በሀገራችን የተጀመረው ለውጥ በመሠረታዊነት ታሳቢ ያደረገው ሕጋዊና ሕገመንግሥታዊ ሥርዓትን በማስፈን ሕዝባችን ለዘመናት ዋጋ የከፈለበትን የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እውን ማድረግ ነው። ይህንንም በማድረግ ሀገራዊ ብልጽግናችንን ከተስፋ ወደ ተጨባጭ እውነታ መለወጥ ነው። ይህ ደግሞ የተለያዩ ዓለም ሀገራትን ተሞክሮም ሆነ የተለያዩ የፖለቲካ አስተምህሮዎችን መሠረት ያደረገ ነው።
በሀገራችን የትናንቱ ብቻ ሳይሆን ከትናንትም በፊት ሀገራዊ የለውጥ መሻት ንቅናቄዎች መሠረት ያደረጉትና ብዙዎች ሕይወታቸውን ያለመሳሳት የከፈሉት ለዚህ ሀገራዊ እውነታ ነው። አንድን የበሰበሰ ሥርዓት በሌላ ከጅምሩ በበሰበሰና አንድ እርምጃ ሀገርና ሕዝብን ማራመድ በማይችል፤ እንዲያውም ሀገርና ሕዝብን ብዙ ዋጋ ሊያስከፍል በሚችል፤ የአስተሳሰብ መሠረት በተገነባ ሌላ ሥርዓት ለመለወጥ አይደለም። የለወጥም መሠረታዊ የቃል ትርጓሜም ቢሆን ይህንን እውነታ የሚሸከም አይደለም።
የለውጥ አስተሳሰብ ሆነ ከዚህ አስተሳሰብ የሚነሳ ኃይል በመሠረታዊነት መነሻው፣ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ፤ በሚያስት እውቀት ይሁን በተገለበጠ የጥፋት እውቀት ብዙ ዋጋ ያስከፈሉንና ወደፊትም ሊያስከፍሉን ከሚችሉት የትናንት መንገዳችን ወጥተን ነገን በተሻለ ተስፋና የአስተሳሰብ ቁመና መቀበል ወደሚያስችል ታሪካዊ ምእራፍ መሸጋገር ነው።
ለዚህ ደግሞ ትናንት የተጓዝንበትን መንገድ፤ መንገዱ የተመራበትን አስተሳሰብ፤ አስተሳሰቡ መሠረት ያደረገውን እውቀት፤ እውቀቱ የተመረጠበትን መመዘኛን በአግባቡ እና በድፍረት ማየት ይፈልጋል። ትናንት ከመጣንበት የተሳሳተ መንገድ ሊያሻግረን ወደሚችል አዲስና የተሻለ መንገድ የሚያስፈነጥረንን የአስተሳሰብ መሠረት መገንባትንም ይጠይቃል። በትናንትናው የአስተሳሰብ መሠረት ዛሬን መሻገር አይቻልም፤ ይቻላል ብሎ ማሰብም በጊዜና በትውልድ ላይ ማፌዝ ነው። ይህ ደግሞ የጊዜን አልፋና ኦሜጋነት አለመረዳትና በጊዜ ሂደት ውስጥ ተንሰላስሎ ለሚመጣ ትውልድ ደንታቢስ መሆንን አመላካች ነው። ትውልድን የሞተ አስተሳሰብ ባሪያ አድርጎ የማምከን ያህል አደገኛ ነው።
የለውጥ ኃይል ሆኖ በሰልፍ ውስጥ ለመገኘት ከሁሉም በላይ ቀድሞ ትናንትን በአግባቡ መረዳት ይፈልጋል። ከትናንት አሮጌ አስተሳሰቦች ራስን ነፃ ማውጣትና በነፃነትና ከነፃነት በሚወለደው ተስፋ ነገን መጠበቅ የሚፈልግ ጥልቅ ሰብአዊ አሴት ነው። ትናንት የተወለዱ ጊዜያቸውን የጨረሱና ትውልድ አምካኝ አስተሳሰቦችን በአስተሳሰብ ልዕልና አምኖ መካድ ይፈልጋል።
እነዚህ በየዘመኑ ትውልዶችን ዋጋ ያስከፈሉ አሮጌና የሞቱ አስተሳሰቦች የቱንም ያህል በውብ ቃላት ብናደምቃቸው የድምቀታቸው መጠን ህያው አያደርጋቸውም። የተዋቡበት ቃለ ለትውልድ ሕይወት እንዲሆኑ አያስችላቸውም። እነሱን በውብ ቃላት ማስጌጥ መቃብር የማስጌጥ ያህል ነው። የቋሚውን ስነልቦና ከፍ ከማድረግ ባለፈ ለሞተው የቱንም ያህል ቢያምሩ በሰከንድ
የሚሰላ ትርፍራፊ ሕይወት አይሰጡትም።
በእኛም ሀገር ከለውጡ ማግስት ጀምሮ እየሆነ ያለው እውነታ ከዚህ በብዙ የተለየ አይደለም። በዘመናት መካከል ያለፉና ብዙ ትውልዶችን ዋጋ ያስከፈሉ፤ ሀገርና ሕዝብን በአንድ ታሪካዊ ምእራፍ ያስቆመ ፤ ሕዝባችንን ከማሰብና ከማለም ባለፈ ወደ አሰበው እና ወደ አለመው እንዳይደርስ ሕያው ግንብ ለሆኑ አሮጌ አምካኝ አስተሳሰቦች በግልጽም ይሁን በስውር፤ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ዘብ የሚቆሙ ኃይሎች እየተበራከቱ መጥተዋል።
አንዳንዶች የዴሞክራሲ ሥርዓት ሐዋርያ ነን እያሉ በየመድረኩ ራሳቸውን በተዋቡ ቃላት ሲገልጹ፤ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አልፋና ኦሜጋ የሆነው የሕግ የበላይነት ነው ብለው ሲጮሁ እንዳልከረሙ፤ ድንገት ሀገራዊ እውነታው የተለየ ገጽታ የተላበሰ ሲመስላቸው ከሕግና ከሕገመንግሥታዊ ሥርዓት ውጪ ሀገርን እንደ ሀገር ማስቀጠል የሚያስችል ሌላ አማራጭ እንዳለ መናገርና መስበክ ጀምረዋል። ይህ አሳፋሪና እጅግ አሳፋሪ ክስተት ነው። ከትናንት ስህተታችን ያለመማር ከስህተት ለማትረፍ የመሻት መታወርም ነው።
ከማሳፈርም በላይ የሚሆነው ደግሞ አማራጭ አድርገው የሚያቀርቡት ሀሳብ ቁጭ ብሎ ለመወያየት በሀገር ሽማግሌ መዳኘት በሚፈልጉ ፤ የተለየ ሀሳብን ሁል ጊዜ ለጠላትነት ፍረጃ አልፋና ኦሜጋ አድርገው በሚቀርቡ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በሚፈጠር የሽግግር መንግሥት ምስረታ መሆኑ ነው።
ሌሎች ደግሞ በሕገመንግሥቱ ላይ የተፈጠሩ ክፍተቶችን በራሳቸው አልፋና ኦሜጋ አድርገው በማግዘፍ ችግሮች ሕጋዊ መፍትሄ እንደሌላቸው አድርጎ በመጮህ ጩኸታቸውን በጩኸትነቱ ብቻ እውነታ ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ ነው። የእነዚህ ደግሞ ክፋቱ ሕገመንግሥቱ ሕገመንግሥታዊ ሥርዓትን ለማስፈን የተቀመጠ ፤ ሕገመንግሥታዊ ሥርዓትን ለማስፈን በየትኘውን ጊዜና ሰዓት ሊለወጥ እንደሚችል ለመስማት ፈቃደኛ አለመሆናቸው ነው ።
የሚያሳዝነው እነዚህም ሕገመንግሥታዊ ሥርዓትን ለማስፈን ከሕገመንግሥቱ የተሻለው አማራጭ የሽግግር መንግሥት ማቋቋም ነው የሚል ሀሳብ ይዘው መነሳታቸው ነው። የሽግግር መንግሥት መሠረታዊ ሀሳብ በዘመናት መካከል በሀገራችን ሆነ በዓለም ታሪክ ሀገራትን እና ሕዝቦችን ለኪሳራ ከመዳረግ ባለፈ እንደሚባልለትና እንደሚዜምለት ያመጣው ወጤት የለም። ከዚህ ይልቅ ሀገራትን ወደ ኋላ የመለሰ፣ ጊዜ ያለፈበትና በየትኛውም መመዘኛ ለለውጥ እየተጋ ያለውን ሕዝባችንን የሚመጥን አይደለም።
በሀገሪቱ በብዙዎች መስዋእትነት የተጀመረው ለውጥ እና ለውጡ የተሸከመው የለውጥ አስተሳሰቡ ሀገርን ለወራት ሳይሆን ከአንድ የታሪክ ምርራፍ ወደ ሌላ የታሪክ ምዕራፍ ሊያስፈነጥር የሚችል ነው። ከዚህም ባለፈ ሕግና ሕገመንግሥታዊ ሥርዓትን በማስፈን አዲስ ታሪክ በአዲስ አስተሳሰብ መስራት የሚያስችል ነው!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 30/2012