አዲስ አበባ፡- የጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎች እና ቅመማ ቅመም ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡ አካላት በጥሬው ከመላክ ይልቅ እሴት ጨምሮ መላክ እንደሚጠበቅባቸው ተገለፀ፡፡
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎች እና ቅመማ ቅመም አዘጋጅቶ ላኪዎች ማህበር ጋር በመተባበር በየዓመቱ የሚያዘጋጀው ዓለም አቀፍ የጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎች እና ቅመማ ቅመም ጉባኤ ለስምንተኛ ጊዜ በሸራተን ሆቴል ትናንት ተጀምሯል፡፡ ማህበሩ በጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመም ምርቶች ላይ እሴት በመጨመር ለውጭ ገበያ ያቀረቡ ሁለት ተቋማትንም ሸልሟል፡፡
በጉባኤው የኢትዮጵያ ጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎች እና ቅመማ ቅመም አዘጋጅቶ ላኪዎች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ኃይሌ በርኼ እንደተናገሩት፤ ላኪዎቹ ያለውን የአገሪቱን የጥራጥሬ፣ የቅባት እህልና የቅመማ ቅመም ምርቶችን እሴት ጨምሮ ወደመላክ መሸጋገር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡ የምርቶቹን ገበያ መዳረሻ ለማስፋትም እሴት የተጨመረበት ምርት ይዘው መቅረብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል፡፡
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የውጭ ንግድ ማስፋፊያ ዳይሬክተር አቶ አሰፋ ሙሉጌታ በበኩላቸው፤ በጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመም ምርት ላይ እሴት ጨምሮ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ቴክኖሎጂ፣ ከፍተኛ የምርት ጥራት እና አቅም ስለሚጠይቅ እየተሰራበት አይደለም፡፡ በዚህ ዓመት እሴት በመጨመር ለውጭ ገበያ ያቀረቡ ተቋማት ማበረታታት የተፈለገው ሌሎቹንም ለማነሳሳት ነው፡፡ ምርቶቹን በጥሬ ወደ ውጭ የሚልኩ ተቋማት እሴት ጨምሮ በመላክ የፖሊሲና የማበረታቻ እድሉን መጠቀም እንዳለባቸውም አመልክተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በ2010 ዓ.ም ከቅባት እህሎች 420 ሚሊዮን ዶላር፣ ከጥራጥሬ 350 ሚሊዮን ዶላር እና ከቅመማ ቅመም 16 ሚሊዮን ዶላር ገቢ አግኝታለች፡፡ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ 20 የጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመም ዓይነቶች ሲሆኑ ሰሊጥና ኑግ ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳሉ፡፡
በጉባኤው ከ15 አገራት የመጡ 260 ዓለምአቀፍ ድርጅቶች የሚሳተፉበት ሲሆን፤ ዛሬ ይጠናቀቃል፡፡
ሰላማዊት ንጉሴ