በአዲሱ ዓመት አለመግባባቶችን በምክክር ለመፍታት እንዘጋጅ

ሀገራዊ ምክክር በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል የሀሳብ ልዩነቶች ሲፈጠሩ፣ በከፍተኛ የፖለቲካ ቀውስ ወቅት፣ ከጦርነት በኋላ በተከሰቱ ሁኔታዎች ወይም ሰፊ የፖለቲካ ሽግግሮች ውስጥ ባሉ በርካታ ባለድርሻ አካላት መካከል መግባባት ለመፍጠር የታለመ በሀገራዊ ባለቤትነት የተያዘ ግልጽ የሆነ ዓላማና ግብ ያለው የምክክር ሂደት ነው።፡፡

የተለያዩ ሀገራት በታሪክ አጋጣሚ የተፈጠሩ ሀገራዊ ችግሮችንና መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ያጋጠሙ አለመግባባቶችን አካታች በሆነ ሀገራዊ ውይይት መፍታት ችለዋል። በዚህም ዘላቂ ሠላም በማስፈን የተሳካ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ለውጥ አምጥተዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ የፖለቲካ እና የሃሳብ መሪዎች መካከል እጅግ መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ሳይቀር የሃሳብ ልዩነት እና አለመግባባት እንዳለ ይታመናል። ልዩነቶችን በሠላማዊ መንገድ በውይይት ለመፍታት ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በአዋጅ ተቋቁሞ ወደ ሥራ ገብቷል። ተስፋ የተደረገበት ሀገራዊ ምክክሩ የተሻለ ሀገራዊ አንድነት ለመገንባት በሂደትም የመተማመን እና ተቀራርቦ የመሥራት ባሕልን ለማጎልበት እንዲሁም የተሸረሸሩ ማኅበራዊ ዕሴቶችን ለማደስ የሚጠቅም ነው፡፡

የቆዩ አለመግባባቶችን ጨምሮ አሁን ላይ የሚስተዋሉ ግጭቶችን በሠላማዊ መንገድ በውይይት በመፍታት፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ለሚደረገው ጉዞ የውይይት ባሕልን ማዳበር እና ወቅታዊ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ይረዳል። በዚህ ረገድ የተሳካ ብሔራዊ ውይይት ማድረግ ሀገሪቱ ለምታደርገው የልማትና የዴሞክራሲ ጉዞ መደላደልን ከመፍጠር በዘለለ ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት ሚናው የጎላ እንደሆነ የሚተመን ነው።

በሀገሪቱ በአብዛኛው አካባቢዎች የፖለቲካ ጥያቄዎቻቸውን በኃይል ለማስፈፀም የሚንቀሳቀሱ በርካታ ቡድኖች አሉ። የእነዚህ አካላት ተግባር ደግሞ የዜጎች ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የመንቀሳቀስ ተፈጥሯዊ መብታቸውን በሚገታበት ደረጃ ላይ ደርሷል። ይህንን ችግር ለመፍታት ሀገሪቱ የወሰደችው አማራጭ ብሔራዊ ሀገራዊ ምክክር መካሄድ ነው። ምክክሩ ሁሉንም የሀገሪቱን ችግሮች ይፈታል የሚል እምነት ባይኖረኝም መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች የጋራ መግባባት ለመፍጠር ጉልህ ሚና እንደሚጫወት አልጠራጠርም።

ሀገራዊ ምክክሩ ውጤታማ ሊሆን የሚችለው ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች ያለምንም አድሎና ማግለል አሳታፊ መሆን ሲችል ነው፤ ስለዚህ ጥያቄ አለን የሚሉ አካላትን ሁሉ በማሳተፍ የሚካሄድ ከሆነ ትላንትና የተፈጠሩና ለዛሬ ግጭቶቻችንና አለመግባባቶቻችን ምክንያት የሆኑ ዋልታረገጥ የሆኑ ሀሳቦችን የሚያስታርቅበት ዕድል አለው።

የትላንትና ችግሮቻችን ለዛሬ አለመግባባቶቻችን ምክንያት የሆኑት በሀገረ መንግሥት ግንባታ ላይ የጎደለን ነገር ስላለን በመሆኑ፤ ይህንን ስብራት ለመጠገን እውነተኛ የሆነ ምክክር ማድረግ ተገቢ ነው። ይህንን ማድረግ ከተቻለ የተረጋጋችና ፊቷን ወደ ልማትና ኢኮኖሚ የምታዞር ሀገር ከምክክሩ በኋላ ልናይ እንደምንችል ይሰማኛል፤ ነገር ግን ሀገራዊ ምክክሩን ሁሉንም ችግሮች እንደሚፈታ ቁልፍ አድርጎ መውሰድ ስህተት ይሆናል።

ለይስሙላ ምክክር አደረግን ለማለት ሳይሆን እንደ ሀገር ሁሉንም የማኅበረሰብ ክፍል የሚያሳትፍና የሚያሻግር እውነተኛ ብሔራዊ ምክክር ለማድረግ መዘጋጀት ከሁሉም እንደሚጠበቅ ብዙዎች ይስማማሉ፤ በምክክር ሂደቱ የሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች ውክልና ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው።

በሌላ በኩል በውይይቱ ብንሳተፍም ውጤት አይኖረውም የሚሉ አካላትን በተቻለ መጠን በማሳመን ወደ ንግግር እንዲመጡ ለማድረግ የምክክር ኮሚሽኑ አሁን እያደረገ ያለውን ጥረት አጠናክሮ በመቀጠል እነዚህን አካላት ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ እንዲመጡ ማድረግ አለበት እላለሁ።

በኢትዮጵያ መሠረታዊና ሀገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ የሀሳብ ልዩነቶች እንዳሉ ይታወቃል። እነዚህን ችግሮችና የሀሳብ ልዩነቶች ለመፍታት የሚካሄድበት መንገድ ደግሞ የኃይል አማራጭ በመሆኑ እንደ ሀገር ብዙ ነገር አጥተናል እያጣንም እንገኛለን።

ከዚህ እሽክርክሪት ለመውጣት እጅግ መሠረታዊና ሀገራዊ በሆኑ የሀሳብ ልዩነቶችና አለመግባባቶች መንስኤ የሆኑ ጉዳዮችን በአጀንዳ መልክ በመለየት እነርሱ ላይ መመካከር ተመካክሮ ወደ መግባባት መድረስ አስፈላጊ ነው። ይህ ሲሆን ብቻ ነው ሀገሪቱ እንደ ሀገር አሁን ካለችበት ችግር ተላቃ ወደፊት መራመድ የምትችለው።

ከዚህ ቀደም በነበሩ ጊዜያት በሀገሪቱ የነበሩ ችግሮችን ለመፍታት የተለያዩ ሙከራዎች ተደርገዋል፤ ነገር ግን እነዚህ ሙከራዎች በአንድ በኩል የአሳታፊነትና አካታችነት ችግር ስለነበረባቸው በሌላ በኩል ደግሞ በተወሰኑ ሥልጣን ላይ ባሉ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት ምክንያት የሚፈለገውንና መምጣት የነበረባቸውን ውጤት ሳያመጡ ቀርተዋል።

አሁን ባለው ሂደት ግን አዲስ ውጤት ለማምጣት አዲስ መንገድ መከተል ተገቢ ስለሆነ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ምክክር ሁሉን አካታችና አሳታፊ እንዲሆን ለማድረግ የምክክር ኮሚሽኑ የተለያዩ ጥረቶች እያደረገ እንደሆነ በተደጋጋሚ እየገለጸ ይገኛል።

ከዚህ አኳያ በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በትጥቅ የታገዘ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ አካላት በ2017 አዲስ ዓመት ሰይፋቸውን ወደ ሰገባቸው መልሰው ለውይይት ዝግጁ እንዲሆኑና ኢትዮ ጵያውያን እርስበርስ በሚያባሉን ጉዳዮች ላይ ወደ መሐል መጥተው የጋራ መግባባት ላይ እንዲደርሱ መንግሥት፣ ሕዝብና የምክክር ኮሚሽኑ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ሊወጡ ይገባል እላለሁ።

ክብረአብ

 አዲስ ዘመን መስከረም 5/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You