እንደምን ከረማችሁ የአዲስ ዘመን ማዕድ ተጋሪዎቼ!
ዋቃ ገለታ ይድረሰው እኔ በጣሙን ደህና ነኝ። ደህና ነኝ እላለሁ እንግዴህ ድፍን ዓለም በጠና ታሞ። ደህና ነኝ ልበል እንጂ ምኑን ደህና ሆንኩት። አምላክ ዓይን የሌለው፣ የማይናገር፣ የማይጋገር፣ ምንም ነገር የማይሰማ፣ ምኑን ዱብዳ እንዳመጣብን እርሱ ብቻ ይወቀው። መቼም ስለምኑ ነው የምታወራው አትሉኝም። አያ ኮሮና ነዋ! የሰው ዘር የተባለን ልቦና በሞላ ያስሸፈተ የወረርሽኞች ሁሉ የጎበዝ አለቃ። የዛሬው ግብዣዬ የትዝብት ማዕድ ነው። ኮሮናንም እንታዘባለን። ይበልጥ ደግሞ እርስበርሳችን እንተዛዘባለን። ምክንያቱም ከትዝብት ብዙ የምንማረው እና ተምረንም የምናርመው አለ ብዬ ስለማስብ። ጎበዝ ስንጀምር አካባቢ ጥሩ ይዘን ውለን ባደርን ቁጥር እየተላመድነው መጣን መሰለኝ ጭራሽ “ኖር” ብለን ቤተኛ እያደረግነውን እንዳለ ነው የሚሰማኝ። አሁን ላለንበት አጣብቂኝ በደካማ ጎኑ ላይ እናትኩር ብለን እንጂ በርካታ ትሩፋቶችንም ይዞልን እንደመጣ መካድ አይቻልም። እንዲያውም ኮሮና በዚህ ረገድ ሊመሰገን ይገባዋል። እግረመንገዳችንን ከነዚህ መካከል ጥቂቶቹን እንኳ እንመልከት።
ኮሮናና ጥቅሞቹ
በዘመነ ኮሮና ሰው ባላወቀ አምላክ ባወቀ ለጊዜውም ቢሆን ዝሙት ተከለከለ፤ መላፋት መዳራት፣ መላከፍ፣ መለካከፍም ቀረ፤ እነ ሁሉ አማረሽም፤ እነ ያዩት አትለፈኝም፤ እነ ሁሉን ቀምሼ ልሙትም አደብ ገዙ። የዝሙት መንፈስ አጋንንቱ ተመታ፣ ኤችአይቪ ኤድስም የሚመሰገንበት ዘመን መጣ፤ በዘመነ ኮሮና ኮንዶምም አያድንህም ተባለ፤ በዘመነ ኮሮና ማንንም አትጠጋም፤ አትጨብጥም፣ አትጎነታትልም፣ አትስምም፤ አትዳብስም። ማሳጅ ቤት ድሪያ፤ ቡና ቤት የዝሙት ድሪያ ቆመ፤ አትንካኝ፣ አትቅረበኝ፤ ወዳልኝ ባዩም በዛ። እናም ይህን ስታይ ኮሮና ቫይረስ ብቻ ሳይሆን አምላክ ለዚች ሰዶማዊት ምድራችን አደብ ማስገዣነት የላከው አርጩሜው ነው ብለህ ለማመን ትገደዳለህ።
ኮሮና ስንቱን አነጸ፣ ስንቱን ልብ እንዲገዛ
አስተማረ መሰላችሁ!
ድንበር ዘግቶ፣ ሱቅ፣ ሱፐርማርኬት፣ ትምህርት፣ ንግድ አዘግቶ ቤቱን በላዩ ላይ በገዛ እጁ እንዲጠረቅም አስደርጎ ስንቱን መከረ ዘከረ መሰላችሁ። ኮሮና የስንቱን የተደበቀ ገመና ገላልጦ አደባባይ ላይ አወጣ። «ጀግና ነኝ፣ ያለእኔ ወንድ የለም አልፈራም» ባዩን አፈጀግና ሁላ በየጎሬው ከተተው። ከያለበት በፍርሃት ገመድ ተሸብቦ ለአፍታም ቢሆን ወደ ልቡናው እንዲመለስ አስገድዷል።
አጅሬ ኮሮና የተከሰተው በዘመነ ሁዳዴ፣ በአብይ ጾም ወቅት ወዲህ ደግሞ በረመዳን ዋዜማ መሆኑን ስታይ ደግሞ የበለጠ ትገረማለህ። ሳትወድ በግድህ 14 ቀን ሁለት ሰባት ዝግ ሱባኤ ትገባለህ። ለይል ቆመህ ሰግደህ ቶውባ ታበዛለህ። ስጋ ቤት የለም፣ ካቲካላ ቤት የለም፣ ሆቴል፣ ሬስቶራንት ጭፈራ ቤት ዝግ ነው፣ ሽሻ ቤት ጫት ቤትም የለም፣ ሴተኛ አዳሪ መሸመትም የለም። ባለጌ ወንበር ላይ ተቀምጦ የወይዛዝርቱን ዳሌ ቸብ ቸብ ማድረግ ሲያምርህ ቀረ፣ ሴተኛ አዳሪነትም ረከሰ፣ ሁሉም አደብ ገዛ – ጭምትም ሆነ ።
ኮሮና ኃያሉን ሀገር ሁላ አስተንፍሶ ገመናቸውንም አደባባይ አወጣ። ጨረቃ ላይ ወጣን አውቶሚክ ቦንብ ሰራን፣ በሕክምናና በሳይንስ ተራቀቅን፣ የጦር ኃይላችን አንደኛ ነው፣ የእድገት ደረጃችን የመጠቀ ነው ወዘተ ባዩን ከመለኮታዊው ዙፋን ስር መሆኑን አሳየው። እናም እኔው ደሃው ኢትዮጵያዊውም ከናጠጠው አውሮጳዊው ወይም አሜሪካዊው እኩል ወደ ፈጣሪ እንድናንጋጥጥ ነው ያደረገን አያ ኮሮና። አሜሪካም ለማኝ ሆነች ከደቡብ ኮሪያም የሕክምና መሣሪያም ለመነች፣ የቻይና እግር ስር ተደፋች።
ኮሮናና የቤተሰብ ፍቅር
በዘመነ ኮሮና አባት ከልጆቹ ጋር የመዋያ ጊዜ አገኘ፤ ሚስት የባሏን የባልነት ጣዕም አጣጣመች፤ አባወራም አደብ ገዛ፤ ቤተሰብ አስርቦ ገንዘብ በየመሸታ ቤቱ ለመጠጥ መበተኑ ቀረ። ካለ ሆቴል ምግብ አልቀምስም ባዩ ቀብራራው ሁላ ነጭ ሽሮ ያለ ዘይት ይጠርገው ጀመር። ትዕቢት ተነፈሰች፣ ያበጠው ጉራ ሰከነ። አጅሬ ባል የሚስቱን ስቃይ እያየ አብሮ ተካፈለ።
አባት ቤቱን ያድርበታል እንጂ ውሎበት አያውቅም። ለልጆቹም ፍቅር ሰጥቶ አያውቅም።እንዲያውም አንዲት ልጅ ከአባቷ ጋር እራት በልታ አታውቅም።የሚሰጣትን ሳንቲም አጠራቅማ አባቷን እራት ልትጋብዘው ስትጠይቀው አባት እስካሁን ያደረገው ስህተት እንደነበር የሚያሳይ አንድ አጭር ፊልም ያየሁ ይመስለኛል።አሁን ግን ቤቱና ቤተሰቡ ምን እንደሚመስል ግቢው ውስጥ ምን ምን አትክልት እንዳለ እያስተዋለ ነው።የቤት ሙያም እየተማረ ነው።ልጆቹን ለማስጠናት እየሞከረ ነው።ደደብ አስተማሪ ሲል የነበረውም፣ ማስተማር ምን ያክል ፈተና እንደሆነ ትንሿ ልጁን ሲያስጠና መምህራን ስንቱን ችለው እንደሚያስተምሩ የተገነዘበ ይመስላል።የሚገርመው ደግሞ ሕፃናት ወላጆቻቸው ወይም እህት ወንድ ሞቻቸው ሲያስጠኗቸው አይቀ በሉም። እውቀት ያላቸውም አይመ ስሏቸው። መምህሮቻቸውን ነው የሚያምኑት። ውዝግቡ በየቤቱ ስላለ ለአንባቢ ልተወው።እናም ኮሮና ለሚስቱም ለልጆቹም ፍቅር እንዲሰጥ ግድ ብሎታል፡፡
ታዲያ ይህን ስታይ አንድዬ ለሶዶማዊት ምድራችን አደብ ማስገዣነት የላከው አርጩሜው ነው ብለህ ለማመን ትገደዳለህ። ኧረ እንዲያውም ኮሮና ከሰባኪ በላይ ተደማጭ፣ ከካህን የበለጠ ተከባሪ ሆኗል። ብዙውን ሰው በግደታ ማጾም ጀምሯል፣ ንስሐ እያስገባም ነው፣ ለስጋ ወ ደሙ እያበቃም ነው። ኮሮና ብዙውን ሰው እየዠለጠ ወደ ቤተመቅደስ እየነዳ ነው። ይህን ስትመለከት አልሃምዱሊላህ እንኳን መጣህ ልትለው ሁላ ይዳዳሃል።
ይኸ ብቻ አይደለም። ኮሮና ጀግና ነው። የተማረም የተመራመረም አያሸንፈውም፣ ኃያላን መንግሥታትንም አፋቸውን አዘግቷል፣ ሀብታምንና ደሃውንም ሳይለይ ሁሉንም እየመከረ እያነጸ ነው።
ኮሮናና አክቲቪስቶቻችን
በአሁኑ ሰዓት ድምጻቸው የጠፋ አፈላልጉኝ ላይ ያለን ብዙ ሰዎች አሉን። ለመታየት ሲባል ብዙ ሲሯሯጡ የከረሙ አንዳንድ ሰዎች ዛሬ ላይ ሆነን ስናያቸው ለካ ለሕዝብ ጥቅም አልነበረም ጩኸታቸው ያስብላል። በዚህ ወቅት ድምጻቸው የጠፋ ፖለቲከኞችም ሆነ አክቲቪስቶች ጉራቸው ለፖለቲካ ትርፍ ነበረ ለማለት የሚያስችል አዝማሚያ ላይ ነን። ለሕዝብ ጥቅም ቢሆንማ ዛሬም ከሕዝባቸው ጎን ቢቆሙ ባልከፋ ነበር።
ይሄ አጋጣሚ ብዙ ነገሮችን እያሳየን ነው። የአክቲቪስቶች ፍላጎት ለሕዝብ ሳይሆን ለግል ጥቅማቸው እንደሆነ አሁን ሁሉም የተረዳ ይመስላል። በዚህ አጋጣሚ ሊመሰገኑ የሚገቡ የሕዝብ ልጆችም እንዳሉ መረዳት ያሻል። ብቻ ኮሮና አምላካዊ ወንፊታችን ሆኖ ጠላትና ዘመድን፣ ወገንና ባዳን እንድንለይ አስችሎናል። እናም ሊመሰገን ይገባል።
ኮሮናና ገበያ
ሌላው የትዝብት መነፅሬ ያረፈበት ደግሞ ሰሞነኛው የማስክና የሳኒታይዘር ገበያ ነው። ሕዝብ ግራ በመጋባትና መፍትሔ የሚለውን ነገር በማፈላለግ ላይ ተጠምዷል። በአዲስ አበባ ትንሽም ብትሆን ገንዘብ አለኝ የሚለው ሕዝብ ተስፋ ባለመቁረጥ አልኮል፣ ሳኒታይዘር፣ ጓንት፣ ማስክ ወዘተ… ፍለጋ ሲባዝን ይስተዋላል። የማስኩን ነገር እናቆየውና፣ በአሁኑ ሰዓት ጓንት በየትኛውም የከነማ ፋርማሲ የሚገኝ ሲሆን አልኮልና ሳኒታይዘር ግን እንደ ዕድል የሚገኙ እየሆኑ ነው። የቫይረሱን በኢትዮጵያ መገኘት እንደተሰማ የእጅ ጓንት የተባለው ነገር ወደ ገበያ እየወጣ ሲሆን የማስኩ ገበያ ደግሞ አጠያያቂም አስጊም ሆኗል።
በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ኮቪድ-19ኝን ለመከላከል ይረዳሉ የተባሉ የተለያዩ ነገሮች በስመ-ማስክ ይቸበቸባሉ። 10 ብር፣ 30 ብር፣ 50 ብር ድረስ ዋጋ ይጠራላቸዋል። ተገቢነታቸውና በሽታ አምጭ ተሕዋሶችን መከላከሉ ላይ ያላቸው ውጤታማነት ያልተረጋገጠላቸው ማስኮችን ጨምሮ፣ ሰዎች ማስክ ተብሎ ገበያ የቀረቡ ነገሮችን ሁሉ ለራሳቸውና ለቤተሰባቸው ገዝተው ሲሄዱ ይታያሉ።
ይህ ግብይት የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤትና ምኒልክ አደባባይ ዙሪያን ጨምሮ ብዙ ሕዝብ በሚርመሰ መስባቸው አደባባዮችና ጎዳናዎች ዳር በጠራራ ፀሐይ የሚካሄድ ነው። ቢሆንም እነዚህ ማስክ የተባሉትን ቁሶች እያመረቱና እያስመረቱ የሚጠቀሙ ወይም ለደንበኞቻቸው የሚያቀርቡ ድርጅቶች የጋዜጠኞችና የሐኪሞች ትኩረት አግኝተው አያውቁም። ሕዝብን የሚያዘናጋና ለአደጋ የሚያጋልጥ ሊሆን ስለሚችል ጉዳዩ የሚመለከታቸው ወገኖች ቁጥጥር ማድረጉን ችላ ባይሉት ጥሩ ነው።
ዱሮ ዱሮ በከተማና በገጠር ጉልትም ሆነ መደበኛ ገበያ በጠባብ ስፍራ ሰዎች በርከት ብለው ይገበያያሉ። ከሁለት በላይ ቁጭ ብለው ይሻሻጣሉ፤ ይሸምታሉ፣ ይጠጣሉ፤ ይበላሉ። በተለይ በአንዳንድ የሀገራችን ባህሎች መሠረት በአንድ መጠጫ ወንዶችና ሴቶች አፍ ለአፍ ገጥመው ቦርዴ/ሻሜታ ይጠጣሉ። በአንድ ዕቃም ይመገባሉ። ይህም ማህበራዊነትን የሚያጠናክር፤ መተሳሰብና ፍቅርን የሚገልጽ ባህል ነበር። ከመራራቅም ይልቅ ተቀራርቦ መብላት፣ መጠጣትና መጫወት ይበረታታ ነበር። አሁን አሁን ግን ዕድሜ ለኮሮና አካላዊ መራራቅ ያንን እሴት ጎጂ ባህል አድርጎታል። ይሁን እንጂ የበሽታው መተላለፊያ እጅግ ውስብስብ መሆኑ የተለመደውን ማህበራዊ መቀራረብ ከልክሏል። በተለይ በገበያ ስፍራ አንዳንዱ በዘልማድ፤ አንዳንዱ ከበሽታው ሽሽት፤ አብዛኛው ደግሞ የወረርሽኙ ጉዳይ ግድ የሌላቸውን ሰዎች ማየት የበሽታው አስከፊነት እንዳልገባቸው የሚያስረዳበት ሁኔታ ይስተዋላል። እንግዲህ አይበለው እንጂ ቫይረሱ እንደሌሎች ዓለም አገራት እየተባባሰ ከመጣ የመትረፉ ሁኔታን አሳሳቢ ያደርገዋል።
ታዲያ መዘናጋትን ምን አመጣው?
ምን ተይዞ ጉዞ?
ኃያላን የሚባሉ ሀገሮች ሳይቀሩ በዓለም ላይ ሕዝብ በኮሮና ቫይረስ እንደ ቅጠል እየረገፈ መሆኑን እናያለን እንሰማለን። ሰው ቤት ከትሞ እንቅስቃሴ ሁሉ ቆሞ ከተሞች ባዶ ሆነው መታየት ከጀመሩ ውሎ አድሯል። ዛሬ ሁኔታው ከፍቶ በብዙ ሀገራት ስጋቱ እንዳየለ ነው።
የዓለም አንዱ ክፍል ነንና ከስጋቱ አንፃር ወደ እኛ ሀገር ስንመለከት ግን እልህ በሚመስል ሁኔታ ቀደም ብለው በመልካሙ ጊዜ የነበሩ ነገሮች ሁሉ ከሞላ ጎደል በብዙዎች ቀጥለዋል። የሚባለውን ምክር የሚሰሙ እና የሚተገብሩ ቢኖሩም።
ምንም እንኳን ሞልቶልን ቤት መቆየት ቢከብድም ቢያንስ ቢያንስ መራራቅ፣ በምናዘው እጃችን አለመ ጨባበጥ፣ በየጊዜው በሳሙና በሚገባ መታጠብ፣ ሕዝብ ወደሚበዛበት ቦታ በተቻለን አቅም አለ መሄድ፣ በየቦታው ቁጭ ብለን ተቃቅፈን ቡና መደጋገም መተውን፣ ስናስልና ስናስነጥስ አፍና አፍንጫችንን መሸፈን ቫይረሱ ነገ ከሚያደርሰው ጉዳት በላይ ከባድ ነው ብዬ አላስብም።
ሁሉ ነገር በርትቶ በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሳለ ሁነቱን ስንገልፅ «መዘናጋት አለ» ብሎ ቀለል አድርጎ ቃሉን ማሳመር ግን ለኔ አልተስማማኝም::
እውነታው እሱ አይደለም። መዘናጋት ሳይሆን ኃላፊነት አለመወጣት፤ ድል የማይገኝበት ይልቁንም ዋጋ ሊያስከፍል የሚችል አጉል ጀግንነት እና አርበኝነት የሚዳዳን መሆናችን ነው::
መዘናጋት የሚመጣው አሻሚ ወይም አማራጭ ያለው ነገር ሲኖርና ማመንታት ሲከተል ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ ምንድነው የሚያዘናጋው? አንድና አንድ ውሳኔ ብቻ ነው መወሰድ ያለበት። በሽታው መድኃኒት የለውም፤ ከሰው ወደ ሰው ይተላለፋል። በቀናት ልዩነት በፍጥነት ዓለምን እያዳረሰ ነው። ገዳይ ነው። ነብስ ይነጥቃል። ለከፋ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ኪሳራ ይዳርጋል።
ከዚህ በላይ ነቅቶና ፈጥኖ ምክር ሰምቶ የዓለም ሕዝብ እየተገበረው ያለውን ተግባር ለመፈፀም ሌላ መተማመኛ የሚፈልግ አይመስለኝም። በሩ ተንኳኩቷል፤ መጥቻለሁ ብሏል ቫይረሱ፤ በተጨባጭ የኛው ወገኖች ተጠቅተው ዛሬ አልጋ ላይ ናቸው። በሕይወት ያጣናቸውም አሉ። ታዲያ ይሄ ሁሉ እያለ የምን መዘናጋት ነው?
ወገኖች ለራሳችን ስንል ኃላፊነታችንን እንወጣ!
አዲስ ዘመን ግንቦት 7/2012
በሐሚልተን አብዱልአዚዝ
አሻም ወዳጆቼ