በ7 አህጉራት እና ከ212 በላይ ሀገራት የተዋቀረችን ዓለማችን ከ7.8 ቢሊዮን በላይ ህዝብ አላት።እ.አ.አ በ1804 ከክርስቶስ ውልደት በኋላ አንድ ቢሊዮን የደረሰው የዓለም ህዝብ ፈጣንና ወጥነት የሌለው ዕድገት አሳይቷል።በህዝብ ብዛት ኢሲያ ከ60 ፐርሰንት በላይ በመያዝ እንደ አህጉር አንደኛ ስትሆን አፍሪካ ደግሞ ከ16 ፐርሰንት በላይ በመያዝ ሁለተኛ ናት።የህዝብ ዕድገት ከፍተኛውን ድርሻም እነዚህ ሁለቱ አህጉራት ይወስዳሉ።
በዓለም ላይ የውልደት ምጣኔ መቀነስ ሲያሳይ በአፍሪካ ግን አሁን ከፍተኛ ደረጃ ላይ ነው።እንደ ተ.መ.ድ 2017 እ.አ.አ ትንበያ በ2050 የዓለም ህዝብ 9.8 ቢሊዮን ይደርሳል ተብሎ ይገመታል።በሪፖርቱ መላምት በሚቀጥሉት 30 ዓመታት የዓለም የህዝብ ቁጥር ዕድገት ከፍተኛውንና ከ50% በላይ ድርሻ ከሚይዙ 9 ሀገራት አምስቱ አፍሪካ ውስጥ ይሆናሉ ተብሎ ይገመታል።እነዚህም ሀገራት፦ ናይጄሪያ፣ ኮንጎ፣ ኢትዮጵያ፣ ታንዛኒያ እና ዩጋንዳ ናቸው፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ ከ110 ሚሊዮን በላይ ህዝብ አላት።በ2.5% የሚጨምረው የሀገራችን የህዝብ ቁጥር በየዓመቱ ከ2.5 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ይጨመርበታል።የውልደት ምጣኔ በሚፈለገው መጠን አለመቀነስና የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት በሚፈለገው መጠን አለመዳረስ ጋር ተያይዞ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የሚገኘው የሀገራችን ህዝብ በአፍሪካ 2ኛና በዓለም 12ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።በሚቀጥሉት 30 ዓመታት የዓለም የህዝብ ቁጥር ዕድገት ከፍተኛውን ድርሻ ከሚይዙ ሀገራት አንዷ ኢትዮጵያ ናት።እንደ እ.ኤ.አ በ2050 የሀገራችን ህዝብ 168.8 ሚሊዮን ይደርስና ከዓለም 10ኛዋ የህዝብ ብዛት ያላት ሀገር ትሆናለች ተብሎ ይገመታል (ተ.መ.ድ. 2017)።
ስነ-ህዝብና ፖለቲካ ተያያዥነት አላቸው።ፖለቲካ ህዝብ የሚመራበትን የአስተዳደር ሥርዓት በማሳለጥ ሀገርን በፅኑ መሠረት ላይ ማቆም ነው።ፖለቲካ ሥርዓት፣ ሠላምና ደህንነት እንዲኖር በማመቻቸት ሳይንስና ቴክኖሎጂ የሀገርን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች እንዲበለፅጉ ያደርጋል።
የኋላ የፖለቲካ ታሪካችን በብዙ ውዝግብ የተሞላ ነው።እንደማሳያም ባለፉት መቶ ዓመታት የነበሩ የሀገራችን መሪዎች የሀገራችንን ሁነኛ ችግሮችን መረዳት የከበዳቸው ይመስላል።በአፄ ሀይለ-ስላሴ ዘመነ-መንግስት የነበረው የጥቂቶች የመሬት ከበርቴነት ለደሃው የሀገራችን የህዝብ ክፍል ኢኮኖሚያዊ መሠረት ያለው የማህበራዊ ፍትህ ጥያቄ አንዲያነሳ አድርጎት ነበር።የደርግ መንግስትም በነበረው አምባገንነትና በገጠመው ፖለቲካዊ ውጥረት የሀገሪቱን ሀብት ለመከላከያ በሰፊው በማዋሉ የሀገር ልማት ተጎሳቅሎ ነበር።ሕወሓት/ኢህአዴግ በስልጣን በቆየበት 27 ዓመታት የተደራጀ ዘራፊ በመሆን የሀገሪቱን ሀብት አሟጦ በመብላቱ ሀገራችንን ከፍተኛ የኢኮኖሚያዊ ሟጥ ውስት ከቷት ነበር።እነዚህ ምክንያቶች የሀገራችን ችግሮች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መሠረት ያደረጉ መሆኑን ቢያሳዩም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ባለመቀረፋቸውም ፖለቲካዊ መስለው ይታዩ ነበር።
የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ በቂ ትኩረት ባለመሰጠቱ በሀገራችን ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ አለመመጣጠንና የማህበራዊ ፍትህ መጓደል አምጥቷል።ብዛት ያለው ከድህነት ወለል በታች የሆነ ዜጋ ሲኖር መካከለኛ ገቢ ያለው ዜጋ እምብዛም አይደለም።ነገር ግን ጥቂት ከፍተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ዜጎች አሉ።ለምሳሌ፦ እንደ አሜሪካ ባሉ ሀገራት ማህበራዊ ፍትህ ማምጣት ከባድ ነው።በሀገሪቱ 99% የሚሆነው መካከለኛ ገቢ ካለው ተርታ ይመደባል።1%ቱ ደግሞ የናጠጠ ሀብታም ነው።ለምርጫ ዘመቻ ከፍተኛ ገንዘብ ስለሚያስፈልግ የሀገሪቱ የመምራት ዕድል ያላቸው ሀብታም ከሆኑት 1% ነው።በዚህም መካከለኛ ኑሮ ላይ የሚገኘው ዜጋ መሪም ሀብታምም የመሆን ዕድሉ ዝቅተኛ ይሆናል።
የዓለም ሀገራት የኢኮኖሚ ዕድገት ሲተነተን ከስነ- ህዝብ ጋር ተያያዥነት አለው።የምዕራብ አውሮፓ ሀገራት የኢንዱስትሪ አብዮት የስነ-ህዝብ ዑደት ክፍልፋይን መሠረት ያደረገ ነው።በወቅቱ የነበሩ የምጣኔ ሀብት ምሁራን ፈጣን የህዝብ ዕድገት ለኢኮኖሚ ዕድገት ጠንቅ ነው በሚል ተንብየው ነበር።በዚህም የህዝብ ዕድገት ምክንያት የሆኑትን ከፍተኛ የውልደት ምጣኔ እና ከፍተኛ የሞት ምጣኔ ወደ ዝቅተኛ የውልደት ምጣኔ እና ዝቅተኛ የሞት ምጣኔ በመለወጥ የስነ-ህዝብ ዑደት ክፍልፋይ በማምጣት የሚገኘውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች በማትረፍ ምዕራባዊያን ሀገራቸውን ማበልፀግ ችለዋል።የምስራቅ ኢሲያ ሀገራትም ምዕራባዊያን የፈጀባቸውን የ200 ዓመታት የስነ-ህዝብ ዑደት ክፍልፋይ ተሞክሮ በመውሰድ በ50 ዓመታት እና አራት እጥፍ ባነሰ ጊዜ የስነ-ህዝብ ዑደት ክፍልፋይ በማምጣት የሚገኘውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች በማትረፍ ሀገራቸውን ማበልፀግ ችለዋል፡፡
የስነ-ህዝብ ጉዳይ ለማህበራዊ፣ ለኢኮኖሚያዊና ለፖለቲካዊ ቀውሶች ምክንያት ሆኖ መቆየት ለፖለቲከኞች ምቹ ያደርገዋል።ፖለቲከኝነት እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች ባሉባቸው ደሃ ሀገራት አመቺ ነው።ምክንያቱም ቀውሶችን መሠረት አድርጎ ቅስቀሳ ለማድረግና ድጋፍ ለማግኘት ቀላል ስለሆነ ነው።ችግር ሲኖር ችግርን አጋኖ በመናገር የህዝብን ልብ መንካት የብዙ የደሃ ሀገራት ፖለቲከኞች ቁልፍ ቀመር ነው።በዚህም ደሃ ሀገራት ላይ ተቋዋሚ ፖለቲከኛ መሆን ገዢ መንግስት ከመሆን እጅግ በጣም ቀላል ያደርገዋል።
በሁለተኛው ምክንያት ደግሞ የህዝብ ቁጥር ትልቅ መሆን በቁጥሩ ልክ የፖለቲካ ተወካዮች እንዲኖር ስለሚረዳ ፖለቲከኞች የሥልጣን ዕድል ስለሚፈጥርላቸው የህዝብ መብዛትን ይደግፋሉ።የህዝብ መብዛት ለማህበራዊና ለኢኮኖሚያዊ ችግሮች መዳረጉ ግድ ለማይላቸው ፖለቲከኞች ጥሩ አጋጣሚ ነው።
ሦስተኛው ምክንያት ተደርጎ የሚወሰደው የህዝብ መብዛት ብዙ አምራች ዜጎች እንዲኖሩ ያደርጋል የሚል ነው።አንድ ዜጋ አምራች እንዲሆን ብዙ ዋጋ ይከፈልበታል።የተመጣጠነ ምግብ፣ ጥራት ያለው ትምህርት፣ ስብዕና የሚገነባ አስተዳደግ እና ምቹ አካባቢ ሲኖር አምራች የሆነ በአካሉና በአዕምሮው ብቁ ዜጋ ይፈጠራል።ይህ እንዲሆን አነስተኛ የቤተሰብ ቁጥር መኖር ያስፈልጋል።ይህ በማይሆንበት ሁኔታ ግን ጥገኛና ሰነፍ ዜጋ ይበረክታል።
ሌላኛው የተዘነጋው ስነ-ህዝብ ከሥራ-አጥነት ጋር ያለው ግንኙነት ነው።በሀገራችን በየዓመቱ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከ3 ሚሊዮን በላይ ተመራቂዎች ሲኖሩ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሥራ-አጥ ወጣቶች ይፈጠራሉ።ከመንግስትና ከግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በየዓመቱ የሚመረቀው ወጣት እና በየዓመቱ ያለው የሥራ ዕድል ተመጣጣኝ አይደለም።ብዛት ያላቸው ወጣቶች የውልደት ምጣኔ ከፍተኛ (5-7 የውልደት ምጣኔ) በነበረበት ወቅት የተወለዱ ናቸው።ምጣኔውን መሠረት ያደረገ የሥራ ፈጠራ ዕድገት ባለመኖሩ ብዛት ያላቸው ሥራ-አጥ ወጣቶች እንዲፈጠሩ ረድቷል።የስነ- ህዝብ ዕድገት ድሮም ግድ የማይላቸው የሀገራችን መንግስታት ለባለፉት ሦስት ዓመታት ለተከሰቱ ፖለቲካዊ ቀውሶች ምክንያት ሆነዋል።
ከላይ የተጠቀሱት ዝርዝር ምክንያቶች የስነ-ህዝብ ጉዳይ ለማህበራዊ፣ ለኢኮኖሚያዊና ለፖለቲካዊ ቀውሶች ዋነኛ መሠረት መሆኑን ያሳያል።እናም መንግስት በስነ- ህዝብ ላይ አተኩሮ መስራት እንዳለበት አመላካች ናቸው።ስለዚህ መንግስት እራሱን የቻለ የስነ-ህዝብ ጉዳዮች ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት አቋቁሞ የህዝብ ቁጥሩ እንዲረጋጋ ማድረግና የረጅም-ጊዜ መፍትሄ ማበጀት ይኖርበታል።
(የማዕከዊ እስታቲስቲክስ ኤጀንሲ እና ተ.መ.ድ. – የመረጃ ምንጮች ናቸው)
አዲስ ዘመን ግንቦት 5/2012
በላይ አበራ ከአርባምንጭ ዩኒቨርስቲ