ዓለም አቀፉ የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ 19) ወረርሽኝ ከተከሰተ ወራትን አስቆጥሯል። በዚህም ሚሊዮኖች በበሽታው ሲያዙ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ እጅግ ፈጣን በሆነ መንገድ ሕይወታቸውን ተነጥቀዋል።
ከወረርሽኙ ሙሉ ለሙሉ ለማዳንም ሆነ ለመከላከል የሚጠቅሙ መድኃኒቶች እስካሁን ድረስ የነጠፉ ይመስላሉ። ብዙዎች የሚመኩበት ሳይንስ ግልፅ ያለ መፍትሄውን ነብሳቸው ለተጨነቁ የሰው ልጆች ሊሰጥ አልቻለም። እራስን ለማዳን ብቸኛ አማራጭ ከባህል፣ ከሃይማኖት፣ ከሰው ልጆች ልማድ አፈንግጦ በቤት ውስጥ መቀመጥ፣ አለመጨባበጥ፣ እጅን ደጋግሞ መታጠብ እና አካላዊ መራራቅ ሆኗል።
ጥቁር ነጭ፣ ሕፃና አዋቂ፣ ሀብታም ድሃ፣ ታዋቂ ተወዳጅ የሚባሉ ማህበረሰባዊ ክፍፍሎች ትርጉም የለሽ ናቸው። በዓለም ላይ ያሉ የሰው ልጆች በቫይረሱ እየተያዙ ገሚሶቹ እንደ ዕድል ሆኖ ሲያገግሙ አዱኛ ፊቷን ያዞረችባቸው ደግሞ እስከወዲያኛው ይህቺን ምድር ተሰናብተዋል።
ይሄ ጽሑፍ እስከተዘጋጀበት ዕለት ድረስ በአፍሪካ ከ50 ሺህ በላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ሲመዘገቡ ከ1ሺህ 900 የሚልቁት ደግሞ ሕይወታቸውን ተነጥቀዋል። ለዚህ መሰል ቫይረስ ከዚህ ቀደምም ተጋላጭነቷ የሰፋው አፍሪካ ከአውሮፓና ሌሎች የዓለማችን ክፍሎች አንፃር ሲመዘን እንዲያውም እስካሁን የተጠበቀው ግዙፍ ማዕበል ወደኋለ ያፈገፈገ ይመስላል። ሆኖም ይህ ሱናሚ ነገም ሆነ ዛሬ በድንገት እንደ ዱብእዳ ሊወርድ እንደማይችል ምንም ማረጋገጫ የለም።
ወረርሽኙ ከሞትና በበሽታው ከመሰቃየት በተጨማሪ ያደረሰው ጉዳይ የትየለሌ ነው። ምጣኔ ሀብታቸው ጠንካራ ከሆነው አገራት አንስቶ በማደግ ላይ ያሉና ታዳጊ አገራትን ክንድ አሽመድምዷል። በቀጥታ ቫይረሱ ያልያዛቸው ድሆች የዕለት ጉርሳቸውን የማግኘት አማራጫቸውን በመዝጋት ሕይወታቸውን በከፋ መልኩ ለመንጠቅ ያቅሙን እየተፍጨረጨረ ነው።
ኢትዮጵያ
ኢትዮጵያም የዚሁ ገፈት ተካፋይ ከሆነች አንድ ወር ከ20 ቀን በላይ አስቆጠረች። በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በተመሳሳይ ቫይረስ ተይዘው አራት ሰዎች ሕይወታቸውን ተነጥቀዋል። ምጣኔ ሀብቱ ተጎድቷል። ተፍጨርጭረው የዕለት ጉርሳቸውን ለማግኘት የሚታትሩ ዜጎችን አማራጭ የሚዘጋ አደጋ ከፊት ለፊት ተደቅኗል።
የግልና የመንግሥት ተቋማት አገልግሎት የመስጠት አቅማቸው በእጅጉ ቀንሷል። ገሚሶቹ ጭርሱኑ ሥራ አቁመዋል። በዚህ ምክንያት ከቀን ወደ ቀን የምጣኔ ሀብት መዳከምና ቀውስ ስጋት ተደቅኗል። ሁሉም ጉዳዮች ፊታቸውን ወደ ኮሮና አዙረዋል።
በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም ጠንካራ ጡጫ ካረፈባቸው ዘርፎች ቀዳሚው ይህ ዘርፍ መሆኑ የሚታበል አይደለም። በዚህ ምክንያት በርካታ ጉሮሮዎች ሊዘጉ ዳር ዳር እያሉ ይመስላሉ። የግሉም ሆነ የመንግሥት አቅሞች ከቀን ወደ ቀን እየነጠፉ ይገኛሉ። በቀጣዮቹ አረፍተ ነገሮች በኢትዮጵያ ይህ ዘርፍ ያሳረፈውን ከባድ ዱላ ጥቂት ምሳሌዎችን በማንሳት ለመመልከት እንሞክር።
ምንም እንኳን የሰው ሕይወት ቀዳሚ ጉዳይ ቢሆንም በዚህ ወረርሽኝ ምክንያት ሲኒማ ቤቶች፣ ቲያትር ቤቶች፣ የሥነ ጽሑፍ ምሽቶች፣ መዝናኛ ስፍራዎች የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ፣ ሥነ ጥበባዊና ሥነ ጽሑፋዊ ዝግጅቶች ሙሉ ለሙሉ ቆመዋል። ጥቂቶቹም ቢኖሩም ከቫይረሱ ሰዎች እራሳቸውን እንዴት መከላከል ይችላሉ በሚለው ጉዳይ ላይ በተወሰነ መልኩ ግንዛቤ ለመስጠት የሚሞክሩ ናቸው። ከዚያ ውጪ ያሉት በኮቪድ ጠንካራ ጡጫ ተነርተው ማዕበሉ እስኪያልፍ በሮቻቸውን ጥርቅም አድርገው ቀርቅረዋል።
በመዝናኛ ዘርፉ የሚዘዋወረው መዋለ ንዋይና በስሩ የሚተዳደሩ ባለሙያዎች ብዛት በግልፅ ተጠንቶ የተቀመጠ ሳይንሳዊ መረጃ ማግኘት አልቻልንም። ይህ ቢሆንም እውነታው አሁን ዓለማችን ከገጠማት ፈተና አንፃር በዚህ ዘርፍ ላይ የሚሰሩ በርካታ ሺህ ዜጎች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተጋላጭ መሆናቸው አጠራጣሪ አለመሆኑን ያምናል። ይህን ጉዳይ የሚያስረዳ መረጃም ከዚህ እንደሚከተሉት ለማቅረብ ይሞክራል። በዋናነትም አስረጂ እንዲሆኑት ሁለት የመንግሥት ቲያትር ቤቶችን ለማየት ሞክሯል።
ቲያትር ቤቶችና የወቅቱ ፈተና
በኢትዮጵያ ውስጥ ጥቂት ቲያትር ቤቶች ቢኖሩም በዚያው ልክ ግን የበርካቶችን ጉሮሮ የሚደፍኑ ናቸው።
ከዚህ ባለፈም በቀጥታ ማህበረሰቡን በመድረስ፣ ስሜቱን፣ ባህሉን፣ ማንነቱን፣ ደስታውንም ሆነ ኀዘኑን የሚገልፁ ጥበባዊ ሥራዎችን የሚያቀርቡ ናቸው። የሥራ ዕድል ከመክፈታቸው በላይ የዜጎች እራስ፤ ዓይንና ጆሮ በመሆን ያገለግላሉ።
በተለምዶ ቲያትር ቤቶች በርካታ ተመልካች የሚያስተናግዱ ናቸው። ከዚህ ባለፈም በመድረክ ላይ ሥራዎቻቸውን የሚያቀርቡ አርቲስቶችም እንዲሁ ከሌሎች ሥራዎች በተለየ መንገድ በቁጥር ከፍ ያሉ ባለሙያዎችን የሚያካትቱ ናቸው። በዚህ ምክንያት ቲያትር ቤቶች ከማዝናናት ባለፈ ማህበረሰባዊ መቀራረብና ንክኪ የሚጠይቁ ናቸው።
ከላይ በመግቢያችን ላይ በስፋት ለመዳሰስ እንደሞከርነው አሁን ዓለምን እንደ ቆዳ ወጥሮ እያስጨነቃት የሚገኘው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ይህን መሰል ማህበራዊ መቀራረብ ሰርግና ምላሹ ነው። ቲያትር ቤቶች በተለመደው መንገድ ሥራዎቻቸውን ይዘው በመድረክ ላይ ቢቀርቡ ለበሽታው መስፋፋትና ለመያዝ ቀዳሚው የተጋለጠ ቦታ የሚሆነው ይህ ስፍራ ነበር። ለዚህ ነው ኢትዮጵያ ውስጥ በሽታው መግባቱ እንደተረጋገጠ እነዚህ ቤቶች ሙሉ ለሙሉ እንዲዘጉ የተደረገው። ይህ ደግሞ በቀጥታ ተመልካቹንም ሆነ ሥራቸውን የሚያቀርቡትን የቲያትር ቤቱ ባለሙያዎች ቀላል የማይባል አሉታዊ አሻራውን አሳርፏል።
የኮሮና ተፅዕኖ በብሔራዊ ቲያትር
አቶ በፍቃዱ ከፈለኝ ይባላሉ። በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቲያትር የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ናቸው። በቲያትር ቤቱ የኮሮና ቫይረስ ከመከሰቱ አስቀድሞ በርካታ ኪነ ጥበባዊና የመዝናኛ ይዘት ያላቸው መደበኛ ሥራዎች ይቀርቡ እንደነበር ይናገራሉ። በተለይ በሳምንት ውስጥ ሰኞን ሳይጨምር ስምንት ቲያትሮች ለተመልካች ይቀርቡ እንደነበር ይናገራሉ።
ቲያትር ቤቱ በሳምንት ውስጥ የሚያቀርባቸው ቲያትሮችን ከመጋቢት ስምንት ጀምሮ ማቆሙን የሚገልፁት ዳይሬክተሩ ምክንያቱ ደግሞ ዓለም አቀፉ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መሆኑን ይገልፃሉ። ቲያትሮቹን ሰርቶ በሚያቀርብበት ወቅት በሳምንት ውስጥ በርካታ ተመልካቾች ይታደሙ እንደነበርም ያነሳሉ። በተለይ ረቡዕ ዕለት የሚቀርበው የኮሜዲ ዘውግ ያለውና በውድነህ ክፍሌ ተደርሶ በተስፋዬ ገብረ ሃና የተዘጋጀው ‹‹ባቢሎን በሳሎን›› የተሰኘው ቲያትር እስከ አንድ ሺህ የሚደርስ ተመልካች ያስተናግድ እንደነበር ያስታውሳሉ። በሌሎች ቲያትሮችም የተመልካቹ ቁጥር ከፍና ዝቅ እያለ በአማካኝ ከአንድ ሺህ እስከ 300 የሚደርሱ ተመልካቾች ይታደሙ እንደነበርም አንስተዋል።
ዳይሬክተሩ ቀደም ሲል በተረጋጋ ሁኔታ ሥራዎቻቸውን ያቀርቡ እንደነበር ገልፀው ሆኖም ወረርሽኙ ከተከሰተ በኋላ በመዝናኛ ዘርፉ ላይና በቲያትር ቤታቸው ላይ ከፍ ያለ ተፅዕኖ እንዳሳደረባቸው ይገልፃሉ። በዋናነትም በልምምድ ላይ የነበሩና ለተመልካች ይፋ ሊሆኑ የደረሱ ቲያትሮች እክል እንደገጠማቸው ይናገራሉ። በተለይ ለልምምድና ዝግጅት በርካታ ወጪ ወጥቶባቸው እንደነበርም ያነሳሉ።
በተለይ በአማራ ክልል ጥናት ተደርጎ የሚቀርብ ‹‹አዲያም ሰገድ እያሱ›› የሚል ቲያትር ተሰርቶ ዝግጅታቸውን ጨርሰው እንደነበር በማንሳት ሆኖም በዚህ ወቅታዊ ጉዳይ የተነሳ ግቡን ሳይመታ እንደቀረ ይናገራሉ። ሌሎች ቲያትሮችም በተመሳሳይ ከእይታ መራቃቸው በአርቲስቶችም ላይ ሆነ በአዘጋጆች ላይ የሥነ ልቦናና የተለያዩ ጫናዎች እንደሚኖረው ያነሳሉ። በተለይ በቲያትር ቤቱ ላይ የገቢ አቅሙን በመቀነስ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ከፍተኛ ነው። በዚህ ምክንያት ሙሉ ለሙሉ ሥራዎች እንደቆሙም አስረድተዋል።
ይሁን እንጂ ዳይሬክተሩ እንደሚሉት የቲያትር ቤቱ አርቲስቶች በግልም ሆነ በቡድን በመሆን በወቅታዊው ወረርሽኝ ዙሪያ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ላይ በመሳተፍ ላይ ናቸው። በዚህም በብሔራዊ ቤተ መንግሥት በአንድነት ፓርክ በተደረገው የሰው አልባ ኮንሰርት ላይም ሆነ የተለያዩ የኮሮና ጉዳይን የሚመለከቱ መሰናዶዎችን በማቅረብ ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል።
ይህን ወቅታዊ ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ ብዙዎች ቀደምት ሥራዎቻቸውን በተለያየ አማራጭ ለኅብረተሰቡ ለማድረስ ጥረት እያደረጉ ነው። አሁን አሁን በተለያዩ ክፍለ ዓለማት መሰል የመዝናኛ ዝግጅቶች የዲጂታል ሚዲያ አማራጩን እየተከተሉ ነው። አቶ በፍቃዱም ይህን መሰል ስልት ነድፈው እየደረሰባቸው ያለውን ተፅዕኖ ለመቀነስ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ነግረውናል። በተለይ በሶሻል ሚዲያው የዩቲዩብ፣ፌስቡክና ሌሎች የቀጥታ ስርጭቶች ላይ ተሳትፎ ለማድረግ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል። ይህ ብቻ ሳይሆን በቴሌቪዥን አማራጭ በማምጣት የአየር ሰዓት ወስደው የተመረጡ ቲያትሮቻቸውን ለማቅረብ እየሰሩ መሆኑንም አሳውቀዋል።
የአገር ፍቅር ቲያትር ቤት
አርቲስት ተሻለ ወርቁ ይባላል። ከቲያትር ባለሙያነቱ ባሻገር በአገር ፍቅር ቲያትር ቤት በጥናትና ምርምር ክፍል ይሰራል። በወቅታዊ ጉዳይ ላይ በሰጠን አስተያየትም ‹‹አገር ፍቅር›› የኮሮና ቫይረስ ከሰነዘራቸው የተፅዕኖ ዱላዎች ማምለጥ እንዳልቻለ ነግሮናል።
በአገር ፍቅር በሳምንት ውስጥ በርካታ ቲያትሮች ይታዩ እንደነበርም ይናገራል። በተለይ ‹‹የመንግሥት ሥራ፣ ገራገሩ፣ከመጋረጃ ጀርባ፣ አሉ (በአብዱልከሪም ጀማል አዘጋጅነት)›› እነዚህ ቲያትሮች ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ መፍጠሩን ይገልፃል። በዚህ ምክንያትም ቲያትር ቤቱ በአዳራሽ ውስጥ የሚያሳያቸውን ሥራዎች ሙሉ ለሙሉ ማቆሙን ተናግሯል። ችግሩ ከመከሰቱ አስቀድሞ በአዘቦት
ቀን እስከ 300 የሚደርስ በእረፍት ቀን ደግሞ እስከ 600 ተመልካቾች ቲያትሮችን ለማየት ይታደም እንደነበር ገልጿል።
አሁን ላይ ቲያትር ቤቱ ተዘግቷል። ከዚህ ቀደም በተመልካች ብዛት የሚጨናነቁ ደጆቹ የጥበብ አፍቃሪ የናፈቃቸው ይመስላሉ። እንደ ተሻለ ገለፃ ልክ እንደ ሌሎች ተመሳሳይ ቲያትር ቤቶች በአገር ፍቅር ላይም ከፍተኛ ጫና ተፈጥሯል። የገቢ ምንጩ ነጥፏል። ዝግጅት ሲደረግባቸው የነበሩ ሥራዎች ቆመዋል። በአርቲስቶች ላይ የሥነ ልቦናው ጫና በርትቷል።
ይህም ሆኖ ግን ይላል አርቲስት ተሻለ የቲያትር ቤቱ ባለሙያዎች የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ዝግጅቶች ላይ ከመሳተፍ አልቦዘኑም። አጫጭር ምስሎችን በሚያዝናና በሚያስተምር መልኩ በመስራት ለዜጎች እንዲደርሱ ጥረት እያደረጉ መሆኑን ይናገራል። በዚህም ውጤታማ ሥራዎች መስራታቸውን ነው የሚገልፀው። መደበኛ ሥራዎቻቸውን በተለያዩ አማራጮች ለመስራትም ስልቶች እየነደፉ፤ ጥናትና ምርምር እያደረጉ እንደሚገኙም ነግሮናል።
ለመጠቅለል
ዓለም ሁሌም በለውጥ ላይ ነች። ለውጥ ደግሞ ጥሩውንም መጥፎውንም በአንድ ላይ ይዞ ይመጣል። ይህን ተከትሎ በምድራችን ላይ አዲስ ነገር ተከስቷል። ለጊዜው ለውጡ ጥሩውን ሳይሆን ክፉውን አጋጣሚ ነው ይዞ የመጣው። ምድር በአስጨናቂ ወረርሽኝ ተከባለች። ከሰው ወደ ሰው ተላልፎ የሞት መቅሰፍት የሚያመጣ በሽታ ገጥሟታል።
ሥልጣኔ፣ የጦር መሣሪያ ብዛትና የገንዘብ አቅም ሊገድበው አልቻለም። አሁን ሁሉም በአንድነት ስለ አንድ ጉዳይ ብቻ የሚያስብበት ወቅት ላይ ደርሰናል። ተመራማሪውም ሆነ ተራው ዜጋ እኩል ወደየ እሚያምነው አምላክ አንጋጦ ምህረት የሚለምንበት ወቅት ነው። ከባድም ጊዜ ነው።
ከየትኛውም ወቅት በተለየ መተባበር፣ መደጋገፍ፣ መተሳሰብ በጥቅሉ አንድነትን የሚፈለግ ነው። ምንም እንኳን የመዝናኛና ጥበብ ዘርፉ በተመሳሳይ የዚህ ተፅዕኖ ዳፋ ቀማሽ ቢሆንም በበጎነትና ትብብር ለመስበክ እና አደጋውን ለመመከት ድርሻው ላቅ ያለ ነው። በመሆኑም የደረሰበትን ጠንካራ ቡጢ በመቋቋም ከችግሩ ለመውጣት የሚደረገውን ርብርብ በሙሉ ልብ መቀላቀል ይኖርበታል።
ከላይ ለማንሳት እንደሞከርነው ይህን መሰል ማህበራዊ ቀውስ በሚከሰትበት ጊዜ ከፊት መስመር መሰለፍ ያለበት የጥበብ ቤተሰቡ ነው። ቀደም ባሉ ጊዜያት በተግባር ያየነውም ይሄንኑ ነው። በመሆኑም የቲያትር ባለሙያዎች ችግራቸውን ዋጥ አድርገው፣ ትከሻቸውን አደድረው ፈተናውን መዋጋት፤ እራሳቸውንም ሆነ ማህበረሰባቸውን ከማቅ ለማውጣት በወኔ መስራት ይኖርባቸዋል የሚል መልዕክት አስተላልፈን ሃሳባችንን እንቋጫለን። ሰላም!
አዲስ ዘመን ግንቦት 2/2012
ዳግም ከበደ