ጥቂት የማይባሉ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በዓለማችን ለተለያዩ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ አካላዊና ስነልቦናዊ ችግሮች የተጋለጡ ወገኖች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ይገኛል፡፡ ጉዳዩን ለማስተናገድ እየተደረገ ያለው ጥረትም እጅግ አዝጋሚና ተስፋ አስቆራጭ ነው፡፡ በተለይ መንግሥታት ለጉዳዩ የሚሰጡት ትኩረት አሳዛኝ ብቻ ሳይሆን አስደንጋጭም ነው፡፡ ስለእነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚያስረዳ በቂ መረጃ እንኳን የላቸውም፤ ተቋማት አልገነቡም፤ ፖሊሲዎቻቸው እኒዚህን ወገኖች እንዲያካትቱ ተደርገው የተቃኙ አይደሉም፡፡ በመሆኑም ለተጋላጮቹ ፍላጎት ተደራሽ መሆን አልተቻለም፡፡
የዓለም የጤና ድርጅት (WHO) “GLOBAL HEALTH AND AGING” በሚል ርእስ ይፋ ያደረገው ጥናትም ሆነ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዘገባ በዓለም የአረጋውያን ቁጥር በ2010(እአአ) 524 ሚሊዮን፣ በ2017(እአአ) 962 ሚሊዮን እንደነበር የተገለጸ ሲሆን፤ በ2030(እአአ) 1.4 ቢሊዮን፣ በ2050 (እአአ) 1.5 ቢሊዮን፣ እአአ በ2100 ደግሞ በ2017 ከነበረው በሰባት እጥፍ ጨምሮ 3ነጥብ1 ቢሊዮን እንደሚሆን፤ እአአ ከ2010 እስከ 2050 ባለው ጊዜ ውስጥ በተለይ በታዳጊ አገራት የአረጋውያን ቁጥር በ250 በመቶ እንደሚጨምር (የብዙዎቹ ተቋማት ጥናት የእድሜ መነሻ 60 እና 65 ነው) ተተንብዮአል፡፡ ጥናቶቹ እንዳብራሩት ከዚህ ውስጥ አብዛኛውን ቁጥር የሚይዙት በታዳጊ አገራት ውስጥ የሚገኙት ይሆናሉ፡፡ በመሆኑም አገራቱ ከወዲሁ አፋጣኝ መፍትሄ መፈለጋቸው አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው፡፡
እንደ የዓለም የጤና ድርጅትም ሆነ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጥናቶች ቁልፉ ጥያቄ እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች መልካም ጤንነታቸው፣ ደህንነታቸውና ማህበራዊ ዋስትናቸው እየተጠበቀ ነው ወይ? የሚለው ሲሆን፤ መልሱንም “አይደለም” ሲሉ ይገልጹታል፡፡ ምክንያቱም ይላሉ፤ እንደ ጥናቶቹ እነዚህ ወገኖች በሽተኛ፣ ታማሚ፣ ጠባቂ፣ ለማኝ እንደሆኑ አሉና ነው፡፡ ብዙ አቅምና የመስራት ፍላጎት እያላቸውም በልማትና በማህበራዊ አገልግሎት ውስጥ እንዲሳተፉ ሲደረግ አይታይም፡፡
ለመንደርደሪያ ያህል ይህን ካልን ወደአገራችን እንመለስና እውነታውን እንመለከት፡፡
በኢትዮጵያ ለተለያዩ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና አካላዊ ችግሮች የተጋለጡ ወገኖቻችን (አረጋውያን፣ አካል ጉዳተኞች፣ ጎዳና ተዳዳሪዎች፣ ሴቶችና ህጻናት) አገራችን በምታካሂደው ሁለንተናዊ ልማትና ፈጣን እድገት ውስጥ ተካታች፣ ተሳታፊና ተጠቃሚ አለመሆናቸው በውይይት መድረክ ላይ ተገልጿል፡፡ በዚሁ ርእሰ-ጉዳይ ላይ ለመምከር ይቻል ዘንድ፤ ሰሞኑን በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካኝነት በተዘጋጀውና ከመንግሥት ከፍተኛ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ጋር የተደረገውን የውይይት መድረክ አስመልክቶ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ሚኒስትሯ ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ እንደገለጹት “ኢትዮጵያ በተለያዩ ተፈጥሮ አመጣሽና ሰው ሰራሽ ችግሮች ሳቢያ ምእተ-ዓመታትን ላስቆጠረ ድህነትና ኋላ ቀርነት ተዳርጋ መቆየቷ ለሁላችንም ግልጽ ነው፡፡ ይህ አስከፊ ገጽታ የወለዳቸው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለተከታታይ ትውልድ ፈተና እየሆኑ፤ ስር እየሰደዱና የጉዳት አድማሳቸውን እያሰፉ የተጓዙበት ርቀት ለስሌትና ለልኬት” አዳጋች ሆኖ ቆይቷል፡፡ በመሆኑም “ርቆ ከሄደው ዘመን አንስቶ ሲወሳሰቡና ሲንከባለሉ የመጡ ማህበራዊ ችግሮች ለዛሬው ትውልድ ፈተና በመሆን ከፊቱ ተደቅነው ይገኛሉ፡፡ ስለሆነም ተሻግሮ የማለፍ ብርታት ሰንቆ በጋራ መስራት” ወቅቱ የሚጠይቀው ግዴታ ነው፡፡
እንደሚኒስትሯ ንግግር “በተለያዩ ምክንያቶች የተፈጠሩና የሚፈጠሩ ማህበራዊ ችግሮችን በጊዜ የመከላከል፣ የመመከትና ዘላቂ እልባት እያበጁ የመሄድ ሥርአት ሳይዘረጋና አገራዊ አቅም ሳይፈጠር መቅረቱ ትውልድ ከችግር አዙሪት የሚወጣበትን መንገድ እንዲፈልግም ሆነ እንዳያገኝ ሳያስችለው” በመቆየቱ ምክንያት አሁን ያለንበት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ልንደርስ ችለናል፡፡ ይህ በችግሩ መጠንና ስፋት ምክንያት የተፈጠረው ተግዳሮትም የራሱ የሆነ ቁጭት ትቶልን አልፏል፡፡ ይህ ቁጭትም “ዛሬ አይነትና መጠናቸው በፍጥነት እየጨመረ ከፊታችን የተደቀኑ ማህበራዊ ችግሮችን ለማቃለልና የተለወጠ ማህበራዊ ድባብ ለማምጣት ይበልጥ ሊያነሳሳን ይገባል፡፡ ዛሬም ጧሪና ደጋፊ ያጡ አረጋውያን በየመንገዱ ዳር ለልመና ሲያዘግሙና እጃቸውን ሲዘረጉ ችግር መበርታቱንና ክብር መዋረዱን ይነግረናል፡፡ በልማት ውስጥ እኩል የመሳተፍና የመጠቀም ሙሉ መብት ያላቸውና የልማት አቅም የመሆን ብቃት ያልጎደላቸው አካል ጉዳተኞችና አረጋውያን እድል የሚነፈጉበት ችግር ገና አልተወገደም፡፡”
ሚኒስትሯ በአጽንኦት እንደገለጹት አሁን አገሪቱም ሆነች የተጠቀሱት የማህበረሰብ ክፍሎች ከፍተኛ ችግር ውስጥ ነው የሚገኙት፤ “እንደ ጎዳና ተዳዳሪነትና ልመና የመሳሰሉ ማህበራዊ ሳንካዎች አሳሳቢ በሚባል ደረጃ ላይ መገኘታቸውን ደብቀን የምናልፍበት መንገድ ካለመኖሩም በላይ፤ በጊዜ ተረባርበን መደበኛ መልክ እንዲይዙ ካልሰራን የከፋ መዘዝ ያስከትላሉ፡፡ በተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች ለተጎዱና የአደጋ ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ፈጥኖ የመድረስ ትጋታችን ካልጨመረ ከችግር ጋር የመኖር እድሜ እየረዘመ ይቀጥላል፤ የሚለው ላይ በጋራ ልናሰምርበት ይገባል” ሲሉም አጥብቀው አሳስበዋል፡፡ እንደሳቸው እምነት ከሆነ ጉዳዩ ቀላል ነው፤ ተባብሮና ተቀናጅቶ በመስራት ውጤት ማምጣት ይቻላል፡፡
የእነዚህን የህብረተሰብ ክፍሎች ችግር ለመፍታትና በአገራችን ማህበራዊ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚያስችሉ በርካታ የህግ ማእቀፎች መኖራቸውን የገለጹት ሚኒስትሯ “ዛሬ ለማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻችን ዘላቂ እልባት እያበጀን በለውጥ መንገድ ለመራመድ የምንችልበት መልካም እድል መኖሩን እንገነዘባለን፡፡ የመጀመሪያው ነገር የመንግሥት የፖለቲካ ቁርተኝነት መኖሩ ነው፡፡ ድህነትና የተለያዩ ችግሮች እየገፈተሩ ትቢያ ላይ የጣሉት ዜጋ ከወደቀበት ሳይነሳ ለውጥ ሙሉ እንደማይሆን ይታመናል፡፡ ማህበራዊ ደህንነት ከማረጋገጥ አኳያ ፖሊሲዎችና ህግጋት፣ ደንቦችና መመሪያዎች፣ ስትራቴጂዎችና ብሄራዊ የድርጊት መርሀ-ግብሮች ሁሉ ረጅም የትግበራ ርቀት ይዘውን ሊጓዙና ለውጤት ሊያበቁን የሚችሉ” መሆናቸውንም በደማቁ አስምረውበት አልፈዋል፡፡ በተለይ የአገራችን የማህበራዊ ዋስትና ጥበቃ ፖሊሲ እጅግ አሰሪ መሆኑ ታምኖበት ሳለ ወደመሬት ማውረድ ግን አልተቻለም፡፡ አሁን ያለው የፖሊሲ ሳይሆን የአስፈጻሚ አካላት ችላ ባይነት ነው፡፡
“የአረጋውያንና የአካል ጉዳተኞች ችግር እንዲቃለልና ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ፣ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ከልማት ጋር ተያይዞ እንዲቃለል መንግሥት በሁሉም አስፈጻሚ አካላት ላይ አደራ መጣሉ ግልጽ ነው፡፡ ስለሆነም፤ በየስራችን ውስጥ እያካተትን ከልብ በመስራት በዜጎች አኗኗር ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ለማምጣት መጣር ከባለድርሻ አካላት ይጠበቃል፡፡ ይህን ስንጠብቅና ይሳካል ብለን ስናስብ ችግሮች የሉም ማለት ግን አይደለም፡፡ በተለይ ተቀናጅቶ መስራት ላይ ከፍተኛ ችግሮች አሉ፡፡”
የእነዚህም ችግሮች መገለጫዎች ብዙ ሲሆኑ፤ እንደሚኒስትር ዴኤታ ጌታሁን አብዲሳ ማብራሪያና እንደቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፍ ግኝቶች፤ ተጋላጮቹ መብቶቻቸው ሳይሸራረፉ ሊከበሩላቸው አለመቻላቸው፣ የግልም ሆኑ የመንግሥት ተቋማት ተገቢውን ትኩረት የመስጠትም ሆነ ከእቅዳቸው ጀምሮ የማካተት ሥራ አለመኖሩ፣ ትምህርት 100 ፐርሰንት ተደራሽ ሆኗል ቢባልም እነዚህ (በተለይ አካል ጉዳተኛ) ወገኖች ሙሉ በሙሉ እድሉን አግኝተዋል ማለት አለመሆኑ፣ የመሰረተ-ልማት አውታሮች ሲገነቡ እነዚህን ወገኖች ታሳቢ አለማድረጋቸው፣ በህብረተሰቡ ዘንድ የተዛባ አመለካከት መኖሩና እሱን ለመቅረፍ አለመሰራቱ፣ ለእነዚህ ወገኖች ተደራሽ ለመሆን ራሱን የቻለ ፈንድ አለመኖሩ፣ የተሟላ መረጃ አለመኖሩ፤ እንዲሁም ተደራሽ መሆን አለመቻሉና በመሳሰሉት ምክንያቶች ለተለያዩ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና አካላዊ ችግሮች ተጋላጭ የሆኑ ወገኖች በከፋ ችግር ውስጥ መገኘታቸው መሆናቸው በጥናቶቹ ተጠቁሟል፡፡ በተወያዮችም ዳብሮ አስቸኳይ መፍትሄ መፈለግ ያለበት ስለመሆኑ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
እንደተባበሩት መንግሥታት ዘገባ ከ1992 (እ.አ.አ) ጀምሮ የጎዳና ተዳዳሪዎችን በተመለከተ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እና በቅንጅት ሲሰራባቸው ከቆዩት አገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ነች፡፡ ይሁን እንጂ፤ የተገኘው ለውጥ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ እንዲያውም ችግሩ እየተባባሰና ተጋላጮቹ የማህበራዊ ዋስትና ተጠቃሚ ሳይሆኑ ቆይተዋል፡፡ ዘገባው እንደሚመለክተው በአሁኑ ሰዓት በዓለማችን ከ150 ሚሊዮን በላይ የጎዳና ተዳዳሪዎች የሚገኙ ከመሆኑና ይህም በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ከመሄዱ አኳያ መንግሥታትና ባለድርሻ አካላት ከምንጊዜውም በላይ ተባብረውና ተቀናጅተው መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡
ውጤታማ ለመሆን ካስፈለገ ተቀናጅቶ፣ ተባብሮና ተናብቦ መስራት የሚገባ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ፣ እስከዛሬ ድረስ ቅንጅታዊ አሰራርና ትብብር ልል ሆኖ ቆይቷል፡፡ ስራው የራሳችን ሆኖ እያለ ባለቤቱ ሌላ እንደሆነ የመቁጠርና ችላ የማለት ችግር አልነበረም ቢባል መሸፋፈን ይሆናል፡፡ ከመናበብና ከቅንጅት ችግር መሻገር ለወገኖቻችን ተደራሽ ያደርገናል፡፡ ስለሆነም የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የዛሬው ጥሪና የምክክር አጀንዳ በዚሁ ላይ ያተኮረ መሆኑ ግልጽ ነው” ሲሉም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ በባለ ድርሻ አካላት ቀና ትብብር፣ ተሳትፎና ሀገራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አኳያ ከመስሪያ ቤታቸው ጋር በትብብር ቢሰሩ ባጭር ጊዜ ውስጥ ውጤታማ እንደሚኮን፤ ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችም ተገቢውን የማህበራዊ ዋስትና ጥበቃ ማድረግ የሚቻል መሆኑን “ጽኑ እምነት አለኝ” ሲሉ ገልጸዋል፡፡ በሌሎች የመንግሥት ከፍተኛ አመራሮችም ይሄው ሀሳብ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡
በውይይት መድረኩ ላይ ከቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፎች መረዳት እንደተቻለው፤ በኢትዮጵያ 1.2 ሚሊዮን ድጋፍና እርዳታ ፈላጊ አረጋዊያን ይገኛሉ ተብሎ የሚገመት ሲሆን፤ በአገሪቱ በሚገኙና በተመረጡ 11 ዋና ዋና ከተሞች በተደረገ ጥናት 88ሺህ 690 የጎዳና ተዳዳሪዎች እንደሚገኙ ታውቋል፡፡
ይህ አሀዝ እውነታውን በትክክል ይገልጻል ተብሎ እንደማይጠበቅ፤ በአንጻሩ ተገቢው ጥናትና ምርምር መደረግና ትክክለኛው ቁጥር መታወቅ እንዳለበት፤ በአገሪቱ የሚካሄደው ልማት እነዚህንም የህብረተሰብ ክፍሎች ማካተት እንደሚገባው፤ ከእድገቱም ተጠቃሚ መሆን እንዳለባቸው በጥናቶቹ ተገልጿል፡፡
የአካል ጉዳተኞች ማህበር ም/ፕሬዘዳንት ወ/ሮ ምህረት ንጉሴ፣ ይህንኑ የተጋላጮቹን ተካታችነት፣ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት በተመለከተ የነበሩትን ችግሮች ያብራሩ ሲሆን፤ አሁን መንግሥት እየወሰደ ያለውን ርምጃ በማድነቅ ፈጥኖ ወደተግባር መለወጥ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቀደም ሲል በጠቀስነው ጥናቱ አማካኝነት እንዳለው አሁኑኑ ፖሊሲን በማስተካከል በፍጥነት መፍታትና መፍትሄ ማበጀት ካልተቻለ ችግሩ እየተባባሰና እየተወሳሰበ ይሄዳል፡፡ ከዚህ መረዳት የሚቻለው ኢትዮጵያም ይህንኑ ተገንዝባ ከወዲሁ የሚሰራውን መስራት የሚጠበቅባት መሆኑን ነው፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 8/2011