የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንደ አዲስ ከተደራጀ በኋላ ሲሰራቸው የቆዩ ጉዳዮች እንዳሉ ሆነው ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ሲያደርግ የቆየው ውይይት በጣም አታካችና ረዥም ጊዜ የወሰደ እንደነበር የሚታወቅ ነው። በዚህ ሂደት ለተሻለ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ያግዛሉ ያላቸውን ሥራዎች ሲሰራ የቆየና ለፖለቲካ ፓርቲዎቹ (ለነባሮቹም ሆነ ለአዲሶቹ) ሕጋዊ ዕውቅና ለመስጠት ሰፊ ጊዜ ሰጥቶ ሂደቱን እንዲጨርሱ ያደረገበት ሁኔታም የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። (በዚህ መሀል የተጠበቀውን የአባላት ቁጥር በብሔራዊ ደረጃና በክልል ደረጃ ማሟላት ያልቻሉ እንዳሉ ሆነው ማለት ነው።)
ይህንን ሂደት ካጠናቀቀ በኋላ የምርጫ ጊዜን መርሀ ግብር ማውጣትና ማስተዋወቅ የቻለ ቢሆንም በጊዜው ላይ በተለይም ክረምት ከመሆኑ አንፃር የሚነሱ ጉዳዮች እንዳሉ ሆነው ወደ ቅድመ ምርጫ ተግባራት በቅጡ እንኳን ሳይገባ የምድራችን ወረርሽኝ የተከሰተበትና በማይጠበቅ ሁኔታ ምስቅልቅል የፈጠረበት፣ የሚያደርሰውን ተፅዕኖ እንኳን በውሉ ያልተረዳነው ደንቃራ ከፊታችን የተደቀነበት የማይተነበይ ጊዜ ላይ ደርሰናል።
ይሄው ምርጫ ነሐሴ 23 ላይ ቀን ተቆርጦለት ምርጫ ቦርድም መርሀግብር በማውጣት ሥራዎችን ሲሰራ የነበረ ቢሆንም ወደዋናው የምርጫ አካል ከመገባቱ በፊት ዓለማችንን እየተፈታተነ የሚገኝ የኮሮና በሽታ የደቀነው ስጋት ብዙ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች እንዲስተጓጎሉ አድርጓል።
በዚህም ሁኔታ የነሐሴው ምርጫ በተያዘለት ጊዜ መካሄድ የማይቻልበት ሁኔታ ግድ ሆኗል። ከዚህ የዋናው ምርጫ ጊዜ በፊት መከወን የሚገባቸው ቅድመ ምርጫ ሥራዎችን ማከናወን የማይቻልበት ከመሆኑ አንጻር እንዲሁም በአጭር ጊዜ ከዚህ ችግር ወጥተን ደረጃውን የጠበቀ ተአማኒ የሆነ ምርጫ ማካሄድ የምንችልበት ሁኔታ ስለሌለ ነው። ይሄም በመሆኑ ምርጫ ቦርድ የተፈጠረውን ሂደትና ምርጫውን ማድረግ የማይችልበትን ሁኔታ ተረድቶ ተጠሪ ለሆነበት ለሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት ጉዳዩ ውሳኔ እንዲሰጥበት መርቷል።
በዚህ ሂደት ላይ ማለትም የምርጫውን መራዘም በተመለከተ ምን ዓይነት ሕጋዊ ማዕቀፍ ልናስቀምጥ ይገባል? እንዲሁም የሀገራችንን ዘላቂ ሰላም በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግር የሚሰሩ ሥራዎችን በማጠናከር በኩል ምን ዓይነት የተሻሉ አማራጮችን መጠቀም አለብን የሚለው ጉዳይ ዘላቂ ለሆነ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚጨነቅ ሁሉ ሊያሳስበው የሚገባ ጉዳይ ነው።
በአንድ በኩል ስድስተኛው የምርጫ ዘመን በብዙ መልኩ ተስፋ የተጣለበትና ሁሉን የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያሳትፍ በዓይነቱ የመጀመሪያ እንደሆነ የሚገመት ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ጉልህ ሚና የሚጫወት እንደሆነም የሚጠበቅ ነው። ነገር ግን ከኮሮና ስጋት ጋር በተያያዘ ቀደም ብለው የተያዙት የቅድመ ምርጫ ሥራዎች ሊሰሩ የሚችሉበት ከባቢያዊ ሁኔታ ባለመኖሩ ምርጫ ማካሄድ የማይቻልበት ሁኔታ እንደተፈጠረና ይህንንም መፍታት እንዲቻል ምርጫ ቦርድ ለተወካዮች ምክር ቤት እንዳቀረበ ምክር ቤቱም በጉዳዩ ላይ ወስኖ እንደሚያስፈጽም ይጠበቃል።
ባለው አጠቃላይ ሁኔታ ስድስተኛው ብሔራዊ ምርጫ የተላለፈና በምርጫው ዘመን የሚከናወኑ ተግባራት ማለትም፡- የመራጮች ምዝገባ፤ ለመራጮች የሚሰጥ ትምህርት፤ የምረጡኝ ቅስቀሳና ሌሎችም ሥራዎችም ከኮሮና ስጋት እንኳን ነፃ ብንወጣ በአጭር ጊዜ ማከናወን የማንችልበት ሁኔታ እንዳለ መገመት የሚከብድ አይመስልም። ከዚህ በኋላ የትኛው መፍትሄ የተሻለ ሀገራዊ መረጋጋትን ለማስፈን በቀጣይ ለሚከናወኑ የኢኮኖሚ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮች
ይሆናል የሚለው ሲሆን መንግሥት ካቀረባቸው አማራጮች አንዱ ላይ ሊወድቅ ግድ የሚልና በአነስተኛ ችግር መጪውን ጊዜ የተሻለ ለማድረግ ሕጋዊ ተቋማቱ የሚወስኑት ሁኔታ ይጠበቃል።
ያጋጠመንን ችግር ለመፍታት መንግሥት የሕግ ባለሙያዎችን በማሰባሰብ የመፍትሄ አማራጮችን እንዲያስቀምጡና ሃሳብ እንዲሰጡበት ያደረገ ሲሆን አራት አማራጮችን የምሁራኑ ስብስብ አዘጋጅቷል። እነዚህ አማራጮች (የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤትን
መበተን የአስቸኳይ ጊዜ ማወጅን ሕገ መንግሥትን ማሻሻል ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ሕገመንግሥታዊ ትርጓሜ መጠየቅ) በጠንካራም በውስንነት የሚጠቀሱ ጎኖቻቸው በዝርዝር የቀረበና ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን ከመካከላቸው የተሻለ የተባለው ሕገመንግሥታዊ ትርጓሜ መጠየቅ የሚለው በተወካዮች ምክርቤት በአብላጫ ድምጽ የጸደቀበትና በሚቀጥለው አንድ ወር ውስጥ ሕገመንግሥታዊ ትርጉም በሚያስፈልግባቸው አንቀጾች ላይ ምላሽ የሚሰጥበት ይሆናል።
በዚህ መሀል ግን የተፎካካሪ ፓርቲዎች ተሰባስበው የሽግግር መንግሥት ይመስርቱ የሚለው ጨዋታ ግን የትም የማያደርሰን ስሌት ሲሆን ከሀገር በላይ የረዥም ጊዜ የፖለቲካ ሥልጣንን መሻት ለማርካት ካልሆነ በስተቀር አሁን ባለው ፅንፍ የወጣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፕሮግራምና እንቅስቃሴ እርባናም ያለው አማራጭ አይሆንም።
እንዲያውም ባለፉት ጥቂት ወራት በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ለውይይት በቀረቡ በርካታ ሀገራዊ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ እንኳን ለመግባባትና ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ይቅርና የአጀንዳ ቅደም ተከተል ለማስቀመጥ ምን ያህል አስቸጋሪ ሁኔታ እንዳሳለፉ ይታወቃል። በፖለቲካ ፓርቲዎቹ ዘንድ ብዙዎቹ ስብሰባዎች በጭቅጭቅና በወቀሳ የሚጠናቀቁ እንደነበር የሚታወቅ ሲሆን የሽግግር መንግሥት ለመመስረትና ቀጣይ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮችን መስመር ለማስያዝ የሚያስችል አውድ ሊፈጠር የሚችልበት ዕድል በጣም አነስተኛ እንደሆነ መረዳት ከባድ አይደለም።
የሽግግር ጊዜያዊ መንግሥት አሁን ባለንበት ነባራዊ ሁኔታ ወደ ባሰ ችግር ውስጥ የሚከተንና አለመረጋጋትን የሚያስከትል መሆኑ የባለፉት በርካታ ዓመታት ልምዶች ምስክሮች ናቸው። በቅርብ ካለፍንበት መፈናቀል፣ ግድያ፣ የጎበዝ አለቃ ዝርፍያ አጠቃላይ ሀገራዊ ስክነት ከጎደለበት በስሜት ከሚነዳ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ውጪ የምናተርፈው ምንም ነገር የለም። በተራዘመው ጊዜ ውስጥና ከኮሮና ስጋት በተላቀቅንበት ሁኔታ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች መስራት የሚገባቸውን ሥራዎች ሰርተው ለሰለጠነ ፖለቲካ ከዚያም ሲያልፍ ሕዝብ በሚሰጣቸው ይሁንታ የፖለቲካ ሥልጣንን መያዝ ይጠበቅባቸዋል።
ለሽግግር መንግሥት ከሚጮሁት የበለጠ ለዘላቂ የዴሞክራሲ ሥርዓት ሽግግር አጋዥ መሆን የሚችሉበትንና በእጃቸው ያለውን ወርቃማ ዕድል ድጋሚ ባለማምከን ይህንን በብዙ ስቃይና ችግር ውስጥ ያለፈን ሕዝብ ማስቀደምና መካስ ይገባል። በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ የፖለቲካ ትግል በማድረግ ለዚህ ለውጥ አስተዋጽኦ ያደረጉ የፖለቲካ አካላት የሀገርን ህልውናን ማስቀደም ካለንበት ድህነትና ኋላቀርነት የሚያወጡን
ዘላቂ መፍትሄዎች ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባቸዋል።
የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው ዓይነት ብሂል ግለሰቦችን ወይም የፖለቲካ ፓርቲዎችን ማየት ሳይሆን የሀገርን ብሔራዊ ጥቅምና ክብር ባስቀደመ መልኩ ከመጠላለፍና ከመወቃቀስ በመውጣት ለተወሰነ ጊዜ በስክነት የውስጥ አቅምን በማጠናከር መዘጋጀት የተሻለ ይሆናል። በጣም ባጠረ ጊዜ ውስጥ ከበሽታው ስጋት ነፃ በሆንን ጊዜ የምርጫው ሥራዎች እንዲጀመሩ ግፊት ማድረግና እስከዚያው ሕዝቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ የመሪነት ሚናቸውን እየተወጡ መቆየት ነው።
በሽግግር መንግሥት አይደለም በሕዝብ በተመረጠ መንግሥት በሚደረግ ውይይት እንኳን በቀላሉ ልንፈታቸው የማንችላቸው ሀገራዊ አጀንዳዎች ያሉባት ሀገር ናት። በዚያ ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ባለፉት አስርት ዓመታት (በቅርብ የተቀላቀሉትን ጨምሮ) ምን ያህል ጫፍ የወጡ የፖለቲካ አቋሞች ላይ እንዳሉ ስናይ የሽግግር መንግሥቱ የሁከትና የንትርክ ሊሆን እንደሚችል ማንም የሚያጣው ጉዳይ አይደለም።
በኢትዮጵያ አሁኑ ወቅት ለሰላማዊ የፖለቲካ ትግል /ከሽፍቶች በስተቀር/ ሁሉም የተመመበት ወቅት ላይ ስንሆን በሀገሪቱ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ የተፈጠሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሁሉ የሚሳተፉበትና ፕሮግራማቸውን ለሕዝቡ የሚያቀርቡበት በቀጣይ ለሚኖረው የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ልምምድ መሠረት የሚጥል ምርጫ ነው።
ሀገራችንን ወደ አዲስ ምዕራፍ የምትገባበትን መልካም አጋጣሚ የሽግግር መንግሥት በሚል ሰበብ የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ ማበላሸት ካልሆነ በስተቀር ሊያስገኝ የሚችለው ሀገራዊ ጥቅም እንዳለ በመረዳት ያሉንን አማራጮች ለማቅረብ እስከአሁን ካደረግነው የተራዘመ የፖለቲካ ትግል አንፃር አነስተኛ በሚባል ጊዜ ውስጥ ለሕዝብ በማቅረብ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታውን ማገዝ ይኖርባቸዋል። በተቻለ መጠን ቀጣዩ ስድስተኛ ብሔራዊ ምርጫ ለይስሙላ ሳይሆን ደረጃውን በጠበቀ መልኩ እንዲከናወን ውጤቱም ለሀገራችን ፖለቲካ አዲስ ምዕራፍ እንዲከፍት ለማድረግ መተባበር ይጠበቅብናል።
ከኮቪዲ 19 በተጨማሪም ሀገራችንን የተደቀነባትን የብሔራዊ ጥቅምና ህልውና ከግምት ውስጥ ማስገባት ለፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች የሚነገር አይደለም። በተለይም ከህዳሴው ግንባታ ጋር በተያያዘ የውኃ ሙሌቱን ሥራ በቅርብ ወራት የሚጀመር ከመሆኑ አንፃር ሊጋርጥብን የሚችለው ብሔራዊ ፈተናም ቀላል አይሆንም።
ይሄንን ጉዳይ በአግባቡ የሚመክትና የሚያስተባብር ጠንካራ መንግሥት የግድ አስፈላጊ ነው። የኮሮና ስጋት ለዓለም መንግሥታት ከባድ ፈተና ቢሆንም በእኛ ሁኔታ ከተጠቀሱት ብሔራዊ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ ድርብ ፈተና እንደሚሆንብን ማንም የሚያጣው ጉዳይ አይደለም። በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የኢኮኖሚ ቀውስ ከአሁኑ በቀላሉ እንዲህ ነውብሎ መተንበይ ባይቻልም የሚያሳድረው ተፅዕኖ እንዲሁ በዋዛ የሚታለፍ አይደለም። በተለይ እንደኛ ባሉ ደሃ ሀገራት ከባድ በትር እንደሚሆንብን የብዙ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ቀውሶችን አስከትሎ እንደመጣ ይገመታል።
በእነዚህና በሌሎችም በርካታ ችግሮች ከተተበተበብን ለመውጣት ብዙጊዜና የሁሉንም ጥረት የሚያስፈልገን ቢሆንም ስድስተኛውን ብሔራዊ ምርጫ ደግሞ ከዚህ አስፈሪ ድባብ ባጠረ ጊዜ ውስጥ ወጥተን ሁላችንም የምንመኘውን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማጠናከር መተጋገዝና በየአቅጣጫው ከመላተም ተቆጥበን ያሉንን አቅሞች በሙሉ ለብሔራዊ ጥቅማችንና ህልውናችን ስንል በጋራ ማዋል አለብን።
አሁን በጅምር ላይ ያሉ የለውጥ እንቅስቃሴዎች ውጤታማ እንዲሆኑና ዘላቂ የሆነ ለውጥ እንዲመጣ በትንሹ ለስድስት ወራት መታገስ /የኮሮና ቫይረስ ስጋት ከተገፈፈና/ የሰለጠነ ለሀገር የሚበጅ ትግል ሕዝባዊ የሆነ ዓላማ ያለው ከግልና ከቡድን ጥቅም በላይ አጀንዳ ያለው የፖለቲካ ቡድን ሊያሳስበው የሚገባ ጉዳይ ነው።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 30/2012
ረ/ፕ አንተነህ መሉ ይልማ