የወቅቱ የዓለማችን ቁጥር አንድ ሥጋት የሆነው ኮሮና በአገራችን መከሰቱ ከተረጋገጠ ሁለት ወራት አልፈዋል። በከፍተኛ ፍጥነትና ተለዋዋጭ ባህሪ እየተዛመተ ያለው ይህ ወረርሽኝ ዓለምን ለከፍተኛ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ዳርጓታል። ይህንን እውነታ በመረዳትም የዓለም ጤና ድርጅት ወረርሽኙን ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ (Pan¬demic Disease) ብሎ ካወጀ ወራት አልፈዋል። ከቫይረሱ የመተላለፊያ ባህሪይ የተነሳ የሰዎች ማኅበራዊ ግንኙነት ባልተለመደ መልኩ እንዲላላና አብዛኛዎቹም በቤታቸው እንዲውሉ አስገድዷል። ከዚህም በላቀ በርካቶችን ለከፍተኛ ማኅበራዊና ሥነ ልቦና ቀውስ ዳርጓቸዋል። ቫይረሱ በዚህ ሳያበቃ በየደቂቃ ልዩነት ፆታ፣ ዕድሜ፣ ብሔር፣ ሃይማኖት፣ አገር ሳይለይ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር የሰው ሕይወት ቀጥፏል፤ አሁንም እየቀጠፈ ይገኛል።
ወረርሽኙ ካስከተለው የጤና ጉዳት ውጭ ኢኮኖሚው ላይ እያሳደረ ያለው ጫና እጅጉን የበረታ ሆኗል። የሥራ አጥነት ቁጥር እንዲጨምር ማድረጉ፣ አምራች ኃይሉ በወረርሽኙ ሥጋት ከምርት መታቀቡ፣ የወጪና ገቢ ንግድ እጅጉን መውረዱና ቱሪዝምና ሆቴሎችን የመሳሰሉ ዘርፎች መቀዛቀዛቸው ወዘተ ወረርሽኙ በኢኮኖሚው ላይ ካሳደራቸው ቀውሶች ዋነኞቹ ናቸው። ስለሆነም ይህንን ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ለመቀነስና የዜጎች የመኖር ዋስትናን ለማስቀጠል አገራት እንደየአቅማቸው የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰዱ ይገኛሉ። በአገራችንም መንግሥት በሽታውን ለመከላከል ከወሰዳቸው እርምጃዎች ጎን ለጎን ለኢኮኖሚው ደህነንት ሲባል ተጨባጭ እርምጃዎችን መውሰዱንና ወደፊትም ይህንኑ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አሳውቋል።
የዜጎች የመኖር ህልውና አደጋ ላይ እንዳይወድቅና ልማት እንዳይስተጓጎል ታሳቢ በማድረግ መንግሥት ኢኮኖሚያዊ ድጋፍ ለማድረግ የወሰነባቸው ዋነኛ ምክንያቶች የሕዝቡን ጤና ለማስጠበቅ መንግሥት የሚያደርገውን ጥረት ማጠናከር፣ የገቢ ምንጮችን ማስቀጠል እና የሠራተኞች ቅነሳን ማስቀረት፣ በኮቪድ 19 የተነሳ በተከሰተው የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ምክንያት አነስተኛ ገቢ ያላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ተጨማሪ ቀውስ እንዳያገኛቸው የመኖሪያ ሁኔታን ማመቻቸት እና የቤት ኪራይን ጨምሮ ልዩ ልዩ ድጋፍ ማድረግ፣ ኮቪድ 19ኝ ለመከላከል የሚደረጉ ልገሳዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ማበረታታት፣ የኢኮኖሚ መረጋጋት እና ከቀውስ ፈጥኖ ማገገምን ማረጋገጥ፣ በወረርሽኙ ክፉኛ ለተጎዱ የንግድ ተቋማት ድጋፍ ማድረግና አገልግሎት ሰጪዎች እና አምራቾች ሥራቸውን እንዲቀጥሉ ማበረታታት የሚሉ ና ቸው።
እነዚህን ታሳቢ በማድረግም የሚከተሉትን ወሳኝ እርምጃዎች እንደወሰደም አስታውቋል። ከ3099 ለሚበልጡ ግብር ከፋዮች እስከ 2015 የግብር ዓመት ማብቂያ ድረስ የሚቆይ ውዝፍ የግብር ክፍያ (ዋናውን ግብር፣ ወለዱን እና ተያያዥ ቅጣቶችን ጨምሮ) ማስቀረት፣ ከ2008 እስከ 2011 ዓ.ም ያለው ጊዜ የግብር መጠን ትንተና የደረሳቸው ግብር ከፋዮችን ወለድ እና ቅጣት መሰረዝ፡ የክልል መንግሥታት እና በከተማ አስተዳደሮች የትምህርት ተቋማት እና የጥቃቅን እና አነስተኛ ተቋማት ከሚከፍሉት 30 በመቶ የኪራይ ግብር ቅነሳ ማድረግ። ይህ የኪራይ ገቢ ግብር ቅነሳ መኖሪያዎችን የሚያከራዩ እና ለተከራዮቻቸው የኪራይ ክፍያን ያስቀሩ፣ የሚያገኙት ወርሐዊ የኪራይ ገቢ መጠን ከ10‚000 ብር የማይበልጥ ባለንብረቶችንም ይጨምራል። ደሞዝ እየተከፈላቸው በቤታቸው የሚቆዩ ሠራተኞች የሚከፍሉትን የአራት ወራት ከመቀጠር የሚገኝ ግብር ማስቀረት፡ ይህም መሥሪያ ቤቶች ለሁለት ወራት ቤት የሚቆዩ ሠራተኞችን ደሞዝ ሲከፍሉ፣ 50 በመቶው በመንግሥት አስተዋጽኦ እንዲሸፈን ያስችላል። የተጨማሪ እሴት ግብር (ቫት) እና የተዘዋዋሪ ግብር የሚከፈሉበትን ቀነ ገደብ ማራዘም። የመጋቢት፣ ሚያዝያ እና ግንቦት ወራት ተቀናሽ የሚደረጉ ወጪዎች እና የተጨማሪ እሴት ግብር እንዲሁም የተዘዋዋሪ ግብር ክፍያዎች የማቅረቢያ ጊዜ እስከ ሰኔ 2012 ዓ.ም. ማራዘም ሲሆን፣ ይህም ያለ ቅጣት እና ወለድ ተግባራዊ የሚደረግ ነው።
በታዳጊ አገር ኢኮኖሚ ይህንን ያህል ከፍተኛ ገቢ የሚያሳጣ እርምጃ መውሰድ ቢከብድም መንግሥት ለዜጎች ህይወትና ለቀጣይ ኢኮኖሚያዊ ደህንነት ሲባል የወሰደው ይህ እርምጃ እጅጉን የሚመሰገን ነው። ከዚህም ባሻገር ቀጣይ ሁኔታዎችን እየተመለከተም ሌሎች እርምጃዎችን እንደሚወስድ ማሳወቁም ለዜጎች ክብርና ህልውና ያለውን ቁርጠኛ አቋም ያሳያል። ስለሆነም በኢኮኖሚው ውስጥ ያሉ ባለድርሻዎች ሁሉ ይህንን የመንግሥት ድጋፍ በምቹ ሁኔታነት በመጠቀም ለኢኮኖሚው ዕድገት የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል!
አዲስ ዘመን ግንቦት 8/2012