መነሻውን የቻይናዋ ሁዋን ያደረገው የኮሮና ወረርሽኝ መላውን ዓለም አዳርሶ በአሁኑ ወቅት ከአራት ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ተጠቂ ያደረገ ሲሆን በሥልጣኔና በኢኮኖሚ ዕድገት ጫፍ ደረሱ የተባሉት አገራትን ሳይቀር በከፍተኛ ሁኔታ ተጠቂ አድርጓል። የዓለም ልዕለ ኃያሏ አገር አሜሪካ እንኳን ከአንድ ሚሊዮን በላይ ዜጎቿ በቫይረሱ ተጠቂ ከመሆናቸውም በላይ የ80 ሺህ ሰዎችንም ሕይወት በዚሁ ወረርሽኝ ጦስ አጥታለች።
ከቫይረሱ ተለዋዋጭ ባህሪ የተነሳ ምንም ምልክት ያላሳዩ ሰዎች ጭምር ተጠቂ ሆነው መገኘታቸውና የመዛመት ባህሪው እጅግ ፈጣን ከመሆኑ የተነሳ ያደጉት አገራትም ቢሆኑ አንዱ በአንዱ ላይ እጅ ከመጠቆም ባለፈ ለቫይረሱ ይህ ነው የተባለ ፍቱን መድኃኒት እስካሁን ድረስ አላገኙለትም። በተለያዩ አገራት ተስፋ ሰጪ የሆኑ የክትባትና የመድኃኒት ሙከራዎች እየተከናወኑ ስለመሆኑ ከመገለጹ ውጪ ፈዋሽነቱ የተረጋገጠ መድኃኒትም ሆነ ክትባት እስካሁን ድረስ ስለመገኘቱ የተገለጸ ምንም ነገር የለም።
ከላይ የተገለጹት እውነታዎች የሚያሳዩት ነገር ቢኖር በአሁኑ ወቅት ያለው አማራጭ ወረርሽኙን ለመከላከል የጤና ባለሙያዎች የሚሰጡትን ምክረ ሃሳብ መተግበር እና መተግበር ብቻ ነው። አካላዊ ርቀትን መጠበቅ፣ ሕዝብ በብዛት ወደሚሰበሰብባቸው ቦታዎች አለመሄድ፣ የግድ ካልሆነ በስተቀር እንቅስቃሴን ለጊዜው መገደብ፣ ሲያስሉና ሲያስነጥሱ አፍና አፍንጫን በመዳፍ ወይም በክርን መሸፈን፣ እጅን በየጊዜው መታጠብና እንደሳሙና፣ አልክሆልና ሳኒታይዘር ያሉ የንጽህና መጠበቂያዎችን በአግባቡ መጠቀም አሁንም ቢሆን የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል የሚያስችሉ የጥንቃቄ መንገዶች ናቸው።
በከፍተኛ ፍጥነት በመሰራጨት መላ ዓለምን ያዳረሰው ይህ ወረርሽኝ በአገራችንም ለመጀመሪያ ጊዜ መጋቢት 3/2012 መከሰቱ ከታወቀ በኋላ በቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር ለተወሰነ ጊዜ የመረጋጋት መልክ ካሳየ በኋላ ሰሞኑን ከፍተኛ መጠን መመዝገብ ጀምሯል። የወርርሽኙን በከፍተኛ ፍጥነት መሰራጨትና የቫይረሱን ተለዋዋጭ ባህሪ በመረዳት መንግሥት የተለያዩ የጥንቃቄ እርምጃዎችን በተከታታይ ከመውሰዱም በላይ ኅብረተሰቡም አስፈላጊውን የጥንቃቄ እርምጃ ያለምንም መዘናጋት እንዲወስድ ሌት ተቀን ሲማጸን ቆይቷል።
ይህንን ተከትሎም በተለይም በመጀመሪያዎቹ ሰሞናት ሕዝባዊ ንቅናቄ በሚመስል መልኩ እጅ የማስታጠብ፣ ኅብረተሰብን የማንቃት ሥራ ላይ ሰፊ እንቅስቃሴ ሲታይ ነበር። ይሁንና በሂደት በየቀኑ የሚሰጠው የታማሚዎች ቁጥር አነስተኛ መሆንን ተከትሎ መዘናጋቱ በከፍተኛ ሁኔታ ሲታይ ቆይቷል። ይህንን ተከትሎም የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የኪነጥበብ ባለሙያዎች፣ መገናኛ ብዙኃን ወዘተ መዘናጋቱ ከፍተኛ ዋጋ ያስከፍለናል፣ በአገራችን አቅም ወረርሽኙ ከፍተኛ ደረጃ ከደረሰ መቆጣጠር ስለሚሳነን ጉዳቱ አስከፊ ይሆናል የሚል ተማጽኖ ቢያቀርቡም ተቀብሎ መተግበሩ ላይ የታየው ዳተኝነት ቀላል አልነበረም።
በተለይም በባለፉት ሳምንታት ይወጡ የነበሩ ሪፖርቶች በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር አነስተኛ እንደሆነ የሚያሳዩ ስለነበሩ ቫይረሱ የጠፋ በሚያስመስል መልኩ የጥንቃቄ እርምጃዎችን የመዘንጋቱ ነገር በስፋት ተስተውሏል። በትራንስፖርት መናኸሪያዎች፣ በገበያ ቦታዎችና በካፍቴሪያዎች አካባቢ የነበረው መጠጋጋትና ግፊያ እጅግ አስደንጋጭ ነበር። በአንዳንድ ቦታዎችም ለእጅ ማስታጠቢያ ተብለው የተቀመጡ ዕቃዎች ሲነሱም ተስተውሏል። በምርመራ ውጤቶቹ የተያዦች ቁጥር አነስተኛ መሆን ቫይረሱ ጠፋ ወይም ደግሞ በቅርባችን የለም ማለት አይደለም ስለዚህ አንዘናጋ የሚሉ መልዕክቶች ከጤና ሚኒስቴርና ከሚመለከታቸው አካላት በተደጋጋሚ የተላለፈ ቢሆንም መተግበሩ ላይ ግን አመርቂ ውጤት ሊታይ እንዳልቻለ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነበር።
እንደተፈራው አልቀረም መዘናጋቱና የሚሰጡ ምክሮችን አለመተግበሩ ዋጋ እያስከፈለ ስለመሆኑ ሰሞኑን ከወጡ ሪፖርቶች መረዳት ይቻላል። ከወር በላይ ለሆነ ጊዜ በቀን አንድና ግፋ ሲልም ከስድስት በልጦ የማያውቀው የተያዦች ቁጥር አሁን በቀን ከ19 እስከ 25 በተደጋሚ መመዘገብ ጀምሯል። ጉዳዩን ይበልጥ አሳሳቢ የሚያደርገው ደግሞ ከሰሞኑ በቫይረሱ እየተያዙ ያሉ ሰዎች የውጭ አገር ጉዞ ታሪክና ከታማሚ ጋር ንክኪ የሌላቸው መሆኑም ነው።
ይህም እውነታ ቫይረሱ እጅግ ቀርቦን አጠገባችን እንደደረሰ የሚያሳይ ነው። ስለሆነም ከዚህ በፊት የነበረውን መዘናጋት ትተን በጥበቅ ዲስፕሊን የመካለከያ እርምጃዎቹን መተግበር ለነገ የምንለው ጉዳይ ሊሆን አይችልም፤ አይገባምም!
አዲስ ዘመን ግንቦት 4/2012