እንደ ቢቢሲ ዘገባ የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ በግንቦት 2019 በሀገሪቱ የሚደረገውን ክልላዊና ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለማሸነፍ ፓርቲያቸው ትኩረት የሰጣቸውን ዋና ዋና ጉዳዮች ለደጋፊዎቻቸው ለማሳወቅ ባለፈው ሳምንት በደርባን ከተማ ተገኝተው ነበር፡፡ የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረንስ ፓርቲ አባላትም ፓርቲያቸው በቀጣዩ የምርጫ ግዜ ምን ምን ፕሮግራሞችን ይዞ ለመወዳደር እንዳሰበ ለማዳመጥ በደርባኑ ሞሰስ ማቢዳ ስታዲየም ታድመዋል፡፡
እንደ ዘገባው በስታዲየሙ ውስጥ ያለው አውድ ግን እንደከዚህ ቀደሙ አይነት አይደለም፡፡ ሁሉም ታዳሚዎች የአንድ ፓርቲ ደጋፊዎች ናቸው ቢባሉም ሆድ ለሆድ ያልተግባቡበት ጉዳይ አለ፡፡ በዚህም ገሚሶች የቀድሞውን ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማን ገሚሶቹም አሁን ሀገሪቱን በመምራት ላይ ያሉትን ሲሪል ራማፎስን በመደገፍ በሁለት የተከፈሉ ናቸው፡፡
ፕሬዚዳንቱ ወደ ስታዲየም ሲገቡም ደጋፊዎቹ ከአሁን በፊት እንደሚያደርጉት በአንድ መንፈስ በመሆን በዘፈንና በእንቅስቃሴ ታጅበው ፓርቲያቸውን ሲደግፉ አልታዩም፡፡ አንዳንዶቹ እንደውም ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ሥልጣናቸውን የለቀቁትንና ፓርቲያቸው በሙስና ቅሌት እየወነጀላቸው ያሉትን ጃኮብ ዙማን ሲያወድሱ ተሰምተዋል፡፡ ይህ ክፍል ታዲያ በደጋፊዎች ብቻ ሳይሆን በአመራሮቹም እንደሚታይ የሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲ አባላት እየተናገሩ ይገኛል፡፡
እንግዲህ በዚህ ጥሩ ያልሆነ አውድ ውስጥ ሆነው ነበር ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎስ ንግግር ያደረጉት፡፡ በንግግራቸውም ፓርቲያቸው በቀጣይ የምርጫ ወቅት በሥራ አጥነት፣ በኢኮኖሚን ዕድገት፣ የሴቶችን ጥቃት በማስወገድ፣ በትምህርት ሥርዓት ማሻሻል፣ በመሬት ይዞታ፣ በዘር ልዩነትና በመሳሰሉት ትኩረት ሰጥቶ ለመሥራት እንደተዘጋጀ ተናግረዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ባደረጉት የዘጠና ደቂቃ ንግግር ውስጥ የመሬት ጉዳይን አስመልክተው ያደረጉት የአርባ ሁለት ሰከንድ ንግግር ብቻ መሆኑ ግን ብዙዎችን አነጋግሯል፡፡ በደቡብ አፍሪካ ዛሬም ድረስ አብዛኛው የእርሻ መሬት የተያዘው በነጮች በመሆኑ ይህ ጉዳይ በአብዛኛዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዘንድ ሰፊ ሽፋን የሚሰጠው አጀንዳ እየሆነ መጥቷል፡፡ እንደውም የሀገሪቱ ህገ መንግሥት የመሬት ጉዳይን በተመለከተ በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት በተወሰነ መልኩ ማስተካከያ እንደሚደረግበት ብዙዎች ተስፋ ያደረጉት ጉዳይ ሆኖ ሳለ ፕሬዚዳንቱ እምብዛም ስለመሬት ሳያወሩ ማለፋቸው አስገራሚ ተብሏል፡፡
ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎስ ባለፈው የምርጫ ዘመን ወደ ስልጣን ሲመጡ ቃል ከገቡት ጉዳይ አንዱ የደቡብ አፍሪካ ዜጎችን የሥራ ዕድል ባጣበቡ ህገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ ነበር፡፡ ዜጎች በስደተኞች ምክንያት ምን ያህል በፈታኝ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ እንዳሉና የመኖሪያ ቦታዎቻቸውም እንደተጨናነቁ ፓርቲያቸው እረዳለሁ ቢልም የተሻለ ነገር ግን አላመጣላቸውም፡፡
ፕሬዚዳንቱ ሙስናን በተመለከተም ፓርቲያቸው ኃላፊነቱን በሚገባ እየተወጣ እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡ ከዛሬ ሃያ አምስት ዓመት በፊት ደቡብ አፍሪካ ዴሞክራሲን መተግበር ከጀመረች ወዲህ እንኳን ፖለቲከኞች በርካታ ብልሹ አሠራሮችን መፈጸማቸውን አስታውሰዋል፡፡ ይህ ንግግራቸውም በአመዛኙ የፓርቲውን ደጋፊዎች ያስማማ ሆኗል፡፡
ራማፎሳ በደቡብ አፍሪካ ባልተለመደ መልኩ እየተባባሰ የመጣውን የሴቶች መደፈርና ወሲባዊ ጥቃትን ለመከላከል ፓርቲያቸው ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡ እርሳቸው እንዳሉት በደቡብ አፍሪካ ከአምስት ሴቶች አንዷ በቤተሰቦቿ ወይም በቅርብ ዘመዶቿ ጥቃት ይደርስባታል፤ በየዓመቱ ቁጥራቸው አርባ ሺ የሚገመት ሴቶች ይደፈራሉ፡፡ በደቡብ አፍሪካ በሴቶች ላይ የሚደረገው ጥቃት በአማካይ በዓለም በሴቶች ላይ የሚፈጸመውን ጥቃት አምስት እጥፍ ይሆናል ሲሉ የጉዳዩን አሳሳቢነት ለማስረዳት ሞክረዋል፡፡
ፓርቲው በየዓመቱ የሥራ አጥ ቁጥርን እቀንሳለሁ ማለቱ መገለጫ ባህሪው ቢሆንም የተናገረውን ግን ሲፈጽም እንደማይታይ የሚናገሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ በስልጣን ዘመናቸው አምስት ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል እፈጥራለሁ ብለው የተናገሩትን ሳይፈጽሙ ቀርተዋል፤ በወቅቱ የዓለም ኢኮኖሚን መዳከምና የተለያ ምክንያቶችን በመጥቀስ ዕቅዱን መተግበር አለመቻላቸውን አሳውቀዋል፡፡ አሁን ደግሞ ራማፎሳ እየደጋገሙ ለደቡብ አፍሪካ አዲስ ቀን አመጣለሁ እያሉ ይገኛል፡፡ በየዓመቱ ለሁለት መቶ ሰባ አምስት ሺ ዜጎች የሥራ ዕድል እፈጥራለሁ በማለት ለደጋፊዎቻቸው ተስፋ በመስጠት ላይ ናቸው፡፡
በዙማ የስልጣን ዘመን ትኩረት ያልተቸረውን ሥር የሰደደ ሙስና ለመዋጋትም በመንግሥት ተቋማት ላይ አዲስ አሠራርና ጥብቅ ክትትል እንደሚያደርጉ አሳውቀዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ይህን ይበሉ እንጂ በተደጋጋሚ የወጡ መረጃዎች እንደሚያመላክቱት የሀገሪቱ የትምህርት ሥርዓት እንኳን ከፍተኛ የሙስና ወንጀል እንደሚፈጸምበት ይነገራል፡፡ ብዛት ያላቸው ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ያቋርጣሉ፣ ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደ ሥራ የተሰማሩትም ቢሆኑ መሰረታዊ የሂሳብ ዕውቀትና የማንበብ ክህሎት እንደሌላቸው ይነገራል፤ በመሆኑም በሥራ ላይ ሲሰማሩ ውጤታማ መሆን አልቻሉም እየተባለ ይገኛል፡፡
ፕሬዚዳንቱ እነዚህን ድክመቶች ለማስወገድ ጠንክረው እንደሚሰሩና የመምህራንን አቅም ለመገንባት የሚያስችሉ ለውጦችን እንደሚያደ ርጉም ተናግረዋል፡፡ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ኢንቨስትመንትን ማስፋፋት ቁልፍ ተግባራቸው ሊሆን እንደሚችልም አስረድተዋል፡፡ በከተማም ሆነ በገጠር የሚኖሩና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች ህይወት ለመለወጥ የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራት እንደሚያከወኑም በመልዕክታቸው ደጋግመው ተናግረዋል፡፡
ራማፎሳ እ.አ.አ 2016 በተደረገው ምርጫ ከሃምሳ ሶስት በመቶ በላይ ድምጽ በማምጣት የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት መሆን የቻሉ ሲሆን፤ አሁን ሀገሪቱን ወደተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ሊፈጽሟቸው ያሰቧቸው ተግባራት ምናልባትም ለሁለተኛ ጊዜ እንዲመረጡ እድል ይፈጥርላቸዋል እየተባለ ነው፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 9/2011
ኢያሱ መሰለ