እንደ ኢትዮጵያውያን የዘመን አቆጣጠር 1888 ዓ.ም ዓድዋ የቅኝ ግዛት ፍላጎቱን ለማሳካት ኢትዮጵያን የወረራው ዒላማ አድርጎ ገስግሶ የመጣው የኢጣሊያ መንግሥት/ጦር/ በኢትዮጵያውያን ልዩና ታሪካዊ አንድነት በተሰጠ ምላሽ የሽንፈት ማቁን ተከናነበ። ጣልያኖች ዓድዋ ላይ ድል ከሆኑ በኋላ ለአጭር ጊዜ በሰሜን ምሥራቅ አፍሪቃ የሚከተሉትን የመስፋፋት ፖሊሲ እንደመግታት ብለው ነበር። ከሽንፈቱ በኋላ አዲስ የተሾመው ጠቅላይ ሚኒስትር ዲ ሩዲኒ ቀዳሚው ፍራንችስኮ ክሪስፒ ያራምድ የነበረውን ፖሊሲ ሽሮታል፤ ለቅኝ ግዛት ማስፋፊያ የተመደበውን በጀት በግማሽ ቀነሰው፤ ከአድዋ ጦርነት በፊት አንገቱን ደፍቶ የነበረው የፀረ-ኮሎኒያሊስት ቡድን አሁን የልብ ልብ አግኝቶ ኢጣሊያ ከነአካቴው የአፍሪቃን ምድር ለቃ እንድትወጣ ለመጠየቅ ተዳፈረ። ይህ ሁሉ ግን የቆየው ለአጭር ጊዜ ነበር።
ከእንግሊዝ ቀጥሎ ከኢትዮጵያ ጋር ረጅም የጋራ ድንበር ያሏቸውን ቅኝ ግዛቶች የምታስተዳድረው ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ችላ ብላ መኖር አልቻለችም። ከዓድዋ ሽንፈት 30 ዓመታት በኋላ ወደ ስልጣን የመጣው አምባገነኑ የፋሺዝም አቀንቃኝ ቤኒቶ ሙሶሊኒ፣ ራሱን እንደ ሮም የቀድሞው ንጉስ ጁሊየስ ቄሳር በመቁጠርና ‹‹የኢጣሊያን ክብር ለዓለም አሳያለሁ›› በሚል የረጅም ጊዜ ተስፋ የቅኝ ግዛት ዘመቻውን ሊያሳካ ላይ ታች ማለቱን ተያያዘው። ነገሩ ይህ ብቻ አልነበረም፤ ኢጣሊያውያን በውስጥ ችግሮቻቸው ላይ የነበራቸውን ትኩረት ለማስቀየር፣ እየጨመረ ለመጣው የኢጣሊያ ህዝብ የማስፈሪያ ቦታ ለመፈለግ እንዲሁም በአውሮፓ መድረክ የከሸፈበትን የመስፋፋት ፖሊሲ ለማካካስ ቅኝ ግዛትን አማራጭ አድርጎ ተነሳ። ከሁሉም በላይ ግን ኢጣሊያ ዐድዋ ላይ የተከናነበችውን ሽንፈት ለመበቀል ሙሶሊኒ ፊቱን ወደ ኢትዮጵያ አዞረ።
ኢጣሊያ ዓድዋ ላይ የተከናነበችውን ሽንፈት ለመበቀል ለአርባ ዓመታት ያህል ስትዘጋጅ ከኖረች በኋላ በየጊዜው ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በባህል መስክ የተፈራረመቻቸውን የሰላምና የትብብር ውሎችና በመንግሥታቱ ማኅበር አባልነቷ የገባቻቸውን ዓለም አቀፍ ግዴታዎች ሁሉ ‹‹ከእንግዲህ አላውቃቸውም›› አለች። ከብዙ ጊዜያት ዝግጅትና የጠብ አጫሪነት እንቅስቃሴዎች በኋላ፣ ፋሺስት ኢጣሊያ በ1928 ዓ.ም ኢትዮጵያን ወረረች።
ይሁን እንጂ መቼውንም ቢሆን በአገሩና በነፃነቱ የማይደራደረው የኢትዮጵያ ሕዝብ የፋሺስትን አገዛዝ ‹‹አሜን›› ብሎ አልተቀበለውም። ይልቁንም ጨርቄን ማቄን ሳይል ‹‹ጥራኝ ዱሩ›› ብሎ ለነፃነቱ መፋለም ጀመረ። የኢጣሊያ ወራሪ ኃይልም አንዲትም ቀን እንኳን እፎይ ብሎ ሳይቀመጥ ከአምስት ዓመታት እልህ አስጨራሽ ትግል በኋላ ሌላ የሽንፈት ማቅ ለብሶ ከኢትዮጵያ ምድር ተባረረ፤ ከሰሜን እስከ ደቡብ፤ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ በተለያዩ ጊዜያት በርካታ ጀግኖችን ያፈራችው ኢትዮጵያም ሉዓላዊቷን በመዳፈር በመዳፏ ስር ሊያስገባት ያሰበውን ኃይል ድል አድርጋ መለሰችው። ታዲያ በዚህ አስገራሚና አኩሪ የመስዋዕትነት ጉዞ ውስጥ ደማቅ የጀግንነት ታሪክ ከፃፉና ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ከተጋደሉ እልፍ የኢትዮጵያ ጀግኖች መካከል አንዱ ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ ነበሩ።
ገረሱ በ1897 ዓ.ም ወሊሶ ውስጥ ማሩ በተባለ ስፍራ ተወለደ። በልጅነቱ መንፈሳዊ ትምህርት ተከታትሏል። አገሩን ለማገልገል በነበረው ፅኑ ፍላጎት ምክንያት ወደ አዲስ አበባ መጥቶ በፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ እዝ ስር ወታደር ሆኖ አገልግሏል። ስመጥሩ አርበኛና አገረ ገዢ ደጃዝማች ገብረማርያም ጋሪ የገረሱን የአገር ፍቅር፣ ጀግንነትና ብልሃት በሚገባ ተመልክተው ስለነበር ‹‹ … ይህ ወጣት ድንቅ ልጅ ጀግናና ብልህ ነው፤ በታማኝነትና በጀግንነት ሊያገለግልዎ ስለሚችል ከጎንዎ አያርቁት …›› በማለት ስለገረሱ ድንቅ ሰብዕና ለንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ነገሯቸው። በዚህም መሰረት ወደ ቤተ መንግሥት ተዛውሮ በቤተ መንግሥት እንዲሰራ ተደረገ። በኋላም ወደ ወሎ ጠቅላይ ግዛት ሄዶ በአልጋ ወራሽ አስፋወሰን ኃይለሥላሴ አስተዳደር ስር እንዲሰራ በንጉሰ ነገሥቱ በመታዘዙ ወደ ስፍራው አቅንቶ የአምባሰል ጦር ክንፍ አዛዥ ሆነ፤ በጦር አመራሩ ባሳየው ብቃትም የሻምበልነት ማዕረግ ተሰጠው። ገረሱ በተመደበበት ቦታ በጦር አመራር ችሎታው አመርቂ ብቃት በማሳየቱ ምክንያት ከአንድ ዓመት በኋላ በአልጋ ወራሹ የሻለቃነት ማዕረግ ተሰጠው። የወሎ ጠቅላይ ግዛት ጦርን የመምራት ብቃት እንዳለው ታመነበት።
ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴም ከፋሺስት ድል
መሆን በኋላ በአንድ ወቅት ባደረጉት ንግግር ‹‹ … በገረሱ አመራር ስር የተመዘገበውን ድል የምንመለከተው በትልቅ ኩራትና እርካታ ነው። የወሎን ጦር እንዲመራ ኃላፊነት የሰጠነውም ለዚህ ነበር … ›› በማለት መስክረዋል።
ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት ሻለቃ ገረሱ ጦሩን ይዞ አምባላጌ ወደሚገኘው የራስ ካሳ ኃይሉ ጦር ዘንድ እንዲሄድ በመታዘዙ በፍጥነት ወደ ስፍራው አቀና። እዚያም ደርሶ ከጠላት ጦር ጋር በተደረገው ውጊያ በጀግንነትና በብልሃት ሲዋጋ የተመለከቱት ራስ ካሣ፣ ስለገረሱ ጀግንነት ለንጉሰ ነገሥቱ ነገሯቸው። ምንም እንኳ የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር በዓለም አቀፍ ሕግ የተከለከለ የመርዝ ጋዝ በመጠቀም በኢትዮጵያውያን ላይ አሰቃቂ ጭፍጨፋ ቢፈፅምም እነሻለቃ ገረሱ ከጠላት ጦር ጋር አስገራሚ ፍልሚያ አድርገዋል። ሻላቃ ገረሱም በውጊያዎቹ ላይ ላሳየው ጀግንነት ቤልጅግ ጠመንጃ ከንጉሰ ነገሥቱ እጅ ተሸልሟል። የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ኃይል አመዝኖ ፋሺስት ከሰሜን በኩል ወደ መሐል አገር ሲገሰግስና ንጉሰ ነገሥቱና አልጋ ወራሹ ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ ለንጉሰ ነገሥቱና ለአልጋ ወራሹ ሽፋንና ከለላ ሲሰጥ የነበረው የሻለቃ ገረሱ ጦር ነበር።
ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ወደ ውጭ በመሄድ ዲፕሎማሲያዊ ትግል ለማድረግ ሲወስኑ ሻለቃ ገረሱ ደግሞ ወደ ትውልድ አካባቢያቸው ተመልሰው የጠላትን ጦር ለመፋለም ወሰኑ። በስፍራው እንደደረሱም ሁለት መሰረታዊ ችግሮች ገጠሟቸው። የመጀመሪያው
የጠላት ጦር የጀመረው ሕዝቡን በብሔርና በመደብ የመከፋፈል ስልት ሲሆን፤ ሌላው ደግሞ ‹‹ገረሱ በፋሺስት ላይ ውጊያ የሚከፍት ከሆነ የፋሺስት ጦር የጥቃት ሰለባ እንሆናለን›› የሚለው የአካባቢው ህዝብ ስጋት ነበር። ሻለቃ ገረሱም ሁለቱን ጉዳዮች በጥልቀት በማጤን መፍትሄ መስጠት ጀመሩ። ‹‹ … ጠላታችን አገራችንን ቅኝ ሊገዛ የመጣው ኃይል ነው። ብቸኛ ዓላማውም ነፃነታችንን መንጠቅ ነው። ሃይማኖቶቻችንና ባሕሎቻችንን የሚያጠፋ ኃይል ነው። እኛን ለመከፋፈል ጠላት እንደሆንን አድርጎ ይሰብካል። ሁላችንም የኢትዮጵያ ልጆች ነን። በጠላት የውሸት ፕሮፓጋንዳ መታለል የለብንም። ለበርካታ ዓመታት በዘርና በሐይማኖት ሳንከፋፈል በአንድነት እንደኖርን ዛሬን አንድነታችንን አስጠብቀን ለአገራችን ነፃነት መሰለፍ አለብን። ጠላት አገራችንን ለቆ እንዲወጣ እናድርገው …›› በማለት የትኛውም ብሔር የየትኛውም ብሔር ጠላት እንዳልሆነና ጠላት የሆነው የፋሺስት ጦር ብቻ እንደሆነ ሕዝቡን ማሳመን ጀመሩ።
በ1930 ዓ.ም 100 የሰለጠኑ የፋሺስት ኢጣሊያ ወታደሮች በባንዳ እየተመሩ በገረሱ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ተንቀሳቀሱ። ገረሱም መረጃው እንደደረሳቸው ከ10 አርበኞቻቸው ጋር በመሆን ለመፋለም ተዘጋጁ። የጠላት ወታደሮችን ወደ እነርሱ ስበው በማስጠጋት በአጭር ጊዜ ውጊያ ውስጥ ድል አደረጓቸው። ከሞት የተረፉት የፋሺስት ወታደሮችም የአካባቢው ነዋሪ ምርኮኛ ሆኑ። እነገረሱ ብዙ መሳሪያም ማረኩ። የድሉን ዜና ሰሙ የማሩ፣ የወሊሶ፣
የሶዶ፣ የጨቦ፣ የአመያ እና የዳዋ ሰዎች የጠላትን ጦር ለመፋለም የገረሱን ጦር ተቀላቀሉ።
የሻለቃ ገረሱ ድል አድራጊነትና የደጋፊዎቻቸው መብዛት ያስጨነቀው የፋሺስት ጦር የጦር አውሮፕላን ጭምር የታጠቀ በርካታ ተዋጊ ኃይል አሰባስቦ በገረሱ አካባቢ አከማቸ። ይሁን እንጂ የጦር ኃይል ማብዛት በነገረሱ ከመሸነፍ ውጭ ለፋሺስት ጦር ይህ ነው የሚባል ፋይዳ ማስገኘት አልቻለም። የፋሺስት አስተዳደር በውጊያ ተስፋ ሲቆርጥ አስታራቂ መላክን ምርጫው አደረገ። ከዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ በኢትዮጵያ በኖረው፣ አማርኛን አቀላጥፎ ይናገር በነበረው እንዲሁም የብዙ መኳንንትና ወይዛዝርት ባለሟል መሆን በቻለው ሙሴ ሰባስቲኖ ካስቴና (በአገሬው አጠራር ‹‹ሙሴ ቀስተኛ››) በተባለው የኢጣሊያ መልዕክተኛ በኩል የ‹‹እንታረቅ›› ጥያቄ አቀረበ። [ሙሴ ቀስተኛ በዓድዋ ጦርነት ወቅት ምርኮኛ የሆነና ከዚያም በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ የኖረ ሲሆን፤ ለፋሺስት ጦር ሰላይ ሆኖ ማገልገሉንም የታሪክ መዛግብት ያሳያሉ። ለአብነት ያህል ስመ ጥሮቹ አርበኞችና አገረ ገዢዎች ራስ ደስታ ዳምጠውና ደጃዝማች ገብረማርያም ጋሪ የዚህ ስለላው ሰለባ እንደሆኑም መዛግብቱ ያስረዳሉ]
ስለሙሴ ቀስተኛ ሰላይነት መረጃ የነበራቸው ሻለቃ ገረሱ ግን አስታራቂ ተብሎ የተላከውን ሙሴ ቀስተኛን አስረው ቅጣት አስተላለፉበት። በዚህ የሻለቃ ገረሱ ውሳኔ ክፉኛ የተበሳጨው የፋሺስት ጦር፣ በጀኔራል ማርቲን የተመራ ግዙፍ ጦር በገረሱና በአርበኞቻቸው ላይ በጅባት በኩል አዘመተ። ሙሉ ቀን የፈጀው ውጊያ በሁለቱም ወገኖች ላይ ብዙ ጉዳት ቢያደርስም በመጨረሻ ድሉ የሻለቃ ገረሱና የአርበኞቻቸው ሆነ። በሌሎች ግንባሮችም እነሻለቃ ገረሱ ድሎችን አስመዘገቡ፤ ብዙ የጦር መሳሪያዎችን ማረኩ። በተደጋጋሚ መሸነፉ ያበሳጨው የፋሺስት ጦር ንፁሃን ኢትዮጵያውያንን ‹‹የገረሱ ሰላዮች ናችሁ›› ብሎ በግፍ ገደላቸው። በዚህ የፋሺስት ተግባር የተቆጡ በርካታ ሰዎች ከሻለቃ ገረሱ ጋር በአርበኝነት መሰለፍን መረጡ። ሻላቃ ገረሱ የሚዋጉት እንደጦር መሪ ብቻም ሳይሆን እንደተራ ወታደር ጭምር ሆነው ነበር። ይህን ጀግንነታቸውን የተመለከተ የወቅቱ አዝማሪ እንዲህ ብሎ ገጠመላቸው …
‹‹መድፍና መትረየስ ጥይት ሲጓረሱ፣
አሳላፊ ነበር የማሩ ገረሱ››
በአርበኝነት ትግሉ ዘመን ሻለቃ ገረሱ በወቅቱ ስመ ጥር ከነበሩት ሌላኛው የአርበኞች መሪ ጃገማ ኬሎ ጋር ተገናኝተው ነበር። ጃገማ ወደ ወሊሶ ሄደው በነበረበት ወቅት የፋሺስት ጦር በሻለቃ ገረሱ ላይ ውጊያ ከፍቶ ስለነበር ጃገማና አርበኞቻቸውም በውጊያው ላይ ተሳትፈው የማታ ማታ ድሉ የአርበኞቹ ሆነ። ጀግናን አብዝተው የሚወዱት ሻለቃ ገረሱም ‹‹ … አንተን የመሰለ ጀግና የወለደች እናት ትባረክ …›› ብለው ጃገማን አመሰገኗቸው።
ገረሱና ጃገማ ሌላ የተገናኙበት አጋጣሚም ነበራቸው። የፋሺስት ጦር ድል ሆኖ ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ወደ አዲስ አበባ ተመልሰው ዙፋናቸው ላይ ቢቀመጡም ጎንደርና ጅማ ከጠላት ጦር አልተላቀቁም ነበር። በዚህ ጊዜ ጀግናው አርበኛ ሻለቃ ገረሱ ዱኪ ጃገማን ያውቋቸው ነበርና ለንጉሰ ነገሥቱ ‹‹ … ጃገማን ቢያዙልኝ በአምቦ መንገድ ሄዶ በኋላ በኩል ይቆርጥልኛል …›› በማለታቸው ጃገማ ከሻለቃ ገረሱ ጋር እንዲዘምቱ ታዘዙ። ከዚያም ጃገማ ከሻለቃ ገረሱ ጋር ዘምተው ወደ አጋሮ ወርደው የለመዱትን ጀብድ ፈፅመው ዋናውን አዛዥ ጨምሮ ብዙ የፋሺስትን የጦር መኮንኖች ማረኩ፤ ጦርነቱንም በድል ፈጸሙ።
ከፋሺስት ጦር መባረር በኋላም በ‹‹ፊታውራሪ›› እና በ‹‹ደጃዝማች›› ማዕረጎች በተለያዩ ኃላፊነቶች ላይ አገልግለዋል። በስማቸው ትምህርት ቤት ተሰይሞላቸዋል። ይሁን እንጂ በርካታ ሰዎች ደጃዝማች ገረሱን ጨምሮ ሌሎች ብዙ አርበኞች ለአገራቸው ነፃነት የመድከማቸውን ያህል ከነፃነት በኋላ ተገቢውን ስፍራ እንዳላገኙ በቁጭትና በቅሬታ ተናግረዋል፤ ጽፈዋል።
በፈረስ ስማቸው አባ ቦራ በመባል የሚታወቁት ጀገናው ደጃዝማች አርበኛ ገረሱ ዱኪ፣ ከራሳቸው በተጨማሪ ልጃቸውንም ጭምር በአርበኝነት በማሰለፍ ለኢትዮጵያ አገራቸው ታላቅ ጀብዱ የፈጸሙ ሰው ናቸው። ‹‹ሀገር ከሁሉም ነገር ይቀድማል›› በማለት ብላቴናውን ልጃቸውን ጀግንነት አስተምረውታል። ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ የጦር አርበኛ ብቻ አልነበሩም፤ በህዝብ አገልግሎትና በፀጥታ ማስከበር ዘርፍም ብዙ ተግባራትን አከናውነዋል። በመጨረሻም በ1957 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 28/2012
አንተነህ ቸሬ