የእኛ የኢትዮጵያውያን የአኗኗር ስልት እርስ በእርሱ የተጎናጎነ ነው። በሰፈር በጉርብትና፣ በእድር፣ በእቁብ፣ በሀዘንና በደስታ፣ በሥራ ቦታ፣ በቤት አሰራራችን ብቻ በሁሉም መስክ ትስስራችን የበረታ ነው። ይህ መልካም መስተጋብራችን የአንዱ ቤት ሀዘን ለሌላው ቤት፣ የአንዱ ቤት ደስታ እንዲሁ ከሌላው ጋር እንዲተሳሰር ምክንያት ያደረገ ነው። አንዳንዴ አልስማ ብትልም፣ በግድ ጆሮህ ውስጥ ጥልቅ የሚል የሳግ ድምጽ፣ ፉጨት፣ ኡኡታ፣አፍንጫህ አላሸትም ቢል እንኳ ዓይነቱ በትክክል ምን እንደሆነ የምታውቀውም፣ የማትለየውም አይነት የወጥ ሽታ ከጎረቤት መጥቶ አፍንጫህ ውስጥ ጥልቅ ይላል፤ ያኔ በሰማኸውም ነገር ይሁን ባሸተትከው ወጥ ቀልብህ ይገዛና እርምጃ ትወስዳለህ። ነገራችን እንዲህ ነው።
“የዚህ ቤቴ ነገር እጅጉን ገረመኝ፣ እዚህ ያለሁ ሲመስለኝ ለካ እዛኛው ቤት ነኝ።” የሚል ነባር ግጥም አለ። ብዙዎቻችን ባንሄድም እዛኛው ቤት ሄደናል። በዚህም እጅግ በጎ ልምዶችን መዋዋሳችን አልቀረም። ባተሌ የሆኑ እናቶች ከሚጠቡ ልጆቻቸው ውጭ ያሉ ድክ ድክ የሚሉትን ህጻናት ለጎረቤት ጥለው የመውጣታቸው ልምድ ያለ የኖረና የቀጠለ የበጎነታችን መገለጫ ነው። የጎረቤቲቱ እናት የገዛ ልጆቿን በምታይበት ዓይንና በምታጎርስበት እጅ ነው፤ የጎረቤቷን ልጆች የምትይዘው፤ አንዳንዴም አራስ ልጅን ጥለው ወጥተው የልጆቿን ጡት ማጋራት በሐበሻ የጎረቤት ኑሮ ያልተለመደ ነገር አይደለም። ይህንን ደግነት በመላይቱ ገጠርና ከተማ ቀመስ የገጠር አኗኗር ውስጥ ማግኘት አይከብድም ።
ወጣት ልጆች ከትምህርት ቤት መልስ ከጎረቤት ልጆች ቤት መክሰስ መጋራት እንግዳ ነገር አይደለም። ይሁንና እነዚህ መልካም የግንኙነት መረቦች ታዲያ በመልካምነት ብቻ አይዘልቁም። በዚህ ግንኙነት ውስጥ ስሑትም ሳንካም ነገሮች አይታጡም።
ወደቀደመ ነገሬ ልመልሳችሁና ልጆች የቤታቸው የሰፈራቸውና በከፊልም የትምህርት ቤታቸው ውጤቶች ናቸው። በዚህ የውሎ ሰንሰለታቸው ውስጥ በአእምሯቸው የተጻፈውን መመዝገባቸው አሌ የሚባል አይደለም። ለዚህ ነው “ልጅህን 12 ዓመት ሳይሞላው በፊት ስጠኝ ምርጥ ካቶሊክ አደርገዋለሁ፤ ከ12 ዓመት በኋላም እንዲሁ ሆኖ ይቀራል”፤ ሲሉ ነባር የቫቲካን ጽሑፎች የሚያመላክቱት።
እውነት ነው፣ በልጅነታችን የተጻፈብን መልካምነት ስናድግ አብሮን ያድጋል፤ እርግማንም ካለ በልባችን ጓዳ ውስጥ ይህንኑ ይዞ ያኖራል። ከፍ ስንልም ይህንን እየተረጎምን እንኖራለን፤ ለዚህ ነው ደስተኛነት የራቃቸው ነገራቸው ዝግ የሆኑ ወጣቶች ስታገኙ ጠጋ ብላችሁ መጠየቅ ያለባችሁ።
“የሰው ልጅ አመጸኛነት በህይወቱ ውስጥ ካየለ፤ ሊያዩለት የሚገባ አንዳች ነገር በውስጡ አለ።” የሚባለው። እውነት ነው፣ በልጅነታችን የተጻፈብን መልካምነት ስናድግ አብሮን ያድጋል፤ እርግማንም ካለ በልባችን ጓዳ ውስጥ ይህንኑ ይዞ ያኖራል። ከፍ ስንልም ይህንን እየተረጎምን እንበላዋለን፤ እንኖረዋለን፤ ታዲያም ደስተኛነት የራቃቸው ነገራቸው ዝግ የሆኑ ወጣቶች ስታገኙ ጠጋ ብላችሁ፣ መጠየቅ ያለባችሁ።
‹‹የሰው ልጅ አመጸኛነት በህይወቱ ውስጥ ካየለ፣ ሊያዩለት የሚገባ አንዳች ነገር በውስጡ አለ።” የሚባለው ልክ እንደዚሁ ባፈነገጠና ባልታወቀ ሁኔታ ነገር አለሙ የዞረበት ወጣት በጎረቤት፣ በሰፈርና በቤተዘመድ መሐል ስታገኙ ለብቻውና ለራሱ ከመተው ይልቅ ጠጋ ብላችሁ በማናገር ሸክሙን ልትጋሩት ይገባል። በእኛ አኗኗር ውስጥ እንደዘበት ከወላጆች አንደበት የሚወረወሩ የእርግማን ቃላት በልጅ ልብ ውስጥ የሚተዉአቸው ቁስሎች ብዙዎች ናቸው።
አንድ ጊዜ ያገኘኋት የማውቃቸው ሰዎች ልጅ ለብቻዋ ታለቅሳለች። በቁጥር ጥቂት የማይባል ወጣት በየትናንሹ ነገር ስለሚከፋውና ስለሚያለቅስ ላልፋት ፈለግሁና ተጠግቼ “ምን ነክቶሽ ነው እንዲህ እንባሽ የሚወርደው ?” አልኳት።
በአንድ በኩል እናቴ፣ “ቤት ውስጥ እኔን ከወንድሞቼ ጋር በማወዳደር ወንድሞችሽን አታይም እንዴት ጎበዞች እንደሆኑ! የእነሱን ግማሽ እንኳን መሆን እንዴት ያቅትሻል?” ትለኛለች።
አባቴ ደግሞ ደጋግሞ “ድሮም ሴት ልጅ ›› ይላል። እኔ ራሴን እንጂ ማንንም መሆን እንደማልችል እንዴት ልንገራቸው፤ እንዴትስ ይሰሙኛል? አለችኝ። የሚገርመው ብዙ ወላጆች ወደ ልጆቻችን የምንወረውራቸው ቃላት ምንኛ ልባቸውን እንደሚሰብሩ መገመት ያቅተናል። ቆም ብዬ አሰብኩና ምን ማድረግ እንዳለብኝ ማውጠንጠን ጀመርኩ። ዝም ብሎ መሄድ ስላቃተኝም፣ “ማንበብ ትወጃለሽ?” አልኳት።
‹‹አዎ በጣም›› ስትለኝ፣
“መጻፍስ ?”
“በሚገባ! ›› ስትል መለሰችልኝ። ወዲያውኑ ማንበብሽን ቀጥይ። የምትጽፊያቸውን ጽሑፎች ግን አምጪና በሬዲዮ ጣቢያ ላይ እንዲቀርቡልሽ አደርጋለሁ፤ ከዚያም በጊዜ ውስጥ ራስሽ ታቀርቢያቸዋለሽ፤ ተባብለን ተለያየን። እንደገመትኩትም ከጊዜ በኋላ፣ ውጤታማ ጸሐፊ መሆኗን አወቀች። ልጆቻንን የማይችሉትንና እኛ የምንፈልግባቸውን ነገሮች ከመነዝነዝ የሚችሉትን ለይተንና አውቀን በመቀበል ልናጀግናቸው ይገባናል።
ወንድሟን አልመሰለችምና ምን ይፈጠር ? ጎበዟን እህቱን አልመሰለምና ምን ይደረግ ? እርሱ በእውነት የሚችለውን ነው፤ መሆን ያለበት። ይልቅ መሆን የማይገባውን ክፉ እንዳይሆን መከላከል፣ መምከር፣ መደገፍና ማረቅ ይገባል።ለዚህም የልጆቹ የራሳቸው ድርሻ አለ። ነገር ግን እንትናን ካልመሰልክ ብሎ ማወዳደር ልጁን ያሰቃየው ይሆናል እንጂ አይረባውም። እንዳልኳችሁ ትልቁ ነገር ለመልካም መትጋቱ ነው፤ ልጁ የሚወድደውንና የሚችለውን እንጂ የፈለግነውን እንዲያደርግ አንጫነው።
“አንተ የማትረባ፣ ስትወለድ ውሃ ሆነህ በቀረህ፣ ሲበሉ የላኩህ፣ ቀልበ-ቢስ፣ ደንቆሮ፣ ኳስ ፊደሉ፣ ዳገት እርሙ ፣ ከንቱ፣ ዶሮ ራስ፣ ሁለት ግራ እግር (ደንጋራ ለማለት ነው)”፣… “የለበስከው የማያምርብህ፣ የሰራሽው የማይጥምልሽ፣(ሴትን ልጅ አብዝተን ከኩሽና ህይወት ጋር አቆራኝተን ስለምናስብ ) ወዘተ…” ብለን በነገር የላሥናቸው ልጆቻችን አንደኛ ለራሳቸው ያላቸው ግምት አነስተኛ ስለሆነ ትልቅነትን ለሌሎች የሚሰጡና ታናሽነት ተጣብቋቸው የተወለደ የማይላቀቅ የኑሮ ዕጣ እንደሆነ ያስባሉ። ሁለተኛ፣ ሌላውን ሰው በቀና አይን አያዩም። ስለዚህ አንድም ክፉና ማህበረሰብ ጠል (Anti-social) ፀባይ ያሳድጋሉ፤ ሁለትም ለራሳቸውም ክብር አይሰጡም። ራሱን ከማያከብር ሰው ሌላውን እንዲያከብርና እንዲያደንቅ መጠበቅ ሞኝነት ነው።
“ዶሮ ራስ” ሲባል ስለኖረ፣ “ድንጋይ ራስ “ብሎ ሌላውን ለመዝለፍ አያመነታም። ከአፉ የሚወነጨፈው እርግማን ነው፤ እርግማን ደግሞ ቤት አያሰራም፤ ካሰራም አያስኖርም፤ አከራይቶት በአከራዮች የደረሰበትን እንግልት በሌላው ላይ መወጣት ነው የሚፈልገው።
በነገራችን ላይ “ዶሮ ራስ”፣ የሚለው ሐረግ ምንጩ ሲፈተሽ፣ ከኢጣሊያ ነው። የጠሉትንና ነገር ቶሎ አልገባው ያለውን፣ ሲሰራም የልብ አድራሽ ያልሆነ ሰውን ማንቋሸሽ ሲፈልጉ “ቴስታ ዲ ጋሊና” ፤ ሲሉ ቃሉን ይጠቀሙበታል። ይህንን ነው፤ በቀጥታ የወረስነው። ሰው ቴክኖሎጂያዊ ቃል፣ የቴክኒክ አሰራርንና አካሄድን ይቀስማል፤ መልካምነትን አመልካችና አበረታች ቃላትን ይወስዳል እንጂ ነውር እንዴት ይቃርማል። ይሁንና ይኸው ቃል የመዝገበ-ቃላችን አካል ሆኖ አለ።
“ዶሮ ራስ” ለሰው ሲሆን የማያስብ፣ የማያስተውል፣ ጥሬ ለቃሚ፣ አብስሎ የማይበላ፤ አብስሎ የማይሰራ፣ የተሰራ የሚያበላሽ፣ (ስጥ የሚደፋ) አድኖ የማያመጣ፣ እንከፍ የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ የሚይዝ ነው። ይህንን ነው ወራሪዎቹ ኢጣሊያኖች ያወረሱን። ለነገሩ ለዘረኞቹ ፋሽስቶች ጥቁርነት ያለማወቅ፣ የድንቁርናና ያለመሰልጠን ማንነት እንደሆነ ስለሚገመትና ስለሚታመን ያሉትን ቢሉ ዓላማቸው እኛን ማሳነስና ራሳቸውን መቆለል ስለሆነ አይገርምም።
እኛ ግን ምን ሲሆን ነው የነጭ ስድብ እንደጌጥ የምንለጥፈው። ራሳችን የቀባባናቸውና የምንችላቸው ነባር የእርግማን ቃላትና ሐረጎች እኮ “ሞልተውናል”። ደሞ ለማሳነስ፣ ደሞ ለማንኳሰስ፣ ደሞ ለማንቋሸሽ ማን ብሎን ? “የበላችው ያገሳታል፤ በላይ በላዩ ያጎርሳታል” እንዲሉ ሆነና በጎ ነገር ሳናጣ ስድብ ከባህር ማዶ እንዋሳለን እንዴ? ያኔ የዛሬ 79 ዓመት የወጡ ጣሊያኖች በልባችን ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሻገሩ ነገሮች ጥለውብን ነው የወጡት። ከፈለጋችሁ ፒያሳን፣ ማርካቶን፣ ፖፖላሬን፣ ካዛአንችስን፣ ባልዲን፣ አካፋን፣ ሶሌቶን፣ ሴንኬሎ፣ (ማንደጃ ያልነውን ) ፈርሜሎን፣ ባርኔጣን፣ ጋዜጣን፣ ሰጥተውናል። ይኼ ደግም የደግነቱን ያህል ክፉ አሻራም አለው። ይሁንና ጥሩነታቸው ያመዝናል፤ ምክንያቱም አንድም ያለፍንበት ዘመን አመልካቾች ሲሆኑ፤ ሁለትም በደረስንበት እውቀት ጽንሰ- ሐሳቡን አሳምሮ ሊገልጽ የሚችል ቃል ባልነበረን ጊዜ የተገኙ ስያሜዎች ናቸውና። እርግማንና ስድቦቹን ግን ከቶውንም በአንደበታችን ተዘርተው በአእምሯችን ማሳ ደርጅተው ከቤት ወደ ቤት፤ ከጓደኛ ወደ ጓደኛ እናዘዋውራቸዋለን። ለምን?
እርግማን ዘር አለው፤ ግዴላችሁም ወገኖቼ ክፉ ቃል ተንጋልለው የተፉት አይነት ነው። ስለዚህ መራገምና ክፉ የቃል ዝናብ ማዝነብ የትም አያደርሰንም፤ ትንሽ የስድብ ጅረት ዶፍ ሆኖ ቤትህን ያጠፋዋል። ይህ የመዝራትና የማጨድ ህግ ነው።
አሁንም የአንድ ልጅ ታሪክን ላጫውታችሁ፤ ልጅቱን ከቤት ወደ ትምህርት ቤት- ከትምህርት ቤት ወደ ቤት የሚያመላልሷት በቤት መኪና ነው። በተለይ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከገባች በኋላ ወደ ጭንቅላቷ የሚመላለሱ ጥያቄዎች ነበሩና ከማን ጋር እንደምታወራው ችግር ይላታል።
አባት በልጅ አያያዝ እምነቱ ጥብቅ ነው፤ ለልጅ ፊት ማሳየት አይገባም፤ ብሎ በጽኑ የሚያምን ዓይነት ሰው ነው። እናትም እንደዚሁ ሃይማኖቷን ወዳድ የሆነች ሴት ናት። አስጠኚ ተብላ ወደ ቤት የምትመጣ ሴት አለች፤ አንድ ቀን ‹‹ እባክሽን አንድ ጥያቄ አለኝ›› ትላታለች።
“ምንድነው ጠይቂኝ ”
“ለምንድነው ወንዶች ፍጥጥ ብለው የሚያዩኝ ?”
“ኦው… እስካሁን አናግረውሽ አያውቁም?”
“አያውቁም፤ የስልክ ቁጥርሽን ስጪኝ ብሎ የራሱን ስልክ ቁጥር ጽፎ የሰጠኝ ልጅ አለ። እንደምታውቂው እኔ ስልክ የለኝም።”
“ልትደውይለት ትፈልጊያለሽ?”
“ለምን ሊያናግረኝ እንደፈለገ ለማወቅ እፈልጋለሁ።”
ለማንኛውም ቁጥሩ ላይ እንደውልለት ብላ ታስደውላታለች። ድምጽ-ማጉያው ላይ አድርጊና አውሪው፤ አለቻት። እንደተባለችው አደረገች።
ስትጨርስም ‹‹ ምንድን ነው የሚፈልገው ?›› ስትላት ልምዷን አካፈለቻት። ልታደርግ ስለሚገባት ጥንቃቄ ነገረቻት። በነገራቸው መጨረሻ ላይም ‹‹ ለእማማ ልንገራት ?›› ስትላት ‹‹ አዝማሚያዋን አይተሽ አናግሪያት ›› ስትል መከረቻት። የዚያን ቀን የተከፈተው የማግባቢያ ንግግር ለተሻለ ቀን ያዘጋጃት መሰለ።
ይሁንና እናትየው ይህንን ስታውቅ ወዲያው ያሰበችው ትምህርት ቤቱን ለመቀየር ነው። ደመናው በከበደበት በዚያ ዝናብ ይኖራል፤ ቢቻል ዝናቡ የሚያስከትለውን ዶፍ በዘዴ ለማለፍ ጥረት ማድረግ ይሻላል እንጂ፤ ዝናቡንም ደመናውንም ለማስቀረት መታገል ትርፉ በማይቀረው ዝናብ ተመትቶና ተፍገምግሞ መበስበስ ነው። ልጅቱን ከትምህርት ቤት ማስቀረትም ሆነ ትምህርት ቤት መቀየር ወደ እልህ ውስጥ ከመክተት ያለፈ ነገር አይፈጥርም።
ከዚህ ባለፈ እኛ ያሳደግንሽ፣ የደከምንብሽ ደፋ ቀና ብለን የለፋንብሽ….ብሎ ለእርግማን ዳር ዳር ማለት ምን የሚሉት ፈሊጥ ነው። እውነት ነው፤ አብልታችሁና አጠጥታችሁ አሳድጋችኋታል። ግን የቀለባችኋት ልትበሏት አይደለም፤ ያስተማራችኋት ልትማሩባት አይደለም፤ ያኖራችኋት ልትኖሩባት አይደለም። እናንተ ከለፋችሁበት የተሻለ ኑሮ በመኖር በመልካም ስማችሁን እንድታስጠራ ነው። ስለዚህ በመንገዷ ላይ የሚያጋጥማትን ችግር የማለፊያውን ዘዴ ከልምዳችሁ ማካፈል፣ ከኑሮ ሰበዝ የፈተናችሁን ሳር መዝዛችሁ በማሳየት መምከር እንጂ ምን ሲደረግ በዚህ መንገድ ታልፊያለሽ፤ አታስተውይም ? አእምሮሽ አይሰራም፣ ነገርሽ “እንጉልፋቶ” (የጣሊያንኛ ቃል ነው፤ የማይሰራ ወይም ከጥቅም ውጭ የሆነ፣ ማለትን ይወክላል) ነው? “አውራዶሮ ስታይ የምታስካካ ዶሮ ብቻ ናት፣ አንቺ “ዶሮ ራስ” ነሽ እንዴ?!” እያሉ ልጅን ቀልብ ማሳጣት አዋቂነትም አስተዳዳሪነትም አይደለም።
የሚያጋጥሙንን ችግሮች የምንፈታበት ዘዴ ወደምንፈልገው ማጠቃለያ እንዲያደርሰን በማሰብ ነው እንጂ የማይቀረውን ለማስቀረት በመጣር አይደለም። ስለዚህ፣ ልጆቻችን ወጣቶቻችን ሊደርሱበት ወዳሰቡበት ግብ እንዲደርሱ በቅንነት እንርዳቸው፤ አናስተጓጉላቸው። “አትረባም ፣ … ጀምረህ መጨረስ አይሆንልህም ፣… የእነእንትናን ልጅ አታይም? አንተስ እንጀራ አይደል እንዴ የምትበላው፣… ነው ወይስ እናትህ በስድስት ወሯ ነው የጨነገፈችህ?” የሚሉ መራራና አጥንት ሰባሪ ቃላት በመሰንዘር፣ ከልጆቻችንና ወጣቶቻችን ልብ ውስጥ ልናወጣው የምንፈልገውን ወርቅ አያወጣልንም።
አንዳንድ ሰዎች፣ ሰራተኛውን ንብ በጣም ስትጭመቀው ማሩን ታወጣለህ፤ ሲሉ ይናገራሉ። በጨመቃ ውስጥ ማር ማውጣት የሚቻል ቢሆን ኖሮ አበቦች ባላስፈለጉ፤ ጨመቃው ለንቦቹ ሞት ምክንያት እንደሚሆን ማወቅ ያስፈልጋል። ስለዚህ ምንን እንዴት ማድረግ እንዳለብን ከማሰባችን በፊት ተፈጥሯዊ ፍሰቱን መረዳትና ለዚያ ተገቢውን ትብብር ማድረግ መባረክ ነው። ለወጣቶቻችንም እንደዚሁ ነው።
እርግማንና ስድብ ሐገርና ነገር የሚለውጡ ቢሆኑ ኖሮ እንደ ሶሻሊስት መንግስታት ለማይመስላቸው ቅፅል ስም በማውጣት የሚራገም አልታየም፤ አልነበረምም። ሶሻሊስት መንግስታት የማይፈልጉትን እውነትና እምነት ደጋግሞ በማውገዝ ድርጊቱን በሰው ህሊና ወንጀል ማድረግና ደጋግሞ በመዋሸት እውነት አስመስሎና አድርጎ በማቅረብ ከፋሽዝም መሰረታዊ መርሆዎች የሚወራረሱት ገራሚ ጠባይ ስላላቸው የአንድ እናት ታላቅና ታናሽ ልጆች ናቸው ይሏቸዋል።
ውግዘትና ማሳነስ፣ በሰው አእምሮ ውስጥ ጎልብቶና ቤት ሰርቶ ሰውየውን በትንሽነት ስሜት ውስጥ ጨምሮ እንደማያልፍለት እንደማይሳካለት፣ እንደማይወጣውና ለሌሎች እንደተሰጠ ፀጋ አድርጎ ካሳየው ያኔ ነገር ተበላሸ ማለት ነው። ይህ አልሆነም፤ አልተደረገም፤ ብላችሁ ካሰባችሁ ተሳስታችኋል። ምክንያቱም በማሳነስ የተገፉ በማንኳሰስ የተነቀፉ ብዙ ሰዎች በማህበራዊ አኗኗር ደረጃቸው ከፍ እንዳይሉ ሆነው ቀርተው ታይተዋልና።
በምድራችን ላይ በጂፕሲዎች (Gypsies) ላይ (ራሳቸውን ሮማኒ ነን ነው የሚሉት)፣ በመላይቱ አውሮፓ ከ1ኛው ዓለም ጦርነት ጀምሮ የደረሰባቸውን እንግልትና መንከራተት ስናስብ፣ በህንድ፣ የተገለሉና አይነኬ (The untouchables) የተባሉ ጎሳዎች (አጫጭሮችና ጠያይም ናቸው) የሚደርስባቸውን ፅየፋ ስናየው፣ እኛም ሐገር ዘመናውያን ዘመናዊ አይደሉም፤ በምንላቸው ወገኖች ላይ የምናሳየው ክፉ ጠባይ፣ የዘመናት ማሳነስ ውጤትና ያንንም ማህበረሰቡ ራሱ ቅቡል አድርጎት እንዲወስደው ማድረጋችንን እናያለን። ይህ እንደዚህ ስር እስኪሰድ መቆየት አይገባንም ነበረ። ማህበራዊ ክፉ ግፊት ከቶውንም ህብረት ነስቶ፣ አቅም ያሳጣናል አይረባንም።
እና ማንኛውንም ወገን፣ የሥራ ባልደረባን፣ የትዳር አጋርን፣ የገዛ ልጅንም ቢሆን በንቀት ዓይን በማየት የምናሰፋው መሬት፣ የምናበረክተው ወረት፣ የምናፈራው ጥሪት የለንም፤ አይኖርምም። ይልቅስ በህብረትና በመተናነጽ የምናበረክተውና የምናበዛው ይኖራል እንጂ። ይህንንም የምንጀምረው ከቤተሰብ ነው። በቤት ውስጥ ለልጆቻችን፣ በትምህርት ቤት ለተማሪዎቻችን፣ በሰፈር ለጎረቤት ወጣቶች የሞራል ድጋፍ እጆች እንጂ የሞራል ስብራት ፈንጂዎች ልንሆን አይገባንም።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 24/2012
አገልጋይ ዮናታን አክሊሉ