አዲስ አበባ፡- የደቡብ ዞን የኦነግ ጦር የቀረበለትን የሰላም ጥሪ ተቀብሎ በሰላማዊ መንገድ ትግል ለማድረግ መወሰኑ አባ ገዳዎችን በማሳተፍ የማይፈታ ችግር እንደሌለ ያሳያል ሲሉ የጉጂ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ሮባ ቱርጬ ተናገሩ፡፡
አቶ ሮባ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት፤ ባለፉት ሁለት ሳምንታት በጉጂ ዞን አባገዳዎች አማካኝነት የሰላም ሳምንት ታውጇል፡፡ በአካባቢው ይንቀሳቀስ የነበረው የኦነግ ሠራዊትም የሰላም ጥሪውን ተቀብሏል፡፡ አባገዳዎች በህብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ተደማጭነት አላቸው፡፡ በርካታ ችግሮች በነበሩበት ወቅትም ጭምር በውይይት በመፍታት ፋይዳቸው የላቀ ሲሆን፤ የአሁኑ ሁኔታም ይህን ያረጋግጣል፡፡ የደቡብ ዞን የኦነግ ጦር የቀረበለትን የሰላም ጥሪ መቀበሉ አባ ገዳዎችን በማሳተፍ የማይፈታ ችግር እንደሌለ ያሳያል፡፡
እንደ አቶ ሮባ ገለጻ፤ የሰላም ሳምንቱ ዋና ዓላማ በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ የኦነግ ታጣቂዎች መንግሥት ያስተላለፈውን ጥሪ ተቀብለው የትጥቅ ሳይሆን የሃሳብ ትግል እንዲያደርጉ ለማስቻል ነበር፡፡
በዚህም ጥሩ ተስፋዎች ታይተዋል፡፡ የኦነግ ታጣቂዎች ከአካባቢው አባገዳዎች ጋር የተነጋገሩ ሲሆን፤ በቀጣይም መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ሁሉም ነገር ይከናወናል፡፡ ከዚህ ቀደም መንግሥት ባደረገው ጥሪ መሰረት ወደ ሀገር ቤት የገቡ የኦነግ ታጣቂዎች ሥልጠና በመውሰድ ወደ ተለያየ ሥራ ተሰማርተዋል፡፡
‹‹ጦርነት ካለ ሰላምን ማሰብ አይቻልም›› ያሉት አስተዳዳሪው ዛሬ ሰላም ቢሆን ነገ የሚሆነው አይታወቅም ከታጠቀ ኃይል ጋር ግጭት ሲፈጠር ቁሳዊም ሆነ ማህበራዊ ጉዳት ሊከተል ስለሚችል ሁኔታዎችን አስተውሎ ጉዳዩን በሰላማዊ መንገድ መፍታት አስፈላጊ ነው፡፡ ይህም የሰው ህይወት መጥፋት፣ መፈናቀልና የንብረት መውደም እንዳይኖር ህብረተሰቡ በሰላም ወጥቶ እንዲገባ ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል፡፡
አባገዳዎቹም ሆኑ እኛ እንደመንግሥት ያለን አቋም ሰላም ማምጣት ነው የሚሉት አቶ ሮባ፤ አሁን ላይ የዴሞክራሲያዊ ትግል ሜዳው በመስፋቱ ማንኛውም አካል በሰላም መታገል እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ በአካባቢው የትጥቅ ትግል፣ ሁከትና ግጭት አብቅቶ ህብረተሰቡ በሰላም ወጥቶ መግባት እንዲችል ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
‹‹ማንኛውም አካል በሰላም መታገል ይችላል፡፡ በጥይት መታገል ግን ከእንግዲህ ማብቃት አለበት፡፡ መሆን ያለበት የሐሳብ ትግል ነው፡፡ ጦርነት ባለበት አገር ህብረተሰቡ በሰላም ወጥቶ መግባት አይችልም›› ያሉት አቶ ሮባ በአባገዳዎች የተደረገው ጥረት ስጋቶችን እንደሚያስቀር አመልክተዋል፡፡
የጉጂ ዞን የኦነግ ጦር አዛዥ ኤሊያስ ጋምቤላ ጎሎ የጉጂ አባ ገዳዎች ባወጁት የሰላም ሳምንት ወቅት ያቀረቡለትን የሰላም ጥሪ ተቀብሎ ወደ ሰላማዊ ትግል መመሰሉም ይታወቃል፡፡ የጉጂ አባ ገዳ ጂሎ መንኦ ሂደቱን አስመልክቶ እንደተናገሩት፣ በጉጂ እና ምእራብ ጉጂ ዞን የሚገኙ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ጦር አመራሮች የቀረበላቸውን የሰላም ጥሪ ተቀብለዋል፡፡ ማንኛውም የፖለቲካ ኃይል መንግሥት ባመቻቸው የሰላማዊ ትግል መንገድ ብቻ መታገል አለበት፡፡ ከሰላማዊ ፉክክር ውጪ የሚደረግ የትጥቅ ትግል ተቀባይነት የለውም።
አዲስ ዘመን ጥር 9/2011
በኢያሱ መሰለ