ምድራችን ለነዋሪዎቿ ከምታቀርበው ውስን አቅርቦት የተነሳ ለሀብት ሽሚያ፣ ለበላይነትና ለዘላቂነት የሚደረጉ ግጭቶችና ቅራኔዎችን ስታስተናግድ መኖሯ እሙን ነው። ባለጸጋው ክምችቱን ለማሳደግ፤ ምስኪኑም ያለችውን ላለማስነጠቅና ከባለጸጋው ተርታ ለመመደብ የሚያደርገው ጥረት በዓለማችን የተከሰቱ ግጭቶች ሥር መሰረት ነው። በምድር ላይ ያለን ቀጣይነት የማይወሰኑ ቅራኔዎች በአብዛኛው በተመሳሳይ የኑሮ ደረጃ ላይ በሚገኙ ማህበረሰቦች የበላይነትን ለማስፋትና ለማስቀጠል የሚደረጉ ናቸው። አሁን ሰልጥኗል የምንለው የዓለም ክፍል ከተቀረው ሕዝብ ጋር ሲወዳደር ቁጥር ስፍር በሌለው ጦርነት ውስጥ ያለፈ ነው። ነገር ግን ዛሬ ለግጭት ጀርባውን በመስጠት፣ ያለፈውን ላለመድገም ቃል ኪዳን ገብቶ በሰላምና ብልጽግና ተረጋግቶ ይኖራል። የሀሳብ ልዩነቶች መቼም አይቆሙምና ግጭቶችን በሰለጠነ መንገድ የሚፈቱበትንም መላ በማበጀት ሙሉ ትኩረቱን በህዋና በመጪው ዘመን ቴክኖሎጂ ላይ አድርጓል። ከስህተቶቻቸው ተምረው ችግሮችን በመለየት አቅምና እውቀታቸውን መፍትሄው ላይ በማድረግ እኛ ዛሬ ያለንበትን እነሱ ትናንት እያሉ ይጠሩታል እኛ ትናንት የነበርንበትን ዛሬም እሱን ይዘን እንቆዝማለን።
በሀገራችን ፖለቲካዊ ለውጥ ከተስተናገደበት ጊዜ ጀምሮ እንኳን ጥቂት የማይባሉ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ግጭቶች ከዚህ በፊት በታሪክ ሂደት ውስጥ ተደርገዋል በሚባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ ሲመረኮዙ ተመልክተናል። ይህም የሚያሳየው የሀገራችን ችግር የሚፈታው የወደፊቱን ብርሃን በማየት ብቻ ሳይሆን የኋላውን ጨለማ በመዝጋት እንደሆነ ነው። ከሰሜኑ ጫፍ እስከ ደቡቡ፤ ከምዕራቡ ጫፍ እስከ ምሥራቁ ሁሉም ምን ደረሰብህ ብንለው ቶሎ እንደማያባራ ዶፍ በደሉን በዓይነትና በጥልቀት ሊዘረዝር ይችል ይሆናል። ሁሉም በየራሱ በደል ላይ ያተኩር ይሆናል እንጂ ያልበደለና አፉን ሞልቶ ንጹህ ነኝ የሚል ግለሰብም ሆነ ቡድን በሀገራችን ማግኘት አስቸጋሪ ነው። ስለዚህ ሁሉንም ጥፋታችንን አሸክመን ከመካከላችን ተለይቶ ይጥፋ የምንለው የመስዋዕት ፍየል (scapegoat) የለም።
በሀገራችን ‘ውሾን ያነሳ ውሾ ነው’፤ ፈረንጆቹም ‘ክሎዠር’ እንደሚሉት ያለፈውን በደል በብሔራዊ ዕርቅ ዘግተን ሀገራችን ወደፊት እንድትራመድ የሚደረገውን ጥረት በብዙ እጥፍ ማሳደግ አለብን። የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ ወደ ሥልጣን ሲመጡ ቃል በገቡት መሠረት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 13ኛ መደበኛ ስብሰባ የዕርቀ ሰላም ኮሚሽን እንዲቋቋም የወሰነ መሆኑ ይታወቃል። ይህ ኮሚሽንም ብሔራዊ መግባባት ለማስፈን ጥሩ መፍትሄ ነው ሊባል ይችላል። ብሔራዊ ዕርቅ ፖለቲካዊ ችግር የሚያጋጥማቸው ሀገራት በሙሉ ብሔራዊ የሀገር አንድነትን ለማምጣት የሚጠቀሙት ወሳኝ የመፍትሄ ሃሳብ ነው። በርካታ በችግር ውስጥ ያለፉ ሀገራት ብሔራዊ ዕርቅን ተጠቅመው ዛሬያቸውን ከግጭትና ከአላስፈላጊ ኪሳራ ማዳን ችለዋል። የዕርቀ ሰላም ኮሚሽናችን ሥራውን ማከናወን የጀመረ ቢሆንም አሁን በዓለማችን ብሎም በሀገራችን ላይ የተደቀነውን የኮሮና ቫይረስ ስጋት እንደ አጋጣሚ በመጠቀም ለዋናው ዕርቅ የሚያዘጋጁ ተግባራትን በማከናወን ከመራራ ነገር ጣፋጭ ነገር ሊያወጣ ይችላል ብዬ አስባለሁ።
አሁን ያለንበትን ጊዜ ሁሉም ሰው ቤቱ እንዲቀመጥ እንዲረጋጋና እንዲያስተውል ዕድልን ይዞ በመምጣቱ ሁሉም በየሃይማኖቱ ወደ ፈጣሪው በንስሃና በይቅርታ ልብ እየቀረበ መሆኑን እንመለከታለን። ለዕርቀ ሰላም ደግሞ ከስሜታዊነት የራቀ፣ ወደ ውስጥ ራሱን ከሚመለከትና
ይቅርታ ለማለት ከተዘጋጀ ሰው በላይ አስፈላጊ የሚባል ነገር የለም። በመሆኑም ይህን ጊዜ ኮሚሽኑ ለዋናውና የሀገራችንን መሠረታዊ ቅሬታዎችን ይፈታል ብለን ለምንጠብቀው ዕርቀ ሰላም እንደ ጥርጊያ መንገድ ሊጠቀመው ይገባል። ዕርቀ ሰላም ኮሚሽን ወቅቱን በተለይ አንድ ትልቅ ተግባር ለማከናወን ሊጠቀመው ይገባል ብዬ አስባለሁ፤ ማስተማር።
ዕርቅ ሰላም በልብ የሚከናወን ታላቅ ድርጊት ቢሆንም በእውቀት ቢታገዝ ደግሞ ዘለቄታዊና ለታሪክ የሚቀመጥ ሌሎችም የሚማሩበት ይሆናል። በሀገራችን በሁሉም ባህል ለማለት በሚያስደፍር ሁኔታ የተጣላን የማስታረቅ፣ የተለያየን የማገናኘትና ሰላም የመፍጠር የቆየ ልምድ አለን። ይሄ ጠቃሚ ባህላችን ላይ ተመስርተን በዘመናችን ከተከናወኑ ሀገራዊ ዕርቆች ትምህርት በመቅሰም ለሕዝባችን ትምህርት ልንሰጠው ይገባል። ዕርቅ ምንድነው? ዕርቅ ለምን ይፈጸማል፣ ዕርቅ እንዴት ይፈጸማል፣ ዕርቅ የሚያስፈጽሙ አካላት እነ ማናቸው እንዲሁም ዕርቅ ከተጠያቂነት እውነት ከፍትህ እንዴት ይጣጣማሉ በሚለው ዙሪያ ትምህርት መሰጠት አለበት። ለዚህም ደግሞ በሀገራችን ከትምህርት ተቋማት፣ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች፣ ከሃይማኖት ተቋማት እንዲሁም ከማህበረሰብ አንቂዎች ብዙ የበቁ አስተማሪዎች አሉን።
በነጮቹ ዘንድ ‘from the mouth of the horse” እንደሚባለው ሀገራችን በውጭ ሀገራት ያሏትን ሚሲዮኖች በመጠቀም የተሳካ ዕርቀ ሰላም ካካሄዱ ሀገራትም ዋና አስተባባሪ የነበሩትን ወደ ዚህ በመምጣት ልምዳቸውን እንዲያጋሩ ማድረግ ይቻላል። ለማስተማር ደግሞ በሁሉም የመንግሥት ሚዲያዎችና ተባባሪ በሚሆኑ የግል መገናኛ ብዙኃን እንዲሁም በኢንተርኔትና ማህበራዊ ሚዲያ በተመሳሳይ ሰዓት እንዲተላለፍ ማድረግ ይቻላል። ከዚህ በተጨማሪ በየክልሉ በተቋቋሙ ሚዲያዎችና የማህበረሰብ ቻናሎች በመጠቀም በየቋንቋው ማስተማር ተደራሽነቱን ሰፊ ያደርገዋል። ከዚህ በተጨማሪ በመቶ ሺዎችን የሚያስከትሉ የማህበረሰብ አንቂዎችን መጠቀም ዕውቀቱን ለማጋራት ለተደራሽነቱ ትልቅ ሚናን ይጫወታል።
በትምህርትና በዕውቀት የታረሰው ልብ ላይ እውነተኛ ዕርቅ ሰላምን መዝራት ይችላል። ጉዳዩ በትልቅ ትኩረት ተሰርቶ ስለ ዕርቅ ሰላም አስፈላጊነት የሚበዛው ሕዝባችን ከተረዳው ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር ቁልፍ ሚና ይኖረዋል። መቼም ኢትዮጵያ ሀገሬ ናት የጋራ እጣ ፈንታ አለኝ የሚል ሁሉ በቂምና በጥላቻ፣ በጸብና በመቆራቆስ እንዲሁም እየተካሰሰ ሊኖር አይገባውም። ከጥፋት ከሚያተርፉት በቀር ሕዝባችን ይሄ ነገር አንድ ቦታ ቆሞለት ከወንድሙና እህቱ ጋር ሳይሆን ከእውነተኛ ጠላቱ ድህነት ጋር ተፋልሞ ሕይወቱን ማሻሻል ይፈልጋል። እኔም የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤን በመራሁበት ወቅት ጠጋ ብዬ የአብዛኛውን ባለድርሻ አካላት የልብ ትርታ ለማዳመጥ በሞከርኩበት ወቅት ዕርቅን የማይፈልግ ግለሰብም ሆነ ቡድን አላጋጠመኝም። ነገር ግን ከየት መጀመር እንዳለበት፣ እንዴት መጀመር እንዳለበትና ምን መጠበቅ እንዳለበት ሕዝባችንን ማስተማር ይኖርብናል።
በደፈናው የሚደረግ እርቀ ሰላም ባለመኖሩ በሀገራችን የተከሰቱ የመብት ጥሰቶችን ከታሪካዊ፣
ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ከኢኮኖሚያዊ አውድ አንፃር ቦታ ቦታ ለመስጠት ለነዚህ ሁሉ የመብት ጥሰቶች ዋና መንስዔ የነበሩ ምክንያቶች ለይቶ ለማስቀመጥ በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ዕርቅ አስፈላጊ ነው። ችግሮችን በየዘርፉ መለየት ቁጥር ስፍር የሌላቸውን በደሎቻችን እየዘረዘርን ከምንደክም ሙሉ አቅማችንን በመፍትሄው ላይ እንድናውለው ይረዳናል። ያለዕውቀት ዓይን ተጨፍኖ ዝም ብለህ ይቅር ተባባል ማለትም በተቃራኒው ደግሞ የማያቋርጥና ቅርቃር የሚፈጥር የበደል ሙሾ በመስማት ልንቆጣጠረው የማንችለውን ኃይል ማንቀሳቀስም የለብንም። እውነተኛ ዕርቅ ሁለቱን በሚዛን አስቀምጦ የሚሄድ በመሆኑ ነው ስለ ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊና ሳይንሳዊ የዕርቅ ዓይነቶች በቂ ትምህርት ሊሰጥ የሚገባው።
በዚህ ወቅት የሚሰጠው ትምህርት አስፈላጊ የሚሆነው ሰዉ ዝግ ያለበት፣ ዘላለም በምድር የማይኖር መሆኑን፣ ጥቂት በዓይን የማትታይ ቫይረስ ልታስቆመው እንደምትችል እንዲሁም ያለቺው ጥቂት ጊዜ አንኳን በጎሳ፣ በዘር በሃይማኖት በጾታ ተለያይቶ ሊገዳደል ይቅርና በፍቅር ለመኖር የማትበቃው መሆኑን የተረዳበት በመሆኑ ነው። ስለዚህ ከሐሰትና ወደ ሌሎች ከማላከክ ይልቅ እውነተኛ የሆነውን ስሜቱን ስለሚገልጽ አጋጣሚው ወርቅ ነው። እንዲሁም እኛና እነሱ የሚል አጥር ቀርቶ ሁሉም የጋራ መንፈስ የማሳየት አዝማሚያ በማሳየቱ በሙሉ አቅም ልንሰራ ይገባል።
በአጠቃላይ ለዛሬም ሆነ ለወደፊት ለምናልመው የጋራ ስንቃችን ብሔራዊ መግባባትና ዕርቅ ማድረግ ሊዘገይ የማይገባው ወሳኝ ጉዳይ ነው። ከባለፈው ታሪክ በተረፉ ግጭቶች ስለትናንት ተጠያቂ ያልሆነ፤ የራሱ ህልምና ኑሮ ያለው የዛሬው ትውልድ ጉዳት ሊደርስበት አይገባም። ፈጣሪ የሰጠንን የጋራ ስንቅ በከንቱ አምባጓሮ ደፍተነው ሁላችንም ከሳሪዎች እንዳንሆን በተማመንባቸው ነገሮች ላይ ተግባብተን ባልተስማማንባቸው ጉዳዮች ላይ ተከባብረን ነገን እናትርፍ። ፖለቲከኞቻችንም ቢሆኑ ከእኛ የተፈጠሩ ስለሆኑ እኛን አስተባብረው የጋራ ሀገር እንዲገነቡ እንጂ እርስ በእርስ እንዲያጫርሱን ልንፈቅድላችው አይገባም እላለሁ!
አዲስ ዘመን ግንቦት 1/2012
መጋቢ ዘሪሁን ደጉ