በተለወጠ ልብ የተለወጠ ሀገር እንፍጠር

አዲስ ዓመትን በአዲስ ልብ ካልተቀበልነው አሮጌ ነው። አዲስ ዓመት አዲስ የሚሆነው እኛ በአስተሳሰብ ስንልቅና አዲስ ስንሆን ብቻ ነው። የሰው ልጅ ታሪክ አለው..ታሪክ ደግሞ በጊዜና በዘመን ውስጥ ያልፋል። የእያንዳንዳችን ታሪክ ከውልደት የሚጀምር በሞት የሚጠናቀቅ የዘመን ሀቅ ነው። ይህ ተፈጥሮአዊ እውነት ደግሞ የሰውን ልጅ ማረፊያ አድርጎ በተቀመጠለት የስርዐት አውድ ውስጥ እየመጣ የሚሄድ ነው።

ጊዜ ሀጂውን እየሸኘ..መጪውን እየተቀበለ በማይዛነፍ ፍጹም እውነት ውስጥ ይጓዛል..የሰውን ልጅ ጉዳይ አድርጎ። ጊዜ ጌታ ነው..ጊዜ ፈራጅ ነው። ጊዜ መጽናናት መሻርም ሁሉንም ነገር ነው። በተፈጥሮ እውነት የጸና..በሚዛናዊነት ምህዋር ውስጥ ሳይንገዳገድ የቆመ መለኮታዊ ጽኑ ቃል እንዲህም ነው። የጊዜ ጌትነት ግን በራሱ የሚሆን ሳይሆን በሰው ልጅ የማሰብ አቅም የሚወሰን የአእምሮ ነጸብራቅ ነው። የእያንዳንዳችን ትላንት የእያንዳንዳችን ዛሬና ነገ፣ የእያንዳንዳችን ድሮና ዘንድሮ፣ አምናና ካቻምና በዚህ በጊዜና በሰው ልጅ የጋርዮሽ መስተጋብር የተቃኘ ነው።

የሰው ልጅ በጊዜ ውስጥ ባለታሪክ ነው። ጊዜ በሰው ልጅ ውስጥ ጉልበታም ነው። የጊዜና የሰው ልጅ ቁርኝት ታሪክን እየደገመ፣ ተፈጥሮን እያጣቀሰ የሚያዘግም ነው። ጊዜ የታሪክ መፈጠሪያ፣ የህልምና ምኞት ካዝና ነው። የምንፈልጋቸው ነገሮች በጊዜ ውስጥ አልፈው የእኛ የሚሆኑ ናቸው። ካለጊዜ ሰው፣ ካለሰው ጊዜ ምንም ናቸው። ጊዜና የሰው ልጅ እጅና ጓንት፣ መዳፍና አይበሉባ፣ መረብና አሳ ናቸው። ሁለት አካል አንድ ገጸ ሰብ፣ ሁለት ገላ አንድ አይነት መልክ። በተፈጥሮ እውቀትና ጥበብ ተሰናስለው የተዳሩ የዳበሩም ናቸው።

ለዚህም ነው አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር አዲስ አስተሳሰብና አዲስ ነፍስና ስጋ ፍለጋ የምንዋትተው። ለዚህ እኮ ነው አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር ከአምናው የተለየን ለመሆን በአዲስ እቅድና በአዲስ ምኞት የምንሳበው። ለዚህ እኮ ነው እድሜአችን የሚያሳስበን፣ ሞታችን የሚያስጨንቀን። ትልቁ የዘመን መለወጥ ፋይዳው በአስተሳሰቡ ለተቀየረና ተሀድሶን መሰረት ላደረገ አእምሮ ነው። ለለውጥ ካልተጠቀምንበት ጊዜ መጥቶ ከመሄድ ባለፈ ትርጉም የለውም። ትርጉም ያለው ሆኖ እንዲያልፍ የምናደርገው እኛ ነን።

አዲስ ዓመት እንደ ትርጉሙ አዲስ ነው። በውስጡ አንዳች ኃይልና ብርታት አለው። ለሰው ልጅ ሁሉ የሚሆን የመታደስ፣ የመበርታት መንፈስን በውስጡ ይዟል። ብዙዎቻችን ይሄን ኃይል እንፈልገዋለን። በዚህ ኃይል ውስጥ መኖር እንፈልጋለን። ለዚህም ዓመት ጠብቀን የምናቅድ፣ ዓመት ጠብቀን የምንጀምር፣ ዓመት ሲመጣ የምንበረታ ባጠቃላይ ለምንም ነገር አዲስ ዓመት የምንል ብዙዎች ነን።

ብዙዎቻችን ጋ የአዲስነት ስሜት የሚያድርብን አዲስ ዓመት ሲመጣና ሲቃረብ ነው። የመስራት የመለወጥ ፍላጎታችን የሚነሳሳው መስከረም ሊጠባ ጥቂት ሲቀረው ነው። ሕልሞቻችን የሚታወሱን የአበቦቹን ሽታ ተከትለን ነው። ከአሮጌነት የምንወጣው፣ ከድሮነት የምንሸሸው ጳጉሜን ተሻግረን አበባየ ሆይ ሲባል የሚመስለን እልፍ ነን። ሕይወታችን፣ መኖራችን ትርጉም ያሚያገኝ የሚመስለን በዚህ ጊዜ ነው። ለአዲስ ሕይወት የምንዘጋጀው ይሄን አዲስ ዘመን ታከን ነው። ሁሉ ነገራችንን ለአዲስ ዓመት አሳልፈን የሰጠን ነን።

ይሄ ስህተት ነው የሰው ልጅ የጊዜ ባሪያ መሆን የለበትም። ዛሬን ለለውጥና ለስኬት መጠቀም ይኖርበታል። የምንፈልገውን ማንኛውንም ነገር ከዛሬ በመጀመር፣ ከአሁን በማቀድ ማሳካት እንችላለን። ብዙዎቻችን ዛሬን አናውቀውም። የአሁኑን ኃይል አልተረዳነውም። የቆምንባት ቅጽበት የኃይል የለውጥ መጀመሪያ እንደሆነች ገና አልደረስንበትም። አዲስ ዓመት የምንም ነገር መጀመሪያ እንደሆነ አምነን የተቀበልን ነን። በአዲስ ዓመት ሰሞን ከሞት የምንነቃ፣ ካንቀላፋንበት የምንባንን ብዙ ነን።

በዚህ አስተሳሰብ ውስጥ ለውጥ የለም። በዚህ እምነት ውስጥ ስኬት የለም። ስኬት መነሻውም መድረሻውም አዲስ ዓመት ሳይሆን አዲስ አስተሳሰብ ነው። አዲስ አስተሳሰብ ደግሞ ዛሬን ከመጠቀም አሁን ከመኖር የሚጀምር ነው። አዲስ ዓመት ሲያልፍ ምኞታችን አብሮ የሚያልፍ ከሆነ፣ አዲስ ዓመት ሲመጣ ምኞታችን ከሞተበት የሚነቃ ከሆነ የአዲስ ዓመትን ትርጉም አልተረዳነውም ማለት ነው። ጊዜና ለውጥን አስታከው የተጻፉ ብዙ የስኬት መጽሀፎች አሉ። አንዳቸውም ለውጥ ከአዲስ ዘመን እንደሚጀምር አልጻፉም። የሁሉም የጋራ ሀሳብ ለውጥ ያለው ከዛሬና ከአሁን የሚል ነው።

ጥያቄ አንድ..አዲስ ዓመት ማለት ምን ማለት ነው? በአስተሳሰቡ ላልተቀየረ ማኅበረሰብ አዲስ ዓመት ምኑ ነው? ከመጠበቅና ተስፋ ከማድረግ ላልወጣ ሰውነት አዲስ ዓመት ዋጋው ስንት ነው? ፍቅርን ለማያውቅ ይቅርታን ላልተማረ ልብ ጊዜ ዘመን ምኑ ነው? ለማይሰሩ እጆች፣ ለማያስቡ ጭንቅላቶች መጠበቅ ፋይዳው ምንድ ነው? በብሄር፣ በጎሳ ለሚባላ ሀገርና ሕዝብ የዘመን መቀየር ፋይዳው ምንድነው? ከወንድሞቹ ጋር ሆድና ጀርባ ሆኖ ለሚኖር፣ ተነጋግሮ መግባባት፣ ተወያይቶ መስማማት ላቃተው ፖለቲካና ፖለቲከኛ፣ ትውልድና ዜጋ መሻገር ምንድነው? እኚህ ጥያቄዎች አሁን ላለነው እኛ መሰረታዊ ናቸው። የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ስናውቅና ስንረዳ ብቻ ነው የአዲስ ዓመትን ዋጋ ልንረዳው የምንችለው።

ያለፈውን ዓመት እንዲህ እንደ አሁኑ ለመነቃቃት ተጠቅመነው ነበር። አምናን እኮ በእልልታና በፌሽታ ተቀብለነው ነበር። ካቻምናን እኮ የደስታና የሰላም ዘመን ብለነው ነበር። ያለፈውን ዓመት ብዙ ልንሰራበት ብዙ ልናተርፍበት አውርተን ነበር። 2016 እኮ እንደ ሀገር፣ እንደግለሰብ ብዙ ያቀድንበት ብዙ ያሰብንበት ዘመን ነበር ግን እንደሀሳባችን አልተጠቀምንበትም። እንደምኞታችን አላዋልነውም። ምክንያቱም ከዘመን ጋር የተቀየረ አእምሮ ስለሌለን።

በተቃራኒው መጥፎና እድለ ቢስ እንደነበር አወራን። ምንም ያላተረፍኩበት ዓመት ነው ስንል ነቀፍነው። አያችሁ የዘመንን እውነት? ዘመን የሚዘወረው በሰው ልጅ አስተሳሰብ ነው። ያለፉት ዓመታቶች ጥሩ ያልነበሩት ዘመኑ ጥሩ ስላልነበር ሳይሆን እኛ ጥሩ ስላልነበርን ነው። እኛ ስላልተቀየርን ዘመኑም አልተቀየረም። የሰው ልጅ ልቡና አእምሮው፣ ሀሳቡና ምኞቱ ካልተቀየረ አዲስ ዓመት ምንም ነው። ሀሳባችንን ሳናድስ፣ ከድሮነት ሳንወጣ ሰኔና ሐምሌ ገመገም ላይ ቆመን 2016 ለኔ ጥሩ ጊዜ አልነበረም፣ ለሀገራችን መልካም አልነበረም ብንል ልክ አይደለንም።

ዘመን ለሰው ልጅ ሎሌ እንጂ ሰው ለዘመን ሎሌ አይደለም። ሁሉን ነገር ለአዲስ ዓመት ትተን መቀመጣችን የዘመን ጥገኞች መሆናችንን ከማሳየቱ ባለፈ እያንዳንዱን ቀን ዋጋ ለመስጠት የምናደርገው የበረታ እንቅስቃሴ እንደሌለም የሚያሳይ ነው። ዘመን በእኛ ስር ነው። አዲስ ዓመት አዲስ የሚሆነው በእኛ አዲስ ልብ ነው። ልቦቻችንን አሳድፈን፣ መንፈሳችንን አስነውረን፣ ፍቅርና ይቅርታን ሳንማር፣ በመነጋገር ሳንግባባ፣ በእርቅ አንድ ሳንሆን ብንቀበለው ያው ነው እንደ ድሮው..እኛም ከእርግማን አንወጣም።

ተስፋ ያደረግንው አዲሱ ዓመት ያሰብነውን እንደሚሰጠን ዋስትናችን ምንድ ነው? የሚመጣው አዲስ ዓመት የምንመኘውን እርቅ፣ የምንፈልገውን አንድነት፣ የራቀንን ሰላም እንደሚሰጠን መተማመኛችን ምንድ ነው? ምንም መተማመኛ የለንም። ልንተማመንበት የሚገባ አንድ ነገር ቢኖር ራሳችን ነን። ራሳችንን ለፍቅር፣ ለይቅርታ፣ ለመነጋገር ዝግጁ ካደረግን እንዳሰብነው አዲስ ዓመት አዲስ ይሆናል። ይሄ ባልሆነበት ሁኔታ አዲስ ዓመትን አዲስ ይሆናል ብሎ መጠበቅ ሞኝነት ነው የሚሆነው።

ታሪኮቻችን ውብ የሚሆኑት በእኛ ነው። ጊዜ እኛ ተኝተን የሚያነቃ ኃይል የለውም። ለምንፈልገው ሰላም፣ ለምንፈልገው አንድነት፣ ለምንፈልገው እድገት ዘመን አስተዋጽኦ የለውም። ለዚህ ምስክር የሚሆኑን ያለፉ በአዲስ ምኞት ተቀብለናቸው አዲስነትን ያልሰጡን ዘመኖች ናቸው። ተስፋዎቻችን ሀሳቦቻችን በኩል የሚያብቡ እንጂ በመስከረም ጥባት በኩል የሚታዩ አይደሉም። እንደዚህ አይነት መለማመዶች ለማንም አይጠቅሙም። ዘመን ያው እንደትላንቱ ነው። የተፈጥሮን እውነት ጠብቆ መጥቶ የሚሄድ ነው። አትምጣ ብንለውም፣ ና ብንለውም በእኛ ፍቃድ ስር አይደለም። መጥቶ መሄድ ተፈጥሮአዊ ግብሩ ነው።

ከዚህ እውነት በመነሳት አዲስ ዓመት ሲመጣም ሆነ ሲሄድ የተለየ ተፈጥሮ እንደሌለው መተማመን ላይ መድረስ እንችለለን። አዲስም ሆነ አሮጌ የሚሆነው በሰዎች ተጽዕኖ ነው። ቀን ሳንጠብቅ፣ ጊዜ ሳናሰላ፣ አዲስ ዓመት ሳንል የምንፈልገውን ማንኛውንም ነገር አሁን ላይ መፍጠር እንችላለን። ሰላም ከሆነ የምንሻው፣ አንድነት ከሆነ ፍላጎቶቻችን ሰላምና አንድነት በሚያመጡ ሀሳቦች ላይ በማተኮር የምንፈልገውን ማግኘት እንችላለን።

ባልተለወጠ እምነት የተለወጠች ሀገር አትኖርም። ለውጥ ሁልጊዜም መነሻው አእምሮ ነው። በአእምሯችን ስንለወጥ ብቻ ነው ባለውም በሚመጣውም ዘመን ላይ ጀግና የምንሆነው። ከጊዜ ባርነት መውጣት ይኖርብናል። ለምንም ነገር ነገን መጠበቃችን፣ ለምንም ነገር አዲስ ዓመትን መሻታችን ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ነው የሚያመዝነው።

ሰላም ሊሰጡን የሚችሉ፣ ሕልምና ራዕዮቻችንን ልናሳካባቸው የሚችሉ ብዙ ቀናት፣ ብዙ ጊዜዎች አብረውን አሉ። ራሳችንን ማንቃት ከቻልን ወደትላንት ሳንሄድ፣ ወደነገም ሳናዘግም መለወጥ እንችላለን። ችግሩ ከአዲስ ዓመት አስተሳሰብ አልወጣንም። ችግሩ ከዛሬ ይልቅ ነገን ተስፋ የምናደርግ መሆናችን ነው። ከቻልን ጊዜ የእኛ ባሪያ እንዲሆን እንቆጣጠረው። ከቻልን እያንዳንዱን ቀናችንን የምንም ነገር አዲስ ዓመታችን አድርገን እንቀበለው።

በጊዜ ባርነት ውስጥ ልዕልና የለም። በመጠበቅ ውስጥ ንግስናና ክብር ምንም ናቸው። ሰው ከትጋት ሲጎድል፣ ከጥረት ሲላላ ለምንም ነገር ጊዜን መጠበቅ ይጀምራል። ጊዜን የመጠበቃችን ምክንያት ስንፍናና አጉል የኑሮ ዘይቤ መልመዳችን ነው። በእውቀትና በእቅድ መኖር ብንጀምር እያንዳንዷ ቀን አዲስ ዓመታችን ትሆን ነበር ወይም ደግሞ ከአዲስ ዓመት በበለጠ ምን ያክል ለለውጥና ለስኬት አስፈላጊ እንደሆነች እንረዳ ነበር። በትጋት ስንሞላ ለምንም ነገር ጊዜ እኛን መጠበቅ ይጀምራል። በትጋት ስንሞላ ምንም ነገር ከአሁን እንጀምራለን። ጊዜን መጠበቅና በጊዜ መጠበቅ ሁለት የተለያዩ እውነቶች ናቸው። ልክ ለምንም ነገር አዲስ ዓመትን እንደሚጠብቁት እና ለምንም ነገር ዛሬ የተሻለ ቀን ነው ብለው እንደሚያምኑት ሁለት ጉራማይሌ ነፍሶች አይነት።

ትጉ ነፍሶች የሚፈልጉትን ዘመን ዛሬ ላይ ይፈጥሩታል። ታካች ነፍሶች ደግሞ በመንቀፍ፣ በመሰልቸት፣ በስንፍና፣ በአይሆንልኝም፣ በማመንታት፣ በመወላወል፣ ቆይ ነገ በሚል እሳቤ በመጠበቅ ውስጥ ይቆማሉ። ብዙ ዛሬዎችን፣ ብዙ አሁኖችን፣ ብዙ ነገዎችን ዘለን አዲስ ዓመትን መጠበቃችን ስንፍናና ስልቹነት ምን ያክል ስር እንደሰደደብን አመላካች ነው። ብልህ ሰው በብሩህ ሀሳቡ በኩል ዛሬን አዲስ ዓመት ማድረግ ይችላል። ጠንካራ ሰው ወደ ነገ ሳይሄድ፣ ወደ አምና ሳይሳብ አሁንን ለለውጥና ለስኬት መጠቀም ይቻለዋል።

ለተጋ ልብ፣ ለበረታ አእምሮ ሁሌም ስኬት፣ ሁሌም አዲስ ዓመት አለ። ከፍ ብዬ እንደገለጽኩት አዲስ ዓመት ለእኛ ብሎ የሚያደርገው ምንም ነገር የለም። መጥቶ እንዲሄድ የተፈጥሮ ግዳጁን እየተወጣ ነው። እኛ ነን ከተፈጥሮ የራቅነው። እኛ ነን ማስተዋል የጎደለን..በጊዜ ሀቅ ውስጥ ቆመን እንኳን መማር አልቻልንም። ለመማር ዝግጁ ብንሆን ጊዜ የሚያስተምረን ብዙ ነበረው።

አምናን በጉጉት ጠብቀነው የምንፈልገውን ሰላምና አንድነት ካልሰጠን፣ 2015 ለነበሩብን ችግሮች መፍትሄ አድርገንው ቃሉን ከበላ ችግሩ ከጊዜው ሳይሆን ከእኛ እንደሆነ ልንረዳ ይገባል። አዲሱን 2017 በአምና ልብ ሳይሆን በታደሰና በተቀየረ ልብ ልንቀበለው ይገባል። ያኔ ያለጥርጥር የምንፈልገውን እናገኛለን..እንደምኞታችንም ዘመኑ አዲስ መሆን ይጀምራል።

የሚሰማ ጆሮ የሚያስተውል ልብ ቢኖረን ኖሮ የጊዜን ሹክሹክታ እናደምጠው ነበር። ጊዜ ህላዊ ኖሮት መናገር ቢችል ኖሮ ‹..እባካችሁ አትጠብቁኝ እኔ ለሰው ልጅ የሚሆን ምንም የለኝም፣ ለበረቱ እየመጣሁ የምሄድ፣ ለጠንካሮች ሚዛኔን የደፋሁ ነኝ› የሚለን ይመስለኛል። በዚህ አያበቃም ‹ከኔ ይልቅ ዛሬና ነገ የላቀ ዋጋ አላቸው።

አስራ ሁለት ወራትን አልፋችሁ፣ ሀምሳ ሁለት ሳምንታትን ትታችሁ፣ ሶስት መቶ ስልሳ አምስት ቀናትን ሽራችሁ የምትጠብቁኝ ምናችሁ ሞኝ ነው? ሲል የሚያላግጥብን ይመስለኛል። መች በዚህ ያበቃና ‹ልቦቻችሁን ሳታድሱ፣ አመለካከታችሁን ሳትቀይሩ ጥሩ ነው መጥፎ ነው እያላችሁ አትሙኝ። እኔ ጥሩና መጥፎ የመሆን ስልጣን የለኝም። መጥቼ እንድሄድ የታዘዝኩ የተፈጥሮ መንገደኛ ነኝ እናም አትጠብቁኝ በአሁናችሁ ላይ በርትታችሁና ተልቃችሁ ቁሙ› ይለን ነበር።

ምኞታችን መልካም ጊዜ ከሆነ እጆቻችንን በስራ፣ ልቦቻችሁን በትጋት እንጥመድ። ምኞታችን ሰላም፣ ፍቅር፣ አንድነት፣ ወንድማማችነት ከሆነ ደግሞ ለነዚህ የሚሆን የተግባቦት ሰውነትን መፍጠር ይኖርብናል። ካልሰራንበት፣ ካልበረታንበት አዲሱ ዓመትም እንደ አምናና ካቻምና ርባና ቢስ ሆኖ ነው የሚያልፈው። አዲስ ዓመት የዛሬ አብራክ ነው። ብዙ ዛሬዎች ተቆጥረው ነው የምንቦርቅበትን አዲስ ዓመት የሰጡን። ለምንድነው ዛሬአችንን አዲስ ዓመት አድርገን የማንቀበለው? ለምንድነው አዲስ ዓመት ሲመጣ የምናገኘውን ኃይልና ብርታት በቆምንባት ዛሬ ላይ የማንፈጥረው?

አንሳት ..አዲስ ዓመት የቀናት ጥርቅም ነው። አዲስ ዓመት የሳምንታት የወራት ሂደት ነው። ለመለወጥ ካልተጋን የሚሰጠን አንዳች ነገር የለውም። እኛ እስካልተለወጥን ድረስ የአዲስ ዓመት መምጣት ምንም ነው..ቤስቲ ቤስታ የለውም። ጊዜ በተለይም አዲስ ዘመን በእያንዳንዳችን ሕይወት ላይ ዋጋ የሚኖረው የአሁኑን ወይም ደግሞ የዛሬን ዋጋ ስናውቅ ብቻ ነው። አምና አዲስ ያልነው ዘንድሮ አሮጌ ብለን ሸኝተነዋል። ምንም አላተረፍንበትም። ስለዚህ ከዘመን ቁራኛነት ወጥተን ዛሬን አዲስ ዓመት እናድርግ። በተለወጠ ልብ በተለወጠ ሀሳብ የተለወጠ ሀገርና ሕዝብ እንፍጠር።

ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መስከረም 4 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You