ኮቪድ 19 (ኮሮና ቫይረስ) በዓለም ላይ በተለይም በቻይናዋ ውሃን ግዛት መከሰቱ ከተሰማበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ከሶስት ሚሊየን አራት መቶ ሺህ በላይ ሰዎችን አጥቅቷል። 240 ሺህ አካባቢ ሰዎችን ደግሞ ለህልፈተ ህይወት ዳርጓል። ለዓለም ኢኮኖሚ መናጋትም ትልቅ ምክንያት ሆኗል። ማህበራዊ ፣ ፖለቲካዊ እና ሀይማኖታዊ ቀውሶችን አስከትሏል። ሀገራት ባሰቡት እና ባቀዱት እንዲሁም እናሳካዋለን ብለው ከያዙት አቅጣጫ እንዲወጡም ጋሬጣ ሆኗል።
ይሄ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ በኢኮኖሚ፣ በቴክኖሎጂ እንዲሁም በህክምና እና በሳይንሱ ጭምር ብቁ ያልሆነውን አፍሪካን በመጎብኘት የጥፋት እጅን ዘርግቷል። እስከአሁን ባለው ሁኔታ በአፍሪካ 39 ሺህ አካባቢ ሰዎች በቫይረሱ ሲጠቁ ከአንድ ሺህ ስድስት መቶ በላይ ሰዎችን ለሞት ተዳርገዋል። ይሄ ጉዳይ ቀድሞውንም ኢኮኖሚያቸው ዝቅተኛ ለሆኑ የአፍሪካ ሀገራት እጅግ ከባድ ፈተናና አስደንጋጭ ክስተት ሆኗል። ከዚህ ስጋት እና ቀውስ መውጣት የሚቻልበት ብቸኛው አማራጭ ከዓለም ጤና ድርጅት እና ከጤና ባለሙያዎች የሚሰጡ መመሪያና መልዕክቶችን መተግበር፣ አስፈላጊውን የጥንቃቄ መንገዶችን መከተል ብቻ ነው።
ወደ ሀገራችን ስንመጣም እነዚህኑ የጥንቃቄ መንገዶችን መከተል የግድ ነው። በኢትዮጵያም የኮሮና ወረርሽኝ መታየቱ ከተሰማበት ከመጋቢት መጀመሪያው ሳምንት ጀምሮ እስከአሁን ባለው መረጃ 133 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል፣ ሶስት ሰዎች ሞተዋል፣ 69ኙ ደግሞ አገግመዋል። ወረርሽኙ ከፍተኛ የሆነ ሞት እና ጉዳት እንዳያስከትል በመንግስት አስቀድሞ በተሰራው ስራ የስርጭት መጠኑ አነስ ብሎ ይታያል። የሚያገግሙ ሰዎች ቁጥርም ከሌሎች የአለም ሀገራት አንጻር ሲታይ የተሻለ ነው።
ይሁን እንጂ የኮሮና ቫይረስ ዛሬም ለሀገራችን ትልቅ ስጋት ሆኖ ቀጥሏል። በየቀኑ ምርመራ ከሚደረግላቸው አንድ ሺህ አካባቢ ሰዎች መካከል ቁጥራቸው ጥቂት ቢሆንም የበሽታው ባህሪ አስቸጋሪ ነውና በዚህ ማንም ሊኩራራ አይችልም። እስካሁን ባለው ሁኔታ የኮሮና ቫይረስን ስርጭት ማቆምና መቆጣጠር ገና አልተቻለም። ስለሆነም አሁንም ቢሆን የሚያዋጣው መዘናጋት ሳይሆን አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረጉ ነው።
የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ማንም ሰው ሊተገብረው የሚችለው ቀላሉ መንገድ እጅን በሳሙናና በውሀ መታጠብ፣ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ እንዲሁም በጣም ወሳኝ ላልሆኑ ጉዳዮች ካልሆነ በስተቀር ከቤት አለመውጣት መሆኑን በተደጋገሚ የጤና ባለሙያዎች እየመከሩ ነው። ይሁን እንጂ አሁንም መዘናጋት ይታያል። በተለይ በገበያ ስፍራዎች፣ በስራ ሰዓት መግቢያ እና መውጪያ ጠዋትና አመሻሽ ላይ የትራንስፖርት ጥበቃ እና የታክሲ ላይ ግፊያ ወረርሽኙ በሀገራችን የሌለ እስኪመስል ድረስ በስፋት ይስተዋላል። ወረርሽኙን ለመከላከል ተብሎ የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም በተገቢው መንገድ እየተተገበረ ነው ለማለት አያስደፍርም። ምክንያቱም በአንዳንድ አካባቢዎች በርከት ያለ የህዝብ እንቅስቃሴ መመልከት የየዕለቱ ትዕይንት ሆኖ ቀጥሏልና። ይሄ የሚታየው መዘናጋት አንዳንድ የዓለም ሀገራትን ያስከተለው አይነት ከፍተኛ የህዝብ ሞት እንዳያስከትል ሊታሰብበት ይገባል።
በአሁኑ ወቅት የጎረቤት ሀገራትን በምናይበት ወቅት የኮቪድ 19 ቫይረስ ስርጭት እየጨመረ እንዳለ እንረዳለን። ከዚሀም ጋር ተያይዞ በተለይ እንደ ሱዳን፣ ጅቡቲና ኬንያ ካሉ ጎረቤት ሀገራት ከትራንስፖርት ግንኙነት በተጨማሪ ድንበር አካባቢ በአካል የመገናኙቱ ዕድል ሰፊ በመሆኑ ቫይረሱን በቀላሉ ለመቀባበል የሚቻልበት አጋጣሚ አለ። ስለዚህ በዓለም ላይ ካየነውና ከሰማነው ልምድ በመነሳት የቫይረሱ ስርጭት አዘናግቶ በአንድ ጊዜ የሚስፋፋ በመሆኑ መዘናጋቱ ዋጋ እንዳያስከፍለን ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል። በጎረቤት ሀገራት የምናየው የወረርሽኝ ስርጭት ለሁላችንም የማንቂያ ደውል መሆኑን በመረዳት እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁንና ሌሎች መመሪያዎችን በጥብቅ ዲስፕሊን መተግበር ያስፈልጋል!
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 25 ቀን 2012 ዓ.ም