ከቤት የሚያውሉ ነባር ”የተፈጥሮ ጀግኖች‘
“ቤታችሁ ውስጥ ተሰብሰቡ!” የሚለው መንግሥታዊ ትዕዛዝ ለእኛ ለኢትዮጵያዊያን በይፋ ከደረሰን ሳምንታት ተቆጥረዋል። ስሙን ቄስ ይጥራውና (ለነገሩ ከቄስ ይልቅ የጤና ባለሙያዎች እርግማኑን ቢያጸኑልን የሚሻል ይመስለኛል) ይሄ ምንትስ የሚባለው ወረርሽኝ ከቤት ኮርኩዶ ሊያውለን ግድ ሆኗል። እንደ ካሁን ቀደምቶቹ ጽሑፎቼ ሳይሆን በዚህኛው ጽሑፌ ስሙን ለመጥራት የተጸየፍኩት ሰሞንኛ ወረርሽኝ እኛን ብቻ ሳይሆን መላውን ዓለም እያስጨነቀና እያስማጠ እንዳለ እየሰማንም፣ እያየንም፣ እየደረሰብንም ነው።
የወረርሽኙ ግዝፈት ጉልበቱን ሳይሰስት እያሳየ ያለው በቀዳሚነት “በጉልበተኛው አሜሪካ” ላይ ይመስላል። ለተፈጠረባት የቻይና ምድር ራርቶም ይሁን ወይንም ተሸንፎ ብቻ ኮተቱን ጠቅልሎ በሌሎች ሀገራት ላይ ዘምቶ ሥልጣኑን እያሳየ እንዳለ እያስተዋልን ነው። የአውሮፓ ሀገራትም በጡንቻው ተደቁሰዋል። ሰልጥነናል፣ በልጽገናል የሚሉት ሀገራት “የራሳቸው ማረሩን ልብ ሳይሉ በአፍሪካ አህጉር ላይ እያሟረቱ የሌላውን ገበና ሲያማስሉ ለትዝብት ተዳርገዋል። እኛስ የማታ ማታ ወረርሽኙን በቀላሉ እንገታዋለን ይብላን ለድሃዎቹ የአፍሪካ ሀገራት! ምን ይውጣቸው ይሆን?” እያሉ በመጠቃቀስ አፍሪካን ወደመሳሰሉ ታዳጊ ሀገራት በአንዱ ጣታቸው ሲቀስሩ ሦስቱ ጣታቸው ወደ እነርሱ መጠቆሙን ያስተዋሉ አይመስልም። የሀገራችን ዜመኛ እንዳንጎራጎረው፤
”በአንዱ ስትጠቁም በጣቶችህ መሃል፣
ሦስቱ ግን ራስህን ይመለከቱሃል።‘
መሆኑ ነው። ግሩም ቅኔ ነው ጃል! እኔም አንድ ሃሳብ ላክልበት። በአንዱ ጣታችን ወደ ሌላው ስንጠቁም ሦስቱ ወደ ጠቋሚው መመልከታቸው እንዳለ ሆኖ አራተኛው አውራ ጣት ወደ ላይ ወደ ፈጣሪ ማመልከቱ ልብ ሊባል ይገባል።
“ከቤት ዋሉ!” ትዕዛዝ ለሀገራችን እንግዳ ሆኖ ግር ቢያሰኘንም አብዛኞቹ በዚህ ምንትስ ባልነው ወረርሽኝ እየተጠቁ ያሉት ሀገራት ለዘመናት ከዓመት ዓመት ሲፈጽሙት የኖሩት ትዕዛዝ እንደሆነ እንረዳለን። ከአፍሪካ ውጭ በሚገኙ ብዙ ሀገራት ቶርኔዶ፣ ሱናሚ፣ ሄሪኬን፣ ሳይክሎን ወዘተ. በሚል ስያሜ የሚታወቁ የተፈጥሮ ነውጦች ብዙዎቹን ሀገራት እንደቀጠቀጡ አሉ። የብዙ ዜጎቻቸውን ሕይወት ሲነጥቁ፣ ከፍተኛ ንብረትና መሠረተ ልማቶችን ሲያወድሙም እየተመለከትንና እየሰማን ነው።
በሀገራችን ቋንቋዎች “በረዶ የቀላቀለ ዐውሎ ነፋስ፣ የባህር ወጀብ፣ የውቂያኖስ ቁጣ፣ የበረዶ መዓት” እያልን ስም የሰየምንላቸው “የተፈጥሮ ጀግኖች” የሚያናውጧቸው ሀገራት የቁጣውንና የመቅሰፍቱን አመጣጥ በቴክኖሎጂያቸው ተንብየው ዜጎቻቸው ከቤት እንዲውሉ የማስጠንቀቂያና የማሳወቂያ መልእክቶችን የሚያደርሱላቸው በነጋ በጠባ ነው። እንዲያውም ብዙ የሰለጠኑት ሀገራት ዜጎች በንቃት የሚከታተሉት መገናኛ ብዙኃን የሚሰጡትን የየዕለቱን የአየር ንብረት ትንበያ ነው። የተፈጥሮ አደጋ ሊከሰት እንደሚችል መረጃው የደረሳቸው ዜጎችም ለትዕዛዙ አሜን ብለው ወደየመሸሸጊያቸው መደበቃቸው የተለመደ ክስተት ሲሆን መሸሸጊያዎቹ ከቁጣ በትር አላድን ብሏቸው የሚያልቁ ምስኪኖች ቁጥርም በቀላሉ የሚገመት አይደለም።
ይህ ጸሐፊ “የበረዶ ግምጃ ቤት በሆነችው” በአሜሪካዋ የሚኒሶታ ክፍለ ግዛት በቆየባቸው አራት ያህል ዓመታት ይህንን መሰሉን “ከቁጣ ሽሹ ትዕዛዝ” አክብሮ ወደ መሸሸጊያው ፈጥኖ በመሰወር የሰነበተባቸው በርካታ ቀናት ዛሬም እንደ ትኩስ ክስተት ከአእምሮው አልጠፋም። የተፈጥሮ ቁጣ እስኪያልፍ ድረስ መከለልና መጠለል ለሰው ልጆች እንግዳ አይደለም የሚባለውም ስለዚሁ ነው። ለእኛ ለኢትዮጵያዊያን ይህን መሰሉ ትዕዛዝ እንግዳ ሆኖ ቁጣው እስኪያልፍ ድረስ ቤት
መዋሉ ቢያቁነጠንጠንም መንግሥታዊ ትዕዛዙን በበጎነት ተቀብለን “በረከተ መርገም” (ፈረንጆቹ A blessing in disguise እንዲሉ) አንዳች ቁምነገር ብንሰራበት የታሪካችን አንዱ ክፍል ሆኖ ለልጅ ልጆቻችን ሳይቀር የሚተላለፍ መታሰቢያ ልናቆም እንችላለን።
ከቤት ውሏችን ጋር የተሰጡ ”የቤት ሥራዎች‘፤
በርካታ የመንግሥት ተቋማትና አንዳንድ የግሉ ዘርፍ ድርጅቶች እየፈተነን ባለው ወረርሽኝ ምክንያት ለብዙ ሠራተኞቻቸው ፈቃድ ሰጥተው ሥራቸውን ቤት ውስጥ እንዲያከናውኑ ፈቅደውላቸዋል። ውሳኔው ችግር እንደሌለበትና የሚያስመሰግን መሆኑን ብንረዳም አንዳንድ መሠረታዊ ጥያቄዎች መነሳታቸው ግን አልቀረም።
ቤት ውስጥ ተሠርቶ የሚዋለው ሥራ ምን ዓይነት ነው? በየትኛው ቴክኖሎጂ ተደግፎ? ሥራው እንደታቀደው በተባለለት ጊዜ ተከናውኗል ቢባል እንኳ ውጤት መመዝገቡ የሚረጋገጠው በምን ዓይነት ዘዴ ነው? ሠራተኛውስ ምን ያህል ለዲሲፕሊን ተገዢ ይሆናል? እና መሰል ጥያቄዎችን ማዥጎድጎድ ይቻላል።
እርግጥ ነው የቤት ሥራን ስንለማመድ የኖርነው ከልጅነታችን የተማሪነት ዘመን ጀምሮ መምህራኖቻችን በሚሰጡን “Home Work” ስለነበር አሠራሩ ግር ላይለን ይችላል። ሙግት ካስፈለገ ሊያሟግተን የሚችለው “ማን ይሙት በሀገራችን የቴክኖሎጂ እጥረትና የሥራ መሳሪያ ባልተሟላበት ሁኔታ እንደምን ትዕዛዙ ሊተገበር ይችላል? ሁላችንም ኑሯችንን ስለምናውቀው እንኳንስ የቤት ውስጥ ቢሮ ልናደራጅ ይቅርና “የምግብ ጠረጴዛ” እንኳ ብርቅ በሆነበት የኑሯችን ዘይቤ ውስጥ ምን ያህል ለሥራ እንነቃቃለን? ምን ያህልስ ውጤታማ መሆን ይቻላል? ሌላው ቢቀር “ቤት ውለህ ሥራህን አከናውን?!” የተባለው ታዛዥ ሠራተኛ ምን ያህሉ ሰው የኮምፒውተርና የኢንተርኔት አገልግሎት ያገኛል? ብለን ብንከራከር ለመማማር ይበጃል እንጂ “በእኛ ሥራና እንጀራ ምን አገባችሁ?” ተብለን ልንወቃቀስ አይገባም። ሀገሬ በተግባር እንድትለማመዳቸው ከምጓጓባቸው ምኞቶች መካከል አንዱ “ታክስ ከፋይ እኮ ነኝ!” የሚሉ መብታቸውን ጠያቂ ዜጎችን ፈጥራ ማየት ነው። ለእኛ እንኳ የዚህ ፉከራ ፀጋ ባይደርሰን ከልጆቻችን አልፎ ወደ ልጅ ልጆቻችን እንዳይተላለፍ መጸለዩ አይከፋም።
ሥራ አልባ “የቤት ሥራ ተሰጥቶት” ሰሞኑን ቤት ከዋለ አንድ ወዳጄ ጋር ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ ስንወያይ የጠቀሰልኝ የራሱ ተሞክሮ ብዙዎችንም ያጋጠመ ይመስለኛል። ይህ ሰው የአንድ ትልቅ የመንግሥት ተቋም ከፍተኛ ኤክስፐርት ነው። እርግጥ ነው መ/ቤቱ የአገልግሎት ጊዜዋ ሊያልቅ አንድ ሐሙስ የቀራት አሮጌ ላብቶፕ ኮምፒውተር ሰጥቶታል። ሥራ አልተሰጠውም እንዳይባልም ፋይዳው እጅግም የሆነ ጥናት እንዲሰራ ታዟል።
ለጥናቱ የሚረዱትን መረጃዎች ለመሰብሰብ እንዲያግዘው ግን የኢንተርኔት አገልግሎት የለውም። ይህንን ችግሩን ለአለቆቹ ደጋግሞ ቢያስረዳም ጆሮ የሚሰጠው ኃላፊ ሊያገኝ አልቻለም። ያለው አማራጭ “ኢንተርኔት ካፌ” ጎራ እያለ ልጆቹ ከሚሆኑ ጎረምሶች ጋር እየተጋፋ አገልግሎት ማግኘት ነበር። አገልግሎቱን ማግኘት አንድ ነገር ሆኖ ወረርሽኙን በሚመለከት ያለውን አደጋ መገመት አይከብድም። ይሄው ወዳጄ እንዳጫወተኝ መሠረታዊ ጥያቄ ያቀረበለት አለቃው እርሱ ላቀረበለት ጥያቄ ፊት ነስቶት ለራሱ ግን ወደ መቶ ሺህ ብር የሚጠጋ ሞባይል እንዲገዛለት ጥያቄ ማቅረቡን ገልጾልኛል። ለዚህ ወዳጄ አክብሮት ቢኖረኝም “መቶ ሺህ ብር ለሞባይል ግዢ ጠየቀ” በሚለው ንግግሩ ግን “ለምን ማጋነን አስፈለገው?” ብዬ በሆዴ ማማቴ አልቀረም።
ያ ወዳጄ አልተሳሳተም። እውነቱን ነበር። ንግግሩም ግነት አልነበረበትም። ማረጋገጫውን ያገኘሁት ደግሞ ከወዳጆቼ ጋር ሃሳብ በምንለዋወጥበት የማሕበራዊ
ትሥሥር ገጽ ላይ ነው። መረጃውን ያሰራጩትን ሁለት ሰዎች በቅርበት አውቃቸዋለሁ። አንደኛው ሰው የቀድሞ የኮሌጅ ጓደኛዬ ሲሆን ሌላኛው ሰው ደግሞ የገንዘብና የኢኮኖሚ ሚኒስቴር መ/ቤት የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ ሆኖ በማገልገል ላይ ያለ ባለሙያ ነው። ይህ “የታላቁ መሥሪያ ቤት” የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ የለጠፈውን መራር ትዝብት ወደ እኔ ያሸጋገረው ጓደኛዬ አንዳችም ቃል ሳይጨምርና ሳይቀንስ ነው። እንዲህ ይላል፤ “ወደ 30 ሚሊዮን የሚጠጋ ከድህነት ወለል በታች በሚኖርባት አገራችን 94,000.00 ብር ሞባይል (አይፎን 11) ለመንግሥት ሹም ይገዛል ብዬ አስቤ አላውቅም። አንድዬ ፍረድ!!” የህሊና ቁስል እየጠዘጠዘ ፋታ የነሳው ይህ ታዛቢ በምን ዓይነት ስሜት ውስጥ ሆኖ የፈጣሪን ቁጣ እየተማጸነ መልእክቱን እንዳስተላለፈ መረዳት አይከብድም።
ዳሩ ይህ አንድ ዘለላ ሀገራዊ ችግር እንጂ እያንዳንዱ ተቋም ቢፈተሽ ምን ያህል ጉድ እንደሚዘረገፍ ዜጎችም ፈጣሪም በሚገባ ያውቁታል። የምናከብራቸው ጠቅላይ ሚኒስትራችን ሥልጣን በያዙ ሰሞን V-8 እና መሰል ቅንጡ መኪኖችን ሹመኞቻቸው ከተማ ውስጥ እንዳያሽከረክሩ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸው አይዘነጋም።
ትዕዛዙን የሰጡት መሪያችንም ሆኑ ሹሞቹ ዘንግተውት ከሆነ እኛ ተራ ዜጎች መቀናጫ መኪኖቹ የተገዙት “ከደማችን በሚመነጨው ታክስ” ስለሆነ ትኩረት ይሰጠው በማለት “ኤሎሄ አሎሄ” እያልን በመንግሥታችንና በፈጣሪ ፊት ቀን ከሌት ብንጮኽ አይፈረድብንም። ምክንያቱም ትዕዛዙ አልተከበረም ብቻ ሳይሆን በሀገር ውስጥ የሚገጣጠሙ ኦቶሞቢሎችን በተለዋጭነት እንዲጠቀሙባቸው የተወሰነው ውሳኔም ተግባራዊ መሆን አልቻለም። የተገዙት ተለዋጭ መኪኖችም ምክንያቱን አንድዬና ሹፌሮች ብቻ በሚያውቁት ምሥጢር ብዙዎቹ (ሁሉም ለማለት መዳፈር መስሎን ነው) ተሰነካክለው በየጋራጁና በየጥጋጥጉ እንደቆሙ አሉ። ቅንጡዎቹ የV-8 መኪኖችም ዛሬም በየአውራ ጎዳናዎቻችን ላይ ጥቁር ቱቢት ተጋርዶባቸው ሹሞቻችን ፊጥ ብለውባቸው እንደሚውሉ እያስተዋልን ነው። በዚህ ሁኔታ ነው “መንግሥታዊ ተቋማት ገንዘብ ተቸግረው” ቤት የሚውሉት “ሠራተኞች” የቤት ሥራቸውን እንዲያከናውኑ የሚጠበቀው።
”ሀገር አፍራሾች‘ የሚፈበርኳቸው ወቅታዊ አጀንዳዎች፤
“ዕድሜው ይጠርና!” ይሄ ምንትስ ወረርሽኝ ቤት ካዋለን ጊዜ ጀምሮ በዚሁ በፈረደበት ማሕበራዊ ሚዲያ አማካይነት ብዙ ነገሮችን ለመታዘብ አስችሎናል። አንዳንዱ ቤቱ ተቀምጦ “ሀገርን ለማፍረስ” መርዝ ሲነሰንስ እያስተዋልን ነው። በጸሐፊው የግል ምልከታ በእስካሁኑ የቤት ውሏችን አበጥ አበጥ ያሉ አፍራሽ አጀንዳዎች እየተፈበረኩ ሕዝቡ እንዲንጫጫ መዘየዱን እያስተዋልን ነው። አጀንዳዎቹን በሁለት ከፍሎ መመልከት ይቻላል።
የመጀመሪያዎቹ አጀንዳዎች የሀገርን ሉዓላዊነት የሚመለከቱ ሆነው ጥቂት እውነታነት ያላቸውን ሃሳቦች እየመዘዙ ሕዝብን ለማሸበር ሆን ተብለው የተፈበረኩ “የፓንዶራ ሙዳዮች” ናቸው። ለማሳያነት ጥቂቶቹን ልጥቀስ።
ሀገራዊ ምርጫው በተያዘለት ጊዜ የማይከናወን ከሆነ ሀገሪቱን “ክፉ እጣ ይገጥማታል!” የሚለው ሟርት ተቀዳሚ ሲሆን፤
-የአንበጣ ወረርሽኙ ከቁጥጥር በላይ ስለሆነ በሚቀጥለው ዓመት የሚላስ የሚቀመስ አይኖርም የሚል የክፉ መተተኞች ንግር ሁለተኛው ነው።
-የታላቁ ህዳሴ ግድባችንን በተመለከተም “ግብፅ በከፍተኛ የጦርነት ዝግጅት ላይ ስለሆነች ጉድ ሳታፈላብን አትቀርም” የሚል ነጭ ውሸትም ተደጋግሞ እየተጮኸበት ነው።
-የምንገኝበት ቀጣናዊ ጂኦ ፖለቲካ ለኢትዮጵያ ቀጣይ ህልውና በብዙ መልኩ ፈታኝ ስለሆነ ሉዓላዊነታችን
ለአደጋ ተጋርጧል የሚለው ክፉ ምልኪም አንዱ የክፋት ፕሮፓጋዳ ነው።
እነዚህ አሸባሪ አጀንዳዎች በማንና እንዴት እየተፈበረኩ እንደሚሰራጩ መንግሥት አልደረሰበትም ብሎ መደምደሙ ያዳግታል። ምንም እንኳ ለእያንዳንዱ እንቶ ፈንቶ ሟርት በነጋ በጠባ አታካራ መግጠም ያስፈልጋል ማለት ቢያዳግትም የመገናኛ ብዙኃን፣ ሀገር ወዳድ ምሁራንና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የምክቶሽና ሕዝቡን የማረጋጋት ሥራቸውን አጥብቀው መሥራት እንደሚኖርባቸው ማስታወሱ አይከፋም። “የት እንዳይደርሱ ነው!?” የሚል ንቀትና ትምክህት ግዙፉን ደርግ እንደምን እንደ ሸክላ ገል ሰባብሮ እንዳንኮታኮተው የሚዘነጋ አይሆንም።
መለስተኛና እያንጫጩ ያሉት ሁለተኛዎቹ ወቅታዊ አጀንዳዎች ሕዝብን ከሕዝብ፣ መንግሥትን ከሃይማኖት፣ ቡድንን ከቡድን፣ ግለሰቦችን ከግለሰቦችና ከእምነታቸው ጋር የሚያላትሙ ዓይነት ስለሆኑ በቸልታ የሚታለፉ ሊሆን አይገባም። አንዳንዱን ጉዳይ በቀጥታ የሚመለከታቸው የመንግሥት ኃላፊዎች በማብራሪያ የሚያከሽፉት ሲሆን አንዳንዱም ግለሰቦቹ ወይንም ቡድኖቹ በሚፈበርኩት አጀንዳዎች እንዳይናወጡ መምከር ብቻ ነው። ለአብነት እንጠቃቅስ።
-“በመስቀል አደባባይ እየተሠራ ያለው የሸገር ማስዋብ ፕሮጀክት አካል የሆነው ግንባታ ለሕዝብ ጥቅም ታስቦ ሳይሆን ከበስተ ጀርባው የጥፋት ዓላማ አንግቦ የሚሰራ ነው።” የሚለው በቀዳሚነት ይጠቀሳል።
ሠይጣን ቤት በመባል የሚታወቀው የመጀመሪያው ሲኒማ ቤት እንዲፈርስ የተደረገው ነባር ታሪክን ለማጥፋት ታቅዶ ነው። የሚለውም እንዲሁ።
-ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጽ/ቤታቸው ዋና መግቢያ በር ላይ ያቆሟቸው ሁለት የፒኮክ ቅርጾች ስውርና ድብቅ ተልዕኮ የሚያንጸባርቁ ናቸው። ሦስተኛውና በመርዝ የተለወሰ አጀንዳ ነው።
– የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዩዋ ሶፊያ ሽባባው ከሦስቱ ታዋቂ እንስት ድምጻዊያን (ዘሪቱ፣ ቤቲ ጂ. እና ቻቺ) እና እስራኤል ከሚባል ወጣት ጋር ያቀነቀነችው “የሰላም መዝሙር ዓለማዊነትን ወደ ቤተክርስቲያን የሚያስገባ እኩይ ሥራ” ስለሆነ ዘማሪዋ “በድንጋይ ተወግራ ትሙት” ዓይነት ይዘት ያላቸው እሩምታዎች ሲተኮሱባት ባጅተዋል።
በመሠረቱ የሚሰጡት ሃሳቦችና የሚወረወሩት አስተያየቶች በሙሉ “ከክፋት ምንጭ” እንደተቀዱ አድርጎ መቁጠሩ አግባብ አይሆንም። አንዳንዱ በቅንነት፣ አንዳንዱ ባለማወቅ፣ አንዳንዱ በሚነፍሰው ዐውሎ ነፋስ ድንገት ጥልቅ ብሎ በመወሰድ፣ አንዳንዶቹና መሠሪዎቹ በልዩ ተልእኮና የማፍረስ ስትራቴጅ ተነድፎላቸው የሚሰራጩ መሆኑ ሊጤን ይገባል።
የሆነው ሆኖ በቤታችን ውስጥ ዘግተን እየተፋለምን ያለነው ምንትሱ ቫይረስ እስኪረታ ድረስ ብቻ ሳይሆን በሚፈበረኩ የክፋት አጀንዳዎች ተጠልፈን ሌላ የጥላቻ፣ የመራርነትና የግጭት ሰለባ እንዳንሆን ልንጠነቀቅ ይገባል። አንድ የማሕበራዊ ሚዲያ ፖስተኛ በጥያቄ መልክ የተሳለቀበት ወቅታዊ ትዝብት ፈገግ ማስደረግ ብቻ ሳይሆን ጥሩ ማሳሰቢያም ሊሆን ስለሚችል ጽሑፌን ላሳርግበት ወድጃለሁ። እንዲህ ነበር ያለው፤ “ለመሆኑ ቤት የዋለው ኮሮና ነው ወይንስ እኛ?” ሰላም ይሁን!!!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 24/2012
(ጌታቸው በለጠ – ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com