆነ አመለካከት ነው ያላቸው። እነሱም በተመሳሳይ ከኢራቅ ጋር ግድብ አትገድቡም ተብለው ውዝግብ የገቡበት አጋጣሚ ነበራቸው። እኔም ቱርክ ውስጥ በተዘጋጁ ሁለት ጉባኤዎች ይህንን መሰረት ያደረገና የሁለቱን አገራት ገጠመኞች በማስተሳሰር ጥናት አቅርቢያለሁ። በዚህም ብዙዎቹ እውነታውን ተረድተውታል ብዬ አምናለሁ።
እኔ የሚያሳስበኝ ሌሎች ያላቸው አመለካከት ሳይሆን የእኛን ሚና በሚገባ ተጫውተናል ወይ? የሚለው ነው። ሌላው ይቅርና በቱርክ ያለውን አቅም አልተጠቀምንበትም ባይ ነኝ። የኢትዮጵያን ገፅታ በሙስሊም ሀገራት ውስጥ መቀየር ያስፈልጋል። ምክንያቱም ለዓመታት ኢትዮጵያ ሙስሊም የማይኖርባት አገር እንደሆነች ተደርጎ የተቀረፀ ታሪክ በመኖሩ ነው። ይህንን መቀየር የሚቻለው እዚህች አገር ውስጥ ስንስማማ ነው። ሙስሊሞች በጎ ሚናቸውን እንዲጫወቱ ማድረግ ያስፈልጋል። በፖለቲካው ዘርፍ ያለው ችግር በሃይማኖት እንዳይደገም መስራት ይገባል። ብበደልም እዚሁ ተከራክሬ ችግሩ እንዲፈታ ማድረግ እንጂ አገር በሚባለው ጥቅም ላይ ልደራደር አይገባም።
ሌላው የቋንቋ ችግር አለብን ብዬ አምናለሁ። ለምሳሌ ብጠቅስልሽ አንድ 20 ዓመት ሳውዲአረቢያ ኖሮ ምንም አረብኛ ሳይችል የተመለሰ ዲፕሎማት መኖሩን አውቃለሁ። የሚገርምሽ ሰውየው እንደኩራት ነው የሚያወራው። ለእኔ ግን ሊያሳፍረን የሚገባን ጉዳይ ነው። በነገራችን ላይ ፖለቲካ ማሳመን የመቻል ብቃትን ይጠይቃል። እኛ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ያለውን እውነታ ለማሳወቅ በምናደርገው እንቅስቃሴ ቋንቋቸውን በሚገባ ማወቅ ይጠበቅብናል።
አዲስ ዘመን፡- እንደታሪክ ባለሙያ አሁን ያለው የፖለቲካ ሁኔታ እንዴት ነው የምታየው?
አቶ ኢብራሂም፡- በመጀመሪያ ደረጃ ኢትዮጵያ ለየት ያለ ታሪክ ውስጥ የገባች አገር ነች። ምን ውስጥ እንዳለን የማናውቅበት ሂደት ውስጥ እንዳንገባ እፈራለሁ። ሊበራላይዜሽኑና ትንሽ ፈታ ማለቱ ያመጣቸው በርካታ ጥሩ ነገሮች ቢኖሩም ያስከተላቸው መጥፎ ነገሮችም አሉ። ድሮ የማናውቃቸው አስተሳሰቦችና ሰዎች ወደ ሚዲያ እየፈሰሱና ወደ ሕ ዝብ እየመጡ መደናገሮች ፈጥረዋል። እነዚህ ነገሮች እንደጥሩ አጋጣሚ ባያቸውም ግን የምንቀበልበትና የምናስተናግድባቸው መንገዶች ያስፈሩኛል። ምክንያቱም የፖለቲካ ባህላችንም አላደገም። እኛ ማሸነፍና መሸነፍን ብቻ ነው የምናውቀው። ፈረጆቹ 50 በ50 የሚሉትን አናውቅም። ሁሉም ማሸነፍ እንደሚችል አናውቅም። እናም አንዱ አሸንፎ ይመጣና እሺ ብለን አንገት ደፍተን መኖር ነው የለመድነው። በዚህች አገር የምንስማማባቸው ነገሮች መኖር አለባቸው። በዋነኝነት የዚህችን አገር መቀጠል ላይ ሁላችንም መስማማት ይጠበቅብናል። ኢትዮጵያ የምትባል አገር ብትቀጥል እኔም አንቺም ተጠቃሚዎች ነን በሚለው ነገር ሁላችንም መስማማት መቻል አለብን። በአገሪቱ መቀጠል ላይ ትንሽም ቢሆን ጥርጣሬ ሊኖረን አይገባም። ይህች አገር ብትጠፋ አንቺ ከእኔ የበለጠ አትጎጂም። ማንም እዚህች አገር ላይ የሚጠቀም የለም። ወይም በተለየ መልኩ የሚጎዳ አካል የለም። ይህንን ማመን አለብን። የምንጠፋ ከሆነ ሁላችንም ነን የምንጠፋው። ስለዚህ እዚህ ላይ መግባባት መቻል አለብን። በተቻለ መጠን ብሔራዊ ጥቅሞቻችንን ማስቀደም አለብን። ሌላው የሌሎችን ስሜት መረዳት መቻል አለብን። ሌላው ተበድያለሁ ሲል አይ አንተ አልተበደልክም የሚል ትክክል ያልሆነ አቀባበል ሊኖረን አይገባም።
አዲስ ዘመን፡- ይህንን ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?
አቶ ኢብራሂም፡- ለምሳሌ አንድ በበፊት ሥርዓቶች ተበድያለሁ የሚል ብሔር ሊኖር ይችላል፤ አሁንም እየተበደልኩ ነው የሚልም ሊኖር ይችላል። አይ አንተ ዝም ብለህ ስትቃዥ ነው ማለት የለብሽም። መስማት አለብሽ። አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ አንዳንድ የፖለቲካ ኃይሎች እነሱ የኢትዮጵያ ጠበቃ፤ ሌላው ግን የኢትዮጵያ ጠላት ፤ የእነሱ የታሪክ አመላከከት ቅዱስ፤ የሌላው ግን እርኩስ አድርገው ነው የሚቆጥሩት። ይህንን ነገር ማቆም አለብን። መሰማማት አለብን። አንዱ የሌላው ቁስል ሊገባው ይገባል። ግልፅ የሆነ የፖለቲካ ውይይት ባህል ማዳበር አለብን። ምንም የሚያስፈራ ነገር የለም።
እንደሙስሊም እኔ እዚህች አገር ውስጥ ሙስሊሞች ተበድለዋል ብል እዚህ አገር ውስጥ ሙስሊሞችን የበደሉት ክርስቲያኖች ናቸው ማለት አይደለም። የፖለቲካና ማህበራዊ ግንኙነት ይለያያል። እዚህ አገር ውስጥ ሙስሊምና ክርስቲያን ተጣልቶ አያውቅም ተዋዶ የሚኖር ሕዝብ ነው። ይህ ማለት ግን ኢትዮጵያ ውስጥ በፖለቲካ ሥ ርዓቱ ሙስሊምና ክርስቲያን እኩል ነበር ማለት ነው? ስለዚህ አንዱ ተበድያለሁ ሲል ሥርዓቱ በደለኝ ነው የሚለው የጎንዮሽ እከሌ በደለኝ አይደለም ማለት ያለበት። ብዙ ጊዜ ሁለቱን ጉዳዮች ስለምናምታታ ክርስቲያኑ ራሱን የኢትዮጵያ ጠበቃ አድርጎ ያቀርባል፤ ሙስሊሙም በተሳሳተ መንገድ ክርስቲያን በደለኝ ሊል ይችላል። ሥርዓቱ ማንም ይበድል ማን አሁን ላይ ግን አስተሳሰባችን መለወጥ መቻል አለበት ባይ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡- ከመስከረም 30 በኋላ የዚህች አገር ዕጣ ፈንታ ምን መሆን አለበት የሚለው ጉዳይ የሰሞኑ የፖለቲከኞች አወዛጋቢ ጉዳይ ሆኗል፤ ይህ ችግር በምን መልኩ ሊፈታ ይገባል ይላሉ?
አቶ ኢብራሂም፡- አንደኛ ፖለቲከኞች ፖለቲከኛ ሲሆኑ ስልጣን መያዝ ብቻ ሳይሆን ኃላፊነትም እንዳለባቸው መገንዘብ አለባቸው። እርግጥ ሁሉም ወደ ፖለቲካ ሲመጣ ስልጣን ለመያዝ ነው፤ ግን የመጨረሻ ግብ አይደለም። ፖለቲከኞች የመጨረሻ ግባቸው ስልጣን መያዝ ሳይሆን የኢትዮጵያን ማስቀጠል ሊሆን ይገባል። መንግሥት ከተቃዋሚዎች ጋር ያለውን ልዩነት የጠላት ሊያደርገው አይገባም። ተቃዋሚዎች ሊሰሙ ይገባል። ምክንያቱም ዴሞክራሲ መገለጫው ይህ በመሆኑ ነው። መንግሥትን የምንከስበትና የምንቆጣጠርበት ዘዴ ሊኖር ይገባል።
ሌላው ተቃዋሚዎች የዚህች አገር ችግር በአንድ ጊዜ የሚፈታ ነው ብለው መጠበቅ የለባቸውም። ይህች አገር በብዙ ትርምስ ውስጥ እያለፈች ያለች አገር ነች። ተቃዋሚዎች ራሳቸው እንኳን አብረው ቁጭ ብለው የማይፈቷቸውና የበለጠ ችግር የሚፈጥሩባቸው ሁኔታዎች አሉ። ከሁሉ በፊት አገርን ማስቀደም ይቀድማል። ይህች አገር ስላለች እኮ ነው እኔና አንቺ ዛሬ ቁጭ ብለን የምናወራው። ስለሆነም ፖለቲከኞቻችን የሚያደርጉት ውዝግብ በቀላሉ የሚፈታ እንኳ ባይሆንም እርስበርስ የሚያደርጉት ትግል ግን በሰለጠነ መንገድ ሊሆን የሚገባው። የሰለጠነ የፖለቲካ አካሄድ ያስፈልገናል። መስዋዕትነትም መክፈል ካለብን በሰላማዊ መንገድ መሆን አለበት። እነ ማህተመ ጋንዲ እኮ ትልቅ ደረጃ የደረሱት በሰላማዊ መንገድና በትዕግስት ነው። ይህ አሁንም፤ ነገም ይቻላል። ይህን ማመን አለብን። ምክንያቱም ሰላም ለሁሉ ነገር ምንጭ ነው።
ደግሞም እኮ መንግሥት ስልጣኑንና ኃ ይሉን ይዞ ዕ ድሜልኩን አይዘልቅም። ዋናው ነገር ይህንን መንግሥት እንጥላለን ብለን የምናደርገውን ሩጫ ሊያመጣ የሚችለውን ቀውስ መገንዝብ ይገባናል። መንግሥት ደግሞ ከሁሉም በላይ ኃላፊነት ሊሰማው ይገባል። ትልቁ የኢትዮጵያ መንግሥታት ችግር ስልጣን የተረጋጋ ሲመስላቸው ሁሉንም ነገር መጫን እንደሚችሉ ማመናቸው ነው። ይህ ስህተት ነው። መንግሥታት ትልቅ ደረጃ የደረሱ ጊዜ ነው የሚወድቁት። በነገራችን ላይ የቀድሞው ኢህአዴግ የወደቀው በ2002ዓ.ም ምርጫ መቶ በመቶ አሸነፍኩ ያለ ጊዜ ነው። ልክ ሁሉም ሰው ኢህአዴግ መሆን የጀመረ ቀን ነው ያከተመለት። ላይኛው ጫፍ የደረሰ ወደታች መዘቅዘቁ አይቀርም። ይህ የፖለቲካ ባህል መቀየር አለበት። መንግሥት በዚህ ጉዳይ ላይ ቁርጠኛ መሆን አለበት።
አዲስ ዘመን፡-ከዚሁ ጋር ተያይዞ በተለይ ህወሓት እየተከተለ ያለው መስመር ትናንት አገሪቱ ወደ ነበረችበት ትርምስ ውስጥ ይከታታል የሚል ስጋት የለዎትም?
አቶ ኢብራሂም፡- ሊመልሰን የሚችልበት አጋጣሚ ይኖራል፤ ግን እኔ ይህንን ያህል አያሰጋኝም። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ትልቅ አገር ነች፤ የምር ትግራይ ከኢትዮጵያ ተገንጥዬ እጠቀማለሁ ማለት የምትችል አይመስለኝም። ግን ደግሞ ትግራይን እንደክልል መቀበል መቻል አለብን። ህወሓት ተሸንፏልና ምን አገባው የሚል አካሄድ ካለ ልክ አይመስለኝም። አሁንም ቢሆን ለድርድርና ለውይይት ልባችንንም ሆነ በራችንን ክፍት ማድረግ ይገባናል። እነዚህ ሰዎች ስልጣን ላይ የነበሩ ሰዎች እንደመሆናቸው ህሊናቸው ሽንፈትን ቶሎ ለመቀበል እንደሚቸገር ማመን ይገባናል። ደግሞም ማንኛውም አካል እየወደቀ ሲመጣ የሚፈራቸው ስጋቶች አሉ። እነሱን ተረድተናቸዋል የሚል እምነት የለኝም። ለምሳሌ «በሰራነው ነገር እንጠየቃለን» የሚልም ስጋት ሊኖራቸው ይችላል። የእውነትም ደግሞ የፌዴራል ሥርዓቱ ሊፈርስ ነው ብለው ሊፈሩ ይችላሉ። እነዚህ ላይ ግልፅ ውይይት አድርገናል ወይ? የሚለው ጉዳይም አሁንም ጥያቄ ነው።
በሌላ በኩል ብልፅግና ከተለያዩ ኃይሎች ጋር እያደረገ ያለው ውይይት በግልፅ ተረድተነዋል ወይ? የሚለው ነገር በደንብ መገምገም አለብን። እኔ አሁንም ቢሆን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ተጽእኖ ያለው አይደለም ህወሓት ማንኛውም ጥያቄ ያለው አካል መግፋት ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። አገር ላይ ጉዳት የሚያስከትል ነገር እንዳይኖር አንዱ የአንዱን መኖር ተቀብሎ አንዱ ከአንዱ ጋር ለመደራደር ዝግጁ መሆን አለበት። በተጨማሪም አሁን ከዚህ ቀደም ከግምት ውስጥ ያላስገባነው ኮሮና የሚባል ነገር መጣብን። ይህንን አዲስ ክስተት ብልሃት በተሞላበት መንገድ በታማኝነት ተጋፍጠን የሚመጣውን መፍትሄ ለመቀበል ዝግጁ ነን ወይስ አይደለንም? እሱ ነው መገምገም ያለበት። በእርግጥ የማንም ጥፋት ላይሆንም ይችላል። ግን ደግሞ ፖለቲካ ድርጅቶች ባገኙት አጋጣሚ የራሳቸውን ጥቅም ለማስከበር ጥረት ከማድረግ ይልቅ ሁሉም ወደ ውይይት ለመምጣት ፈቃደኛ ሊሆኑ ይገባል ባይ ነኝ። ይህንን ማድረግ ከቻሉ የማይፈታ ችግር ይኖራል ብዬ አላስብም። መጨረሻ ላይ ሁሉም ወደ አዕምሯቸው ይመለሳሉ ብዬም አምናለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
አቶ ኢብራሂም፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ግንቦት 8/2012
ማህሌት አብዱል