የኮሮና ቫይረስ ወደ ሀገር ወስጥ መግባቱን ተከትሎ በመላው ህዝባችን ውስጥ ተፈጥሮ የነበረው መረበሽና መደናገጥ ትዝታው ብዙም የደበዘዘ አይደለም። በአንድ በኩል በሽታው ምንም አይነት መድኃኒት ያልተገኘለት መሆኑ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የመተላለፊያው መንገድ ፍጥነቱና መንገዱ ብዙዎችን አስደንግጧል። ብዙዎች ራሳቸውን በወረርሽኙ ፊት ተስፋ ቢስ አድርገዋል።
የበሽታው ስጋቱ በየሰው ውስጥ ፈጥሮት ከነበረው መረበሽና ስጋት አንጻርም የጤና ባለሙያዎች ሆኑ መንግሥት በበሽታው ዙሪያ የሚያስተላልፋቸውን መልዕክቶች ዋጋ ሰጥቶ ከማዳመጥ ጀምሮ ተግባራዊ በማድረግ ሂደት ውስጥም የነቃና የተሻለ ተሳትፎ እንደነበረው ይታወሳል።
መንግሥት በሽታው ወደ ሀገር ወስጥ ከመግባቱ በፊት ሆነ ከገባም በኋላ እያከናወናቸው ካሉ ሰፋፊ የመከላከል ሥራዎች አንጻር በሽታው በወረርሽኝ ደረጃ በሀገሪቷ የመከሰት እድሉ ቀንሷል።የተፈራውን ያህልም አደጋ የማስከተል አቅሙ ቀንሷል። በበሽታው የሚያዙ ሰዎችም ቁጥር እለት ተእለት እየቀነሰ ተያዙ ከሚለው ዜና ይልቅ አገገሙ የሚለው ዜና ስ ፍራውን መያዝ ጀምሯል።
ይህ የሆነው ግን የጥንቃቄ ህጎችን ከመፈጸምና ካለመፈጸም ጋር ያለውን ተጨባጭ እውነታ አስልቶ በማወራረድ አይደለም። በሽታው ሀገር ውስጥ ከገባ በኋላ እንኳን ምን ያህል መዘናጋቶች እንደነበሩና አሁንም እንዳሉ ለመታዘብ አስቸጋሪ አይደለም።
እጅ በመታጠብ ራስንና ቤተሰብን ከዛም በላይ መላውን ማህበረሰብ ለመታደግ የሚያስችል በጎ ህሊናና የተነቃቃ መንፈስ የሌላቸውን ቤት ይቁጠረው።ህይወት ሊቀጥፍ በሚችል ጦርነት ውስጥ ተገኝቶ እጅ በመታጠብ ብቻ ጦርነቱን አሸንፎ መውጣት የሚታክተው ስንቱ ሊሆን እንደሚችል ብዙም የሚከብድ አይደለም። በእለት ተእለት እንቅስቃሴያችን የምንታዘበው ነው።
ርቀትን ጠብቆ በመንቀሳቀስ የመኖር ተስፋውን እውን አድርጎ፣ ነገን በትልቅ ተስፋ ከመጠበቅ ይልቅ በደመ ነፍስ በመንጋ እየተጋፋ በመሄድ ነገዎችን የሚያጠለሽ ፣ዛሬዎችን በከፋ ስጋትና ፍርሀት ለማሳለፍ የሚተጋው ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል መገመት አይከብድም።
ከሁሉም የሚከፋው ደግሞ ከወረርሽኙ ስጋት ጋር በተያያዘ ከሥራ ቀርቶ እቤቱ እንዲቀመጥ እድሉን ያገኘው ዜጋ
በየካፌውና ግሮሰሪው ተሰብስቦ ድሪቶ ወሬውን ሲደሰኩር ደክሞት ሲመሽ ወደ ቤቱ ሁለንተናው ዝሎ የሚገባው የቱን ያህል ሊሆን እንደሚችል ወጣ ብሎ ከተማውን መታዘብ በራሱ በቂ ነው።ይህ ሁሉ የሚነግረን ነገር ቢኖር የበሽታውን ወረርሽኝ ባለበት ደረጃ እንዲያገኝ ያደረው የኛ ጥንቃቄና በኃላፊነት የመንቀሳቀስ እውነት አለመሆኑን ነው።
የሚያሳዝነው ግን በዚህ ሁሉ መዘናጋት ውስጥ ሆነን ወረርሽኙ አለመስፋፋቱን በመመልከትና በየእለቱ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በቀነሰ መጠን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚባለው እራሳችንን ለተጨማሪ መዘናጋትና ለአደጋ ወደሚያጋልጡን የእለት ተእለት ተግባሮቻችን ለመመለስ መፍጠናችን ነው።
እዚህ ላይ መላው ህዝባችን አብዝቶ መረዳትና ደግሞ ደጋግሞ ማሰብ ያለበት እስካሁን ባለው ዓለም አቀፍ ተጨባጭ እውነታ አንጻር የቫይረሱ ተለዋዋጭ ባህሪ ስለቫይረሱ እንዲህ ነው ብሎ በርግጠኝነት አፍ ሞልቶ ለመናገር የሚያስደፍር አለመሆኑን ነው። ከሁሉም በላይ ግን የበሽታው የአድቢነት ባህሪ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ መሆኑ ነው።
ከዚህ በላይ ደግሞ በሀገሪቱ ቫይረሱን በሚመለከት በላቦራቶሪ የሚደረጉ የምርመራ አገልግሎቶችና ግኝቶች አጠቃላይ ከሆነው የበሽታው ስጋት አንጻር የሚያዘናጉ አለመሆናቸው ነው። ከዚህም በመነሳት ነው መንግሥት ቫይረሱን የመመርመር ሀገራዊ አቅሙን ለማሳደግ የሚያስችል ሰፋፊ ሥራዎችን በመስራት ላይ የሚገኘው።
እስካሁን ለማየት የሞከርናቸው ተጨባጭ እውነታዎች የሚነግሩን ደረቅ እውነታ ቢኖር በየትኛውም ሰዓትና ጊዜ ለበሽታው ወረርሽኝ የመጋለጣችን እድል ሰፊ መሆኑን ነው። ይህ ደግሞ በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ብንሆን ለመዘናጋት በር ለሚከፍቱ ጉዳዮች ምንም አይነት ክፍተት ሊኖረን እንደማይገባ ነው።
በርግጠኝነት መናገር ከተፈለገ በሽታው በወረርሽኝ ደረጃ ያለመከሰቱ እውነታ እየተወሰደ ካለው የጥንቃቄ እርምጃ ጥንካሬ ወይም ቀናቶችን እየቆጠርንበት ባለው የአኗኗር ዘይቤያችን የመከላከል አቅም አለመሆኑን በአግባቡ መረዳት ያስፈልጋል።
ይህንን በአግባቡ መረዳት ከቻልን ያለን አማራጭ የጤና ባለሙያዎች እና መንግሥት የሚሰጡትን የጥንቃቄ ምክር በመቀበል በኃላፊነት መንፈስ መተግበር እና በተግባር ብቻ ነው። መዘናጋት ሊያስከፍለን የሚችለውን ዋጋ ለአፍታ ወደሚያስረሳ መዘናጋት ፈጽሞ መሄድ የለብንም። የመዘናጋት መንገድ የሞት መንገድ ነው።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 22/2012