‹‹ … ወይኔ! ወይኔ! ወይኔ ገብሬ! ገብሬ የመታውን የዚምባብዌው ሁለት ቁጥር በራሱ ግብ ላይ … በራሱ ግብ ላይ ከመረብ አሳረፈ … በራሱ ግብ ላይ ከመረብ አሳረፈ … ››
‹‹ … አሁን ዳኛቸው ነው የሚመታው … አሁን ዳኙ ሊመታ ነው … አሁን ይገላግለናል … ወይኔ! ወይኔ ዳኙ! ዳኙ አገባ! ዳኝሻ አገባ! በጣም አስደናቂ ግብ ነው ዳኝሻ! ቀኙን አሳይቶ ግራውን፤ ግራውን ዐሳይቶ በቀኙ … አሁን ተጨዋቾቻችን ደስታቸውን እየገለጹ ነው! … ሕዝቡ ወደ ሜዳ እየገባ ነው … ተመልካቹም ‹እንደተመኘኋት አገኘኋት› እያለ ነው … ችቦ በራ! ስታዲዬሙ ተንቀለቀለ …››
ይህ ድምጽ ከ32 ዓመታት በፊት፣ ታኅሣሥ 17 ቀን 1980 ዓ.ም ከጋዜጠኛ ደምሴ ዳምጤ አንደበት የተሰማ ሳቅና እንባ የተቀላቀለበት የደስታ ጩኸት ነበር። ቀኑ ደግሞ ኢትዮጵያ የምሥራቅና መካከለኛው አፍሪካ የእግር ኳስ ሻምፒዮና ዋንጫ (ሴካፋ /CECAFA)ን ለመጀመሪያ ጊዜ ያሸነፈችበት የማይረሳ ዕለት ነበር።
ደምሴ ዳምጤ በዕለቱ ጨዋታውን ለሕዝቡ ሲዘግብ የነበረበት ሁኔታም ከብዙዎች አዕምሮ የሚዘነጋ እንዳልነበር ዛሬም ድረስ ምስክርነታቸውን የሚሰጡት ብዙ ናቸው። ይህ የደምሴ ድምፅ በአሁኑ ወቅት በመገናኛ ብዙኃን በሚቀርቡ ብዙ የስፖርት መሰናዶዎች ላይ የመግቢያ ሙዚቃ (የፕሮግራም ማስተዋወቂያ/ማጀቢያ) ሆኖም ያገለግላል። ብዙ ወጣት የስፖርት ጋዜጠኞችም ደምሴ የሙያ ተምሳሌታቸው እንደሆነ ሲናገሩ መስማት ተለምዷል።
ደምሴ የተወለደው በ1945 ዓ.ም ሲሆን እድገቱም በምስራቃዊቷ ድሬዳዋ ከተማ ነው። ብዙዎች እንደሚናገሩለት ደምሴ ተሰጥኦውን ፈልጎ ለማግኘት ጊዜ አላባከነም ነበር። የስፖርት ዘጋቢነት ሙያውን የመረጠው ገና በልጅነቱ ነው። በድሬዳዋ ከተማ አሸዋማ ስፍራዎች ላይ ይደረጉ የነበሩ የታዳጊ ህጻናትና የወጣቶች የእግር ኳስ ግጥሚያዎች ደምሴ ወደ ስፖርት ዘጋቢነት ሙያ እንዲገባ ትልቅ ሚና ነበራቸው። ደምሴ የኳስ ፍቅር ነበረው። ይሁን እንጂ የኳስ ፍቅሩን በንቁ ተመልካችነት፣ በታዛቢነትና በደጋፊነት ከመግለጽ ባለፈ በተጨዋችነት ታቅፎ የተሳተፈበት የእግር ኳስ ቡድን አልነበረም። የእርሱ ትኩረትና ሕልም መጫወት ላይ አልነበረም፤ መዘገብ ላይ እንጂ።
ደምሴ ለበርካታ ጋዜጠኞች አርዓያ እንደሆነው ሁሉ ለእርሱም አርዓያ የሆነውና እጅግ አብዝቶ እንደሚያደንቀው ደጋግሞ የተናገረለት አንጋፋው ጋዜጠኛ ሰለሞን ተሰማ ነው። የዜና አቀራረቡ እጅግ ይመስጠውና ዘገባ ለመዘገብም ያነሳሳው እንደነበር ተናግሯል።
በግለሰብ ደረጃም ለጋዜጠኛ ሰለሞን አስተዋፅኦ ትልቁን ስፍራ ሰጥቷል። ደምሴ የስፖርት ጋዜጠኛ ለመሆን ያልም በነበረበት ወቅት ሰለሞንን የመሆን ምኞት በሁለንተናው ተናኝቶ፤ በሰለሞን ስራዎች ውስጡ ገዝፎ፤ ለሰለሞን ያለው አድናቆት ጣሪያ ነክቶ … በአጠቃላይ በሰለሞን ስራዎች ቀልቡ ተሰርቆ ነበር።
ተዘራ እሸቴ የተባሉ የደምሴ የቅርብ ወዳጅ ስለደምሴ በጻፉት ጸሑፍ ደምሴ ወደ አማተር የጋዜጠኝነት ስራ የገባበትን አጋጣሚ ሲገልፁ፡-
‹‹ … በወቅቱ የነበሩት የድሬዳዋ ስፖርት ኮሚቴ አባላት የስራና የቤተሰብ ኃላፊነት ጫና የነበረባቸው ሰዎች ነበሩ። በዚህም የተነሳ የስፖርት ዘገባውን አጠናቅሮ ለዜና የማብቃት ድክመት ጎልቶ ይታይባቸው ነበር። በዚህ ክፍተት ነበር ደምሴ የሕይወት ጥሪውን ለማሳካት ብቅ ያለው። ሕልሙን እውን ለማድረግ የነጻ አገልግሎት ለመስጠት ራሱን አቀረበ። አዎንታዊ ምላሽም አገኘ። በሙያው መደበኛ ስልጠና ሳይኖረው ትምህርቱንና የስፖርት ዘጋቢነቱን አጣምሮ ያዘ። በእርሱ የእድሜ ክልል የነበሩት እኩዮቹ ባልሄዱበት ጎዳና ጉዞውን ቀጠለ። ነፃ የስልክ አገልግሎትና ነፃ የስታዲየም መግቢያ ካርድ ተሰጥቶት አገልግሎት መስጠት ጀመረ። በጥረቱም ስኬታማ ሆነ … የድሬዳዋ ስፖርት አፍቃሪዎችንም ቀልብ መግዛት ቻለ። ደምሴን በየመንገዱ እየጠራ አድናቆቱን የሚቸረው የድሬዳዋ ስፖርት አፍቃሪም በረከተ። ስሙ ገነነ። ወደፊት ጎልቶ የሚወጣ የጋዜጠኝነት ሙያ ችሎታ እንዳለውና ለሙያውም የተሰጠ መሆኑንም አሳየ። በጊዜውም ‹‹አማተር ጋዜጠኛ›› ተባለ። በዚህ ወቅት ያጎለበተው ልምድና እውቅና ለኋለኛው
የጋዜጠኝነት ዘመኑ የማዕዘን ድንጋይ ሆኖለት አለፈ …›› ብለዋል።
ደምሴ ገና በታዳጊነቱ ጋዜጣ እየገዛ ያነብ ነበር። ጋዜጦቹን የሚገዛው ለመረጃ ምንጭነት ብቻ ሳይሆን የሙያ ብቃቱንም ከፍ ለማድረግ ጭምር ነበር። በጋዜጦቹ ላይ የተጻፈውን ጽሑፍ ድምፁን ከፍ አድርጎ እንደሰለሞን ተሰማ በፍጥነት ለማንበብ ጥረት ያደርጋል። አንዱን ገጽ ለማንበብ ስንት ደቂቃ እንደፈጀበትም ወዳጁን ያስመዘግባል። ከሌሎቹ አምዶች በተለየ ለስፖርት አምድ ቅድሚያ ይሰጣል።
ደምሴ ስታዲየም ተገኝቶ ያጠናቀረውና በሬዲዮ የተላለፈው ዘገባው የተለያዩ ምላሾችን ያስተናግድ ነበር። ስለዚህ ጉዳይ አቶ ተዘራ ሲያብራሩ፡-
‹‹ … ታዲያ በምሽት የስፖርት ዘገባው ማግስት ወደ መሐል ከተማ ብቅ ሲል የሚገጥመውን ያውቅ ነበር። ጨዋታውን እንደተመለከተው ለዜና በማቅረቡ ከተመልካች አድናቆትን ሲቸር፤ በእግር ኳስ ተጫዋቾች በተለይ በተከላካዮችና በግብ ጠባቂዎች እርግጫና ጥፊን አልፎ አልፎ ይቀምስ ነበር። ለዱላ የሚዳርጉት ጉዳዮች አጥቂው ተከላካዩን እንዴት ሸውዶት እንዳለፈው … ግብ አግቢው በረኛውን አንጠልጥሎት ኳሷን ከመረብ እንዴት እንዳዋህዳት… ለመግለጽ የሚጠቀምባቸው ቃላት ነበሩ። ይህ አገላለፁ አድማጩን ቢያስደስትም በተከላካዮችና በበረኞች ዘንድ አይወደድለትም ነበር። ብዙ ጊዜ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል። ያንን ሳይፈጽም እየቀረ የተመለከተውን በተሰማው መንገድ ገልጾ ለሙያው ሲል ዱላ ይቀምሳል።
በስም እየጠቀሰ ይነግረኝ ስለነበር የምድር ባቡርና የከነማ ተከላካዮች፣ የስሚንቶው በረኛ … በእኔም ትዝታ ውስጥ እስካሁን ድረስ አሉ። አንድ ቀን ታዲያ የምሰማውን ሊያሳየኝ ፈልጎ የገዛውን ጋዜጣ ወደ ቤት እንድወስድለት አስከትሎኝ ሄደ። አጋጣሚ ሆኖ የምድር ባቡር ተከላካይ መንገድ ላይ አግኝቶን ደምሴን ሲመታው አይቻለሁ። ደምሴ ዓይኑ እንባ ሲያቀር እኔ ግን እንባ አውጥቼ አልቅሼለታለሁ …›› ብለዋል።
የቅርብ ወደጁ አቶ ተዘራ እንደጻፉት፣ ደምሴ አማተርነትን ተሻግሮ ዋና/መደበኛ/ ጋዜጠኛ የሆነበት አጋጣሚ ከ10ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ጋር የተያያዘ ነው። ወቅቱ ኢትዮጵያ 10ኛው የአፍሪካ ዋንጫን የምታስተናግድበት ጊዜ ነበር። ጋዜጠኛ ሰለሞን ተሰማና ባልደረባው ይንበርበሩ ምትኬ የተወሰኑትን ጨዋታዎች ተከታትለው ለመዘገብ ከአዲስ አበባ ድሬዳዋ ገብተዋል። የአጋጣሚ ነገር ሆነና ደምሴ ከባድ ትኩሳት የተቀላቀለበት ጉንፋን ያመውና ሲጠብቀው ከነበረው ታላቅ ጨዋታ ቀርቶ ቤት ውስጥ ይውላል። ቀልቡን ከሰረቁት እውቅ ጋዜጠኞች ጋርም ሳይታደም ይቀራል። ሰለሞንና ይንበርበሩም ከጨዋታው ፍጻሜ በኋላ የሙያ ባልደረባቸውን ለመጠየቅ አድራሻውን ያጠያይቃሉ። የደምሴንና የተዘራን ቅርበት ከሚያውቁ ሰዎች በተደረገ ጥቆማ ተዘራ እንደሚፈለግ ከስታዲየሙ የድምጽ ማጉያ ሰማ። የደምሴ ጉዳይ እንደሆነ ፈጥኖ የተረዳው ወዳጁ ተዘራ በተባለው ቦታ ፈጥኖ ተገኘ። ከዚያም በቀረበላቸው መኪና ተያይዘው ወደ ደምሴ መኖሪያ ቤት (ወደ ታላቅ እህቱ ቤት) አመሩ። ታላቅ እህቱ ከባለቤቷና ከሦስት ልጆቿ እንዲሁም ከደምሴ ጋር የሚኖሩባት አንዲት ክፍል ቤት ሲደርሱም ሰለሞንና ይንበርበሩ ባዩት ነገር እጅግ ተገረሙ፤ ተደናገጡ። ሰለሞን ‹‹ … እንደዚህ አልጠበቅኩም ነበር …›› ሲል ይንበርበሩም ፊቱን አቀጭሞ የእርሱም ስሜት ተመሳሳይ መሆኑን ገለፀ። ደምሴ ለብዙ ጊዜያት በነፃ ሲያገለግል የቆየው በአስቸጋሪ ህይወት ውስጥ ሆኖ እንደነበር እነ ሰለሞን ተረዱ።
ወደ መኪናቸው ሲመለሱም ደምሴ የሚኖረው ከማን ጋር እንደሆነ ተዘራን ጠየቁት። ተዘራም ከታላቅ እህቱ ቤተሰብ ጋር እንደሆነ ተናገረ። ደምሴ ራሱን ከሱስ ጠብቆ ከአባቱ ከምትደረግለት ድጎማ ላይ ቆጥቦ፤ አለባበሱን አሳምሮ መታየቱ ጥሩ ገቢ ያላቸው ቤተሰቦች ልጅ እንደሆነ ሳያስጠረጥረው አልቀረም።
እነ ሰለሞንም ባዩት ሁኔታ ውስጣቸው ተረብሾና ግምታቸው ከእውነታው ጋር ተጋጭቶባቸው ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ። በዚያን ሰሞን አንድ የስፖርት ጋዜጠኛ ከሀገር ወጥቶ አልተመለሰም ነበር። እነ ሰለሞንም አዲስ አበባ እንደተመለሱ የደምሴን ጉዳይ ቅድሚያ ሰጥተው ያዙት። በወቅቱ የነበሩት የስራ ኃላፊም ከሀገር ወጥቶ ባልተመለሰው ጋዜጠኛ ቦታ ሌላ አማተር ጋዜጠኛ ለመቅጠር ዝግጅት አጠናቀው ጨርሰዋል። በዚህ ጊዜ ነበር እነኚህ ተደማጭነት የነበራቸው እውቅ ጋዜጠኞች ደምሴ ለአመታት በነፃ ሲያገለግል በአስቸጋሪ ህይወት ውስጥ ሆኖ እንደነበር አለቃቸውን አስረድተው ያሳመኑትና ሀሳቡንም እንዲቀለብስ የተማፀኑት።
እነ ሰለሞንም ደምሴ በአስቸኳይ ወደ አዲስ አበባ እንዲመጣ ነገሩት። ደምሴም በፍጥነት ወደ አዲስ አበባ ሄደ፤ ከአማተር ጋዜጠኛነት ወደ መደበኛ/ዋና/ ጋዜጠኛነት ተሸጋገረ። ጋዜጠኝነትም ሙያው ሆነ። በርቀት ሲያደንቃቸው ከነበሩት ጋዜጠኞች ጋርም በቅርብ ሆኖ ደመወዝ ተከፍሎት ለመስራት በቃ። እነ ሰለሞንም ፈለጋቸውን ሲከተል የነበረውን ደምሴን እጁን ይዘው ከደረሱበት አደረሱት። ደምሴም በሙያውም አንቱ ተባለበት። ከኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይም ከስፖርት አፍቃሪው የኅብረተሰብ ክፍልም አድናቆትንና ተወዳጅነትን አተረፈበት።
የአትላንታ፣ የአቴንስና ቤጂንግ ኦሊምፒኮችን በስፍራዎቹ በመገኘት በማይረሳ አዘጋገብ ለኢትዮጵያ ህዝብ አስተላልፏል። በተጨማሪም የዓለም ሻምፒዮናዎችን፣ የመላ አፍሪካ ጨዋታዎችን፣ የአገር አቋራጭ ውድድሮችን፣ የዓለምና የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የእግር ኳስ ጨዋታዎችን … እየተመለከተ ዜናውን ለሕዝብ አድርሷል።
ከማይዘነጉት የደምሴ ዘገባ አቀራረብ መንገዶች መካከል ደምሴ በዘገባዎቹ ወቅት ኢትዮጵያውያን አትሌቶችን የሚያበረታታበትና የሚያደንቅበት አጋጣሚ አንዱ ነበር። ውድድሮችን በቀጥታ ለሕዝብ እያስተላለፈ ሳለ በስሜት ተሞልቶ ኢትዮጵያውያን አትሌቶችን ያበረታታል፤ ያደንቃል። ለአብነት ያህል ‹‹የአንበሳ ግልገል፣ ጀግና …›› በሚሉ ቃላት አትሌቶችን ያሞካሽ ነበር። ከዚህ በተጨማሪም ደምሴ በ1970ዎቹ መጨረሻና በ1980ዎቹ መጀመርያ ጎልተው ወጥተው የነበሩትን የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ተጨዋቾችንም በግጥም ያወድስ ነበር።
‹‹የምን ማራዶና የምን ፔሌ ፔሌ፣ እኛም አገር አለ ገብረመድኅን ኃይሌ›› የምትለው ጎልታ የምትጠቀስለት ግጥሙ እንደነበረች ይወሳል።
ደምሴ ለሙያው የነበረው ትጋትና ፍቅር ልዩ እንደነበር ይነገርለታል። ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድሎችን ሲያስመዘግቡ በውድቅት ሌሊት ጭምር አስፈሪ አደጋዎችን እየተጋፈጠ ከቤቱ ወደ ቢሮው ሄዶ ድሉን ለሕዝብ ያበስር ነበር።
ደምሴ በበርካታ ኢትዮጵያውያን ዘንድ እንዲታወስ ካደረጉት ዘገባዎች መካከል በ1980 ዓ.ም የተካሄደው 15ኛው የምሥራቅና መካከለኛው አፍሪካ የእግር ኳስ ሻምፒዮና ዋንጫ (ሴካፋ/ CECAFA) አንዱና ዋነኛው ነው ማለት ይቻላል። ኢትዮጵያ ባስተናገደችውና ስምንት አገራት (ኢትዮጵያ፣ ዚምባብዌ፣ ዛንዚባር፣ ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳ፣ ዛምቢያ እና ማላዊ) በተካፈሉበት በዚህ ውድድር ለፍፃሜ የቀረቡት አስተናጋጇ የኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ኢትዮጵያና የሮበርት ሙጋቤዋ ዚምባብዌ ነበሩ።
ታኅሣሥ 17 ቀን 1980 ዓ.ም የፍፃሜው ጨዋታ የተካሄደበት ቀን ነበር። በዕለቱ ሁለት ቁጥር መለያ ለብሶ ለዚምባብዌ ብሔራዊ ቡድን ሲጫወት የነበረው ተጨዋች በራሱ ግብ ላይ አስቆጥሮ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ቡድን የአቻነት ግብ ሲያገኝ በዕለቱ ጨዋታውን ሲያስተላልፍ የነበረው ጋዜጠኛ ደምሴ ዳምጤ ‹‹ … ወይኔ! ወይኔ! ወይኔ ገብሬ! ገብሬ የመታውን የዚምባብዌው ሁለት ቁጥር በራሱ ግብ ላይ … በራሱ ግብ ላይ ከመረብ አሳረፈ … በራሱ ግብ ላይ ከመረብ አሳረፈ … (ደምሴ እንባና ሳቅ እየተናነቀው ነበር) አማኑኤል ለገብረመድኅን … ገብረመድኅን በጭንቅላት ገጭቶ የዚምባብዌው ሁለት ቁጥር በራሱ ግብ ላይ ከመረብ አሳረፈ … ጨዋታው ወደማለቁ ነበር … አሁን አንድ ለ አንድ ካለቀ 30 ደቂቃ ይጨመራል … ተመልካቹ ተደስቷል … 30 ደቂቃ መጨመሩ አይቀርም … ›› እያለ በስሜት ይጮህ ነበር።
መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜው አንድ ለ አንድ በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቀቀ። በተሰጡት የመለያ ምቶች ዳኛቸው የመጨረሻዋን ግብ ሲያስቆጥር ደምሴ ‹‹ … አሁን ዳኛቸው ነው የሚመታው … አሁን ዳኙ ሊመታ ነው … አሁን ይገላግለናል … ወይኔ! ወይኔ ዳኙ! ዳኙ አገባ! ዳኝሻ አገባ! በጣም አስደናቂ ግብ ነው ዳኝሻ! ቀኙን አሳይቶ ግራውን፤ ግራውን አሳይቶ በቀኙ … አሁን ተጨዋቾቻችን ደስታቸውን እየገለጹ ነው! … ሕዝቡ ወደ ሜዳ እየገባ ነው … ተመልካቹም ‹እንደተመኘኋት አገኘኋት› እያለ ነው … ችቦ በራ! ስታዲዬሙ ተንቀለቀለ …›› ብሎ ትንፋሹ ቁርጥ ቁርጥ እያለ የደስታና ሲቃ ስሜት በተቀላቀለበት ድምፀት ያሰማው የደስታ ጩኸት ከብዙ ሰው አዕምሮ የሚዘነጋ አይደለም!
ደምሴ በአማተርነት የሰራባቸውን ጨምሮ በአጠቃላይ ከ40 ዓመታት በላይ በስፖርት ጋዜጠኝነት አገልግሏል። በአገልግሎቱም ለኢትዮጵያ ስፖርት እድገት ደከመኝ ሳይል የሰራና በዚህም በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነትን ያተረፈ ባለሙያ ነበር። በአንድ ወቅት ‹‹በሙያው ተምሬ ያካበትኩት እውቀት ሳይኖረኝ ከሕዝብ ተምሬ ነው ሕዝብ ያገለገልኩት›› ብሎ ተናግሯል። በግል ባህርይውም ተግባቢና ሰላምተኛ እንዲሁም በባልደረቦቹ ዘንድ ተወዳጅ እንደነበር የሚያውቁት ሁሉ ይመሰክሩለታል።
ጋዜጠኛ ደምሴ ለኢትዮጵያ ስፖርት ዕድገት በተለይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ዕድገት እንዲያሳይና ብሔራዊ ቡድኑ ለአፍሪካ ዋንጫ እንዲያልፍ በሙያው ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል። በዓለም አቀፍ መድረኮች የኢትዮጵያ መለያ የሆነው የአትሌቲክስ ስፖርት እንዲያድግም ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር አመራር አባል በመሆንም ሰርቷል።
ከ40 ዓመታት በላይ ያለድካም በቅንነትና በትጋት ያገለገለው አንጋፋው ጋዜጠኛ ደምሴ ዳምጤ፣ ባደረበት ሕመም ምክንያት ሕክምናውን በአገር ውስጥና በውጭ አገር ሲከታተል ቆይቶ በ60 ዓመቱ፣ ጥቅምት 26 ቀን 2005 ዓ.ም. አርፏል። ሥርዓተ ቀብሩም ወዳጅ ዘመዶቹ፣ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት፣ የስፖርት ቤተሰቦችና አድናቂዎቹ በተገኙበት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል። ጋዜጠኛ ደምሴ ዳምጤ ባለትዳርና የሦስት ልጆች አባት ነበር።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 21/2012
አንተነህ ቸሬ
ለ40 ዓመታት በትጋት ያገለገለው ድምፅ