በኮሪደር ልማት የደመቀው አዲስ ዓመት

የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት ከሌሎች ዓውድ ዓመቶች የተለየ ነው፡፡ እንደ ስሙ አዲስ ነገር የሚፈልግና በዚሁ መንፈስ የምንቀበለው ነው፡፡ ከአዲስ ልብስ ከአዲስ ጫማ ባሻገር መንፈሳችንና ልባችንም በአዲስ የሚታደስበት ነው፡፡ ዓይናችን በየዓመቱ አዲስ ነገርን ማየት ይሻል፡፡ ውጫዊ አካላችን ብቻ ሳይሆን ውስጣዊ አስተሳሰባችን፤ ስብዕናችን፤ አካባቢያችን አዲስ እንዲሆን ይፈልጋል፡፡

ዘንድሮ መዲናችን አዲስ አበባ ይህን ዓይነቱን የነዋሪዋን ፍላጎት የማሟላት ጉዳይ ሰምሮላታል፡፡ አዲስ አበባ መሪዎቿ በዕቅድ ዘመናቸው ሲሉት እንደነበሩት በአዲስ እየፈካች ትገኛለች፤ በእርግጥም አዲስ አድርገዋታል፤ እያደረጓትም ይገኛሉ፡፡ ስሟን የሚመጥን የተለያዩ የልማት ሥራዎችን እያከናወኑ መገኘታቸው ምስክር ይሆናቸዋል፡፡ ከ28 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት ያለው የመንገድ ኮሪደር ልማት በዘንድሮ አዲስ ዓመት አዲስ አበባን አዲስ ካደረጓት በዋናነት ይጠቀሳል፡፡

ይህ የመንገድ ኮሪደር ልማት መዲናዋን በቃላት ከሚነገረው በላይ አስጊጧታል፡፡ በከተማዋ አራት አቅጣጫ ሌት ከቀን እየተከናወነ ያለና አብዛኛው ክንውኑ የተጠናቀቀም በመሆኑ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል፡፡ ዘና ፈታ እያለበትም ይገኛል፡፡ የመንገድ ኮሪደር ልማቱ በውስጡ ሌሎች የልማት ፕሮጀክቶች መያዙ ነዋሪዋ ዘና ለማለቱ ምቹ መደላድል ፈጥሮለታል፡፡

አብዛኛው ነዋሪ ከዋናው መንገድ ግራና ቀኝ በተገነባው ምቹ ስፍራ አረፍ ለማለት በቅቷል፡፡ ዘንድሮ በመዲናችን አብዛኞቹ አካባቢዎች አረፍ በማለት የአረንጓዴ ልማት ሽፋኗን 17 በመቶ ካደረሱት ተክሎች የሚመነጨውን ንፁህ አየር መማግ ተችሏል፡፡ ሥፍራዎቹ መንገደኛ ሲደክም ብቻ ሳይሆን አዛውንቶችም አረፍ የሚሉባቸው ሆነዋል፡፡ ለጥናትና ምርምርም ሆነ ለተለያዩ ተግባር የገቡ፤ እየኖሩ ያሉ የውጭ ሀገር ዜጎችም ጭምር አረፍ የሚሉባትና ቅኝትና አድናቆት የሚቸሯት ተመራጭ ሆናለች፡፡ ጥንድ፣ጥንድ ለሆኑ ወጣቶች የፍቅር ወሬ ያስኮመኩማሉ፡፡

በእነዚህ ስፍራዎች ያለው የእንጨት ወንበር ከቀድሞዎቹ ድንጋይ ወንበሮች ይልቅ ምቾት በመስጠት ያስቀምጣል፡፡ ቀድሞ ከአንዳንድ የመነፈሻ ቦታዎች በስተቀር በሁሉም መንገዶች ግራና ቀኝ ድንጋይ ወንበሮቹ ነበሩ እያልኩ አይደለም፡፡ ሲጀመር መንገዶቹ ለእግር መንገድም የማይበቁ በመሆኑ እግረኛው ከመኪና ጋር እየተጋፋና ለአደጋ እየተዳረገ የሚሄድባቸው መሆናቸውንም አልዘነጋሁም፡፡

በኮሪደር ልማቱ እንዲህ ዓይነቶቹ መንገዶች ተወግደዋል፡፡ ምቹና እግረኛው በሰው ብዛት ሳይጨናነቅና ሳይጋፋ እንደልቡ እየተራመደባቸው ባሉ ሰፊ የእግረኛ መንገዶች ተተክተዋል፡፡ በእነዚሁ ሥፍራዎች አቅራቢያ በተገነባው የሞተር አልባ ትራንስፖርት መንገድ አዋቂዎች ያለ እንከን ሳይክላቸውን ይጓዛሉ፡፡ ወላጆች ትምህርት ቤት በመዘጋቱ እረፍት ላይ ያሉ ልጆቻቸውን እሁድና ቅዳሜ ብቻ ሳይሆን ሰርክ ሣይክል ያለማምዳሉ፡፡

ከመንገድ ኮሪደር ልማቱ ፕሮጀክት ጋር ተያይዞ ዘንድሮ የእግር መሸጋገሪያ ድልድዮችም እየተገነቡ ነው፡ ፡ ራስ መኮንን ድልድይን ይዞ በተለያዩ ስፍራዎች የሚገኙ የወንዝ ተፋሰስም አካቷል ልማቱ፡፡ እነዚህ አስፈላጊ በሆኑ ቦታዎች በከተማችን የሚገነቡ የእግር መሸጋገሪያ ድልድዮችና ተፋሰሶች እንደቀድሞው ለኅብረተሰቡ ስጋት የሚሆኑ አይደሉም፡፡ በተለይ የእግር መሸጋገሪያ ድልድዮቹ እንደ ቀድሞው ውበት የሌላቸው ከመሆናቸው በዘለለ በመጥፎ ጠረን በመጠፍነግ አላሳልፍ የሚሉ አይደሉም፡፡

አራት ኪሎ የሚገኘውን ጨምሮ ሁሉም ደረጃቸውን የጠበቁ ናቸው፡፡ በግራ ቀኝ ያሉ መደበቂያዎች በመወገዳቸው ዘረፋና የትኛውንም ዓይነት ነውረኛ ተግባር ለመፈፀም አያመቹም፡፡ ከምንም በላይ ሁሉም ሲጠናቀቁ የመዲናዋን የመንገድ አማራጭ የሚያሰፉ ናቸው፡፡ ግንባታቸው የተከናወነበት ጥሬ ዕቃ ለከተማዋ ውበት ይለግሳል፡፡

ደረጃውን የጠበቀ ፓርኪንግ (የተሽከርካሪ ማቆሚያ) እንዲሁም ከትራንስፖርት በዘለለ ነዋሪው የሕዝብ የጋራ መገልገያ ሥፍራዎችም የ2017 ዓ.ም የመዲናችን አዲስ አበባ ስጦታዎች ናቸው፡፡ እነዚህም የተገነቡትና እየተገነቡ ያሉት በአራቱ አቅጣጫ እየተካሄደ ከሚገኘውና ከተጠናቀቀው ከመንገድ የኮሪደር ልማት ጋር ተያይዘው ነው፡፡

በልማት የሚሸፍኑት ሥፍራም ቀላል አይደለም፡፡ በጥቅሉ ከ28 ኪሎ ሜትር በላይ ይባል እንጂ ለመኪናም ሆነ ለእግርና ለማንኛውም እንቅስቃሴ አስቸጋሪ የነበሩ አካባቢዎችን ምቹ በማድረጉ ረገድ ትልቅ ሚና አለው፡፡

አንድ ባንድ እንያቸው ብንል ከመገናኛ ዲያስፖራ አደባባይ፣ ከአራት ኪሎ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ድረስ 6ነጥብ4 ኪሎ ሜትር በመሸፈን የመዲናችንን አዲስ ገጽታ በእጅጉ እየለወጡ ያሉ ናቸው፡፡ ከአራት ኪሎ በመስቀል አደባባይ እስከ ቦሌ ድልድይ ሰባት ኪሎ ሜትር ዘልቀው ውበትን አጎናጽፈዋታል፡፡

ከፒያሳ ዓድዋ ድል መታሰቢያ ዙሪያ፤ በለገሀር ሜክሲኮ፤ በሣር ቤት በኩል እስከ ወሎ ሰፈር 10 ኪሎ ሜትር፤ ከቦሌ አየር መንገድ እስከ መገናኛ ዲያስፖራ አደባባይ 4ነጥብ9 ኪሎ ሜትር ውበት አጎናፅፈዋል፡፡ በተለይ ፒያሳ ዘንድሮ በእጅጉ ተለውጣ ምቹ ሆናለች፡፡ ሙሉ በሙሉ ውስጥ ለውስጥ የነበረው የጠለሸ ገጽታዋ ተለውጧል፡፡ ከበስተጀርባዋ ከትመው የነበሩት እነ ሠራተኛ ሰፈር፣ ዶሮ ማነቂያና ሌሎች የጠለሹ መንደሮችና ቤቶች ዘንድሮ በኮሪደር ልማት ውበት ተላብሰዋል፡፡

ዛሬ ላይ የደከሙና የፈራረሱ የጭቃ ቤቶች መገኛዋ አቧሬም አልፎላታል፡፡ እነዚያ በየጉራንጉሩ የተገጠገጡ እርጅና የተጫናቸው ቤቶች በፍጥነት በትልልቅ ፎቆች እየተተኩ ነው፡፡ ሪል ስቴትም ሞልቶባቸዋል፡፡ ከፒያሳ ሲመጣ በአራት ኪሎ ታጥፎ ቀበና የሚዘለቅበት መንገድም በየዳሩ የነበሩትን ግንባታዎች አስወግዶ አስፋልቱ ቅቤ መስሎ ተገንብቷል፡፡ ስፋቱም ፈረስ ያስጋልባል፡፡

በአራቱም ማዕዘን ያለው የረጅሙ እግር መንገድ ውበት ታይቶ አይጠገብም፡፡ ደግሞ ምቹና ማራኪዎቹ መናፈሻዎችና ማረፊያዎች አሁን ላይ ክረምት ወለዱና ወቅታዊው ብርድ ባይኖር ቤታችሁ ግቡ ግቡ አያሰኙም፡፡ ዘንድሮ በኢትዮጵያ አዲስ ዓመትን ነዋሪው እየተቀበለው ያለው እንደ ድሮው በየቤቱ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በእነዚህ ስፍራዎች ጭምር ዘና ፈታ በማለት ነው፡፡

በየአካባቢው ያሉትን የውሃ ፏፏቴዎች ከቦ ፎቶ በመነሳት፣ በማየትና አካባቢውን ጠቅላላ በማድነቅ፤ ነው የሚያሳልፈው፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች በተገነቡ የጋራ መገልገያዎች ሻይ ቡና በማለትም አዲስ ዓመትን የተቀበለው ነዋሪ በርከት ነው፡፡ ይህ ወደፊት ነዋሪው በእነዚህ ስፍራዎች የልጆቹን ልደት፣ ሠርጉንና የተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮቹን ሳይቀር የማይከውንበትና አካባቢውን እያደነቀ ዘና ፈታ የማይልበት እንደሌለ ያመላከተ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ መልካም አዲስ ዓመት!

ሰላማዊት ውቤ

አዲስ ዘመን መስከረም 4 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You