ላለፉት አራት ወራት ዓለም በከባድ ወረርሽኝ ተመታ ስትናወጥ ከርማለች። ከሰሜን እስከ ደቡብ፤ ከምዕራብ እስከ ምስራቅ የሰው ዘሮች ምህረት የለሹን ኮቪድ 19ኝን ሽሽተው ቤታቸው ከከተሙም ሰንበት ብሏል። ፖለቲከኞችና ተመራማሪዎች ሚሊዮኖችን እንደ ቅጠል እያረገፈ ላለው ተውሳክ ፈውስ ፍለጋ ቀን ከሌሊት ላይ ታች ሲባዝኑ ሰነበቱ። ጥቂቶቹም ፀረ ኮረና ክትባትና መድኃኒት ይሆናል ብለው ያገኙትን ለአለም ህዝብ አበሰሩ። ይሁንና ደንታ ቢሱ ኮረና ቫይረስ ግን አሁንም ከሊቅ እስከ ደቂቅ፤ ከድሃ እስከ ሀብታም፤ ከአቅመ ደከማ እስከ ሃያሉ ማጥቃቱንና ማንበርከኩን ቀጥሏል።
ሌላው ቀርቶ ዓለምን በአንድ እጃቸው ሲያሽከረክሩ የነበሩ እንደ አሜሪካ ያሉ አገራት ጤናቸው ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚያቸው በፅኑ ታሞ ለበሽታው እጅ ሰጥተው ታይተዋል። ጥናቶችም የአሜሪካ ዓመታዊ የእድገት ምጣኔ በ4 ነጥብ 8 በመቶ እንዳሽመደመደው አመላክተዋል። የኑሮ መሰረታቸውን ነዳጅ ላይ ያደረጉ የአረብ አገራትም በተፈጠረው የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ሳቢያ የነዳጅ ዋጋ መቀነሱን ተከትሎ እድገታቸው ከዜሮ በታች እንደሚሆን የአለም አቀፍ ጥናቶች መስክረዋል።
ይኸው የሃያላኑ ፍዳ ሆኖ የከረመውና ያለው ቀሳፊ በሽታ ታዲያ ቀድሞውንም በድህነት ሲማቅቁ፥ በእርስ በርስ ግጭትና ረሀብ ሲታመሱ ለኖሩት የአፍሪካውያን ደግሞ ከየትኛው ህዝብ በላይ ሊያጠቃቸውና ኑራቸውን ከድጡ ወደ ማጡ እንደሚያደርግባቸው ተነበዩ። እስካሁን የተሰጋውን ያህል ባይሆንም በሽታው የሞት ጥላውን በአብዛኞቹ ድሃ አገራት ላይ ጥላውን ማጥላቱ ግን አልቀረም።
ከዚህ ባሻገር ደግሞ ለወትሮው ለአፍሪካ የማዕድ ቅርጫት የነበሩት ባለፀጋ አገሮች በበሽታው ምክንያት መዘጋታቸው ኢኮኖሚያቸውን በወጭ ንግድ ይደጎም ለነበሩት የአፍሪካ አገራት ምጣኔ ሀብታቸው ላይ አለመረጋጋት ለመፍጠር ብዙ ጊዜ አልወሰደበትም። የዚሁ በሽታ ጦስ ያልቀረላት አገራችን ኢትዮጵያም ኢኮኖሚ መንገዳገዱ አልቀረላትም። በተለይም ደግሞ የኢኮኖሚያችን የጀርባ አጥንት ሆኖ የኖረው አየር መንገዳችን በረራ ማቆም የበሽታውን ኢኮኖሚያዊ ተፅእኖ አጉልቶ አሳይቶናል። የአየር መንገዱ በራራ ማቆም ደግሞ ከየትኛው ዘርፈ በላይ በድጋፍ የቆመውን የወጭ ንግዳችንን እንቅስቃሴ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ አዳክሟል።
ከሰሞኑ የአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ያወጣው ሪፖርት ግን እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገራት ከድቅድቁ ጨለማ ውስጥ የብርሃን ተስፋ መኖሩን የሚያመላክት ነው። አንዳንድ የኢኮኖሚ ተንታኞችም የአለም አገራት ምጣኔ ሀብታዊ እድገት ከዜሮ በታች እያሽቆለቆለ ባለበት በዚህ ወቅት እድገታችን ከሶስት እስከ አራት በመቶ ሊቀጥል እንደሚችል ግምታቸውን አስቀምጠዋል። ለዚህ ደግሞ የግብርና ምርት ትልቁን ድርሻ እንደሚጫወት አስገንዝበዋል። በተለይም አገሪቱ በግንባር ቀደምትነት ወደ ውጭ የምትልካቸው እንደ ቡና የወርቅ ማዕድን የአለም ገበያ ዋጋ ከፍ እያለ መምጣት የዘርፉን ጭላንጭል ተስፋ የሚያለመልሙት መሆኑ እሙን ነው።
በሌላ በኩል በሽታው ገና በአገራችን ሳይገባ በራቸውን የዘጉብን እንደ ሳውዲ ያሉ አገራት ጎተራቸው እየተመናመነ ሲመጣ የማያዋጣቸው መሆኑን በጊዜ ተገንዝበው ዋነኛ የግብርና ውጤቶቻችን እንደቀድሞው ሁሉ መቀበል መቀጠላቸው ዘርፉ ከእንብርክር ጉዞው ሊላቀቅ የሚችልበት እድል መኖሩን አመላክቶናል። የአሜሪካም ሆነ የሌሎች የበለፀጉት አገራት ገበያ በእለታዊ የምግብ ፍጆታዎች እጥረት እየተፈተኑ ባሉበት በዚህ ወቅት ታዲያ ይህ የጭንቅ ወቅት ችግር ብቻ ሳይሆን በረከትም ይዞ መምጣቱን የሚያሳይ በሳል አመራር ይሻል። የተከፈቱትን ብቻ ሳይሆን በሁነኛ ቁልፍ የተከረችሙትን ሳይቀር የንግድ በሮች ማንኳኳት ከአርቆ አስተዋይ መንግስታዊ አስተዳደር ይጠበቃል።
ለዚህ ደግሞ ለወጭ ንግዱ መደላደል ደግሞ በየአገሩ የሾምናቸው ምስለኔዎች ኃላፊነት ዋናውን ድርሻ ይወስዳል። የበሽታውን የመከላከያ ቁሳቁሶችን በእርዳታ ለማግኝት የሚጥሩት ያህል የግብርና ውጤቶቻንን የየአገሩን ሱፐርማርኬቶች እንዲያጨናንቁ ሌት ተቀን መታተር ይገባቸዋል። በእስካዛሬው የዲፕሎማሲ ጉዟቸው ያልሄዱባቸውን አዳዲስ መንገዶችን በመቀየስ ዘርፉ ከተጋረጠበት አደጋ መታደግም ይጠበቅባቸዋል።
የንግዱ ዘርፍ ማነቆ ሆነው የኖሩ ህጎችና አሰራሮችም ደጋግመን ልንፈትሻቸውና እነደጊዜው ሁኔታ ተሻሽለው እንዲወጡ ለማድረግ የመንግስትን ቁርጠኝነት ይጠይቃሉ። በተለይም ደግሞ ለወጭ ንግዱ ፈተና የሆነውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለመቅረፍ ያስላሉ ተብለው በኢኮኖሚ ባለሙያዎች የሚሰጡ ምክሮችን መቀበል የወደፊቱን አሻግሮ ከሚያይ አርቆአሳቢ አመራር የምንናፈቀው ነው።
የሩቁን አንጋጠን ከማየት ባሻገር ደግሞ የጎረቤት አገሮቻችንም የንግድ ኮሪደሮች እንዲከፈቱ የማያቋርጥ የዲፕማሲ ስራ መስራት ያሻል። በተለይም ደግሞ እንደ ኬኒያ፥ ሱዳን፣ ጅቡቲና ሱማሊያ ካሉ አገራት ጋር በብር መገበያየት የሚቻልበትን ስትራቴጂ ከቀጠናው በይነ መንግስታት አመራሮች ጋር መምከርና ፈጥኖ ወደ ትግበራ መግባት ይገባል። ይህም ካልተቻለ የጥንት አባቶቻችንና እናቶቻችን ይጠቀሙበት የነበረውን እቃን በእቃ የመለዋወጥን ባህላዊ ግብይት መቃኘት ከሞኝ አያስመድብም። ለዚህ ደግሞ አብነት መጥቀስ ካስፈለገ ያለምንም የውጭ ምንዛሬ እኛ የምናመነጨውን የኤሌትሪክ ኃይል ለሱዳን ሰጥተን ነዳጅ የምናመጣበትን ስልት መቀየስ የሚቻልበት እድል ሰፊ ነው። በአጠቃላይ አሁን መላው አለም ከተጋረጠበት ጨለማ ውስጥ ዘርፉ የሚያንሰራራበትን ስትራቴጂ መቀየስ ለነገ የሚተው ተግባር መሆን የለብትም።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 24/2012