ተወልዶ ያደገባትን የወልቂጤ ከተማ እስከ አስረኛ ክፍል ተምሮባታል። የልጅነት ህይወቱ በችግር የተፈተነ ነበር። የቤተሰቦቹ አቅም ማጣት በምቾት ባያኖረውም በትምህርቱ እስከ አስረኛ ክፍል ዘልቋል።
መሀመድ ሙሄ በዕድሜው ከፍ ማለት ሲጀምር በትምህርቱ በኩል ተስፋ እንደሌለው ተረዳ። አመታትን ያሳለፈበት የቀለም ትምህርት ከውጤት የሚያደርስ ዋጋ አልነበረውም። እንደ እኩዮቹ ከዩኒቨርሰቲ መድረስ እንዳልቻለ ሲገባው ቆም ብሎ አሰበ። ከዚህ በኋላ የትውልድ ቀየውን ለቆ ካልወጣ በኑሮው ለውጥ እንደማይኖር አወቀ።
በጉዳዩ ደጋግሞ ሲያስብ የቆየው ወጣት አንድቀን ጓዙን በወጉ ሸከፈ። ወደ አዲስ አበባ መንገድ ሲጀምር በስፍራው ያሉትን ያገሩን ልጆች እያሰበ ነበር። እነሱ በአመት አንዴ ብቅ ባሉ ጊዜ አምሮባቸው አይቷል። አለባበስና አነጋገራቸው ከተሜ በመሆኑም ብዙዎች እንዳተኮሩባቸው አስተውሏል። እሱም ቢሆን እንደእነሱ መሆን የተመኘበት ጊዜ ነበር።
አዲስ አበባ እንደደረሰ የሊስትሮነት ስራውን ጀመረ። እሱን ጨምሮ በርካታ ያገሩ ልጆች በሚገኙበት ግንፍሌ ሰፈር እየኖረም ከብዘዎች ተግባባ። በስራው አጋጣሚ የሚያገኛቸው ደንበኞቹ ሲበዙ ለራሱ የሚሆን ጥሪት መያዝ ቻለ። አንዳንዴ አገር ቤት እየሄደ ወላጆቹን ይጠይቃል። ካገሩ ሲመለስ ግን የኪሱ ባዶ መሆን ያስጨንቀዋል።
የሊስትሮነት ስራና መሀመድ ከተገናኙ ጊዜያት መቆጠር ይዘዋል። ከእጅ ወደ አፍ የሆነው ገቢ ከዕለት ወጪና ከቤት ኪራይ ክፍያ ጋር ሲዳመር እምብዛም ትርፍ የለውም። መሀመድም ቢሆን ይህ አይነቱ የህይወት ምልልስ የተመቸው አይመስልም። እሱ እንደሚያውቃቸው አንዳንዶች ኑሮውን በፍጥነት መለወጥ ይፈልጋል። ዛሬ ሊስትሮ ቢሆንም ነገ ደግሞ በተራው ጫማውን በሌሎች ማስጠረግን ይሻል ።
ሁሌም አገሩ ሳለ ገጠር ይመጡ የነበሩ ከተሜዎች ትዝ ይሉታል። ጫማና ልብሳቸው፣ መልክና ጠረናቸው ሁሉ የተለየ ነበር። እነሱን ባስታወሰ ጊዜ ግን አሁን ላይ የቆመበትን የህይወት መገኛ ከልቡ ይጠላዋል። እናም የሊስትሮነት ስራውን እንዴት መቀየር እንደሚችል እያሰበ ሲብከነከን ይውላል።
መሀመድ ከተማውን ለምዶ መውጫ መግቢያውን ሲለይ የአንዳንዶችን መዋያና የገንዘብ መገኛ ምንጮችን አወቀ። ጉዳዩን በግልጽ በተረዳ ጊዜም ከእነሱ ለመቀላቀል አላንገራገረም። እሱ ወር ሙሉ ደክሞ የሚያገኘውን እጥፍ በደቂቃዎች ሊያገኙት ይችላሉ። እናም ወጣቱ ሊስትሮ ትርፍና ኪሳራውን ደጋግሞ አሰላ። ሚዛኑ ወደስርቆቱ አደላበት።
አሁን መሀመድ ከሊስትሮ ዕቃው ጋር የሚውልበት ጊዜ እየቀነሰ ነው። አልፎ አልፎ ብቅ እያለ ለመስራት ቢሞክርም በርካታ ጊዜውን ለስርቆቱ ይሰጣል። ከትናንት በተሻለ ዛሬ ኪሱ በገንዘብ ተሞልቷልና ደስተኛ ነው። የሚነጠቅና የሚዘረፍ በጠፋ ጊዜ ደግሞ ወደ ቀድሞ ሥራው ተመልሶ ጫማ ሲጠርግ ይውላል። ይህ አንገት ደፊነት ግን ከፖሊስ ተጠራጣሪ ዓይኖች አላዳነውም። በስርቆት ወንጀል ተከሶ ለእስራት ማረሚያ ቤት ወረደ።
የእስር ጊዜውን አጠናቆ ከማረሚያ ቤት ሲወጣ ወደቀድሞው ሊስትሮነት መመለስ አስጠላው። ጥቂት ቀናትን አሳልፎ ልቡ ለመንገድ ሸፈተ። ርቆ መሄድ የፈለገው እግሩ ድንበር አቋርጦ ወደ ሱዳን አደረሰው። የሰው አገር ሰው መሆኑ ያሰበውን ያህል አላራመደውም። ጥቂት ቆይቶ አዲስ አበባ ተመለሰ። ነገን ምን ማድረግ እንዳለበት እያሰበም ከአንድ መንደር ለቀናት ተቀመጠ።
በየነ ታሪኩ፡-
ወሎ ተንታ ከሚባል ስፍራ የተወለደው በየነ የቤተሰቦቹ ችግር የከፋ መሆን በድህነት እንዲዘልቅ አስገድዶታል። በልጅነቱ እንደእኩዮቹ ትምህርትቤት የመሄድ እድል አላገኘም። በአቅሙ መጠንከር ሲጀምር ደግሞ ወላጆቹን በስራ መደገፍ ነበረበት። እህት ወንድሞቹን ጨምሮ መላው ቤተሰብ በቂ የሚባል ገቢ የላቸውም። በዚህ ሳቢያም ከእጅ ወደአፍ የሆነ ህይወትን ሲገፉ ቆይተዋል ።
በየነ ከልጅነቱ ጀምሮ ከአዲስ አበባ የሚመጡ አክስቱን ያውቃቸዋል። እነሱን ለመጠየቅ ገጠር በደረሱ ጊዜም የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ ቋጥረው ያመጡላቸው ነበር። ለእሱና ለወንድም እህቶቹ የሚገዙላቸው ልብስም አመታተን በስስት እየለበሱት ኖረዋል።
ልጅ እያለ የአክስቱን የከተማ ህይወትና የኑሮ ደረጃ በተለየ ሁኔታ ሲስለው ቆይቷል። በእሳቸው ምክንያትም አዲስ አበባን በመልካም እያሰበ ሲናፍቀው ነበር። ከፍ እያለ ሲሄድ ከተማ ገብቶ መኖርን ይመኝ ያዘ። ይህን ፍላጎቱን ያወቁ አክስትም ሁሉን አመቻችተው ከእሳቸው ዘንድ እንደሚወስዱት ቃል ገቡ። በሌላ ጊዜ የነበየነ አክስት ገጠር ሊጠይቋቸው መጡ። ይህኔ እሱን ጨምሮ ታናሽ እህቱ አብረዋቸው ለመሄድ ጓዛቸውን ሸክፉ።
የሁለቱን ከተማ ለመሄድ መነሳት ያወቁ ወላጆች ሀሳባቸውን ከልብ ደገፉ። ልጆቻቸው ነገን ሰርተው ከድህነት እንዲያወጧቸው እያሰቡም በዕንባና ምርቃት ሸኟቸው። በየነና እህቱ አክስታቸውን ተከትለው አዲስ አበባ ገቡ።
እህትና ወንድም ከሰፊው የገጠር ሜዳ ርቀው ድምቀት ወዳጀበው አካባቢ ሲዘልቁ ለጊዜው ግርታ ቢጤ አስጨነቃቸው። ቆይቶ ግን ሁሉን ለምደው ከብዙዎች ተግባቡ። ኑሮን በአክስት ቤት የጀመሩት እነበየነ የአዲስ አበባ ህይወት ተመችቷቸው የደስታ ህይወትን ቀጠሉ።
ጥቂት ቆይቶ ግን ኑሯቸውን ከስጋት የሚጥል አጋጣሚ ተፈጠረ። በድንገት የታመሙት አክስት በሽታቸው በረታ። ህክምና ጤናቸውን አልመለሰውም። ድንገቴው ሞታቸው በርካቶችን አስደነገጠ። ከሁሉም ግን የበየነና የታናሽ እህቱ ዕጣ ፈንታ አሳሳቢ ሆኖ ሁኔታዎች ተቀየሩ። እህትና ወንድም ከአክስታቸው ሞት በኋላ ሰብሳቢ አጡ። መተዳደሪያ የሚሆን የዕለት ጉርስ መጥፋቱም ከከፋ ችግር ላይ ጣላቸው።
በየነ እህቱን ለማስተዳደር የሸክም ስራ ጀመረ። ድካሙና የሚያገኘው ገንዘብ አልደራረስ ቢለው ግን ተጨማሪ ስራዎችን ፈለገ። በቀላሉ ማግኘት አልሆነለትም። ቆይቶ ወደቤት መመለስ አቆመ። አውቶቡስ ተራ መንገድ ላይ ከሚገኝ አሮጌ የስልክ ቤት እያደረም የጎዳና ህይወቱን ቀጠለ። ቆይቶ ግን ሌላ መላ ማሰብ ያዘ። ባመቸው ጊዜ የሚሞክረው ስርቆት አዋጣውና ገፋበት።
ስምኦን ታዬ፡-
የአዲስ አበባው ልጅ ስምኦን ታዬ ተወልዶ ያደገው ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ አካባቢ ነው። ወላጆቹ እሱን ለማስተማር አቅሙ ነበራቸው። በልጅነቱ የጀመረው ትምህርት እስከ አስረኛ ክፍል አድርሶታል። በትምህርቱ እምብዛም ብርቱ አልነበረም። ወላጆቹ ግን ከእሱ ብዙ ሲጠብቁ ቆይተዋል።
ማትሪክ ከወሰደ በኋላ ውጤቱ ለዩኒቨርሲቲ አላበቃውም። ለወራት በተማረበት የቴክኒክና ሙያ ትምህርት የሚመጥን ስራ ማግኘት አልቻለም። ቁጭ ብሎ ሲውል ሰዎችን ተዋወቀ። ያወቃቸው ባልንጀሮቹ ስርቆት የለመዱ ነበሩ። ውሏቸውን ሲያውቅ አብሯቸው ተንቀሳቀሰ። እንደዋዛ የጀመረው ድርጊት እየጣመው ሲመጣ ቦታና ሰዓት እየመረጠ በርካቶችን በመደብደብ መዝረፉን ቀጠለ።
ስምኦን ስራ የመፈለግ ሙከራውን እርግፍ አድርጎ በሌብነት ከተሰማራ በኋላ የልቡ ደረሰ። የሚያገኘውን ገንዘብ እየመነዘረም ለሚፈልገው ዓላማ ያውለው ያዘ። አንድ ቀን ግን ሲስረቅ ተያዘና ከፍርድ ቤት ቀረበ። ፍርድቤቱ ሌብነቱን በማስረጃ አረጋግጦ እስራት ወሰነበት። ከሁለት አመት በላይ ሸዋሮቢት ማረሚያ ቤት ቆይቶ ሲወጣ በአዲስ መልክ የስርቆት ስራውን የሚጀምርበትን ስልት መንደፍ ያዘ።
ሦስቱ፡-
የስርቆት አጋጣሚ ያገናኛቸው መሀመድ፣ በየነና ሰምኦን ጓደኛሞች ከሆኑ ቆይተዋል። ቀኑን ተቀምጠው ሲውሉ ምሽቱን ስለሚያካሂዱት ዘረፋ ይመክራሉ። በለስ ቀንቷቸው ገንዘብና ንብረት ሲያገኙም በእኩል ተካፍለው ከጥቅሞቹ ይጋራሉ።
ሦስቱ ባልንጀሮች ዕድገትና ኑሯቸው የተለያየ ነው። በዝርፊያ ምክንያት የቆዩበት የማረሚያ ጊዜ ግን ቋንቋና ልምዳቸውን አንድ አድርጎ ሊያመሳስላቸው ግድ ብሏል። ሶስቱ በተለያየ ጊዜ ቢታሰሩም የሌብነትን አውነታ ያውቁታል። ሲሰርቁ እንደሚያዙና ሲፈረድባቸውም እንደሚታሰሩ አይጠፋቸውም። ከተፈቱ በኋላ ግን መልሰው ከቦታቸው ይገኛሉ። በለመዱት መንገድ ተሰማርተውም እየደበደቡና እየነጠቁ ያሻቸውን ይፈጽማሉ።
ጥቅምት 2 ቀን 2009 ዓ.ም ቦሌ መንገድ፡-
የጥቅምት ወር ገና መግባቱ ነው። ቅዝቃዜ የዋለበት ቀን ምሽቱንም ቀጥሎ ብርዱ ማንዘፍዘፍ ይዟል። ሦስቱ ባልንጀሮች የማታውን ተግባር ለመፈጸም ቦታ ለይተው የጨረሱት ጀንበር ሳትጠልቅ ነው። አየሩ እንዲህ ቅዝቃዜና ዝናብ በሚሆንበት ጊዜ የሚዘርፉባቸውን ቦታዎች ለይተው ያውቋቸዋል። ለዛሬው ዕቅዳቸው የመረጡት ቦታም የቦሌን ጎዳና ሆኗል።
በዚህ ስፍራ በምሽቱ ጊዜ ማን ቀድሞ እንደሚገኝ አያውቁም። እነሱ ግን አስቀድመው የተከራዩትን ሚኒባስ ታክሲ ይዘው በአካባቢው ማንዣበብ ጀምረዋል። መገኛቸውን መስቀል ፍላወር አድርገው አይናቸውን ወደቦሌ መንገድ የጣሉት ዘራፊዎች አሁንም ብቅ የሚል ሰው እየፈለጉ ዙሪያ ገባውን መቃኘት ይዘዋል።
አሁን ከምሽቱ አራት ሰዓት ተኩል ሆኗል። በመንገዱ የሚያልፉ እግረኞች ቀስ በቀስ ወደቤታቸው መግባት እንደያዙ መንገዱ ጭርታውን ተቀብሎ በጸጥታ መተካት ጀምሯል። ድንገት ከአስፓልቱ ጠርዝ የቆሙት ሁለት ወንድና ሴት የቦሌን ጠርዝ መያዛቸውን ያስተዋሉት ሶስቱ ባልንጀሮች ዓይናቸውን ጥለው ፍላጎታቸውን አጤኑ። ወጣቶቹ ወደቦሌ አቅጣጫ ለመሄድ የትራንስፖርት አማራጭ እየፈለጉ መሆኑን ደረሱበት።
ከቆሙበት መስመር ወደሁለቱ አቅጣጫ ማምራት የጀመሩት ሶስቱ አጠገባቸው ከመድረሳቸው አስቀድሞ ስምኦን አንገቱን ወደውጭ አውጥቶ ቦሌ፣ ቦሌ፣ ቦሌ፣ እያለ መጣራት ጀመረ። ይህኔ ሁለቱ ወጣቶች ፊታቸው በደስታ እንደፈካ እጃቸውን ዘርግተው ታክሲውን አስቆሙ። የመኪናውን መሪ የያዘው ሾፌር በትህትና እያግባባ ወደውስጥ እንዲገቡ ጠቆማቸው።
ወጣቱ ተሳፋሪ የሴት ጓደኛውን ከፊት አስቀድሞ ወደታክሲው ገባ። ውስጥ ዘርዘር ብለው የተቀመጡ ሰዎች ነበሩ። ወጣቶቹ እነሱ ዘንድ ከመድረሳቸው በፊት ከሾፌሩ ኋላ ከነበረው ባዶ መቀመጫ ላይ ጎን ለጎን ተቀመጡ። የእነሱን ቦታ መያዝ ያየው ሾፌር ወዲያውኑ ሞተሩን ቀስቅሶ በፍጥነት አሽከረከረ። ይህ ሁሉ ሲሆን አንዳች ያልጠረጠሩት ወጣቶች ታክሲውን በማግኘታቸው ራሳቸውን በዕድለኝነት ቆጥረው ጉዟቸውን ቀጠሉ።
ድንገት ከኋለኛው መቀመጫ ተስፈንጥሮ የመጣው መሀመድ ከወጣቶቹ ጀርባ ደርሶ የወንዱን አንገት ፈጥርቆ ያዘው። በዛው ፍጥነት የደረሰው በየነም እንዲሁ የሴቷን አንገት አንቆ ትንፋሸዋን አፈነው። ወዲያውኑ ስምኦን የወንዱን ደረት ደጋግሞ እየመታ አቅሙን ማዳከም ያዘ። ሁለቱ ወጣቶች ራሳቸውን መከላከል አልሞከሩም በያሉበት ፍንግል ብለው ተዘረሩ። ይህኔ ሁሉም በየተራ የወንዱን ኪስና የሴቷን ቦርሳ እየፈተሹ ያገኟቸውን ሞባይሎችና ጥቂት ገንዘብ ከእጃቸው አስገቡ። ይህ ሁሉ ሲሆን ተሳፋሪዎቹ እንቅስቃሴ አልነበራቸውም።
ሶስቱ ዘራፊዎች ጉዳያቸውን እንዳበቁ መኪናውን አዙረው ወደጨለማው ጥግ ቆሙ። ወዲያውም ወጣቶቹን ተራ በተራ እያወጡ አምባሰል ህንጻ ጀርባ ከሚገኝ መንገድ ላይ ጥለዋቸው ከአካባቢው ተሰወሩ።
የፖሊስ ምርመራ፡-
በምሽቱ በስፍራው ላይ ስለተፈጸመው የወንጀል ድርጊት መረጃ የተጠቆመው ፖሊስ በአካባቢው ደረሰ። ጉዳት አጋጥሟቸው በቦታው ላይ የተጣሉትን ወጣቶች አይቶም ለእርዳታ ፈጠነ። ቀረብ ብሎ የሁለቱንም ትንፋሽ አዳመጠ። ሴቷ በመጠኑ ትተነፍሳለች። ወንዱ ህይወቱ አልፏል።
በአካባቢው ያገኘውን መረጃ አሰባስቦ ምርመራውን የቀጠለው ፖሊስ በረዳት ሳጂን አዲሱ መቻል መሪነት ታግዞ ቡድኖችን በማዋቀር ተጠርጣሪዎችን ማሰስ ጀመረ።
በህይወት ከተረፈችው ወጣት ተጨማሪ ዋቢዎችን አክሎም በየቀኑ የሚገኙ መረጃዎችን በፖሊስ መዝገብ ቁጥር 280/09 ላይ እያሰፈረ ቆየ።
በመጨረሻ ተደጋጋሚ ወንጀሎችን ከሚፈጽሙ ተጠርጣሪዎች መሀል የሶስቱ ማንነት ተለይቶ ታወቀ። ፖሊስ ሁሉንም ይዞ ቃላቸውን ሲቀበል ድርጊቱን ሙሉ ለሙሉ ስለመፈጸማቸው በቃላቸው አምነው አረጋገጡ። በዕለቱ የዘረፏቸውን ሞባይሎችም ከሸጡበት ስፍራ መርተው አሳዩ።
ውሳኔ
መጋቢት 1 ቀን 2012 ዓ.ም በችሎቱ የተሰየመው የልደታው ከፍተኛ ፍርድቤት በከባድ የውንብድና ወንጀል ተጠርጥረው ለክስ የቀረቡትን ተከሳሾች ጉዳይ ሲመረምር ቆይቶ ለመጨረሻው ውሳኔ በቀጠሮው ተገኝቷል። ፍርድቤቱ ተከሳሾቹ የፈጸሙትን የውንብድና ወንጀል በበቂ ማስረጃዎችና መረጃዎች በማረጋገጡም የሁሉንም ጥፋተኝነት አሳውቋል። በዚህ መሰረትም እያንዳንዳቸው እጃቸው ከተያዘበት ጊዜ ጀምሮ የሚታሰብ የዕድሜ ልክ እስራት ይገባቸዋል በማለትና ውሳኔውን በማሳለፍ መዝገቡን ዘግቷል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 1/2012
መልካምስራ አፈወርቅ