ከዚህ ቀደም በሳይንስ እንደማይታወቅ የተነገረለት የኮሮና ቫይረስ ቻይና ውስጥ አደገኛ የሳምባ በሽታን ቀስቅሶ ወደ ሌሎች አገራትም በፍጥነት እየተዛመተ ይገኛል። የተለያዩ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ወረርሽኙ ከቀን ወደ ቀን በሚያስደነግጥ ፍጥነት የሰዎችን ሕይወት እየቀጠፈና እየተዛመተ በመምጣት፣ የሰው ልጆች ትልቅ ስጋት ከሆነ ውሎ አድሯል።በሁሉም የዓለም አገራት የተንሰራፋው በሽታው የሰው ሁሉ ጠላት በመሆን ያለ ርህራሄ ነፍስ እየነጠቀ ነው፡፡
በመጀመሪያ ላይ በቻይናዋ የዉሃን ከተማ መገኘቱ የተዘገበው ቫይረስ እስካሁንም ከሦስት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን በላይ ሰዎችን አጥቅቷል።ባለሙያዎች ይህ ቁጥር እየጨመረ እንደሚሄድም ይገምታሉ።
በዓለም ላይ የወረርሽኙ ተጠቂዎች ቁጥር ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ከ298ሺ በላይ ሰዎች ላይመለሱ ትንፋሻቸውን አጥተዋል። አሜሪካ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ዜጎቿ የተጠቁባት ቀዳሚ አገር ሆናለች።አሳዛኙን ቀን እያሳለፈች የምትገኘው አሜሪካ በሞትም በወረርሽኙ ምክንያት ከዓለም ቀዳሚውን ሥፍራም ይዛለች፡፡
ስፔን ከ272 ሺ በላይ፣ ሩሲያ ከ252ሺ በላይ፣ እንግሊዝ 229 ሺ ጣሊያን ከ222ሺ በላይ፣ ብራዚል ከ190ሺ በላይ፣ ፈረንሳይ ከ178ሺ በላይ፣ ዜጎቻቸውን ወረርሽኙ ያጠቃባቸው ሲሆን፤ እንደአቀማመጣቸውም ይመራሉ።ቫይረሱ የጀመረባት ቻይና ደግሞ ከ82 ሺ በላይ ታማሚዎች ያሉባት አገር ነች፡፡
በዓለም ላይ ከ298 ሺ በላይ ዜጎች በቫይረሱ ሕይወታቸውን የተነጠቁ ሲሆን፤ አሜሪካ ከ85 ሺ 197 በላይ ዜጎቿን በወረርሽኙ ያጣች ቀዳሚ አገር ናት።በዩናይትድ ኪንግደም በ24 ሰዓት ውስጥ 494 ሰዎች ሞተዋል፤ አጠቃላይ የሟቾች ቁጥር ከ33ሺ በልጧል። ስፔን ከ27 ሺ 321 በላይ ዜጎቿ ለሕልፈት የተዳረጉ ሲሆን 186ሺ ያህሉ ደግሞ አገግመዋል።በቻይና ባለፉት 24 ሰዓት 7 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል።
በዓለም ላይ በወረርሽኙ ከተያዙት መካከልም ከአንድ ሚሊዮን 675ሺ 935 በላይ ሰዎች ማገገም ችለዋል።አሁን በሕመም ላይ ከሚገኙት ሁለት ሚሊዮን 478ሺ ሺህ ሰዎች ውስጥ ሁለት ሚሊዮን 432ሺ ሰዎች (98 በመቶ) ሕመማቸው መጠነኛ ነው። 47 ሺ 778 (2በመቶ) በላይ ሰዎች ደግሞ ጽኑ ሕመም ላይ መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።በዓለም ላይ የማገገም ንጽጽሩ 85 በመቶ ሲሆን 15 በመቶ ሞት ተመዝግቧል።
በአፍሪካ በወረርሽኙ የታመሙት ዜጎች ከ74 ሺ በላይ የደረሰ ሲሆን፤ 2ሺ 508 ሰዎች ሞተዋል።ከ26ሺ 342 በላይ ዜጎች ማገገም ችለዋል። ደቡብ አፍሪካ 12ሺ 74 ሰዎች የታመሙባት ቀዳሚ የአፍሪካ አገር ናት።
10ሺ 431 ሰዎች በቫይረሱ የተጠቁባት ሁለተኛዋ የአፍሪካ አገር ደግሞ ግብጽ ናት።ሞሮኮ 6ሺ 593 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘውባት ከአፍሪካ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።አልጀሪያ ከ6ሺ 253 በላይ ዜጎች በወረርሽኙ የተያዙባት በአፍሪካ አራተኛዋ አገር ስትሆን ጋና 5ሺ 408 ዜጎቿም በወረርሽኙ ተጠቅተውባታል።
በኢትዮጵያም ወረርሽኙ ከገባ ጀምሮ 45 ሺ 278 ሰዎች ምርመራ የተከናወነ ሲሆን፤ በወረርሽኙ የተያዙ ሰዎች 272 ደርሰዋል።የአምስት ሰዎች ሕይወት አል ፏል። 108 ሰዎችም ማገገም ችለዋል፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 7/2012