የተወለዱት አዲስ አበባ ቢሆንም ገና በጨቅላ ዕድሜያቸው ቤተሰቦቻቸው ለሥራ ወደ ድሬዳዋ መሄዳቸውን ተከትሎ አብዛኛውን የሕይወት ጊዜያቸውን ድሬዳዋ አሳልፈዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ልክ በድሬዳዋ የተወለዱትን ያህል ለሕዝቡና ለከተማው ልዩ ፍቅር አላቸው፡፡ በድሬ አሸዋ ላይ ከጓደኞቻቸው ጋር ቦርቀው አድገዋል፡፡ እንደ አብዛኛው ኢትዮጵያዊውም በቄስ ትምህርት ቤት ፊደል ቆጥረዋል፡፡ በቄስ ትምህርት ቤት ሳሉም የጭንቅላታቸውን ብሩህነት የተረዱት መምህራቸው ለሚካኤል ቤተክርስቲያን አገልጋይ እንዲሆኑ ይመርጧቸዋል፡፡ ይሁንና በወላጆቸው መካከል አለመግባባት ይፈጠርና የቅስና ትምህርታቸውን ለማቋረጥ ይገደዳሉ፡፡ በመሆኑም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን እዚያው ድሬዳዋ ከተማ በሚገኝና እስላም ክርስቲያኑ በግብረገብና በፍቅር ተቀርፆ ባደገበት በሉትራን ሚሲዮኑ «ክርስቶስ» ትምህርት ቤት ተማሩ፡፡ በልዑል መኮንን ትምህርት ቤት ደግሞ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡
የአስረኛ ክፍል ተማሪ ሳሉ ግን በአገሪቱ በተፈጠረው የፖለቲካ ችግር ምክንያት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አቋርጠው አስመራ በሚገኘው የመምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጅ ይገባሉ፡፡ በዚያም ለሁለት ዓመት በመምህርነት ሰለጠኑ፡፡ ወደአደጉባት ሐረርጌ ክፍለሀገር ተመልሰው ሶቃና ደደር በተባሉ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አስተማሩ፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስር ይገኝ በነበረው ደብረዘይት እርሻ ኮሌጅ ደግሞ የገጠር ምጣኔ ሀብትና የኅብረተሰብ ሳይንስ ትምህርት መስክ ተጨማሪ ዲፕሎማቸውን በማዕረግ አገኙ፡፡ የግለሰቡን የትምህርት አቅም የተገነዘበው ዩኒቨርሲቲም እዚያው በተማሩበት ኮሌጅ እንዲያስተምሩ ቀጠራቸው፡፡ ይሁንና አንድ ዓመት ተኩል ካገለገሉ በኋላ ወደ ሃረማያ ዩኒቨርሲቲ ይልካቸውና ለተጨማሪ አንድ ዓመት ተኩል በመምህርነት አገለገሉ፡፡ በመቀጠልም ሃንጋሪ በሚገኘው ቡዳ ፔስት ዩኒቨርሲቲ ነፃ የትምህርት ዕድል አግኝተው በንግድና በማክሮ ኢኮኖሚክስ ዘርፎች የማስተርስና ዶክትሬት ዲግሪዎችን ማግኘት ችለዋል፡፡ በተጨማሪም በሃንጋሪ ሳይንስ አካዳሚ የልማት ኢኮኖሚ በተሰኘ የትምህርት መስክ ሁለተኛ የዶክትሬት ዲግሪ ሰርተዋል፡፡
የሐረርጌን ውሃ የሕዝቡን ፍቅር ጠጥተው ያደጉት እኚሁ የዛሬ እንግዳችን ታዲያ በየገጠሩ በሚያስተምሩበት ጊዜ የሕዝቡ የከፋ ድህነት በተለይም ደግሞ የአርሶ አደሩ መሬት አልባነትና ረሃብ ቢያሳስባቸው የአፄ ኃይለሥላሴ ሥርዓትን በመቃወም በመምህራን ማህበር ስር ሆነው ብርቱ ትግል አድርገዋል፡፡ ወታደራዊው የደርግ ሥርዓት ከመጣም በኋላ ሳይማር ያስተማራቸውን ሕዝብ ከጭቆና ለማላቀቅ ብዙ መስዋትነት ከፍለዋል፡፡ ታስረዋል፤ ተደብድበዋል፤ ተሰደዋል፡፡ በጥይት ተመተውም አንድ እግራቸው ተቆርጧል፡፡ ሃንጋሪ እያሉ የአሜሪካ ቪዛ ቢያገኙም የሕዝብ ናፍቆት አላስችል ብሏቸው የውጭ ዕድሉን ወደ ጎን በመተው ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል፡፡ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ደግሞ ቀድሞ ባገለገሉበት ሃረማያ ዩኒቨርሲቲ ለአራት ዓመታት ተኩል በረዳት ፕሮፌሰርነት አገለገሉ፡፡ ይሁንና ይከፈላቸው የነበረው ደመወዝ አነስተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሃረማያ ዩኒቨርሲቲን ለቀው በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ተቀጠሩ፡፡ ላለፉት 20 ዓመታትም በዩኒቨርሲቲው የኢኮኖሚክስ ትምህርት በማስተማር ላይ ይገኛሉ፡፡ በተጨማሪም በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲና በተለያዩ የግል ዩኒቨርሲቲዎች ተጋባዥ መምህር በመሆን ሀገራቸውን እያገለገሉ ናቸው፡፡ ከኝሁ የሀገረርና የሕዝብ ባለውለታ ከሆኑ የምጣኔ ሀብት መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ደምመላሽ ሃብቴ ጋር በምጣኔ ሀብትና እና ሀገራዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገናል፡፡ እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ወደ ፖለቲካ ትግሉ የገቡበትን አጋጣሚ ያስታውሱንና ውይይታችንን ብንጀምር?
ረ/ፕሮፌሰር ደምመላሽ፡- አስረኛ ክፍል በደረሰኩበት ወቅት በአገሪቱ የተማሪዎች የፖለቲካ ተቃውሞ እንቅስቃሴ ከመሃል አገር ወደ ድሬዳዋና ሌሎችም ገጠር አካባቢዎች ዘልቆ እየገባ ነበርና እኔም ሆንኩ መላው ተማሪ ትምህርት በአግባቡ መማር የማንችልበት ሁኔታ ተፈጠረ። በዚህ ምክንያት ሁሉም መውጫ ቀዳዳን ይፈልግ ያዘ። ከወታደር ጋር መጋጨት ጀመርን። ድንጋይ ወታደሩ ላይ እንወረውር ነበር። ይሁንና ልክ አሁን ላይ በአውሮፓ እንደሚታየው ሁሉ ተማሪው የፈለገውን ችግር ቢፈጥርም ወታደሩ በፍፁም አይተኩስም ነበር። በአጋጣሚ እንኳን በወታደሩ የተያዘ ተማሪ ወላጅ ልጁን እንደሚቀጣ ሁሉ ተገርፎ ተመልሶ ወደ ቤቱ እንዲገባ የሚደረግበት ሁኔታ እንደነበርም አስታውሳለሁ፡፡
ይህ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ እያየለ ሲመጣ ግን እኔም ሆንኩ ሌሎች ተማሪዎች በሐሰት ዕድሜያችንን ከፍ እያደረግን ወደ ተለያዩ የሙያ ትምህርት ቤቶች ገባን። እኔም በመምህርነት ሙያ ለማገልገል ተወዳድሬ ውጤቴ ጥሩ ስለነበር ቅድሚያ ተሰጥቶኝ ለትምህርት አስመራ ሄድኩኝ። አስመራ ይገኝ በነበረው በመምህራን ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ውስጥ በቆየሁባቸው ሁለት ዓመት የብሔርተኞችን እንቅስቃሴ ምን እንደሆነ የመመልከት ዕድሉን አገኘሁ። በሌላ በኩል በወቅቱ ከተማሪው እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ የአውሮፕላን ጠለፋ ይካሄድና ሲመረመር የኤርትራ ተወላጆች መሆናቸው ይረጋገጣል።
እናም የጎጃም ሰው ባህርዳር የነበሩትን ኤርትራውያን ተማሪዎች ላይ ተነስቶ በጠብንጃ ስለከበበና ስላስፈራራቸው ሸሽተው ወደ አስመራ ይመጣሉ። በምላሹም እነዚያ የኤርትራ ተማሪዎች አማራ አባሮናል በሚል የተሳሳተ አመለካከት በአስመራ በነበርነው ተማሪዎች ላይ ድንጋይ መወርወርና መደብደብ ያዙ።
ወዲያውኑ ግን የአፄ ኃይለሥላሴ ፈጥኖ ደራሽ ወታደሮች መጥተው ድብደባውን ያስቆማሉ። ያን ጊዜ ታዲያ እኛም በተራችን ወደ መጣንበት እንመለሳለን ብለን ሰልፍ ወጣን። ለልዑል ራስ አስራተ ካሳም ቅሬታችንን አቀረብን። እኚህ ሰው በአካባቢው ሰው እጅግ የተከበሩና ረጋ ያሉ ግለሰብ ነበሩና «ክብሪት ወደ መላው አገሪቱ አልክም፤ አትመለሱም፤ አስታርቃችኋለሁ» አሉና አረጋጉን። እኛም በሃሳባቸው ተስማምተን ቆየን። ባሉት መሠረትም በአጭር ጊዜ ውስጥ በሲኒማ ቤት ውስጥ ወጣቱንና የኪነጥበብ ሰዎችን አስመጥተው እንድንጨባበጥ አደረጉና ሰላም ወረደ። በዚህ ምክንያት ትምህርቴን በጥሩ ውጤት አጠናቅቄ ወደ ሐረርጌ ክፍለሀገር በዕጣ ለማስተማር ተመደብኩ። በዚያን ጊዜ የሁላችንም ዋነኛ ዓላማ ከራሳችን ይልቅ ሌሎችን የመርዳት ፅኑ ፍላጎት ነበረንና ገጠር ውስጥ ማስተማርን እንደትልቅ ተልዕኮ ነበር የምንቆጥረው። በዚያ መሠረት በሐረርጌ አውራጃ ወበራ በሚባል አካባቢ ማስተማር ጀመርኩኝ።
አዲስ ዘመን፡- ይህ እስኪሆን ድረስ ታዲያ ፖለቲካው ውስጥ ጠልቀው አልገቡም ማለት ነው?
ረ/ፕሮፌሰር ደምመላሽ፡- አዎ፤ እኔ መጀመሪያም ቢሆን ታላላቆቻችን የሚሉንን በማመን ብቻ ሥርዓቱን እቃወማለሁ እንጂ የነበረውን የፖለቲካ ችግር በቅጡ አልተዳሁትም ነበር። ደግሞም እድገቴ ከተማ ውስጥ ስለነበርና በተለይ ደግሞ ድሬዳዋ ሀብታሙና በድሃ መካከል የነበረው ልዩነት እዚህ ግባ የሚባል ስላልነበር የከፋ የሚባል ድህነት አይቼ አላውቅም ነበር። ያለው ከሌለው ጋር ተካፍሎ የሚኖር ሕዝብ ስለነበር ድህነቱ ያን ያህል አይሰማም ነበር። ሳይበላ የሚያድር ሰው አልነበረም። እንዲያውም ብነግርሽ ልጅ በነበርኩበት ጊዜ አንዳንድ ጊዜ ቤታችን እንጀራ ሲያልቅ እንጀራ ግዛ ተብዬ እላክና በ25 ሳንቲም አምስት እንጀራ ገዝቼ አንድ ይመረቅልኝ ነበር። ስኳር ከወንጂ ስኳር ፋብሪካ በከረጢት 10 ሳንቲም ነበር። ማታ ማታ የቁጢ (የቡና ቅጠል ሻይ ) እየጠጣን ነበር የምናጠናው። ቤት ኪራይም ሁለትና ሦስት ብር ነበር። ስለዚህ ድህነት ምን እንደሆነም በማያውቅ ማህበረሰብ ውስጥ ነው ያደኩት። ለነገሩ ዓይን ያወጣ ችግርም አልነበረም።
በኋላ ግን በመምህርነት ገጠር ላይ ተመድቤ ስሰራ ግን በጣም የሚያሰቅቅ ሁኔታ ተመለከትኩኝ። ለካ ምንም በልቶ የማያድር ሰው አለ! አልኩ። ሰፋፊ መሬቶች ያሏቸው የከበሩ ባላባቶች የነበሩትን ያህል ምንም መሬት የሌላቸው ሰዎች እንዳሉ ተገነዘብኩኝ። ከጊዜ ብዛት ይሄ ጉዳይ በጣም ይቆረቁረኝ ጀመር። በዚህ ምክንያት ወደ ተቃውሞ ውስጥ የመደባለቅ ፍላጎቴ ይበልጥ እያደገ መጣ።
በሌላ በኩል ገጠር ውስጥም ከእኔ ቀደም ብሎ አስተማሪ የነበረ ሰው የሶሻሊዝም እንቅስቃሴ አዘል ጽሑፎችን ይሰጠኝ ነበር። በተለይም የማኦ ሴቶን ትንሽዬ ቀይ መፃሃፍ ያነብና የአፄ ኃይለሥላሴ አስከፊ አገዛዝ በተለይም የመሬት ስሪቱን መጥፎነት ሲያስረዳኝ አመለካከቴን እያሰፋሁ መጣሁ። ስለመደብ ትግል ብዙ እውቀት ባይኖረኝም ባለችኝ ትንሽ መረጃ ከዚህ ሰው ጋር እንከራከር ነበር። በዚህም የሕዝቡ አኗኗር ፍትሃዊ እንዳልሆነ ይበልጥ ተገነዘብኩ። ከዚያም የተማሪው እንቅስቃሴ መምህራን ውስጥም ዘልቆ ስለገባ በመምህራን በኩል መሳተፍ ጀመርኩ። እንዲያውም የሐረር መምህራን ማህበር ጠንካራ ስለነበር «ተነስ» የሚል መፅሄት ነበራቸውና እሱን በማንበብ ይበልጥ ወደ ለውጡ እየተገፋን መጣን፡፡
ከሶቃ ጨርሼ የወበራ አውራጃ ዋና ከተማ የሆነችው ደደር ከተማ ላይ መጣው። እዚያም በመምህራን ማህበር በኩል ጥሩ ተሳትፎ አደርግ ስለነበር የመምህራን ማህበር ኃላፊ ሆንኩኝ። በዚህም እኔ ነበርኩ ከዋናውና ሐረር ከሚገኘው የመምህራን ማህበር ጋር ግንኙነት የማደርገው። እስከዚያ ድረስም ቢሆን እንዲሁ በድፍኑ ለሰው ጥሩ ከመመኘት የመነጨ ብቻ ነበር የነበረኝ። የተጎዱ ሰዎችን ከችግራቸው መላለቀቅ አለባቸው፤ የመሬት ስሪቱ መሻሻል አለበት በሚል ነበር ሥርዓቱን እቃወም የነበረው። በሂደትም መሬት ለአራሹ የሚለውን ሃሳብ እኛም ጋር ትክክለኛነቱን አምነን ያንን ማስተገባት ጀመርን። ይህ ባለበት ሁኔታ የኃይለሥላሴ ከሥልጣን የመውረድና ደርግ የመተካት ሁኔታ መጣ። የደርግ ሥርዓት እንደመጣ ሁለት ዓይነት ጎራ ተፈጠረ። የሚደግፈው ወገን በአንድ በኩል፤ ጨርሶም ደግሞ ይሄ የወታደራዊ መንግሥት ትክክል ሊሆን አይችልም ብለው ያመኑና ከመጀመሪያው የነቁት ደግሞ በሌላ በኩል። እኔም የአዲሱ መንግሥት ሁኔታ የማያዋጣ መሆኑን ስለተገነዘብን የተቃውሞውን እንቅስቃሴ የመደገፍ አዝማሚያ ላይ ደረስኩ። እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ጀመርኩ።
አዲስ ዘመን፡- በማህበሩ ውስጥ ሆነው ነው የተቃውሞ ጎራውን የተቀላቀሉት?
ረ/ፕሮፌሰር ደምመላሽ፡- አዎ፤ በመምህራን ማህበር ውስጥ ያለነው አብዛኞቻችን ይህ ወታደራዊ አገዛዝ የታሰበውን ለውጥ ሊያመጣ እንደማይችል፤ ይልቁንም አፋኝና ጨቋኝ ስለመሆኑ ወዲያውኑ ስለተገነዘብን በማህበሩ ውስጥ ሆነን ትግላችንን አጠናክረን ቀጠልን። በኋላም ላይ የዘመቻ እንቅስቃሴ ተጀመረ። ይሁንና እኛ ከማህበረሰቡ ጋር ቀረቤታ ስለነበር ከዘማቹ ይልቅ እኛ የሕዝቡን ሃሳብ እንረዳ ነበር። ከዩኒቨርሲቲ የመጣው ዘማች ኃይል ደግሞ ራዲካል (አክራሪ) የሆነ አስተሳሰብ ይዞ መጥቶ ስለነበር ከሕዝቡ ጋር ግጭት ውስጥ ገባ። እኛ ደግሞ ከሥራ ውጪ በሚኖረን ጊዜ ጫት ከኅብረተሰቡ ጋር እየተቃወምን እርስበርሳችን የመመማርና ሌላውን የማንቃት ሥራችንን አጠናክረን ቀጥለን ነበር። ይህ ተግባራችንም የአውራጃ ኃላፊዎችና የለውጥ ሃዋርያት ተብለው በተሾሙት ዘንድ ጥሩ መስሎ አልተያቸውም። ምክንያቱም የሚሄዱበት መንገድ የኃይልና የጭቆና አካሄድ ስለነበር ልንስማማ አልቻልንም።
እነዚህ ኃይሎች እነሱ በሚያስቡበት ሁኔታ በአካባቢው ተቀባይነት ባለማግኘታቸው ሻለቃ ጌታቸው ሺበሺ የሚባል የደርግ ሰው መምህራን አስቸግረዋል ብለው ጠቆመብን። አንድ ምሽት እንደተለመደው በጫት ሰበብ ቁጭ ብለን እየተወያየን ባለነበት ወቅት ከበቡን። እኛ ግን እስከሚይዙን ድረስ ስለሰውዬው ማንነትና ስለተጠነሰስብን ሴራ የምናውቀው ነገር አልነበረም። በኋላ ላይ እንደሰማሁት ይህ ሰውዬ ለካ በአዋሽ ሸለቆ ሰው እየጨፈጨፈ ነበር የመጣው። እኛ ጋር ሲደርስ ሁኔታውን እንደሰማ ምንም ጊዜ ሳያጠፋ ሊገድለን አስቦ አሰረን። እውነቴን ነው የምልሽ እነዚህ ኃይሎች ድንገት ከበውን ያደረጉንን ሁኔታ ሳስበው እስከዛሬ ድረስ ፊልም ላይ እንጂ በአካል ሰው ላይ ይፈፀማል ብዬ የምጠበቀው አይደለም። እኛ መጀመሪያ ላይ ቀልድ ነበር የመሰለን። ሰውዬውን ባክህ ቁጭበልና ጫት ቃም ብለነው ነበር። ከዚያ ነገሩ ቁርጥ መሆኑን ስንረዳ በየስርቻው የተሸሸጉ ወታደሮች ወጡብን። እኔና አፈወርቅ የሚባል ግለሰብ ተይዘን ሄድን ፖሊስ ጣቢያ ጣሉን። ከዚያ በኋላ የሆነውን ነገር አናውቅም፡፡
የዚያን ገዳይ ሻለቃ አላማ ሳንረዳ ከአሁን አሁን ይፈቱናል እያልን ስናስብ ለካ የሞት ቀጠሮ ተቆርጦልን ተራችንን እየጠበቅን ነበር። ይህ ሰው በወቅቱ መስቀያ አዘጋጅቶ፤ ሌሊቱን ሙሉ አስነግሮ ሰው ሁሉ በጠዋት እንዲወጣ አድርጓል። ያለምንም ጥያቄም በቀጥታ ሊገድለን አዘጋጀን። ያም ሆኖ ግን እኛ ሥርዓቱን ከመቃወም ባለፈ የተለየ ወንጀል ሰራን ብለን ስለማናምን እዚያ ደረጃ ይደርሳል ብለን አልጠበቅንም። በነገራችን ላይ የሐረርጌ ሰው በተፈጥሮው ከወታደር ጋር ብዙም ስምምነት የለውም።
ያ መንግሥት ገና ሲመጣ ወታደር ስለሆነ ብቻ ጥሩ ይሰራል የሚል እምነት አልነበረንም። ወታደር ድንብር የመጠበቅ እንጂ የማስተዳደር ብቃት አላቸው የሚል እሳቤ አልነበረንም። እናም ሰውዬው ሊሰቅለን ተዘጋጅቶ የነበረ ቢሆንም የደደር ሕዝብ በጠቅላላ ግልብጥ ብሎ ወጥቶ ከስቅላት አተረፈን። ከዚያ ተነስቶ ጥሎን ሄደ። ይሁንና እሱ ወደ ገለምሶ ሲሄድ እኛ
እዚያው እስር ቤት እንድንቆይ ተደረገ። ፍቱን ብንልም የሚሰማን አጣን። በኋላ በወቅቱ በትምህርት ሚኒስቴር ቋሚ ተጠሪ ለነበረው ጎሹ ወልዴ በመምህራን ማህበር አማካኝነት ተደወለለትና ተፈታን።
ከዚያ በኋላ ነው እንግዲህ ይሄ መንግሥት በእርግጠኝነት ትክክል እንዳልሆነ ከመገንዘብ ባለፈ ውስጥ ለውስጥ የነበረው እንቅስቃሴም እየተጠነከረ መጣና እጅ መስጠት የለም የሚል መመሪያ ተላለፈ። በዚያ መሠረትም ሌት ተቀን አድብተን ያንን ዘማች ኃይል ከአካባቢያችን አባረርነው። አብዛኞቻችን ፊት ለፊት መቃወም ጀመርን። በተለይ እኔ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ውስጥ ጠልቄ ገባሁኝ። እንዲያውም ከማስተማር ይልቅ ዋና ሥራዬ እንቅስቃሴውን መምራት ሆነ። ጎን ለጎን የኢህአፓም እንቅስቃሴ እየጠነከረ መጣ። በሐረርጌ 90
በመቶ የሚሆነው ኃይል በኢህአፓ እንቅስቃሴ ውስጥ ገባ። በነገራችን ላይ ከብዙ ቆይታ በኋላ ነው እነመኢሶን የሚባሉ ድርጅቶች የመጡት። ነገር ግን የኢህአፓን ያህል ተቀባይነት ሲያጡ በብሕር ላይ የተመሰረተ እንቅስቃሴ ጀመሩ።
አዲስ ዘመን፡- ለምን ነበር መኢሶን በአካባቢው ተቀባይነት ያጣው?
ረ/ፕሮፌሰር ደምመላሽ፡- የአካባቢው ማህበረሰብ የኦሮሞ ተወላጅ ቢሆንም ከአመራሩ እንጂ ከብሔር ጋር ግጭት አልነበረውም። እነዚህ አካላት ኅብረተሰቡ ጋር ሰበረው መግባት ስላልቻሉ የምናደርገውን እንቅስቃሴ የአማራ በእንቅስቃሴ ነው ወደ ማለት መጡ። «እጅ እጅን አይቆርጥም የመደብ ትግል ለእኛ ጥሩ አይደለም፤ የኦሮሞ ባላባት ራሱ የተጨቆነ ስለሆነ መነካት የለበትም» የሚል አስተሳሰብ ማስረፅ ጀመሩ። በተለይ መሃመድ ሃሰን የሚባልና የመጀመሪያ ዘማች ኃላፊ የነበረ ሰው ይህንን እንቅስቃሴ አስጀመረ። እኛ መጀመሪያ ላይ ደህና ሰው መስሎን ተጠግተን አዋራነው፤ እሱ ግን እኛን ከዚያ አካባቢ ለማጥፋት ጥረት ያደርግ ገባ። ምክንያቱም እኛ ካልተነሳን እዚያ አካባቢ ተቀባይነት ማግኘት አይችልምና ነው። የዘር ፖለቲካውን መንዛት አይችልም ነበር። ስለዚህ ይህንን ፖለቲካውን ለማሰራጨት ሲል ወጣቱን በሙሉ አሰረ። እኛም እጅ መስጠት የለብን የሚለውን ቆራጥ አቋም ይዘን ታገልን። እኔን ሊይዙ ሲመጡ በተኩስ ነው የወጣነው። ያ ሰውዬ በግፍ ከዚያ አካባቢ ስላስወጣን ለመግደል በቀጥታ ሄድንና ከጠባቂዎቹ ጋር ተታኮስን። ከዚያ ጊዜ ወዲህ መምህርነቱን ጥለን ወጣን፡፡
አዲስ ዘመን፡- በወቅቱ ታዲያ በደርግ ሠራዊት እንዴት የመያዝ አጋጣሚ ሳይፈጠር ቀረ?
ረ/ፕሮፌሰር ደምመላሽ፡- የዚያን ጊዜ የሚገርምሽ ነገር ወጣቱ ሁሉ አስተሳሰቡ አንድ ዓይነት ነው። የአንቺ ቤተሰብ የእኔ ቤተሰብ ነው። ችግር ቢደርስብኝ አንቺ ጋር እሄዳለሁ። አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርግልኛል ፤ ያቤተሰብ ከጥቃት ይከላከልኛል። እኔ በኖርኩበት ዘመን ኦሮሞ ማህበረሰብ ውስጥ ሆኜ ኦሮሞኛ አልችልም ነበር። ነገር ግን ልክ እንደራሱ ልጅ ነበር ማህበረሰቡ የሚከላከልልኝ፤ የሚንከባከበኝ። አስፈላጊ ከሆነ በሌሊት ሳይቀር እንቅስቃሴያችንን እየመሩ የሚወስዱን እነዚሁ የአካባቢው ነዋሪዎች ናቸው። እኔ በተለይ በመምሀራን ማህበር ውስጥ ብዙ እንቅስቃሴ ሳደርግ የመጋለጥ ሁኔታ ስለነበር ለመደበቅ ከባድ ሆነብኝ። እዚህም እዚያም የሚያውቀኝ አገኛለሁ። ደግሞም እኔ እንድያዝ ትእዛዝ ስለወጣ መሰወር አልቻልኩም። እንዲህ ዓይነት ጭንቀት ሲመጣ ከመምህራን እንቅስቃሴ ተገፍተን ወደ ፖለቲካው መስመር ውስጥ ገባን። የመምህርነት ሥራዬ ሙሉ ለሙሉ ቢቆምም የፖለቲካ ሥራዬን ቀጠልኩ። በዚያ መሠረት አውራጃውን የማገናኘው እኔ ነበርኩ።
በነገራችን ላይ ከእነሱ ጋር በማደርገው ትግል የነበረኝ የትምህርት ማስረጃ ሁሉ ተወስዶብኝ ነበር። ነገር ግን እያስተማርኩ የተፈተንኩት የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤቴን አዲስ አበባ መጥቼ ከትምህርት ሚኒስቴር መውሰድ ቻልኩ። እናም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት ጥረት አደረኩኝ። በወቅቱ ደግሞ አዲስ አበባ ላይ የደርግ ኃይል በርካታ ወጣቶችን እየጨረሱ የነበረበት ጊዜ ነበር። ያንን ጊዜ ሳስታውስ ከአሁኑ ሁኔታ ጋር ይመሳሰልብኛል። ልክ አሁን ላይ በኮሮና ምክንያት ሰው መንቀሳቀስ ፈርቶ ቤቱ እንደከተመው ዓይነት ሰው በመንገድ ላይ አይታይም ነበር። ይልቁንም ከተማዋ በወታደር ተወራ ነበር። ወጣት በመሆንሽ ብቻ ችግር ይደርስብሻል። ያ አስፈሪ ሁኔታ ቢኖርም ግን በሐርጌ ሊያጋጥመኝ የሚችለውን እስራት በመሸሽ በቀጥታ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሄጄ ተመዘገብኩኝ። ይሁንና ተመዝግበን በቆየንበት ጊዜ ውስጥ ሃዋሳ ላይ አዲስ መለስተኛ እርሻ ኮሌጅ ይከፈትና የምትፈልጉ ሰዎች አመልክቱ ሲባል ተሽቀዳድሜ ገባሁ። ምክንያቱም እንዳልኩሽ በወቅቱ ከሐረርጌ በላይ አዲስ አበባ ችግር ነበር። የመንግሥቱ ደጋፊዎችም ሊያጋልጡኝ ስለሚችሉ ወደ ሃዋሳ ለዲፕሎማ ተመዝግቤ እዛ ገባሁ።
አዲስ ዘመን፡- የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲውን ትምህርት ትተው ማለት ነው?
ረ/ፕሮፌሰር ደምመላሽ፡- አዎ፤ ሃዋሳ ከሄድኩም በኋላም ቢሆን ግን በድርጅት ውስጥ የታቀፍን ስለነበር
ፈልገውኝ አገኙኝና የኮሌጁን እንቅስቃሴ እንዳቀነባብር ተነገረኝ። እዚያም በኢህአፓ ስር ኮሌጁን ከከተማው እንቅስቃሴ ጋራ የማገናኘው እኔ ነበርኩ። ወቅቱ ታዲያ እንደሚገድሉኝ ባውቅም ከመሞቴ በፊት አንድ ነገር ማድረግ አለብኝ የሚል ቆራጥ አቋም ነበረኝ። በመሆኑም ከትምህርቱ በላይ የትግል እንቅስቃሴውን ለመምራት ነበር ጊዜዬን አውል የነበረው። እንዳሰብኩት ሃዋሳም ቢሆን የመታፈስና የመደብደብ ሁኔታዎች አጋጥመውኛል። እናም አንድ ቀን በእንቅስቃሴ ውስጥ እያለሁ ተያዝኩኝ። ይሁንና ብዙም ሳልቆይ ከእስር ቤት አምልጬ ወጣሁኝ። ከሃዋሳ ሻሸመኔ፥ አርሲ ነገሌና አዳማና አዲስ አበባ እየተዘዋወርኩ እንቅስቃሴን ቀጠልኩ። ከዚያም ለመጠለል ወንድሜ ወደሚገኝበት ወደሃብሮ አውራጃ ሄድኩኝ። እዛም ሆኜ ሃንጫር በሚባል ወረዳ ውስጥ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ለማደራጀት ሙከራ በማደርግበት ጊዜ በጥይት ተመታሁ። እናም አዲስ አበባ አምጥተው የማዕከላዊ እዝ ክቡር ዘመኛ ሆስፒታል ውስጥ አስገቡኝ። እግሬን ሁለት ጊዜ ቆርጠው እንደማይሆን ሆኜ ተረፍኩ፡፡
አዲስ ዘመን፡- እግሮት ላይ ብቻ ነበር የተመቱት?
ረ/ፕሮፌሰር ደምመላሽ፡- አዎ፤ ግን ጥንቃቄ ስላላደረጉልኝ ከማከም ይልቅ መቁረጥ ምርጫቸው አደረጉ። ምክንያቱም በዚያ ጊዜ በሱማሌ ጦርነት የቆሰሉ በርካታ ወታደር ስለነበሩ ቀላሉ መንገድ እግሬን መቁረጥ ነበርና ቆረጡኝ። ሆስፒታል ውስጥ ጠባቂ ተመድቦልኝ ነበር። እግሬን የቆረጠኝ ራሺያዊው ዶክተር መዳኔን ነገራቸውና ሦስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ወሰዱኝ። በመቀጠልም በምን ምክንያት እንደሆነ ባለማውቀው ሁኔታ ጉድሼፐርድ የሚባል ማገገሚያ ማዕከል ውስጥ በእስረኝነት እንድገባ ተደረኩኝ። እዚያ ማገገሚያ ውስጥ ያሳለፍኩት ጊዜ በጣም ከባድ ነበር። ነገር ግን ከሚሊሻዎች ጋር መተዋወቅ ጀመርኩ። ለአንድ ዓመት ያህል ቆየሁ። እዛ እያለሁ ሁሉም ወታደር ለሕዝቡ ጠላት እንዳልሆነ ጥቂት ከአመራሩና ከካድሬው በስተቀር ሠራዊቱ የሕዝብ
መሆኑን ተገነዘብኩ። በድፍን ወታደሩን ሁሉ መጥላት እንደሌለብኝ ተረዳሁኝ፡፡በእርግጥም ከሚሊሻዎቹ ጋር ስቀራረብ እስረኝነቴ እየተረሳ መጣ።
እያደር እያገገምኩኝ ስመጣ ያገገሙ ሰዎች ወደሚላኩበት ጀግኖች አምባ ወደሚባል ቦታ እንደምሄድ አወቅሁኝ። ይህ ደግሞ ለእኔ አደጋ ነው የሚፈጥርብኝ፤ ምክንያቱም ተቃዋሚ መሆኔ ይገለጥ ነበርና ነው። ስለዚህ ድሬዳዋ በምትኖር እህቴ አጋዥነት የመውጫ ደብዳቤ አስመስለን አረቀቅን፤ የኃላፊውን ፊርማ አስመስለን ፈረምን። እናም ከሚሊሻዎቹ ጋር ሆነን ማህተም አድርገን አገግሞ ጨርሷል የሚለውን ደብዳቤ ያስኩኝ። በተጨማሪም የልብ ልብ ስለተሰማኝ ያቋረጥኩትን ትምህርት እንድቀጥል ከሚሊሻዎቹ ጋር ተናግሬ ከአንድ ኮሎኔል የማዕከላዊ አዛዥ ከነበሩና የዘመቻ መምሪያ ኃላፊ ከነበሩ ኃላፊዎች ጋር ቀረብኩኝ። እንደአጋጣሚ ሆኖ ግን የእሳቸው ጠባቂ የሆነ እኔ እግሬ ሲቆረጥ ይጠብቀኝ የነበረ ፖሊስ ኖሮ ያስታውሰኝና ከሐረርጌ በፀረ አብዮት ተመቶ የመጣ ነው ብሎ ነገረብኝ። የዚያን ጊዜ በሞት ውስጥ የምንቀሳቀስ ብሆንም ጠባቂው ሲያሳብቅብኝ ትንሽ ተደናገጥኩኝ። በኋላ እንደማጭበረብራቸው ቢገባቸውም ውጪ ጠብቀኝ አሉኝና የሆነ ፎርም ሞልተው ከማገገሚያው እንድወጣ ፈቅደው ደብዳቤ ሰጡኝ፡፡
ጀግኖች አምባ ብገባ ኖሮ ግን ጉዴ ይፈላ ነበር። ግን አመለጥኩኝ። በዚያ ጊዜ ታዲያ በሚሊሻዎቹ ስም ሰው ሰራሽ እግር ሁሉ ተገጥሞልኝ ነበር። እናም ማመልከቻዬን ይዤ ደብረዘይት እርሻ ኮሌጅ ያለመልቀቂያ ገባሁ። እዛም ከማንም ሰው ጋር ሳልገናኝ ሁለት ዓመቱን ጨርሼ በጥሩ ውጤት ዲፕሎማዬን አገኘሁ። የሚገርምሽ እዛ ሆኜም አብረውም የታሰሩ ሚሊሻዎች ቢያገኙም ተመካክረን አንድ ነገር ሳይተነፍሱ ትምህርቴን ለመጨረስኩ ቻልኩ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከዚያ ወዲህ ትግሉን እርግፍ አድርገው ተዉት?
ረ/ፕሮፌሰር ደምመላሽ፡- አዎ፤ እግሬን ከተመታሁ በኋላ ትኩረቴን ራሴን ወደ ማዳኑ ነው ያደረኩት። ደግሞም ከፍተኛ ውጤት ስለነበረኝ እዛው እንድቀር ተደረገ። እዛው እያለሁ የውጭ አገር የትምህርት ዕድል መጣ። በወቅቱ ሃረማያ ዲግሪዬን ለመማር አመልክቼ ነበር። ነገር ግን በአንድ ጓደኛዬ ምክር የውጭ ትምህርት ፎርም ሞላሁ። ይህንን ሁሉ ሳደርግ የነበረው ግን ከፀረ አብዮተኝነት ተደብቆ አብዮተኛ ነው የሚለውን ያንን ደብዳቤ ይዤ ነው። የውጭ ዕድሉ ሲመጣም ያቺን ወረቀት በመያዝ ድጋፍ ማሰባሰብ ቻልኩ፤ አለፍኩኝ። ነገር ግን አውሮፕላኑ እስኪነሳ ድረስ ነፃ መሆኔን እጠራጠር ነበር። ምክንያቱም በርካታ ጓደኞቼ በተመሳሳይ መንገድ ወደ ውጭ ሊሄዱ ሲሉ ከአውሮፕላን ያስወረዷቸውና የገደሏቸው መሆኑን አውቅ ስለነበር ነው። ከዚያ ጊዜ ወዲህ የፖለቲካው ነገር ቆመ።
ሃንጋሪ ከአስር ዓመት በላይ ቆየሁ። ወደ አገር ቤት የመመለስ እቅድም አልነበረኝም። ምክንያቱም የነበረው ሥርዓት እስካልወረደ ድረስ በሰላም ሊያኖሩኝ አይችሉም የሚል እምነት ስለነበረኝ ነው። የማስተርስ ፕሮግራሜን በኢኮኖሚክስ እንደጨረስኩኝ በዚያን ጊዜ የሶሻሊዝም ሥርዓት ጎበዝ የሆነ ከፍተኛ ውጤት ያለው በቀጥታ ዲግሪ ሳይማር ማስተርስ ማመር ይችል ነበር። በሁለተኛ ጊዜ በዚያው መስክ የዶክትሬት ዲግሪ ያዝኩ። ትምህርቴን እንደጨረስኩ ግን ደርግ ወደቀ። ወደ ሀገር ቤት ከመመለሴ በፊትም ያለፍንበትን የፖለቲካ ሁኔታ የመመርመር የማገናዘብ ዕድል ነበረኝ። ሶሻሊዝም ምን ያህል የወደቀ ሥርዓት መሆኑን አመንኩ። መንግሥት ቢቀየርም ብሔር ላይ መሠረት ያደረገውን ፖለቲካ አልወደድኩትም ነበር። ጭንቅ ሲለኝ አሜሪካ ኤምባሲ ሄጄ አመለከትኩኝ። የሁለት ዓመት ቪዛ ሰጡኝ። በሌላ በኩል በእኔ ምክንያት ብዙ መከራ ያሳለፉ ወላጆቼን አሰብኩና ሳይሞቱ ላያቸው ይገባኛል ብዬ ቪዛውን ይዤ ወደ አገሬ ተመለስኩ።
እዚህ እንደመጣሁም በሰራሁበት ሃረማያ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ አመለከትኩና በፈተና ተቀበሉኝ። በረዳት ፕሮፌሰርነት አራት ዓመት አገለገልኩኝ። ቤተሰቦቼን ልረዳ ብመጣም ደመወዙ ጥሩ ስላልነበር ራሴ ተረጂ ሆንኩኝ። በዚያ ወቅት ደመወዜ 1ሺ600 ብር ነበር። መጨረሻ ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ማስታወቂያ ያወጣል፤ ደመወዙ አራት ሺ ብር እንደሆነ ሰማሁ። አመለከትኩና አልፌ ተቀጠርኩኝ። እ.ኤ.አ ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ በማገልገል ላይ እገኛለሁ። ያ የአሜሪካ ቪዛ ለመጠባበቂያ ነበር የያዝኳት። ምንአልባት ወያኔ እኔ ብቻ ነኝ ታጋይ ስለሚል ይይዘኛል የሚል ስጋት ነበረኝ። ነገር ግን ብገላመጥም ማንም ዞር ብሎኝ አያውቅም። በዚህ ምክንያት እዚሁ ቀረሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡- እንደኢኮኖሚ ባለሙያ ኮሮና መምጣት ጋር ተያይዞ ዓለም ላይ የፈጠረው የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ኢትዮጵያን በምን ያህል ደረጃ ይጎዳታል ይላሉ?
ረ/ፕሮፌሰር ደምመላሽ፡- እንደምታውቂው ይህ በሽታ የመጣው አገሪቱ በራሷ ችግሮች በተጠመደችበት ጊዜ ነው። ፖለቲከኞች በአገሪቱ ላይ ባለመስማማታቸው ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት በደረሰበት ሁኔታ ነው የመጣው። ይህም በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚባለው ዓይነት ነው የሆነብን። ይህ በሽታ የዓለም ሀገራት ራስን ከመከላከል አልፈው ወደ ከፍተኛ መቀዛቀዝና ድብርት ውስጥ ሊሸጋግራቸው የሚችልበት ዕድል አለ። የእኛ ኢኮኖሚም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከደረሰው ጉዳት አያመልጥም። ምክንያቱም እኛ እቅዳችን ይህንን የግብርና ማህበረሰብ ወደ ኢንዱስትሪ የማሸገጋር ነው። ወደኢንዱስትሪ የምናደርገውን ሽግግር ልናመጣ የምንችለው የነበረው እኛ እሴት ያልተጨመረባቸውን ምርቶች ልከን ኢኮኖሚያችንን ወደ ኢንዱስትሪ መር ለመውሰድ ነበር ጥረት ስናደርግ የነበረው። አሁን ላይ ከዚህ በሽታ ጋር ተያይዞ ይህ ጥረት ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ቆሟል። በተለይ ድሮውንም በጣም ዝቅተኛ የነበረው የውጭ ንግዱ ተዳክሟል። ባሰብነው ኢንዱስትሪ ሽግግሩን ባላካሄድንበት ሁኔታ መፈጠሩ ይቺኑ የምናገኛትን የውጭ ምንዛሬ የምናጣበትን አደጋ ፈጥሮብናል። በሌላ በኩል በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በተፈጠረው ችግር ምክንያት ሥራ አልባ ሆነዋል። በዚህ ምክንያት ወደዚህ ይልኩት የነበረው ሬሜታንስ ሊቀንስ ይችላል፡፡
ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንትም በአሁኑ ጊዜ ይመጣል ብሎ ማሰብ ይከብዳል። እርዳታና ብድር የምናገኝበትም ተስፋ ተመናምኗል። ምክንያቱም እርዳታና ብድር የሚሰጡት እራሳቸው ችግር ውስጥ ናቸው። ስለዚህ ከውጭ የሚመጣው ፋይናንስ እያዘቀዘቀ ነው የሚመጣው። ይህም ወደኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ የምናደርገው ጉዞ ይገታል። ይህም ሆኖ ግን የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ያወጣው ሪፖርት የሚያሳየው በዚህ ሁሉ ውጣውረድ ውስጥ ኢትዮጵያ እድገት መታየቱን ነው።
ምክንያቱም እድገቱ በግብርና ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ጥሩ ዝናብ ስለነበርም ነው የተመዘገበው። የኮንስራክሽን ዘርፉ አጠቃላይ እንቅስቃሴ ምንም እንኳ ከበፊቱ አንፃር የቀነሰ ቢሆንም ከአፍሪካ አገሮች አንፃር አሁን ፈጣን እድገት አስመዝግበናል። ይህ ማለት ኮሮና ኢኮኖሚውን አልጎዳውም ማለት አይደለም። በጣም ጎድቶትም እያለ ግን ተፈጥሮ ችግር ስላልፈጠረችብን ውጤት አይተናል። አሁን ያለንበት ሁኔታ በጣም አሳሳቢ ነው። አሁን ባለንበት ሁኔታ እድገታችን ቢያንስ ቢያንስ ወደ ሦስት በመቶ ሊቀንስ ይችላል።
አሁንም ቢሆንም ተስፋችን ግብርና ነው። የበሽታውን እንቅስቃሴ ስንመለከት ገና ገጠሩን እያጠቃ አይደለም። በሌሎች አገራትም ስንመለከት ከፍተኛ የሰው ክምችት ባሉባቸው አካባቢዎች ነው የተንሰራፋው። በአንፃሩ የእኛ የገጠሩ አሰፋፈር ርቀት ያለው መሆኑ ለዚህ በሽታ ጥሩ አጋጣሚ ፈጥሯል። አሁን የሚሰጠነን ምክር የምንተገብር ከሆነ ገጠሩ አካባቢ ያለው እንቅስቃሴ ይህንን ጊዜ ሊያሻግረን ይችላል። ያውም ጥሩ የአየር ንብረት ካጋጠመን ማለት ነው። ምርታማነትን ሊያሳድጉ የሚችሉ እንደማዳበሪያና ምርት ዘሮችን ማዳረስም ይጠበቅብናል። እናም ግብርናው ይዞን እንደሚያስወጣን አምነን እዛ ላይ ትኩረት አድርገን የምንሰራ ከሆነ ተሸክሞን ይወጣል። በተዘጋ ኢኮኖሚ ውስጥ ስለሆን ትኩረታችን ራሳችንን የምችልበት መንገድ መቀየሱ ላይ ሊሆን ነው የሚገባን፡፡
በሌላ በኩልም የኢንዱስትሪ ማኑፋክቸሪንጉም እንቅስቃሴው ተወስኗል። በመጀመሪያም በኢኮኖሚያችን ውስጥ የነበረው ድርሻ አነስተኛ ነው። አሁን እንግዲህ ከኢንዱስትሪ ውስጥ ተስፋ ልናደርግበት የምንችለው የኮንስትራክሽን ዘርፉ ነው። በዚህ ጊዜ ውስጥ ጥሩ እንቅስቃሴ ለማድረግ እንዲችልም ዘርፉ መልካም አስተዳደር ሊሰፍንለት ይገባል። ይህም በዋናነት ይህንን መንግሥት ይመለከታል። በምርጫ የመጣ መንግሥት አይደለም። ይሁንና ፈላጭ ቆራጭም አይደለም። አንድ አገር ውስጥ እድገት እንዲመጣ የግድ መድብለ ፓርቲ ሥርዓት ሊኖር ይገባል። አሁን ያለው መንግሥት ያልተመረጠም ቢሆን ለልማት ቁርጠኛ እና የሚሰራ እስከሆነ ድረስ ድጋፍ መስጠት አለብን፡፡
አዲስ ዘመን፡- ታዲያ ኢኮኖሚው እንዲያ ንሰራራ በቅድሚያ ሊወሰድ ይገባል የሚሉት እር ምጃ አለ?
ረ/ፕሮፌሰር ደምመላሽ፡- እንግዲህ ተስፋችን ግብርና ነው ካልን ሥርዓቱን ማስተካከል ይገባል። ገበሬው ኃላፊነት እንዳለበት ማሳወቅ ያስፈልጋል። ይህ ወቅት ትርፍ የሚያስገባበት ሳይሆን ሕዝብን የሚመግብበት መሆኑንና ትልቅ ተልዕኮ እንደተሸከመ መረዳት ይገባዋል። ይህንን ተልዕኮ እንዲያሟላ መንግሥት መደገፍ ይጠበቅበታል። ልክ አሁን ላይ ኮሮናን ለመከላከል ከጤና ጥበቃ ግንዛቤ ማስጨበጫ እንደሚሰራው ሁሉ ለገበሬው በግብርና ሚኒስቴር በኩል በየቀኑ ተልዕኮውን እንዲያውቅ ማድረግ ያስፈልጋል። በዚህ አስጨናቂ ጊዜ ተስፋችን አርሶ አደሩ መሆኑን ተገንዝቦ ምርት በጥሩ ሁኔታ የሚደርስበትን መንገድ ማዘጋጀት ይገባል ።
በተጨማሪም ገጠሩ ከከተማው ጋር ያለውን የገበያ ትስስር ማሳለጥ ለዚህ ደግሞ እንቅፋት በሚሆኑት ላይ እርምጃ የመውሰድ ሥራ ማከናወን ይገባዋል። በሌላ በኩል ለገበሬው የመሬቱ ጉዳይ ዋና ጉዳይ ነው። መሬት የኢኮኖሚ አንድ መሰረት ነው። እዛ አካባቢ ላይ ቢያንስ በአሁኑ ጊዜ ገበሬው የመጠቀም መብት እንድኖረው እንደተደረገ ሁሉ በመሬቱ ላይ የባለቤትነት መብቱንም ማረጋገጥ የሚቻልበትን መንገድ ማመቻቸት ያስፈልጋል።
ደግሞም የመንግሥት መሬት ልኩ መታወቅ አለበት። ስንት ነው የመንግሥት መሬት?። የአነስተኛ ገበሬውስ? የማህበራትስ የቱ ነው? መለየትና መታወቅ አለበት። ይህ በአገር ደረጃ መታወቅ አለበት። አለበለዚያ ሲቸበችብ ነው የሚኖረው። ምክንያቱም መንግሥት የእኔ ነው በሚል አዲስ አበባ ላይ እንዳየነው ሁሉ የፈለገውን ሊያደርግ የሚችልበት እድል ሰፊ ነው። ይህ ሲባል ግን መንግሥት አያርስም ማለት አይቻለም፤ ለእርሻ፥ ለደንም ሆነ ለሌሎች ልማት የሚውሉትን መሬቶች በአግባቡ መታወቅ ይገባቸዋል። ገበሬው ይህንን ኃላፊነት እንዲወጣ የባለቤትነት መብቱ መረጋገጡ ትልቅ ጠቀሜታ ይኖረዋል።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉና በአንባቢዎቼ ስም ከልብ ለማመሰግን እወዳለሁ፡፡
ዶክተር ደምመላሽ፡- እኔም አመስግናለሁ።
አዲስ ዘመን ግንቦት 1/2012
ማህሌት አብዱል