ዝንጀሮ መጀመሪያ መቀመጪያዬን አለች ተብሎ ሲወራ እሰማለሁ፤ ማስቀደም ያለባትን ማስቀደም ፈልጋ ነው እንጂ ምን ሥልጣን አላትና? ፋይዳውንስ የት ታቅና? መጀመሪያ መቀመጫዬን መንበሬን ትላለች? ጥያቄውን አንባቢዎቼ መልሱት።
ያለንበት ወቅት የኮረና ወረራ በዓለም አቀፍ ደረጃ መስፋፋት ብቻ ሳይሆን ስጋት የሆነበት ወቅት ነው። ጥሮ አደሩን፣ ወዛአደሩን፣ አርሶአደሩን አርብቶ አደሩን፣ አምባሳደሩንና አመራሩን ሁሉ እያነጋገረ ያለ በሽታ ነው። የበለፀጉትንና የደኸዩትን ሀገሮች ያለ ልዩነት እያንቀጠቀጠ እና እያዘቀጠ ያለ፤ ከጭንቀትና ከሞት አልፎ ምጣኔ ሀብትም ላይ ጫናውን እያሳረፈ ያለ ክፉ በሽታም ነው።
ሰዎች የታመሙ ቤተሰቦቻቸውን ማነጋገር ቀርቶ ፊታቸውን ለማየት የሚከለከሉበት፣ የሞቱ ቤተሰቦቻቸውን በአግባቡ ሊቀብሩ ያልቻሉበት፣ ከቤተሰቦቻቸው ውስጥ አንዱ ብቻ እንዲቀብር የሚፈቀድበት፣ ተሰባስቦ እርምን ማውጣትና ሟችን መሰናበት የማይቻልበት የህመም ዓይነት። ይህም በተለያዩ ሀገሮች በመገናኛ ብዙሃን ከተላለፉ ዘገባዎች ያየነው ዕውነታ ነው።
ኮረና ጤና ላይ ብቻ ሳይሆን ምጣኔ ሀብቱንም ቢሆን የሚያንገዳግድና በሀገር ህልውና ላይ ጠባሳውን የሚያሳርፍ ክፉ ወረርሺኝ ነው። በአሁኑ ወቅት ተማሪውና መምህሩ፣ አለቃና ምንዝሩ፣ ልጅና ወላጅ ሁሉ ትኩረታቸው የዚህ በሽታ ጉዳይ ነው። መንግሥት ወረርሽኙን ለመከላከል አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጀው በሽታው ዜጎች እና ሀገር ላይ ከሚያደርሰው ጉዳት ለመታደግ ነው። ህዝብና መንግሥት በጋራ የኮረናን ወረራ ለመከላከል ጦርነት ላይ ናቸው። መንግሥት ኮረና ላይ ቁርጠኛ ሆኖ መንቀሳቀሱ ጉዳዩ አሳሳቢና የጤናና የኅልውና ጉዳይ ስለሆነ ይመስለኛል።
ባለንበት በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ የብሔራዊ ምርጫ አጀንዳ ነበረባት። ነገር ግን ኮረና የሚሉት ወራሪ መጣና አጀንዳዋን አስቀየረ፤ ሀገራችን ወረርሽኙን ለመከላከል
ብሄራዊ ጦርነት ላይ እያለች ብሄራዊ ምርጫን የመሰለ አጀንዳ ማካሄድ አትችልም። አንዳንድ ተቃዋሚዎች ግን ምርጫ መካሄድ አለበት የሽግግር መንግሥት ይመስረት የሚሉ አጀንዳዎችን ከፍተው እሪ በከንቱ እያሉ ነው።
አያድርሰውና ሀገር በጠላት ብትወረር ድንበር ለማስከበር ጦር እናዘምታለን ወይስ ጎን ለጎን ብሄራዊ ምርጫ እናካሂዳለን? ለተቃዋሚ ፓርቲዎች የማቀርበው ጥያቄ ነው። መጀመሪያ ጤናችን ደህንነታችንና ህልውናችን ይቀድማል። ሀገርን ኮረናን የመሠለ አስከፊ ወረርሽኝ ደርሶባት ምርጫ መካሄድ አለበት ብሎ መነሳሳት ለዜጎች ጤንነት ያለን ግዴለሽነት ያሳየኛል።
አንዳንዶቹም የጎሰኝነት ነጋሪት ሲጎስሙት የነበረው ለጎሳቸው ተቆርቁረው መብትና ጥቅሙን ሊያስከብሩ ሳይሆን አጋጣሚውን ተጠቅመው ሥልጣን ሊቆናጠጡበት መሆኑ የአደባባይ ሚስጢር ነው። ብዙዎች እትብታቸው ከተቀበረበት እንዲፈናቀሉ ሲደረግ ሕይወታቸውን ያጡ ነበሩበት። ስንረገጥ ስንበዘበዝ የሚል ፓርቲ መብት ማስከበር ያለበት ሲኮንነው በነበረው ጎሳ ላይ በጡጫና እርግጫ በማሳየት እንዲሁም በማፈናቀልና ሕይወት በማጥፋት አልነበረም።
አንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶች በመጪው መስከረም ምርጫ መካሄድ አለበት እያሉ የሚወተውቱት በኮረና ወረራ ዘመን ለህዝብ በመጨነቅ ሳይሆን ሥልጣን ላይ ለመቆናጠጥ ናፍቀው ነው።
ህዝብ በአደባባይ ሊሰባሰብባቸው በማይችልበት ሁኔታ ወይም በኮረና ሰበብ የህዝብ መሰባሰብ ለወረርሽኙ አመቺ ሆኖ እያለ ምርጫ መካሄድ አለበት እያሉ ማላዘን ህዝቡ የራሱ ጉዳይ እኛ በኮረና እርካብ መንበር ላይ እንውጣ እንደማለት ነው። ለመቃወም ብቻ ብለው በጋራ መግለጫ የሰጡ የጎሪጥ የሚተያዩ ፓርቲዎችንም አይቻለው። ይህ ለኔ አህያና ጅብ በጋራ የሰጡት መግለጫ ይመስለኛል።
ከለውጡ በፊት ከውጪ ሆነው የሀገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር የጠበበ ነው ያሉ ሁሉ፤ ከለውጥ ወዲህ የፖለቲካ
ምህዳሩን ለማስፋፋት ጥረት ተደረገና ተቃዋሚ ከሚለው ስያሜ ይልቅ ተፎካካሪ የሚለው ስያሜ ተሰጣቸው። አንዳንዶቹ የአውራው ፓርቲ ተቃዋሚ መስለው በህዝቦች መካከል ግጭት እየፈጠሩ አውሬ ሆነው ተገኙ። በዚህ እኩይ ጎዳና ከቀጠሉ ወደፊት ያማራቸው አውራ ፓርቲ መሆን ይቀርና ጭራ ፓርቲ ሆነው እንዳይቀሩ እሰጋለሁ።
ተፎካካሪዎች ምንግዜም ለዜጎች ለሀገርና መንግሥት ማሰብ አለባቸው፤ መንግሥት ከፊቱ ሦስት ጦርነቶች አሉበት አንደኛው ድህነትን መዋጋት፣ ሁለተኛው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሲሆን ሦስተኛው ደግሞ አሁን የተከሰተብን ዓለም አቀፉ የኮረና ወረርሽኝ ነው። ለእነዚህ ጉዳዮች ከሀገር ከህዝብና መንግሥት ጎን ሊቆሙ ግድ ነው።
ለሀገሪቱ ባዳ ለሰው እንግዳ የሆኑ አንዳንድ ተፎካካሪዎች ህዝብን ለመታደግ መንግሥት ከሚሠራው ሥራ ጎን ካልቆሙ ከባንዳ ለይቼ ላያቸው እቸገራለሁ። የፖለቲካ ምህዳሩ ጠበበ እያሉ ሲቃወሙ የነበሩ ሁሉ ሜዳውና ፈረሱ ሲሰጣቸው መጋለብ አቃታቸውና ሀገሪቱን ሊያሳፍሩ ፈለጉ እነሱ ያፍራሉ አንጂ ሀገራችን አታፍርም አትሸማቀቅም።
በውጪ ሆነው የፖለቲካ ምህዳሩ ጠበበ እያሉ ሲጮኹ ከርመው እንዲገቡ ሲፈቀድላቸው ደጋፊ መሰብሰብ ሲሳናቸው ጠባብ ሆኑና ሁከትና ግጭት መፍጠር የዘወትር ሥራቸው አደረጉት።
ይህ ተግባራቸው ተቆረቆርኩልህ በሚሉት ህዝብ ስም ግጭት በመፍጠር «የወዳጆቻችን» ጉዳይ አስፈፃሚ ሆነው ለመሥራትና የአባይን ግድብ ለማጓተት ይመስለኛል። ጊዜን የመሰለ ፈራጅ ደግሞ «የማታ የማታ ዕውነት ይረታ» እንደሚባለው ዕውነቱን የሚገልፀው ይሆናል። ለማንኛው አካላዊ ፈቀቅታ እጅን በውሃና በሳሙና በየ15 ደቂቃው በመታጠብ ከቤት ባለመውጣት ራሳችን እንጠብቅ።
አዲስ ዘመን ግንቦት 1/2012
ይቤ ከደጃች.ውቤ