የሚያናግረን፣ የሚያስጽፈን፣ የሚያስዘምረን፣ የሚያነጫ ንጨን፣ የሚያስቆጣን፣ የሚያስደስተን የሚያሳዝነንና የሚያቆላጨን የሰው ልጅ ነገር ነው። የራሳችን ነገር! በዚህ ጉዳይ እውነት እውነቱን እንድንነጋገር ነው፤ ይህንን ርእስ ያነሳሁት።
የሰው ልጆች፣ በተለይም በዕድሜ ከፍ ያልን ነን ብለን የምናስብ ወገኖች፣ ራሳችንን ማየት ካልቻልን ራሳችንን መመርመር ካላሰብን ከቶውንም ለሌሎች በጎነት ምክንያት መሆን ያቅተናል። ዋናው ነገርም ለራስ መሆን ነው፤ ለራስ ማወቅ በራስ ምህዋር ውስጥ በትክክልና በተገቢው ሁኔታ ቆሞ መገኘት መልካም ነው።
ልጁና ልጅቱ፣ እንደ ወዳጃሞች (Boy friend and girl friend or partners) ሆነው እርስ በእርስም ተጎራብተው ለመተዋወቅም አንዴ እሷ ክፍል ሌላ ጊዜ ደግሞ እርሱ ክፍል ያሳልፋሉ። ወደቤቱ የመጣችና የተጎዳኙ፣ ሰሞን በቤቱ ውስጥ የፈጠረውን ትርምስምስ ያለ የዕቃ አቀማመጥ በማየትና በፍቅር በመንገር፣ አስተካክላና አስውባ አሳምራ ወልውላ ትወጣለች፤ ስትሄድ ግን ነገ ስመጣ ዛሬ ያደርንበት ክፍል ተስተካክሎና ሥርዓት ይዞ ማየት እፈልጋለሁ ብላው ትወጣለች። በሦስተኛው ቀን ስትመጣም ከትናንት ወዲያ አውቃ ሸፈፍ አድርጋ የጣለችው የአበባ ማስቀመጫ እንኳን ቦታው ሳይስተካከል አልጋው ሳይነጠፍና መጋረጃው ሳይዘጋ ታገኘዋለች። እንደገናም መክራውና አስተካክላ ትሄዳለች። ይህንን እያደረገች በጥቂት ወራት ውስጥ፣ ቀስ በቀስ እግሯን ከእርሱ ቤት ቀነሰች። ትንሽ ግራ ቢገባው እሷ ቤት መምጣት ስለጀመረ የራሱን ክፍል መተዉን ስትገነዘብ ሄዳ የልብስህን አቀማመጥ፣ መኝታህን እንኳን ማስተካከልና ማዝረክረክ ለምን አታቆምም፤ በማለት ትገስፀዋለች።
የእርሱን ቤት ትርምስ፣ ወደ እሷ ክፍልም አመጣው። አንድ ቀን ግን መጠጥ ቤት መሄዱን ትቶ መጠጡን ቤት አምጥቶ ከጓደኞቹ ጋር ሲጠጣ አገኘችውና ምርር ብሏት፣ እኔና አንተ ሕይወትን የምንመራበት መንገድ የተለያየ ስለሆነ እዚህ ላይ ቢበቃን ይሻላል፤ መልካም ጊዜ ይሁንልህ ቻው፤ ብላው የእጮኛነትና የፍቅሩ ጊዜ ማብቃቱን ነግራው ትሄዳለች።
ከዚያም ትንሽ ቆይቶ፣ ከዕለቶች አንድ ቀን በስፖርት ልብስ እንደሆነ በሯን ያንኳኳና መጥቻለሁ፤ ይቅር በይኝ ይላታል። ለይቅርታ ልቤ አልተዘጋጀም፤ ደህና ሁን ብላው ትገባለች፤ ሳያንገራግር መለስ አለ። ትንሽ ሳምንት ቆይቶ መለወጡን በሚያሳይ መልኩ፣ የሚያምር ሙሉ ልብስ ለብሶ መጣና በሩን መትቶ ከፍታለት ወደ ውስጥ ሊገባ ሲል፣ ሌላ ሰው ተቀምጦ ያይና ቱግ ብሎ፡- «ምን እያደረግሽ ነው?
ንጽህናህን ጠብቅ አልሺኝ፤ ጠበቅሁልሽ። ስፖርት ሥራ አልሺኝ፤ ጂም ገባሁልሽ። መጠጥ አትጠጣ አልሺኝ፤ ቀነስኩልሽ፤ ቤትህን ጠብቅ አልሺኝ በንጽህና መጠበቅ ጀመርኩልሽ፤ ከዚህ ሌላ ምን ፈለግሽ? እና በሦስት ወር ከአስራአምስት ቀን ውስጥ ከሌላ ሰው ጋር…. እንዴት፣» ብሎ ሲያንባርቅ፣ «አንደኛ፣ ድምጽህን ቀንስ አትጩህ እሺ? ሁለተኛ ያደረግኸውን ሁሉ ያደርግኸው ለራስህ ስትል እንጂ ለእኔ አይደለም። የልዩነታችንም ሁሉ መነሻ ይኸው ነው፤ አንተ የምታደርገውን መልካም ሁሉ የምታደርገው ለእኔ ስትል እንደሆነ የነገርኸኝን ያህል፣ ነገ ደግሞ ወደመጠጥህና «ጀዝባነትህ» ስትመለስ የምትሆነውን ሁሉ የምትሆነው በእኔ የተነሳ እንደሆነ ከማላከክ አትመለስም። ስለዚህ እኔና አንተ ልዩ ልዩዎች ነን። ስለዚህ ፣ እስከወዲያኛው ቻው፤» ብላ በሩን ዘጋችበት።
እናንተስ በልጅቱ ቦታ ብትሆኑ ምን ታደርጋላችሁ? እንዲህ ያለ ነገርስ በቤታችሁ በሰፈራችሁ በግል ሕይወታችሁ ገጥሟችሁ አያውቅምን? ያለጥርጥር እንደሚገጥማችሁ አልጠራጠርም።
የቀድሞ ጓደኛዬ፤ በልጁ ባህሪ ክፉኛ ኀዘን ገጥሞት እንደነበረ አስታውሳለሁ። ከእኔ ሌላ ከአራት ወዳላነሱ ፀበሎችና አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ በመሄድ እንዲጸለይለት እንዳደረገና ጸበል እንዳስረጨው ገልጾልኛል። እርሱ ከሚያውቃቸው ከአራቱ ሦስቱ ቤተክርስቲያናት በልጁ ውስጥ ከመልቲነት በስተቀር፣ ምንም ዓይነት የክፉ መንፈስ አሠራር እንደሌለና የሥነ-ልቦና አማካሪ ቢያገኝ እንደሚሻለውና ጉዳዩ፣ ልጁ ለራሱ ካለው የተጋነነ ስሜት የሚመነጭ ችግር መሆኑን ነገሩኝ፤ አለኝ። አንደኛው ቤተ-እምነት ግን «አጋንንቱ ፌዘኛ» መሆኑን ከመንገር ውጪ ችግሩ ያለው በልጁ አስተሳሰብ ላይ መሆኑን ነው፤ የነገረኝ። እና ሳትታክት ለስምንተኛ ጊዜ የመጣኸው ምን እንዳደርግልህ አስበህ ነው፤ ስል ጠየቅኩት።
ወደራሱ እንዲመለስልኝና ሥራውን እንዲሰራ መደበኛ አኗኗር እንዲኖረው ነው፤ አለኝ።
እውነት ነው፤ ወላጅ ልጁ ጥሩ እንዲሆን መመኘቱ ያለና
የሚኖር ነው። ነገር ግን፣ ልጁ የሚያጠፋውን ሁሉ የሚያጠፋው አውቆ ከሆነስ? ልጁ የሚሰራውን ነገር ሁሉ የሚሰራው፣ የሚያበላሸውን ነገር ሁሉ የሚያበላሸው ወላጆቹን ለመረበሽ ከሆነ ግን፣ ይኼ ጤነኛም ቅቡልነት ያለውም አይደለምና ጸባይ ማረሚያ፤ ይግባ፤ ብታሳስረው ይቀልህ ይሆናል፤ አልኩት። እርሱንም መሞከሩን ገለጸልኝ። ገራሚ ነው፤ በቁንጥጫም በእርግጫም በልምምጫም ሞክሮት አልሳካ ያለውን የኑሮ ፈተና ነው፤ ያመጣልኝ።
በቅድሚያ አንድ ነገር ተረዳልኝ፤ አሁን ቢመጣና ባናግረው «በእምነት የምትለወጠው ለእኔ ስትል ነው፤ አልለውም። ለአንተ ስል ጂም ልስራልህና፤ ሰውነትህ ይፈርጥም፣ እኔ “ዳምፕቤል” ላንሳልህ፤ ጡንቻህ ይዳብራል፤ ለህመሜ አንተ መድኃኒት ውሰድና እኔ ልዳን አልለውም ፤ አይሆንማ ። ክብደት የሚያነሳው ለራሱ ጤንነት ነው፤ ሥራ የሚሰራው ለራሱ ደመወዝ ነው፤ የሚያፈቅረው ለራሱ ደስታ ነው፤ ልጅ ቢወልድ ዘሩን የሚተካው ለራሱ ነው፤ እባክህ የልጅ ልጅ አሳየኝ፤ ብሎ ልመና ምንድነው? በምድር ላይ ራሴን መልሼ ማየት እወዳለሁ ያለ ያገባል፤ ይወልዳልም፤ እለወጣለሁ ያለ ሰውም፣ ለውጡ በቅድሚያ ለራሱ እንጂ ለማንም አለመሆኑን በቅጡ መረዳት አለበት፤ አልኩት።
ልጅህ ቀድሞ፣ ይሄንን አምኖ እዚህ ካልመጣ «ወደ አስቸጋሪው ሕይወቱ» ቢመለስ ይሻለዋል፤ ያኔም አንድም ብርዱ፣ አለዚያም ንዳዱ ያስተምረዋል፤ ስል ነገርኩት። ይሄ መደምደሚያዬ ጨካኝና ያልወለደ አንጀት የሚሰጠው አስተያየት ሊመስልብኝ ይችላል። ይህንን ጽሑፍ ሳዘጋጅ ስለትውልዱ የሚያስጨንቀኝ ነገር ስላለ እንጂ ባይሆን አላነሳውም። እንዲያውም ለትውልዱ ካለኝ ጭንቀት የተወለደ የመፍትሔ ሐሳብ እንጂ ተራ አስተያየትም አይደለም። መክረዋለሁ፤ ዘክረዋለሁ፤ በምሳሌ ነግረዋለሁ ፤ ሲለወጥ ግን የሚለወጠው ልጁ ለወላጁም ለቤተክርስቲያንም፣ ለመንግሥትም አይደለም፤ በቅድሚያ ለራሱ ነው፤ ይህንን ካልተቀበለ «ውሃ ቢወቅጡት እምቦጭ ነው» ። የሚያዛልቀውን የሚያውቅ እርሱ ነው፤ በሐሺሽ ደንዝዞ የሚያገኘውን ጊዜያዊ “ፍንደቃ”ና የቀን ሙሉ “ፍዘት” ካደነቀ ምን ይደረጋል? የአስተውሎት አእምሮውን በብረት ሰንሰለት አስሮና ቆልፎ ቁልፉን አርቆ ወደጫካ የወረወረ፣ ዘመናዊ ባሪያ ነው፤ ማለት ነው።
ወጣቶቻችን በተለያየ ምክንያት ወዳልተፈለገ ሐሳብ ራሳቸውን የሚወስዱት፤ ወላጆቻቸውን ለጥፋታቸው በመውቀስ ነው፤ ፍቅር ስላልሰጡኝ ነው፤ እንክብካቤ ስለነፈጉኝ ነው፤ ችላ ስላሉኝ ነው፤ እኔን “ጣል ጣል” ስላደረጉኝ ነው፤ ማለት ይቀናቸዋል። ይሁንናም እውነተኛው ጉዳይ ራሳቸውን ከጣሉበት ድብርት እና ከሳሽ አስተሳሰብ ውስጥ ማውጣት ስላቃታቸው ነው።
እነኚህ ራሳቸውን ወደሕይወት ጠርዝ የገፉ ወጣቶቻችን (ልጆቻችን)፣ በትምህርት ቤት መምህሮቻችውን፣ በሰፈር ትላልቅ ጎረምሶችን፣ በዩኒቨርሲቲ ሌክቸሮቻቸውን (እሱንም ከደረሱበት ነው) መወንጀል እና ማሳበብ ልማዳቸው ነው። በድንገት A እና B ባመጡበት ውጤት ራሳቸውን የመቆለላቸውን ያክል፣ D እና F ሲገኝ የመምህራኑ ጣጣ ብዙ ነው፤ ትምህርቱ ያልገባቸው እነርሱ ሆነው ሳለ ተከሳሾቹ መምህራኑ ናቸው። በውጤቱም ወላጆቻቸውን፣ «አለፍኩላችሁ፣ ወደቅኩላችሁ» ማለት ይቀናቸዋል።
ከጓደኞቻቸው ጋር «እንቀውጥ» (Let’s chill) ተባብለው ወጥተው ፣ «ቅወጣው» የሚያስከትለውን ጦስ ግን በጓደኞቻቸው ማሳበብ የሚያበዙ ወጣቶች ቁጥራቸው የትየለሌ ነው። ከዚህም ውጤት ተነስተህ አይሆንም፣ አታድርጊው፣ አትሂጂበት ብለህ ስትመከራት፣ «ያዙኝ ልቀቁኝ» ያለችው ልጅ፣ መከራው ሲደቁሳት የሆነችውን ሁሉ የሆነችው በግምቷ ስህተት እንደሆነ ከመቀበል ይልቅ፣ ጓደኞቿን፣ ለመምሰልና «ለማስደሰት» ያደረገችው፣ መሆኑን ትናገራለች። «ያልተፈለገ እርግዝና» የገጠማት፣ «ሲጋራ የምትስበው» ፣ «ሺሻ የምታትጎለጉለው» ፣ ጓደኞቿን ለማስደሰት ነው ማለት ነው። የምሞተው እኮ፣ ለእነሱ ስል ነው፤ እንደማለት ያለ «ኩምክና» ነው። አንዳንዴም የማይታረም ስህተት ተሳስተውና የማይቀረው ሞት ገጥሟቸው የሚያሸልቡ ጥቂቶች አይደሉም።
የርዕሰ ጉዳዬ ዋነኛ ዓላማም ሌላ አይደለም። ከምትወዳት ልጅ ጋር እያለህ ልክ አይደ ለህም፤ ብላ የምታሳይህን ነገር የምታርመው ለእርሷ ስትል አይደለም፤ ለራስህ ስትል ነው፤ ከወላጆችህ ጋር ሳለህ ተው አታድርገው፤ ተብሎ የሚነገርህን ነገር የማታደርገው ለወላጆችህ አይደለም፤ በሥራ ስፍራ ሥራህን በተገቢው ሰዓትና አፈጻፀም እንድታከናውነው የሚነገርህ ለመስሪያ ቤቱ ወይም ለድርጅቱ ተብሎ አይደለም ለራስህ ነው።
ይኸው መጠጡን ተውኩልሽ ፤ ህእ…..! ይኸው
ስፖርቱን ጀመርኩልሽ፤ ህእ…!. ይኸው ሥራውን ሰራሁላችሁ ህእ….!፣ ይኸው ትምህርቱን ተማርኩላችሁ…ህእ! ፣ እያሉ መገበዝ፣ ምግብ አልበላም፤ ብሎ ያስቸገረ ክፉና ደጉን ያልለየ ጨቅላ ሕፃን ምላሽ ነው። ትንሽ ልጅ፣ በኑሮው አልበስል ሲል ነው ፤ አፍንጫው ተሰንጎ ወተት በጉሮሮው እንዲወርድ የሚጋተው። የበሰለ 20፣ 30 እና 40 ዓመቱን የደፈነ ትልቅ ሰው፣ «ያው በላሁልሽ…ምን ትፈልጊያለሽ» ካለ፣ ገበያ ውስጥ ድንገት እንዳያመልጣቸው ተሰግቶ ከእናትዬው ነጠላ ጋር ልብሱ የተቋጠረን ሕፃን መስሏል፤ ማለት ነው።
ስለዚህ ቋጠሮውን ፈትተህ ቆመሃል፤ ወይስ አሁንም የምትበላውና የምትጠጣው «ለእናትህ» ነው? ቋጠሮህን ፈትተህ የምትሄድበትን እና የምትደርስበትን ቦታ ወስነሃል ፤ ወይንስ እዛው እዛው ለመዳከር ቆርጠህ ነው የወጣኸው። ሕይወት እሽሩሩ ማለቷን የምታበቃበት ዕድሜ ላይ ደርሰሃልና፤ አስብበት። ይህ ቁጥራቸው ቀላል ያልሆኑ ወጣቶቻችን ችግር ነው፤ በፆታ አንፃር የወንዶቹ ቁጥር ከሴቶቹ ይልቃል እንጂ፤ የወጣትነት መዘዝና ውጤቱ ያው ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ በሥራ ቦታ ያለውን በደል በአለቆቹ ከሚያላክክና ጠጪ ሆኖ የቀረው በዚህ ነው፤ ተብሎ በኀዘን ከንፈር ከሚመጠጥለት ጎልማሳ ጀምሮ ፤ «ምቀኞች ጉድ ሰሩኝ» እስከምትለው «ባል-ጠል» ድረስ ተመሳሳይ አቤቱታ መስማት የተለመደ ነው። ለስካሩና ክፉ ባህሪው፣ ሚስቱንና ልጆቹን የሚያሳብብም አይጠፋም። ወንድሜ ሆይ! ጠጪ የሆንከው ሚስትህ ስላስቸገረችህ ፣ የማትመች ሴት በመሆኗ ሳይሆን ሚስትህን በሚያስቸግረው ክፉ ጠባይህ አደገኛነት የተነሳ መሆኑን አጢን ።
እንዲህ መሰሎቹን አላካኪ ጎልማሶች፣ ጠጋ ብላችሁ ብትጠይቋቸው፣ «ባለቤቴ በፍጹም አትሰማኝም ፤ ቤት ስገባ በነገር ስለምትቀበለኝና ልጆቼን አሳድማ ስለምትጠብቀኝ ነው… በ…ጣ…ም (የስካር ድምጸት ጨምሩበት) የምጠጣው…. በዚህ ሳቢያ ነው»-ነው፤ የሚላችሁ።
በእውነቱ ግን፣ ከዛሬ ነገ ወደ መልካም ባህሪው ይለወጣል፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ ይሻሻላል፤ ብላ በትዕግስት የምታየውና ከስካሩ ስቃይ ሲገላገልና ጽሞና ላይ ሲሆን ተጸጽቶ አንድ ቀን ወደ ቀልቡ ይመጣል፤ ብላ የምትጠብቀው ሚስቱ ነች ፤ ተቸጋሪዋ እንጂ፤ ይኸው ችግሩን ሁሉ በሰው ላይ የሚያላክከው «ባል ተብዬ»፣ «ሽንቁር በርሜል» አይደለም ። «የምሰክረው ለእሷ ብዬ ነው!» ያላለው ስለማይባል ነው እንጂ ፤ አንዳንዱ የተገላቢጦሽ ማሰቡ አይቀርም። ስለዚህ ማታ ይጠጣል፤ ቀን ይጠጣል ፤ ከተገኘ ጠዋትም ይጠጣል፤ ኪሱ እስከፈቀደና ዱቤ ሰጭዎች ተጠራጥረው እስኪከለክሉት ድረስ ይጠጣል።
ማታ ከቆርኪ ጋር ተጠርጎ ወጥቶ ከሥራ በኋላ (ሠራ ከተባለም ነው ) እንደገና ዝንጥ ብሎ ትናንትና «ልንተኛ ነው፤ ወደቤትህ ሂድ፤ ወይም አልጋ ያዝ ተብሎ ተነግሮት ፤ ውጣልን» ወደተባለው መሸታ ቤት ሲሄድ አያፍርም። የሚያየው የሚጠጣው መጠጡን እንጂ፣ መጠጡን ከጠጣ በኋላ የሚመጣበትን ነውረኛ ባህሪ አያስበውም። እየኖረው ነዋ! የሰው ልጅ፣ እኮ ልክ አለመሆንን ኑሮው ካደረገ በኋላ፣ ልክ አለመሆን ልክነት ነው፤ የሚመስለው።
ለሰካራም ሰክሮ መንገዳገድ የልክነቱ መገለጫ ነው። ለሰካራም የሚስቱን በር በሚረብሽ ድምጽና በር ድብደባ፣ አስበርግጎ ልጆቹን ከአልጋ ላይ ማንጠሩ ልክነት ነው፤ ለሰካራም ከገባ በኋላ እንደአይጥ መደበቂያ የሚፈልጉ ምስኪን ልጆቹን «የታሉ» ብሎ ከእንቅልፍ ቀስቅሶ፣ ስለእናታቸው መጥፎነት በተወላገደ አፉ ዲስኩር ማድረግ ልክነት ነው። ለሰካራም ያለህሊና ወቀሳ ሚስትን መወንጀል ልክ ካልሆነ፣ ሰካራም ባል ምን ይናገር? ልክነት የቤቱ የጨዋታ ሕግ ነው፤ የሚመስለው።
ድሮ ጎረቤቶቼ የነበሩ ባልና ሚስት ነበሩ። ማታ ማታ የግንባታ ሠራተኛ የሆነው ባሏ ጠጥቶ ሲመለስ ፤ እኔ ሰዓቱ 4፡30 መሆኑን አውቃለሁ፤ ቶሎ ብዬም የጆሮ ማዳመጫዬን ጆሮዬ ላይ እሰካለሁ። ምክንያቱም፤ እንደገባ በቴስታ ይምታት በቦቅስ ባይታወቅም «ግው!» የሚል ድምጽ እሰማለሁ፤ ከዚያ ቀጥሎ የእሷ እልኸኛነት የታከለበት የስድብና የዕቃ መልስ ውርወራ ይከተላል። ክትክቱ ይቀጥላል ። ከዱላው በተጨማሪ በየጊዜው በሚፈጠር ግብግብ ዕቃው ተሰብሮ አለማለቁና የስድቡ ናዳ ይገርመኛል። ጠዋት-ጠዋት ለሽምግልና ሌሎች
ሰዎችና አከራዮቻችን ሲቀመጡ የቀጥታ የድምጽና ለማንበብ ያለመቻል ተጠቂ ስለሆንኩ የሚታየኝ «እናንት ለሰው የማታስቡ ባለጌዎች…፤ በግላችሁ የራሳችሁ ጉዳይ ወይ ግደላትና ይውጣልህ ! ብዬ “መንጭቄ” እናገራለሁ። (ምንጨቃ በዘንድሮ ቋንቋ ንዴት ነው፤ ብለውኛል አራዶቹ)
ከዚያም «አቶ ባል» ዋናውን አርእስት ይለውጣል፤ “ከእሷ ጋር ግንኙነት አለህ እንዴ፤ ምነው ለእሷ አዳላህ” ….ጎበዝ ልብ ብላችኋል እኔን ነፍሰ-ገዳይ እያለኝ እኮ ነው፤ በማለት የጥያቄዬንና የተቃውሞዬን መንፈስ የሚያደፈርስ ሐሳብ ይሠጣል። “ሰካራም!” ለመሆኑ ስካሩን ትቶት ይሆን? መቼም ያኔ ጋዜጠኛ አግኝቶ በትርፍ ጊዜ ምን ታደርጋለህ ቢለው “ ኦው ሆቢዬ… መስከር ነው!” ሳይለው አይቀርም። ምክንያቱም የስካር ትምክህቱ ግንባሩ ላይ ይነበባልና።
ከዚያም ሌሎች ተው ተው! ብለው፣ ለምነውና አረጋግተውት ሲጠየቅ፣ “ስጠጣ የምታውቀኝ ሳላገባት ነው፤ አሁን ምን ተገኘና ነገር ትፈልገኛለች? ስለዚህ የምጠጣው ለእሷ ስል ነው” ብሎ “በኩራት” (አንገቱን ሰበር ስለማያደርግ ነው ፤ኩራት ያልኩት) ይናገራል። የወደደችኝ እየጠጣሁ ነው፤ የምኖረውም እየጠጣሁ ነው፤ በማለት ባልተቆጠበ የጠጪነት ኩራት (ቅሌት ብለው ይሻለኛል) ያወራል።
የአከራያችን ሚስት ይቀጥላሉ፤ “ይቺ ሴት ነፍሰጡር ናት ፤ አንተም አባት ልትሆን ነው። ስለዚህ አደብ መግዛቱ አይሻልም ?” አዩ እትዬ ፣ ያረገዘችው እኔን ጉድ ለመስራት ነው፤ እንጂ (ገና አልኮል እንደጡጦ ጠጥቼ ሳልጠግብ በሚል ድምፀት) ለምን እንደነገረቻችሁ አውቃለሁ። ታውቃላችሁ ….የምጠጣበት አንዱ ምክንያት በዚህ የተነሳ ነው፤ ቤት ሳንሰራ ተይ ብያት ነበረ…(ጣቱን እያወዛወዘ) እና ሆን ብላ ነው፤ ብሎ እርፍ ።
እትዬ፣ የአከራይ ሚስትም አያርፉም።” አሃ… ስትጠጣ ነው፤ ብር የምታጠራቅመዋ!” እንደዛ ከሆነ ቤቴን ለቃችሁ ውጡልኝ፤ እኔም ሌላውም ተከራይ በእናንተ ተንገላታን ብለው ብድግ ሲሉ፤ ተንደርድሮ እግር ላይ ይወድቅና “እትየ ሁለተኛ አልጠጣም በቃ! የዛሬን ብለው ይማሩኝ፤” ይላል። መብራቱ የሚባል ሌላው ተከራይ በቃ እርግጠኛ እንድንሆን የዚህን ወር ደመወዝህን አከራያችን ከመስሪያ ቤት ተቀብለው ይምጡና አስቤዛውን ለባለቤትህ ይሠጥ፤ ሲል ከዚህ አስቸጋሪ ሰው፣ የሚወጣው ድምጽ ፣ ትንሽ የቀበሮ፣ ትንሽ የጅብና ትንሽ የምታስካካ ዶሮ ቅልቅል የሆነ አስፈሪና ለጆሮ የሚቀፍፍ ጩኸት ነው። ከዚያ ቀጭን ሰውነት እንዲህ ያለ አስፈሪ ድምጽ መውጣቱን ሳስብ እገረማሁ፤ ዛሬም። እሱ ግን ተበድሮም ቢሆን ማታውኑ ጠጥቶ ይመጣል። ድብድቡ ለአንድ ሳምንት ላይኖር ይችላል፤ ግን ይቀጥላል። የሚጠጣው ለሚስቱ ሲል ነዋ፤ ሲጠጣ ላገኛት ሚስቱ፤ እየጠጣ ትዳሩን ያደምቅበታል፤ ይገርማል። (”አሁን ደህና ናችሁ? አንድ ላይ ይሆኑ ይሆን?”)
እንዲህ ዓይነት መላ የጠፋቸው የሚያገቡት ለሰው፤ የሚኖሩት ለሰው፣ የሚያረግዙት ለሰው፣ የሆነባቸው ከንቱዎች ሁሉንም ክፉና ደግ የሚያደርጉት በተሰጣቸው ተፈጥሯዊ ግዴታና እውነት ሳይሆን ለሰው ብለው እንደሆነ ይነግሯችኋል። እውነቱ ግን የሚሆኑትን ሁሉ የሚሆኑት ለራሳቸው ነው። “ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ…” ነው፤ ነገሩ።
በዚህ የኮሮና (የኮቪድ-19) ወቅት እጃችንን መታጠብ በአልኮል መታሸትም ሆነ ተራርቀን መጓዝና መኖር ለራስ ደህንነት ሲባል የሚደረግ ነው፤ ለራስህ ስትል ስታደርግ፤ አዎ ሌላው ሰላም ያገኛል፤ ሌላው ጤና ያገኛል። ስለዚህ ለራሳችን ስንል ንጽህናችንን እንጠብቅ።
ግሩም ቢለብሱ ለራስ፣ ግሩም ቢበሉ ለራስ ፣ ግሩም ቢሰሩ ለራስ ፣ ውብ ቢያገቡ ለራስ ፣ ቢወልዱና ቢያሳድጉ ለራስ፣ እውቅና ቢያገኙ ለራስ ነው። የሚያበላሹትንም ነገር የሚያበላሹት እና የሚበላሹት ራሳቸውና በራሳቸው ብቻ ነው። ለራስህ ስትል አድርገህ ማንንም “የጦስ ዶሮ” አታድርግ፤ የባለውለታነት ካባም ለራስህ አታጎናጽፍ፤ ጉደኛ!!
አዲስ ዘመን ግንቦት 1/2012
አገልጋይ ዮናታን አክሊሉ