አዎ! ተደጋግሞ እንደሚነገረው የምርጫ ዓላማ ሠላማዊ ሽግግርን ማምጣት ነው። ሥልጣን ላይ መወጣጫ ድልድይ ነው። በዴሞክራሲ ሥርዓት የሥልጣን ምንጭ ሕዝብ ነው። እኛ ጋ ሲደርስ ግን የተገላቢጦሽ የሚሆንበት ጊዜ ብዙ ነው። ባለፉት ዓመታት የምርጫ መምጣት ብቻውን የሽኩቻ፣ ግጭት፣ የአለመግባባት…መቀፍቀፊያ ሆኖ ታይቷል። ከምርጫ አለመግባባት ጋር ተያይዞ የሰው ልጆች ክቡር ሕይወት የተቀጠፈባቸው አጋጣሚዎች ተደጋግመው ታይተዋል።
ጊዜው ዓለም ኮሮና በተሰኘ ክፉ ደዌ ተመትታ እየማቀቀች የምትገኝበት ነው። አድገናል፣ ተመንድገናል…የሚሉ ኃያላን አገራት ሳይቀር ዜጎቻቸውን ማዳን አቅቷቸው በከፍተኛ ግራ መጋባት ውስጥ የወደቁበት ታሪካዊ ጊዜ ነው። እስከ ሐሙስ ሚያዚያ 22 ቀን 2012 ዓ.ም ቀትር ድረስ በታላቋ ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ የተያዘው ሰዎች ቁጥር አንድ ሚሊየን የተሻገረ ሲሆን 61 ሺ680 ሞት ተመዝግቧል። ስፔን 236 ሺ 899 ሰዎች ተይዘው 24 ሺ275 ሰዎች ሞተዋል፣ በጣሊያን 203 ሺ591 ሰዎች ተይዘው 27 ሺ 682 ሞት ተመዝግቧል። ወደአፍሪካም ስንመጣ በደቡብ አፍሪካ 5ሺ350 ሰዎች የተያዙ ሲሆን 103 ሰዎች ሞት፣ በግብጽ 5ሺ268 ሰዎች በመያዝ 380 ሰዎች ሞት፣ በአልጄሪያ 3ሺ848 ሰዎች ተይዘው 444 ሰዎች ሞትን አስከትሏል። በኢትዮጵያም እስከ ሐሙስ ዕለት ድረስ በየቀኑ አንድና ሁለት ቁጥሮች እየተደማመሩ የተያዘው ሰዎች ቁጥር 131 ደርሷል። ሶስት ሰዎችንም በሞት ተነጥቀናል። እኛም ያው የዓለም አካል ነንና መንግሥት በአቅሙ የመከላከል ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል። ይኸም የወረርሽኙን ሥራ ማስፈጸም በመደበኛ ህግና ሥርዓት የማይቻል በመሆኑ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወጥቶ በሥራ ላይ ውሏል።
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት፣ እሱን ተከትሎም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መውጣት እንዲሁም ከችግሩ ጋር ተያይዞ በነሐሴ ወር ሊፈጸም ቀን ተቆርጦለት የነበረው ብሔራዊ ምርጫ በጊዜ ገደቡ ማከናወን እንደማይቻል በምርጫ ቦርድ በኩል በጥናት መታወቁ በፓርቲዎች በኩል ሌላ ዙር ፍትጊያን ፈጥሯል። እያንዳንዱን እንደ ኮሮናው መላ ቅጡ የማይታወቅ ተቃውሞ ውስጥ ጥዶታል። በአንድ በኩል ተቀናቃኝ ፓርቲዎች የኮሮና ወረርሽኝ ዓለም አቀፍ ችግርን ለመከላከል መንግሥት የወሰዳቸው እርምጃዎች ትክክለኝነት እየመሰከሩ በሌላ በኩል ምርጫ በጊዜ ሰሌዳው መሠረት ማካሄድ አለመቻሉን ላለመቀበል የሚያንገራግሩበት ሁኔታ ተፈጥሮ እያየን ነው። አንዳንድ ፓርቲዎች መንግሥት ኮቪድ 19 ገዥው ፓርቲ ሆን ብሎ የምርጫ ጊዜውን ለማራዘም በሰበብነት መጠቀሙ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ሲናገሩም ተሰምተዋል።
ሌሎች “ቀድሞም ምርጫው እንደማይካሄድ ተናግረናል፣ ኮሮና ሰበብ ነው” በሚል አጀንዳውን ወደ ፖለቲካ ጠቅለው ለማዞር ዳር ዳር ብለዋል። አንዳንዶችም ፈጠን ብለው ጉዳዩ ሕገመንግሥታዊ ሳይሆን ፖለቲካዊ መፍትሔ ያስፈልገዋል በማለት የሽግግር መንግሥት ምሥረታ (የሥልጣን መጋራት) ፕሮፖዛላቸውን ከመሳቢያቸው ውስጥ ብቅ ማድረግ ጀምረዋል።
እነዚህ ፖለቲከኞች (ከብልጽግና እና ኢዜማ በስተቀር) ይህንኑ ሁሉ የሚያወሩት የኮቪድ 19 ወረርሽኝን እያስከተለ ያለውን ቀውስ ወደጎን ገሸሽ በማድረግ ጭምር መሆኑ ሲበዛ ያሳዝናል።
የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ሐሙስ ሚያዚያ 22 ቀን 2012 ዓ.ም ፓርላማ ቀርበው የኮቪድ ወረርሽኝን ተከትሎ ቦርዱ በተያዘው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ምርጫ ማካሄድ ያለመቻሉን ጉዳይ አስረዱ። ቦርዱ ለፓርላማው ባቀረበው ጥናታዊ ሀሳብ ይዘትንም ምን እንደሆነ ካብራሩ በኋላ ፓርላማው በአብላጫ ድምጽ ተቀብሎት ምክረ ሀሳቡን ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መርቶታል።
የሆኖ ሆኖ እንደ ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ዓይነት ልባም እና የአገር ጉዳይን ከምንም በላይ የሚያስጨንቀው ፓርቲ ስለቀጣዩ ምርጫ ዕጣ ፈንታ በጥናት ላይ የተመሰረተ ዝርዝር ያለ ሰነድ ማውጣቱ ትልቅ ተስፋን ይሰጣል። የኮሮና ወረርሽኝን ተከትሎ አገሪቱ ተገድዳ የገባችበት የምርጫ ማራዘም አጣብቂኝ መውጫ መንገድ ለማመላከት ስለጉዳዩ
ዝርዝር ጥናት ያደረጉ ሌሎች ፓርቲዎች ስለመኖራቸው የዚህ ጹሑፍ አቅራቢ መረጃ የለውም። ካሉ ግን በአድራሻዬ ቢያሳውቁኝ በሌላ ጊዜ የምመለስበት ይሆናል።
የፓርቲው ሰነድ በጨረፍታ
የዓለማችንና የሀገራችን የወቅቱ ዋነኛ የጤና ተግዳሮት በሆነው የኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት በዚህ ዓመት ይካሄድ የነበረውን ጠቅላላ ምርጫ ማካሄድ እንደማይችል የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ መግለጹ ይታወሳል። ይህንኑ ውሳኔ ተከትሎ ቀጣዩ ምርጫ መቼ እና እንዴት ይካሄዳል? በስልጣን ላይ ያለው መንግስት የስልጣን ዘመኑ ሲጠናቀቅ ሀገር እንዴት ትተዳደራለች? የሚሉ እና ተያያዥ ጥያቄዎች በስፋት እየቀረቡ ይገኛል። ላጋጠመን ህገ መንግስታዊ አጣብቂኝ ተገቢ መፍትሔ በጊዜ መፈለግ ያስፈልጋል።
ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የምርጫ መራዘምን ተከትሎ የገጠመንን ህገ መንግስታዊ አጣብቂኝ ለመፍታት ባለፉት ጥቂት ወራት ጥናት ሲያደርግ የቆየ ሲሆን፣ በህገ መንግስቱ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን የሥራ ዘመን በተመለከተ (አንቀጽ 58/3) ላይ ማሻሻያ ማድረግ የተሻለው አማራጭ ነው የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሷል።
በዚሁ መሰረት በአንቀጽ 58 (3)፡
“የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚመረጠው ለአምስት ዓመታት ነው፤ የስራ ዘመኑ ከማብቃቱ ከአንድ ወር በፊት አዲስ ምርጫ ተካሂዶ ይጠናቀቃል”
በዚህ ላይ ማሻሻያ በማድረግ ምርጫው ሊራዘም የሚችልበትን ህጋዊ መሰረት መፍጠር ያስፈልጋል። ይህንን ማሻሻያ ማድረግ ከሌሎች አማራጮች በተሻለ እንደ ሀገር የገጠመንን አጣብቂኝ በቀላሉ አልፈን፣ ሙሉ አቅማችንን ወረርሽኙን ለመከላከል እንድንጠቀም ብሎም አላስፈላጊ የፖለቲካ ቀውሶችን ለማስወገድ ይረዳናል ብሎ ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ያምናል።
የእነ አቶ ልደቱና ኢ/ር ይልቃል – አብሮነት
“….በህገ-መንግስቱ አንቀፅ 58/3 እና አንቀፅ 72/3 መሰረት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የስራ ዘመን አምስት ዓመት ብቻ ስለመሆኑ በግልፅ ተቀምጧል። አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ወይም ምርጫ ማካሄድ የማይቻልበት አስገዳጅ ሁኔታ ሲገጥም የመንግስትን ዕድሜ እንዴት ማራዘም እንደሚቻል ህገ-መንግስቱ ምንም ዓይነት ድንጋጌ አላስቀመጠም። ስለሆነም ብልፅግና ፓርቲ እንዲህ ዓይነት ህገ-መንግስታዊ ቀውስ እንዲከሰት ምክንያት የሆኑትን የህገ-መንግስቱን አርቃቂዎች እና ለህገ-መንግስቱ ክፍተት መታየት ምክንያት የሆነውን ኮሮና ቫይረስን “ከመርገም” ውጭ በህጋዊ መንገድ የሥልጣን ዘመኑን ለአንድም ቀን የሚያራዝምበት ምንም ዓይነት መብትና ስልጣን በህገ- መንግስቱ አልተሰጠውም።
በህገ-መንግስቱ አንቀፅ 60 ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን በትነው በ6ወር ጊዜ ውስጥ ምርጫ እንዲያካሂዱ ስልጣን የተሰጣቸውም በሕገ-መንግስቱ የተቀመጠውን አምስት ዓመት የመንግስት የስልጣን ዘመን ለመጨረስ ነው እንጂ ከአምስት ዓመት በላይ የመንግስትን የስራ ዘመን ለማራዘም አይደለም። እንዲያውም በህገ- መንግስቱ አንቀፅ 60/1 ላይ በግልፅ እንደተቀመጠው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔ ድጋሚ ምርጫ መካሄድ የሚችለው በስልጣን ላይ ያለው መንግስት የስራ ዘመን ከመጠናቀቁ በፊት ብቻ ነው። ስለዚህ ይህ ህገ-መንግስታዊ ድንጋጌ በህግ የተሰጠን የስራ ዘመን ለማጠናቀቅ ከመቻል ጋር እንጂ የስራ ዘመንን ከማራዘምና የመንግስት የስራ ዘመን ካለቀ በኋላ ከሚካሄድ ምርጫ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የለውም።
በህገ-መንግስቱ አንቀፅ 93/1፣ ሀ እና ለ ላይ በግልፅ እንደተደነገገውም የመንግስትን የስልጣን ዘመን ለማራዘም ተብሎ ሊታወጅ የሚችል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የለም። አሻሚና አከራካሪ ባልሆነ መንገድ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለምን ዓይነት ጉዳዮች ሊታወጅ እንደሚችል ህገ-መንግስቱ በዝርዝርና በግልፅ ስላስቀመጠ መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ ስልጣኑን ለአንድም ቀን ለማራዘም የሚያስችለው ህጋዊ መብትና ስልጣን የለውም።
እንደ ሶስተኛ አማራጭ እየታየ ያለው ህገ-መንግስቱን አሻሽሎ የመንግስትን የስራ ዘመን ለማራዘም መሞከርም ህጋዊነትን የተከተለ አሰራር አይደለም። አንድ በስልጣን ላይ የሚገኝ መንግስት የራሱን የስልጣን ዘመን ለማራዘም ሲል በስራ ላይ ያለውን ህገ-መንግስት የሚያሻሽል ከሆነ፣ እንዲህ ዓይነቱ ድርጊት እንደ አንዳንድ አምባገነን የአፍሪካ መሪዎች በአለም ፊት መሳቂያ እና መሳለቂያ የሚያደርግ የአምባገነኖች ድርጊት እንጂ ህጋዊ አሰራር ተደርጎ ሊቆጠር አይችልም። እንዲህ ዓይነቱ የስልጣን ዘመንን ለማራዘም ሲባል ህገ- መንግስትን ለማሻሻል የመሞከር ዕርምጃም ከህግ መኖርና አስፈላጊነት መሰረታዊ መርህ ጋር የሚጋጭ ህገ-ወጥ ተግባር ነው። በእንዲህ ዓይነቱ ሂደትም ማንኛውም የፖለቲካ ሃይል የህዝብ ቅቡልነት ሊያገኝ አይችልም።
እንዲህ ዓይነቱን ከባድ አገራዊ ጉዳይ አሳታፊና ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ለመወሰን መሞከርም አገራችን በአሁኑ ወቅት ምን ያህል ሁለንተናዊ የህልውና ፈተና ውስጥ እንደምትገኝ አለመረዳት ነው። ይህም እንደተለመደው የገዥውን ፓርቲ ከአገር ጥቅም ይልቅ የራሱን ስልጣን የማስቀደም ሃላፊነት የጎደለው ፍላጎት የሚያሳይ ነው።
ስለዚህ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የህገ-መንግስቱ አርቃቂዎች በሰሩት ስህተት እና በኮሮና ቫይረስ ወደ አገራችን መግባት ምክንያት በአሁኑ ወቅት በአገራችን የመንግስት የስራ ዘመንን አስመልክቶ ህገ-መንግስታዊ ቀውስ (Constitutional Crisis) መፈጠሩን አምኖ መቀበል ያስፈልጋል። እንዲህ ዓይነት ህገ-መንግስታዊ ቀውስ በአንድ አገር ሲፈጠር ደግሞ ለችግሩ መፍትሄ መስጠት የሚቻለው በመደበኛ የህግ አሰራር ሳይሆን ከመደበኛ የህግ አሰራር ውጭ (Extra Constitutional) በሆነ መንገድ ነው። እንዲህ ዓይነቱን መፍትሄ ለመስጠትም በተለየ ሁኔታ በህግ መብት የተሰጠው የፖለቲካ ፓርቲ ወይም መንግስታዊ ተቋም ስለሌለ የተፈጠረውን ህገ-መንግስታዊ ቀውስ እንዴት እንፍታው? በሚለው ጥያቄ ተነጋግሮ የመፍትሄ አቅጣጫ የሚያስቀምጥ ሁሉን አቀፍ አገራዊ የምክክር ሂደት (National Dialogue) መጥራት ያስፈልጋል …..”
ጀዋር መሐመድ
ገዥው ፓርቲ (መንግሥት) ምርጫውን ከማራዘም ጋር ተያይዞ ሕገመንግሥቱን መሰረት በማድረግ በባለሙያዎች አስጠንቶ የቀረበውን አራት አማራጮች ከተሰሙ በኋላ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረንስ (ኦፌኮ) አባል የሆኑት አቶ ጀዋር መሐመድ ተቃውሞአቸውን በፌስቡክ ገጻቸው አቅርበዋል።
“አራቱም አማራጮች ሕጋዊ መሠረት የላቸውም፤መፍትሔው ሕጋዊ ሳይሆን ፖለቲካዊ ስምምነት መፍጠር ነው” ብለዋል።
ኢዜማ
“ከምርጫ በፊት ጤናን ማስቀደም ይገባል” በሚል አቋም ወገንን የሚታደግ ሰፊ የደም ልገሳ መርሃግብር በመዘርጋት ከከፍተኛ አመራሩ ጀምሮ በየደረጃው አባላቱ ደም የመስጠት ሥራ ማከናወናቸው ፓርቲው ማህበራዊ ኃላፊነትን ለመወጣት የሄደበትን ርቀት የሚያሳይ ነው።
የገዥው ፓርቲ ሀሳብ
በኮቪድ19 ምክንያት ቀጣዩን ምርጫ ለማካሄድ አስቸጋሪ በመሆኑ ገዥው ፓርቲ (መንግስት) አራት የመፍትሄ አማራጮችን ስለማቅረቡ ከሰሞኑ ተሰምቷል።
“ኮቪድ19 ምርጫን ማራዘም እና የሕግ አማራጮች” በሚል ርዕስ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት ባለፈው ዕረቡ ዕለት መንግስት ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ሲቪክ ማህበራት ጋር ውይይት አካሂዷል።
ኢትዮጵያ በሕገ መንግስቱ መሠረት እስከ ነሃሴ ወር ማለቂያ ድረስ አጠቃላይ ምርጫ የማካሄድ ግዴታ ቢኖርባትም የኮቪድ19 ወረርሽኝ ምርጫን ማከናወን የማያስችል ደረጃ ላይ በማድረሱ ምክንያት ህግና እውነታውን አጣጥሞ መሄድ አስፈላጊ መሆኑ ተነስቷል።
የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ምክትል አቃቤ ህግ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ እንዳሉት ችግሩን ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱን በማያፋልስ መልኩ ለመቅረፍ አራት የመፍትሄ አማራጮች ተቀምጠዋል።
- የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን መበተን፤
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን መበተን፤ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 60/1 መሰረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የስልጣን ዘመኑ ከማለቁ በፊት አዲስ ምርጫ ለማካሄድ በምክር ቤቱ ፈቃድ ምክር ቤቱ እንዲበተን ማድረግ ይችላል የሚለውን ታሳቢ ያደረገ ነው። - የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ፤
በህገ መንግስቱ አንቀጽ 93/1 መሰረት የውጭ ወረራ ሲያጋጥም ወይም ህገ መንግስታዊ ስርአቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲከሰትና በተለመደ የህግ ማስከበር ስርአት መቋቋም የማይቻል ሲሆን፤ ማናቸውም የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም ወይም የህዝብን ጤንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰት የፌደራሉ መንግስት የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመደንገግ ስልጣን አለው የሚለውን ታሳቢ ያደረገ ነው። - ህገ መንግስት ማሻሻል፤
አማራጭ ሶስት ህገ መንግስት ማሻሻል፤ በህገ መንግስቱ ግልጽ የሆነ መሰረት ያለው ሲሆን አንቀጽ 104 እና 105 ላይ በግልጽ ተቀምጧል። የህገ መንግስት ማሻሻያ ሃሳብን ለማመንጨት ሶስት ምዕራፎች አሉ።
የህገ መንግስት ማሻሻያ ሃሳብን ማመንጨት፤ የፌደራል መንግስት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ2/3 ድምጽ ከደገፈው ወይም የፌዴሬሽን ምክር ቤት በ2/3 ድምጽ ሲያጸድቀው ነው።
የፌዴሬሽኑ አባል ከሆኑ ክልሎች 1/3 ድምጽ (አሁን ባለው ሁኔታ ከዘጠኙ ሶስቱ ክልሎች በምክር ቤቶቻቸው ከደገፉት የማሻሻያ ሃሳብ መንጭቷል ማለት ይቻላል።
የማሻሻያ ሃሳቡን ማጸደቅ፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት በጋራ ስብሰባ በ2/3 ድምጽ የቀረበውን ማሻሻያ ሲያጸድቁት እና ከፌዴሬሽኑ አባል ክልሎች ምክር ቤቶች የ2/3 ክልሎች ምክር ቤቶች በድምጽ ብልጫ የቀረበውን ማሻሻያ ሲያጸድቁት ነው የሚለውን ታሳቢ ያደረገ ነው ። - የህገ መንግስት ትርጓሜ መጠየቅ
የህገ መንስት ትርጓሜ መጠየቅ፤ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 62/1 እና አንቀጽ 84/1 መሰረት በግልጽ ተቀምጧል የሚለውን ታሳቢ ያደረገ ነው።
እንደ መውጫ
ምርጫው በመራዘሙ ምክንያት አገራችን የገባችበትን አጣብቂኝ መውጫ መንገዱ መንግሥት ያቀረበው አራት አማራጮች ብቻ ናቸው ማለት አይቻልም። በመንግሥት በኩል በይፋ እንደተገለጸው ሌሎች አማራጭ ሀሳቦች የማቅረብ በሩ ለፖለቲካ ኃይሎች ሁሉ አልተዘጋም። የኮሮና ወረርሽኝ በድንገት መከሰት የምርጫ የጊዜ ሰሌዳን ማዛባት የፈጠረው በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ አይደለም። በተለያዩ አገሮች ሊደረጉ የነበሩ አጠቃላይ የምክር ቤትና ፕሬዚዳንታዊ ምርጫዎች፣ ድጋሚ ምርጫዎች፣ አካባቢያዊ ምርጫዎች ተራዝመዋል። (IFES) የተባለ ዓለም ዓቀፍ ተቋም ባጠናቀረው ሪፖርት መሰረት አርባ ሰባት አገሮች የተለያዩ አይነት ምርጫዎችን አራዝመዋል። በአሜሪካ የሚገኙ ሀያ ሁለት ግዛቶች ደግሞ አካባቢያዊ ምርጫዎችንና የዕጩ ፕሬዚዳንቶችን ቅድመ ምርጫ ውድድር አራዝመዋል። አንዳንድ አገሮች ምርጫውን ከስድስት ወር እስከ አንድ ዓመት ለሚሆን ጊዜ ያራዘሙ ሲሆን ሌሎች ደግሞ ምርጫውን ላልተወሰነ ጊዜ እንዲራዘም አድርገዋል።
በኢትዮጵያም የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ተከትሎ ያጋጠመው የምርጫ ማራዘም አጣብቂኝን ለማለፍ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች በፍጹም መግባባት፣ በቅንነት፣ በአርቆ አሳቢነት መንፈስ ሊንቀሳቀሱ ይገባል። ጉዳዩን ከፖለቲካና ከራስ ጥቅም በላይ በማየት ጥቃቅን ልዩነቶችን፣ አለመግባባቶችን ለጊዜው ተወት በማድረግ ችግሩን በጋራ ለመጋፈጥ መተባበሩ ሁሉንም ወገኖች አሸናፊ ያደርጋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 24/2012
ፍሬው አበበ