ማንነታቸውና ዘራቸው ኢትዮጵያውያን የሆኑ ሰዎች ለኢትዮጵያ ነፃነት፣ አንድነት እና እድገት መስዋዕትነትን ቢከፍሉና አስተዋፅዖ ቢያበረክቱ ብዙም የሚያስገርም ላይሆን ይችላል። ነገር ግን የዘር ሀረጋቸው ከሌሎች አገራት የሚመዘዝ ሰዎች ለኢትዮጵያ በዋጋ የማይተመን አስተዋፅዖ ሲያበረክቱ መስማት/ማየት አስደናቂ ነው። ከዚህ ቀደም በዚሁ አምድ ላይ ታሪካቸውንና አበርክቷቸውን በመጠኑም ቢሆን የተመለከትንላቸው ወይዘሮ ሲልቪያ ፓንክረስትና ልጃቸው ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት እንዲሁም ላለፉት 61 ዓመታት ኢትዮጵያውያን ሴቶችን ሲያገለግሉ ኖረው ባለፈው መጋቢት ወር ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ዶክተር ኤሊኖር ካትሪን ሐምሊን በምሳሌነት ይጠቀሳሉ።
ኢትዮጵያ ውስጥ ኖረው፣ ለኢትዮጵያ ነፃነት፣ አንድነት እና እድገት ደክመው … ‹‹የትም ብሞት መቀበሪያዬ ኢትዮጵያ ትሁን›› ብለው በሌሎች አገራት አርፈው መቃብራቸው በሚወዷት ኢትዮጵያ የሆነላቸው የፎርድ ቤተሰቦችም ከመሰል የኢትዮጵያ ባለውለታዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። ለዛሬ የዚሁ ቤተሰብ አባል የሆኑትንና ለኢትዮጵያ ብዙ በጎ ተግባራትን ያከናወኑትን የፕሮፌሰር አብርሃም (ዐቢይ) ፎርድን ታሪክ በጥቂቱ እንመለከታለን።
አብርሃም ፎርድ በ1927 ዓ.ም በፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ ዋዜማ አዲስ አበባ ውስጥ ተወለደ። የኢትዮጵያ አርበኞችና የእንግሊዝ ሠራዊት አባላት የፋሺስትን ጦር እየወጉ አዲስ አበባ ሲገቡ በልጅነት አዕምሮው ያስታውሳል። ማርከስ ጋርቬይን ጨምሮ በወቅቱ የነበሩ ፓን-አፍሪካኒስቶች የአፍሪካ ዝርያ ያላቸው ሁሉ ወደ አፍሪካ እንዲሄዱ ይቀሰቅሱ ነበር። የኢጣሊያንን ጦር ዓድዋ ላይ ያሸነፈችው ኢትዮጵያ ደግሞ የመላው ጥቁር ሕዝብ የነፃነት ተምሳሌት ስለነበረች የነፃይቱን አገር አፈር መርገጥ ልዩ እድልና ስኬት ነበር። በዚህ ወቅት (በ1920ዎቹ) ነበር የአብርሃም ወላጆች ኢትዮጵያን ስለተወለዱባት ሳይሆን የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ተምሳሌትነቷን ከሩቅ ተረድተው፤ ኢትዮጵያን አልመዋትና ተመኝተዋትም ጭምር በካሪቢያን ቀጣና ከምትገኘው ባርባዶስ ደሴት ወደ ኢትዮጵያ የመጡት።
የዐቢይ አባት አርኖልድ ፎርድ የሃይማኖት መምህር፣ የቋንቋ ጥናት ባለሙያ፣ ሙዚቀኛና አስተማሪ ሲሆኑ እናቱ ወይዘሮ ሚኞን-ሎሪን ኢኒስ ደግሞ ሙዚቀኛና መምህርት ነበሩ። ወይዘሮ ሚኞን ፎርድ በጣፋጭ ምግቦች አዘጋጅነታቸውም የታወቁ ነበሩ።
ጥንዶቹ ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣታቸው በፊት በሀርለም የፓን-አፍሪካ ንቅናቄ ውስጥ ተሳታፊዎች ነበሩ። ጋብቻቸውን የፈፀሙት ኢትዮጵያ ውስጥ ነው። አብርሃምም ኢትዮጵያ ውስጥ ተወልዶ ክርስትና ከተነሳ በኋላ ስሙ ወደ ‹‹ዐቢይ›› ተቀየረ።
የማርከስ ጋርቬይ ወዳጅ የነበሩት አባት አርኖልድ ፎርድ፣ የመጀመሪያውን ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ መዝሙር (Universal Ethiopian Anthem) ያቀናበሩ ሰው ናቸው። የደሴቲቱ ሰዎች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው መኖር እንደጀመሩ ብዙም ሳይቆዩ ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ወረረች። ከእነርሱ ጋር ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ወዳጆቻቸው ወደ አገራቸው ሲመለሱ የፎርድ ቤተሰብ ግን ‹‹እኛ የመጣነው ኢትዮጵያውያን ለመሆን እንጂ ተመልሶ ለመሄድ አይደለም›› ብሎ ኢትዮጵያን ለማገልገል ተዘጋጀ።
ጥንዶቹ ኢትዮጵያን በተለያዩ መስኮች የማገዝ ፍላጎትም ስለነበራቸው እናቱ ቤተ-ኡራኤል (በኋላ ልዕልት ዘነበወርቅ) የተባለ ትምህርት ቤት አቋቋሙ። ዐቢይም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን የተማረው በዚሁ ትምህርት ቤት ነው። [ደራሲና ጋዜጠኛ በዓሉ ግርማም የተማረው እዚሁ ትምህርት ቤት ነው] ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በሊሴ ገብረማርያም ትምህርት ቤት ተከታትሏል። ‹‹አውራ ጎዳና›› ይባል በነበረው መስሪያ ቤት ውስጥ ለሁለት ዓመታት ያህል በሬዲዮ ኦፕሬተርነት አገልግሏል። ከዚያም በ1949 ዓ.ም ወደ አሜሪካ፣ ሚሲሲፒ ግዛት በማቅናት ከፓኔ ውድስ ጁኒየር ኮሌጅ በአንደኛ ደረጃ ሥርዓተ ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪውን አገኘ። በመቀጠልም ከኒውዮርኩ ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ የአጠቃላይ ጥናቶች ትምህርት ቤት በፊልም ጥናት የሁለተኛ ዲግሪውን ተቀበለ።
ዐቢይ በሃዋርድ ዩኒቨርሲቲ ለ33 ዓመታት ያህል የጋዜጠኝነት እና የፊልም አሠራር ጥበብ ትምህርት አስተምረዋል። በቆይታቸውም በዩኒቨርሲቲው በኮሚዩኒ ኬሽን ትምህርት ክፍል የሬዲዮ፣ ቴሌቪዥን እና ፊልም ትምህርቶች እንዲሰጡ አድርገዋል። በፊልምና ጋዜጠኝነት ላይ ያተኮሩ ትምህርቶችን አዘጋጅተዋል፤ጥናታዊ ጽሑፎችን አሳትመዋል። ከዚያም አልፎ ኢትዮጵያን ስለሚወዱ እንደፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ ያሉ ኢትዮጵያውያን በዩኒቨርሲቲው እንዲያስተምሩ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። ዩኒቨርሲቲውም በዋጋ ለማይተመን አገልግሎታቸው የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ሰጥቷቸዋል። ፕሮፌሰር ዐቢይ ወደ አሜሪካ ተጉዘው ካሳለፉት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ቆይታቸው ባሻገር በአሜሪካ አየር ኃይል መስሪያ ቤት ውስጥም የጦር ጄት አብራሪ ሆነው አገልግለዋል። ፕሮፌሰር ዐቢይ በሃዋርድ ዩኒቨርሲቲ መምህር በነበሩበት ወቅት ቢያንስ በሳምንት አንድ ቀን ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር እየተገናኙ ስለኢትዮጵያ ይወያዩ ነበር። ትኩረታቸውን በኢትዮጵያ መሻሻል ላይ አድርገው በተቋቋሙ አደረጃጀቶች ውስጥ ከአባልነት እስከ አመራርነት ድረስ በንቃት ይሳተፉ ነበር።
እ.አ.አ በ2006 ከሃዋርድ ዩኒቨርሲቲ ጡረታ ከወጡ በኋላ እርሳቸውም እንደወላጆቻቸው ሁሉ ለተወለዱባትና ላደጉባት ኢትዮጵያ የሚጠቅም ነገር የማከናወን ፅኑ ፍላጎት ስለነበራቸው ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ። በሃዋርድ ዩኒቨርሲቲ ሲያስተምሩ የቆዩት የጋዜጠኝነትና የፊልም ትምህርቶችን ስለነበርና በኢትዮጵያ የዳበረ የመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ እንዲኖር ፍላጎት ስለነበራቸው በጋዜጠኝነት የትምህርት መስክ ላይ የመሰማራት ፍላጎት አደረባቸው። ይህም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ቤት የድኅረ ምረቃ ክፍል መምህርና ዲን ሆነው እንዲያገለግሉ ምክንያት ሳይሆን አልቀረም። በቆይታቸውም ሙያው በተሻለ የሥልጠና ሥርዓት እንዲመራና ብቁ ምሩቃን እንዲመረቱ አስተዋፅኦ አድርገዋል።
ከዚህ ኃላፊነታቸው ጎን ለጎን በኢትዮጵያ የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተሻለ አደረጃጀትና አቅም እንዲኖራቸው በአሜሪካ ቆይታቸው የቀሰሙትን ዘርፈ ብዙ ልምድ አጋርተዋል፤ በተግባር ላይ እንዲውልም ጥረዋል። በተለይ ከሃዋርድና ከኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የነበራቸውን መልካም ግንኙነት ተጠቅመው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዘርፈ ብዙ ድጋፎችን እንዲያገኝ አድርገዋል።
ፕሮፌሰር ዐቢይ ኢትዮጵያ ውስጥ የፊልም ጥበብ ዘመናዊ ሥርዓትን ተከትሎ ራሱን በቻለ የማስተማሪያ ተቋም ውስጥ እንዲሰጥ ትልቅ ምኞት ነበራቸው። ይህ ምኞታቸው በሃዋርድ ዩኒቨርሲቲ ለበርካታ ዓመታት የፊልም ትምህርት ጥበብን ከማስተማራቸው ጋር ተደምሮ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፊልም ትምህርት ቤት እንዲያቋቁም ምክረ ሃሳብ አቅርበዋል።
የዩኒቨርሲቲው የሥነ ጥበባት ትምህርት ቤት ልዩ አማካሪ በመሆንና በዩኒቨርሲቲው የፊልም ጥናት ትምህርት ክፍል ለመጀመር የተደራጀውን ግብረ ኃይል በማማከር ውጤት አስገኝተዋል። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ በአንድ ወቅት ስለጉዳዩ ሲናገሩ ‹‹ … የፊልም ትምህርት ቤት ለማቋቋም ተነድፎ በነበረው እቅድ ውስጥ የዐቢይ ድርሻ ትልቅ ነበር። ሙያዊ ችሎታውን በመጠቀም ባልደረቦቹ በሥራው ውስጥ እንዲሳተፉ ያነሳሳ ነበር። በሙዚቃ ሥራዎች ላይም ትልቅ ተሳትፎ ነበረው …›› ብለዋል። ፓን አፍሪካኒስቱ ፕሮፌሰር ዐቢይ ከ26 በላይ የሚሆኑ ዘጋቢ ፊልሞችን ሰርተዋል።
ፕሮፌሰር ዐቢይ በርካታ ወጣት ኢትዮጵያውያን የፊልም ባለሙያዎች የውጭ የትምህርትና የሥልጠና ዕድሎችን እንዲያገኙ ሁኔታዎችን ያመቻቹ ነበር። ይህም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከብዙ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ግንኙነት እንዲመሰርት አግዞታል። የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት የዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ከፍተኛ አማካሪ ሆነውም አገልግለዋል።
ፕሮፌሰር ዐቢይ ለሙዚቃ ልዩ ፍቅር ያላቸውና ራሳቸውም ጥሩ ሙዚቀኛ ነበሩ። ይህም ከብዙ ኢትዮጵያውያን ሙዚቀኞች ጋር ሙዚቃ እንዲጫወቱና ከኪነጥበብ ሰዎች ጋር ከፍ ያለ ወዳጅነት እንዲኖራቸው አስችሏቸዋል። ሙዚቃን መውደድ ብቻ ሳይሆን የተለያዩ የሙዚቃ መሣሪያዎችንም በመጫወት ከራሳቸው አልፈው ሌሎችን ያስደስቱበታል። ጊታር፣ ሳክስፎን እና ፒያኖ የሚጫወቱት ፕሮፌሰሩ፣ ቆየት ያሉ ሙዚቃዎችን ይወዳሉ።
በብዙዎች ‹‹ጋሽ ዐቢይ›› እየተባሉ የሚጠሩት ፕሮፌሰር ዐቢይ ፎርድ፤ ተጫዋችና ከሁሉም ሰው ጋር ወዳጅነት መመስረት የሚችሉ ትሁት ምሁር እንደነበሩ የሚያውቋቸው ሁሉ ይናገራሉ። በተለይ ደግሞ በአሜሪካ ለተማሩ ኢትዮጵያውያን ደጋፊና ታላቅ ወንድም ነበሩ። ከወላጆቻቸው የወረሱት ኢትዮጵያዊነትም ሰፊ ትርጉም ያለውና የዓለምን ጥቁር ሕዝቦች የሚጠቀልል የነፃነት መንፈስ እንደሆነ ይናገሩ ነበር።
ፕሮፌሰር አንድርያስ ‹‹ … በአፍሪካ-አሜሪካውያን፣ በአፍሮ-ካሪቢያን እና በኢትዮጵያውያን መካከል ጠንካራ ትስስር እንዲፈጠር ያደረገ ጠንካራ ሰው ›› በማለት ፕሮፌሰር ዐቢይን ይገልጿቸዋል። ግልፅነትን አብዝተው የሚወዱት ፕሮፌሰር ዐቢይ፣ ግልፅነት የልዩነቶች መፍቻ፣ ሰውን የማገልገያና የመቻቻል መሣሪያ እንደሆነ ያምናሉ።
ደራሲና ጋዜጠኛ ነብይ መኮንን በአንድ ወቅት ስለፕሮፌሰር ዐቢይ በገለፀበት ጽሑፉ …
«… ‹ይህን ያህል ተምሮ ምን ሰርቷል? ምንስ ሆኖ አገልግሏል?› ማለት መቼም ያባት ነው። የሰራው ሥራ ሲደረደር ያስደነግጣል። አንዳንዶቻችን በዕድሜያችን እዚህ ግባ የማትባል ትንሽ ሥራ ያስመዘገብን እንደሆነ የዓለምን ሪኮርድ የሰበርን ይመስል ዘራፍ ማለትን እንደባህል ሰልጥነንበታልና ፕሮፌሰር የሰራበትን ቦታና ሙያ ብደረድረው መልካም መሰለኝ … የማስ ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ የአፍሪካና የሦስተኛው ዓለም የልማት ጽንሰ ሀሳብ ስፔሻሊስት፣ በአሜሪካ አየር ኃይል ዲሲ ስኳድሮን ዋና ፓይለትና የኤሮኖቲክስ ኢንስትራክተር፣ የቴሌቪዥን መሐንዲሶች ማኅበር የቀድሞ አባል፣ የአፍሪካውያን የመላው ዓለም የፊልም ሥራዎችና የቪዲዮ ግራፊክስ ፌዴሬሽን መስራችና የአደራጅ ኮሚቴው ሰብሳቢ ነበሩ። የፓን አፍሪካን ፌዴሬሽን አባል፣ የዋሽንግተን ዲሲ ትምህርት ቦርድ የመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ አማካሪ፣ የቀድሞው የፖዘቲቭ ኢንኮርፖሬሽን ፕሬዚዳንት፣ የሰምና ወርቅ የጥናትና ምርምር መጽሔት የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀ መንበር፣ በቡርኪና ፋሶ ኡጋዱጉ ከተማ በሚገኘው የጥቁር ኢንስቲትዩት በሚባለው ተቋም ውስጥ የዓለም አቀፍ የሥራ አመራር አባል፣ የፋና ፕሮዳክሽንስ ፕሬዚዳንት፣ የወርልድ ስፔስ አማካሪ፣ የሚኞን-ሎራን ኢኒስ ፎርድ ፋውንዴሽን ፕሬዚዳንት … ሌላም ናቸው። ታዲያ ብዙ ኃላፊነት ብዙ እንደሚያሰራ ከዚህ አንረዳምን?» በማለት ጽፏል።
ከፕሮፌሰር ዐቢይ ጋር የሚተዋወቁት የምጣኔ ሀብትና የፖለቲካ ባለሙያው ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በበኩላቸው ‹‹ …ዐቢይ ባለ ልዩ ተሰጥኦና ባለ ብሩህ አዕምሮ ተመራማሪ ነበሩ። ለኢትዮጵያ ሚዲያ ልዕልና የታገሉ ምሁር ናቸው። እስከመጨረሻው የነበራቸው እምነትም ‹የአገሪቱ ሚዲያዎች አራተኛ የመንግሥት አካልነታቸውን ሚና ጠንክረው መወጣት አለባቸው› የሚል ነበር። ለሀገሪቱ የሚዲያ ምኅዳር መሻሻልም ቀናኢ የሆኑ ሙግቶችን የሚያቀርቡ የሚዲያው ጠበቃ ነበሩ …›› በማለት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
ፕሮፌሰር ዐቢይ አማርኛ፣ እንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛና ጣሊያንኛ ቋንቋዎችን አቀላጥፈው የሚናገሩ ሲሆን፤ አረብኛ እና ራሺያኛም ይሞክራሉ። ይህ ችሎታቸውም በአፍሪካ፣ በአሜሪካ፣ በአውሮፓና በካናዳ የሃዋርድና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተወካይና አማካሪ ሆነው እንዲሰሩ አስችሏቸዋል።
ኢትዮጵያን የማገልገል ተልዕኮን ከቤተሰቦቻቸው የወረሱት ፕሮፌሰር ዐቢይ ተልዕኳቸውን ፈፅመው፣ ግንቦት 1 ቀን 2010 ዓ.ም በአሜሪካ ሳሉ አርፈዋል። «የትም ብሞት ኢትዮጵያ መቀበር እፈልጋለሁና ይህንን አድርጉልኝ» ብለው ስለነበር በቃላቸው መሠረት አስክሬናቸው ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ በጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን እንዲያርፍ ተደርጓል። የፕሮፌሰር ዐቢይ አባት አርኖልድ ፎርድ ያረፉትም የተቀበሩትም ኢትዮጵያ ነው። እናታቸው ወይዘሮ ሚኞን ፎርድ ልጆቻቸውን ለመጠየቅ ወደ አሜሪካ ሄደው ሳለ እዚያው ቢያርፉም የተቀበሩት ኢትዮጵያ ውስጥ ነው። ወንድማቸው ዮሴፍ ፎርድም አሜሪካ ውስጥ አርፈው ቀብራቸው በኢትዮጵያ እንዲሆን ቃል በማስገባታቸው እንደሌላው የቤተሰብ አባል ሁሉ መቀበሪያቸው ኢትዮጵያ ሆናለች። ፕሮፌሰር ዐቢይ ፎርድ የአንዲት ሴት ልጅ አባት ነበሩ፤ፋሲል የተባለ የልጅ ልጅም ለማየት በቅተዋል።
የኢትዮጵያ ባለውለታ የነበሩት አንጋፋው የፊልም፣ የሙዚቃ፣ የጋዜጠኝነትና የተግባቦት ባለሙያው ፕሮፌሰር ዐቢይ ፎርድ፣ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን የሰሯቸው በጎ ሥራዎች እንዲሁም ያሳዩት ፍቅርና ክብር በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ሕያው ሆኖ የሚኖር ነው።
አዲስ ዘመን ግንቦት 5/2012
አንተነህ ቸሬ