ተወልደው ያደጉት ሆለታ ገነት በሚገኝ ካምፕ ውስጥ ነው። የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት እዚያው ሆለታ ገነት ይገኝ በነበረ የካቲት 25 በተባለ ትምህርት ቤት ነው። የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና በከፍተኛ ውጤት በማለፍ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሳይንስ ትምህርት ክፍል ገቡና ኬሚስትሪ አጠኑ። ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁም በኬሚስትነት በአንጋፋው ሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ ተቀጠሩ።ሁለት አመት ካገለገሉ በኋላ ግን የውጭ እድል ያጋጥማቸውና ወደ እንግሊዝ ሀገር ሄዱ።በእንግሊዝም ለ20 ዓመታት የቆዩ ሲሆን በማቴሪያል ሳይንስ፤ ሳይንስና ኢንጅነሪኒግና ኤሌክትሪክ ዘርፎች ሶስት የተለያዩ ማስተርስ ዲግሪዎችን ሰርተዋል።ዩሮፕ ሃወር፥ ሃይድሮሊክስ ሊሚትድ፥ ኤቮን በተባሉ ትላልቅ የእንግሊዝ ኩባንያዎችና ኢንዱስትሪዎች ውስጥም በባለሙያነት፥ በተመራማሪነትና በአመራርነት አገልግለዋል።
በእንግሊዝ ታላላቅ ኩባንያዎችና ኢንዱስትሪዎች ለ16 ዓመታት የመስራት እድሉን ያገኙት እኚሁ ግለሰብ ታዲያ ምንም እንኳን ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ባይሰሩም በሳይንሱ ዘርፍ በርካታ ጥናቶችንንና ምርምርችን አካሂደው ለህትመት አብቅተዋል። በጊዜ ሂደት ግን የቴክኒክ ስራው እየሰለቻቸው በመምጣቱ ስራቸውን ለመልቀቅ ይወስናሉ።ይሁንና ይህንን ውሳኔ በወሰኑበት አጋጣሚ የሚሰሩበት ኩባንያ የፋይናንስ ቀውስ ውስጥ በመግባቱ በሌላ አካል እጣ ፈንታ ያጋጥመዋል።አዳዲሶቹ ሃላፊዎች ኢትዮጵያዊውን ባለሙያ በኩባንያው አስተዳደር ውስጥ እንዲሰሩ ይሾሟቸዋል።ከዚህም አልፈውም ወደ ቢዝነሱ አለም ትኩረታቸውን እንዲያደርጉ ግፊት ያደርጉባቸው ያዙ።ለዚህ ደግሞ ትምህርት ቤት እንዲገቡ ምክር ቢጤ ጣል ያደርጉላቸዋል።እሳቸውም የአለቆቻቸውን ምክር ተቀብለው ዩኒቨርሲቲ ገብተው ተጨማሪ የማስተርስ ዲግሪያቸውን ሰሩ። ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ ግን ከተቀጣሪነት ወጥተው የግላቸውን ድርጅት አቋቋሙና ወደ ማማከር ስራ ገቡ።
ከስምንት አመታት በፊት ደግሞ ወደ ተወለዱባት አገር መጥተው በግሉ ዘርፈ የመንቀሳቀስ ሃሳብ ይጠነስሳሉ።ከእንግሊዝ እየተመላለሱ ለመስራት ቢያስቡም አዋጭና አመቺ አለመሆኑን በመረዳታቸው ቤተሰቦቻቸውን እዛው እንግሊዝ አገር በመተው ብቻቸውን ጓዛቸውን ጠቅልለው ወደ አገራቸው ገቡ።ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ በኋላም ዋይ ኤች ኤም ኮንሰልቲንግ የተባለ የአማካሪ ድርጅት ከፈቱና ተመሳሳይ ስራ መስራት ጀመሩ።በዋናነትም ኩባንያቸው የውጭ አገራትን ታላላቅ ባላሃብቶች ኢትዮጵያ ውስጥ መዋዕለንዋያቸውን እንዲያፈሱ የማድረግ ዓላማን በመሰነቅ የተለያዩ ስራዎችን አከናውኗል።በዚህም ቦብ ጊልድ ኦፍ በቦርድ ሰብሳቢነት የሚመራው ኤይት ማይልስ የተባለውና የአዋሽ ወይን ፋብሪካን የገዛውን ኩባንያ ማምጣት ቻሉ።የኩባንያው መምጣትም ሰፊ የሰው ሃይል የስራ እድል ለመፍጠር ከመቻሉም ባሻገር ጥቅም ላይ ያልዋለውን መሬት በወይን እንዲለማ ዕድል ፈጥሯል፡፡
ከእኚሁ ዘርፈ ብዙ ባለሙያ ጋር በተለያዩ ወቅታዊ በተለይም ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገናል እንደሚከተለው ይቀርባል።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ተመልሰው በሰሩባቸው አመታት ከሞቀው የእንግሊዝ አገር ኑሮና ደመወዝ ትተው መምጣትዎ ያሳደረቦት የቁጭት አጋጣሚ ካለ ያንሱልንና ውይይታችን ብንጀምር ?
አቶ ያሬድ፡- እርግጥ ውጭ አገር መኖር ብዙ ጥቅሞች አሉት።በተለይ እኛ በሄድንበት ዘመን መማማር ለሚፈልግ ሰው ነፃ እድል መኖሩ እንደመልካም አጋጣሚ የሚወሰድ ነው። በሁለተኛ ደረጃ በካፒታሊዝም ሲስተም ውስጥ ገብቶ መስራቱ የራሱ የሆነ ጠቀሜታ አለው።በዋናነትም ልምድ ለማግኘት ያስችላል።ከጊዜ በኋላ ግን ለሌላ አገር ተቀጥሮ መስራቱ በራሱ አሰልቺ ይሆናል።ብዙ ጊዜ ስራ ለቅቄ የራሴን ቢዝነስ ለመክፈት ወስኜ አውቃለሁ።ይሁንና የቤተሰብና የኑሮው ሁኔታ ያሳስበኝና ውሳኔዬን ከዳር ሳላደርስ እቀራሉ።በዚህ ሁኔታ ብዙ አመታት ቆይቻለሁ።
በአገር ውስጥ መስራት መቻሉ ትልቁ ነገር የሞራል እርካታ ያመጣል።አንድ ትልቅ አለምአቀፍ ኩባንያ ውስጥ ተቀጥሬና ጥሩ ደመወዝ ተከፍሎኝ በምሰራበት ጊዜ ይሄነው የሚባል የውስጥ ደስታ የሚፈጥርልኝን ስራ ሰርቻለሁ ለማለት አልችልም።እኔ በመጀመሪያም ከአገሬ የወጣሁበት ዋነኛ ምክንያት ለመማር ነው።በኋላም የፖለቲካውና የኑሮ ሁኔታ ጊዜ ገዛብኝ።ያም ሆኖ ግን በዛው ጠፍቶ የመቅረት ምኞት አልነበረኝም።ስለዚህ በአገሬ የመስራት ህልም ስለነበረኝ ጨክኜ መምጣት ነበረብኝ።ይህንን በማድረጌ ደስተኛ ነኝ።ይህንን ስልሽ ግን ከሃብትና ምቾት አንፃር አይደለም።ነገር ግን በምሰራው በነገር እኮራበታለሁ።የምሰራውም ያመንኩበትን ነገር በመሆኑ ውጤት እያየሁበት ነው።ይህም ለእኔ በገንዘብ የማይለካ ትልቅ ነገር ነው።በአጠቃላይ በእኔ በኩል አገሬ ተመልሼ መስራት መቻሌ ቁጭት የሚፈጥርብኝ ሳይሆን እንደስኬት ነው የማየው፡፡
አዲስ ዘመን፡- የዓለም የጤና እና የኢኮኖሚ ቀውስ ምክንያት የሆነውን ኮቪድ 19 የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ እየተከናወነ ያለውን ጥረትና ዝግጅት እንዴት ያዩታል?
አቶ ያሬድ፡- እርግጥ ኮረና በአለም አቀፍ ደረጃ በወረርሽኝ መልኩ በተከሰተበት ወቅት እንግሊዝ አገር ነበርኩ። በወቅቱ የተገነዘብኩት ነገር ቻይና 50 ሚሊዮን ህዝብ ኳራንቲን ( ለይታ ማቆያ) ማድረግ ከፈለገች የፈራችው ትልቅ ነገር ነው ማለት ነው።ይህምማለት የኢትዮጵያን ግማሽ ያህል ህዝብ ማለት ነው።ሌላው ይቅርና አዲስ አበባን መዝጋት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ መገንዘብ አይከብድም።ይህንን በሚመለከተ በወቅቱ የኢትዮጵያ መንግስት አስቸኳይ እርምጃ እንዲወስድ በቲዊተር ላይ ፅፌ ነበር።እኔ ወደ እዚህ በተመለስኩበት ጥር አጋማሽ አካባቢ ምንም አይነት ምርመራ እየተደረገ አልነበረም።እናም በዚያ ወቅት በሽታው ቢኖርብኝ ኖሮ ምን ያህል ህዝብ በእኔ ምክንያት ሊጎዳ እንደሚችል ማሰብ አይከብድም።እንዳውም በወቅቱ ይታሰብ የነበረው የአሜሪካና የቻይና የንግድ ጦርነት እንደሆነ ነው።እንዳውም እኛ እስከ መጋቢት ድረስ በሽታው ባለመግባቱ እድለኞች ነን።
በወቅቱ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ፥ ለአለም የጤና ድርጅትና ለቻይና መንግስት ፅፌ ነበር።በመጀመሪያ ደረጃ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሙሉ ለሙሉ ማቆም ባይገባውም በቂ ዝግጅት ማድረግ ይገባዋል የሚል መከራከሪያ ነበር ያነሳሁት።የእኛ አውሮፕላን ወደ ቻይና የሚበር ከሆነ ደግሞ የቻይና መንግስትን የኳራንቲን (ለይቶ ማቆያ) ቦታ እንዲገነባልን መጠየቅ ይገባናል የሚል ሃሳብም አንስቻለሁ።ምክንያቱም በእኛ አገርም ትላልቅ የቻይና ኩባንያዎች በመኖራቸው በሶስት ሳምንት ውስጥ ሚሊኒየም አዳራሽን የመሰለ ገንብተው ሊያስረክቡን ይችላሉ የሚል እምነት ስለነበረኝ ነው።
በሁለተኛ ደረጃ እንደምታስታውሽው በመጀመሪያ አካባቢ የኮረና ናሙና የሚመረመረው ደቡብ አፍሪካ በመላክ ነበር።ለምርመራው የምናባክነውን ወጪና ጊዜ ለማስቀረት ይቻል ዘንድ የምርምራ ማዕከል የአለም የጤና ድርጅትም ሆነ ሌሎችም እንዲያግዙን በመጠየቅ መገንባት ይገባናል የሚል ሃሳብ አንስቼ ነበር።እነዚህ ሶስት አካላት በዋናነት መጠየቅ ይገባናል የምለውም ለእኛ ጤንነት ሃላፊነት አለባቸው ብዬ ስለማምን ነው።በዚህ ረገድ ግብፅ እንኳ ያደረገችው ዝግጅትና ስራ አስተማሪ ነው። የእኛ ሃኪሞችና ፖሊሶች አሁንም ድረስ በስራ ልብሳቸው ነው እያገለገሉ ያሉት።ምንም አይነት መከላከያ የላቸውም። ስለዚህ ለእኔ በአጠቃላይ ዝግጅቱ በጣም አዝጋሚና አደጋውን ዝቅ አድርጎ የማየት ችግር እንደነበር እረዳለሁ።አሁን የመንግስት አመለካከት ሲቀየርና ተጠንቀቁ ሲል ደግሞ ህዝብ ደግሞ አልፈራም።እናም አሁን ትልቅ ፈተና ነው ያለው ባይ ነኝ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ያን ጊዜ የነበረው መዘናጋት በተለይም በኢኮኖሚው ላይ የፈጠረውን ተፅእኖ
እንዴት ይገልፁታል?
አቶ ያሬድ ፡- በእኔ እምነት ከመጀመሪያውኑ ትልቁ መፍትሄ የነበረው የቻይናን መስመር መከተል ነበር።ግን ያንን መስመር ባለመከተላችን አሁን ላይ ግን እኛንም ጨምሮ የአለም ህዝብ ችግር ውስጥ ወድቋል።በዚህ ረገድ አስቀድሜ እንዳልኩሽ የኢትዮጵያ አየር መንድ በረራ አለማቋረጡ የሚደገፍ ቢሆንም የሚገባውን ያህል ጥንቃቄ አለማድረጉ ስህተት ነው።በሌላ በኩል ግን አየር መንገዱ የሌሎችን ስሜት ተከትሎ አለመሄዱ እንደ ትልቅ ስኬት ሊወሰድ የሚችል ነው።በነገራችን ላይ በደርግም ሆነ ሆነ በኢህአዴግ ዘመን መንግስት አየር መንገዱን በፖለቲካ ለመቆጣጠር ጥረት ተደርጎ ነበር።ነገር ግን ማኔጅመንቱና ሰራተኛው ባደረገው ተደጋጋሚ ትግል ነፃነቱን አስጠብቆ ቆይቷል።ለዚህም ነው ዛሬ ለደረሰበት የእድገት ደረጃ የበቃው የሚል አስተሳሰብ አለኝ።እናም አየር መንገዱ በህዝብና በመንግስት አስተያየት የሚሰራ ቢሆን አደጋ ውስጥ ይወድቅ ነበር። አሁን እንዳየነውም እስካሁን ባለው ሂደት 550 ሚሊዮን ዶላር የሚያጣ ከሆነ በሽታው ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ ምንያህል ኪሳራ ውስጥ ሊገባ እንደሚችል ማሰብ ካባድ አይደለም።ስለዚህ የወሰዱት እርምጃ ትክክል ነበር።ምን አልባት በሽታው በቀጥታ ከቻይና የመጣ ቢሆን ኖሮ ብዙ ውርጅብኝ ይደርስባቸው እንደነበር አስባለሁ፡፡
በሌላ በኩልም ከአገልግሎት ዘርፉ ላይ ከሚታየው የጎላ ተፅዕኖ ባሻገር በሌሎች ዘርፎች ላይ ጉዳቱን እንደሌሎች አገሮች ያን ያህል እያየን አይደለም። ነገር ግን በአፋጣኝ ልንታደጋቸው ከሚገባቸው ዘርፎች መካከል ግንባር ቀደሙ ግብርናውን ነው።እንደምታውቂው 80 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ኑሮ የተመሰረተው በግብርና ላይ ነው።ስለዚህ እኛ ልንከላከል የሚገባን ያንን ኢኮኖሚ የሚመራውን በእርሻ ላይ የተሰማራውን ገበሬ ነው።በመጀመሪያ ደረጃ ማድረግ ይገባን የነበረው ከተማውን ከገጠሩ መነጠል ነበር።በተለይ በሽታው የተገኘባቸውን አካባቢዎች መለየትና መዝጋት ያስፈልግ ነበር። ይህንን ማድረግ ሲገባን ሰሞኑን ግን እንዳውም ወደ ክልሎች የሚደረገው የትራንስፖርት አገልግሎት መክፈቱ ትልቅ ስህተት ነው ባይ ነኝ፡፡
አዲስ ዘመን፡- በሽታው በከፍተኛ ደረጃ በጉዳት አሜሪካም ቢሆን እንቅስቃሴ መገደብ የለበትም በሚል ተቃውሞ እየቀረበ ባለበት ወቅት ይህን ማድረጉ አሉታዊ ተፅእኖ የለውም ይላሉ?
አቶ ያሬድ፡- ተፅእኖ ማምጣቱማ አይቀሬ ነው። እንዳልሽው የበሮች መዘጋት አገልግሎት ዘርፉን በቀጥታ ሊጎዳው ይችላል።ግን ቫይረሱ ወደ ግብርናው ከተንሰራፋ ሙሉ ለሙሉ ኢኮኖሚያችን ይዞ ነው ገደል የሚገባው።በተለይ ደግሞ አሁንም የምንከላከልበት አቅምም ሁኔታም የለም።10 ሚሊዮኑ ህዝብ ምግብ ለስራ የሚኖርበትና ስምንት ሚሊዮን ደግሞ ተደጋፊ በሆነበት አገር የቫይረሱ መስፋፋት ሊያመጣብን የሚችለውን ከፍተኛ ቀውስ መገመት አይከብድም። በተጨማሪም በፖለቲካው ቀውስ ደግሞ ተፈናቅሎ የነበረው ወደ 3 ሚሊዮን የሚሆነው ህዝብ ደግሞ ባለፈው አመት ያላረሰና አሁን ገና በመቋቋም ላይ ነው።
ስለዚህ አምራች ሃይሉ በዚህ በሽታ ከተጠቃ የነበረው ምርት ሙሉ ለሙሉ የሚቆምበትና ሁሉም እርዳታ ፈላጊ ነው የሚሆነው። አሁን ደግሞ መላው አለም የተጠቃበት ጊዜ በመሆኑ እርዳታ ብንጠይቅ እንኳን የሚደግፈን የለም። አየሽ! የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር ማደጉ ትልቁ አደጋ ይሄ ነው።እንበልና አገሪቱ ለ30 ሚሊዮን ህዝብ የሚሆን እህል አስመጥቼ ልመግብ ብትል እንኳን የጅቡቲ ወደብ አይችለውም።ስለዚህ መንግስት በከፍተኛ ደረጃ መጨነቅ አለበት ብዬ የማምነው በሽታው ወደ ገበሬው እንዳይዛመት ማድረጉ ላይ ነው። በተወሰነ ደረጃ የግንባታ ዘርፉ እየቀጠለ ቢሆንም ቁጥጥራችን ካለጠናከርን ጉዳቱ ከፍተኛ ነው የሚሆነው፡፡
በመሆኑም በአሁኑ ወቅት የመንግስት ዋነኛ ስራ ሊሆን የሚገባው በሽታው ብልጭ ያለበት ቦታ ሁሉ እየሄዱ እንቅስቃሴን መያዝ ነው። በሽታው የት አካባቢ ላይ እንዳለ አስቀድሞ መለየት ከዚያ መመርመርና መቆጣጠር ይገባል።በዚህም ሳንወሰን ሊያመጣ የሚችለውን ጉዳት አስፍተን ማየት ያስፈልገናል። አገሪቱን ለተጨማሪ ኢኮኖሚ ቀውስ ይዳርጋታልና መላውን የአገሪቱን በር መዝጋት አንችልም። ለግብርናው ስንጠነቀቅ ለኮንስትራክሽኑና ማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ካልተጠነቀቅን አንድ ላይ ተያይዞ መውደቅ ያጋጥማል። ከለየነው ግን በተለይ ግብርናውንና አምራች ኢንዱስትሪውን መታደግ እንችላለን።በተለይ በአሁኑ ወቅት የወጭ ንግዱ የተሻለ ገበያ የሚያገኝበት ሰዓት ነው። ምክንያቱም በአለም ላይ የቡና እና የወርቅ ዋጋ ጨምሯል።እኛ ደግሞ እሴት ያልተጨመረበት ምርት ስለሆነ የምንልከው ያለውን ሰፊ አማራጭ መመልከት ያሻናል።
አዲስ ዘመን፡- አለም ከበሽታው ባሻገር በኢኮኖሚ ቀውስ እየተናጋች ባለችበትና በሮች ሁሉ በተዘጉበት በዚህ ወቅት የገበያ አማራጭ ይኖራል ብሎ ማሰብ አይከብድም ?
አቶ ያሬድ፡- ልክ ነሽ፤ እንዳልሽው እንደ ሳውዲአረብያ ያሉ አገራት እኛ ጋር በሽታው ሳይገባ ነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንዳይገባ ያገዱት።ግን ሳምንት ሳይሞላ ደግሞ ሃሳባቸውን ቀይረው ካርጎ እንዲገባ አደረጉ። ምክንያቱም ህዝባቸውን መመገብ አለባቸው። እነሱ ደግሞ ስለማያመርቱ የሱፐርማርኬት መደርደሪያቸው ባዶ ሊሆን ነው ማለት ነው።ስለዚህ የአቅርቦት ሰንሰለታቸው መቀጠል ስለነበረበት ነው ያንን ውሳኔ የወሰኑት። አሁን ላይ የሆርቲ ካልቸሩ ምርት ወደ አውሮፓም ይበራል። ምክንያቱም ሱፐርማርኬቶቹ አልተዘጉም።በእርግጥ በዚህ የችግር ጊዜ አበባ የሚገዛ ላይኖር ይችላል።ስለዚህ ከዚህ ቀደም አበባ ያመርቱ የነበሩ እርሻዎች ገበያቸውን ለአገር ውስጥ ማቅረብ ሌሎችንም ምርቶች ወደማምረት ሊገቡ ይገባል።
በሌላ በኩል ግን በአለም ላይ በአሁኑ ወቅት ነዳጅ የሚያመርቱ አገራት ትልቅ ኪሳራ ውስጥ ገብተዋል። የነዳጅ ዋጋ ከ65 ዶላር ወደ 25 ዶላር ገብቷል። ይህ ለእነሱ ትልቅ ኪሳራ ነው። ምክንያቱም ከማምረቻው ዋጋም በታች ነው የሚሆነው።አንዳንዶቹም ነዳጅ ተመርቶ ማስቀመጫም ሊቸገር ይችላል። ለእኛ ግን ትልቅ እድል ነው። ምክንያቱም 70 በመቶ የነዳጅ ወጪያችንን ከቀነስን ሌላውን ዘርፍ መደገፍ እንችላለንና።በተጨማሪም አቅሙ ካለን የስድስት ወር የነዳጅ ፍላጎታችን አሁን በረከሰበት ወቅት ማሟላት እንችላለን። ምክንያቱም ኢኮኖሚው እየተከፈተ በመጣ ቁጥር ዋጋው መጨመሩ አይቀርምና።ሰሜን አፍሪካ አካበቢ ያሉ በነዳጅ ላይ የተመሰረቱ አገራት አሁን ላይ ኢኮኖሚያቸው የሚወድቅበት ጊዜ ላይ ያለነው።
ከቱሪዝም ዘርፉ የምናገኘው ገቢ ካለፈው ሁለት አመት ወዲህ እየተሻሻለ ቢመጣም ለኢኮኖሚው እያበረከተ ያለው አስተዋፅኦ የጎላ ነው ማለት አንችልም።ስለዚህ ጉዳቱ ከግብርናው ጋር የሚመጣጠን አይደለም። በእርግጥ ሆቴሎቻችን ትልቅ የገቢ ምንጭ የሚባለው የኮንፍረንስ ቱሪዝም እንደመሆኑ ስብሰባዎች መቆማቸው ጉዳት እንዳለው ይታወቃል።ይህንን ደግሞ ማቆም አንችልም።ምክንያቱም ሰው ለሶስት ቀን ኮንፍረንስ 14 ቀን ኮራንቲን (ለይቶ ማቆያ) ውስጥ ገብቶ አይወጣም።ስለዚህ በአለም ላይ በሽታው እስኪገታ ድረስ ሊቆም አይችልም።ግን እንደ ኬንያና ግብፅ ካሉ አገሮች አንፃር ጉዳቱ የከፋ ነው ማለት አንችልም።ይህም ሲባል በእነሱ መጎዳት መፅናናት ይገባናል ማለቴ አይደለም። ማኑፋክቸሪንግ ላይ ያለው ስራ ቆሟል ማለት ይቻላል።ሲጀመርም አነስተኛ ነው።ኢንዱስትሪ ፓርኮችን አሰራር መቀየር ይገባናል።መንግስት ኢንዱስትሪዎቹ ከዚህ ቀደም ለውጭ ገበያ የሚቀርቡት ምርት ህጉን ላላ በማድረግ ለአገር ውስጥ እንዲያቀርቡ ማድረግ ይጠበቅበታል።
እንደ አጠቃላይ ግን ኮቪድ 19 በኢኮኖሚው ላይ የሚያሳድረው ተፅእኖ ከሌሎች አገሮች ጋር ማነፃፀሩም መልካም ነው።የአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም የሰሞኑ ሪፖርት እንደሚያሳየው የአሜሪካ ኢኮኖሚ ከዜሮ በታች 3 በመቶ ይወርዳል፥ በአውሮፓ 7 ነጥብ 5 በመቶ ኢኮኖሚያቸው ይጋሽባል።በአፍሪካ አንድ በመቶ ያህል የኢኮኖሚው እድገት ይቀንሳል።የኢትዮጵያ ግን አሁንም ሲተነበይ 3 በመቶ አሁንም ያድጋል።ስለዚህ ምን አልባትም ይህ አጋጣሚ ለእኛ ጥሩ እድል ይዞልን ይመጣ ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- በምን መልኩ ነው ጥሩ እድል ይዞልን ሊመጣ የሚችለው?
አቶ ያሬድ፡- እንዳልኩሽ የአንዳንድ ምርቶች ዋጋ ጨምሯል፤ በሌላ በኩል የነዳጅ ዋጋ ቀንሷል።ይህንን እንደጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም የወጭ ንግዳችንን ማሳደግ የምንችልበት አጋጣሚ ሰፊ ነው።ይሁንና ይህን ለማድረግ የማያሰሩ ህጎችንና አሰራሮችን ማሻሻል ከመንግስት ይጠበቃል። አንዳንድ ህጎች እንዳውም በደርግ ጊዜ የወጡ ናቸው። ለምሳሌ ከፋይናንስ ዝውውር አኳያ የኬንያን ተሞክሮ ብትመለከቺ ባለፈው አመት በኤሌክትሮኒክስ መንገድ ብቻ 38 ቢሊዮን ዶላር ማስተላለፍ ችላለች። ወደ እኛ አገር ስንመጣ ግን ይህ በዲጂታል መንገድ ገንዝብ የማስተላለፉ ልምድ በጣም ወደ ኋላ የቀረ ነው ማለት እንችላለን።ለዚህ ደግሞ ዋነኛ ምክንያት የሆነው የብሄራዊ ባንክ ፖሊሲና አሰራር ነው። እኔ ይህንን ጉዳይ በሚመለከት ለዓመታት ስቃወመውና ሊሻሻል ይገባል ብዬ ስወተውት ቆይቻለሁ። አይተሽ እንደሆነ ኢትዮጵያ ትልቁ ባንኮች ችግራቸው ካፒታል የላቸውም።ብሩ ያለው በየቤቱ ነው። አሁን አሁን ብር ካስገባህ ሎተሪ እንሰጥሃለን ወደ ማለትና መለመን ሁኔታ ገብተዋል።ሃርጌሳ ብትሄጂ ሁሉም የሚጠቀመው ዲጂታል የሆነ የባንክ አገልግሎት በመሆኑ ባንኮች ብራቸውን የሚያስቀምጡበት ቦታ ነው የቸገራቸው። በመሆኑም የእኛም ባንኮች ይህንን አሰራር ቢያሳድጉት ቁጠባውን ከፍ ማድረግ ይችላሉ።
በተመሳሳይ ከውጭ ምንዛሬ ዝውውር ጋር ተያይዞያለው አሰራርም ሊሻሻል ይገባል ብዬ አምናለሁ።እኔ እንዳውም ከዚህ ጋር ተያይዞ ከአንድ አመት በፊት ጥናት አጥንቼ ዘጠኝ የሚሆኑ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ጠቁሜ ነበር። የተወሰኑት ተግበራዊ እየሆኑ ነው። የመጀመሪያው ነገር ዲያስፖራው ሪሚታንስ አካውንት ሊከፈትለት ይገባል የሚል ሲሆን ይህንን ማድረግ ከተቻለ የውጭ ምንዛሬ አቅማችንን ማሳደግ እንችላለን የሚል ነበር። ይህንን ጉዳይ ስታነሺ ግን የማይቻልበትን ትክክለኛ ምክንያት የሚገልፅልሽ አታገኚም። ለምሳሌ ብጠቅስልሽ የውጭ ጉዳይ ሰራተኞች ሆነ በተለያዩ አገራት በሰላም ማስከበር ላይ ያሉ የመከላከያ ሰራዊት አባላት በሚኖሩበት አገር ሁሉ አካውንት ከፍተው ነው ገንዘባቸውን የሚያስቀምጡት። ለምን በፖሊሲ ብር እንዳይመጣ አግደን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለማግኘት አላስፈላጊ ውጥረት ውስጥ እንደምንገባ አይገባኝም። ስለዚህ እዚህ አገር አካውንት ከፍተው ቢያስቀምጡ ለአገር ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው በመገንዘብ ይህንን የማያሳራ ፖሊሲ ማንሳት ያስፈልጋል፡፡
በተጨማሪም አሁንም ያልተፈታው ሌላው ችግር ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉና በውጭ ምንዛሬ የሚከፈላቸው እንደ አፍሪካ ህብረት፥ የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን፥ የኢትዮጵያ አየር መንገድና በተለያዩ ተቋማት የሚሰሩ ሰዎች ብራቸውን በዶላር ማስቀመጥ የሚችሉበት ስርዓት አለመፈጠሩ ነው። የሚያገኙት ገንዘብ በዶላር እስከሆነ ድረስ አካውንት መክፈት መብታቸው ሆኖ ሳለ ለምን ተከለከለ ብለሽ ብትጠይቂ መልስ የሚሰጥሽ አታገኚም።
ሌላው ግን እዚህ አገር በኖርኩባቸው ስምንት አመታት ኢምግሬሽን እንደመሄድ የሚያሳቅቀኝ ምንም ነገር የለም።ለምሳሌ የእኛ ተቋም የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሰዎች ለስብሰባና ለስልጠና እናመጣለን ግን ኦን አርይቫል ቪዛ መስጠት አይቻልም። ለሶስት ቀን ስብሰባ የመጣ አንድ የውጭ አገር ዜጋ የአምስት ቀን ቪዛ ብቻ ነው የሚሰጠው። እነዚህ ሰዎች አንድ ሁለት ሳምንት ቪዛ ቢሰጣቸውና ሌላው ይቅርና ደብረዘይትና ሃዋሳን ጎብኝተው ቢሄዱ ለአገሪቱ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ ያስገኙ ነበር። አንድ ሰው በቀን 250 ዶላር በቀን ኢትዮጵያ ውስጥ ካወጣ አንድ ኩንታል ቡና ገዛ ማለት ነው።በሌላ በኩል አንድ ኩንታል ቡና ወደ ውጭ ብንልከው የትራንስፖርቱ፥ የጆንያውና የሰራተኛ ሲቀነስ እዚህ አገር የሚቀረው ሃብት 30 በመቶ አይሆንም። ስለዚህ እዚህ አገር ለሚመጣው እንግዳ ልታወጪ የምትችይው ግን አንሶላ መቀየርና ሳሙና ሻምፖ አውጥተሽ 50 ብር አይሞላም። በነገራችን ላይ ከአሜሪካ ወይ ከአውሮፓ መጥቶ ጥገኝነት የሚጠይቅ ሰው ይኖራል ተብሎ አይታሰብም። ስለዚህ ምንድን ነው የሚያሰጋን?። ትልቁ ችግር የነበረው ደግሞ ኢሜግሬሽን በብሄራዊ ደህንነት ኤጀንሲ ስር ስለነበር የእነሱን ፍላጎት ነበር የሚያስፈፅመው። ስለዚህ ይህንን አሰራር እንዲቀርና በተቻለ መጠን ሰዎች ወደአገር መጥተው ገንዘብ እንዲያወጡ ማድረግ ያስፈልጋል:: ወንጀል ሊሰራ የመጣ ካለ በቴክኖሎጂ አማካኝነት ነጥሎ ለህግ ማቅረብ ነው እንጂ በር በመዝጋት አገር ሰላም ማድረግ አይቻልም። በመሆኑም ኢምግሬሽን ያለው አሰራር ሊሻሻል ይገባል ብዬ ብዙ ስናገር ነበር። ባለፉት ሁለት አመታት ግን መሻሻሎች እየታዩ ነው።
ከዚህ ባሻገር የሚያስገርመኝ ነገር ማንም ሰው ብር ይዞ ከኢትዮጵያ መውጣት አይቻልም።ለ42 ዓመታት 200 ብር ብቻ ነው ሰው ይዞ ይወጣ የነበረው። ከአለም 70 በመቶ የሚሆነው ህዝብ በአሜሪካ የሚገበያየው ምንም ጉዳት ስላላደረሰበት ነው። በተቃራኒው በእኛ አገር ግን በሶሻሊዝም ርዕዮተ አለም የተቃኘውና በ1977 ዓ.ም የወጣን ህግ ይዞ ገንዘብ ማውጣት አይቻልም ሲባል ነው የተኖረው። አሁን ተሻሻለ ተብሎም አንድ ሺ ብር ብቻ ነው ይዞ መውጣት የሚቻለው። እስኪ ፈጣሪ ያሳይሽ አንድ ሺ ብር በአሁኑ ወቅት ከአገር እንኳ ሳትወጪ በረራው ቢዘገይብሽ ኤርፖርት ውስጥ ምግብ ልትበይበት እንኳን አትቺዪም። ሌላው ይቅርና ሻንጣሽን ለተሸከመልሽ ሰው ከ200 ብር በታች አትሰጪውም። እናም ይህ በድህነት ላይ የተመሰረተ አስተሳሰብ ሊቀየር ይገባል። ይህንን አሰራር ብንፈትሸውና ልናስቀረው ይገባል። ሌላው ይቅርና እንደ ጅቡቲ፥ ኬኒያና ሶማሌያ ካሉ ጎረቤት አገሮች ጋር ያለ ዶላር መገበያየት የምንችልበት እድል መፍጠር ያስችለናል።
አዲስ ዘመን፡- ከተፈጠረው ችግር አኳያ መንግስት በተለይም የግሉን ዘርፍ ለመደገፍ ህጎችን እስከማሻሻል ደርሷል።እርስዎ በተለየ መልኩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል የሚሉት ዘርፍ አለ?
አቶ ያሬድ፡- እኔ አሁንም ቢሆን ደጋግሜ ማንሳት የምፈልገው የመኸር ወቅት እንደመሆኑ አርሶ አደሩ በሙሉ ጤና እንዲያመርት መደገፍ ይገባናል የሚል ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ የወጭ ንግዱንም ማሳደግ ያስፈልገናል። ምክንያቱም እንዳውም ከመቸውም በበለጠ የግብርና ውጤቶች በአለም ላይ ተፈላጊ እየሆኑ ነው። የምግብ ፍጆታዎች በአለም ደረጃ ከፍተኛ እጥረት ይታይባቸዋል። ስለዚህ የግብርና ውጤቶችንና በስፋት በማምረት እሴት ጨምረን የምንልካቸውን ምርቶች መጠን ከፍ በማድረግ የአለምን ገበያ ልንይዝ ይገባል። ምክንያቱም ሰው ቤቱ ቢቀመጥም ቡና መጠጣትን አያቆምም። መብላቱም አይቀርም። ስለዚህ ሁሉን ነገር ጭልም አድርገን ልናየው አይገባም።ምክንያቱ የወጭ ንግድ ኮሪደሮቻችን እንዳይዘጉ ለማድረግ ትልቅ ትኩረት መስጠት የሚገባን ጊዜ ነው።
በሌላ በኩል አበዳሪዎቻችን እዳችንን እንዲቀንሱልን ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይገባናል። በዚህ ረገድ ትልቋ አበዳሪያችን ቻይና ናት። በሽታውም የመጣው ከዚያ ሆኖ ሳለ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያለምንም ገደብ ሲበር ነበር። ስለዚህ ቻይና አንዳንድ የህክምና ቁሳቁሶችን ከመደገፍ ባለፈ እዳችንን እንድትሰርዝልን በአግባቡ ልንደራደር ይገባናል። ሌላው ይቅርና ዶክተር አብይ ከአለም ባንክ ለጠየቁት የገንዘብ ድጋፍ አንዳንድ አገራት ለእኛ የሚሰጠው ድጋፍ ለቻይና ብድር መክፈያ ያደርጉታል የሚል አቋም ይዘዋል። ስለዚህ ጠንከር ያለ አቋም ይዘን ቻይና ያለብንን እዳ እንድትሰርዝልን ማድረግ ይገባናል። አፍሪካ 168 ቢሊዮን ዶላር አካባቢ የቻይና እዳ አለባት። በነገራችን ላይ ቻይኖቹ ይሉኝታ የላቸውም። አሁን ዛምቢያ የቻይና እዳ ባለመክፈሏ የእነሱን መዳብ ማምረቻ ስፍራ ካልወሰድን እያሉ አለምአቀፍ ጫና እያደረጉ ነው። ስለዚህ እኛም አገር ጠበቅ አድርገን ካልያዝን ለኢትዮጵያ አየር መንገድ አበድረው ከሆነ ሆቴሉን እንውሰድ ሊሉ ይችላሉ። ለባቡር፥ መንገድና ግድቦቻችን ግንባታ ያበደሩትን ካልመለስን እንደዚሁ በምላሹ ሌላ ነገር ሊጠይቁን ይችላሉ። ደግሞም ወደድንም ጠላንም ቻይና የሚቀጥለው ቀኝ ገዢ ነው የምትሆነው።
ስለዚህ በደንብ መረዳት ያለብን ነገር ቻይናውያን የሚሰጡትን ለፅድቅ አይደለም። ቻይና ላይ ያለን ፖሊሲ በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ፍቅር የተጠመደ ሊሆን አይገባም። ይልቁኑ ምክንያታዊ የሆነ ግንኙነትና የጋራ ተጠቃሚ የሚያደርገን ነው መሆን ያለበት። እኛ ካለብን 27 ቢሊዮን ዶላር ብድር ውስጥ ምንአልባት ግማሽ ያህሉ የቻይና ነው ብዬ ነው የማስበው።ከዚህ ውስጥ ከፊሉን እንኳ ብናሰርዝ ለእኛ ትልቅ እምርታ ነው። ምክንያቱም ከወጭ ንግድ የምናገኘው ከሶስት ቢሊዮን ዶላር አይበልጥም። በመሆኑም አሁን ያለው የአገሪቱ መንግስት በዚህን ጊዜ ብድር የማሰረዙን ጉዳይ ሊያስብበት ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- ቻይና ብድር ለመሰረዝ ምን አስገዳጅ ሁኔታ አለባት ተብሎ ይታመናል?
አቶ ያሬድ፡- ይህ በሽታ ከቻይና ስለመምጣቱ ምንም ጥያቄ የለውም፤ ምንም እንኳን እነ ዶናልድ ትራምፕ ለፖለቲካ ግብዓት ቢጠቀሙበትም፤ በእኔ እምነት ግን ቻይና ላይ ቢገደብ ኖሮ የእኛ ችግር አይሆንም ነበር። ይህ ሆኖ እያለ እኛ ወገንተኝነታችንን ለቻይና አሳይተናል። ድጋፋችን አስመስክረናል።እነሱ ከአሊባባ ማስክ ባሻገር በመሰረታዊነት ወሳኝ የሆነ የብድር ስረዛ እንዲያደርጉልን ጫና ማሳደር ይገባናል። ደግሞ አሊባባ አንድ የቻይና ባለሃብት እንጂ መንግስታቸው ያደረገው ድጋፍ አለመሆኑን ማስታወስ ይጠበቅብናል። አሁን ያለብን ግማሽ እዳ ማሰረዝ ከቻልን በሁለትና በሶስት አመት በውጭ ንግድ የማናገኘውን ነገር ነው የምናተርፈው። በአጠቃላይ ከመጥፎ ነገር ውስጥ ጥሩ ነገር ይዘን መውጣት እንችላለን ለማለት ነው የምፈልገው። ይሁንና በዚህ ጊዜ ዝም ብለን ቻይና አንዴ ካመለጠችን ትልቁ ስህተት ነው የሚሆነው። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለጂ20 አገራት 150 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልገናል እንደሚሉት ሁሉ ለቻይና መንግስትም የብድር ስረዛ እንዲደረግልን ደብዳቤ መፃፍ አለባቸው ባይ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡– አንዳንድ ጥናቶች ኢትዮጵያ በአፍሪካ በከፋ ረሃብ ውስጥ ይዳረጋሉ ተብለው ከሚጠበቁ 10 አገራት አንዷ እንደምትሆን እየተነበዩ ነው።ይህ በእርግጥ ለእርሶ ስጋት ነው?
አቶ ያሬድ፡- እውነት ሊሆን የሚችልበት እድል አለ።ለምሳሌ አሁን በሽታው ገበሬው ጋር ከገባ ትልቅ ችግር ሊፈጥር ይችላል።አሁን 18 ሚሊዮን ህዝብ በመንግስት ድጋፍ ውስጥ ያለ ነው። አሁን ግን ሁሉም አገር በራሱ ችግር ውስጥ ነው ያለው።እንደ ድሮው ኢትዮጵያ ውስጥ ሰው በርሃብ ሊሞት ነው ቢባል ቶሎ ምላሽ ሊሰጡን አይችሉም። ምክንያቱም እነሱም የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ናቸው ያሉት። አሁን ባለንበት ሁኔታ 30 እና 40 ሚሊዮን ህዝብ ችግር ውስጥ ቢገባ የትኛውም አለም ሊረዳን አይችልም።ምግብም ብንፈልግም በዚህ በነፃ ገበያው ተፎካክረን በገንዘባችን እንኳ ልንገዛ የምንችልበት ሰዓት አይደለም።በጣም አሳፋሪ ነገር ውስጥ ልንገባ እንችላለን።አሁንም ደግመን ደግመን ማሰብ ያለብን ገበሬው እንዳይታመም ነው። ቢያንስ ቢያንስ የመኸሩንና የክረምቱን እርሻ ካረሰ ለሚቀጥለው አመት ህዝቡ የሚበላው አያጣም።
ሌላው በሰሞኑ የፖለቲካ ቀውስ ምክንያት አትክልትና ፍራፍሬ የሚያመርቱ በርካታ እርሻዎች መዘጋታቸው የሚታወስ ነው። አብዛኛው ባላሃብት መሸጥ፣ መውጣትና መዝጋት ይዟል። የተቃጠሉም አሉ። በመሆኑም መንግስት ለእነዚህ አካላት እንዴት ከለላ ሰጥቶ ቶሎ ወደ ስራ እንዲገቡ ማድረግ እንደሚገባ ሊያስብበት ይገባል። በተለይ ቶሎ ሊደርሱ የሚችሉ የመስኖ ሰብሎች ላይ ትኩረት ማድረግ አለበት።
ከዚህም ባሻገር በአሁኑ ወቅት የውጭ ምንዛሬም ዋጋ ቀንሷል። ይህም የውጭ ምንዛሬ ክምችታችንን ልናሳድግ የምንችልበትን እድል ሰፊ ያደርገዋል። በተመሳሳይ ሪሚታንስ ሊጨምር ይችላል።ምክንያቱም አሁን ላይ ጉዞ ከመገደቡ ጋር ተያይዞ በጥቁር ገበያ የሚላክበት መንገድ ቆሟል። አሁን ግን በቀጥታ በባንክ ስለሆነ ሊላክ የሚችለው ይህም የአገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ክምችት እንዲጨምር ያደርጋል።ለዚህ ነው የኢትዮጽያ ኢኮኖሚ ብዙ ሳይጎዳ ተቀይረን ልንወጣ እንችላለን የምለው።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉና በአንባቢዎቼ ስም ከልብ አመሰግናለሁ፡፡
አቶ ያሬድ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 24/2012