ዜጎች ከቫይረሱ ጋር የተግባቡ ይመስል ድንጋጤያቸውንና መጠንቀቃቸውን ጭርሱኑ ዘንግተው የተለመደ እንቅስቃሴያቸውን ሲያደርጉ ማስተዋል ከማሳሰብ አልፎ እጅጉን ያስጨንቃል። ይህን የበዛ ቸልታችንን የታዘበ አንድ የታክሲ ሹፌር በንዴት ‹‹የግዴታ የበሽታው ገዳይነት የሚገባን ልጆቻችንን፣ አክስት አጎቶቻችንን አሊያም ጎረቤቶቻችንን ከአጠገባችን ስንነጠቅ ነው እንዴ?›› ሲል ነበር ያደመጥኩት። ጥያቄው ምፀትና ንዴት የተቀላቀለበት ጭምር ነበር።
ታክሲ ውስጥ ለመግባት የሚታየው ግፊያ ወደ ሞት የሚደረግ ጥድፊያ ይመስላል። በየገበያ ማዕከሉ የምናየው ግርግርና ጥንቃቄ የጎደለው እንቅስቃሴም የሚያስተዛዝብ ነው። መርካቶ፣ ጃን ሜዳ እና ሌሎች አማካኝ የገበያ ቦታዎች በህዝብ ብዛት ተጨንቀው በተለመደው መንገድ ሲገበያዩ ማየት ያማል። ቸልተኝነታችን የሚያሳስባቸው አንዳንድ ወገኖች እንደውም በፌዝ መልክ ‹‹ኢትዮጵያ ለዓለም ህዝብ ይፋ አላደረገችም እንጂ መድሃኒቱንማ አግኝታዋለች!›› በማለት ግርምት በተቀላቀለበት ስላቅ የውስጣቸውን ብስጭት ሲተነፍሱ ይደመጣሉ።
በዚህ ሳምንት ወደ ቢሮ ለመግባት እየተጣደፍኩ ያጋጠመኝ የአንድ ወጣት ድርጊት ደግሞ የአስተሳሰባችንን ደረጃ የሚፈታተን ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ነገሩ እንዲህ ነው። የመንግስት ትራንስፖርት አቅራቢዎች በተለይ አንበሳና ሸገር ባስ ተሳፋሪዎች ወደ ውስጥ ሲዘልቁ ሳኒታይዘር አሊያም አልኮል እንዲያደርጉ ያስገድዳል። ሁሉም ተራውን ጠብቆ ይሄን ይፈፅማል። ይህ ልጅ በሚሳፈርበት የሸገር ባስ ተራው ደርሶ ሊገባ ሲል አልኮል እንዲጠቀም ትኬት ቆራጯ እጇን ዘረጋችለት።
እርሱ ግን እንዳላየ ለማለፍ ፈለገ። ተከትላ የግዴታ አልኮሉን አድርጋለት ዞር ስትል ግን ሁለቱንም እጆቹን በሱሪው ላይ በማድረግ ፈትጎ አስለቀቃቸውና እየተበሳጨ ወደ ውስጥ ገባ። ይህ ወጣት ሃላፊነት ከሚሰማው የህግ አስከባሪ ጋር ቢገናኝ ቅጣት ይገባው
ነበር። እኔም ከርቀት ካለ ታክሲ ውስጥ ነበር ሁኔታውን ስከታተል የነበረው።
የምናየው ብቻ ሳይሆን በከተማዎቻችን የሚሰሙ ዜናዎች አስደንጋጭ አንዳንዴም ግርምትን የሚያጭሩ ናቸው። በተለይ ይህ መዘናጋት አሁን አሁን በወጣቶች ላይ እየታየ ነው። ጫት ቤቶች በድብቅ ተከፍተው 40ና 50 ሰው በአንድ ጠባብ ቦታ ታጉረው በሱስ አቅላቸውን ስተው ይውላሉ። በሽታውን የማስፋፋት አቅማቸው እጅግ ከፍተኛ የሆኑ ሺሻ ቤቶችም እንዲሁ።
የዚህ ፅሁፍ አዘጋጅ በሳሪስ አዲስ ሰፈር፣ መርካቶ፣ ግንፍሌ (ራስ አምባ ሆቴል) አካባቢ ተዘዋውሮ የቃኛቸው ድርጊቶች ጫት ቤቶች ቅርፃቸውን እየቀያየሩ የተለመደው ድርጊታቸውን መቀጠላቸውን የሚያሳይ ነው። ጉዳዩ እንዲህ ነው….አንዳንድ መኪና ለማቆም ምቹ የሆኑ ጥላ ያላቸው ስፍራዎች ለዚህ አዲስ ስልት መተግበሪያነት ውለዋል። በነዚህ ስፍራዎች በተለይ ደግሞ በተለምዶ ‹‹ላዳ›› ታክሲ እየተባሉ የሚጠሩት የትራንስፖርት መስጪያ መኪናዎች ይበዛሉ።
እነዚህ የላዳ ታክሲዎች በአንድ ቦታ ላይ ለረጅም ሰዓት ቆመው ይውላሉ። ለስራ ሲንቀሳቀሱ አይታዩም። እንዲያውም በውስጣቸው በአብዛኛውን ጊዜ 4 አንዳንዴም አምስት የሚደርሱ ወጣቶች በውስጡ ይታያሉ። በአንዱ ላዳ ታክሲ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ላይ ተመሳሳይ ትዕይንት ይታያል።
ታዲያ በማይሄዱ ታክሲዎች ውስጥ በዚህ መጠን ወጣቶች ለምን ተፋፍገው ሊቀመጡ ቻሉ? ነገሩ ወዲህ ነው። ሁሉም በእጆቻቸው ላይ ረጃጅም የጫት እንጨቶች ይዘው ጉንጫቸውን ወጥረው (ወጣቶቹ በአራዳ ቋንቋ አሊያም በሌላ ባህል ይመስለኛል ተርዚና ይሉታል) በምቾትና በድሎት ያለ ማንም ከልካይ ይቅማሉ። በራስ አምባ አካባቢ በሚገኝ አንድ ወዳጄን ስለ ጉዳዩ ስነግረው ፈገግ ብሎ አሁን አሁን ድርጊቱ ይጨምር እንጂ የተለመደ የእለት ተለት ተግባር መሆኑን አረዳኝ። ይሄን መሰል ድርጊት አሁን በጠቀስኩላችሁ ሰፈሮችና ሌሎች ቦታዎች የተለመደ ሆኗል።
ወዳጄ ‹‹የላዳ ላይ ጫት ቤቶች›› የሚል ስያሜ ሰጥቷቸዋል። እንዲያውም እኔ በግሌ ስለ ሁኔታው ማረጋገጥ ባልችልም እነዚህ ታክሲዎች ለሁለትና
ለሶስት ሰዓታት ታክሲዎቻቸውን ለቃሚዎቹ ልክ እንደ አልጋ ክፍል እንደሚያከራዩት አጫውቶኛል። ታዲያ የዚህ ድርጊት ተሳታፊዎች ላዳዎች ብቻ ሳይሆኑ እንደ ኮሮላ የመሳሰሉ መኪኖች ጭምር መሆኑን ታዝቤያለሁ። በግል መኪናቸው በቡድን መጥተው ፓርቲውን የሚቀላቀሉ እንዳሉም ለመታዘብ ችያለሁ። ስፍራዎቹ የመኪና ፓርኪንግም ይመስላሉ።
እነዚህ ብዙም ሰው የማይተላለፍባቸው ቦታዎች የተመረጡት ደግሞ ከህግ አስከባሪዎችና ለመሸሽና ከተጠያቂነት ለማምለጥ ነው። አሁን አሁን ዓለም አቀፉ ወረርሽኝ እየበዛ በመጣበት ሰዓት ደግሞ እነዚህ የላዳ ላይና የመኪና ውስጥ ጫት ቤቶች እየተስፋፉ መሆኑ ሁኔታውን አሳሳቢ ያደርገዋል። ይህ ድርጊት ቀስ በቀስ ወደ ህጋዊነት አይመጣም ማለት ይከብዳል። በተለይ በአዲስ ሰፈር ሳሪስ አካባቢ ሎተሪ አዟሪዎች፣ ሱቅ በደረቴዎች እንዲሁም ሻይና ቡና አቅራቢዎች ጭምር ተሳታፊ ሆነው ድርጊቱን ሞቅ ሞቅ እያደረጉት መሆኑን ባሳለፍነው ሳምንት ወደ ስፍራው ባቀናሁበት ጊዜ ለመታዘብ ችያለሁ።
ይህን ድርጊት ህግ አስከባሪዎች ሊያስቆሙት እንደሚገባ አምናለሁ። በመኪናዎች ላይ አራትና ከዚያ በላይ ሆነው ጫት የሚቅሙ ወጣቶች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ መደረግ ይኖርበታል። አንዱ ቀዳዳ ሲዘጋ በአንዱ መክፈት ችግሩን ይበልጥ እንደሚያባብሰው ሊታወቅ ይገባል። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተደነገጉ የመብት እገዳዎችን፣ እርምጃዎችን፣ የተሰጠ መመሪያን፣ ትዕዛዝን የጣሰ ማንኛውም ሰው እስከ 3 አመት በሚደርስ ቀላል እስራት ወይም ከ አንድ ሺህ እስከ 200 ሺህ ብር በሚደርስ የገንዘብ ቅጣት እንደሚቀጣ መደንገጉን አስታውሳለሁ። የህግ አስከባሪው ይህን ጉዳይ በቸልታ ሳያይ በጥብቅ ክትትል ሊያደርግበት ይገባል የሚል መልክት ለማስተላለፍም እወዳለሁ። በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ‹‹የላዳ ላይ ጫት ቤቶች›› መኖራቸው ታውቆ ጥብቅ ክትትል ይደረግ።
ይህ ካልሆነ በቸልታችን እራሳችንን በራሳችን የምናጠፋበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን እያሳሰብኩ ጥንቃቄ አይለየን እያልኩ ፅሁፌን ቋጨሁ። ሰላም!
አዲስ ዘመን ግንቦት 2/2012
ዳግም ከበደ