“ታይዋን ፈጥኖ ከቸነፈር፣ ከችጋርና ከወረርሽኝ በማገገም የምትታወቀ ደሴት ናት። ታይዋናውያን ለዘመናት የተሻገሯቸው መከራዎች በቀላሉ ፈተናዎችን እንዲቋቋሙ፣ እንዲላመዱና እንዲሻገሩ ጉልበት ፣ ብርታት ሆኗቸዋል። የኮቪድ – 19 አደገኛ ወረርሽኝ ደግሞ እስከዛሬ በጽናት ካለፍናቸው ሀገራዊ አሳሮች የተለየ አይደለም። …” ይላሉ የታይዋን ፕሬዚዳንት። እዚህ ላይ ሁለት ነጥቦችን እግረመንገድ ላንሳ ። የመጀመሪያው ተወዳጁ ታይም መፅሔት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን አስመልክቶ መልዕክታቸውን እንዲያስተላልፉ እድሉን ከፈጠረላቸው 100 ታዋቂና ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎች አንዷ ሆነው የተመረጡት የታይዋን ፕሬዚዳንት ጻይ ኢግ – ዌን ከመሆናቸው ጋር የሚያያዝ ነው።
ታይም መፅሔት በየአመቱ በአለማችን 100 ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑ መሪዎችን ፣ ፓለቲከኞችን፣ ታዋቂዎችንና ዝነኞችን እየመረጠ የ” አመቱ 100 ተፅዕኖ ፈጣሪዎች “ እያለ አጠር ካለ ግለ ታሪካቸው ጋር የማውጣት ፋና ወጊና የበለጸገ ልማድ አለው ። ከድህረ ኮቪድ – 19 በኋላ መፅሔቱ በተመሳሳይ ቅርፅ / ፍሬም / ግን ወቅታዊ በሆነ ይዘት መጥቷል። የመረጣቸውን ታዋቂ ሰዎች ፕሮፋይል ይዞ ከመውጣት ይልቅ ስለኮሮና ቫይረስ ያስተላለፉትን መልዕክት ለንባብ ማብቃትን መርጧል። ታይም መፅሔት ወዲያው ወረርሽኙን ለመከላከል ያግዛል ያለውን ለውጥ ተግብሯል። አርትኦቱን፣ አዘጋገቡን ፣ ትንተናውን ፣ አሰራሩን ፣ አደረጃጀቱን ፣ ወዘተረፈ ከኮቪድ -19 አንጻር ቃኝቷል። ከልሷል። ከሀገራችን ሚዲያዎች ምን ያህሉ ከቫይረሱ አኳያ የዘገባቸውን፣ የመጣጥፋቸውን፣ የርዕሰ አንቀጻቸውን፣ የፕሮግራሞቻቸውን ፣ ወዘተረፈ ቅርጽና ይዘት / content / ቃኝተዋል ? አሰራርና አደረጃጀታቸውን ፈትሸዋል? ምን አልባት ሊከተል የሚችለውን ቀውስ ታሳቢ በማድረግ ስንቶቹ አበክረው የቀውስ አመራር ኮሚቴ አቋቁመዋል ? ምላሹን ለራሳቸው ትቸዋለሁ። ሁለተኛው ታይዋን ከታሪኳ በመማር ኮቪድ -19ን ጨምሮ አሁናዊ ችግሮቿን እንዴት መፈታት እንደቻለች ፕሬዚዳንቷ በኩራት የገለጹበት መንገድ ነው። የታይዋንን ታሪክ ፣ ያለፈችባቸውን ውጣ ውረዶችና ፈተናዎችን በአንክሮ ብንመለከት ከሀገራችን ኢትዮጵያ የ5ሺህና ከዚያ በላይ ከሆነ ታሪክ እና ካለፍንባቸውና እያለፍናቸው ካሉ እልፍ አእላፍ ከሆኑ ፈተናዎችና ችግሮች አንጻር ስናየው የአጭር ጊዜ ከመሆኑ ባሻገር ያለፈችባቸው መከራዎች እዚህ ግቡ የሚባሉ ላይሆኑ ይችላሉ። ፕሬዚዳንቷ ግን ታይዋን በአለፈ ታሪኳ በመነታረክ ሳይሆን በመማር የችግሮቿ መፍቻ ቁልፍ አበጅታለች። እኛስ ከዳጎሱት የታሪክ ስንክሳሮቻችን፣ እንደ ቋጥኝ ከገዛዘፉ የትላንት አሳሮቻችን ተምረን፣ ተዘክረን ወቅታዊ ለሆኑ ፈተናዎቻችን ተጠቅመንባቸዋል? እየተጠቀምንባቸው ነው። ከክፉ ቀን ፣ ከ67ቱ፣ ከ77ቱ ርሀቦች ፤ ከጥቁሩ ሞት፣ ከፈንጣጣና ከሕዳር በሽታ፣ ከኤች አይ ቪ/ኤድስ ወረርሽኞች፤ ከስልጣን ሽኩቻዎቻችን፣ ከእርስ በርስ ግጭቶቻችን፣ ከውጭ ወረራዎች፤ ተምረን፣ ቀምረን ፣ ጨምቀን የተግባር መማሪያ፣ የችግር መፍቺያ መንገድ አመላክተናል ? የምርምር ተቋማት፣ እንደ አሸን የፈሉት ዩኒቨርስቲዎቻችን፣ በየአመቱ ፉክክር በሚመስል ከየዩኒቨርስቲዎቻችን በፕሮፌሰርነት ከሚንበሸበሹቱ ውስጥ ስንቱ ካለፉ ህማማት ፣ ህዳሴዎች፣ ወርቃማ ዘመኖች፤ ቀምረው ምን ያስቀሩልን ነገር አለ? ከዛሬው ኮሮና ቫይረስ ምን እየተማርን፣ እየመዘገብን፣ እየቀመርን ነው?
ወደ ታይዋኗ ፕሬዚዳንት ስንመለስ፣ “…ምንም እንኳ ቫይረሱ በፍጥነት የሚዛመትና ለቻይናም ቅርብ ብንሆንም ወረርሽኙ ሳይስፋፋ መቆጣጠር ችለናል። በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር ከ400 ያልበለጠ ነው።
(ፕሬዚዳንቷ ይሄን ያሉት ከሚያዝያ 10 ቀን 2012 ዓ.ም በፊት ስለሆነ የአኃዝ ለውጥ ሊኖር ይችላል። ) ውጤታማ የሆነው በአጋጣሚ አይደለም። በ2003 እ.ኤ.አ ከተከሰተው የሳርስ ቫይረስ ወረርሽኝ በመማር የጤና ባለሙያዎችን፣ መንግስትን ፣ የግሉን ዘርፍና መላ ሕዝቡን በማቀናጀትና በማስተባበር ኮቪድ – 19ን መቆጣጠር ችለናል። በቻይና ውሃን ታህሳስ ላይ የመተንፈሻ አካልን የሚያጠቃ በሽታ መከሰቱን ስንሰማ ከአካባቢው የሚመጡ ሰዎችን በቅርብ መከታተል ጀመርን። በቀጣዩ ወር ጥር ላይ ወረርሽኙን አስቀድሞ መከላከል የሚያስችል እርምጃ ለመውሰድ የማዘዣ ጣቢያ አቋቋምን። በማስከተል የእንቅስቃሴ ገደብ ጣልን፤ የቁጥጥር ስርዓት ዘረጋን። የመጀመሪያው ተጠቂ ጥር 12 ቀን 2012 ዓም እንደተለየ የጉዞና የግንኙነት ታሪኩን በመከታተል በለይቶ ማቆያ አድርገን እንዳይዛመት ጠንካራ ቁጥጥር ማድረግ ጀመርን። ከጤና ባለሙያዎቻችን የቀንና ሌሊት ርብርብ ጎን ሕዝቡ የዜግነት ድርሻውን በአግባቡ ተወጥቷል። የግል ንግድ ድርጅቶች እና የአፓርታማ ነዋሪዎች በራሳቸው ተነሳሽነት የሙቀት ልየታንና አካባቢን በኬሚካል የማፅዳት ስራ ማከናዎን መጀመራቸው ለመንግስት ትልቅ ወኔና አቅም ሆኖታል። …” የCNNኑ ፋሪድ ዘካርያ ምንጭ ጠቅሶ በተጠቀመበት ቀመር፤ ታይዋን የተጠናከረ ምርመራ እና የእንቅስቃሴ እቀባ ባታደርግ ኖሮ በወረርሽኙ የሚያዘው ሰው ከ400 በ67 እጥፍ አሻቅቦ 26 ሺህ 800 ይደርስ ነበር። እንዲሁም የምርመራና የእቀባ ስራዋን ከጀመረችበት ቀን አንድ ሳምንት ቀድማ ማካሄድ ብትጀምር ኖሮ ደግሞ በወረርሽኙ የተያዘውን ዜጋ ቁጥር ከ400 በ66 በመቶ ቀንሶ ማለትም በ264 ቀንሶ ወደ 136 መቀነስ ትችል ነበር ። ሀገራችን ወረርሽኙን በተመለከተ የወሰነችውን ውሳኔ ከአንድ ሳምንት ቀድማ ብታደርገው ኖሮ ዛሬ የተሻለ ውጤት ባስመዘገበች። እዚህ ላይ የታይዋን መንግስት ፈጥኖ መንቀሳቀስ መቻሉ በወረርሽኙ ይጠቃ የነበረን 26ሺህ 400 ሰው መታደግ ችሏል። ሕዝቡ በራሱ ተነሳሽነት የወሰዳቸው የመከላከል ስራዎች የመንግስትንም ሆነ የሕክምና ባለሙያዎችን ጫና በእጅጉ ቀንሶታል። ኢኮኖሚያችን፣ ግንዛቤአችንና የስነ ልቦና ውቅራችን የተለያየ ቢሆንም ሕዝባችን ወረርሽኙን ለመከላከል ንቁ ተሳታፊ ቢሆን ኖሮ እንደ ታይዋን ውጤታማ መሆን በተቻለ። በሀገራችን እየሆነ ያለው ግን ከዚህ በተቃራኒው ነው። አይደለም በራስ ተነሳሽነት የመከላከል ጥረቱን መቀላቀል መንግስት ለመከላከል የሚያደርገውን ጥረት እያደናቀፈ ነው ማለት ይቻላል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁንም በቅጡ እያከበረ አይደለም። ሕዝብ መንግስት የሚለውን አድምጦ ተባባሪና የመከላከል ጥረቱ አካል መሆን ካልቻለ በአንድ እጅ እንደ ማጨብጨብ ነው። መንግስት ምንም ያህል የተቀናጀና የተናበበ ጥረት ቢያደርግ ብቻውን ውጤታማ ሊሆን አይችልም። ዛሬም አልረፈደምና ሕዝብ በተቻለ አቅም ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል። የመከላከሉ ጥረት አካል ለመሆን የግድ ከእልቂትና ከሞት ጋር ፊት ለፊት መጋፈጥ አያስፈልግም። እንደ አሜሪካ ፣ ጣሊያን፣ ስፔን ሕዝብ ማለቅ የለበትም። እንደ ሩሲያ በአንድ ቀን 10ሽህ ሰው በቫይረሱ መጠቃት የለበትም ።
“…ወረርሽኙ እንደ ገባ በሸማቾች መደናገጥ፣ መረበሽና መደናገር የተነሳ ገብያው ወደለየለት ቀውስ እንዳያመራና በሸቀጦች ላይ ያልተገባ እጥረትና ይህን ተከትሎ የዋጋ ጭማሪ እንዳይከሰት መንግስት ቁጥጥር ከማድረጉ ባሻገር የአፍንጫ የአፍ መሸፈኛ ምርትንና ስርጭትን በቁጥጥሩ ስር በማዋል ፣ የመከላከያ አልባሳትንና የሌሎችን የህክምና ቁሳቁሶችን ፍትሐዊ በሆነ አግባብ ለማዳረስ ጥረት ተደርጓል። በቂ የአፍንጫ የአፍ መሸፈኛዎቹን ለሕዝቡም ሆነ ለሕክምና ተቋማት ከማከፋፈል አልፈን በወረርሽኙ ክፉኛ ለተጠቁ ሀገራት መርዳት ችለናል። …” ሲሉ በልበ ሙሉነት ይናገራሉ። አንዳንድ ስግብግ ነጋዴዎችና አምራቾች በሀገራችን የወረርሽኙን መግባት ተከትሎ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ምርት በመጋዘን፣ በመደበቅና ሰው ሰራሽ እጥረት በመፍጠር ከፍተኛ ዋጋ በመጨመር ቀውስ በመፍጠራቸው በብዙ ሺህዎች በሚቆጠሩ ነጋዴዎችና አምራቹ ሕጋዊ እርምጃ በመውሰዱ ጋብ ያለ ቢመስልም ሰሞኑን ደግሞ ከሀገርና ከዜጋ ጋር ሌባና ፓሊስ መጫወቱን ቀጥለዋል። እንደ ዘይት፣ ዱቄትና ባሉ መሰረታዊ ሸቀጦች ላይ እጥረት በመፍጠር ከፍተኛ ዋጋ በመጨመር በእንቅርት ላይ እንዲሉ በሕዝቡ ላይ ምሬትንና ብሶትን እየጎነቆሉ ነው። መንግስት ጨከን ያለ ሕጋዊ እርምጃ በመውሰድ የሸማቹን መብት ሊያስከብር ይገባል። ይህን በጊዜ ማድረግ ካልቻለ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ በመጨረሻ ወደለየለት የፖለቲካ፣ የደህንነትና የጸጥታ ቀውስ ሊያመራ ይችላል። እና አበው እማት እንደሚሉት ሳይቃጠል በቅጠል ።
ፈጣሪ ሀገራችን ኢትዮጵያንንና ሕዝቧን ከኮቪድ – 19 ይጠብቅ ! ይማር ! አሜን ።
አዲስ ዘመን ግንቦት 3/2012
በቁምላቸው አበበ ይማም ( ሞሼ ዳይን )
fenote1971@gmail.com